በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ እርስ በርስም እንበረታታ

አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ እርስ በርስም እንበረታታ

“እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ።”—ዕብ. 10:24

1, 2. በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በተካሄደው የሞት ጉዞ ላይ የነበሩት 230 የይሖዋ ምሥክሮች በሕይወት እንዲተርፉ የረዳቸው ምንድን ነው?

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ የናዚ አገዛዝ ሲንኮታኮት በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ ትእዛዝ ተላለፈ። በመመሪያው መሠረት በዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ የሚገኙት እስረኞች በግዳጅ ወደ ወደቦች እንዲጓዙ ከተደረጉ በኋላ በመርከብ ተሳፍረው ባሕር ውስጥ እንዲሰምጡ ለማድረግ ታስቦ ነበር። ይህ እቅድ ከጊዜ በኋላ የሞት ጉዞ ተብሎ ተጠርቷል።

2 በዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ የሚገኙ 33,000 እስረኞችን 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሉቤክ የተባለች የጀርመን የወደብ ከተማ እንዲጓዙ ለማድረግ ታስቦ ነበር። ከእነዚህ መካከል ከስድስት አገሮች የመጡ 230 የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙ ሲሆን እነሱም አብረው እንዲጓዙ ተደረጉ። እስረኞቹ በሙሉ በረሃብና በበሽታ ዝለው ነበር። ታዲያ ወንድሞቻችን ከዚህ ጉዞ መትረፍ የቻሉት እንዴት ነው? በጉዞው ላይ ከነበሩት ወንድሞች አንዱ “ሁልጊዜ አንዳችን ሌላውን እናበረታታ ነበር” ብሏል። ከአምላክ ካገኙት ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ በተጨማሪ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር ከዚህ አሰቃቂ ጉዞ እንዲተርፉ ረድቷቸዋል።—2 ቆሮ. 4:7

3. እርስ በርስ መበረታታት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

3 እኛ እንዲህ ያለ የሞት ጉዞ እንድናደርግ ባንገደድም የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተቋቋመ በኋላ ሰይጣን ከሰማይ ተባርሮ በምድር አካባቢ ብቻ ተወስኖ እንዲኖር ተደርጓል፤ ሰይጣን “ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ [ተሞልቷል]።” (ራእይ 12:7-9, 12) ይህ ዓለም በአርማጌዶን የሚጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ ሰይጣን እኛን በመንፈሳዊ ለማዳከም የተለያዩ ፈተናዎችና ተጽዕኖዎች ያደርስብናል። በዚህ ላይ ደግሞ ኑሮ የሚያሳድርብን ጫና አለ። (ኢዮብ 14:1፤ መክ. 2:23) ችግሮች ሲደራረቡብን በጣም እንዝል ይሆናል፤ በዚህም የተነሳ መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከርና ስሜታችን እንዳይደቆስ ለማድረግ የቱንም ያህል ብንጥርም የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መቋቋም ያቅተን ይሆናል። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ብዙዎችን በመንፈሳዊ  የረዳ አንድ ወንድም ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። ይህ ወንድም ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ እሱና ባለቤቱ ጤና በማጣታቸው በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተዋጠ። ልክ እንደዚህ ወንድም፣ ሁላችንም ከይሖዋ የምናገኘው ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ እንዲሁም አንዳችን ለሌላው የምንሰጠው ማበረታቻ ያስፈልገናል።

4. ሌሎችን ማበረታታት ከፈለግን የትኛውን የጳውሎስን ምክር ልብ ማለት ያስፈልገናል?

4 ለሌሎች የብርታት ምንጭ ለመሆን እንድንችል ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈውን ማሳሰቢያ ልብ ማለት ይኖርብናል። እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ እንበረታታ።” (ዕብ. 10:24, 25) ይህን ጠቃሚ ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

“አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ”

5. “አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ” ሲባል ምን ማለት ነው? ይህስ ምን ማድረግን ይጠይቃል?

5 ‘አንዳችን ለሌላው ትኩረት መስጠት’ የሚለው አገላለጽ “ስለ ሌሎች እንዲሁም ስለሚያስፈልጋቸው ነገር ማሰብን” ያመለክታል። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከወንድሞቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ከሰላምታ ያለፈ ካልሆነ ወይም የምንጨዋወተው ምንም እርባና ስለሌላቸው ጉዳዮች ከሆነ ወንድሞቻችን ለሚያስፈልጋቸው ነገር ትኩረት መስጠት እንችላለን? እንደዚህ ማድረግ እንደማንችል ግልጽ ነው። እርግጥ ነው፣ “በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት” መጠንቀቅ ይኖርብናል። (1 ተሰ. 4:11፤ 1 ጢሞ. 5:13) ይሁን እንጂ ወንድሞቻችንን ለማበረታታት ከፈለግን እነሱን በቅርበት ማወቅ ይኸውም ያሉበትን ሁኔታ፣ ባሕርያቸውን፣ መንፈሳዊነታቸውን እንዲሁም ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን ማወቅ ያስፈልገናል። ጓደኛ ልንሆናቸው እንዲሁም እንደምንወዳቸው ልናረጋግጥላቸው ይገባል። ይህ ደግሞ ችግር ሲያጋጥማቸው ወይም ተስፋ ሲቆርጡ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጊዜያትም አብረናቸው ጊዜ ማሳለፍን ይጠይቃል።—ሮም 12:13

6. አንድ ሽማግሌ ለበጎቹ ‘ትኩረት ለመስጠት’ ምን ማድረግ ይኖርበታል?

6 የጉባኤ ሽማግሌዎች ‘በአደራ የተሰጣቸውን የአምላክ መንጋ በፈቃደኝነትና ለማገልገል በመጓጓት እንዲጠብቁ’ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥ. 5:1-3) እነዚህ ወንድሞች እንዲጠብቁ በአደራ የተሰጣቸውን መንጋ በሚገባ ካላወቁ የእረኝነት ሥራቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዴት ማከናወን ይችላሉ? (ምሳሌ 27:23ን አንብብ።) የጉባኤ ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመርዳት ፈቃደኞች እንደሆኑና ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስደስታቸው የሚያሳዩ ከሆነ በጎቹም እርዳታ ሲያስፈልጋቸው ከመጠየቅ ወደኋላ አይሉም። ከዚህም ሌላ ወንድሞችና እህቶች ስሜታቸውንና የሚያሳስባቸውን ነገር በግልጽ ለመናገር ይነሳሳሉ፤ ይህም ሽማግሌዎቹ በአደራ ለተሰጣቸው መንጋ ‘ትኩረት ለመስጠትና’ አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ ያስችላቸዋል።

7. በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠ ሰው ‘ኃይለ ቃል’ ቢሰነዝር ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

7 ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ደካሞችን ደግፏቸው” ብሎ ነበር። (1 ተሰሎንቄ 5:14ን አንብብ።) ‘የተጨነቁ ነፍሳት’ ደካማ ናቸው ሊባል ይችላል፤ በተስፋ መቁረጥ የተዋጡትም ቢሆን ሁኔታቸው ተመሳሳይ ነው። ምሳሌ 24:10 (NW) “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል!” ይላል። በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠ ሰው ‘ኃይለ ቃል’ ይናገር ይሆናል። (ኢዮብ 6:2, 3) እንዲህ ላሉት ሰዎች ‘ትኩረት በምንሰጥበት’ ጊዜ፣ የሚናገሩት ነገር እውነተኛ ማንነታቸውን የሚያንጸባርቅ ላይሆን እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። ራሼል ካጋጠማት ሁኔታ ይህን ተገንዝባለች፤ እናቷ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ትሠቃያለች። ራሼል እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ በጣም መጥፎ ነገር የተናገረችባቸው በርካታ ወቅቶች አሉ። በእነዚህ ጊዜያት በተቻለኝ መጠን የእናቴን እውነተኛ ማንነት ይኸውም አፍቃሪ፣ ደግ እና ለጋስ ሰው መሆኗን ለማስታወስ እሞክራለሁ። በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃዩ ሰዎች የሚናገሩት አብዛኛው ነገር ከልባቸው እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ። በዚህ ወቅት በንግግራችን ወይም በድርጊታችን መጥፎ ምላሽ መስጠት ሁኔታውን ከማባባስ በቀር የሚፈይደው ነገር የለም።” ምሳሌ 19:11 “ጥበብ ሰውን  ታጋሽ ታደርገዋለች፤ በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው” ይላል።

8. በተለይ ለእነማን ፍቅራችንን ‘ልናረጋግጥ’ ይገባል? ለምንስ?

8 ቀደም ሲል በፈጸመው ኃጢአት የተነሳ ተስፋ ለቆረጠ ሰው ‘ትኩረት መስጠት’ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለው ሰው የፈጸመውን ስህተት ለማስተካከል እርምጃ ቢወስድም እንኳ ያንን ስህተቱን ማውጠንጠኑ የሚፈጥርበት የኃፍረት ወይም የሐዘን ስሜት ተስፋ ሊያስቆርጠው ይችላል። በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የነበረ አንድ ሰው ለፈጸመው ኃጢአት ንስሐ ገብቶ ነበር፤ ጳውሎስ እሱን አስመልክቶ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሰው ከልክ በላይ በሐዘን እንዳይዋጥ በደግነት ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል። ስለዚህ ለእሱ ያላችሁን ፍቅር እንድታረጋግጡለት አሳስባችኋለሁ።” (2 ቆሮ. 2:7, 8) አንድ መዝገበ ቃላት እንደገለጸው እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘ማረጋገጥ’ የሚለው ቃል “ማጽደቅ፣ በተግባር ማሳየት፣ በሕግ ማስከበር” የሚል ፍቺ አለው። እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ እንደምንወደውና እንደምናስብለት ያውቃል ብለን መደምደም የለብንም። ለእሱ ባለን አመለካከትና በምናደርጋቸው ነገሮች ፍቅራችንን ልናሳየው ይገባል።

“ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት”

9. “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት” ሲባል ምን ማለት ነው?

9 ጳውሎስ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ” በማለት ጽፏል። የእምነት ባልንጀሮቻችን ለሌሎች ፍቅር እንዲያሳዩና በመልካም ሥራዎች እንዲካፈሉ ልናበረታታቸው ይገባል። እሳት ሊጠፋ ከተቃረበ እንደገና ለማቀጣጠል መቆስቆስና ማራገብ ያስፈልጋል። (2 ጢሞ. 1:6) በተመሳሳይም ወንድሞቻችን ለአምላክና ለባልንጀሮቻቸው ፍቅር እንዲያሳዩ በፍቅር ተነሳስተን ልናነቃቃቸው እንችላለን። ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ሌሎችን ማመስገናችን ለመልካም ሥራዎች ያነቃቃቸዋል።

ከሌሎች ጋር አብራችሁ አገልግሉ

10, 11. (ሀ) ምስጋና የሚያስፈልገው ማን ነው? (ለ) ምስጋና ‘የተሳሳተ እርምጃ የወሰደን ሰው’ ሊረዳው የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

10 ማናችንም ብንሆን፣ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ባንዋጥም እንኳ ምስጋና ያስፈልገናል። አንድ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አባቴ አንድም ቀን አመስግኖኝ አያውቅም። በመሆኑም ከልጅነቴ ጀምሮ በራስ የመተማመን ስሜት አልነበረኝም። . . . አሁን 50 ዓመት ቢሆነኝም ጓደኞቼ፣ የሽምግልና ኃላፊነቴን ጥሩ አድርጌ እየተወጣሁ እንደሆነ ሲነግሩኝ  በጣም ደስ ይለኛል። . . . ለሌሎች ማበረታቻ መስጠት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከራሴ ሕይወት ስለተማርኩ በተቻለኝ መጠን ሌሎችን ለማመስገን እጥራለሁ።” አቅኚዎችን፣ በዕድሜ የገፉትንና ተስፋ የቆረጡትን ጨምሮ ሁሉም ሰው ሲመሰገን ለሥራ ይነሳሳል።—ሮም 12:10

11 ‘መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንድሞች፣ የተሳሳተ እርምጃ የወሰደን ሰው ለማስተካከል ጥረት ሲያደርጉ’ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ምክር መስጠታቸው እንዲሁም ግለሰቡን ቀደም ሲል ላከናወነው ነገር ማመስገናቸው እንደገና መልካም ሥራዎችን ማከናወን እንዲጀምር ሊያነሳሳው ይችላል። (ገላ. 6:1) ሚርያም የተባለች ክርስቲያን ያጋጠማት ሁኔታ ይህን ያረጋግጣል። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “አንዳንድ የቅርብ ጓደኞቼ እውነትን ተዉ፤ በዚሁ ጊዜ ላይ ደግሞ አባቴ በአንጎሉ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ታመመ፤ ይህ ወቅት በጣም ከብዶኝ ነበር። ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያዘኝ። ጭንቀቴን ለመቋቋም ስል የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የወንድ ጓደኛ ያዝኩ።” ይህን በማድረጓ ይሖዋ ሊወዳት እንደማይችል ስለተሰማት እውነትን ለመተው አሰበች። በዚህ ወቅት አንድ ሽማግሌ፣ ከዚህ ቀደም በታማኝነት ስላከናወነችው አገልግሎት ሲያስታውሳት እንደገና ተበረታታች። ሽማግሌዎቹ ይሖዋ እንደሚወዳት አረጋገጡላት። ይህ ደግሞ ለይሖዋ የነበራት ፍቅር እንዲታደስ አደረገ። ከማያምነው ሰው ጋር የነበራትን ግንኙነት አቁማ ይሖዋን ማገልገሏን ቀጠለች።

ለፍቅር እና ለመልካም ሥራዎች ተነቃቁ

12. አንድን ሰው በማሳፈር፣ በመተቸት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማው በማድረግ ለሥራ ለማነሳሳት መሞከር ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?

12 አንድን ሰው ከሌሎች ጋር በማነጻጸር እንዲያፍር ማድረግ፣ ድርቅ ያሉ መመሪያዎችን ማውጣትና ያንን መመሪያ ባለመከተሉ መተቸት ወይም የሚያደርገው ነገር በቂ እንዳልሆነ በመግለጽ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግ ለጊዜው ለሥራ ሊያነሳሳው ቢችልም ዘላቂ ውጤት አያስገኝም። በሌላ በኩል ግን የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማመስገንና ለአምላክ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው እንዲያገለግሉት ማበረታታት ዘላቂና ጠቃሚ ውጤት ያስገኛል።—ፊልጵስዩስ 2:1-4ን አንብብ።

“እርስ በርስ እንበረታታ”

13. ሌሎችን ማበረታታት ምን ማድረግን ይጨምራል? (መግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።)

13 “ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ [መበረታታት]” ያስፈልገናል። ሌሎችን ማበረታታት ሲባል አምላክን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ማነሳሳትን ያመለክታል። ለፍቅር እና ለመልካም ሥራዎች ማነቃቃት፣ ሊጠፋ የተቃረበ እሳትን ከማቀጣጠል ጋር እንደተመሳሰለ ሁሉ ሌሎችን ማበረታታት ደግሞ እሳት መንደዱን እንዲቀጥል ወይም ይበልጥ እንዲነድ ማገዶ ከመጨመር ጋር ይመሳሰላል። ሌሎችን ማበረታታት ሲባል መንፈሳቸው የተደቆሰ ሰዎች እንዲጠነክሩ እና እንዲጽናኑ መርዳትን ይጨምራል። እንዲህ ያለውን ሰው የማበረታታት አጋጣሚ ስናገኝ እንደምንወደው እንዲሁም እንደምናስብለት በሚያሳይ መንገድ መናገር አለብን። (ምሳሌ 12:18) በተጨማሪም ‘ለመስማት የፈጠንን እና ለመናገር የዘገየን’ ልንሆን ይገባል። (ያዕ. 1:19) የእምነት ባልንጀራችንን ስሜቱን እንደምንረዳለት በሚያሳይ መንገድ ካዳመጥነው ተስፋ ያስቆረጠው ነገር ምን እንደሆነ ልንረዳና ያጋጠመውን ነገር ለመቋቋም የሚያስችል ሐሳብ ልናካፍለው እንችላለን።

አስደሳች ነገሮችን በማከናወን አብራችሁ ጊዜ አሳልፉ

14. ተስፋ ቆርጦ የነበረ አንድ ወንድም እርዳታ ያገኘው እንዴት ነው?

14 አንድ ሽማግሌ፣ ለተወሰኑ ዓመታት አገልግሎት  አቁሞ የነበረን አንድ ወንድም በደግነት እንዴት እንደረዳው እስቲ እንመልከት። ሽማግሌው ከዚህ ወንድም ጋር ባደረገው ውይይት፣ ወንድም አሁንም ይሖዋን ከልቡ እንደሚወድ መገንዘብ ቻለ። ይህ ወንድም እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ እትም የሚያጠና ከመሆኑም ሌላ በጉባኤ ላይ አዘውትሮ ለመገኘት ጥረት ያደርጋል። ይሁን እንጂ፣ በጉባኤ ውስጥ አንዳንዶች የሚያደርጉት ነገር አሳዝኖትና አበሳጭቶት ነበር። ሽማግሌው፣ ይህን ወንድም ከመንቀፍ ይልቅ ስሜቱን እንደተረዳለት በሚያሳይ መንገድ አዳመጠው፤ እንዲሁም የጉባኤው አባላት እሱንም ሆነ ቤተሰቡን እንደሚወዷቸውና እንደሚያስቡላቸው አረጋገጠለት። ወንድም ከዚህ ቀደም ያጋጠሙት መጥፎ ነገሮች፣ የሚወደውን አምላክ እንዳያገለግል እንቅፋት እንደሆኑበት ቀስ በቀስ ተገነዘበ። ሽማግሌው፣ አብሮት አገልግሎት እንዲወጣ ወንድምን ጋበዘው። ወንድምም ሽማግሌው የሰጠውን እርዳታ በመቀበል እንደገና በአገልግሎት መካፈል የጀመረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ እንደ ቀድሞው ሽማግሌ ሆኖ ማገልገል ችሏል።

ማበረታቻ የሚያስፈልገው ሰው ሲያነጋግራችሁ በትዕግሥት አዳምጡት (አንቀጽ 14, 15ን ተመልከት)

15. ተስፋ የቆረጡ ሰዎችን በማበረታታት ረገድ ከይሖዋ ምን እንማራለን?

15 ተስፋ የቆረጠ ሰው፣ የሚሰማው መጥፎ ስሜት ቶሎ ላይወገድ ወይም የምንሰጠውን እርዳታ ወዲያውኑ ላይቀበል ይችላል። በመሆኑም ያልተቋረጠ ድጋፍ መስጠት ያስፈልገን ይሆናል። ጳውሎስ “ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ” ብሏል። (1 ተሰ. 5:14 የ1954 ትርጉም) ደካሞችን በምንረዳበት ጊዜ ቶሎ ከመሰልቸት ይልቅ ‘መትጋት’ በሌላ አባባል ያለማቋረጥ ድጋፍ መስጠት ይኖርብናል። በጥንት ጊዜ፣ ይሖዋ ተስፋ የቆረጡ አገልጋዮቹን በትዕግሥት ይዟቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ የኤልያስን ስሜት በመረዳት ደግነት አሳይቶታል። ይሖዋ፣ ለዚህ ነቢይ አገልግሎቱን ለመቀጠል የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሰጥቶታል። (1 ነገ. 19:1-18) ዳዊትም ከልቡ ንስሐ ስለገባ አምላክ በደግነት ይቅር ብሎታል። (መዝ. 51:7, 17) የመዝሙር 73 ጸሐፊ፣ ይሖዋን ማገልገሉን ሊያቆም ተቃርቦ በነበረበት ወቅት አምላክ ረድቶታል። (መዝ. 73:13, 16, 17) ይሖዋ፣ በተለይ በሐዘን በምንዋጥበት እና ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ በደግነትና በትዕግሥት ይይዘናል። (ዘፀ. 34:6) ምሕረቱ “ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው” ደግሞም “አያልቅም።” (ሰቆ. 3:22, 23) ይሖዋ፣ የተጨነቁ ሰዎችን በደግነት በመያዝ የእሱን ምሳሌ እንድንከተል ይጠብቅብናል።

በሕይወት ጎዳና መጓዛችንን ለመቀጠል እርስ በርስ እንበረታታ

16, 17. የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየተቃረበ ሲሄድ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል? ለምንስ?

16 የሞት ጉዞ ካደረጉት በዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ የነበሩ 33,000 እስረኞች መካከል በሺዎች የሚቆጠሩት ሞተዋል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑት 230 እስረኞች ግን ከመካከላቸው አንድም ሰው ሳይሞት ያንን መከራ ማለፍ ችለዋል። እርስ በርስ መበረታታታቸውና መደጋገፋቸው ከዚያ የሞት ጉዞ በሕይወት ለመትረፍ አስችሏቸዋል።

17 በዛሬው ጊዜ እኛም ‘ወደ ሕይወት በሚያስገባው መንገድ’ ላይ እየተጓዝን ነው። (ማቴ. 7:14) በቅርቡ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በአንድነት ሆነው ጽድቅ ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም ይገባሉ። (2 ጴጥ. 3:13) እንግዲያው ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው በዚህ ጎዳና ላይ በምናደርገው ጉዞ እርስ በርስ ለመረዳዳት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።