በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥበብ የታከለበት ውሳኔ አድርግ

ጥበብ የታከለበት ውሳኔ አድርግ

“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ።”—ምሳሌ 3:5

1, 2. ውሳኔ ማድረግ ያስደስትሃል? ከዚህ በፊት ስላደረግሃቸው አንዳንድ ውሳኔዎች ምን ይሰማሃል?

ዛሬም ውሳኔ! ነገም ውሳኔ! አዎ፣ ውሳኔ ማድረግ የሕይወታችን ክፍል ነው ሊባል ይቻላል። ታዲያ ውሳኔ የሚያሻው ነገር ሲያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? አንዳንድ ሰዎች ሁሉንም ነገር በራሳቸው መወሰን ይፈልጋሉ። የራሳቸውን ውሳኔ ራሳቸው ማድረግ እንዳለባቸው ስለሚሰማቸው ሌላ ሰው ስለ እነሱ ለመወሰን ሲቃጣ እንኳ ይናደዳሉ። ሌሎች ደግሞ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከሚያደርጓቸው ውሳኔዎች ትንሽ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው መወሰን በጣም ይፈራሉ። በዚህ ጊዜ እነዚህ ሰዎች መጻሕፍትን ያነብባሉ ወይም አማካሪዎችን ይጠይቃሉ፤ እንዲያውም ምክር ለማግኘት ሲሉ ብዙ ገንዘብ የሚያወጡበት ጊዜ አለ።

2 ብዙዎቻችን ግን ወደ ሁለቱም ጽንፍ አንሄድም። አንዳንድ ነገሮች ከእኛ አቅም በላይ እንደሆኑና ምንም ማድረግ እንደማንችል ይሰማን ይሆናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደፍላጎታችን ውሳኔ ማድረግ የምንችልባቸው ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ እንገነዘባለን። (ገላ. 6:5) ያም ቢሆን የምናደርጋቸው ውሳኔዎች በሙሉ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ወይም ጠቃሚ ላይሆኑ እንደሚችሉ እናምናለን።

3. ውሳኔ በማድረግ ረገድ ምን መመሪያ አለን? ሆኖም ተፈታታኝ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

3 የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በሕይወታችን ውስጥ በጣም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ይሖዋ ግልጽ መመሪያ ስለሚሰጠን ደስተኞች ነን። እነዚህን መመሪያዎች ከተከተልን ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሁም እኛን የሚጠቅም ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። ያም ሆኖ በአምላክ ቃል ውስጥ ግልጽ የሆነ መመሪያ ያልተሰጠባቸው ጉዳዮች ወይም ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን መወሰን የምንችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ መስረቅ እንደሌለብን ሁላችንም እናውቃለን። (ኤፌ. 4:28) ይሁንና አንድ ሰው ሰረቀ የሚባለው መቼ ነው? ይህን የሚወስነው የተሰረቀው ዕቃ ያለው ዋጋ ነው? ወይስ ግለሰቡ ለመስረቅ ያነሳሳው ምክንያት? ምናልባት ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን? ጥቁርና ነጭ ሆነው ያልተቀመጡ ጉዳዮች ሲያጋጥሙን ውሳኔ የምናደርገው እንዴት ነው? ከዚህ ጋር በተያያዘ መመሪያ ሊሆነን የሚችል ነገር አለ?

 ጤናማ አእምሮ አዳብሩ

4. ብዙ ጊዜ የእምነት ባልንጀሮቻችን ከባድ ውሳኔ ልናደርግ እንደሆነ ሲያውቁ ምን ብለው ሊመክሩን ይችላሉ?

4 አንድ ከባድ ውሳኔ ልናደርግ እንደሆነ ለአንድ የእምነት ባልንጀራችን ስንነግረው ጉዳዩን በደንብ እንድናስብበት ይመክረን ይሆናል፤ በሌላ አባባል ጤናማ አእምሮ እንዳለው ሰው እንድንወስን እየነገረን ነው ሊባል ይችላል። እርግጥ ይህ ምክር ጥሩ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 21:5) ታዲያ ጤናማ አእምሮ ማዳበር ሲባል ምን ማለት ነው? ጊዜ ወስዶ በጉዳዩ ላይ ማሰብ፣ ምክንያታዊ መሆን እንዲሁም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታን መጠቀም ማለት ነው? እነዚህ ነገሮች በሙሉ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ቢሆኑም ጤናማ አእምሮ ለማዳበር ግን ተጨማሪ ነገር ያስፈልጋል።—ሮም 12:3፤ 1 ጴጥ. 4:7

5. በተፈጥሯችን ፍጹም ጤናማ የሆነ አእምሮ የሌለን ለምንድን ነው?

5 ማናችንም ብንሆን ፍጹም ጤናማ የሆነ አእምሮ ይዘን እንዳልተወለድን አምነን መቀበል ይኖርብናል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞችና ፍጽምና የጎደለን ስለሆንን ነው፤ በዚህም የተነሳ በአካልም ሆነ በአእምሮ ሙሉ በሙሉ ጤናማ አይደለንም። (መዝ. 51:5፤ ሮም 3:23) በተጨማሪም በአንድ ወቅት ብዙዎቻችን ሰይጣን አእምሯቸውን ‘ካሳወራቸው’ ሰዎች መካከል ነበርን፤ ይሖዋንም ሆነ የጽድቅ መሥፈርቶቹን አናውቅም ነበር። (2 ቆሮ. 4:4፤ ቲቶ 3:3) በመሆኑም ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ምንም ያህል በጉዳዩ ላይ ብናስብበትም፣ ውሳኔያችን የተመካው ጥሩና ምክንያታዊ እንደሆነ መስሎ በተሰማን ነገር ላይ ስለሚሆን በወቅቱ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የተሳሳቱ የመሆናቸው አጋጣሚ ሰፊ ነበር።—ምሳሌ 14:12

6. ጤናማ አእምሮ ለማዳበር ምን ያስፈልገናል?

6 እኛ በአካልም ሆነ በአእምሮ ጤናማ ባንሆንም በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ በሁሉ ነገር ፍጹም ነው። (ዘዳ. 32:4) በመሆኑም አእምሯችንን እንድናድስና ጤናማ አእምሮ እንዲኖረን ያስችለናል። (2 ጢሞቴዎስ 1:7ን አንብብ።) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ማስተዋል በታከለበት መንገድ ማሰብና ማመዛዘን ብሎም ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ እንፈልጋለን። አስተሳሰባችንንና ስሜታችንን በመቆጣጠር ከይሖዋ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ድርጊት ጋር እንዲስማማ ማድረግ ይኖርብናል።

7, 8. አንድ ሰው ተጽዕኖ ቢደረግበትም ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመውም ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንደሚችል የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

7 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በስደት ውጪ አገር የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ልጅ በሚወልዱበት ጊዜ ሥራ እንዳያቆሙና ገቢያቸው እንዳይቋረጥ ሲሉ የተወለደውን ልጅ ዘመዶቻቸው እንዲያሳድጉላቸው ወደ አገር ቤት መላካቸው የተለመደ ነው። * እስቲ በስደት የምትኖር አንዲት ሴት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት፦ ይህች ሴት ወንድ ልጅ ትወልዳለች። በወቅቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራ የነበረ ሲሆን ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እያደረገችም ነበር። ወዳጆቿና ዘመዶቿ ልጁን ወደ አያቶቹ እንዲልኩት በእሷና በባሏ ላይ ጫና ማድረግ ጀመሩ። ይሁን እንጂ አምላክ ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት የሰጠው ለወላጆች እንደሆነ እናትየው ከጥናቷ ተገንዝባ ነበር። (መዝ. 127:3፤ ኤፌ. 6:4) ታዲያ ብዙዎች ምክንያታዊ እንደሆነ የሚሰማቸውን ልማድ ትከተል ይሆን? ወይስ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማረችውን ነገር ተግባራዊ በማድረግ በገንዘብ ረገድ የሚያጋጥማትን ችግርና የሰዎችን ትችት ለመቀበል ትመርጣለች? አንተ በእሷ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?

8 ይህች ሴት ጫና ስለበዛባትና በጣም ስለተጨነቀች በጉዳዩ ላይ መመሪያ ለማግኘት የልቧን አውጥታ ወደ ይሖዋ ጸለየች። ስለ ጉዳዩ መጽሐፍ ቅዱስን ከምታስጠናት እህትና ከሌሎች የጉባኤው አባላት ጋር በመነጋገሯ በዚህ ረገድ ይሖዋ ምን አመለካከት እንዳለው መረዳት ቻለች። በተጨማሪም ልጆች ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ከወላጆቻቸው መለየታቸው የሚያስከትልባቸውን ስሜታዊ ጉዳት ግምት ውስጥ አስገባች። ከቅዱሳን መጻሕፍት ባገኘችው እውቀት ተጠቅማ በጉዳዩ ላይ በደንብ ካሰበችበት በኋላ ግን ልጇን መላኳ ተገቢ እንዳልሆነ ወሰነች። ባለቤቷም ቢሆን የጉባኤው አባላት እንዴት ድጋፍ እንደሰጧቸውና ልጁም ምን ያህል ጤነኛና ደስተኛ እንደሆነ  ማስተዋል ቻለ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና ከባለቤቱ ጋር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ።

9, 10. ጤናማ አእምሮ ማዳበር ሲባል ምን ማለት ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

9 ይህ ተሞክሮ ጤናማ አእምሮ ማዳበር ሲባል በእኛ ወይም በሌሎች አስተሳሰብና ስሜት፣ ምክንያታዊ ወይም ጠቃሚ መስሎ የታየንን ነገር መከተል ብቻ እንዳልሆነ ከሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች አንዱ ነው። ፍጹም ያልሆኑት አእምሯችንና ልባችን በጣም ከሚፈጥን ወይም በጣም ወደ ኋላ ከሚቀር ሰዓት ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። እንዲህ ባለ ሰዓት መመራት ከባድ ችግር ያስከትላል። (ኤር. 17:9) ትክክለኛውን ጊዜ በማየት ሰዓቱን እንደምናስተካክለው ሁሉ አእምሯችንንና ልባችንንም አስተማማኝ በሆኑት የአምላክ መመሪያዎች መሠረት ማስተካከል አለብን።—ኢሳይያስ 55:8, 9ን አንብብ።

10 መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ምክር መስጠቱ ተገቢ ነው፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) “በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” የሚለውን አባባል ልብ በል። ከዚያም ምን ማድረግ እንዳለብን ሲመክረን “[ይሖዋን] ዕወቅ” ይላል። ምክንያቱም ፍጹም ጤናማ አእምሮ ያለው እሱ ብቻ ነው። በመሆኑም ውሳኔ የሚያሻው ጉዳይ ሲያጋጥመን የአምላክን አመለካከት ለማወቅ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዞር ማለት ይኖርብናል። ከዚያም በዚያ ላይ ተመሥርተን ውሳኔ ማድረግ ይገባናል። እንዲህ ካደረግን ጤናማ አእምሮ አለን ማለትም የይሖዋን አስተሳሰብ ይዘናል ሊባል ይችላል።

የማስተዋል ችሎታችሁን አሠልጥኑ

11. ጥበብ የታከለበት ውሳኔ ለማድረግ ቁልፉ ምንድን ነው?

11 ጥበብ የታከለበት ውሳኔ ማድረግና ከውሳኔያችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ መማር ቀላል አይደለም። በተለይ በእውነት ውስጥ አዲስ ለሆኑና መንፈሳዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ለሚጣጣሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ማድረግ ከባድ ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ሕፃናት ብሎ የሚጠራቸው እነዚህ ክርስቲያኖች እንኳ እውነተኛ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ይችላሉ። ለምሳሌ መራመድ የሚማርን ሕፃን ወደ አእምሯችን ማምጣት እንችላለን። ልጁ በዚህ ረገድ እንዲሳካለት ከተፈለገ በትንሽ በትንሹ መራመድና ይህን በተደጋጋሚ ጊዜ ማድረግ ይኖርበታል። በመንፈሳዊ ሕፃናት የሆኑ ክርስቲያኖችም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ መወሰን ከፈለጉ ተመሳሳይ ነገር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ጎልማሳ ሰዎች ሲናገር ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል  ችሎታቸውን በማሠራት እንደሚያሠለጥኑ’ መግለጹን አስታውስ። “ማሠራት” እና ‘ማሠልጠን’ የሚሉት አገላለጾች ቀጣይና ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግን ያመለክታሉ፤ ከአዲሶችም የሚጠበቀው ይህ ነው።—ዕብራውያን 5:13, 14ን አንብብ።

በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ትክክለኛ ውሳኔ ስናደርግ የማስተዋል ችሎታችንን እናሠለጥናለን (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

12. ጥበብ የታከለበት ውሳኔ የማድረግ ችሎታችንን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

12 በመግቢያው ላይ እንደተመለከትነው በየዕለቱ ትንሽም ይሁን ትልቅ በርካታ ውሳኔዎችን እናደርጋለን። አንድ ጥናት እንዳሳየው ከሆነ በሕይወታችን ውስጥ ከምናከናውናቸው ነገሮች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑትን የምናደርገው አስበንባቸው ሳይሆን በዘልማድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በየቀኑ ጠዋት ላይ የትኛውን ልብስ መልበስ እንዳለብህ ትወስን ይሆናል። ነገሩን አክብደህ ስለማትመለከተው በተለይ ከቸኮልክ ብዙ ሳትጨነቅ የምትለብሰውን ልብስ ትመርጣለህ። ይሁንና የምንለብሰው ልብስ ለአንድ የይሖዋ አገልጋይ የሚስማማ መሆን አለመሆኑን ማሰባችን በጣም አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮ. 6:3, 4) ልብስ በምትገዛበት ጊዜ በአንተ ላይ ስለ ማማሩና ስለ ፋሽኑ ታስብ ይሆናል፤ ሆኖም ልከኛ መሆኑንና ዋጋውን ግምት ውስጥ ማስገባት አይኖርብህም? እንዲህ በመሰሉ ጉዳዮች ረገድ ትክክለኛ ምርጫ ማድረጋችን የማስተዋል ችሎታችንን እንድናሠለጥን አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ ከባባድ ጉዳዮች ሲያጋጥሙን ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳናል።—ሉቃስ 16:10፤ 1 ቆሮ. 10:31

ትክክል የሆነውን የማድረግ ፍላጎት አዳብሩ

13. የወሰንነውን ነገር ተግባራዊ በማድረግ ረገድ እንዲሳካልን ምን ሊረዳን ይችላል?

13 ሁላችንም እንደምንገነዘበው ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ አንድ ነገር ሲሆን በውሳኔያችን መጽናትና ከዚያ ጋር ተስማምቶ መኖር ሌላ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ሲጋራ የሚያጨሱ አንዳንድ ሰዎች፣ ይህን ልማዳቸውን ማቆም ይፈልጉና ሳይሳካላቸው ይቀራል፤ ምክንያቱም ቁርጠኝነት ይጎድላቸዋል። በመሆኑም አንድ ሰው አንድ ነገር ማድረግ ከፈለገ በውሳኔው ለመጽናት ጠንካራ ፍላጎት ሊኖረው ይገባል። አንዳንዶች ፍላጎትን ከጡንቻ ጋር ያመሳስሉታል። ጡንቻችንን ይበልጥ ባሠራነው ቁጥር የዚያኑ ያህል ጠንካራ እየሆነ ይሄዳል። የምናሠራው አልፎ አልፎ ብቻ ከሆነ ግን ደካማና ልፍስፍስ ይሆናል። ታዲያ የወሰንነውን ነገር ተግባራዊ የማድረግ ፍላጎታችን እንዲዳብርና እንዲጠነክር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ወደ ይሖዋ ዞር ማለታችን ሊጠቅመን ይችላል።—ፊልጵስዩስ 2:13ን አንብብ።

14. ጳውሎስ ማድረግ የሚገባውን ነገር የማድረግ ጥንካሬ ያገኘው እንዴት ነው?

14 ጳውሎስ የይሖዋ እርዳታ ወሳኝ መሆኑን በሕይወቱ መገንዘብ ችሏል። በአንድ ወቅት “መልካም የሆነውን ነገር የመመኘት ችሎታ በውስጤ አለ፤ ያን የማድረግ ችሎታ ግን የለም” በማለት በምሬት ተናግሯል። ጳውሎስ ምን ማድረግ እንደሚፈልግ ወይም ምን ማድረግ እንደሚገባው ያውቅ ነበር፤ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የፈለገውን ነገር እንዳያደርግ የሚያግደው አንድ ነገር ነበር። ይህ ምን እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋና በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” ታዲያ ጳውሎስ ምንም ተስፋ አልነበረውም ማለት ነው? በጭራሽ። “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” ብሏል። (ሮም 7:18, 22-25) በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ” በማለት ጽፏል።—ፊልጵ. 4:13

15. ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ወይም አለመውሰድ ምን ለውጥ ያመጣል?

15 ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አምላክን ለማስደሰት ቆራጥ የሆነ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው። ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ለተሰበሰቡ የበአል አምላኪዎችና ከሃዲ የሆኑ እስራኤላውያን ምን እንዳላቸው ልብ በል፦ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አምላክ ከሆነ [እሱን] ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ።” (1 ነገ. 18:21) እስራኤላውያን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ቢያውቁም ውሳኔ ማድረግ ስላቃታቸው ‘ይዋልሉ’ ነበር። ከብዙ ዓመታት በፊት የኖረው ኢያሱ ግን ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል።  ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ማምለክ የማያስፈልግ መስሎ ከታያችሁ ግን፣ . . . የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] እናመልካለን።” (ኢያሱ 24:15) ታዲያ ቆራጥ እርምጃ በመውሰዱ ምን ውጤት ተገኘ? ኢያሱና ከእሱ ጋር የተባበሩ እስራኤላውያን ‘ማርና ወተት ወደምታፈሰው’ ተስፋይቱ ምድር በመግባት ተባርከዋል።—ኢያሱ 5:6

ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ በማድረግ ተባረኩ

16, 17. ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ውሳኔ ማድረግ ያለውን ጥቅም የሚያሳይ አንድ ተሞክሮ ተናገር።

16 እስቲ በዘመናችን የተፈጸመ የአንድ ወንድም ተሞክሮ እንመልከት። ይህ ወንድም የተጠመቀው በቅርቡ ሲሆን ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነው። አንድ ቀን የሥራ ባልደረባው ከፍተኛ ደሞዝና የበለጠ ጥቅማ ጥቅሞችን በሚያስገኝ ሌላ ድርጅት ውስጥ ቢቀጠሩ የተሻለ እንደሆነ ለወንድም ሐሳብ አቀረበለት። ወንድም በጉዳዩ ላይ በደንብ አሰበበት፤ እንዲሁም ጸለየበት። ወንድም አሁን ያለውን ሥራ የመረጠው ቅዳሜና እሁድ እረፍት ስላለው፣ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና ከቤተሰቡ ጋር በአገልግሎት ለመካፈል ስለሚያስችለው እንጂ ክፍያው ከሌሎች ድርጅቶች የተሻለ ሆኖ አይደለም። አዲስ ያገኘውን ሥራ ቢቀበል ቢያንስ ለተወሰኑ ጊዜያት አሁን ያለውን ፕሮግራም መከተል እንደማይችል አሰበ። አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?

17 ከፍተኛ ገቢ ከማግኘት ይልቅ በመንፈሳዊ ለሚያገኛቸው ጥቅሞች ትልቅ ቦታ ስለሰጠ አዲሱን ሥራ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። ይህ ወንድም ባደረገው ውሳኔ የተጸጸተ ይመስልሃል? በምንም ዓይነት። እሱም ሆነ ቤተሰቡ በመንፈሳዊ የሚያገኟቸው በረከቶች ከፍተኛ ደሞዝ ከሚያስገኝላቸው ጥቅሞች ጋር ፈጽሞ ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ተገንዝበዋል። የአሥር ዓመት ዕድሜ ያላት ትልቋ ልጃቸው ወላጆቿን እንደምትወድ፣ ወንድሞችና እህቶችን እንደምትወድ እንዲሁም ይሖዋን በጣም እንደምትወድ ስትናገር እሱና ባለቤቱ በመስማታቸው ደስታቸው ወሰን አልነበረውም። እንዲሁም ራሷን ለይሖዋ መወሰንና መጠመቅ እንደምትፈልግ ተናግራለች። ይህች ልጅ አባቷ የይሖዋን አምልኮ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ በመስጠት ጥሩ ምሳሌ ስለሆናት በጣም አመስጋኝ እንደምትሆን ምንም ጥርጥር የለውም!

ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ በማድረግ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ደስታ አግኙ (አንቀጽ 18ን ተመልከት)

18. በእያንዳንዱ ዕለት ጥበብ የታከለበት ውሳኔ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

18 ታላቁ ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድረ በዳ በተመሰለው የሰይጣን ዓለም ውስጥ የይሖዋን እውነተኛ አምላኪዎች ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲመራ ቆይቷል። ኢየሱስ ታላቁ ኢያሱ እንደመሆኑ መጠንም ይህን ብልሹ ሥርዓት በማጥፋት ተከታዮቹን ተስፋ ወደተሰጠው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ለማስገባት በዝግጅት ላይ ነው። (2 ጴጥ. 3:13) በመሆኑም አሁን ወደ ቀድሞ አስተሳሰባችን፣ ወደ ድሮው ልማዳችን፣ እሴታችን ወይም ምኞታችን የምንመለስበት ሰዓት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእኛ ያለውን ፈቃድ ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ የምንረዳበት ወቅት ነው። (ሮም 12:2፤ 2 ቆሮ. 13:5) እንግዲያው በእያንዳንዱ ዕለት የምታደርጓቸው ውሳኔዎችና ምርጫዎች የአምላክን ዘላለማዊ በረከት ከሚያገኙ ሰዎች መካከል መሆናችሁን የሚያሳዩ ይሁኑ።—ዕብራውያን 10:38, 39ን አንብብ።

^ አን.7 በውጭ አገር የሚኖሩ ሰዎች ልጃቸውን ወደ አገር ቤት የሚልኩበት ሌላው ምክንያት ደግሞ አያቶች፣ የልጅ ልጃቸውን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ለማሳየት ነው።