በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎችን ለማስጠንቀቅ የበለጠ ጥረት ማድረግ ትችላለህ?

ሰዎችን ለማስጠንቀቅ የበለጠ ጥረት ማድረግ ትችላለህ?

ኤ ትሪፕ ዳውን ማርኬት ስትሪት የተባለ አንድ ድምፅ አልባ ፊልም በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ በሳን ፍራንሲስኮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የነበረውን የሰዎች የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ በማሳየት የበርካታ ተመልካቾችን አድናቆት አትርፏል። የፊልም ባለሙያዎች፣ በሐዲድ ላይ በሚጓዝ መኪና (ኬብል ካር) ላይ በእጅ የሚጠነጠን ካሜራ ገጥመው እንቅስቃሴ በሚበዛበት መንገድ ላይ እየተጓዙ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ቀርጸው ነበር። በፊልሙ ውስጥ በፈረስ የሚጎተቱ ሠረገላዎችና የድሮ አውቶሞቢሎች እንዲሁም የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን የሚያከናውኑ ገበያተኞችና ጋዜጣ አዟሪዎች ይታያሉ።

ይህን ፊልም እጅግ አሳዛኝ እንዲሆን የሚያደርገው በወቅቱ የተፈጸመ አንድ ክስተት ነው፤ ፊልሙ እንደተቀረጸ ከሚታሰብበት ወቅት ከጥቂት ቀናት በኋላ ማለትም ሚያዝያ 18 ቀን 1906፣ የመሬት መንቀጥቀጥ እና የእሳት አደጋ ተከሰተ፤ በዚህም የተነሳ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁ ከመሆኑም ሌላ በፊልሙ ላይ የሚታየው አብዛኛው የከተማዋ ክፍል ወድሟል። በፊልሙ ላይ ከሚታዩት ብሩህ ፊት ያላቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ከቀናት የዘለለ ዕድሜ አላገኙም። ከፊልሙ አዘጋጆች የአንዱ ዘመድ የሆነው ስኮት ማይልስ “በዚያ የነበሩት ሰዎች ከፊታቸው ምን እንደሚጠብቃቸው የሚያውቁት አንዳች ነገር አልነበረም። በጣም ያሳዝናሉ” ብሏል።

በ1906 በድንገት የተከሰተው የምድር መናወጥና በዚያ ምክንያት የተነሳው የእሳት አደጋ አብዛኛውን የሳን ፍራንሲስኮ ከተማ ማዕከላዊ ክፍል አውድሟል

በዘመናችንም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አሳሳቢ ሁኔታ አለ። እኛም ሰዎች ያሉበት ሁኔታ ያሳዝነናል። ብዙዎች፣ ከፊታቸው ስለሚጠብቃቸው ታላቅ እልቂት ይኸውም ይህ ክፉ ሥርዓት እንደሚጠፋ ሳያውቁ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን ይጣደፋሉ። ይሁን እንጂ ባልታሰበ ሰዓት ድንገት ከሚመጣ የመሬት መናወጥ በተቃራኒ ስለ ይሖዋ የፍርድ ቀን ሰዎችን ለማስጠንቀቅ የሚያስችል አጭር ጊዜ አለን። በየሳምንቱ ከቤት ወደ ቤት እየሄድክ ለማገልገል ጊዜ መድበህ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ሰዎችን ለማስጠንቀቅ ከዚህ የበለጠ ጥረት ማድረግ ትችል ይሆን?

ኢየሱስ አገልግሎቱን ከማከናወን ያረፈበት ጊዜ የለም

ኢየሱስ የስብከት ሥራውን ከማከናወን ልረፍ ያለበት ጊዜ አለመኖሩ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ፣ ለሚያገኛቸው ሰዎች በሙሉ ሰብኳል፤ መንገድ ላይ ያገኘውን ቀረጥ ሰብሳቢ እንዲሁም ቀትር ላይ ለማረፍ ቁጭ ሲል ውኃ ጉድጓድ አጠገብ ያገኛትን ሴት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። (ሉቃስ 19:1-5፤ ዮሐ. 4:5-10, 21-24) ልረፍ ብሎ ባሰበበት ጊዜ እንኳ ሰዎች ወደ እሱ ሲመጡ ምንም ቅር ሳይለው ማረፉን ትቶ አስተምሯቸዋል። ለሰዎች ርኅራኄ ስለነበረው አገልግሎቱን ያከናወነው ራሱን ምንም ሳይቆጥብ ነው። (ማር. 6:30-34) በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች፣ የኢየሱስን የጥድፊያ ስሜት እየኮረጁ ያሉት እንዴት ነው?

ባገኙት አጋጣሚ በሙሉ ይጠቀማሉ

ሜሊካ የምትኖረው ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት የመኖሪያ ሕንፃ ውስጥ ነው። ብዙዎቹ ጎረቤቶቿ ከሌላ አገር የመጡ ተማሪዎች ሲሆኑ የሚጠቀሙባቸው የሞባይል ስልክ ቁጥሮች በስልክ  ማውጫ ዝርዝር ላይ አይገኙም፤ ስማቸውም ቢሆን በነዋሪዎች ዝርዝር ውስጥ አልተመዘገበም። ሜሊካ፣ በመተላለፊያዎች ላይ እና በአሳንሰር ውስጥ ከምታገኛቸው ተከራዮች ጋር መንፈሳዊ ውይይት ለማድረግ የሚያስችላት ልዩ አጋጣሚ ስላላት ደስተኛ ነች። “ይህ ቦታ የእኔ የአገልግሎት ክልል እንደሆነ ይሰማኛል” ትላለች። ሜሊካ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችን የምትይዝ ሲሆን ብዙዎቹ ነዋሪዎች ትራክቶችንና መጽሔቶችን ይወስዳሉ። በተጨማሪም jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን እንዲጎበኙ ትጋብዛለች። ከበርካታ ሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራለች።

ሶንያ የተባለችው እህትም በተቻላት መጠን ላገኘችው ሰው ሁሉ ለመመሥከር ትጥራለች። ተቀጥራ የምትሠራው በአንድ ክሊኒክ ውስጥ ሲሆን ለሥራ ባልደረቦቿ በሙሉ ጥሩ ምሥክርነት የመስጠት ግብ አወጣች። በመጀመሪያ፣ ጊዜ ወስዳ እያንዳንዱ ሰው ስለሚያስፈልገውና ትኩረቱን ስለሚስበው ነገር ለማወቅ ጥረት አደረገች። ከዚያም የምሳ እረፍቷን በመጠቀም ከእያንዳንዳቸው ጋር መንፈሳዊ ውይይት ለማድረግ ሞከረች። ሶንያ እንዲህ ያለ ጥረት በማድረጓ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማግኘት ችላለች። በተጨማሪም አንዳንድ ቀን የምሳ እረፍቷን በሕክምና ማዕከሉ የእንግዳ መቀበያ ቦታ ለማሳለፍና ተራቸውን የሚጠብቁ ታካሚዎችን ለማነጋገር አቅዳለች።

በምታገኟቸው አጋጣሚዎች ተጠቀሙ

በ1906 ከደረሰው የምድር መናወጥ የተረፈ አንድ ሰው፣ ይህ ክስተት “በየትኛውም ግዛት ወይም ከተማ ደርሶ የማያውቅ አሰቃቂ አደጋ” እንደሆነ ገልጿል። ይሁንና በቅርቡ ይሖዋ፣ እስከ ዛሬ ከደረሱት አደጋዎች ሁሉ ጋር ሊወዳደር የማይችል የበቀል እርምጃ “አምላክን በማያውቁ” ሰዎች ላይ ይወስዳል። (2 ተሰ. 1:8) ይሖዋ፣ ሰዎች ሁሉ ልባቸውና አእምሯቸው እንዲለወጥ እንዲሁም ምሥክሮቹ የሚሰጡትን ማስጠንቀቂያ እንዲሰሙ በጣም ይፈልጋል።—2 ጴጥ. 3:9፤ ራእይ 14:6, 7

የዕለት ተዕለት ተግባርህን ስታከናውን፣ ለመመሥከር የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች በሙሉ ትጠቀምባቸዋለህ?

ሰዎች፣ ዓይናቸው እንዲከፈትና በፊታችን ያለው ጊዜ አሳሳቢ መሆኑን እንዲያስተውሉ እንዲሁም የግል ጉዳዮቻቸውን ከማሳደድ ይልቅ ይሖዋን እንዲፈልጉ የመርዳት መብት አለህ። (ሶፎ. 2:2, 3) ታዲያ ለሥራ ባልደረቦችህ፣ ለጎረቤቶችህና የዕለት ተዕለት ተግባርህን ስታከናውን ለምታገኛቸው ሰዎች በሙሉ ለመመሥከር በሚያስችሉህ አጋጣሚዎች ትጠቀማለህ? ሰዎችን ለማስጠንቀቅ የበለጠ ጥረት ማድረግ ትችላለህ?