በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ”

“በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ”

“ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ፤ እንዲሁም በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ።”—1 ጴጥ. 4:7

1, 2. (ሀ) “በጸሎት ረገድ ንቁዎች” መሆን እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በጸሎት ረገድ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ አለብን?

የሌሊት ፈረቃ ሠራተኛ የነበረ አንድ ሰው “ከሌሊቱ ክፍለ ጊዜ በእንቅልፍ ሳይሸነፉ በንቃት ለማሳለፍ እጅግ የሚከብደው ጎህ ከመቅደዱ በፊት ያለው ሰዓት ነው” ሲል ተናግሯል። ሌሊቱን ሙሉ ምንም ሳይተኙ ለማሳለፍ የሚገደዱ ሌሎች ሰዎችም በዚህ ሐሳብ መስማማታቸው አይቀርም። ይህ ሁኔታ እኛ ከምንኖርበት ዘመን ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አሁን የምንገኘው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ማብቂያ በተቃረበበት ወቅት ላይ ነው። ይህ ሥርዓት በታሪክ ዘመን በሙሉ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በከፍተኛ ጨለማ ተውጧል፤ በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ንቁ ሆነው ለመኖር ከፍተኛ ትግል ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። (ሮም 13:12) በዚህ የመጨረሻ ሰዓት ላይ በእንቅልፍ ብንሸነፍ የሚደርስብን አደጋ ምንኛ አስከፊ ይሆናል! “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዛችንና “በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረጋችን ወሳኝ ነገር ነው።—1 ጴጥ. 4:7

2 በጊዜ ሂደት የት ቦታ ላይ እንደምንገኝ ስለምንገነዘብ እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘በጸሎት ረገድ ምን ያህል ንቁ ነኝ? በሁሉም የጸሎት ዓይነቶች እጠቀማለሁ? በተደጋጋሚስ እጸልያለሁ? ስለ ሌሎች የመጸለይ ልማድ አለኝ? ወይስ አብዛኛውን ጊዜ የምጸልየው ስለሚያስፈልጉኝና ስለምፈልጋቸው ነገሮች ብቻ ነው? ደግሞስ ለመዳን ካለኝ ተስፋ ጋር በተያያዘ ጸሎት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?’

ሁሉንም ዓይነት ጸሎት አቅርቡ

3. አንዳንዶቹ የጸሎት ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “በሁሉም ዓይነት ጸሎት” የመጸለይን አስፈላጊነት ጠቅሷል። (ኤፌ. 6:18) ወደ ይሖዋ ስንጸልይ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንዲያሟላልንና የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች ለመወጣት እንዲረዳን በተደጋጋሚ ልመና እናቀርብ ይሆናል። ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው አምላክ እርዳታ እንዲያደርግልን የምናቀርበውን ልመና በደስታ ያዳምጣል። (መዝ. 65:2) ይሁን እንጂ  ለሌሎች የጸሎት ዓይነቶችም ትኩረት ለመስጠት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እነዚህም ውዳሴን፣ ምስጋናንና ምልጃን ያካትታሉ።

4. ጸሎት ስናቀርብ ይሖዋን ደጋግመን ማወደስ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

4 ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ለእሱ ውዳሴ ማቅረባችን ተገቢ የሚሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ “ስለ ብርቱ ሥራው” እና ‘ስለ ታላቅነቱ’ በምናስብበት ጊዜ እሱን ለማወደስ እንገፋፋለን። (መዝሙር 150:1-6ን አንብብ።) በአዲስ ዓለም ትርጉም መዝሙር 150 ላይ የሚገኙት ስድስት ቁጥሮች ብቻ እንኳ 13 ጊዜ ያህል፣ ይሖዋን እንድናወድስ ያበረታቱናል! ሌላ መዝሙራዊ ደግሞ ለአምላክ ካለው ጥልቅ አክብሮታዊ ፍርሃት በመነሳት “ጻድቅ ስለ ሆነው ሕግህ፤ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ” ወይም አወድስሃለሁ ሲል ዘምሯል። (መዝ. 119:164) በእርግጥም ይሖዋ ሊወደስ ይገባዋል። ታዲያ ወደ እሱ ስንጸልይ “በቀን ሰባት ጊዜ” ይኸውም ደግመን ደጋግመን ልናወድሰው አይገባም?

5. ጸሎታችን የአመስጋኝነት መንፈስ የሚንጸባረቅበት መሆኑ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

5 ሌላው አስፈላጊ የጸሎት ዓይነት ደግሞ ምስጋና ነው። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ከተማ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።” (ፊልጵ. 4:6) ስንጸልይ ለይሖዋ ከልብ የመነጨ ምስጋና ማቅረባችን በራሱ የሚያስገኝልን ጥቅም አለ። ሰዎች “የማያመሰግኑ” በሆኑበት በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ የምንኖር በመሆኑ ይህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ያሻዋል። (2 ጢሞ. 3:1, 2) በእርግጥም ዓለም ምስጋና ቢስ የመሆን መንፈስ ተጠናውቶታል። ጠንቃቃ ካልሆንን ይህ መንፈስ በቀላሉ ሊጋባብን ይችላል። በጸሎት ለአምላክ ምስጋና ማቅረባችን ባለን ረክተን እንድንኖር የሚያስችለን ከመሆኑም ሌላ ‘አጉረምራሚና በኑሯችን የምናማርር’ እንዳንሆን ይረዳናል። (ይሁዳ 16) በተጨማሪም የቤተሰብ ራሶች ከቤተሰባቸው ጋር በሚጸልዩበት ጊዜ ምስጋና ማቅረባቸው ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው የአመስጋኝነት መንፈስ እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

6, 7. ምልጃ ምንድን ነው? ስለ የትኞቹ ጉዳዮችስ ለይሖዋ ምልጃ ማቅረብ እንችላለን?

6 ምልጃ ውስጣዊ ስሜታችንን የምናፈስበት ከልብ የመነጨ ጸሎት ነው። ለይሖዋ ምልጃ ስናቀርብ የትኞቹን ጉዳዮች ማካተት እንችላለን? ስደት በሚያጋጥመን ጊዜ ወይም ለሕይወት አስጊ የሆነ በሽታ ሲይዘን ምልጃ ማቅረብ እንችላለን። በእንደዚህ ዓይነት ወቅቶች አምላክ እንዲረዳን የምናቀርበው ጸሎት የምልጃ ይዘት እንደሚኖረው የታወቀ ነው። ይሁንና ለይሖዋ ምልጃ ማቅረብ የምንችለው በእነዚህ ወቅቶች ብቻ ነው?

7 የኢየሱስን የጸሎት ናሙና አንብብና ስለ አምላክ ስም እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥትና ፈቃድ ምን ሐሳብ እንደጠቀሰ ለማስተዋል ሞክር። (ማቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።) ይህ ዓለም በክፋት ተሞልቷል፤ ሰብዓዊ መንግሥታት ደግሞ የዜጎቻቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶች እንኳ ማሟላት እየተሳናቸው መጥቷል። ከዚህ አንጻር በሰማይ የሚኖረው አባታችን ስም እንዲቀደስና መንግሥቱ ከምድር ላይ የሰይጣንን አገዛዝ እንዲያስወግድ መጸለያችን በእርግጥ ተገቢ ነው። በተጨማሪም ይህ ወቅት የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም ላይ እንዲፈጸም ለይሖዋ ምልጃ የምናቀርብበት ጊዜ ነው። በመሆኑም በሁሉም የጸሎት ዓይነቶች በመጠቀም ንቁ ሆነን እንኑር።

‘ሳታሰልሱ ጸልዩ’

8, 9. ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ በእንቅልፍ በመሸነፋቸው በእነሱ ላይ ከመፍረድ መቆጠብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

8 ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች “በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” የሚል ማበረታቻ ቢሰጥም ቢያንስ በአንድ ወቅት እሱ ራሱ ይህን ሳያደርግ ቀርቷል። በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ኢየሱስ ይጸልይ በነበረበት ወቅት እንቅልፍ ከወሰዳቸው ደቀ መዛሙርት አንዱ ጴጥሮስ ነበር። ኢየሱስ “ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ” ካላቸው በኋላ እንኳ የተባሉትን ማድረግ አልቻሉም።—ማቴዎስ 26:40-45ን አንብብ።

9 ይሁን እንጂ መንቃት ባለመቻላቸው በጴጥሮስና  በሌሎቹ ሐዋርያት ላይ ከመፍረድ ይልቅ የዕለቱ ውሏቸው በደካማ ሥጋቸው ላይ ከባድ ተጽዕኖ ማሳደሩን መዘንጋት አይኖርብንም። ለፋሲካ በዓል አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያደርጉ ውለዋል፤ ምሽት ላይ ደግሞ በዓሉን አክብረዋል። ከዚያም ኢየሱስ የጌታን ራት በዓል አቋቋመ፤ እንዲህ ማድረጉ ወደፊት የሞቱ መታሰቢያ በተመሳሳይ መንገድ እንዲከበር የሚያስችል ነበር። (1 ቆሮ. 11:23-25) “በመጨረሻ የውዳሴ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዱ”፤ ይህም ጠባብ የሆኑትን የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች አቆራርጠው የተወሰነ ርቀት መጓዝ ጠይቆባቸዋል። (ማቴ. 26:30, 36) በዚህ ጊዜ እኩለ ሌሊት ሳያልፍ አይቀርም። በዚያ ሌሊት እኛም በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ብንገኝ ኖሮ እንቅልፍ ሊጥለን ይችል ነበር። ኢየሱስ በድካም የዛሉትን ሐዋርያቱን ከመንቀፍ ይልቅ ያሉበትን ሁኔታ በመረዳት “መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው” ብሏቸዋል።

ጴጥሮስ የተሰናከለ ቢሆንም እንኳ “በጸሎት ረገድ ንቁ” የመሆንን አስፈላጊነት ተገንዝቧል (አንቀጽ 10ንና 11ን ተመልከት)

10, 11. (ሀ) ጴጥሮስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ካጋጠመው ሁኔታ ምን ትምህርት አግኝቷል? (ለ) ጴጥሮስ ካጋጠመው ነገር ምን ትማራለህ?

10 ጴጥሮስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ያጋጠመውን ሁኔታ ፈጽሞ ሊረሳው አይችልም። ንቁ ሳይሆን በመቅረቱ ከፈጸመው አሳዛኝ ስህተት ትምህርት ቀስሟል። ቀደም ሲል ኢየሱስ “በዚህች ሌሊት ሁላችሁም በእኔ ምክንያት ትሰናከላላችሁ” ብሏቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልሰናከልም!” በማለት አስረግጦ ተናግሮ ነበር። ከዚያም ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ተናገረ። ጴጥሮስ በዚህም ሳይበገር “አብሬህ መሞት ቢያስፈልገኝ እንኳ በምንም ዓይነት አልክድህም” አለ። (ማቴ. 26:31-35) ይሁንና ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ጴጥሮስ መሰናከሉ አልቀረም። ጴጥሮስ ኢየሱስን በመካዱ በጸጸት ስሜት ተውጦ “ምርር ብሎ አለቀሰ።”—ሉቃስ 22:60-62

11 ጴጥሮስ ካጋጠመው ከዚህ ሁኔታ ትምህርት እንዳገኘ ምንም ጥያቄ የለውም፤ በራስ የመመካት ዝንባሌውንም አሸንፏል። በዚህ ረገድ ጸሎት ጴጥሮስን እንደረዳው ግልጽ ነው። ደግሞም “በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” የሚለውን ምክር የሰጠው ጴጥሮስ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። በመንፈስ መሪነት የተሰጠውን ይህን ምክር በሥራ እያዋልን ነው? ደግሞስ ‘ሳናሰልስ በመጸለይ’ በይሖዋ ላይ እንደምንመካ እናሳያለን? (መዝ. 78:7) በተጨማሪም “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ማሳሰቢያ መዘንጋት አይኖርብንም።—1 ቆሮ. 10:12

ነህምያ ያቀረባቸው ጸሎቶች ምላሽ አግኝተዋል

12. ነህምያ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

12 በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የፋርሱ ንጉሥ የአርጤክስስ ወይን ጠጅ አሳላፊ የነበረው ነህምያ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። ነህምያ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ሰው ነው። በኢየሩሳሌም  የሚኖሩ አይሁዳውያን የደረሰባቸውን መከራ በተመለከተ ለብዙ ቀናት በአምላክ ፊት ‘ሲጾምና ሲጸልይ’ ቆይቷል። (ነህ. 1:4) አርጤክስስ ፊቱ ለምን እንዳዘነ ሲጠይቀው ነህምያ ወዲያውኑ ‘ወደ ሰማይ አምላክ ጸለየ።’ (ነህ. 2:2-4) ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ይሖዋ፣ ነህምያ ላቀረባቸው ጸሎቶች መልስ ሰጠ፤ ደግሞም ሕዝቡን የሚጠቅም ነገር እንዲከናወን አደረገ። (ነህ. 2:5, 6) ይህ ሁኔታ የነህምያን እምነት ምንኛ አጠናክሮት ይሆን!

13, 14. ጠንካራ እምነት ለመያዝና ሰይጣን እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚያደርገውን ጥረት ለመቋቋም ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 ነህምያ እንዳደረገው ያለማሰለስ መጸለይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ይረዳናል። ሰይጣን ምሕረት የሚባል ነገር አያውቅም፤ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ጥቃት የሚሰነዝረው በደከምንበት ወቅት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ከሕመም ወይም ከመንፈስ ጭንቀት ጋር እየታገልን ከሆነ በየወሩ በአገልግሎት የምናሳልፈውን ጊዜ አምላክ ከቁብ እንደማይቆጥረው ማሰብ እንጀምር ይሆናል። አንዳንዶቻችን የሚያስጨንቁ ሐሳቦች ይረብሹን ይሆናል፤ እንዲህ የሚሰማን ከዚህ ቀደም በሕይወታችን ባጋጠሙን ሁኔታዎች የተነሳ ሊሆን ይችላል። ሰይጣን አልረባም የሚል ስሜት እንዲያድርብን ይፈልጋል። በአብዛኛው የእሱ ጥቃት የሚያነጣጥረው በስሜታችን ላይ ነው፤ በዚህ መንገድ እምነታችንን ለማዳከም ይጥራል። ይሁን እንጂ “በጸሎት ረገድ ንቁዎች” መሆናችን እምነታችንን ሊያጠነክርልን ይችላል። በእርግጥም ‘ትልቁ የእምነት ጋሻ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ለማምከን ያስችለናል።’—ኤፌ. 6:16

“በጸሎት ረገድ ንቁዎች” መሆናችን የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎችን እንድንቋቋም ያስችለናል (አንቀጽ 13ንና 14ን ተመልከት)

14 “በጸሎት ረገድ ንቁዎች” ከሆንን ተዘናግተን አንገኝም፤ ይህ ደግሞ ያልታሰበ የእምነት ፈተና ሲያጋጥመን አቋማችንን እንዳናላላ ይረዳናል። ፈተናዎችና መከራዎች ሲያጋጥሙን የነህምያን ምሳሌ በማስታወስ ምንም ጊዜ ሳናጠፋ ወደ አምላክ እንጸልይ። ተፈታታኝ ሁኔታዎችን በመቋቋም ረገድ ሊሳካልንና በእምነታችን ላይ የሚደርሰውን ፈተና በጽናት ልናልፍ የምንችለው በይሖዋ እርዳታ ብቻ ነው።

ለሌሎች ጸልዩ

15. ስለ ሌሎች መጸለይን በተመለከተ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

15 ኢየሱስ የጴጥሮስ እምነት እንዳይጠፋ ምልጃ አቅርቧል። (ሉቃስ 22:32) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ታማኙ ክርስቲያን ኤጳፍራ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በቆላስይስ ላሉት ወንድሞቹ በትጋት ይጸልይ ነበር። ጳውሎስ “በአምላክ ፈቃድ ሁሉ የተሟላችሁና ጽኑ እምነት ያላችሁ ሆናችሁ እንድትቆሙ ዘወትር በጸሎቱ ስለ እናንተ እየተጋደለ ነው” በማለት ጽፎላቸው ነበር። (ቆላ. 4:12) ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘በዓለም ዙሪያ ላሉ ወንድሞቼ በትጋት እጸልያለሁ? በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው የእምነት ባልንጀሮቼ ምን ያህል እጸልያለሁ? በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ከባድ ኃላፊነት ለተሸከሙት ወንድሞች ለመጨረሻ ጊዜ የጸለይኩት መቼ ነው? በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ መከራ እየደረሰባቸው ላሉ ወንድሞች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጸልዬ አውቃለሁ?’

16. ለሌሎች መጸለያችን በእርግጥ ለውጥ ያመጣል? አብራራ።

16 ለሌሎች ወደ ይሖዋ አምላክ መጸለያችን በእጅጉ ሊረዳቸው ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 1:11ን አንብብ።) ይሖዋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አገልጋዮቹ በጸሎት አንድን ጉዳይ ደጋግመው ስለጠየቁት የሆነ እርምጃ ለመውሰድ አይገደድም፤ ይሁንና አገልጋዮቹ በቡድን ደረጃ ያላቸውን ፍላጎት የሚመለከት ከመሆኑም ሌላ አንዳቸው ለሌላው የሚያሳዩትን ከልብ የመነጨ አሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት ለጸሎታቸው ምላሽ ይሰጣል። በመሆኑም ስለ ሌሎች የመጸለይ መብታችንንም ሆነ ኃላፊነታችንን አክብደን ልናየው ይገባል። ኤጳፍራ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ለክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጸሎት በመጋደል ለእነሱ ያለንን ልባዊ ፍቅርና አሳቢነት ማሳየት ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን የላቀ ደስታ ያስገኝልናል፤ ምክንያቱም “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—ሥራ 20:35

‘መዳናችን ቀርቧል’

17, 18. “በጸሎት ረገድ ንቁዎች” መሆናችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

17 ጳውሎስ “ሌሊቱ እየተገባደደ ነው፤ ቀኑም ቀርቧል” የሚለውን ሐሳብ ከመግለጹ በፊት “ዘመኑን ስለምታውቁም ይህን አድርጉ፤ አማኞች ከሆንበት ጊዜ ይልቅ አሁን መዳናችን ይበልጥ ስለቀረበ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን ነው” ሲል ጽፏል። (ሮም 13:11, 12) አምላክ ቃል የገባው አዲስ ዓለም በቅርቡ ይመጣል፤ መዳናችንም እኛ ከምናስበው በላይ በጣም ቀርቧል። በመሆኑም መንፈሳዊ እንቅልፍ ሊይዘን አይገባም፤ በዓለም ውስጥ ያሉት ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ብቻችንን ሆነን ወደ ይሖዋ መጸለይ የምንችልበት ጊዜ እንዳያሳጡን መጠንቀቅ አለብን። ከዚህ ይልቅ “በጸሎት ረገድ ንቁዎች” እንሁን። እንዲህ ማድረጋችን ‘ቅዱስ ሥነ ምግባር እየተከተልንና ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮች እየፈጸምን’ የይሖዋን ቀን እንድንጠባበቅ ይረዳናል። (2 ጴጥ. 3:11, 12) ደግሞም አኗኗራችን በመንፈሳዊ ንቁ እንደሆንና የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም መቅረቡን በእርግጥ እንደምናምን የሚያሳይ ይሆናል። እንግዲያው ‘ያለማቋረጥ እንጸልይ።’ (1 ተሰ. 5:17) በተጨማሪም የኢየሱስን አርዓያ በመከተል ለብቻችን ሆነን ወደ ይሖዋ መጸለይ የምንችልበት ምቹ ሁኔታ ለማግኘት እንጣር። ጊዜ ወስደን ወደ ይሖዋ የምንጸልይ ከሆነ ይበልጥ ወደ እሱ እንቀርባለን። (ያዕ. 4:7, 8) እንዲህ ማድረጋችን ታላቅ በረከት ያስገኝልናል!

18 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ክርስቶስ በሥጋ በኖረበት ዘመን ከሞት ሊያድነው ለሚችለው በከፍተኛ ለቅሶና እንባ ምልጃና ልመና አቀረበ፤ አምላካዊ ፍርሃት በማሳየቱም ተሰሚነት አገኘ።” (ዕብ. 5:7) ኢየሱስ ምልጃና ልመና ያቀርብ የነበረ ሲሆን ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆኗል። ከዚህም የተነሳ ይሖዋ የሚወደውን ልጁን ከሞት በማስነሳት በሰማይ የማይሞት ሕይወት በመስጠት ክሶታል። እኛም ወደፊት ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ታማኝ መሆን እንችላለን። “በጸሎት ረገድ ንቁዎች” ከሆን የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንደምናገኝ የተረጋገጠ ነው።