የትዳር ጓደኛ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም
መጽሐፍ ቅዱስ ለባልና ሚስት የሚሰጠው መመሪያ ግልጽ ነው፦ አንድ ባል “ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ።” እንደዚሁም አንዲት ሚስት “ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል።” ባልና ሚስት እንደ “አንድ ሥጋ” ሊሆኑ ይገባል። (ኤፌ. 5:33፤ ዘፍ. 2:23, 24) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በባልና ሚስት መካከል ያለው ቅርርብና አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር እየጠነከረ ይሄዳል። በመካከላቸው ያለውን ቅርበት ጎን ለጎን ከተተከሉ ዛፎች ሥሮች ጋር ማወዳደር ይቻላል። የዛፎቹ ሥሮች እርስ በርስ እንደሚተሳሰሩ ሁሉ ደስተኛ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስትም የአንዳቸው ሕይወት ከሌላው ጋር የተቆራኘ ነው።
ይሁን እንጂ ባል ወይም ሚስት ቢሞቱስ? በዚህ ጊዜ፣ በሕይወት ሳሉ የነበራቸው ትስስር ይበጠሳል። የትዳር ጓደኛውን ያጣው ወገን መሪር ሐዘንና ብቸኝነት ይሰማው ምናልባትም ብስጭት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት ያድርበት ይሆናል። በትዳር ውስጥ 58 ዓመታት ያሳለፈችው ዳንዬላ፣ ብዙዎች የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ሲያጡ ተመልክታለች። * ይሁን እንጂ ባሏ ከሞተ በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ሁኔታው ምን ስሜት እንደሚፈጥር ጨርሶ አልገባኝም ነበር። ራሳችሁ ደርሶባችሁ ካላያችሁት በቀር ይህ ስሜት ፈጽሞ ሊገባችሁ አይችልም።”
ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ሐዘን
አንዳንድ ተመራማሪዎች፣ የሚወዱትን የትዳር ጓደኛ በሞት ከማጣት የበለጠ ከባድ ጭንቀት የሚያስከትል ነገር ሊኖር እንደማይችል ይናገራሉ። እንዲህ ዓይነት ሐዘን የደረሰባቸው ብዙ ሰዎች በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ሚሊ ባሏ ከሞተ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። ያም ሆኖ የ25 ዓመታት የትዳር አጋሯን በሞት ማጣቷ የፈጠረባትን ስሜት ስትገልጽ “አካሌ እንደጎደለ ሆኖ ይሰማኛል” ብላለች።
ሱዛን፣ የትዳር ጓደኛቸው ከሞተ ከዓመታት በኋላም ሐዘናቸው ስለማይወጣላቸው ሚስቶች ስታስብ ሐዘናቸው ከልክ ያለፈ እንደሆነ ይሰማት ነበር። ከጊዜ በኋላ እሷም የ38 ዓመታት የትዳር ጓደኛዋን በሞት አጣች። ባሏ ከሞተ ከ20 ዓመታት በላይ ቢያልፉም “በየቀኑ አስታውሰዋለሁ” ትላለች። በጣም ስለሚናፍቃት ብዙ ጊዜ ታለቅሳለች።
መጽሐፍ ቅዱስ የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት የሚያስከትለው ሐዘን መሪርና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ እንደሆነ ይገልጻል። ሣራ በሞተች ጊዜ ባሏ አብርሃም ምን እንደተሰማው መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “እጅግ አዘነ፤ አለቀሰም” ይላል። (ዘፍ. 23:1, 2 የ1980 ትርጉም) አብርሃም በትንሣኤ ቢያምንም የሚወዳት ሚስቱ ስትሞት በጣም አዝኗል። (ዕብ. 11:17-19) ያዕቆብም ሚስቱ ራሔል ከሞተች በኋላ ሐዘኑን ለመርሳት ጊዜ ወስዶበታል። ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላም ከወንዶች ልጆቹ ጋር ሲያወራ ስለ እሷ የገለጸበት መንገድ ሐዘኑ እንዳልወጣለት ያሳያል።—ዘፍ. 44:27፤ 48:7
ከእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ምን እንማራለን? ባል ወይም ሚስት የሞተባቸው ሰዎች፣ ብዙውን ጊዜ ሐዘኑ ለበርካታ ዓመታት አይወጣላቸውም። በመሆኑም እንባቸውን ቢያፈስሱ ወይም ሐዘናቸውን ቢገልጹ ይህን የሚያደርጉት ከባድ ሐዘን ስለገጠማቸው እንደሆነ ልንረዳላቸው እንጂ እንደ ደካማ ልንቆጥራቸው አይገባም። የእኛ ድጋፍ እና እርዳታ ለረጅም ጊዜ ያስፈልጋቸው ይሆናል።
ስለ ነገ አትጨነቁ
የትዳር ጓደኛቸውን ያጡ ሰዎች እንደገና ብቻቸውን መኖር ቀላል አይሆንላቸውም። ባልና ሚስት በትዳር ብዙ ዓመታት ካሳለፉ በኋላ ባል፣ ሚስቱ ስትተክዝ ወይም ተስፋ ስትቆርጥ እንዴት እንደሚያጽናናትና መንፈሷን እንደሚያድስላት ያውቃል። በመሆኑም ባል ሲሞት ሚስቱ ፍቅር የሚሰጣትንና ሲከፋት የሚያጽናናትን አጋሯን ታጣለች። በተመሳሳይም አንዲት ሚስት ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ባሏ በራሱ እንዲተማመንና ደስተኛ እንዲሆን ምን ማድረግ እንዳለባት ትገነዘባለች። በፍቅር ስትደባብሰው፣ በሚያጽናና መንገድ ስታዋራው እንዲሁም የሚወዳቸውንና የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ጥረት ስታደርግ ልዩ ስሜት ይሰማዋል፤ በመሆኑም ማንም እንደ እሷ ሊሆንለት አይችልም። እሷ ስትሞት ሕይወቱ ባዶ እንደሆነ ይሰማዋል። ከዚህ አንጻር የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ አንዳንድ ሰዎች፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ስጋትና ፍርሃት ያድርባቸዋል። ታዲያ መረጋጋትና ሰላም እንዲያገኙ ሊረዷቸው የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይኖሩ ይሆን?
“ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።” (ማቴ. 6:34) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ በዋነኝነት የሚሠራው በሕይወታችን ውስጥ ከሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች ጋር በተያያዘ ነው፤ ያም ቢሆን ይህ ጥቅስ፣ የሚወዱትን ሰው በሞት የተነጠቁ ብዙ ሰዎች የደረሰባቸውን መከራ ተቋቁመው እንዲኖሩም ረድቷቸዋል። ሚስቱን በሞት ያጣ ቻርልስ የተባለ አንድ ሰው፣ ባለቤቱ ከሞተች ከጥቂት ወራት በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሞኒክን በማጣቴ የሚሰማኝ ሥቃይ አሁንም አልቀነሰም፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እየባሰ ያለ ይመስለኛል። ይሁን እንጂ ይህ ስሜት የሚጠበቅ እንደሆነና ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሐዘኔ ቀስ በቀስ እንደሚቀንስ ተገንዝቤያለሁ።”
አዎን፣ ቻርልስ ሐዘኑ የቀነሰለት “ጊዜ እያለፈ ሲሄድ” ነው። ታዲያ እስከዚያው ሐዘኑን የቻለው እንዴት ነው? “ይሖዋ፣ ስለ ነገ እንዳልጨነቅ ረድቶኛል” ብሏል። ቻርልስ፣ ሐዘኑ በአንድ ጀምበር ባይጠፋም ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠረው አልፈቀደም። እናንተም የትዳር ጓደኛችሁን በሞት ተነጥቃችሁ ከሆነ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ አትጨነቁ። ነገ፣ ያልጠበቃችሁት ጥሩ ነገር ወይም ማጽናኛ ታገኙ ይሆናል።
ይሖዋ፣ የሰው ልጆች እንዲሞቱ ዓላማው አልነበረም። ሞት ‘የዲያብሎስ ሥራ’ ካመጣቸው ችግሮች መካከል አንዱ ነው። (1 ዮሐ. 3:8፤ ሮም 6:23) ሰይጣን፣ ብዙዎችን ለሞትና ሞት ለሚያስከትለው ፍርሃት ባሪያ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ሲሆን ከዚህ የባርነት ቀንበር ነፃ የሚወጡበት ተስፋ እንዳላቸውም አያውቁም። (ዕብ. 2:14, 15) አንድ ሰው፣ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥም እንኳ እውነተኛ ደስታ የማግኘት እና ትርጉም ያለው ሕይወት የመኖር ተስፋው ሲጨልም ሰይጣን ይደሰታል። በመሆኑም የትዳር ጓደኛቸውን በሞት የተነጠቁ ሰዎች የሚሰማቸው ጭንቀት የአዳም ኃጢአትና የሰይጣን ሴራ ያስከተሉት ውጤት ነው። (ሮም 5:12) ይሖዋ የሰይጣን ጨካኝ መሣሪያ የሆነውን ሞትን ድል በማድረግ ሰይጣን ያስከተለውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ ይሽራል። ሰይጣን በውስጣቸው ካሳደረው ፍርሃት ነፃ ከወጡ ሰዎች መካከል ልክ እንደ እናንተ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት የተነጠቁ ብዙ ሰዎች ይገኙበታል።
ትንሣኤ አግኝተው ምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች የተለያዩ ለውጦች እንደሚያጋጥሟቸው የታወቀ ነው፤ ሰዎች እርስ በርሳቸው በሚኖራቸው ዝምድና ረገድ ለውጥ ይኖራል። ለምሳሌ ያህል፣ ከሞት የሚነሱ ወላጆች፣ አያቶች እንዲሁም ቅድመ አያቶች ሁሉ ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። እርጅና ያስከተላቸው ችግሮች ይወገዳሉ። በዚህም የተነሳ ሰዎች፣ ለአያት ቅድመ አያቶቻቸው ያላቸው አመለካከት አሁን ካለው የተለየ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ለውጦች መኖራቸው ሰብዓዊው ቤተሰብ እንዲሻሻል ያደርጋል።
ትንሣኤ የሚያገኙትን በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል፤ ለምሳሌ፣ ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ያገቡ ሰዎች ምን ይሆናሉ? ሰዱቃውያን፣ የመጀመሪያ ባሏ ስለሞተባትና ከዚያ በኋላ ያገባቻቸውን ሰዎችም በሞት ስላጣች ሴት ለኢየሱስ ጥያቄ አቅርበው ነበር። (ሉቃስ 20:27-33) እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች በትንሣኤ ጊዜ ምን ዓይነት ዝምድና ይኖራቸው ይሆን? የምናውቀው ነገር የለም፤ ደግሞም የግምት ሐሳብ መሰንዘር ወይም ገና ስላላወቅነው ነገር መጨነቅ አስፈላጊ አይደለም። ማድረግ የምንችለው ብቸኛ ነገር በአምላክ መተማመን ነው። ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ይሖዋ ወደፊት የሚያደርገው ነገር ሁሉ ጥሩና በጉጉት የሚጠበቅ እንጂ የሚያስፈራ አይደለም።
የትንሣኤ ተስፋ መጽናኛ ይሆናል
የአምላክ ቃል ከያዛቸው ግልጽ ትምህርቶች መካከል አንዱ የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ የሚገልጸው ትምህርት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በፊት ስለተከናወኑ ትንሣኤዎች የያዘው ታሪክ ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ የኢየሱስን ድምፅ ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት እንደሚመጣ’ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ዮሐ. 5:28, 29) በዚያን ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ከሞት መዳፍ ነፃ ከወጡት ሰዎች ጋር ሲገናኙ እጅግ ደስ ይላቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች ምን ያህል እንደሚደሰቱ መገመት እንኳ አንችልም።
ሙታን እንደገና ሕልውና ሲያገኙ ምድር ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ ደረጃ በደስታ ትሞላለች። በቢሊዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች እንደገና ምድር ላይ መኖር ይጀምራሉ። (ማር. 5:39-42፤ ራእይ 20:13) የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ ሁሉ ወደፊት በሚፈጸመው በዚህ ተአምር ላይ በማሰላሰል መጽናናት ይችላሉ።
የሞቱ ሰዎች በሚነሱበት ወቅት የሚያዝን ሰው ሊኖር ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህ እንደማይሆን ይነግረናል። ኢሳይያስ 25:8 እንደሚለው ይሖዋ ‘ሞትን ለዘላለም ይውጣል።’ ትንቢቱ በመቀጠል “ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” በማለት ስለሚናገር ሞት የሚያስከትለው ጭንቀትም ጭምር ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። የትዳር ጓደኛችሁን በሞት በማጣታችሁ አዝናችሁ ከሆነ የትንሣኤ ተስፋ እንደሚያስደስታችሁ ጥርጥር የለውም።
አምላክ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚያከናውነውን ነገር ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚችል ሰው የለም። ይሖዋ “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው” ይላል። (ኢሳ. 55:9) ኢየሱስ፣ ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር የሰጠው ተስፋ ለእኛም አንደ አብርሃም በይሖዋ ላይ እንደምንተማመን ለማሳየት አጋጣሚ ይሰጠናል። አሁን ከእያንዳንዱ ክርስቲያን የሚፈለገው ቁልፍ ነገር ቢኖር አምላክ ከእኛ የሚጠብቅብንን ነገር ማድረግ ነው፤ እንዲህ ካደረግን ከሞት ከሚነሱት ጋር ‘የሚመጣውን ሥርዓት ማግኘት የሚገባን’ እንሆናለን።—ሉቃስ 20:35
ለተስፋ መሠረት የሆነ ነገር
ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከመስጋት ይልቅ ተስፋ ይኑራችሁ። ከሰው አመለካከት አንጻር ሲታይ የወደፊቱ ጊዜ ጨለማና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። ይሖዋ ግን የተሻለ ነገር እንደሚያመጣ ተስፋ ሰጥቶናል። ይሖዋ የሚያስፈልገንንና የምንመኘውን ነገር ሁሉ የሚያረካልን እንዴት እንደሆነ ማወቅ ባንችልም ይህን እንደሚያደርግ መጠራጠር የለብንም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ተስፋ የሚደረገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ አንድ ሰው የሚያየውን ነገር ተስፋ ያደርጋል? የማናየውን ነገር ተስፋ የምናደርግ ከሆነ ግን ጸንተን እንጠባበቀዋለን።” (ሮም 8:24, 25) አምላክ፣ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ጠንካራ እምነት ማዳበር ለመጽናት ይረዳችኋል። ከጸናችሁ ደግሞ ይሖዋ ‘የልባችሁን መሻት’ የሚፈጽምበትን አስደሳች ጊዜ ለማየት ትበቃላችሁ። በዚያን ጊዜ ይሖዋ “የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት [ያረካል]።”—መዝ. 37:4፤ 145:16፤ ሉቃስ 21:19
ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ ሐዋርያቱ በጭንቀት ተውጠው ነበር። ኢየሱስ የሚከተለውን ሐሳብ በመናገር አጽናናቸው፦ “ልባችሁ አይረበሽ። በአምላክ እንደምታምኑ በተግባር አሳዩ፤ በእኔም እንደምታምኑ በተግባር አሳዩ።” እንዲሁም “ሐዘን ላይ ትቻችሁ አልሄድም። ወደ እናንተ እመጣለሁ” አላቸው። (ዮሐ. 14:1-4, 18, 27) ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ባለፉት መቶ ዘመናት የኖሩ ቅቡዓን ተከታዮቹ ሁሉ ተስፋ እንዲኖራቸውና እንዲጸኑ ረድተዋቸዋል። በሞት የተለዩአቸውን የሚወዷቸውን ሰዎች በትንሣኤ ለማግኘት የሚናፍቁ ሰዎችም በዚህ ተስፋ ሊጽናኑ ይችላሉ። ይሖዋና ልጁ ሐዘን ላይ አይተዉአቸውም። ይህን ፈጽሞ አትጠራጠሩ!
^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።