ለ100 ዓመት የዘለቀ ንጉሣዊ አገዛዝ—የአንተን ሕይወት የሚነካው እንዴት ነው?
“ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ሥራዎችህ ታላቅና አስደናቂ ናቸው። የዘላለም ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው።”—ራእይ 15:3
1, 2. የአምላክ መንግሥት ምን ያከናውናል? መንግሥቱ እንደሚመጣ እርግጠኞች መሆን የምንችለውስ ለምንድን ነው?
በ31 ዓ.ም. በጸደይ ወቅት ቅፍርናሆም አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር። (ማቴ. 6:10) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የመንግሥቱን መምጣት ይጠራጠራሉ። እኛ ግን የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ከልብ በመነጨ ስሜት የምናቀርበው ጸሎት መልስ እንደሚያገኝ እርግጠኞች ነን።
2 ይሖዋ በዚህ መንግሥት አማካኝነት በሰማይም ሆነ በምድር ያለውን ቤተሰቡን አንድ ያደርጋል። ይህ መለኮታዊ ዓላማ በእርግጥ ይፈጸማል። (ኢሳ. 55:10, 11) እንዲያውም ይሖዋ እኛ በምንኖርበት በዚህ ዘመን ነግሷል! ባለፉት 100 ዓመታት የታዩት አስደናቂ ክንውኖች ለዚህ ማስረጃ ይሆናሉ። አምላክ በሚሊዮን ለሚቆጠሩት ታማኝ ተገዢዎቹ አስደናቂ የሆኑ ታላላቅ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። (ዘካ. 14:9፤ ራእይ 15:3) ይሁንና የይሖዋ መንገሥና ኢየሱስ ባስተማረው ጸሎት ላይ የተጠቀሰው የአምላክ መንግሥት መምጣት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እነዚህ ሁለት ክንውኖች የሚለያዩት እንዴት ነው? የእኛን ሕይወት የሚነኩትስ እንዴት ነው?
ይሖዋ የሾመው ንጉሥ እርምጃ መውሰድ ጀመረ
3. (ሀ) ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ የተሾመው መቼና የት ነበር? (ለ) መንግሥቱ የተቋቋመው በ1914 መሆኑን እንዴት ማረጋገጥ ትችላለህ? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
3 በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ፣ ዳንኤል ከ2,500 ዓመታት በፊት በጻፈው አንድ ትንቢት ላይ ብርሃን ፈነጠቀ፤ ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስ . . . መንግሥት ይመሠርታል።” (ዳን. 2:44) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች 1914 ልዩ ዓመት እንደሚሆን ለአሥርተ ዓመታት ሲናገሩ ቆይተዋል። በዚያን ጊዜ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት ነበራቸው። አንድ ጸሐፊ እንደገለጹት “በ1914 የነበረው ዓለም በመልካም ምኞትና ተስፋ የተሞላ ነበር።” ይሁን እንጂ በዚያው ዓመት መገባደጃ ላይ አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ። ጦርነቱን ተከትሎ የተከሰተው ረሃብ፣ የምድር መንቀጥቀጥና ቸነፈር እንዲሁም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ማግኘታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 በሰማይ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት መጀመሩን በማያሻማ መንገድ አረጋግጠዋል። * ይሖዋ ልጁን መሲሐዊ ንጉሥ አድርጎ በመሾም በአዲስ መንገድ ነግሷል ሊባል ይችላል!
4. አምላክ የሾመው አዲስ ንጉሥ ወዲያውኑ ምን እርምጃ ወሰደ? ቀጥሎስ ምን አደረገ?
4 አምላክ የሾመው አዲስ ንጉሥ በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ የአባቱ ቀንደኛ ጠላት በሆነው በሰይጣን ላይ ጦርነት መክፈት ነበር። ኢየሱስና መላእክቱ ዲያብሎስንና አጋንንቱን ከሰማይ አባረሯቸው። ይህም በሰማይ ታላቅ ደስታ ያስገኘ ሲሆን በምድር ላይ ግን ታይቶ የማይታወቅ የመከራ ዘመን አስከትሏል። (ራእይ 12:7-9, 12ን አንብብ።) በመቀጠል ንጉሡ በምድር ላይ ያሉት ተገዢዎቹ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም እንዲችሉ እነሱን ማጥራት፣ ማስተማርና ማደራጀት ጀመረ። ንጉሡ በእነዚህ ሦስት መስኮች ለወሰደው እርምጃ ተገዢዎቹ የሰጡት በጎ ምላሽ በዛሬው ጊዜ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
መሲሐዊው ንጉሥ ታማኝ ተገዢዎቹን አጠራ
5. በ1914 እና በ1919 መጀመሪያ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ምን የማጥራት ሥራ ተካሂዷል?
5 መግዛት የጀመረው ንጉሥ ሰማይን ሰይጣንና አጋንንቱ ከሚያሳድሩት መጥፎ ተጽዕኖ ካጸዳ በኋላ በምድር ላይ ያሉት ተከታዮቹ የሚገኙበትን መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲመረምርና እንዲያጠራ ይሖዋ መመሪያ ሰጠው። ነቢዩ ሚልክያስ ይህ እርምጃ መንፈሳዊ የማጥራት ሥራ እንደሆነ ገልጿል። (ሚል. 3:1-3) ይህ የተከናወነው በ1914 እና በ1919 መጀመሪያ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ታሪክ ያሳያል። * የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ክፍል ለመሆን ንጹሕ ወይም ቅዱስ መሆን አለብን። (1 ጴጥ. 1:15, 16) በሐሰት ሃይማኖት ወይም በዚህ ዓለም ፖለቲካ እንዳንበከል መጠንቀቅ ይኖርብናል።
6. መንፈሳዊ ምግብ የሚዘጋጀው እንዴት ነው? አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
6 ከዚያም ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ሾሟል። ይህ ባሪያ በኢየሱስ ጥበቃ ሥር ባለው “አንድ መንጋ” ውስጥ ለታቀፉት ሁሉ ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ በየጊዜው ያቀርባል። (ማቴ. 24:45-47፤ ዮሐ. 10:16) ከ1919 አንስቶ የተቀቡ ወንድሞችን ያቀፈ አንድ ትንሽ ቡድን ‘አገልጋዮቹን’ የመመገቡን ከባድ ኃላፊነት በታማኝነት ሲወጣ ቆይቷል። ታማኝና ልባም ባሪያ በእምነት ማደግ እንድንችል የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል። ይህ ምግብ በመንፈሳዊ፣ በሥነ ምግባር፣ በአእምሮና በአካላዊ ሁኔታ ንጹሕ ሆነን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። ከዚህም ሌላ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ እየተከናወነ ባለው በጣም አስፈላጊ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እንድናደርግ ያስተምረናል እንዲሁም ያስታጥቀናል። በእነዚህ ዝግጅቶች በሚገባ እየተጠቀምክ ነው?
ንጉሡ ተገዢዎቹን በዓለም ዙሪያ እንዲሰብኩ ያስተምራቸዋል
7. ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የትኛውን አስፈላጊ ሥራ ማከናወን ጀመረ? ሥራው የሚቆየውስ እስከ መቼ ድረስ ነው?
7 ኢየሱስ በምድር ላይ ማገልገል በጀመረበት ወቅት “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በሕይወቱ ውስጥ ያከናወነው ትልቅ ሥራ ይህ ነበር። ለደቀ መዛሙርቱ “ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 10:7) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ተከታዮቹ ይህን መልእክት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” እንደሚያሰራጩ ትንቢት ተናግሯል። (ሥራ 1:8) እስከ ሥርዓቱ ፍጻሜ ድረስ ለዚህ አስፈላጊ ሥራ እሱ ራሱ ድጋፍ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።—ማቴ. 28:19, 20
8. ንጉሡ ምድራዊ ተገዢዎቹን ለተግባር ያነሳሳው እንዴት ነው?
8 በ1919 “የመንግሥቱ ምሥራች” ተጨማሪ መልእክት ያዘለ ሆነ። (ማቴ. 24:14) ንጉሡ በሰማይ በመግዛት ላይ የነበረ ሲሆን በመንፈሳዊ ሁኔታ የጠሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ምድራዊ ተገዢዎች ሰብስቦ ነበር። ‘በሰማይ የተቋቋመውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች በመላው ምድር ስበኩ’ በማለት ኢየሱስ ለሰጣቸው ለተግባር የሚያነሳሳ መመሪያ ፈጣን ምላሽ ሰጡ። (ሥራ 10:42) ለምሳሌ ያህል፣ በመስከረም 1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ወደ 20,000 የሚጠጉ የመንግሥቱ ደጋፊዎች ተሰብስበው ነበር። ወንድም ራዘርፎርድ “የአምላክ መንግሥት” በሚል ርዕስ በሰጠው ንግግር ላይ እንደሚከተለው ብሎ በተናገረ ጊዜ የተሰማቸውን ደስታ መገመት አያዳግትም፦ “እነሆ ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው! እናንተ ደግሞ የእሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ።” በማግስቱ ልዩ በሆነ “የአገልግሎት ቀን” ላይ ሁለት ሺህ የሚሆኑ ልዑካን ስብሰባው ከሚካሄድበት ቦታ አንስቶ እስከ 72 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኙ ቤቶች በመስበክ ለጥሪው ምላሽ ሰጥተዋል። አንድ ወንድም “መንግሥቱን እንድናስታውቅ የቀረበው ጥሪና እዚያ ተሰብስቦ የነበረው ሕዝብ ያሳየው ቅንዓት መቼም አይረሳኝም!” በማለት ተናግሯል። እንዲህ የተሰማው እሱ ብቻ አልነበረም።
9, 10. (ሀ) የመንግሥቱን አዋጅ ነጋሪዎች ለማሠልጠን ምን ዝግጅቶች ተደርገዋል? (ለ) ከዚህ ሥልጠና በግለሰብ ደረጃ ምን ጥቅም አግኝተሃል?
9 በ1922 በዓለም ዙሪያ በ58 አገሮች ውስጥ ከ17,000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ምሥራቹን ይሰብኩ ነበር። ይሁንና እነዚህ አስፋፊዎች ሥልጠና ያስፈልጋቸው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዕጩው ንጉሥ ለደቀ መዛሙርቱ ምን፣ የትና እንዴት መስበክ እንዳለባቸው ግልጽ መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴ. 10:5-7፤ ሉቃስ 9:1-6፤ 10:1-11) በተመሳሳይ ሁኔታ ዛሬም ኢየሱስ ሁሉም የመንግሥቱ ሰባኪዎች አስፈላጊውን መመሪያ እንዲያገኙ እንዲሁም ውጤታማ በሆነ መንገድ መስበክ የሚያስችሉ መሣሪያዎች እንዲሟሉላቸው ያደርጋል። (2 ጢሞ. 3:17) ኢየሱስ ተገዢዎቹን በክርስቲያን ጉባኤ በኩል ለአገልግሎት እያሠለጠናቸው ነው። እነሱን የሚያሠለጥንበት አንዱ መንገድ በምድር ዙሪያ ከ111,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚካሄደው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ነው። ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰባኪዎች በዚህ ሥልጠና በመጠቀም ምሥራቹን “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ማራኪ በሆነ መንገድ ለመስበክና ለማስተማር ብቁ ሆነዋል።—1 ቆሮንቶስ 9:20-23ን አንብብ።
10 ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በተጨማሪ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች የተቋቋሙ ሲሆን የጉባኤ ሽማግሌዎችን፣ አቅኚዎችን፣ ነጠላ ወንድሞችን፣ ክርስቲያን ባለትዳሮችን፣ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትንና ሚስቶቻቸውን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስቶቻቸውን እንዲሁም ሚስዮናውያንን ያሠለጥናሉ። * ለባለትዳሮች በተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተካፈሉ ተማሪዎች ለትምህርት ቤቱ ያላቸውን አድናቆት እንደሚከተለው በማለት ገልጸዋል፦ “ያገኘነው ልዩ ሥልጠና ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ያሳደገልን ከመሆኑም ሌላ ሌሎችን ለመርዳት የተሻለ ብቃት እንዲኖረን አስችሎናል።”
11. የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ተቃውሞ እያለም መስበካቸውን መቀጠል የቻሉት እንዴት ነው?
11 ይህ መጠነ ሰፊ የስብከትና የማስተማር ሥራ ጠላት ከሆነው ከሰይጣን እይታ የተሰወረ አይደለም። ሥራውን ለማስቆም በሚያደርገው ጥረት በመንግሥቱ መልእክትም ሆነ በመልእክተኞቹ ላይ ቀጥተኛና ስውር ጥቃት ይሰነዝራል። ይሁንና ሰይጣን አይሳካለትም። ይሖዋ ለልጁ “ከየትኛውም መንግሥት፣ ሥልጣን፣ ኃይልና ጌትነት. . . እጅግ የላቀ ቦታ ሰጥቶታል።” (ኤፌ. 1:20-22) ኢየሱስ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን የአባቱን ፈቃድ ለማስፈጸም ሲል ሥልጣኑን ደቀ መዛሙርቱን ለመጠበቅና ለመምራት ይጠቀምበታል። * ምሥራቹ መታወጁን ቀጥሏል፤ ቅን ልብ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም የይሖዋን መንገዶች እየተማሩ ነው። በዚህ ታላቅ ሥራ ላይ መካፈል መቻላችን ወደር የሌለው መብት ነው!
ንጉሡ ተገዢዎቹን ለበለጠ ሥራ ያደራጃቸዋል
12. የአምላክ መንግሥት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተካሄዱትን አንዳንድ ድርጅታዊ ማሻሻያዎች ግለጽ።
12 የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ንጉሡ፣ የአምላክ አገልጋዮች የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጁበት መንገድ እየተሻሻለ እንዲሄድ አድርጓል። (ኢሳይያስ 60:17ን አንብብ።) በ1919 በእያንዳንዱ ጉባኤ ለስብከቱ ሥራ አመራር የሚሰጥ የአገልግሎት ዳይሬክተር ተሹሞ ነበር። በ1927 እሁድ እሁድ በቋሚነት ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ተጀመረ። የመንግሥቱ ደጋፊዎች በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም መጠራት ከጀመሩ በኋላ ለበለጠ ሥራ ተነሳሱ። (ኢሳ. 43:10-12) በ1938 በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚያገለግሉ ወንድሞችን በድምፅ ብልጫ መምረጡ ቀርቶ ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ መሾም ተጀመረ። በ1972 የጉባኤውን ሥራ በበላይነት የሚመራው አንድ የጉባኤ የበላይ ተመልካች መሆኑ ቀርቶ ኃላፊነቱ ለሽማግሌዎች አካል ተሰጠ። ብቃቱን ያሟሉ ወንዶች ሁሉ ‘የአምላክን መንጋ በመጠበቁ’ ሥራ ለመካፈል ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ማበረታቻ ተሰጣቸው። (1 ጴጥ. 5:2) በ1976 የበላይ አካሉ በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ በበላይነት ለመከታተል በስድስት ኮሚቴዎች ተደራጀ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይሖዋ የሾመው ንጉሥ የመንግሥቱን ተገዢዎች በቲኦክራሲያዊ መንገድ ወይም ከአምላክ አገዛዝ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ደረጃ በደረጃ ማደራጀቱን ቀጥሏል።
13. መሲሐዊው ንጉሥ በገዛባቸው 100 ዓመታት የተከናወኑት ነገሮች የአንተን ሕይወት የነኩት እንዴት ነው?
13 መሲሐዊው መንግሥት መግዛት ከጀመረ ወዲህ ባሉት 100 ዓመታት ውስጥ ያከናወነውን ነገር እስቲ ቆም ብለህ አስብ! ተከታዮቹን በመንፈሳዊ በማንጻት የይሖዋን ስም መሸከም እንዲችሉ አድርጓል። የመንግሥቱ ምሥራች በ239 አገሮች እንዲሰበክ አመራር የሰጠ ከመሆኑም ሌላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋን መንገድ እንዲማሩ አስችሏል። የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡትን ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ታማኝ ተገዢዎች አንድ ማድረግ ችሏል። (መዝ. 110:3) በእርግጥም ይሖዋ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ያከናወናቸው ሥራዎች በጣም አስደናቂ ናቸው። ይሁንና ከዚህ ይበልጥ አስደሳች የሆኑ ክንውኖች ከፊታችን ይጠብቁናል!
መሲሐዊው መንግሥት የሚያመጣቸው በረከቶች
14. (ሀ) “መንግሥትህ ይምጣ” ብለን ስንጸልይ አምላክ ምን እንዲያደርግ መጠየቃችን ነው? (ለ) የ2014 የዓመት ጥቅሳችን ምንድን ነው? ተስማሚ ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በ1914 መሲሐዊ ንጉሥ አድርጎ የሾመው ቢሆንም “መንግሥትህ ይምጣ” ብለን የምናቀርበው ጸሎት የተሟላ ምላሽ አግኝቷል ማለት አይደለም። (ማቴ. 6:10) ኢየሱስ ‘በጠላቶቹ መካከል ሆኖ እንደሚገዛ’ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል። (መዝ. 110:2) በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰብዓዊ መንግሥታት አሁንም የአምላክን መንግሥት ይቃወማሉ። የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ስንጸልይ አምላክ፣ በመሲሐዊው ንጉሥና በተባባሪ ገዢዎቹ አማካኝነት ሰብዓዊውን አገዛዝ እንዲያስወግድና በምድር የሚገኙትን የመንግሥቱን ተቃዋሚዎች እንዲያጠፋ መጠየቃችን ነው። በዚህ ጊዜ የአምላክ መንግሥት “እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል” የሚለው በዳንኤል 2:44 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል። የመንግሥቱ ጠላቶች የሆኑትን የፖለቲካ ኃይሎች ይደመስሳል። (ራእይ 6:1, 2፤ 13:1-18፤ 19:11-21) ይህ የሚፈጸምበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። የአምላክ መንግሥት በሰማይ የተቋቋመበት 100ኛ ዓመት የሆነው የ2014 የዓመት ጥቅሳችን “መንግሥትህ ይምጣ” የሚለው የማቴዎስ 6:10 ጥቅስ መሆኑ ተስማሚ ነው!
የ2014 የዓመት ጥቅሳችን፦ “መንግሥትህ ይምጣ።”—ማቴዎስ 6:10
15, 16. (ሀ) በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ምን አስደሳች ነገሮች ይፈጸማሉ? (ለ) መሲሐዊ ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ በመጨረሻ ምን ያደርጋል? ይህስ ይሖዋ ለፍጥረታቱ ሁሉ ካለው ዓላማ ጋር በተያያዘ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
15 መሲሐዊው ንጉሥ የአምላክን ጠላቶች ካጠፋ በኋላ ሰይጣንንና አጋንንቱን ለአንድ ሺህ ዓመት ወደ ጥልቁ ይወረውራቸዋል። (ራእይ 20:1-3) ይህ ጎጂ ተጽዕኖ ከተወገደ በኋላ የአምላክ መንግሥት ሰዎች ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅም እንዲያገኙ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ የአዳም ኃጢአት ያስከተላቸውን መዘዞች ያስወግዳል። ንጉሡ በሞት ያንቀላፉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያስነሳል፤ እንዲሁም ስለ ይሖዋ እንዲማሩ መጠነ ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር ይዘረጋል። (ራእይ 20:12, 13) መላዋ ምድር እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ ገነት ትሆናለች። ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ፍጹማን ይሆናሉ።
16 በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ መሲሐዊው መንግሥት ዓላማውን ከዳር ያደርሳል። ከዚያም ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ ያስረክባል። (1 ቆሮንቶስ 15:24-28ን አንብብ።) ከዚህ በኋላ በይሖዋና በምድራዊ ልጆቹ መካከል አማላጅ አያስፈልግም። በሰማይ የሚገኙት የአምላክ ልጆችም ሆኑ በምድር ያሉት ልጆቹ የአጽናፈ ዓለማዊው ቤተሰቡ አባል በመሆን ከሰማዩ አባታቸው ጋር አንድነት ይኖራቸዋል።
17. ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?
17 የአምላክ መንግሥት መግዛት ከጀመረ በኋላ በነበሩት 100 ዓመታት የተከናወኑት አስደሳች ነገሮች ይሖዋ ሁሉንም ነገር እንደሚቆጣጠርና ለምድር ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም እርግጠኞች እንድንሆን ያደርጉናል። እንግዲያው በታማኝነት እሱን ማገልገላችንን እንዲሁም ንጉሡንና መንግሥቱን ማስታወቃችንን እንቀጥል። ይህን የምናደርገው ይሖዋ “መንግሥትህ ይምጣ” ብለን ለምናቀርበው ከልብ የመነጨ ጸሎት በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጥ በመተማመን ነው።