በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጭንቀት ጊዜ ከመምጣቱ በፊት ይሖዋን ማገልገል

የጭንቀት ጊዜ ከመምጣቱ በፊት ይሖዋን ማገልገል

“ፈጣሪህን አስብ።”—መክ. 12:1

1, 2. (ሀ) ሰለሞን በመንፈስ መሪነት ለወጣቶች ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) በ50ዎቹ ዕድሜ የሚገኙና ከዚያ በላይ የሆናቸው ክርስቲያኖችም ሰለሞን ለሰጠው ምክር ትኩረት መስጠት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

ንጉሥ ሰለሞን በመንፈስ መሪነት ለወጣቶች “የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣ . . . በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” የሚል ምክር ሰጥቷል። “የጭንቀት ጊዜ” የተባለው ምንድን ነው? ሰለሞን ትኩረት የሚስብ ቅኔያዊ አነጋገር በመጠቀም በመከራ የተሞላውን የእርጅና ዘመን ሲገልጽ እጆች እንደሚንቀጠቀጡ፣ እግሮች እንደሚብረከረኩ፣ ጥርስ እንደሚረግፍ፣ ዓይን እንደሚፈዝ፣ ጆሮ እንደሚደክም፣ ፀጉር እንደሚሸብትና ሰውነት እንደሚጎብጥ ተናግሯል። የትኛውም ሰው ቢሆን ይሖዋን ለማገልገል ዕድሜው ገፍቶ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ መጠበቅ አይኖርበትም።መክብብ 12:1-5ን አንብብ።

2 በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙና ከዚያ በላይ የሆናቸው ብዙ ክርስቲያኖች አሁንም ከፍተኛ ብርታት አላቸው። ፀጉራቸው በተወሰነ ደረጃ ሸብቶ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ሰለሞን የገለጻቸው የጤና ችግሮች አላጋጠሟቸው ይሆናል። እነዚህ በዕድሜ ጠና ያሉ ክርስቲያኖች ሰለሞን በመንፈስ መሪነት ለወጣቶች ከሰጠው “ፈጣሪህን አስብ” ከሚለው ምክር ጥቅም ማግኘት ይችላሉ? ይህ ምክር ምን መልእክት ያስተላልፋል?

3. ታላቁ ፈጣሪያችንን ማሰብ ሲባል ምን ማለት ነው?

 3 ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ስናገለግል የቆየን ቢሆንም እንኳ ፈጣሪያችን ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ አንዳንድ ጊዜ ቆም ብለን በአድናቆት ማሰባችን ይጠቅመናል። ሕይወት እጅግ አስደናቂ ስጦታ አይደለም? እጅግ ውስብስብ የሆነ ንድፍ ያለው ከመሆኑ የተነሳ ከሰዎች የመረዳት ችሎታ በላይ ነው። ይሖዋ ብዙ ዓይነት አስደናቂ ነገሮችን የፈጠረ በመሆኑ በሕይወት እንድንደሰት የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎች አሉን። በይሖዋ የፍጥረት ሥራ ላይ ባሰላሰልን ቁጥር ለፍቅሩ፣ ለጥበቡና ለኃይሉ ያለን የአድናቆት ስሜት ይታደሳል። (መዝ. 143:5) ሆኖም ስለ ታላቁ ፈጣሪያችን ማሰብ በእሱ ዘንድ ያሉብንን ግዴታዎች ማሰብንም ይጨምራል። እንዲህ ቆም ብለን ማውጠንጠናችን በሕይወት ዘመናችን በሙሉ ፈጣሪያችንን ለማገልገል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ለእሱ ያለንን አድናቆት ለመግለጽ ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ ያነሳሳናል።—መክ. 12:13

በኋለኞቹ ዓመታት የሚገኙ ልዩ አጋጣሚዎች

4. የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያኖች ራሳቸውን ምን ብለው መጠየቅ ይችላሉ? ለምንስ?

4 የብዙ ዓመት ተሞክሮ ያለህ ሰው ከሆንክ ‘አሁን ያለኝን ጉልበትና ጥንካሬ እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ በጣም አስፈላጊ ነው። ተሞክሮ ያካበትክ ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን ሌሎች የሌሏቸው አጋጣሚዎች አሉህ። ከይሖዋ የተማርከውን ነገር ለወጣቶች ማካፈል ትችላለህ። አምላክን ስታገለግል ያገኘሃቸውን ተሞክሮዎች በመናገር ሌሎችን ማበረታታት ትችላለህ። ንጉሥ ዳዊት፣ አምላክ እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ እንዲሰጠው ጸልዮአል። “አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ . . . አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ ክንድህን ለመጭው ትውልድ፣ ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣ እስከምገልጽ ድረስ” ሲል ጽፏል።—መዝ. 71:17, 18

5. በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች የቀሰሙትን እውቀት ለሌሎች ማካፈል የሚችሉት እንዴት ነው?

5 በረጅም ዓመታት ውስጥ ያካበትከውን ጥበብ ለሌሎች ማካፈል የምትችለው እንዴት ነው? አምላክን የሚያገለግሉ ወጣቶችን ቤትህ በመጋበዝ የሚያንጽ ጊዜ ማሳለፍ ትችል ይሆን? ከእነሱ ጋር አገልግሎት በመውጣት ይሖዋን ማገልገል ምን ያህል እንደሚያስደስትህ እንዲያዩ ማድረግ ትችላለህ? ከበርካታ ዘመናት በፊት የኖረው ኤሊሁ “ዕድሜ ይናገራል፤ ረጅም ዘመን ጥበብን ያስተምራል” ብሏል። (ኢዮብ 32:7) ሐዋርያው ጳውሎስ ተሞክሮ ያካበቱ ክርስቲያን ሴቶች በቃልም ሆነ በተግባር ሌሎችን እንዲያበረታቱ አሳስቧቸዋል። “አረጋውያን ሴቶች . . . ጥሩ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ” በማለት ጽፏል።—ቲቶ 2:3

ሌሎችን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

6. የብዙ ዓመት ተሞክሮ ያካበቱ ክርስቲያኖች ያላቸውን አቅም አቅልለው መመልከት የሌለባቸው ለምንድን ነው?

6 ተሞክሮ ያካበትክ ክርስቲያን ከሆንክ ሌሎችን ለመርዳት ልታደርገው የምትችለው ብዙ ነገር አለ። በዕድሜ ከበሰልክ በኋላ የተማርካቸውን ነገሮች እስቲ ቆም ብለህ አስብ፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከዛሬ 30 ወይም 40 ዓመት በፊት የማታውቃቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ታውቃለህ። የሌሎችን ልብ በሚነካ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዴት ማስተማር እንደሚቻል ተምረሃል። ሽማግሌ ከሆንክ ደግሞ የተሳሳተ እርምጃ የወሰዱ ወንድሞችን እንዴት መርዳት እንዳለብህ ታውቃለህ። (ገላ. 6:1) የጉባኤ ሥራዎችን፣ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ያሉትን የተለያዩ የሥራ ምድቦች ወይም የመንግሥት አዳራሽ ግንባታን እንዴት በበላይነት መከታተል እንደሚቻል የቀሰምከው ልምድ ይኖር ይሆናል። ዶክተሮች ያለ ደም ሕክምና መስጠት የሚችሉባቸውን መንገዶች እንዲጠቀሙ እንዴት ማግባባት እንደሚቻል ታውቅ ይሆናል። እውነትን ያወቅከው በቅርቡ ቢሆንም እንኳ ጠቃሚ የሕይወት ተሞክሮ አለህ። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆች ያሳደግክ ከሆንክ ከፍተኛ እውቀትና ችሎታ አካብተሃል ማለት ነው። በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች፣ ወንድሞችንና እህቶችን በማስተማር፣ በመምራትና በማበረታታት የይሖዋን ሕዝቦች መጥቀም የሚችሉበት ከፍተኛ አቅም አላቸው።ኢዮብ 12:12ን አንብብ።

7. በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ለወጣቶች ምን ዓይነት ጠቃሚ ሥልጠና መስጠት ይችላሉ?

7 ያለህን ችሎታ በተሟላ መንገድ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንዴት ማስጀመርና መምራት እንደሚቻል ለወጣቶች  ማሳየት ትችላለህ። እህት ከሆንሽ፣ ወጣት እናቶች ትናንሽ ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ ምክር መለገስ ትችያለሽ? ወንድም ከሆንክ ደግሞ ወጣት ወንድሞች ንግግራቸውን በግለት እንዲያቀርቡና ይበልጥ ውጤታማ የምሥራቹ ሰባኪዎች እንዲሆኑ ማሠልጠን ትችላለህ? ደግሞስ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችንና እህቶችን ስትጠይቅ በመንፈሳዊ የምታበረታታቸው እንዴት እንደሆነ ልታሳያቸው ትችላለህ? የቀድሞውን ያህል አካላዊ ብርታት ባይኖርህም እንኳ ወጣቶችን ማሠልጠን የምትችልበት ግሩም አጋጣሚ አለህ። የአምላክ ቃል “የጎልማሶች ክብር ብርታታቸው፣ የሽማግሌዎችም ሞገስ ሽበታቸው ነው” ይላል።—ምሳሌ 20:29

ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል

8. ሐዋርያው ጳውሎስ በኋለኛው የሕይወት ዘመኑ ምን አድርጓል?

8 ሐዋርያው ጳውሎስ በኋለኛው የሕይወት ዘመኑ ባለው አቅም ሁሉ አምላክን አገልግሏል። በ61 ዓ.ም. ገደማ ሮም ውስጥ ከእስር በተፈታበት ጊዜ በሚስዮናዊነት አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት ብዙ ደክሟል፤ በመሆኑም ሮም ውስጥ ተደላድሎ ተቀምጦ መስበክ ይችል ነበር። (2 ቆሮ. 11:23-27) በዚያ ትልቅ ከተማ የሚኖሩት ወንድሞች ጳውሎስ እዚያው ተቀምጦ ቢረዳቸው እንደሚደሰቱ ምንም ጥርጥር የለውም። ጳውሎስ ግን ከፍተኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሌሎች አገሮች እንዳሉ ተገንዝቦ ነበር። ከጢሞቴዎስና ከቲቶ ጋር ሆኖ ሚስዮናዊ አገልግሎቱን በመቀጠል ወደ ኤፌሶን ከዚያም ወደ ቀርጤስ ተጓዘ፤ ወደ መቄዶንያም ሳይሄድ አልቀረም። (1 ጢሞ. 1:3፤ ቲቶ 1:5) ወደ ስፔን ስለመሄዱ የምናውቀው ነገር ባይኖርም ወደዚያ የመሄድ ዕቅድ እንደነበረው ተናግሯል።—ሮም 15:24, 28

9. ጴጥሮስ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ያገለገለው መቼ ሊሆን ይችላል? (የመጀመሪያውን ሥዕል ተመልከት።)

9 ሐዋርያው ጴጥሮስ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ በተዛወረበት ወቅት ዕድሜው ከ50 ዓመት በላይ ሳይሆን አይቀርም። ይህን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በዕድሜ የኢየሱስ እኩያ ከሆነ ወይም ኢየሱስን ትንሽ ይበልጠው ከነበረ በ49 ዓ.ም. ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ኢየሩሳሌም ውስጥ በተገናኘበት ጊዜ 50 ዓመት ገደማ ሊሆነው ይችላል። (ሥራ 15:7) ይህ ስብሰባ ከተካሄደ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ በባቢሎን ለመኖር ወደዚያ ሄዷል፤ እንዲህ ያደረገው በዚያ አካባቢ ለሚኖሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያን ለመስበክ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ገላ. 2:9) በ62 ዓ.ም. ገደማ በመንፈስ መሪነት የመጀመሪያውን ደብዳቤ የጻፈው በባቢሎን በነበረበት ጊዜ ነው። (1 ጴጥ. 5:13) ውጭ አገር መኖር ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ጴጥሮስ በዕድሜ የገፋ መሆኑ ይሖዋን በተሟላ መንገድ ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታ እንዲያሳጣው አልፈቀደም።

10, 11. በኋለኛው የሕይወት ዘመናቸው ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ስለተዛወሩ ባልና ሚስት የሚገልጸውን ተሞክሮ ተናገር።

10 በዛሬው ጊዜ በ50ዎቹ ዕድሜ የሚገኙና ከዚያ በላይ የሆናቸው ብዙ ክርስቲያኖች ያሉበት ሁኔታ እንደተለወጠና ከቀድሞው ለየት ባለ መንገድ ይሖዋን ማገልገል እንደሚችሉ ተገንዝበዋል። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሮበርት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔና ባለቤቴ በ50ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ በነበርንበት ጊዜ ልንጠቀምባቸው የምንችል በርካታ አጋጣሚዎች እንዳሉን ተገነዘብን። ያለን አንድ ልጅ ራሱን ችሎ መኖር ጀምሯል፤ የእኛን እርዳታ የሚሹ በዕድሜ የገፉ ወላጆች የሉንም፤ በዚህ ላይ ደግሞ አነስተኛ ውርስ አግኝተን ነበር። መኖሪያ ቤታችንን ብንሸጥ የቤቱን ዕዳ መክፈልና የጡረታ አበል መቀበል እስክጀምር ድረስ በዚህ ገንዘብ መተዳደር እንደምንችል ተገነዘብኩ። በቦሊቪያ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች እንዳሉና ኑሮ ርካሽ እንደሆነ ሰማን። በመሆኑም ወደዚያ ለመዛወር ወሰንን። አዲሱን መኖሪያችንን መልመድ ቀላል ሆኖ አላገኘነውም። ሁሉም ነገር በሰሜን አሜሪካ ከለመድነው በጣም የተለየ ሆኖብን ነበር። ሆኖም ያደረግነው ጥረት በሚገባ ክሶናል።”

11 ሮበርት በማከል እንዲህ ብሏል፦ “በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችን በሙሉ በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናናቸው አንዳንድ ሰዎች ተጠምቀዋል። ያስጠናናቸው የአንድ ቤተሰብ አባላት ኑሯቸው ዝቅተኛ ሲሆን የሚኖሩት ደግሞ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ መንደር ውስጥ ነው። ሆኖም የቤተሰቡ አባላት በየሳምንቱ ከተማ ውስጥ  በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ለመገኘት አድካሚ ጉዞ ያደርጋሉ። ቤተሰቡ እድገት ሲያደርግና የመጀመሪያ ልጃቸው የአቅኚነት አገልግሎት ሲጀምር በማየታችን የተሰማንን ታላቅ ደስታ መገመት ትችላላችሁ!”

የውጭ አገር ቋንቋ በሚነገርባቸው ክልሎች ሰባኪዎች ያስፈልጋሉ

12, 13. አንድ ክርስቲያን ጡረታ የሚወጣበት ዕድሜ ላይ ከደረሰ በኋላ በአዲስ መንገድ ይሖዋን እንዴት ማገልገል እንደጀመረ ተሞክሮውን ተናገር።

12 በውጭ አገር ቋንቋ የሚካሄዱ ጉባኤዎችና ቡድኖች በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች የሚተዉትን ምሳሌ በመመልከት በእጅጉ ሊጠቀሙ ይችላሉ። በተጨማሪም በእንዲህ ዓይነቱ ክልል ማገልገል በጣም አስደሳች ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ብራየን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እንግሊዛውያን ጡረታ የሚወጡበት ዕድሜ ላይ ስደርስ ይኸውም 65 ዓመት ሲሞላኝ እኔና ባለቤቴ ሥራ እንደፈታን ሆኖ ተሰማን። ልጆቻችን ራሳቸውን ችለው መኖር ጀምረዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች ደግሞ እምብዛም አይገኙም። በዚህ ጊዜ በከተማችን በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጥናታዊ ምርምር እያደረገ ካለ አንድ ቻይናዊ ወጣት ጋር ተገናኘሁ። ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ስጋብዘው ፈቃደኛ ሆነ፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናው ጀመር። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ቻይናዊ የሥራ ባልደረባውን ይዞ መምጣት ጀመረ። ከሁለት ሳምንት በኋላ ሦስተኛ ሰው፣ ከዚያም አራተኛ ሰው ይዞ መጣ።

13 “በምርምር ሥራ ላይ የተሠማራ አምስተኛ ቻይናዊ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳስጠናው ሲጠይቀኝ ‘65 ዓመት ሞላኝ ማለት እኮ ከይሖዋ አገልግሎት በጡረታ እገለላለሁ ማለት አይደለም’ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ ከእኔ በሁለት ዓመት የምታንሰውን ባለቤቴን ቻይንኛ መማር ትፈልግ እንደሆነ ጠየቅኳት። ከዚያም በቴፕ በተቀዳ የቋንቋ ማስተማሪያ መጠቀም ጀመርን። ይህ ከሆነ አሥር ዓመት ገደማ ሆኖታል። የውጭ አገር ቋንቋ በሚነገርበት ክልል ማገልገላችን እንደገና ወጣት እንደሆንን እንዲሰማን አድርጓል። እስካሁን ድረስ 112 ቻይናውያንን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንተናል! አብዛኞቹ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ ነበር። ከእነሱ መካከል አንዷ በአሁኑ ጊዜ አቅኚ ሆና አብራን በማገልገል ላይ ትገኛለች።”

ዕድሜህ የገፋ ቢሆንም እንኳ አገልግሎትህን ማስፋት ትችል ይሆናል (አንቀጽ 12ንና 13ን ተመልከት)

አቅማችሁ የሚፈቅደውን በማድረግ ደስታ ለማግኘት ጣሩ

14. በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ምን ነገር ሊያስደስታቸው ይገባል? የጳውሎስ ምሳሌ ሊያበረታታቸው የሚችለውስ እንዴት ነው?

14 በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖች ከይሖዋ አገልግሎት ጋር በተያያዘ አዳዲስ ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችሉ ግሩም አጋጣሚዎች ያሏቸው  ቢሆንም ይህን ማድረግ የሚችሉት ሁሉም አይደሉም። አንዳንዶች የጤንነት ችግር አለባቸው፤ ሌሎች ደግሞ አረጋውያን ወላጆቻቸውን ወይም በእነሱ ሥር የሚተዳደሩ ልጆቻቸውን ይንከባከቡ ይሆናል። ይሁንና ይሖዋ ከእሱ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የምታከናውኑትን ማንኛውንም ተግባር እንደሚያደንቅ መዘንጋት የለባችሁም። ስለዚህ ማድረግ በማትችሉት ነገር ከመበሳጨት ይልቅ ማድረግ በምትችሉት ነገር ለመደሰት ጥረት አድርጉ። የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ተመልከቱ። ለዓመታት የቁም እስረኛ ሆኖ ስለነበር የሚስዮናዊነት ጉዞውን መቀጠል አልቻለም ነበር። ሆኖም ሊጠይቁት ለሚመጡት ሰዎች ሁሉ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ይነግራቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ በእምነት እንዲጸኑ ያበረታታቸው ነበር።—ሥራ 28:16, 30, 31

15. አረጋውያን ክርስቲያኖች ከፍ ያለ ግምት የሚሰጣቸው ለምንድን ነው?

15 በተጨማሪም ይሖዋ አረጋውያን እሱን ለማገልገል የሚያደርጉትን ጥረት ያደንቃል። ሰለሞን የጤና ችግሮች የሚከሰቱበት ይህ አስጨናቂ የሕይወት ዘመን ተፈታታኝ እንደሚሆን ያመለከተ ቢሆንም ይሖዋ አረጋውያን ክርስቲያኖች እሱን ለማወደስ የሚያደርጉትን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ሉቃስ 21:2-4) የጉባኤው አባላትም ቢሆኑ በመካከላቸው የሚገኙት በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች ለረጅም ጊዜ በታማኝነት በማገልገል ረገድ የተዉትን ምሳሌ ያደንቃሉ።

16. አረጋዊቷ ሐና የትኞቹን መብቶች አላገኘች ይሆናል? ሆኖም ለይሖዋ አምልኮ ማቅረብ የቻለችው በምን መንገድ ነው?

16 መጽሐፍ ቅዱስ ሐና የተባለች አረጋዊት ሴት በእርጅና ዘመኗም ይሖዋን በታማኝነት ታወድስ እንደነበር ይገልጻል። ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት ሐና የ84 ዓመት መበለት ነበረች። በመሆኑም በዕድሜዋ መግፋት የተነሳ የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ ለመቀባትና የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ የሚያስችል አጋጣሚ አላገኘች ይሆናል። ሆኖም ሐና በወቅቱ ማድረግ የምትችለውን ነገር ታደርግ ነበር። “ሌትና ቀንም . . . ቅዱስ አገልግሎት እያቀረበች ከቤተ መቅደስ ፈጽሞ አትጠፋም ነበር።” (ሉቃስ 2:36, 37) ካህኑ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በየዕለቱ ጠዋትና ማታ ዕጣን በሚያጥንበት ጊዜ ሐና በግቢው ውስጥ ከሚሰበሰቡት ሰዎች ጋር ሆና ምናልባትም ለግማሽ ሰዓት ያህል በልቧ ትጸልይ ነበር። ሕፃኑን ኢየሱስን ስትመለከት ‘የኢየሩሳሌምን መዳን ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ መናገር ጀመረች።’—ሉቃስ 2:38

17. አረጋውያንና አቅመ ደካማ የሆኑ ክርስቲያኖች በእውነተኛው አምልኮ እንዲካፈሉ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

17 በዛሬው ጊዜ አረጋውያን ወይም አቅመ ደካማ የሆኑትን ክርስቲያኖች ለመርዳት ንቁዎች መሆን አለብን። አንዳንዶቹ በጉባኤ ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የሚጓጉ ቢሆንም ያሉበት ሁኔታ አይፈቅድላቸው ይሆናል። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎች በአሳቢነት ተነሳስተው እንዲህ ያሉ አረጋውያን ስብሰባዎቹን በስልክ እንዲከታተሉ ዝግጅት አድርገውላቸዋል። በሌሎች ቦታዎች ግን እንዲህ ማድረግ አይቻል ይሆናል። ያም ሆኖ በስብሰባዎች ላይ መገኘት የማይችሉ ክርስቲያኖች እውነተኛውን አምልኮ በመደገፍ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ጉባኤው እየተጠናከረ እንዲሄድ ጸሎት ማቅረብ ይችላሉ።መዝሙር 92:13, 14ን አንብብ።

18, 19. (ሀ) አረጋውያን ክርስቲያኖች ለሌሎች የብርታት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) “ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እነማን ናቸው?

18 አረጋውያን ክርስቲያኖች ለሌሎች ምን ያህል የብርታት ምንጭ እንደሆኑ አይገነዘቡ ይሆናል። ለምሳሌ ሐና ለብዙ ዓመታት በታማኝነት በቤተ መቅደሱ አምልኮ ታቀርብ የነበረ ቢሆንም እሷ የተወችው ምሳሌ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላም ለሌሎች የብርታት ምንጭ እንደሚሆን አልተገነዘበች ይሆናል። ሐና ለይሖዋ የነበራት ፍቅር በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። በተመሳሳይ እናንተም ለአምላክ ያላችሁ ፍቅር በሌሎች ወንድሞችና እህቶች ልብ ውስጥ እንደሚቀረጽ ጥርጥር የለውም። የአምላክ ቃል “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ማለቱ ምንም አያስደንቅም!—ምሳሌ 16:31

19 ሁላችንም የአቅም ገደብ ያለብን በመሆኑ በይሖዋ አገልግሎት ልናከናውነው የምንችለው ነገር የተወሰነ ነው። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የተወሰነ አቅምና ብርታት ያለን ሰዎች ሁሉ “የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣ . . . ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ቃል በቁም ነገር መመልከት ይኖርብናል።—መክ. 12:1