በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ከታሪክ ማኅደራችን

አንድ መቶ ዓመት ያስቆጠረ የእምነት ገድል

አንድ መቶ ዓመት ያስቆጠረ የእምነት ገድል

“ከወንድም ራስል ይበልጥ ወንድም ራስልን ይመስላል!”—በ1914 “ፎቶ ድራማን” የተመለከተ አንድ ግለሰብ የተናገረው

በዚህ ዓመት፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ስለመሆኑ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ለመርዳት ሲባል የተዘጋጀው “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ ከበቃ 100 ዓመት ይሞላዋል። የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰነዘር ትችትና ሁሉን ነገር የመጠራጠር አስተሳሰብ የብዙዎችን እምነት ሸርሽሮ በነበረበት በዚያ ዘመን “ፎቶ ድራማ” ይሖዋ ፈጣሪ መሆኑን በሰፊው አሳውቋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን በግንባር ቀደምትነት ሲመራ የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ውጤታማና ፈጣን በሆነ መንገድ ማሰራጨት የሚቻልበትን ዘዴ ሲፈልግ ቆይቷል። በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በታተሙ ጽሑፎች አማካኝነት ለሦስት አሥርተ ዓመታት እውነትን ሲያሰራጩ ቆይተዋል። በዚህ ጊዜ ግን አንድ አዲስ ዘዴ ትኩረታቸውን ሳበው፤ ይህም ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መጠቀም ነበር።

በተንቀሳቃሽ ምስሎች አማካኝነት ወንጌልን ማሰራጨት

በ1890ዎቹ ዓመታት ድምፅ አልባ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በሰዎች ዘንድ እየታወቁ መጥተው ነበር። በ1903 መጀመሪያ አካባቢ በኒው ዮርክ ሲቲ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ሃይማኖታዊ ፊልም ታይቶ ነበር። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ወንድም ራስል በ1912 “ፎቶ ድራማን” ለማዘጋጀት በድፍረት ሲነሳ የተንቀሳቃሽ ምስል ኢንዱስትሪ ገና ጨቅላ ነበር። ወንድም ራስል ይህ ዓይነቱ የመገናኛ ዘዴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማሳወቁ ሥራ ጽሑፎች ብቻ ሊያስገኙት የማይችሉትን ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር።

ስምንት ሰዓት የሚወስደውና ብዙውን ጊዜ በአራት ክፍል የሚታየው “ፎቶ ድራማ” በዘመኑ ብዙዎች ድምፁን በሚያውቁት እውቅ ተናጋሪ የቀረቡ 96 አጫጭር የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ያካተተ ነው። አብዛኞቹ ትዕይንቶች በክላሲካል ሙዚቃ የታጀቡ ነበሩ። ጥሩ ችሎታ ያላቸው ወንድሞች የተቀዳውን ንግግርና ሙዚቃ በፎኖግራፍ አማካኝነት እያጫወቱ ከባለቀለም ስላይዶቹና በድራማ መልክ ከተሠሩት የታወቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ጋር በማቀናበር ያሳዩ ነበር።

“ፎቶ ድራማ” ጥር 11, 1914 ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ የበቃው በወቅቱ የዓለም አቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር ንብረት በሆነው በኒው ዮርክ ሲቲ ቲያትር ቤት ነበር

አብዛኞቹ ፊልሞችና መስተዋት ስላይዶች ከተለያዩ የፊልም ድርጅቶች የተገዙ ነበሩ። በፊላደልፊያ፣ በኒው ዮርክ፣ በፓሪስና በለንደን የሚገኙ በሙያው የተካኑ ሰዓሊዎች እያንዳንዱን ትዕይንት በመስተዋት ስላይዶቹና በፊልሞቹ ላይ ይስሉ ነበር። አብዛኞቹን ሥዕሎች የሚስሉት በቤቴል የሥነ ጥበብ ክፍል ውስጥ ያገለግሉ የነበሩ ወንድሞችና እህቶች ሲሆኑ ስላይዶቹ በሚሰበሩበት  ጊዜም በምትካቸው ሌሎች ስላይዶችን ያዘጋጁ ነበር። ከተገዙት ፊልሞች በተጨማሪ የቤቴል ቤተሰብ አባላት በዮንከርስ፣ ኒው ዮርክ አቅራቢያ አብርሃምን፣ ይስሐቅንና አብርሃም ልጁን ሊሰዋ ሲል የከለከለውን መልአክ ወክለው ሲተውኑ ተቀርጸዋል።—ዘፍ. 22:9-12

ልምድ ያካበቱ ወንድሞች ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለውን ፊልም፣ 26 የፎኖግራፍ ቅጂዎችንና ወደ 500 የሚጠጉ የመስተዋት ስላይዶችን ምንም ዝንፍ ሳያደርጉ ጊዜያቸውን ጠብቀው ያሳዩ ነበር

የወንድም ራስል የሥራ አጋር የነበረ አንድ ወንድም ይህ ዘዴ “በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደረገ ሲሆን ከዚህ በፊት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ለማስፋፋት ከተደረጉት ጥረቶች ሁሉ የላቀ ውጤት አስመዝግቧል” በማለት ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሮ ነበር። የሃይማኖት መሪዎች መንፈሳዊ ጥማት ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት የተደረገውን ይህን ጥረት አድናቆት ቸረውት ይሆን? በፍጹም! በጥቅሉ ሲታይ የቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት “ፎቶ ድራማን” ያወገዙት ከመሆኑም ሌላ አንዳንዶቹ ሕዝቡ እንዳያየው ለማድረግ የተለያዩ መሰሪ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ይህ ፊልም ሊታይ ታቅዶ በነበረበት ቦታ አንድ የቀሳውስት ቡድን መብራት እንዲቋረጥ አድርጎ ነበር።

በአካባቢው ከሚገኙት ጉባኤዎች የመጡ በፊልም ቤቱ የሚያስተናግዱ እህቶች “በፎቶ ድራማ” ላይ የሚታዩ ምስሎች የታተሙባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ በራሪ ወረቀቶችን በነፃ አሰራጭተዋል

ትዕይንቱን ለማየት የተሰበሰቡት ታዳሚዎች የኢየሱስ የሕፃንነት ሥዕል ያለባቸው የደረት ጌጦች ይሰጧቸው ነበር። እነዚህ ጌጦች ሰዎቹን “የሰላም ልጆች” መሆን እንዳለባቸው ያሳስቧቸው ነበር

ያም ሆኖ “ፎቶ ድራማን” በነፃ ለማየት ብዙ ሕዝብ ወደ ትያትር ቤቶች ይጎርፍ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ በየዕለቱ በ80 ከተሞች “ፎቶ ድራማ” ይታይ ነበር። ከተመልካቾቹ መካከል አብዛኞቹ ‘ድምፅ ያለው ፊልም’ ለመጀመሪያ ጊዜ በማየታቸው ተደንቀው ነበር። ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው በፍጥነት በሚቀያየሩ ፎቶዎች አማካኝነት አንዲት ጫጩት ስትፈለፈል እንዲሁም አበባ ሲፈካ መመልከት ችለው ነበር። በጊዜው በነበሩ ሳይንሳዊ ግኝቶች አማካኝነት የይሖዋን ጥበብ ማጉላት ተችሎ ነበር። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው አንድ ግለሰብ፣ ወንድም ራስል “ፎቶ ድራማን” ሲያስተዋውቅ በስክሪኑ ላይ ሲመለከት “ከወንድም ራስል ይበልጥ ወንድም ራስልን ይመስላል!” በማለት አስተያየት ሰጥቷል።

መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ረገድ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ ፊልም

“ፎቶ ድራማ” ጥር 11, 1914 ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ የበቃው በወቅቱ የዓለም አቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር ንብረት በሆነው በኒው ዮርክ ሲቲ ቲያትር ቤት ነበር

ደራሲና የፊልም ታሪክ ምሁር የሆኑት ቲም ዲርክስ “ፎቶ ድራማን” አስመልክተው ሲናገሩ “ድምፅ (የተቀዳ ንግግር)፣ ተንቀሳቃሽ ፊልምና ብርሃን የሚያልፍባቸው ባለ ቀለም ስላይዶች ተቀናጅተው የቀረቡበት የመጀመሪያው ፊልም ነው” ብለዋል። “ከፎቶ ድራማ” በፊት የተሠሩ ፊልሞች ከእነዚህ ዘዴዎች መካከል አንዳንዶቹን ተጠቅመው የነበረ ቢሆንም ሁሉንም ዘዴዎች በአንድነት አቀናጅቶ የያዘ (ያውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ያለው) ፊልም ግን አልነበረም። በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያና በኒው ዚላንድ የሚኖሩ ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአንድ ዓመት ብቻ የተመለከቱት ሌላ ፊልም አልነበረም!

“ፎቶ ድራማ” ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ የቀረበው ጥር 11, 1914 በኒው ዮርክ ሲቲ ነበር። ከሰባት ወር በኋላም እጅግ አስከፊ የሆነውና ከጊዜ በኋላ አንደኛው የዓለም ጦርነት የሚል ስያሜ የተሰጠው ጦርነት ጀመረ። ይሁን እንጂ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ሰዎች “ፎቶ ድራማን” ለማየት መጉረፋቸውን አላቋረጡም፤ በዚያም የአምላክ መንግሥት ወደፊት የሚያመጣቸውን በረከቶች የሚያሳዩትን ሕያው የሆኑ ትዕይንቶች በመመልከት ማጽናኛ ያገኙ ነበር። በእርግጥም በ1914 “ፎቶ ድራማን” የሚተካከል ትዕይንት አልነበረም።

በመላው ሰሜን አሜሪካ “ፎቶ ድራማን” የሚያሳዩ ሃያ ቡድኖች ነበሩ