ይሖዋ—የሚያስፈልገንን የሚሰጠንና የሚጠብቀን አምላክ
“ወዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን አውቆአልና እከልለዋለሁ።”—መዝ. 91:14
ቤተሰብን የመሠረተው ይሖዋ ነው። (ኤፌ. 3:14, 15) የአንድ ቤተሰብ አባላት ብንሆንም እንኳ በባሕርይ ልንለያይና በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ሁኔታዎች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ከልጅነት እስከ እውቀት ድረስ ያደጋችሁት ከወላጆቻችሁ ጋር ሊሆን ይችላል። አንዳንዶቻችሁ በበሽታ፣ በአደጋ ወይም በሌሎች አሳዛኝ ክስተቶች የተነሳ ወላጆቻችሁን በሞት አጥታችሁ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ የወላጆቻቸውን ማንነት እንኳ ፈጽሞ ላያውቁ ይችላሉ።
1, 2. የቤተሰባችንን ሁኔታና እውነትን የሰማንበትን መንገድ በተመለከተ በመካከላችን ምን ዓይነት ልዩነቶች ይታያሉ?
2 የይሖዋን አምላኪዎች ባቀፈው ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ወደ እውነት የመጡበት መንገድ የተለያየ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ‘እውነት ውስጥ አድገህ’ ይሆናል፤ ወላጆችህ መለኮታዊ መመሪያዎችን አስተምረውህ ሊሆን ይችላል። (ዘዳ. 6:6, 7) ወይም ደግሞ የይሖዋ አገልጋዮች በሚያከናውኑት የስብከት ሥራ አማካኝነት እውነትን ከሰሙት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ልትሆን ትችላለህ።—ሮም 10:13-15፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4
3. ሁላችንንም የሚያመሳስሉን አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
3 ከላይ የተጠቀሱት ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው ሁላችንንም የሚያመሳስሉን አንዳንድ ነገሮች አሉ። የአዳም አለመታዘዝ ያስከተላቸው መዘዞች ገፈት ቀማሽ ከመሆናችንም ሌላ አለፍጽምና፣ ኃጢአትና ሞት ወርሰናል። (ሮም 5:12) ያም ሆኖ እውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋን “አባታችን” ብለን መጥራታችን ተገቢ ነው። ኢሳይያስ 64:8 በጥንት ዘመን ስለነበሩት የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች ሲናገር ይሖዋን “አንተ አባታችን ነህ” ብለው መጥራት ይችሉ እንደነበር አመልክቷል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ባስተማረው የጸሎት ናሙና ላይ ጸሎቱን የከፈተው “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት ነው።—ማቴ. 6:9
4, 5. ለአባታችን ለይሖዋ ያለንን አድናቆት ማሳደግ እንድንችል ለየትኛው ጉዳይ ትኩረት መስጠታችን ይጠቅመናል?
4 በሰማይ የሚኖረው አባታችን ስሙን በእምነት ስለምንጠራ በቡድን ደረጃ የሚያስፈልገንን እንክብካቤና ጥበቃ ያደርግልናል። መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዩን በተመለከተ እንዲህ ብሎ መናገሩን ጠቅሷል፦ “ወዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን አውቆአልና እከልለዋለሁ።” (መዝ. 91:14) አዎ፣ ይሖዋ አምላክ የእሱ ሕዝብ በመሆናችን ሙሉ በሙሉ ለጥፋት እንዳንዳረግ በፍቅር ተነሳስቶ ከጠላቶቻችን እጅ ያድነናል፤ ደግሞም ይጠብቀናል።
5 በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ያለንን አድናቆት ለማሳደግ የሚረዱንን ሦስት አበይት ጉዳዮች እንመልከት፦ (1) አባታችን የሚያስፈልገንን ነገር ያሟላልናል። (2) ይሖዋ ጠባቂያችን ነው። (3) አምላክ የቅርብ ወዳጃችን ነው። እነዚህን ነጥቦች ስንመረምር ከአምላክ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ማሰላሰላችንና ለአባታችን አክብሮት ማሳየት የምንችልበትን መንገድ ማስተዋላችን ጠቃሚ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች በሚሰጠው በረከት ላይ ማሰላሰላችን ይጠቅመናል።—ያዕ. 4:8
ይሖዋ፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ የሚሰጠን አምላክ
6. ይሖዋ ‘የመልካም ስጦታ ሁሉ’ ምንጭ መሆኑን ያሳየበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?
6 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤ ምክንያቱም ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት [ነው]” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 1:17) ሕይወት በራሱ ከይሖዋ ያገኘነው ድንቅ ስጦታ ነው። (መዝ. 36:9) በመሆኑም ሕይወታችንን መለኮታዊውን ፈቃድ ለመፈጸም የምንጠቀምበት ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፈ በረከት እናገኛለን፤ ወደፊት ደግሞ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖረናል። (ምሳሌ 10:22፤ 2 ጴጥ. 3:13) ይሁንና የአዳም አለመታዘዝ ካስከተለው አሳዛኝ መዘዝ አንጻር ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
7. አምላክ ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖረን መንገዱን የከፈተልን እንዴት ነው?
7 ይሖዋ ዘርዝረን ልንጨርሰው በማንችል መንገድ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ የሚሰጠን አምላካችን ነው። ለአብነት ያህል፣ ከታላቅ ደግነቱ የተነሳ እኛን ለማዳን ዝግጅት አድርጓል። አዎ፣ ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን፤ ይህም የሆነው ከመጀመሪያው አባታችን አለፍጽምና ስለወረስን ነው። (ሮም 3:23) ይሁንና ይሖዋ ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሳ ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት እንድንችል ቅድሚያውን ወስዶ መንገዱን ከፍቶልናል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሚከተለው መንገድ ተገልጧል፤ ምክንያቱም እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል። ፍቅር የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው፤ እኛ አምላክን ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን ስለላከ ነው።”—1 ዮሐ. 4:9, 10
8, 9. ይሖዋ በአብርሃምና በይስሐቅ ዘመን ታላቅ ሰጪ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
8 ኢየሱስ ከመወለዱ ከ1,900 ዓመታት በፊት ይሖዋ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያደረገውን ፍቅራዊ ዝግጅት የሚያሳይ ትንቢታዊ ድርጊት ተፈጽሟል። ዕብራውያን 11:17-19 እንዲህ ይላል፦ “አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ድረስ እምነት አሳይቷል፤ የተስፋን ቃል በደስታ የተቀበለው ይህ ሰው አንድያ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል፤ ይህን ያደረገው ‘“ዘርህ” በይስሐቅ በኩል ይጠራል’ ተብሎ ተነግሮት እያለ ነው። ይሁንና አምላክ ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር፤ እንደ ምሳሌ ሆኖ በሚያገለግል ሁኔታም ልጁን ከሞት አፋፍ መልሶ አገኘው።” አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ እንደነበረ ሁሉ ይሖዋ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሰው ልጆች ሲል መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል።—ዮሐንስ 3:16, 36ን አንብብ።
9 ይስሐቅ መሥዋዕት ከመሆን በመትረፉ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! አምላክ በእሱ ፋንታ መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብ በአቅራቢያው ባለ ቁጥቋጦ መካከል የተያዘ አንድ አውራ በግ በማዘጋጀቱ ይስሐቅ ከፍተኛ የአመስጋኝነት ስሜት እንደተሰማው ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘፍ. 22:10-13) ይህ ስፍራ “ያህዌ ይርኤ” ወይም ይሖዋ “ያዘጋጃል” ተብሎ መጠራቱ ምንም አያስደንቅም።—ዘፍ. 22:14
እርቅ የሚያስገኝ ዝግጅት
10, 11. “የማስታረቅ አገልግሎት” በማከናወኑ ሥራ ግንባር ቀደም የሆኑት እነማን ናቸው? ሥራውን ያከናወኑትስ እንዴት ነው?
10 ይሖዋ ባደረገልን ዝግጅቶች ሁሉ ላይ ስናሰላስል ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ወሳኝ ሚና በታላቅ አድናቆት እንመለከታለን፤ ጳውሎስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አንድ ሰው ለሁሉም መሞቱን ስለተረዳን ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል፤ ምክንያቱም ሁሉም ቀድሞውኑ ሞተዋል፤ በሕይወት ያሉት ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።”—2 ቆሮ. 5:14, 15
11 የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ለአምላክ ካላቸው ፍቅርና የእሱ አገልጋይ በመሆን ላገኙት በዋጋ የማይተመን መብት ከነበራቸው አመስጋኝነት የተነሳ የተሰጣቸውን “የማስታረቅ አገልግሎት” በደስታ ተቀብለዋል። የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራቸው ልበ ቅን የሆኑ ግለሰቦች ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲመሠርቱ፣ የእሱ ወዳጆች እንዲሆኑና በመጨረሻም መንፈሳዊ ልጆቹ እንዲሆኑ መንገድ ከፍቷል። በዛሬው ጊዜ በመንፈስ የተቀቡ የይሖዋ አገልጋዮች ተመሳሳይ አገልግሎት ያከናውናሉ። የአምላክና የክርስቶስ አምባሳደሮች በመሆን የሚያከናውኑት ሥራ ይሖዋ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ወደ ራሱ እንዲስባቸውና አማኞች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 5:18-20ን አንብብ፤ ዮሐ. 6:44፤ ሥራ 13:48
12, 13. ይሖዋ ላደረገልን በርካታ ዝግጅቶች ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?
12 በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ሁሉም ክርስቲያኖች ታላቅ ሰጪ ለሆነው ለይሖዋ ካላቸው አድናቆት የተነሳ ከቅቡዓኑ ጋር ሆነው የመንግሥቱን ምሥራች ይሰብካሉ። በዚህ ሥራ ስንካፈል በመጽሐፍ ቅዱስ እንጠቀማለን፤ ይህም ሌላው ግሩም የሆነ የአምላክ ዝግጅት ነው። (2 ጢሞ. 3:16, 17) በስብከቱ ሥራ ስንካፈል በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ቃሉን በሚገባ በመጠቀም ሌሎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ አጋጣሚ እንከፍትላቸዋለን። ይህን ሥራ ስናከናውን ድጋፍ የሚሰጠን ሌላም የይሖዋ ዝግጅት አለ፤ ይህም ቅዱስ መንፈሱ ነው። (ዘካ. 4:6፤ ሉቃስ 11:13) በየዓመቱ የሚዘጋጀው የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) እንደሚያሳየው የስብከቱ ሥራ አስደናቂ ውጤቶች እያስገኘ ነው። የሚያስፈልገንን ሁሉ የሚሰጠን አምላካችንና አባታችን እንዲወደስ በሚያስችለው በዚህ ሥራ መካፈላችን ታላቅ ክብር ነው!
13 አምላክ ካደረገልን ከእነዚህ ዝግጅቶች ሁሉ አንጻር እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ይሖዋ ላደረጋቸው ዝግጅቶች ካለኝ ጥልቅ አድናቆት የተነሳ አቅሜ የሚፈቅደውን ያህል እያገለገልኩ ነው? የምሥራቹ ሰባኪ እንደመሆኔ መጠን በየትኞቹ መስኮች ማሻሻያ ማድረግ እችላለሁ? ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምችለውስ እንዴት ነው?’ በሕይወታችን ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት አምላክ ላደረገልን ግሩም ዝግጅቶች አመስጋኝነታችንን ማሳየት እንችላለን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ የሚያስፈልጉን ነገሮች እንዲሟሉልን ያደርጋል። (ማቴ. 6:25-33) አምላክ ፍቅር ስለሚያሳየን የእሱን ልብ ደስ ለማሰኘት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንደምንፈልግ የተረጋገጠ ነው።—ምሳሌ 27:11
14. ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚታደግ ያሳየው እንዴት ነው?
14 መዝሙራዊው ዳዊት “እኔ ድኻና ችግረኛ ነኝ፤ ጌታ ግን ያስብልኛል። አንተ ረዳቴና አዳኜ ነህ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 40:17) ይሖዋ ሕዝቡን በቡድን ደረጃ እንደሚታደግ በተደጋጋሚ አሳይቷል፤ በተለይ ጠላቶቻቸው ከባድ ስደት ሲያደርሱባቸውና እረፍት ሲነሷቸው ታዳጊያቸው መሆኑን አስመሥክሯል። በእነዚህ ጊዜያት አምላክ ለሚያደርግልን እርዳታና በተለያየ መንገድ ለሚያቀርብልን የማያቋርጥ መንፈሳዊ ዝግጅት እጅግ አመስጋኞች ነን!
ይሖዋ ሕዝቡን ይጠብቃል
15. አንድ አፍቃሪ አባት ልጁን ከአደጋ ለመጠበቅ ምን እንዳደረገ ግለጽ።
15 አንድ አፍቃሪ አባት ለልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚያቀርብ ከመሆኑም ሌላ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። አደጋ ከተደቀነባቸው እነሱን ለማዳን አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል። አንድ ወንድም ልጅ እያለ ያጋጠመውን ሁኔታ ፈጽሞ አይረሳውም። እሱና አባቱ ከአገልግሎት ወደ ቤት እየተመለሱ ሳለ አንድ ወንዝ አቋርጠው መሄድ ነበረባቸው። የዚያን ቀን ጠዋት ከጣለው ኃይለኛ ዝናብ የተነሳ ወንዙ በጣም ሞልቶ ነበር። ውኃውን መሻገር የሚችሉበት ብቸኛው አማራጭ ትላልቅ ድንጋዮቹን ዘልለው እየረገጡ መሄድ ነበር። ከአባቱ ፊት ይሄድ የነበረው ልጅ አንደኛውን ድንጋይ ስቶ ጎርፉ ውስጥ ወደቀ፤ ከዚያም ከአንዴም ሁለቴ ብቅ ጥልቅ አለ። አባትየው ትከሻውን አፈፍ አድርጎ በመያዝ ልጁን ከመስመጥ በማዳኑ ልጁ በአመስጋኝነት ስሜት እንደሚሞላ የታወቀ ነው! በሰማይ የሚኖረው አባታችን በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ከሚደርስብንና የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን ከሚሰነዘርብን እንደ ማዕበል ያለ ችግር ያድነናል። የትኛውም ሰው ቢሆን ከይሖዋ የተሻለ ጠባቂ ሊያገኝ እንደማይችል የተረጋገጠ ነው።—ማቴ. 6:13፤ 1 ዮሐ. 5:19
16, 17. እስራኤላውያን አማሌቃውያንን ሲዋጉ ይሖዋ የረዳቸውና የጠበቃቸው እንዴት ነበር?
16 ይሖዋ በ1513 ዓ.ዓ. እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣና ቀይ ባሕርን በተአምራዊ መንገድ እንዲሻገሩ ካደረገ በኋላ የተከናወነው ነገር በፍቅር ተነሳስቶ ጥበቃ ማድረግ እንደሚችል በሚገባ ያሳያል። እስራኤላውያን ምድረ በዳውን አቋርጠው ወደ ሲና ተራራ እያመሩ ሳሉ ራፊዲም ደረሱ።
17 በዘፍጥረት 3:15 ላይ ከሰፈረው መለኮታዊ ትንቢት አንጻር ሰይጣን ደካማ መስለው የሚታዩትን እስራኤላውያን ለማጥቃት የተቻለውን ሁሉ ጥረት አድርጎ ሊሆን ይችላል። የአምላክ ሕዝብ ጠላት የሆኑትን አማሌቃውያንን በመጠቀም ይህን ለማሳካት ሞክሯል። (ዘኍ. 24:20) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ በሆኑት በኢያሱ፣ በሙሴ፣ በአሮንና በሖር አማካኝነት ያከናወነውን ነገር ተመልከት። ኢያሱ አማሌቃውያንን እየተዋጋ ሳለ ሙሴ፣ አሮንና ሖር በአቅራቢያው በሚገኝ ኮረብታ ላይ ነበሩ። ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ ሲያነሳ እስራኤላውያን በውጊያው ያሸንፉ ነበር። እጆቹ በዛሉ ጊዜ አሮንና ሖር ወደ ላይ ይደግፉለት ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ባደረገላቸው እርዳታና ጥበቃ “ኢያሱ የአማሌቃውያንን ሰራዊት በሰይፍ ድል አደረገ።” (ዘፀ. 17:8-13) ሙሴ በዚያ መሠዊያ ሠርቶ “ይሖዋ ንሲ” ብሎ የሰየመው ሲሆን ትርጉሙም ይሖዋ “አርማዬ ነው” የሚል ነው።—ዘፀአት 17:14, 15ን አንብብ።
ሰይጣን ከሚሰነዝርባቸው ጥቃት ጥበቃ አግኝተዋል
18, 19. በዛሬው ጊዜ አምላክ ለአገልጋዮቹ ምን ዓይነት ጥበቃ አድርጓል?
18 ይሖዋ የሚወዱትንና የሚታዘዙትን ሰዎች ይጠብቃል። በራፊዲም እንደነበሩት እስራኤላውያን እኛም ከጠላት ጋር ስንፋጠጥ አምላክ እንዲረዳን ወደ እሱ ዞር እንላለን። ይሖዋ በቡድን ደረጃ ብዙ ጊዜ ጠብቆናል፤ እንዲሁም በዲያብሎስ መዳፍ ውስጥ እንዳንወድቅ ይጠብቀናል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው ለኖሩ ወንድሞቻችን ብዙ ጊዜ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። በ1930ዎቹ ዓመታትና በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ የናዚ አገዛዝ በጀርመንና በሌሎች አገሮች ሰፍኖ በነበረበት ወቅት ለሕዝቦቹ ጥበቃ አድርጓል። በስደት ወቅት አምላክ ለአገልጋዮቹ ያደረገውን ጥበቃ የሚያወሱ የሕይወት ታሪኮችንና በዓመት መጽሐፍ ላይ የሚወጡ ዘገባዎችን ማንበባችንና በዚያ ላይ ማሰላሰላችን ይሖዋ አስተማማኝ መጠጊያ እንደሚሆነን ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።—መዝ. 91:2
19 በተጨማሪም ይሖዋ በድርጅቱና በጽሑፎች አማካኝነት ፍቅራዊ ማሳሰቢያ በመስጠት ጥበቃ ያደርግልናል። በቅርብ ጊዜያት ከዚህ ምን ጥቅም እንዳገኘን ተመልከት። በዚህ ዓለም ላይ የሥነ ምግባር ብልግና እና የብልግና ምስሎች እንደ ወረርሽኝ እየተስፋፉ ሲሄዱ ይሖዋ እኛን ከሥነ ምግባር አደጋ ለመጠበቅ ወቅታዊ ማሳሰቢያና ጠቃሚ እርዳታ ሰጥቶናል። ለምሳሌ ያህል፣ በማኅበራዊ ድረ ገጽ አማካኝነት መጥፎ ጓደኝነት እንዳንመሠርት አባታዊ ምክር አግኝተናል። *—1 ቆሮ. 15:33
20. በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ምን ዓይነት ጥበቃና አመራር እናገኛለን?
20 ‘ከይሖዋ የተማርን’ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ትእዛዛቱን በጥብቅ በመከተል ነው። (ኢሳ. 54:13) በጉባኤ ውስጥ በሽምግልና የሚያገለግሉ ታማኝ ወንዶች ቅዱስ ጽሑፋዊ እርዳታና ምክር ይሰጡናል፤ በመሆኑም የሚያሰጋ ነገር በሌለበት በጉባኤያችን ውስጥ አስፈላጊውን መመሪያና ጥበቃ እናገኛለን። (ገላ. 6:1) ይሖዋ አብዛኛውን ጊዜ በእነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ አማካኝነት አሳቢነቱን ይገልጽልናል። (ኤፌ. 4:7, 8) ታዲያ ምላሻችን ምን መሆን ይኖርበታል? በፈቃደኝነት መገዛትና መታዘዝ የአምላክን በረከት ያስገኛል።—ዕብ. 13:17
21. (ሀ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል? (ለ) በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
21 የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ ደግሞም በሰማይ የሚኖረው አባታችን የሚሰጠንን መመሪያ እንከተል። በተጨማሪም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልንን ከሁሉ የላቀ አርዓያ መከተል እንችል ዘንድ በምድራዊ ሕይወቱ ላይ እናሰላስል። ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ በመሆኑ ብዙ በረከት አግኝቷል። (ፊልጵ. 2:5-11) እኛም እንደ እሱ በሙሉ ልባችን በይሖዋ በመታመናችን በረከት እናገኛለን። (ምሳሌ 3:5, 6) እንግዲያው የሚያስፈልገንን ሁሉ በመስጠትና ጥበቃ በማድረግ ረገድ ተወዳዳሪ በማይገኝለት በይሖዋ ምንጊዜም እንታመን። እሱን ማገልገል እጅግ የሚያስደስት ከመሆኑም ሌላ ታላቅ መብት ነው! አምላክ ለእኛ ያለውን አሳቢነት የገለጸበት ሦስተኛው መንገድ ከእኛ ጋር ወዳጅነት መመሥረቱ ነው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰላሰላችን ለእሱ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ያደርጋል። ቀጣዩ ርዕስ ይሖዋ የቅርብ ወዳጃችን የሆነው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
^ አን.19 ለምሳሌ፣ በነሐሴ 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 3-5 ላይ “ኢንተርኔት—ዓለም አቀፉን የመረጃ መረብ በጥበብ መጠቀም” እና በነሐሴ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 20-29 ላይ “ከዲያብሎስ ወጥመዶች ተጠንቀቁ!” እንዲሁም “ጸንታችሁ በመቆም የሰይጣንን ወጥመዶች ተቋቋሙ!” በሚሉት ርዕሶች እንዲህ ያሉ ማሳሰቢያዎች ወጥተዋል።