በመካከላችሁ ያሉትን አረጋውያን አክብሯቸው
“ሽማግሌውን አክብር።”—ዘሌ. 19:32
1. የሰው ልጆች የሚገኙት በምን ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ነው?
ይሖዋ፣ የሰው ልጆች በእርጅና ምክንያት እንዲጎሳቆሉ ዓላማው አልነበረም። ከዚህ በተቃራኒ የሰው ልጆች ፍጹም ጤንነት ኖሯቸው በገነት ውስጥ እንዲኖሩ ይፈልጋል። ይሁንና በዛሬው ጊዜ “ፍጥረት ሁሉ . . . በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት” ላይ ይገኛል። (ሮም 8:22) አምላክ፣ ኃጢአት በሰው ልጆች ላይ ያመጣውን አስከፊ መዘዝ ሲመለከት ምን የሚሰማው ይመስልሃል? ሌላው የሚያሳዝን ነገር ደግሞ በርካታ አረጋውያን፣ ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ወቅት ችላ የሚባሉ መሆኑ ነው።—መዝ. 39:5፤ 2 ጢሞ. 3:3
2. ክርስቲያኖች ለአረጋውያን ልዩ አክብሮት የሚያሳዩት ለምንድን ነው?
2 የይሖዋ ሕዝቦች፣ በጉባኤያቸው ውስጥ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች በመኖራቸው ደስተኞች ናቸው። እነዚህ አረጋውያን ካካበቱት ተሞክሮ ጥቅም የምናገኝ ከመሆኑም ሌላ እምነታቸው ግሩም ምሳሌ ስለሚሆነን ይበልጥ እንድንሠራ ያነሳሳናል። አብዛኞቻችን በዕድሜ የገፉ ክርስቲያን ዘመዶች አሉን። በጉባኤያችን ያሉ አረጋውያን፣ የሥጋ ዘመዶቻችን ሆኑም አልሆኑ ደኅንነታቸው ያሳስበናል። (ገላ. 6:10፤ 1 ጴጥ. 1:22) በመሆኑም አምላክ ለአረጋውያን ያለውን አመለካከት መመርመራችን ሁላችንንም ይጠቅመናል። በተጨማሪም ተወዳጅ የሆኑትን እነዚህን አረጋውያን ክርስቲያኖች በመንከባከብ ረገድ ቤተሰባቸውም ሆነ ጉባኤው ስላለበት ኃላፊነት እንመለከታለን።
“አትጣለኝ”
3, 4. (ሀ) የመዝሙር 71 ጸሐፊ ለይሖዋ ምን ዓይነት ልመና አቅርቧል? (ለ) በዕድሜ የገፉ የጉባኤው አባላት ለአምላክ ምን ዓይነት ልመና ሊያቀርቡ ይችላሉ?
3 መዝሙር 71:9ን በመንፈስ መሪነት የጻፈው መዝሙራዊ “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ጕልበቴም ባለቀበት ጊዜ አትተወኝ” በማለት አምላክን ለምኗል። በመዝሙር 70 አናት ላይ “የዳዊት መዝሙር” የሚል መግለጫ ይገኛል፤ መዝሙር 71 ደግሞ ከዚህ የቀጠለ ይመስላል። ከዚህ አንጻር በመዝሙር 71:9 ላይ ያለውን ልመና ያቀረበው ዳዊት ሳይሆን አይቀርም። ዳዊት ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ እርጅና ዘመኑ ድረስ አምላክን አገልግሏል፤ ይሖዋም ታላላቅ ነገሮችን ለማከናወን ተጠቅሞበታል። (1 ሳሙ. 17:33-37, 50፤ 1 ነገ. 2:1-3, 10) ያም ቢሆን ዳዊት፣ ይሖዋ ምንጊዜም ሞገሱን እንዲያሳየው መለመን እንዳለበት ተሰምቶታል።—መዝሙር 71:17, 18ን አንብብ።
4 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ አረጋውያን እንደ ዳዊት ይሰማቸዋል። ዕድሜያቸው በመግፋቱ “የጭንቀት ጊዜ” ቢያጋጥማቸውም አቅማቸው በሚፈቅደው መጠን አምላክን ማወደሳቸውን ቀጥለዋል። (መክ. 12:1-7) ብዙዎቹ፣ አገልግሎታቸውን ጨምሮ የተለያዩ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን እንደ ቀድሞው ማከናወን አይችሉ ይሆናል። እነዚህ ክርስቲያኖችም እንደ ዳዊት፣ ይሖዋ ምንጊዜም ሞገሱን እንዲያሳያቸውና እንዲንከባከባቸው ሊለምኑ ይችላሉ። ታማኝ የሆኑት እነዚህ አረጋውያን አምላክ ጸሎታቸውን እንደሚሰማቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። ዳዊት ያሳሰበው ነገር ተገቢ በመሆኑ አምላክ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እንዲያሰፍረው በመንፈሱ መርቶታል፤ እነዚህ አረጋውያን የሚያቀርቡት ልመናም ተመሳሳይ ነው።
5. ይሖዋ፣ በዕድሜ የገፉ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዴት ይመለከታቸዋል?
5 ይሖዋ፣ በዕድሜ የገፉ ታማኝ አገልጋዮቹን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸውና ሌሎች አምላኪዎቹም እንዲያከብሯቸው እንደሚፈልግ ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ይናገራሉ። (መዝ. 22:24-26፤ ምሳሌ 16:31፤ 20:29) ዘሌዋውያን 19:32 “ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ይላል። ይህ ሐሳብ በተጻፈበት ጊዜም ሆነ ዛሬ በአምላክ ጉባኤ ውስጥ ያሉትን አረጋውያን ማክበር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው። ይሁንና አረጋውያንን ስለ መንከባከብስ ምን ማለት ይቻላል? ይህን ማድረግ የማን ኃላፊነት ነው?
ቤተሰብ ያለበት ኃላፊነት
6. ወላጆችን በመንከባከብ ረገድ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?
6 የአምላክ ቃል “አባትህንና እናትህን አክብር” ይላል። (ዘፀ. 20:12፤ ኤፌ. 6:2) ኢየሱስ፣ ለወላጆቻቸው አስፈላጊውን ነገር ለማቅረብ ፈቃደኛ ያልነበሩትን ፈሪሳውያንና ጸሐፍት በመውቀስ ይህ ትእዛዝ ከፍ ተደርጎ ሊታይ እንደሚገባ አሳይቷል። (ማር. 7:5, 10-13) በዚህ ረገድ ኢየሱስ ራሱ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ለምሳሌ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት በተቃረበበት ወቅት፣ ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ለዮሐንስ እናቱን ማርያምን እንዲንከባከባት አደራ ሰጥቶታል፤ በጊዜው ማርያም መበለት የነበረች ይመስላል።—ዮሐ. 19:26, 27
7. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ወላጆችን መንከባከብን አስመልክቶ ምን መመሪያ ሰጥቷል? (ለ) ጳውሎስ የጻፈው ሐሳብ ዐውድ ምንድን ነው?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልገውን ነገር የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8, 16ን አንብብ።) እስቲ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈውን የዚህን ሐሳብ ዐውድ እንመልከት። ጳውሎስ፣ ጉባኤው በገንዘብ መርዳት የሚገባው እነማንን እንደሆነና እነማንን መርዳት እንደማያስፈልገው እያብራራ ነበር። በዕድሜ የገፉ መበለቶችን የመንከባከቡ ኃላፊነት በዋነኝነት የሚወድቀው አማኝ በሆኑ ልጆቻቸው፣ የልጅ ልጆቻቸውና ሌሎች ዘመዶቻቸው ላይ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። እንዲህ ካደረጉ ጉባኤው አስፈላጊ ላልሆነ ወጪ አይዳረግም። በዛሬው ጊዜም ቢሆን ክርስቲያኖች “ለአምላክ የማደርን ባሕርይ” ማሳየት የሚችሉበት አንዱ መንገድ እርዳታ ለሚያሻቸው ዘመዶቻቸው አስፈላጊውን ቁሳዊ ነገር በማሟላት ነው።
8. በዕድሜ የገፉ ወላጆችን በመንከባከብ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር መመሪያ አለመስጠቱ ምን ያስገነዝበናል?
8 ነጥቡን በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል፣ ራሳቸውን ችለው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ለወላጆቻቸው የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር የማሟላት ግዴታ አለባቸው። ጳውሎስ የተናገረው አማኝ ስለሆኑ ዘመዶች ቢሆንም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ያልሆኑ ወላጆችም ችላ ሊባሉ አይገባም። እርግጥ ነው፣ ልጆች ወላጆቻቸውን የሚንከባከቡበት መንገድ ሊለያይ ይችላል። በዕድሜ የገፉት ወላጆች የሚያስፈልጋቸው ነገር፣ ሁኔታቸው እንዲሁም ጤንነታቸው ተመሳሳይ አይሆንም። አንዳንድ አረጋውያን ብዙ ልጆች ሲኖሯቸው ሌሎች ግን አንድ ልጅ ብቻ ሊኖራቸው ይችላል። የመንግሥት እርዳታ ማግኘት የሚችሉ አረጋውያን እንዳሉ ሁሉ ይህን ማግኘት የማይችሉም አሉ። የግል ምርጫዎቻቸውም ቢሆን ይለያያሉ። በመሆኑም አንዳንዶች በዕድሜ የገፉ ዘመዶቻቸውን የሚንከባከቡበትን መንገድ መተቸት ጥበብም ሆነ ፍቅር የሚንጸባረቅበት ነገር አይደለም። ደግሞም በሙሴ ዘመን እንደታየው በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ የሚደረግን ማንኛውንም ውሳኔ ይሖዋ ሊባርከውና ውጤታማ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል።—ዘኍ. 11:23
9-11. (ሀ) አንዳንዶች ምን አስቸጋሪ ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) ከወላጆቻቸው ርቀው የሚኖሩ ልጆች የሙሉ ጊዜ አገልግሎታቸውን ለመተው መቸኮል የሌለባቸው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
9 ወላጆችና ልጆች የሚኖሩበት አካባቢ የተራራቀ ከሆነ በዕድሜ ለገፉ ወላጆች የሚያስፈልገውን እርዳታ መስጠት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ወላጆች በመውደቃቸው፣ አጥንታቸው በመሰበሩ ወይም በሌላ ችግር ምክንያት ጤንነታቸው በድንገት ማሽቆልቆሉ ልጆቻቸው ካሰቡት ጊዜ ቀደም ብለው እናትና አባታቸውን ለመጠየቅ እንዲሄዱ ያስገድዳቸው ይሆናል። ከዚያ በኋላም ቢሆን ወላጆቻቸው ለተወሰነ ጊዜ ወይም በቋሚነት እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። *
10 በተለይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉና በዚህም የተነሳ ከቤተሰባቸው ርቀው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከዚህ ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ ሊከብዳቸው ይችላል። ቤቴላውያን፣ ሚስዮናውያን እንዲሁም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የተመደቡበትን የአገልግሎት መስክ እንደ ውድ መብት እንዲሁም ከይሖዋ እንዳገኙት በረከት ይቆጥሩታል። ያም ቢሆን ወላጆቻቸው ሲታመሙ መጀመሪያ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ሐሳብ ‘ወላጆቻችንን ለመንከባከብ ምድባችንን ትተን ወደ ቤት መመለስ ይኖርብናል’ የሚል ሊሆን ይችላል። ይሁንና ወላጆቻቸው የሚያስፈልጋቸው ወይም የሚፈልጉት ነገር ይህ መሆኑን ልጆች በጸሎት ማሰባቸው ጥበብ ነው። ማንም ቢሆን የአገልግሎት መብቱን ለመተው መጣደፍ አይኖርበትም፤ ልጆች፣ ምድባቸውን ትተው መመለሳቸው አስፈላጊ የሚሆነው ሁልጊዜ ላይሆን ይችላል። የወላጆች የጤና ችግር ጊዜያዊ ከሆነ በጉባኤያቸው ያሉ ወንድሞች ሊረዷቸው ይችሉ ይሆን?—ምሳሌ 21:5
11 ከቤተሰቦቻቸው ርቀው የሚያገለግሉ የሁለት ወንድማማቾችን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንደኛው በደቡብ አሜሪካ ሚስዮናዊ ሲሆን ሌላው ደግሞ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት ያገለግላል። የእነዚህ ወንድሞች አረጋዊ ወላጆች እርዳታ አስፈለጋቸው። ሁለቱም ወንድሞች ከሚስቶቻቸው ጋር በመሆን፣ ወላጆቻቸውን መርዳት የሚቻልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ እና ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለመወሰን ወላጆቻቸው ወዳሉበት ወደ ጃፓን ሄዱ። ከጊዜ በኋላ፣ በደቡብ አሜሪካ የሚያገለግለው ወንድምና ባለቤቱ ምድባቸውን ትተው ወደ ወላጆቻቸው ለመመለስ አሰቡ። በዚህ መሃል፣ ወላጆቻቸው ያሉበት ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ስልክ ደወለላቸው። ይህ ሽማግሌ፣ የጉባኤው ሽማግሌዎች ስለ ሁኔታው እንደተወያዩና ሚስዮናውያኑ ሁኔታዎች እስከፈቀዱላቸው ድረስ በተመደቡበት ቦታ ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚፈልጉ ነገራቸው። እነዚህ ሽማግሌዎች፣ የሚስዮናውያኑን አገልግሎት የሚያደንቁ ከመሆኑም ሌላ ወላጆቻቸውን በመንከባከብ ልጆቹን ለማገዝ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር። ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ፍቅር የተንጸባረቀበትን ይህን ዝግጅት ከልባቸው አድንቀዋል።
12. ክርስቲያን ቤተሰቦች፣ በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ከሚንከባከቡበት መንገድ ጋር በተያያዘ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
12 አንድ ክርስቲያን ቤተሰብ በዕድሜ የገፉ ወላጆችን ለመንከባከብ ያወጣው እቅድ ምንም ይሁን ምን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ እቅዱ ለአምላክ ስም ክብር የሚያመጣ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት የሃይማኖት መሪዎች መሆን እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (ማቴ. 15:3-6) የምናደርገው ውሳኔ አምላክንም ሆነ ጉባኤውን የሚያስከብር እንዲሆን እንፈልጋለን።—2 ቆሮ. 6:3
ጉባኤው ያለበት ኃላፊነት
13, 14. ከቅዱሳን መጻሕፍት አንጻር፣ ጉባኤዎች አረጋዊ ወንድሞችንና እህቶችን የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው የምንለው ለምንድን ነው?
13 ከላይ በተጠቀሰው መንገድ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ማገዝ የሚችሉት ሁሉም ክርስቲያኖች አይደሉም። ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከተከሰተ አንድ ሁኔታ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ጉባኤዎች ምሳሌ የሚሆኑ አረጋዊ ወንድሞችንና እህቶችን የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሩሳሌም ስለነበረው ጉባኤ ሲናገር “ከመካከላቸውም አንድም ችግረኛ አልነበረም” ይላል። ይህ የሆነው ሁሉም ባለጸጎች ስለነበሩ አይደለም። ከሁኔታዎች ማየት እንደሚቻለው አንዳንዶች ያላቸው ቁሳዊ ነገር በጣም ትንሽ ነበር፤ ያም ቢሆን “ለእያንዳንዱ ሰው በሚያስፈልገው መጠን ይከፋፈል ነበር።” (ሥራ 4:34, 35) በኋላ ላይ ግን አንድ ችግር ተፈጠረ። “በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማከፋፈል ሥራ” አንዳንድ መበለቶች ችላ ተብለው ነበር። በመሆኑም ሐዋርያት፣ ብቃት ያላቸው ወንድሞችን ሾሙ፤ እነዚህ ወንድሞች ደግሞ መበለቶቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በተሟላ ሁኔታ እና ከሌሎች እኩል እንዲያገኙ ዝግጅት አደረጉ። (ሥራ 6:1-5) እርግጥ ነው፣ በየዕለቱ ምግብ ማከፋፈሉ በ33 ዓ.ም. ክርስትናን ለተቀበሉትና መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ሲሉ ለተወሰነ ጊዜ በኢየሩሳሌም ለቆዩት ክርስቲያኖች ሲባል የተደረገ ጊዜያዊ ዝግጅት ነበር። ያም ቢሆን ሐዋርያት ጉዳዩን የያዙበት መንገድ ጉባኤው ችግር ላይ የወደቁ አባላቱን መደገፍ እንደሚችል የሚጠቁም ነው።
14 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ጳውሎስ ከጉባኤው ቁሳዊ እርዳታ ማግኘት የሚችሉት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ መበለቶች እንደሆኑ የሚገልጽ መመሪያ ለጢሞቴዎስ ሰጥቶት ነበር። (1 ጢሞ. 5:3-16) በመንፈስ መሪነት መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች አንዱ የሆነው ያዕቆብም በተመሳሳይ ክርስቲያኖች ወላጅ የሌላቸውን ልጆች፣ መበለቶችንና በሌላ መከራ ውስጥ ያሉ ወይም የተቸገሩ ወንድሞቻቸውን የመርዳት ግዴታ እንዳለባቸው ገልጿል። (ያዕ. 1:27፤ 2:15-17) ሐዋርያው ዮሐንስ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ለኑሮ የሚያስፈልጉ ቁሳዊ ነገሮች ያሉት ሰው ወንድሙ ሲቸገር ተመልክቶ ሳይራራለት ቢቀር የአምላክ ፍቅር በእሱ ውስጥ እንዴት ሊኖር ይችላል?” (1 ዮሐ. 3:17) እያንዳንዱ ክርስቲያን የተቸገሩትን በመርዳት ረገድ እንዲህ ያለ ኃላፊነት ካለበት ጉባኤዎችስ እንዲህ ማድረግ የለባቸውም?
15. በዕድሜ የገፉ ወንድሞችንና እህቶችን ከመንከባከብ ጋር በተያያዘ ግምት ውስጥ መግባት የሚያስፈልጋቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
15 በአንዳንድ አገሮች መንግሥት የጡረታ አበል በመስጠት፣ በተለያዩ መንገዶች ድጎማ በማድረግ አልፎ ተርፎም ቤታቸው ሄደው የሚንከባከቧቸው ሰዎች በማዘጋጀት በዕድሜ ለገፉ ዜጎቹ ድጋፍ ያደርጋል። (ሮም 13:6) በአንዳንድ ቦታዎች ግን እንዲህ ዓይነት ዝግጅት የለም። በመሆኑም የአረጋውያኑ ዘመዶች እንዲሁም ጉባኤው መስጠት የሚገባቸው እርዳታ መጠን እንደ ሁኔታው ይለያያል። አማኝ የሆኑት ልጆች የሚኖሩት ከወላጆቻቸው ርቀው ከሆነ ይህ ወላጆቻቸውን ለመርዳት ማድረግ በሚችሉት ነገር ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ልጆቹ፣ ወላጆቻቸው ካሉበት ጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር በግልጽ በመነጋገር የሚመለከታቸው ሁሉ የቤተሰቡን ሁኔታ እንዲያውቁ ማድረጋቸው ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በዕድሜ የገፉት ወላጆች ከመንግሥት ወይም ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማግኘት ስለሚችሏቸው ጥቅሞች እንዲያውቁና ከዚህም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሽማግሌዎቹ ሊረዷቸው ይችሉ ይሆናል። በተጨማሪም ሽማግሌዎች በቤት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሁኔታዎችን ለምሳሌ ያልተከፈሉ ወጪዎች እንዳሉ ወይም አረጋውያኑ መድኃኒት በአግባቡ እንደማይወስዱ ከተመለከቱ ጉዳዩን ርቀው ለሚኖሩት ልጆቻቸው ሊያሳውቁ ይችላሉ። እንዲህ ያለ በአሳቢነትና በደግነት የሚደረግ የሐሳብ ልውውጥ መኖሩ ሁኔታዎች እንዳይባባሱ ለመከላከልና ጥሩ መፍትሔዎችን ለማግኘት ሊረዳ ይችላል። በዚህ መንገድ አረጋውያኑን ባሉበት አካባቢ ሆኖ በመርዳትና በማማከር ለልጆቹ እንደ “ዓይን” ሆኖ የሚያገለግል ሰው መኖሩ የቤተሰቡን ጭንቀት እንደሚቀንስ ግልጽ ነው።
16. አንዳንድ ክርስቲያኖች በዕድሜ የገፉ የጉባኤ አባላትን የሚረዱት እንዴት ነው?
16 አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ በዕድሜ ለገፉ ወዳጆቻቸው ባላቸው ፍቅር በመነሳሳት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን መሥዋዕት አድርገው አቅማቸው የፈቀደውን ያህል አረጋውያኑን ለመንከባከብ ጥረት ያደርጋሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች በዕድሜ ለገፉ የጉባኤው አባላት ይበልጥ ትኩረት ለመስጠት የተቻላቸውን ያደርጋሉ። አንዳንዶች ከሌሎች የጉባኤው አባላት ጋር ተራ በመግባትና ሥራውን በመከፋፈል በዕድሜ የገፉትን ለመንከባከብ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀርባሉ። እነሱ ራሳቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሳተፍ ሁኔታቸው ባይፈቅድላቸውም በዚህ አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩትን የአረጋውያኑን ልጆች ሁኔታዎች እስከፈቀዱ ድረስ በተመደቡበት ቦታ ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ በደስታ ይረዷቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች የሚያሳዩት መንፈስ በጣም የሚደነቅ ነው! እርግጥ ነው፣ የጉባኤው አባላት እንዲህ ዓይነት ደግነት ቢያሳዩም የአረጋውያኑ ልጆች ወላጆቻቸውን ለመርዳት አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው።
አረጋውያንን በማበረታታት እንደምታከብሯቸው አሳዩ
17, 18. በዕድሜ የገፉትን በመንከባከብ ረገድ አመለካከት ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?
17 አረጋውያንን የሚንከባከቡ ሁሉ በተቻለ መጠን አስደሳች ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ መጣር ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ ዓይነት ኃላፊነት ካለህ አዎንታዊ አመለካከት ይዘህ ለመቀጠል ጥረት አድርግ። አንዳንድ ጊዜ አረጋውያን ሊከፋቸው አልፎ ተርፎም በመንፈስ ጭንቀት ሊዋጡ ይችላሉ። በመሆኑም ከአረጋውያን ወንድሞችና እህቶች ጋር የሚያንጹ ጭውውቶችን በማድረግ እነሱን ለማክበርና ለማበረታታት ልዩ ጥረት ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። ይሖዋን በማገልገል ላሳለፏቸው ዓመታት ሊመሰገኑ ይገባል። ይሖዋ፣ እሱን ለማገልገል ያደረጉትን ጥረት አይረሳም፤ የእምነት ባልንጀሮቻቸውም ይህን ሊረሱ አይገባም።—ሚልክያስ 3:16ን እና ዕብራውያን 6:10ን አንብብ።
18 በተጨማሪም አረጋውያኑም ሆኑ የሚንከባከቧቸው ሰዎች አልፎ አልፎ ለመቀለድ ወይም ጨዋታ ለመፍጠር መሞከራቸው በየዕለቱ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቋቁመው ማለፍ ቀላል እንዲሆንላቸው አስተዋጽኦ ያደርጋል። (መክ. 3:1, 4) በርካታ አረጋውያን፣ ብዙ ነገር እንዲደረግላቸው ላለመጠየቅ ይሞክራሉ። የእነሱ ባሕርይ ሌሎች በሚሰጧቸው ትኩረትና በሚያደርጉላቸው እንክብካቤ ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ይገነዘባሉ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉ አረጋውያንን ለማበረታታት የሄዱ ሰዎች፣ እነሱ ራሳቸው ተበረታትተው እንደተመለሱ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው።—ምሳሌ 15:13፤ 17:22
19. ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን አመለካከት ሊይዙ ይችላሉ?
19 ሥቃይና አለፍጽምና የሚያስከትሏቸው ችግሮች የሚወገዱበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን። እስከዚያው ድረስ ግን የአምላክ አገልጋዮች፣ ዘላለማዊ በሆነው ተስፋ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። አምላክ በሰጠን ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት በጭንቀት ወይም በመከራ ጊዜ እንዳንናወጥ እንደ መልሕቅ ሊሆነን እንደሚችል እናውቃለን። እንዲህ ዓይነት እምነት ስላለን “ምንም እንኳ ውጫዊው ሰውነታችን እየተመናመነ ቢሄድም ውስጣዊው ሰውነታችን ግን ከቀን ወደ ቀን እየታደሰ እንደሚሄድ” እርግጠኞች ነን። (2 ቆሮ. 4:16-18፤ ዕብ. 6:18, 19) ያም ቢሆን ሌሎችን በመንከባከብ ረገድ ያለባችሁን ኃላፊነት ለመወጣት አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት ከመገንባት በተጨማሪ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንመለከታለን።
^ አን.9 በዕድሜ የገፉ ወላጆችን ለመንከባከብ የሚያስችሉ አንዳንድ አማራጮች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ተብራርተዋል።