በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአገልግሎታችሁ ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ አድርጉ

በአገልግሎታችሁ ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ አድርጉ

“ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል።”—ማቴ. 7:12

1. በአገልግሎት ላይ ሰዎችን የምንይዝበት መንገድ ለውጥ ያመጣል? ምሳሌ ስጥ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ በፊጂ የሚኖሩ አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ እየጋበዙ ነበር። አንዲትን ሴት ደጅ ላይ ሆነው እያነጋገሯት እያለ ዝናብ መዝነብ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ወንድም ለሴትየዋ ጃንጥላ ሰጣትና እሱ ከሚስቱ ጋር በአንድ ጃንጥላ ተጠለለ። እነዚህ ባልና ሚስት፣ በመታሰቢያው በዓል ላይ ይህችን ሴት ሲያይዋት በጣም ተደሰቱ። ሴትየዋ፣ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ባነጋገሯት ወቅት ምን እንዳሏት ያን ያህል ባታስታውስም ባደረጉላት ነገር ልቧ ስለተነካ ወደ መታሰቢያው በዓል እንደመጣች ተናግራለች። እንዲህ ዓይነት ጥሩ ውጤት እንዲገኝ አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው? ባልና ሚስቱ፣ ብዙውን ጊዜ ወርቃማው ሕግ በመባል የሚታወቀውን መመሪያ መከተላቸው ነው።

2. ወርቃማው ሕግ የሚባለው ምንድን ነው? ይህን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

2 ወርቃማው ሕግ የሚባለው ምንድን ነው? ኢየሱስ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል” በማለት የሰጠው ምክር ነው። (ማቴ. 7:12) ይህን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ ሁለት እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልገናል። በመጀመሪያ፣ ‘እኔ በዚህ ሰው ቦታ ብሆን ኖሮ ምን እንዲደረግልኝ እፈልግ ነበር?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ከዚያም ሰውየው የሚፈልገውን ነገር ለማሟላት የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረግ ይገባናል።—1 ቆሮ. 10:24

3, 4. (ሀ) ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ያለብን ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ብቻ አይደለም የምንለው ለምን እንደሆነ አብራራ። (ለ) በዚህ ርዕስ በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ እንወያያለን?

 3 ብዙውን ጊዜ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ እናደርጋለን። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ያለ አሳቢነት ማሳየት ያለብን ለእምነት ባልንጀሮቻችን ብቻ እንደሆነ አልተናገረም። እንዲያውም ስለ ወርቃማው ሕግ የጠቀሰው ሁሉንም ሰው ሌላው ቀርቶ ጠላቶቻችንን እንኳ እንዴት መያዝ እንዳለብን በተናገረበት ወቅት ነው። (ሉቃስ 6:27, 28, 31, 35ን አንብብ።) ከጠላቶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ካለብን ምሥራቹን ከምንመሠክርላቸው ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነትማ ይህን አብልጠን ልናደርገው እንደሚገባ ጥያቄ የለውም፤ ምክንያቱም ከእነዚህ ሰዎች ብዙዎቹ “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሊሆኑ ይችላሉ።—ሥራ 13:48

4 በአገልግሎት ስንካፈል በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡ አራት ጥያቄዎችን ከዚህ ቀጥሎ እንወያያለን፤ እነሱም፦ የማነጋግረው ሰው ማን ነው? ሰዎችን የማነጋግረው የት ነው? እነሱን ለማግኘት የተሻለው ጊዜ መቼ ነው? ላነጋግራቸው የሚገባው እንዴት ነው? የሚሉት ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ እንደምንመለከተው እነዚህ ጥያቄዎች፣ የምናነጋግራቸውን ሰዎች ስሜት ከግምት እንድናስገባ እንዲሁም ከእነሱ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ አቀራረባችንን ማስተካከል እንድንችል ይረዱናል።—1 ቆሮ. 9:19-23

የማነጋግረው ሰው ማን ነው?

5. ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

5 በአገልግሎታችን ላይ ብዙውን ጊዜ የምናነጋግረው የተለያየ ማንነት ያላቸውን ሰዎች ነው። የእያንዳንዱ ሰው አስተዳደግና ያሉበት ችግሮች ይለያያሉ። (2 ዜና 6:29) ምሥራቹን ለአንድ ሰው በምትናገርበት ጊዜ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ምሥራቹን የሚነግረኝ እሱ ቢሆን ኖሮ ይህ ሰው ለእኔ ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረው እፈልግ ነበር? ማንነቴን ሳያውቅ ስለ እኔ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ቢደርስ ደስ ይለኛል? ወይስ እኔን በግለሰብ ደረጃ ለማወቅ ጥረት እንዲያደርግ እፈልጋለሁ?’ እንደ እነዚህ ባሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላችን፣ የምናነጋግረውን ግለሰብ የራሱ ማንነት ያለው ሰው እንደሆነ አድርገን እንድንመለከተው ይረዳናል።

6, 7. በአገልግሎት ላይ ያገኘነው አንድ ሰው ቢቆጣን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

6 ማናችንም ብንሆን “ሥርዓት የሌለው ሰው” ተብለን እንድንፈረጅ አንፈልግም። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን “ንግግራችሁ ምንጊዜም ለዛ ያለው . . . ይሁን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የምንችለውን ያህል እንጥራለን። (ቆላ. 4:6) ይሁን እንጂ ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት፣ በኋላ ላይ የምንቆጭበትን ነገር የምንናገርባቸው ጊዜያት አሉ። (ያዕ. 3:2) በቀኑ ውስጥ ባጋጠመን መጥፎ ነገር በመበሳጨታችን አንድን ሰው ደግነት የጎደለው ነገር ብንናገረውና በዚህ የተነሳ ግለሰቡ “ሥርዓት የሌለን” ወይም “አሳቢነት የጎደለን” እንደሆንን አድርጎ ቢቆጥረን ደስ እንደማይለን የታወቀ ነው። ግለሰቡ ያለንበትን ሁኔታ እንዲረዳልን እንፈልጋለን። ታዲያ እኛስ ለሌሎች እንዲህ ማድረግ አይገባንም?

7 በአገልግሎት ላይ ያገኘነው አንድ ሰው ቢቆጣን እንዲህ ያደረገበት ሌላ ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ማሰቡ የተሻለ አይሆንም? ምናልባት በሥራ ቦታው ወይም በትምህርት ቤት ውጥረት በዝቶበት ይሆን? አሊያም ካለበት ከባድ የጤና ችግር ጋር እየታገለ ይሆን? አብዛኛውን ጊዜ፣ መጀመሪያ ላይ ተበሳጭተው የነበሩ ሰዎች የይሖዋ ሕዝቦች በገርነትና በአክብሮት ካነጋገሯቸው በኋላ ጥሩ ምላሽ እንደሰጡ ተስተውሏል።—ምሳሌ 15:1፤ 1 ጴጥ. 3:15

8. የመንግሥቱን መልእክት “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ከመስበክ ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?

8 በአገልግሎታችን ላይ የተለያየ ዓይነት ሕይወት ያላቸውን ሰዎች እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጠበቂያ ግንብ ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚለው ዓምድ ሥር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ60 በላይ ተሞክሮዎች ወጥተዋል። በእነዚህ ርዕሶች ላይ ተሞክሯቸውን ከተናገሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ሌቦች፣ ሰካራሞች፣ ወሮበሎች ወይም የዕፅ ሱሰኞች ነበሩ። ሌሎቹ ደግሞ የፖለቲካ ሰዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች አሊያም ለሙያቸው ትልቅ ትኩረት የሚሰጡ ነበሩ። አንዳንዶቹ በሥነ ምግባር የተበላሸ ሕይወት ይመሩ የነበሩ ናቸው። ያም ሆኖ ሁሉም ምሥራቹን ሰምተው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኞች ሆነዋል፤ እንዲሁም በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ በማድረግ ወደ እውነት መምጣት ችለዋል። እንግዲያው አንዳንድ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ሊቀበሉ እንደማይችሉ አድርገን ፈጽሞ  ማሰብ የለብንም። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብብ።) ከዚህ ይልቅ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” ምሥራቹን ሊቀበሉ እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 9:22

ሰዎችን የማነጋግረው የት ነው?

9. ለሌሎች ሰዎች ቤት አክብሮት እንዳለን ማሳየት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

9 በአገልግሎታችን ላይ ሰዎችን የምናነጋግራቸው የት ነው? ብዙውን ጊዜ የምናነጋግራቸው ቤታቸው ሄደን ነው። (ማቴ. 10:11-13) ሰዎች ለቤታችንም ሆነ ለንብረታችን አክብሮት ሲያሳዩ ደስ ይለናል። ምክንያቱም ቤታችን ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ነገር ነው። ቤታችን ገመናችንን የሚሸፍንልንና ከስጋት ነፃ መሆን የምንችልበት ቦታ እንዲሆን እንፈልጋለን። ሌሎች ሰዎችም ቢሆን ቤታቸው እንዲከበርላቸው እንደሚፈልጉ ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ለሰዎች ቤታቸውን እንደምናከብርላቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ልናስብበት ይገባል።—ሥራ 5:42

10. በአገልግሎታችን ላይ ሌሎችን የሚያስቆጣ ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

10 በዚህ በዓመፅ በተሞላ ዓለም ውስጥ ብዙዎች፣ የማያውቁት ሰው ቤታቸው ሲመጣ ግለሰቡን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከቱታል። (2 ጢሞ. 3:1-5) በመሆኑም ሰዎች ይበልጥ እንዲጠራጠሩ መንገድ የሚከፍት ነገር እንዳናደርግ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ አንድ ቤት ሄደን በሩን እያንኳኳን ነው እንበል። በሩ ካልተከፈተልን በመስኮት በኩል ለማየት ወይም የቤቱን ባለቤት ለማግኘት ስንል በጀርባ በኩል ለመዞር እንፈተን ይሆናል፤ አሊያም በሩ ክፍት ከሆነ ዝም ብለን እንገባ ይሆናል። በአካባቢያችሁ እንዲህ ብታደርጉ የቤቱ ባለቤቶች ይበሳጫሉ? ጎረቤቶችስ እንዲህ ስታደርጉ ቢያዩዋችሁ ምን ይላሉ? እርግጥ ነው፣ በስብከቱ ሥራችን ላይ ለሁሉም ሰው የተሟላ ምሥክርነት መስጠት ይኖርብናል። (ሥራ 10:42) የያዝነውን መልካም መልእክት ለሰዎች ለመንገር እንጓጓለን፤ ይህንንም የምናደርገው በቅን ልቦና ተነሳስተን ነው። (ሮም 1:14, 15) ያም ቢሆን በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሳያስፈልግ የሚያስቆጣ ምንም ነገር ላለማድረግ መጠንቀቃችን የጥበብ አካሄድ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “አገልግሎታችን እንከን እንዳይገኝበት በምንም መንገድ ማሰናከያ የሚሆን ነገር እንዲኖር አናደርግም” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮ. 6:3) በክልላችን ውስጥ ላሉት ሰዎች ቤትም ሆነ ንብረት አክብሮት የምናሳይ ከሆነ አንዳንድ ሰዎች በመልካም ምግባራችን ተማርከው ወደ እውነት ሊመጡ ይችላሉ።—1 ጴጥሮስ 2:12ን አንብብ።

ምንጊዜም ለሰዎች ቤትም ሆነ ንብረት አክብሮት እንዳለን እናሳይ (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

ሰዎችን ለማግኘት የተሻለው ጊዜ መቼ ነው?

11. ሰዎች ጊዜያችን ውድ መሆኑን እንደተገነዘቡ ሲያሳዩን ደስ የሚለን ለምንድን ነው?

11 አብዛኞቻችን በሕይወታችን ውስጥ ብዙ የምናከናውናቸው ነገሮች አሉ። በመሆኑም ኃላፊነቶቻችንን ለመወጣት እንድንችል ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ከለየን በኋላ ጊዜያችንን እንዴት እንደምንጠቀምበት ፕሮግራም እናወጣለን። (ኤፌ. 5:16፤ ፊልጵ. 1:10) ፕሮግራማችንን የሚያስተጓጉል ነገር ሲያጋጥመን እንበሳጭ ይሆናል። ከዚህ አንጻር ሌሎች፣ ጊዜያችን ውድ መሆኑን እንደተገነዘቡ ሲያሳዩን እንዲሁም እንድንሰጣቸው በሚፈልጉት ጊዜ ረገድ ምክንያታዊ ሲሆኑ ደስ ይለናል። ታዲያ እኛስ ወርቃማውን ሕግ በአእምሯችን በመያዝ ከጊዜ ጋር በተያያዘ፣ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ተመሳሳይ አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

12. በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎችን ቤታቸው ሄደን ለማነጋገር የተሻለው ጊዜ መቼ እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

12 ሰዎችን ቤታቸው ሄደን ለማነጋገር የተሻለው ጊዜ መቼ እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በክልላችን ውስጥ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ቤታቸው የሚገኙት መቼ ነው? መልእክቱን ለመስማት ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ የሚችሉትስ ምን ጊዜ ነው? ከሰዎች ፕሮግራም አንጻር ቤታቸው የምንሄድበትን ሰዓት ማስተካከላችን ተገቢ ይሆናል። በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዓት በኋላ ወይም አመሻሹ ላይ ከቤት ወደ ቤት መሄድን ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። በእናንተ አካባቢም ሰዎች የሚገኙበት ጊዜ ይሄ ከሆነ ቢያንስ የተወሰኑ ቀናት በዚህ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ለማገልገል ፕሮግራማችሁን ማመቻቸት ትችሉ ይሆን? (1 ቆሮንቶስ 10:24ን አንብብ።) በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎች በሚመቻቸው ሰዓት ለመስበክ ስንል ማንኛውንም መሥዋዕት መክፈላችን የይሖዋን በረከት እንደሚያስገኝልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

13. ለምናነጋግረው ሰው አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

 13 ለምናነጋግረው ሰው አክብሮት ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? ምሥራቹን የሚቀበል ሰው ስናገኝ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት ያለብን ቢሆንም ከሚገባው በላይ መቆየት ተገቢ አይሆንም። ግለሰቡ በዚያ ጊዜ ሊያከናውነው ያሰበው ሌላ ሥራ ይኖረው ይሆናል። የቤቱ ባለቤት ጊዜ እንደሌለው ከገለጸልን መልእክታችንን አጭር እንደምናደርግ ልንነግረው እንችላለን፤ እንዲህ ካልነው ቃላችንን ልንጠብቅ ይገባል። (ማቴ. 5:37) ውይይታችንን ስንደመድም መቼ ተመልሰን ብንመጣ እንደሚመቸው ግለሰቡን መጠየቁ ጥሩ ነው። አንዳንድ አስፋፊዎች እንደሚከተለው ማለቱን ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል፦ “እንደገና ብንገናኝ ደስ ይለኛል፤ ከመምጣቴ በፊት ስልክ ብደውል ወይም መልእክት ብልክ ይሻል ይሆን?” ፕሮግራማችንን በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እንደሚስማማ አድርገን ካስተካከልን ‘ብዙዎች እንዲድኑ ሲል የእነሱን እንጂ የራሱን ጥቅም እንደማይፈልግ’ የተናገረውን የጳውሎስን ምሳሌ እንከተላለን።—1 ቆሮ. 10:33

ላነጋግራቸው የሚገባው እንዴት ነው?

14-16. (ሀ) የመጣንበትን ምክንያት ለቤቱ ባለቤት በግልጽ መናገር ያለብን ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ። (ለ) አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ውጤታማ ሆኖ ያገኘው አቀራረብ የትኛው ነው?

14 አንድ ቀን የሆነ ሰው ስልክ ደወለልን እንበል፤ ሆኖም ሰውየው ማን እንደሆነ በድምፁ መለየት አልቻልንም። ደዋዩ ማንነቱን ሳይነግረን ስለምንወዳቸው የምግብ ዓይነቶች ይጠይቀናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ሰውየው ማን እንደሆነና ምን እንደሚፈልግ ማሰባችን አይቀርም። አክብሮት ለማሳየት ስንል ግለሰቡን ለተወሰነ ጊዜ ብናነጋግረውም ትንሽ ቆይተን ግን ውይይቱን ማቆም እንደምንፈልግ እንጠቁመው ይሆናል። በሌላ በኩል ግን የደወለው ሰው ማንነቱን ወዲያውኑ ከነገረን በኋላ ሙያው ከአመጋገብ ጋር የተያያዘ እንደሆነና አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን  ሊያካፍለን እንደሚፈልግ በአክብሮት ገለጸልን እንበል። እንዲህ ዓይነቱን ሰው ለማዳመጥ ይበልጥ ፈቃደኞች ልንሆን እንችላለን። ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር በቀጥታ ሆኖም አክብሮት በተሞላበት መንገድ ቢነግሩን ደስ ይለናል። ታዲያ እኛስ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች እንዲህ ያለ አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15 በብዙ ቦታዎች ሰዎች ወደ እነሱ የሄድንበትን ምክንያት በግልጽ እንድንነግራቸው ይፈልጋሉ። እርግጥ ነው፣ እኛ የያዝነው መልእክት ጠቃሚ ሲሆን ሰዎች ደግሞ ይህን መልእክት አያውቁትም፤ ሆኖም ራሳችንን በደንብ ሳናስተዋውቅ “በዓለም ላይ ያለ ማንኛውንም ችግር መፍታት ቢችሉ ኖሮ እርስዎ የትኛውን ችግር ያስወግዱ ነበር?” እንደሚለው ዓይነት ጥያቄ በማንሳት በድንገት ውይይቱን ብንጀምር የቤቱ ባለቤት ምን ይሰማዋል? እኛ ለግለሰቡ እንዲህ ያለ ጥያቄ የምናቀርብበት ዓላማ የሰውየውን አመለካከት ለመረዳትና ውይይቱን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ለመምራት እንደሆነ እናውቃለን። ይሁንና የቤቱ ባለቤት ‘ይሄ ደግሞ ማነው? እንዲህ ብሎ የሚጠይቀኝ ለምንድን ነው? እያወራ ያለው ስለምንድን ነው?’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ስለዚህ የቤቱ ባለቤት ተረጋግቶ እንዲያዳምጠን ለማድረግ መጣር አለብን። (ፊልጵ. 2:3, 4) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

16 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸውን አቀራረብ ውጤታማ ሆኖ አግኝቶታል። ከቤቱ ባለቤት ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? የተባለውን ትራክት እያሳየ እንዲህ ይለዋል፦ “ዛሬ በዚህ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይህንን ትራክት እየሰጠን ነው። ትራክቱ ብዙ ሰዎች የሚያነሷቸውን ስድስት ጥያቄዎች የሚያብራራ ነው። እርስዎም ይህን ትራክት መውሰድ ይችላሉ።” አብዛኞቹ ሰዎች ለምን እንደመጣን ሲያውቁ ዘና ማለት እንደሚጀምሩ ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ተናግሯል። ከዚህ በኋላ ውይይቱን መቀጠል ብዙውን ጊዜ ቀላል ይሆናል። ቀጥሎም ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ “እነዚህን ጥያቄዎች አስበውባቸው ያውቃሉ?” በማለት የቤቱን ባለቤት ይጠይቀዋል። የቤቱ ባለቤት ከጥያቄዎቹ አንዱን ከመረጠ ወንድም ትራክቱን ገልጦ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚያ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ያወያየዋል። ግለሰቡ ዝም ካለ ደግሞ ወንድም ሰውየው እንዳይሸማቀቅ እሱ ራሱ አንዱን ጥያቄ ይመርጥና ውይይቱን ይቀጥላል። እርግጥ ነው፣ ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉ በርካታ መንገዶች አሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች፣ የመጣንበትን ዓላማ ከመናገራችን በፊት ከባሕሉ አንጻር የሚጠበቁብን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ዋናው ነገር፣ በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች እንድናነጋግራቸው በሚፈልጉት መንገድ አቀራረባችንን ማስተካከላችን ነው።

በአገልግሎታችሁ ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረጋችሁን ቀጥሉ

17. በዚህ ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ወርቃማውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

17 እስካሁን እንደተመለከትነው ወርቃማውን ሕግ በአገልግሎታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? የምናነጋግረውን ሰው የራሱ ማንነት እንዳለው አድርገን መመልከት ይኖርብናል። ለሰዎች ቤትም ሆነ ንብረት አክብሮት ማሳየት ይገባናል። ሰዎች ቤታቸው በሚገኙበትና መልእክቱን ለመስማት ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ በሚችሉበት ጊዜ ለማገልገል ጥረት እናደርጋለን። እንዲሁም በክልላችን ካሉ ሰዎች ጋር ውይይት ስንጀምር መልእክቱን ሊቀበሉ በሚችሉበት መንገድ ለማቅረብ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።

18. ሌሎች ለእኛ እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር በክልላችን ላሉ ሰዎች ማድረጋችን ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

18 ሌሎች ለእኛ እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር በክልላችን ላሉ ሰዎች ማድረጋችን ብዙ ጥቅሞች ያስገኛል። ሰዎችን በደግነትና በአክብሮት ስንይዝ ብርሃናችን በሰው ፊት እንዲበራ ማድረግ፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን መከተል ያለውን ጥቅም በግልጽ ማሳየት እንዲሁም ለሰማያዊው አባታችን ክብር ማምጣት እንችላለን። (ማቴ. 5:16) ሰዎችን የምናነጋግርበት መንገድ ብዙዎች ወደ እውነት እንዲመጡ ሊያደርግ ይችላል። (1 ጢሞ. 4:16) የመንግሥቱን መልእክት የምንሰብክላቸው ሰዎች መልእክቱን ተቀበሉም አልተቀበሉ አገልግሎታችንን ለመፈጸም የምንችለውን ያህል እንዳደረግን ስለምናውቅ እርካታ እናገኛለን። (2 ጢሞ. 4:5) እንግዲያው ሁላችንም “ምሥራቹን ከሌሎች ጋር እካፈል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ” በማለት የጻፈውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንከተል። (1 ቆሮ. 9:23) ይህንንም ለመፈጸም በአገልግሎታችን ላይ ወርቃማውን ሕግ ምንጊዜም ተግባራዊ እናድርግ።