በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሕይወት ታሪክ

የይሖዋ እርዳታ ፈጽሞ አልተለየኝም

የይሖዋ እርዳታ ፈጽሞ አልተለየኝም

እኔና ኤቭሊን ከተጋባን ገና ሁለት ሳምንታችን ቢሆንም ባቡር ተሳፍረን በደን በተሸፈነው በሰሜናዊ ኦንታሪዮ፣ ካናዳ ወደምትገኘው ወደ ሆርንፔን ከተማ ተጓዝን። ከባቡር የወረድነው ማለዳ ላይ ስለነበር በጣም ይበርዳል። የተቀበለን በአካባቢው የሚኖር አንድ ወንድም ሲሆን ወደ ቤቱ ወስዶ ጥሩ ቁርስ አበላን፤ አካባቢው በበረዶ የተሸፈነ ቢሆንም እንኳ ከእሱ፣ ከባለቤቱና ከልጁ ጋር በመሆን ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመርን። የወረዳ የበላይ ተመልካች ከሆንኩ በኋላ የመጀመሪያዬ የሆነውን የሕዝብ ንግግር የዚያኑ ዕለት ከሰዓት ላይ አቀረብኩ። በስብሰባው ላይ ከአምስታችን ውጪ የተገኘ ሌላ ሰው አልነበረም።

እውነቱን ለመናገር፣ በዚህ ወቅት ማለትም በ1957 ንግግር ሳቀርብ የነበሩት ተሰብሳቢዎች ጥቂት መሆናቸው አልከፋኝም፤ ምክንያቱም በተፈጥሮዬ በጣም ዓይናፋር ነኝ። እንዲያውም ትንሽ ልጅ እያለሁ፣ የማውቃቸው ሰዎች እንኳ ወደ ቤታችን ሲመጡ እደበቅ ነበር።

በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያገኘኋቸው አብዛኞቹ መብቶች ከማውቃቸውም ሆነ ከማላውቃቸው ብዙ ሰዎች ጋር መገናኘትን የሚጠይቁ መሆናቸውን ስታውቁ ልትገረሙ ትችላላችሁ። ዓይናፋርነትንና በራስ ያለመተማመን ስሜትን ለማሸነፍ አሁንም ድረስ ትግል አደርጋለሁ፤ በመሆኑም በተመደብኩበት ሥራ ያገኘሁት ማንኛውም ስኬት በራሴ ችሎታ እንደተገኘ አይሰማኝም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ “አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ” በማለት የሰጠው ተስፋ እውነት መሆኑን ተመልክቻለሁ። (ኢሳ. 41:10) ይሖዋ እኔን ከረዳባቸው መንገዶች ሁሉ የሚበልጠው የእምነት አጋሮቼ በሆኑት ክርስቲያኖች አማካኝነት የሰጠኝ ድጋፍ ነው። እስቲ ከልጅነቴ ጀምሮ ስላገኘሁት እርዳታ ልንገራችሁ።

መጽሐፍ ቅዱስና ትንሽ ጥቁር መጽሐፍ ተጠቅማ አስተማረችን

በደቡብ ምዕራብ ኦንታሪዮ በሚገኘው የቤተሰባችን እርሻ ላይ

በ1940 አንድ እሁድ ጠዋት ላይ ኤልሲ ሀንቲንግፎርድ የተባለች እህት በደቡብ ምዕራብ ኦንታሪዮ ወደሚገኘው የቤተሰባችን  እርሻ መጣች። በሩን የከፈተችላት እናቴ ነበረች፤ እንደ እኔ ዓይናፋር የነበረው አባቴ ከእኔ ጋር ውስጥ ሆኖ የሚባባሉትን ይሰማ ነበር። አባቴ፣ እህት ሀንቲንግፎርድ ዕቃ ሻጭ ስለመሰለችው እናቴ የማያስፈልገንን ነገር እንዳትገዛ በማሰብ ወደ በሩ ሄደና ምንም እንደማንፈልግ ተናገረ። እህት ሀንቲንግፎርድ “መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፍላጎት የላችሁም ማለት ነው?” በማለት ጠየቀችው። አባቴም “እሱንማ እንፈልጋለን” በማለት መለሰላት።

እህት ሀንቲንግፎርድ ወደ ቤታችን የመጣችው ጥሩ ጊዜ ላይ ነበር። ወላጆቼ ዩናይትድ ቸርች ኦቭ ካናዳ በተባለው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ ግን ይህን ቤተ ክርስቲያን ለመልቀቅ ወስነው ነበር። ለምን? ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ ገንዘብ የለገሱ ሰዎችን ስም ዝርዝር፣ በሰጡት መጠን በቅደም ተከተል ጽፎ በቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ በር ላይ ይለጥፍ ነበር። አነስተኛ ገቢ የነበራቸው ወላጆቼ አብዛኛውን ጊዜ ስማቸው የሚሰፍረው በስም ዝርዝሩ መጨረሻ አካባቢ በመሆኑ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲሰጡ የቤተ ክርስቲያኑ ሽማግሌዎች ጫና ያደርጉባቸው ነበር። አንድ ሌላ አገልጋይ ደግሞ ከሥራው እንዳይባረር በመስጋት የሚያምንባቸውን ነገሮች ለማስተማር እንደሚፈራ ተናግሯል። በዚህ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኑን ለቀን ወጣን፤ ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን የምናሟላበትን መንገድ እየፈለግን ነበር።

በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በካናዳ ታግዶ ስለነበር እህት ሀንቲንግፎርድ ቤተሰባችንን የምታስጠናው መጽሐፍ ቅዱስንና አንዳንድ ነገሮች የጻፈችበትን አንድ ትንሽ ጥቁር ማስታወሻ ደብተር በመጠቀም ነበር። በኋላም ለባለሥልጣናቱ አሳልፈን እንደማንሰጣት እርግጠኛ ስትሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አመጣችልን። እኛም እያንዳንዱን ጥናት ስንጨርስ ጽሑፎቹን እንዳይገኙ እንደብቃቸው ነበር። *

ወላጆቼ ከቤት ወደ ቤት ሲመሠከርላቸው ጥሩ ምላሽ በመስጠታቸው በ1948 ተጠመቁ

እህት ሀንቲንግፎርድ ተቃውሞና ሌሎች ችግሮች ቢያጋጥሟትም ምሥራቹን በቅንዓት ትሰብክ ነበር። ቅንዓቷ ያስደንቀኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከእውነት ጎን እንድቆም አነሳስቶኛል። ወላጆቼ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ከአንድ ዓመት በኋላ ራሴን ለአምላክ ወሰንኩ። ገበሬዎች ከብቶቻቸውን ውኃ በሚያጠጡበት የብረት ገንዳ ውስጥ የካቲት 27, 1949 ተጠመቅሁ። በወቅቱ የ17 ዓመት ልጅ ነበርኩ። በዚያ ወቅት ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ቆርጬ ነበር።

 ይሖዋ ደፋር እንድሆን ረድቶኛል

በ1952 በቤቴል እንዳገለግል ስጋበዝ በጣም ተደሰትኩ

ወዲያውኑ አቅኚ ለመሆን ፈርቼ ነበር። ራሴን ችዬ በአቅኚነት ለማገልገል ገንዘብ ያስፈልገኛል ብዬ ስላሰብኩ ባንክ ውስጥና አንድ ሌላ ቢሮ ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ምንም ተሞክሮ የሌለኝ ወጣት ስለነበርኩ የማገኘውን ገንዘብ ወዲያው አጠፋው ነበር። ስለዚህ ቴድ ሳርጀንት የሚባል አንድ ወንድም ደፋር እንድሆንና በይሖዋ ላይ እምነት እንዲኖረኝ አበረታታኝ። (1 ዜና 28:10) እንዲህ ያለ ጠቃሚ ማበረታቻ በማግኘቴ ኅዳር 1951 አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። በዚያ ጊዜ የነበረኝ ንብረት 40 ዶላር፣ አንድ ያገለገለ ብስክሌት እና አንድ አዲስ ቦርሳ ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን የሚያስፈልጉኝን ነገሮች አላሳጣኝም። ቴድ የአቅኚነት አገልግሎትን እንድጀምር ስላበረታታኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ! ምክንያቱም ብዙ በረከት አስገኝቶልኛል።

በ1952 ነሐሴ ወር መገባደጃ አንድ ምሽት ላይ ከቶሮንቶ ስልክ ተደወለልኝ። የካናዳ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ መስከረም ላይ ቤቴል ገብቼ እንዳገለግል ጋበዘኝ። ምንም እንኳ ዓይናፋርና ቅርንጫፍ ቢሮውን ጎብኝቼ የማላውቅ ብሆንም ወደ ቤቴል ስጠራ በጣም ደስ አለኝ፤ ምክንያቱም ስለ ቤቴል ግሩም ነገሮችን ከአቅኚዎች ሰምቼ ነበር። ደግሞም የቤቴልን ሕይወት ለመልመድ ጊዜ አልፈጀብኝም።

“ወንድሞችን እንደምታስብላቸው አሳያቸው”

ቤቴል ከደረስኩ ከሁለት ዓመት በኋላ በቶሮንቶ ባለው ሾ የተባለ ዩኒት ውስጥ ቢል ያኮስን ተክቼ የጉባኤ አገልጋይ (በአሁኑ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ይባላል) ሆኜ ተሾምኩ። * በዚህ ጊዜ ገና 23 ዓመቴ ነበር፤ ምንም የማያውቅ የገጠር ልጅ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ይሁን እንጂ ወንድም ያኮስ ማድረግ ያለብኝን በትሕትናና በፍቅር አሳየኝ። በእርግጥ ይሖዋም ረድቶኛል።

አጠር ደልደል ያለና ፈገግታ የማይለየው ወንድም ያኮስ ለሰዎች አሳቢ ነበር። ያኮስ ወንድሞችን ይወድድ ነበር፤ እነሱም ይወዱታል። ወንድሞችን ችግር ሲያጋጥማቸው ብቻ ሳይሆን ዘወትር ቤታቸው እየሄደ ይጠይቃቸዋል። ቢል ያኮስ እኔም እንዲሁ እንዳደርግና ከወንድሞችና እህቶች ጋር አብሬ እንዳገለግል ያበረታታኝ ነበር። እንዲህ ይለኝ ነበር፦ “ኬን፣ ወንድሞችን እንደምታስብላቸው አሳያቸው። እንዲህ ማድረግ በርካታ ጉድለቶችን ይሸፍናል።”

ባለቤቴ ጽኑ ፍቅር አሳይታለች

ከጥር 1957 ጀምሮ ደግሞ ይሖዋ ለየት ባለ መልኩ ረድቶኛል። በዚህ ወር፣ የጊልያድ ትምህርት ቤት የ14ኛው ክፍል ተመራቂ የሆነችውን ኤቭሊንን አገባሁ። ኤቭሊን ከመጋባታችን በፊት፣ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ባሉበት በኩዊቤክ ግዛት ታገለግል ነበር። በወቅቱ ኩዊቤክ በአብዛኛው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር ሥር ነበረች። በመሆኑም ኤቭሊን የተመደበችበት ቦታ አስቸጋሪ ነበር፤ ያም ቢሆን የተሰጣትን የሥራ ድርሻ በታማኝነት አከናውናለች፤ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር በታማኝነት ተጣብቃለች።

እኔና ኤቭሊን በ1957 ተጋባን

ኤቭሊን ከእኔም ጋር በታማኝነት ተጣብቃ ኖራለች። (ኤፌ. 5:31) እንዲያውም ታማኝነቷ የተፈተነው ከተጋባን ብዙም ሳይቆይ ነው! ከተጋባን በኋላ ወደ ፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለመሄድ አስበን ነበር፤ ሆኖም ቅርንጫፍ ቢሮው፣ በካናዳ ቤቴል ውስጥ አንድ ሳምንት በሚፈጅ ስብሰባ ላይ እንድካፈል በሠርጋችን ማግስት ጠየቀኝ። ይህ ስብሰባ ከፕሮግራማችን ጋር የሚጋጭ ቢሆንም እኔና ኤቭሊን ይሖዋ የጠየቀንን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበርን። በመሆኑም የጫጉላ ሽርሽራችንን ሰረዝን። በዚያ ሳምንት ኤቭሊን በቅርንጫፍ  ቢሮው አቅራቢያ መስክ ላይ ስታገለግል ቆየች። ክልሉ ከኩዊቤክ በጣም የተለየ ቢሆንም በጽናት አገልግላለች።

በዚያው ሳምንት መጨረሻ ላይ አንድ ፈጽሞ ያላሰብኩት ነገር አጋጠመኝ፤ በሰሜናዊ ኦንታሪዮ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተመደብኩ። በወቅቱ ገና ትዳር የመሠረትኩ የ25 ዓመት ወጣትና ተሞክሮ የሌለኝ ሰው ነበርኩ፤ ያም ቢሆን በይሖዋ በመተማመን ወደ ተሰጠን ምድብ ለመሄድ ዝግጁ ነበርን። በካናዳ በጣም ቀዝቃዛ በሆነው ወቅት፣ ወደተመደቡበት ቦታ እየተመለሱ ካሉ ተሞክሮ ያካበቱ በርካታ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጋር ሌሊት በሚጓዝ ባቡር ተሳፈርን። እነሱም በጣም አበረታትተውናል! እንዲያውም አንድ ወንድም ባቡሩ ውስጥ ለራሱ የያዘውን አልጋ እኛ እንድንተኛበት ለቀቀልን፤ ይህም ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብለን ከመጓዝ አድኖናል። በቀጣዩ ቀን ጠዋት፣ ማለትም ከተጋባን በ15 ቀናችን መግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት በሆርንፔን የሚገኘውን አነስተኛ ቡድን መጎብኘት ጀመርን።

እኔና ኤቭሊን ገና ብዙ ለውጦች ይጠብቁን ነበር። በ1960 በአውራጃ ሥራ ላይ እያለን ሳለን ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው በጊልያድ ትምህርት ቤት 36ኛው ክፍል ላይ እንድካፈል ተጋበዝኩ፤ ይህ አሥር ወር የሚፈጅ ሥልጠና የሚጀምረው በ1961 የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። እርግጥ ነው፣ ግብዣው በጣም ቢያስደስተኝም ኤቭሊንን የማይጨምር መሆኑ ደስታዬን ቀንሶብኛል። በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙት ሌሎች ሚስቶች ሁሉ ኤቭሊንም ቢያንስ ለአሥር ወራት ተለያይተን እንድንቆይ ፈቃደኛ መሆኗን የሚገልጽ ደብዳቤ እንድትጽፍ ተጠየቀች። ኤቭሊን በሁኔታው በጣም አዝና ብታለቅስም በትምህርት ቤቱ እንድካፈል ተስማማች፤ ደግሞም በጊልያድ ጠቃሚ ሥልጠና እንደማገኝ በማወቋ ተደስታ ነበር።

በሥልጠናው ወቅት ኤቭሊን በካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ ስታገለግል ቆየች። በዚያም ማርጋሬት ለቮል ከምትባል አንዲት ቅቡዕ እህት ጋር በአንድ ክፍል የመኖር ልዩ መብት አግኝታ ነበር። እርግጥ እኔና ኤቭሊን በጣም ተነፋፍቀን ነበር። ይሁንና በይሖዋ እርዳታ ለጊዜው በተመደብንበት ቦታ ጸንተን መቆየት ችለናል። ኤቭሊን ይሖዋና ድርጅቱ ይበልጥ እንዲጠቀሙብን ስትል አብረን ማሳለፍ የሚገባንን ጊዜ መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗ በጥልቅ ነክቶኛል።

በጊልያድ ሦስት ወር ገደማ ከቆየሁ በኋላ በዚያ ጊዜ ዓለም አቀፉን ሥራ እየመራ የነበረው ወንድም ናታን ኖር አንድ ያልተለመደ ግብዣ አቀረበልኝ። በጊልያድ የምከታተለውን ትምህርት አቋርጬ በካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ በሚካሄደው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ጊዜያዊ አስተማሪ ሆኜ ለማገልገል ወደ ካናዳ መመለስ እችል እንደሆነ ጠየቀኝ። ይሁንና ይህን ግብዣ የመቀበል ግዴታ እንደሌለብኝም ነገረኝ። ከፈለግኩ ደግሞ በጊልያድ ትምህርት ቤት የጀመርኩትን ትምህርት ጨርሼ በሚስዮናዊነት ልመደብ እንደምችል አስታወቀኝ። በተጨማሪም ወንድም ኖር ወደ ካናዳ ለመመለስ ከወሰንኩ በድጋሚ ወደ ጊልያድ ላልጋበዝ እንደምችል እንዲሁም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ካናዳ ውስጥ መስክ ላይ እንዳገለግል ልመደብ እንደምችል ገለጸልኝ። ከባለቤቴ ጋር ተመካክሬ ውሳኔ እንዳደርግም ነገረኝ።

ኤቭሊን ለቲኦክራሲያዊ ምድቦች ያላትን አመለካከት ከዚህ በፊት ነግራኝ ስለነበረ ወዲያውኑ ለወንድም ኖር “የይሖዋ ድርጅት አድርጉ የሚለንን ነገር ሁሉ ለማድረግ ደስተኞች ነን” ብዬ መለስኩለት። የእኛ ምርጫ ምንም ሆነ ምን፣  ምንጊዜም የይሖዋ ድርጅት ወደመደበን ቦታ ሁሉ መሄድ እንዳለብን ይሰማን ነበር።

በመሆኑም ሚያዝያ 1961 በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ለማስተማር ከብሩክሊን ወደ ካናዳ ተመለስኩ። በኋላም የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነን ማገልገል ጀመርን። ከዚያም በ1965 በሚካሄደው የጊልያድ ትምህርት ቤት 40ኛ ክፍል ላይ እንድካፈል ስጠራ በጣም ገረመኝ። ኤቭሊን ተለያይተን እንድንቆይ መስማማቷን የሚገልጽ ደብዳቤ አሁንም መጻፍ ነበረባት። ይሁን እንጂ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እሷም ከእኔ ጋር በትምህርት ቤቱ እንድትካፈል ግብዣ ሲቀርብላት በጣም ተደሰትን።

ጊልያድ ትምህርት ቤት ከደረስን በኋላ ወንድም ኖር ፈረንሳይኛ ቋንቋ የምንማር ተማሪዎች ወደ አፍሪካ ልንላክ እንደምንችል ነገረን። በምረቃው ፕሮግራም ላይ ግን በድጋሚ ካናዳ ውስጥ እንደተመደብን ተነገረን! እኔ የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች (አሁን የቅርንጫፍ ኮሚቴ አስተባባሪ ይባላል) ሆኜ ተሾምኩ። ገና 34 ዓመቴ ስለነበረ ለወንድም ኖር “ዕድሜዬ እኮ በጣም ገና ነው” አልኩት። እሱ ግን አበረታታኝ። ከመጀመሪያው አንስቶ ከባድ ውሳኔዎችን ከማድረጌ በፊት በዕድሜና በተሞክሮ የሚበልጡኝን በቤቴል ያሉ ወንድሞች ለማማከር ጥረት አደርግ ነበር።

ቤቴል—ለመማርም ሆነ ለማስተማር ምቹ የሆነ ቦታ

የቤቴል አገልግሎት ከሌሎች መማር የምችልበት ግሩም አጋጣሚዎችን ከፍቶልኛል። አብረውኝ የሚሠሩትን የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት አከብራቸዋለሁ እንዲሁም እጅግ አደንቃቸዋለሁ። በተጨማሪም በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥም ሆነ በተመደብንባቸው የተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ጥሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ተዋውቀናል፤ ወጣቶችም ይሁኑ አረጋውያን እነዚህ ክርስቲያኖች በጎ ተጽዕኖ አሳድረውብኛል።

በካናዳ ቤቴል የማለዳ አምልኮ ፕሮግራም ስመራ

የቤቴል አገልግሎት ሌሎችን እንዳስተምርና እምነታቸውን እንዳጠናክርም አስችሎኛል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “በተማርካቸው . . . ነገሮች ጸንተህ ቀጥል” በማለት ነግሮታል። በተጨማሪም እንዲህ ብሎታል፦ “ከእኔ የሰማኸውንና ብዙዎች የመሠከሩለትን ነገር፣ ታማኝ ለሆኑና እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር በሚገባ ብቁ ለሚሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ።” (2 ጢሞ. 2:2፤ 3:14) አንዳንድ ጊዜ፣ የእምነት ባልንጀሮቼ በቤቴል አገልግሎት ባሳለፍኳቸው 57 ዓመታት ውስጥ ምን ትምህርቶችን እንዳገኘሁ ይጠይቁኛል። እኔም “ይሖዋ እንደሚረዳን በመተማመን የይሖዋ ድርጅት አድርጉ የሚለንን ሁሉ ወዲያውኑ በፈቃደኝነት ማድረግን ተምሬያለሁ” የሚል ቀላል ምላሽ እሰጣቸዋለሁ።

ዓይናፋርና ተሞክሮ የሌለው ወጣት ሆኜ ወደ ቤቴል ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣሁበት ቀን ትናንት መስሎ ይታየኛል። ይሁንና በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ይሖዋ ‘ቀኝ እጄን ይዞ’ ሲመራኝ ቆይቷል። በተለይም የእምነት ባልንጀሮቼ በሚያሳዩኝ ደግነትና በሚያደርጉልኝ ወቅታዊ እገዛ አማካኝነት “አትፍራ፤ እረዳሃለሁ” እያለ ማበረታታቱን ቀጥሏል።—ኢሳ. 41:13

^ አን.10 የካናዳ መንግሥት በሥራችን ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ ግንቦት 22, 1945 አንስቷል።

^ አን.16 በዚያ ጊዜ በአንድ ከተማ ውስጥ ከአንድ በላይ ጉባኤዎች ካሉ እያንዳንዱ ጉባኤ ዩኒት ተብሎ ይጠራ ነበር።