በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እድገት ለማድረግ “የእግርህን ጐዳና አስተካክል”

እድገት ለማድረግ “የእግርህን ጐዳና አስተካክል”

የአምላክ ሕዝቦች በ537 ዓ.ዓ. ከባቢሎን በወጡ ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡ ያለምንም እንቅፋት እንዲጓዙ ፈልጎ ነበር፤ በመሆኑም እንዲህ አለ፦ “ለሕዝቡ መንገድ አዘጋጁ፤ አስተካክሉ፤ ጐዳናውን አስተካክሉ፤ ድንጋዩን አስወግዱ።” (ኢሳ. 62:10) አንዳንድ አይሁዳውያን ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም ምን እንዳደረጉ እስቲ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ምናልባትም የተወሰኑ ሰዎች ከፊት ቀድመው በመሄድ መንገዱ ላይ ያሉትን ጉድጓዶች ሞልተው እንዲሁም ለጉዞ የማይመቹ ቦታዎችን አስተካክለው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ማድረጋቸው ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ከኋላቸው ተከትለው ለሚመጡ ወንድሞቻቸው ትልቅ እርዳታ እንደሆነላቸው ምንም ጥያቄ የለውም።

ይህ ሁኔታ ወደ መንፈሳዊ ግቦች ለመድረስ ከሚደረግ ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይሖዋ ሁሉም አገልጋዮቹ በዚህ ጎዳና ላይ ምንም ዓይነት እንቅፋት ሳይገጥማቸው እንዲጓዙ ይፈልጋል። የአምላክ ቃል “የእግርህን ጐዳና አስተካክል፤ የጸናውን መንገድ ብቻ ያዝ” በማለት ይመክረናል። (ምሳሌ 4:26) ወጣትም ሆንክ ጎልማሳ፣ ይህ መለኮታዊ ምክር ጥበብ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ በሕይወትህ ማየት ትችላለህ።

ጥሩ ውሳኔዎችን በማድረግ መንገዱን አስተካክል

ሰዎች በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ስለሚገኙ ወጣቶች ‘እሷማ ብዙ አጋጣሚዎች አሏት’ ወይም ‘እሱ እኮ ስንት ቦታ መድረስ ይችላል’ ሲሉ ሰምተህ ይሆናል። በአጠቃላይ ሲታይ ወጣቶች ጥሩ ጤንነት፣ ፈጣን አእምሮ እንዲሁም ስኬት የማግኘት ከፍተኛ ጉጉት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው” ብሎ መናገሩ ትክክል ነው። (ምሳሌ 20:29 NW) ተሰጥኦውንና ጉልበቱን ይሖዋን ለማገልገል የሚጠቀምበት ወጣት መንፈሳዊ ግቦች ላይ በመድረስ እውነተኛ ደስታ ማግኘት ይችላል።

ይሁንና የይሖዋ ምሥክር ወጣቶች ያላቸው ችሎታ በዓለም ላይ ተፈላጊ እንደሆነ አስተውለህ ይሆናል። ለምሳሌ አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ሲያገኝ የተማሪዎች አማካሪው፣ መምህሩ ወይም አብሮት የሚማር ተማሪ ከፍተኛ ትምህርት በመከታተል በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስኬት እንዲያገኝ ጫና ያደርጉበታል። ወይም ደግሞ በአትሌቲክስ ዘርፍ ወጣቶችን የሚመለምሉ ሰዎች በዚህ ረገድ ጥሩ ችሎታ ያለውን አንድ ክርስቲያን ወጣት ወደ ስፖርቱ ዓለም  እንዲገባ ሊያግባቡት ይሞክሩ ይሆናል። አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? ወይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት ተጽዕኖ እየደረሰበት ያለ ወጣት ታውቃለህ? ለመሆኑ አንድ ክርስቲያን ጥበብ የታከለበት ምርጫ እንዲያደርግ ምን ሊረዳው ይችላል?

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አንድን ሰው ከሁሉ በተሻለው የሕይወት መንገድ ላይ እንዲጓዝ ሊረዱት ይችላሉ። መክብብ 12:1 “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” በማለት ይናገራል። ታዲያ አንተ ራስህ ወይም አንድ የምታውቀው ወጣት ከሁሉ በተሻለ መንገድ ‘ፈጣሪያችሁን ማሰብ’ የምትችሉት እንዴት ነው?

በምዕራብ አፍሪካ የሚኖረው ኤሪክ * ያጋጠመውን ነገር እስቲ እንመልከት። ኤሪክ እግር ኳስ መጫወት ይወድ ነበር። ኤሪክ 15 ዓመት ሲሆነው ለብሔራዊ ቡድኑ እንዲጫወት ተመረጠ። ይህ ደግሞ ብዙም ሳይቆይ በአውሮፓ ከፍተኛ የስፖርት ሥልጠና የማግኘት አልፎ ተርፎም ፕሮፌሽናል ተጫዋች የመሆን አጋጣሚ ይከፍትለታል። ታዲያ ኤሪክ “ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ደግሞስ ይህ ለአንተ ወይም ለወጣት ጓደኛህ ምን ትምህርት ይዟል?

ኤሪክ ተማሪ ሳለ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በዚህ ጊዜ የሰው ልጆችን ችግር ለዘለቄታው የሚፈታው ፈጣሪ መሆኑን ተረዳ። በመሆኑም ኤሪክ ጊዜውንና ጉልበቱን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ማዋሉ አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘበ። ኤሪክ ይህን ጥበብ ያዘለ እውነታ ስላወቀ በስፖርቱ ዓለም ለመሰማራት የሚያደርገውን ጥረት ለመተው ወሰነ። ከዚያም ተጠመቀ፤ እንዲሁም ትኩረቱን በሙሉ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ አደረገ። ከጊዜ በኋላ የጉባኤ አገልጋይ ሆነ፤ ቆየት ብሎም ለነጠላ ወንድሞች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብቶ እንዲሠለጥን ተጋበዘ።

ኤሪክ በስፖርቱ ቢቀጥል ኖሮ ሀብትና ዝና ማትረፍ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ “ሀብታሞች ግን ሀብታቸው በከተማ ዙሪያ እንዳለ ከፍተኛና ጠንካራ ግንብ፥ የሚጠብቃቸው ይመስላቸዋል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነተኝነት ተረዳ። (ምሳሌ 18:11 የ1980 ትርጉም) አዎ፣ አንድ ሰው በሀብት አማካኝነት ዋስትና ያለው ሕይወት የሚያገኝ ይመስለዋል እንጂ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የሕልም እንጀራ ነው። ከዚህም ሌላ ሀብትን የሚያሳድዱ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ‘ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ይወጋሉ።’—1 ጢሞ. 6:9, 10

ደስ የሚለው ነገር፣ ብዙ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን በመምረጥ ደስታና አስተማማኝ ሕይወት አግኝተዋል። ኤሪክ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋን በሙሉ ጊዜ የሚያገለግል አንድ ትልቅ ‘ቡድን’ ውስጥ ገብቻለሁ። ደግሞም ከዚህ የተሻለ ሌላ ቡድን የለም፤ በሕይወቴ እውነተኛ ደስታና ስኬት የማገኝበትን ብቸኛ መንገድ ስላሳየኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።”

አንተስ? ዓለማዊ ግቦችን ከማሳደድ ይልቅ በአቅኚነት አገልግሎት በመካፈል ‘መንገድህ’ በይሖዋ ፊት የጸና እንዲሆን ብታደርግ የተሻለ አይሆንም?—“ በዩኒቨርሲቲ ሊገኙ የማይችሉ በረከቶች” የሚለውን ተመልከት።

መንገድህ ላይ ያሉ እንቅፋቶችን አስወግድ

አንድ ባልና ሚስት በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ በጎበኙበት ወቅት በዚያ ይሖዋን የሚያገለግሉ ቤቴላውያን ያላቸውን ደስታ አስተዋሉ። እህት “ባለን ሕይወት ረክተን እንኖር ነበር” በማለት ከጊዜ በኋላ ጽፋለች። ባልና ሚስቱ ለሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚያውሉትን ጊዜና ጉልበት በመቀነስ የተለያዩ የአገልግሎት መብቶች ላይ ለመድረስ ወሰኑ።

እነዚህ ባልና ሚስት በአኗኗራቸው ላይ ለውጥ ማድረግ በጣም ተፈታታኝ ሆኖባቸው ነበር። አንድ ቀን ግን የዕለቱን ጥቅስ ሲያነብቡ ሁኔታቸውን ቆም ብለው እንዲመረምሩ የሚያደርግ ሐሳብ ተመለከቱ። ጥቅሱ ዮሐንስ 8:31 ሲሆን እዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ “በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ” ብሏል። እነሱም ጥቅሱን ሲያነቡ “ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ቢያስከፍለን ኑሯችንን ለማቅለል የምናደርገው ነገር ሁሉ አያስቆጭም” ብለው አሰቡ። ትልቅ የሆነውን ቤታቸውን ሸጡ፤ ሌሎች ሸክሞቻቸውንም በማቅለል እርዳታ ወደሚያስፈልገው አንድ ጉባኤ ተዛወሩ። በአሁኑ ጊዜ አቅኚዎች ሆነው እያገለገሉ ሲሆን በመንግሥት አዳራሽ ግንባታና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ያገለግላሉ። ታዲያ ምን ይሰማቸዋል? “የይሖዋ ድርጅት እንደሚያበረታታው ቀላል ኑሮ በመምራታችን ያገኘነውን ደስታ ስናይ ይገርመናል” ብለዋል።

በጀመርከው የመንፈሳዊ እድገት ጎዳና ላይ መጓዝህን ቀጥል

ሰለሞን “ዐይኖችህ በቀጥታ ይመልከቱ፤ ትክ ብለህም ፊት ለፊት እይ” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 4:25) ትኩረቱን ከፊት ለፊት ባለው መንገድ ላይ አድርጎ እንደሚያሽከረክር ሹፌር ሁሉ እኛም ትኩረታችንን በመከፋፈል መንፈሳዊ ግቦችን እንዳናወጣ ወይም ግቦቻችን ላይ እንዳንደርስ የሚያግዱ እንቅፋቶችን ሁሉ ማስወገድ ይኖርብናል።

ታዲያ ልትደርስባቸው የምትችላቸው ምን ዓይነት መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ትችላለህ? ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት አንዱ ነው። ሌላው ደግሞ ሰፊ ክልል ወዳለውና ተሞክሮ ያላቸው የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት  በአቅራቢያህ የሚገኝ ጉባኤ ተዛውሮ ማገልገል ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ጉባኤ ብዙ ውጤታማ አስፋፊዎች ቢኖሩትም የሽማግሌና የጉባኤ አገልጋይ እጥረት ሊኖርበት ይችላል። ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ መርዳት ትችል ይሆን? እገዛ ማበርከት ትችል እንደሆነ እንዲጠቁምህ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ስለ ጉዳዩ ለምን አታነጋግረውም? ከአካባቢህ ርቆ በሚገኝ እርዳታ የሚያስፈልገው ጉባኤ ውስጥ ማገልገል የምትፈልግ ከሆነ ይህን በሚመለከት መረጃ መጠየቅ ትችላለህ። *

እስቲ በኢሳይያስ 62:10 ላይ ወደተገለጸው ታሪክ እንመለስ። የአምላክ ሕዝቦች ወደ አገራቸው መመለስ እንዲችሉ አንዳንድ አይሁዳውያን መንገዱን በመደልደል እንዲሁም እንቅፋትና ጋሬጣ የሆኑ ነገሮችን በማስወገድ በትጋት ሠርተው መሆን አለበት። ከቅዱስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረግክ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። በአምላክ እርዳታ አንተም ግቦችህ ላይ መድረስ ትችላለህ። ከፊትህ የሚጋረጡ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ስትጥር ምንጊዜም ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጥህ ጠይቅ። እንዲህ ካደረግክ ይሖዋ ‘የእግርህን ጎዳና እንድታስተካክል’ የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ማየት ትችላለህ።—ምሳሌ 4:26

^ አን.8 ስሙ ተቀይሯል።

^ አን.18 የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 111-112 ተመልከት።