ታስታውሳለህ?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
በኒሳን 14 ዕለት የፋሲካው በግ የሚታረደው ስንት ሰዓት ላይ ነው?
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በጉ መታረድ ያለበት “በሁለት ምሽት መካከል” እንደሆነ ይናገራሉ፤ በመሆኑም በጉ የሚታረደው ጀምበር ከጠለቀች በኋላ ሆኖም ሙሉ በሙሉ ከመጨለሙ በፊት ነው። (ዘፀ. 12:6)—12/15፣ ከገጽ 18-19
ወጣቶች ጥበብ የተንጸባረቀበት ምርጫ ማድረግ እንዲችሉ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዷቸው ይችላሉ?
ሦስቱ የሚከተሉት ናቸው፦ (1) ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ። (ማቴ. 6:19-34) (2) ሌሎችን በማገልገል ደስታ ለማግኘት ጣሩ። (ሥራ 20:35) (3) በወጣትነታችሁ ይሖዋን በማገልገል እርካታ አግኙ። (መክ. 12:1)—1/15፣ ከገጽ 19-20
ከ1914 አንስቶ እየጋለቡ ያሉት አራቱ ፈረሰኞች የትኞቹ ናቸው?
በነጩ ፈረስ ላይ እንደሚጋልብ ተደርጎ የተገለጸው ኢየሱስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ አባርሯል። ደማቅ ቀይ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ጋላቢ በሰው ዘር ላይ የደረሱትን አስከፊ ጦርነቶች ያመለክታል። የጥቁሩ ፈረስ ጋላቢ ረሃብን ይወክላል። የግራጫው ፈረስ ጋላቢ ደግሞ ገዳይ በሆኑ መቅሰፍቶች አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ይገድላል። (ራእይ 6:2-8)—2/1፣ ከገጽ 6-7
“የበጉ ሠርግ” የሚከናወነው መቼ ነው? (ራእይ 19:7)
“የበጉ ሠርግ” የሚከናወነው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ጦርነቱን በድል ካጠናቀቀ በኋላ ነው፤ ይኸውም ከታላቂቱ ባቢሎን ጥፋትና ከአርማጌዶን በኋላ ነው።—2/15፣ ገጽ 10
በኢየሱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን መሲሑን “ይጠባበቁ” የነበረው ለምንድን ነው? (ሉቃስ 3:15)
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዶች ዳንኤል ስለ መሲሑ የተናገረውን ትንቢት እኛ በተረዳንበት መንገድ ተረድተውት እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። (ዳን. 9:24-27) መልአኩ ለእረኞች የተናገረውን ሐሳብ ወይም ነቢዪቱ ሐና ሕፃኑን ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ስታየው ያለችውን ነገር ሰምተው ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ኮከብ ቆጣሪዎች ‘የተወለደውን የአይሁድ ንጉሥ’ ፍለጋ መጥተው ነበር። (ማቴ. 2:1, 2) ከጊዜ በኋላ ደግሞ አጥማቂው ዮሐንስ ክርስቶስ እንደሚገለጥ ተናግሯል።—2/15፣ ከገጽ 26-27
ቃላችን አዎ ከሆነ አይደለም እንዳይሆን መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው? (2 ቆሮ. 1:18)
አንዳንድ ጊዜ ቃላችንን እንዳንጠብቅ የሚያደርግ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ እንደሚያጋጥመን የታወቀ ነው። ይሁንና አንድ ነገር እንደምንፈጽም ቃል ከገባን ቃላችንን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።—3/15፣ ገጽ 32
ፖርኖግራፊ እንድንመለከት የሚገፋፋንን ስሜት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
ሦስት እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን፦ (1) የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ነገር ድንገት ብንመለከት ቶሎ ብለን ዓይናችንን ማዞር። (2) መልካም በሆኑ ሐሳቦች ላይ በማተኮርና ወደ አምላክ በመጸለይ የምናስበውን ነገር መቆጣጠር። (3) ፖርኖግራፊን ከሚያሳዩ ፊልሞችና ድረ ገጾች በመራቅ እርምጃችንን መቆጣጠር።—4/1፣ ከገጽ 10-12
አንድ ክርስቲያን ገንዘብ ለማግኘት ሲል ቤተሰቡን ትቶ ወደ ውጭ አገር መሄዱ ምን ያልተጠበቁ መዘዞች ሊያስከትል ይችላል?
ወላጆች ከቤተሰባቸው ተለያይተው መኖራቸው ከስሜትና ከሥነ ምግባር አንጻር በልጆች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ልጆቹ በወላጆቻቸው መበሳጨት ሊጀምሩ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ከትዳር ጓደኛው ተለይቶ የሚኖር ከሆነ ሁለቱም የፆታ ብልግና ለመፈጸም ሊፈተኑ ይችላሉ።—4/15፣ ከገጽ 19-20
ወንጀለኞች በእንጨት ላይ ተሰቅለው በሚገደሉበት ጊዜ እግራቸው የሚሰበረው ለምን ነበር?
ሮማውያን አንዳንድ ወንጀለኞችን በእንጨት ላይ ይሰቅሉ ነበር። አይሁዳውያን፣ ከኢየሱስ አጠገብ የተሰቀሉት ወንጀለኞች እግራቸው እንዲሰበር ጠይቀው ነበር። ይህ መሆኑ ሰዎቹ መተንፈስ ከባድ እንዲሆንባቸው ስለሚያደርግ ሞታቸውን ያፋጥነዋል። እንዲህ የሚደረገው በእንጨት ላይ ተሰቅለው እንዳያድሩ ነው። (ዘዳ. 21:22, 23)—5/1፣ ገጽ 11
በአገልግሎት ላይ ሰዎችን ስናነጋግር በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡ አራት ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
የማነጋግረው ሰው ማን ነው? ሰዎችን የማነጋግረው የት ነው? እነሱን ለማግኘት የተሻለው ጊዜ መቼ ነው? ላነጋግራቸው የሚገባው እንዴት ነው?—5/15፣ ከገጽ 12-15
ሲጋራ ማጨስ ምን ያህል ገዳይ ነው?
ባለፈው መቶ ዓመት ውስጥ 100,000,000 ሰዎችን ገድሏል። በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ 6,000,000 የሚያህሉ ሰዎች ሲጋራ በማጨስ ሕይወታቸውን ያጣሉ።—6/1፣ ገጽ 3