በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎች ያላቸውን አቅም በተሟላ ሁኔታ እንዲጠቀሙበት እርዷቸው

ሌሎች ያላቸውን አቅም በተሟላ ሁኔታ እንዲጠቀሙበት እርዷቸው

“እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።”—መዝ. 32:8

1, 2. ይሖዋ በምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹን የሚመለከታቸው እንዴት ነው?

ወላጆች፣ ልጆቻቸው ሲጫወቱ በሚመለከቱበት ጊዜ ልጆቹ ባላቸው ተፈጥሯዊ ችሎታ መደነቃቸው አይቀርም። አንተም ይህን ሁኔታ ተመልክተህ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ልጆች በስፖርት ጎበዝ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ የቤት ውስጥ ጨዋታ ወይም ሥዕል ይወዱ ይሆናል። የልጆቻቸው ችሎታ ምንም ይሁን ምን ወላጆች የልጆቻቸውን ተሰጥኦ ማሳደግ ደስ ይላቸዋል።

2 ይሖዋም በተመሳሳይ ምድር ላይ ያሉ ልጆቹን በትኩረት ይከታተላል። በዘመናችን ያሉ አገልጋዮቹን የሚመለከታቸው ‘ከብሔራት የመጡ የከበሩ ነገሮች’ አድርጎ ነው። (ሐጌ 2:7 NW) በይሖዋ ፊት የከበሩ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው እምነታቸውና ለእሱ ያደሩ መሆናቸው ነው። ያም ቢሆን በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የተለያየ ተሰጥኦ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች መኖራቸውን አስተውለህ ይሆናል። አንዳንድ ወንድሞች ንግግር በማቅረብ ረገድ ጎበዝ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ነገሮችን በማደራጀት ረገድ ውጤታማ ናቸው። በርካታ እህቶች የውጭ አገር ቋንቋ ተምረው በአገልግሎት በመጠቀም ረገድ ጥሩ ችሎታ አላቸው፤ አንዳንዶች ደግሞ ማበረታቻ በመስጠት ወይም የታመሙትን በመንከባከብ ረገድ የተዋጣላቸው ናቸው። (ሮም 16:1, 12) እንዲህ ያሉ ክርስቲያኖችን ባቀፈ ጉባኤ ውስጥ መገኘት ልዩ መብት ነው ቢባል አትስማማም?

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

 3 ወጣቶችንና በቅርብ የተጠመቁ ወንድሞችን ጨምሮ አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን በጉባኤ ውስጥ ምን ድርሻ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ገና አላወቁ ይሆናል። ታዲያ ያላቸውን አቅም በተሟላ ሁኔታ እንዲጠቀሙበት እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? የይሖዋን ምሳሌ በመከተል በውስጣቸው ያለውን መልካም ነገር ለማየት ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

ይሖዋ በአገልጋዮቹ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ያያል

4, 5. መሳፍንት 6:11-16 ላይ ያለው ዘገባ ይሖዋ አገልጋዮቹ ያላቸውን አቅም እንደሚመለከት የሚያሳየው እንዴት ነው?

4 የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እንደሚያሳዩት ይሖዋ በአገልጋዮቹ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ብቻ ሳይሆን ያላቸውን አቅምም ይመለከታል። ለምሳሌ ያህል፣ ጌዴዎን የይሖዋን ሕዝብ ከምድያማውያን ጭቆና ነፃ እንዲያወጣ ሲመረጥ አንድ መልአክ “አንተ ኀያል ጦረኛ! እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” ብሎት ነበር፤ በዚህ ጊዜ ጌዴዎን በጣም ተደንቆ መሆን አለበት። በወቅቱ ጌዴዎን ራሱን “ኀያል” አድርጎ እንደማይቆጥር ግልጽ ነው። እንዲያውም ስጋቱን አልፎ ተርፎም ብቃት የሌለው መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ ከመልአኩ ጋር ያደረገው ውይይት እንደሚያሳየው ይሖዋ፣ ጌዴዎን እንኳ ስለ ራሱ የማያውቃቸውን መልካም ነገሮች ተመልክቷል።—መሳፍንት 6:11-16ን አንብብ።

5 ይሖዋ የጌዴዎንን ችሎታ ስላስተዋለ እስራኤላውያንን ነፃ ማውጣት እንደሚችል ተማምኖበታል። ለምሳሌ የይሖዋ መልአክ፣ ጌዴዎን ስንዴውን ሲወቃ ምን ያህል ጉልበት እንደነበረው ተመልክቷል። የመልአኩን ትኩረት የሳበ ሌላም ነገር ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ገበሬዎች እህል የሚወቁት ሜዳ ላይ ነበር፤ ይህም ነፋሱ እብቁን እንዲወስደው ያስችላል። ጌዴዎን ግን ያገኘውን ጥቂት ስንዴ ከምድያማውያን ለመደበቅ ሲል እህሉን በወይን መጭመቂያ ውስጥ መውቃቱ የሚያስገርም ነው። እንዴት ያለ ብልህነት ነው! ጌዴዎንን ጠንቃቃ ገበሬ ብቻ ሳይሆን አስተዋይ ሰው ነበር። በእርግጥም ይሖዋ፣ ጌዴዎን ያለውን አቅም በመመልከቱ ከእሱ ጋር እንዲሠራ መርጦታል።

6, 7. (ሀ) ይሖዋ ለአሞጽ የነበረው አመለካከት አንዳንድ እስራኤላውያን ለእሱ ከነበራቸው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው? (ለ) አሞጽ ያልተማረ ሰው አልነበረም እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

6 በተጨማሪም ይሖዋ፣ ነቢዩ አሞጽ ያለውን አቅም ተመልክቷል፤ እርግጥ ነው፣ በወቅቱ ብዙዎች ይህ ነቢይ እዚህ ግባ የሚባል ሰው እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። አሞጽ ስለ ራሱ ሲናገር እረኛና የባሉጥ ፍሬ ለቃሚ እንደሆነ ገልጿል፤ ይህ ፍሬ ደግሞ የድሆች ምግብ እንደሆነ ይቆጠር ነበር። ይሖዋ፣ ጣዖት አምላኪ በሆነው አሥሩን ነገድ ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ላይ የፍርድ መልእክት ለማስተላለፍ ይህን ነቢይ በመረጠው ጊዜ አንዳንድ እስራኤላውያን አሞጽ ለሥራው የሚመጥን እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል።—አሞጽ 7:14, 15ን አንብብ።

7 አሞጽ የሚኖረው ገጠር ውስጥ ነበር፤ ይሁን እንጂ ስለ አካባቢው ባሕልና በዙሪያው ስላሉት ገዥዎች ጥሩ ግንዛቤ ያለው መሆኑ ያልተማረ ሰው እንዳልነበረ ያሳያል። በእስራኤል ስላለው ሁኔታ በደንብ ያውቅ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ እንዲሁም ከተጓዥ ነጋዴዎች ጋር መገናኘቱ በዙሪያው ስላሉት ብሔራት ጠንቅቆ እንዲያውቅ ረድቶት ሊሆን ይችላል። (አሞጽ 1:6, 9, 11, 13፤ 2:8፤ 6:4-6) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አሞጽ ጥሩ የሥነ ጽሑፍ ችሎታ እንዳለው ይሰማቸዋል። ነቢዩ ለመረዳት ቀላል ሆኖም ኃይለኛ መልእክት ያላቸው ቃላትን ተጠቅሟል፤ እንዲሁም ሐሳቡን እያነጻጸረ የመግለጽ እንዲሁም ቃላትን በተለያየ ትርጉማቸው የመጠቀም ችሎታ እንዳለው አሳይቷል። አሞጽ ምግባረ ብልሹ ለሆነው ለካህኑ አሜስያስ በልበ ሙሉነት ምላሽ መስጠቱ ይሖዋ ለሥራው የሚሆን ትክክለኛ ሰው እንደመረጠ እንዲሁም አሞጽ ያለውን አቅም እንደተጠቀመበት ያሳያል።—አሞጽ 7:12, 13, 16, 17

8. (ሀ) ይሖዋ ለዳዊት የሰጠው ማረጋገጫ ምንድን ነው? (ለ) በመዝሙር 32:8 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በራስ መተማመን የሚጎድላቸውን ወይም ችሎታ የሌላቸውን የሚያበረታታው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ፣ እያንዳንዱ አገልጋዩ ያለውን አቅም  ይመለከታል። ሁልጊዜ እንደሚመራውና ‘በዓይኑም እንደሚከታተለው’ ለንጉሥ ዳዊት ገልጾለታል። (መዝሙር 32:8ን አንብብ።) ይህ ሐሳብ የሚያበረታታን እንዴት ነው? በራስ የመተማመን መንፈስ ባይኖረንም እንኳ እናደርጋለን ብለን ጨርሶ የማናስባቸውን ነገሮች በይሖዋ እርዳታ ማከናወን እንችላለን። አንድ አባት ልጁን ብስክሌት መንዳት ሲያለማምደው አመራር በመስጠት እንደሚያሠለጥነው ሁሉ ይሖዋም መንፈሳዊ እድገት ስናደርግ ሊመራን ፈቃደኛ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ያለንን አቅም በተሟላ ሁኔታ እንድንጠቀምበት ለመርዳት የእምነት ባልንጀሮቻችንን ይጠቀማል። እንዴት?

በወንድሞች ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ተመልከቱ

9. ጳውሎስ ለሌሎች ጉዳይ ‘ትኩረት እንድንሰጥ’ የጻፈውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

9 ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ጉዳይ ‘ትኩረት እንዲሰጡ’ አሳስቧል። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4ን አንብብ።) ጳውሎስ የሰጠው ምክር፣ የሌሎችን ተሰጥኦ ማስተዋልና ይህን ጠቅሰን ማድነቅ እንዳለብን ይጠቁማል። አንድ ሰው በእኛ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር በመመልከት ጥረታችንን ቢያደንቅልን ምን ይሰማናል? እንዲህ ያለው ማበረታቻ ብዙውን ጊዜ ችሎታችንን ይበልጥ በመጠቀም እድገት እንድናደርግ ያነሳሳናል። በተመሳሳይም የእምነት ባልንጀሮቻችን ያላቸውን ችሎታ ተመልክተን ማድነቃችን በመንፈሳዊ ይበልጥ እድገት እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።

10. በተለይ የእኛ ትኩረት የሚያሻቸው እነማን ናቸው?

10 በተለይ የእኛ ትኩረት የሚያሻቸው እነማን ናቸው? ሁላችንም የተለየ ትኩረት የሚያስፈልገን ጊዜ እንደሚኖር የታወቀ ነው። ያም ቢሆን ወጣቶች ወይም በቅርቡ የተጠመቁ ወንድሞች የበለጠ ትኩረት ይፈልጋሉ፤ በመሆኑም እንዲህ ያሉ ወንድሞች በጉባኤው ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ልናስገነዝባቸው ይገባል። ይህ ደግሞ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ቦታ እንዳላቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል። የአምላክ ቃል፣ ወንዶች ለተጨማሪ ኃላፊነት እንዲጣጣሩ ያበረታታል፤ ለእነዚህ ወንድሞች ተገቢውን እውቅና የማንሰጥ ከሆነ ግን እንዲህ የማድረግ ፍላጎታቸው ሊጠፋ ይችላል።—1 ጢሞ. 3:1

11. (ሀ) አንድ ሽማግሌ፣ የዓይን አፋርነትን ችግር እንዲያሸንፍ አንድን ወጣት የረዳው እንዴት ነው? (ለ) ከዡልያን ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

11 በወጣትነቱ ሌሎች ትኩረት ስለሰጡት የተጠቀመ ሉዶቪክ የተባለ አንድ ሽማግሌ “ለአንድ ወንድም ከልቤ ትኩረት ስሰጠው ፈጣን እድገት ያደርጋል” ብሏል። ሉዶቪክ፣ ዡልያን ስለተባለ አንድ ዓይን አፋር ወጣት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ የሚያደርገው ነገር ጥንቃቄ የጎደለው ስለሚመስል የእሱ ባሕርይ ግራ የሚያጋባ ነበር። እኔ ግን በጣም ደግ እንደሆነና የጉባኤውን አባላት ከልቡ መርዳት እንደሚፈልግ ማስተዋል ቻልኩ። በመሆኑም ውስጣዊ ዝንባሌውን ከመጠራጠር ይልቅ በመልካም ባሕርያቱ ላይ በማተኮር አበረታታሁት።” ከጊዜ በኋላ ዡልያን የጉባኤ አገልጋይ የሆነ ሲሆን በኋላም የዘወትር አቅኚ ለመሆን ችሏል።

ያላቸውን አቅም በተሟላ ሁኔታ እንዲጠቀሙበት እርዷቸው

12. አንድ ወንድም ያለውን አቅም በተሟላ መንገድ እንዲጠቀምበት ለመርዳት ከፈለግን የትኛው ባሕርይ ሊኖረን ይገባል? ምሳሌ ስጥ።

12 ሌሎች ያላቸውን አቅም በተሟላ መንገድ እንዲጠቀሙበት ለመርዳት ከፈለግን አስተዋይ መሆን እንዳለብን ግልጽ ነው። የዡልያን ተሞክሮ እንደሚያሳየው አንድ ሰው ካለው ደካማ ጎን ባሻገር ያሉትን ሊዳብሩ የሚችሉ መልካም ባሕርያትና ክህሎቶች ማስተዋል ይኖርብናል። ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ከነበረው አመለካከት ይህን መረዳት እንችላለን። ጴጥሮስ አንዳንድ ጊዜ የመወላወል ባሕርይ ቢታይበትም ወደፊት እንደ ዐለት ጽኑ እንደሚሆን ኢየሱስ ተረድቶ ነበር።—ዮሐ. 1:42

13, 14. (ሀ) በርናባስ፣ ወጣቱ ማርቆስ ያለውን መልካም ነገር ያስተዋለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ወጣት ወንድም ልክ እንደ ማርቆስ ከሌሎች ባገኘው እርዳታ የተጠቀመው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

13 በርናባስም በተመሳሳይ በዮሐንስ (ሮማዊ ስሙ ማርቆስ ነው) ውስጥ ያለውን መልካም ነገር አስተውሏል። (ሥራ 12:25) ጳውሎስ ከበርናባስ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞ ወቅት ማርቆስ “አገልጋይ ሆኖ ይረዳቸው ነበር”፤ ምናልባትም ይህ ሐሳብ ማርቆስ በቁሳዊ ረገድ ፍላጎታቸውን በማሟላት ይንከባከባቸው እንደነበረ የሚያሳይ  ሊሆን ይችላል። ጵንፍልያ በደረሱ ጊዜ ግን ማርቆስ የሥራ ባልደረቦቹን ጥሏቸው ሄደ። በመሆኑም የሰሜንን አቅጣጫ ይዘው ወንበዴዎች የሚበዙበትን መንገድ አቋርጠው ለብቻቸው ለመሄድ ተገደዱ። (ሥራ 13:5, 13) ማርቆስ በአቋም ያለመጽናት ባሕርይ ቢኖረውም ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በርናባስ በዚያ ላይ አላተኮረም፤ ከዚህ ይልቅ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የተሟላ ሥልጠና የሰጠው ይመስላል። (ሥራ 15:37-39) ይህ ደግሞ ወጣቱ ማርቆስ የጎለመሰ የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆን ረድቶታል። የሚገርመው ደግሞ ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ማርቆስ ከጎኑ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በቆላስይስ ጉባኤ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሰላምታ ከላኩት መካከል አንዱ ነበር፤ እንዲሁም ጳውሎስ ማርቆስን ያነሳው በመልካም ነው። (ቆላ. 4:10) በተጨማሪም ጳውሎስ ራሱ የማርቆስ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ሲናገር በርናባስ ምን ያህል የእርካታ ስሜት እንደተሰማው መገመት ይቻላል።—2 ጢሞ. 4:11

14 በቅርቡ ሽማግሌ የሆነ አሌክሳንድረ የተባለ ወንድም አንድ ሽማግሌ ያደረገለትን እርዳታ አስታውሶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ወጣት እያለሁ በሰዎች ፊት መጸለይ በጣም ይከብደኝ ነበር። አንድ ሽማግሌ እንዴት መዘጋጀትና መረጋጋት እንደምችል አሠለጠነኝ። ይህ ሽማግሌ፣ የጸሎት መብት ከመከልከል ይልቅ በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ላይ ብዙ ጊዜ የመጸለይ አጋጣሚ ይሰጠኝ ነበር። በጊዜ ሂደት በራስ የመተማመን መንፈስ እያዳበርኩ መጣሁ።”

15. ጳውሎስ ለወንድሞቹ ያለውን አድናቆት የገለጸው እንዴት ነው?

15 አንድ የእምነት ባልንጀራችን መልካም ባሕርይ ወይም ችሎታ እንዳለው ስናስተውል ያንን በመጥቀስ አድናቆታችንን እንገልጽለታለን? በሮም ምዕራፍ 16 ላይ ጳውሎስ ከ20 በላይ የሚሆኑ የእምነት ባልንጀሮቹን የሚያደንቅላቸውን ነገር እየጠቀሰ አመስግኗቸዋል። (ሮም 16:3-7, 13) ለምሳሌ ያህል አንድሮኒኮስና ዩኒያስ ከእሱ ቀደም ብለው የክርስቶስ ተከታዮች እንደሆኑ በመግለጽ ስላሳዩት ጽናት የሚጠቁም ነገር ተናግሯል። ጳውሎስ ስለ ሩፎስ እናትም መልካም ነገር የጠቀሰ ሲሆን ምናልባትም ይህን የተናገረው ቀደም ሲል ያደረገችለትን እንክብካቤ አስታውሶ ሊሆን ይችላል።

ፍሬዴሪክ (በስተ ግራ) ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርግ ሪኮን አበረታትቶታል (አንቀጽ 16ን ተመልከት)

16. ወጣቶችን ማድነቅ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

16 ሌሎችን ከልብ ማድነቅ ግሩም ውጤቶች ሊያስገኝ ይችላል። የሪኮን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በፈረንሳይ የሚኖረው ይህ ታዳጊ፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው አባቱ እንዳይጠመቅ ስለተቃወመው ተስፋ ቆርጦ ነበር። ሪኮ ይሖዋን በሙሉ ነፍሱ ለማገልገል 18 ዓመት እስኪሆነው መጠበቅ እንዳለበት ተሰምቶት ነበር። ከዚህም ሌላ ትምህርት ቤት ውስጥ ስለሚሾፍበት በጣም አዝኖ ነበር። ይህን ልጅ እንዲያስጠናው የተጠየቀው ፍሬዴሪክ የተባለው የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ተቃውሞ የሚደርስበት መሆኑ በራሱ እምነቱን ለሌሎች በድፍረት የሚናገር መሆኑን እንደሚጠቁም በመጥቀስ ሪኮን አመሰገንኩት።” ሪኮ ይህን ማበረታቻ ማግኘቱ መልካም ስሙን እንደያዘ ለመቀጠልና ከአባቱ ጋር ያለውን ዝምድና ለማሻሻል ረድቶታል። በመጨረሻም ሪኮ በ12 ዓመቱ ተጠመቀ።

ዤሮም (በስተ ቀኝ) ሚስዮናዊ እንዲሆን ራያንን ረድቶታል (አንቀጽ 17ን ተመልከት)

17. (ሀ) ወንድሞቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሚስዮናዊ ወንድም፣ ወጣት ወንዶችን ትኩረት ሰጥቶ የሚረዳው እንዴት ነው? ምን ውጤትስ አገኘ?

17 አንድ የእምነት ባልንጀራችን የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ ሲወጣ ወይም ጥረት ሲያደርግ  ካመሰገንነው ይሖዋን በሙሉ አቅሙ ለማገልገል ይነሳሳል። በፈረንሳይ ቤቴል ለበርካታ ዓመታት ያገለገለችው ሲልቪ * እህቶችም ቢሆኑ ወንድሞችን ማመስገን እንደሚችሉ ተናግራለች። ሴቶች፣ ወንዶች የማያስተውሏቸውን አንዳንድ ነገሮች መመልከት እንደሚችሉ ገልጻለች። በመሆኑም እነሱ “የሚሰጡት ሐሳብ ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች የሚሰጡትን ማበረታቻ የሚያጠናክር” እንደሚሆን ተናግራለች። አክላም “እንደ እኔ ከሆነ፣ ማመስገን ኃላፊነት ነው” ብላለች። (ምሳሌ 3:27) በፈረንሳይ ጊያና ሚስዮናዊ ሆኖ የሚያገለግለው ዤሮም በርካታ ወጣቶች ለሚስዮናዊነት ብቁ እንዲሆኑ ረድቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ወጣት ወንድሞች ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ያላቸውን መልካም ጎን ጠቅሼ ሳመሰግናቸው ወይም በጉባኤ ውስጥ ለሰጡት የታሰበበት መልስ አድናቆቴን ስገልጽላቸው በራስ የመተማመን ስሜታቸው እንደሚጨምር ማየት ችያለሁ። በውጤቱም ችሎታቸው ይበልጥ እየዳበረ ይሄዳል።”

18. ወጣቶችን በሥራ ማሳተፍ ምን ጥቅም አለው?

18 የእምነት ባልንጀሮቻችንን በሥራ ማሳተፍ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል። አንድ ሽማግሌ የኮምፒውተር እውቀት ያለውን አንድ ወጣት ከjw.org ላይ አንዳንድ መረጃዎችን በማተም ኮምፒውተር ለሌላቸው አረጋውያን እንዲሰጥ ሊጠይቀው ይችላል። አሊያም ደግሞ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የምትሠራው ሥራ ካለህ አንድ ወጣት ወንድም እንዲያግዝህ ለምን አትጠይቀውም? በዚህ መንገድ ወጣቶችን በሥራ ማሳተፍህ አቅማቸውን ለማስተዋልና ለማመስገን አጋጣሚ ይከፍትልሃል፤ እንዲሁም ለውጥ ሲያደርጉ ማየት ትችላለህ።—ምሳሌ 15:23

ለወደፊቱ ጊዜ መሠረት መጣል

19, 20. ሌሎች እድገት እንዲያደርጉ መርዳት ያለብን ለምንድን ነው?

19 ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲመራ ኢያሱን የሾመው ሲሆን በዚህ ወቅት ሙሴ ኢያሱን ‘እንዲያደፋፍረውና እንዲያበረታታው’ ታዝዞ ነበር። (ዘዳግም 3:28ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ወደ ዓለም አቀፉ ጉባኤ እየጎረፉ ነው። በመሆኑም ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ተሞክሮ ያላቸው ሁሉም ክርስቲያኖች፣ ወጣቶችና በቅርብ የተጠመቁ ወንድሞች ያላቸውን አቅም በተሟላ ሁኔታ እንዲጠቀሙበት ሊረዷቸው ይገባል። እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ ብዙዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉና “ሌሎችን ለማስተማር በሚገባ ብቁ” እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል።—2 ጢሞ. 2:2

20 የምናገለግለው በትልቅ ጉባኤ ውስጥም ሆነ ጉባኤ ለመሆን እድገት በሚያደርግ ትንሽ ቡድን ውስጥ ለወደፊቱ ጊዜ ከአሁኑ መሠረት መጣላችን አስፈላጊ ነው። ለዚህ ቁልፉ በሰዎች ውስጥ ያለውን መልካም ነገር የሚመለከተውን ይሖዋን መምሰል ነው።

^ አን.17 ስሟ ተቀይሯል።