በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደካሞችን የምትመለከቱት በይሖዋ ዓይን ነው?

ደካሞችን የምትመለከቱት በይሖዋ ዓይን ነው?

“ደካማ የሚመስሉት የአካል ክፍሎች . . . በጣም አስፈላጊ ናቸው።”—1 ቆሮ. 12:22

1, 2. ጳውሎስ ደካማ የሆኑትን ክርስቲያኖች ስሜት ለመረዳት ያስቻለው ምንድን ነው?

ሁላችንም አልፎ አልፎ ድካም ይሰማናል። ጉንፋን ወይም ሌሎች በሽታዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን ማከናወን እስኪያቅተን ድረስ እንድንደክም ሊያደርጉን ይችላሉ። ይህ የድካም ስሜት ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንት ሳይሆን ለወራት የሚቀጥል ቢሆንስ? በዚህ ወቅት ሌሎች ስሜትህን እንደተረዱልህ የሚያሳይ ነገር ቢያደርጉ ደስ አይልህም?

2 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ከጉባኤም ሆነ ከውጭ ተጽዕኖዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ሁኔታው ምን ያህል ጫና እንደሚያሳድር አልፎ ተርፎም እንደሚያዳክም ጠንቅቆ ያውቃል። ነገሮች ከአቅሙ በላይ እንደሆኑበት የተናገረባቸው ወቅቶች ነበሩ። (2 ቆሮ. 1:8፤ 7:5) ስላሳለፈው ሕይወትና ታማኝ ክርስቲያን በመሆኑ ስላጋጠሙት ብዙ መከራዎች ቆም ብሎ ሲያስብ “ደካማ ማን ነው? እኔስ ድካም አይሰማኝም?” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮ. 11:29) እንዲሁም የክርስቲያን ጉባኤ አባላትን ከሰውነት ክፍሎች ጋር አመሳስሎ በተናገረበት ወቅት “ደካማ የሚመስሉት የአካል ክፍሎች . . . በጣም አስፈላጊ” መሆናቸውን ገልጾ ነበር። (1 ቆሮ. 12:22) ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? ደካማ የሚመስሉትን ክርስቲያኖች ይሖዋ በሚመለከታቸው መንገድ ማየት ያለብን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

 ይሖዋ ደካማ ለሆኑት ያለው አመለካከት

3. በጉባኤ ውስጥ ላሉ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ምን ሊሆን ይችላል?

3 የምንኖረው በፉክክር በተሞላ ብሎም ለጥንካሬና ለወጣትነት ትልቅ ቦታ በሚሰጥ ዓለም ውስጥ ነው። ብዙዎች የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም፤ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ በደካሞች ላይ ተረማምደው ማለፍ ይፈልጋሉ። እንዲህ ያለውን ባሕርይ እንደማንደግፍ የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን በጉባኤ ውስጥ ጭምር በየጊዜው እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሳይታወቀን አሉታዊ አመለካከት ልናዳብር እንችላለን። ከዚህ ይልቅ አምላክ ያለው ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበራችን አስፈላጊ ነው።

4, 5. (ሀ) በ1 ቆሮንቶስ 12:21-23 ላይ የሚገኘው ምሳሌ ይሖዋ ለደካሞች ያለውን አመለካከት እንድንረዳ የሚያስችለን እንዴት ነው? (ለ) ደካማ የሆኑትን መርዳት ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

4 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ የጠቀሰው ምሳሌ ይሖዋ ለደካሞች ያለውን አመለካከት በተመለከተ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል። ጳውሎስ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ወይም ደካማ የሆኑ የሰውነት ክፍሎች ጭምር ጠቃሚ ድርሻ እንዳላቸው በምዕራፍ 12 ላይ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 12:12, 18, 21-23ን አንብብ።) አንዳንድ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ጳውሎስ የሰው አካልን አስመልክቶ የሰጠው ይህ መግለጫ ትክክል እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ያም ቢሆን በሰው አካል ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች፣ ቀደም ሲል ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ይታሰቡ የነበሩ የሰውነት ክፍሎች ጠቃሚ ሥራ እንደሚያከናውኑ ደርሰውበታል። * ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች ትንሹ የእግራችን ጣት ጠቃሚ ስለ መሆኑ ጥያቄ አንስተው ነበር፤ አሁን ግን ሰውነታችን ሚዛኑን እንዲጠብቅ በመርዳት ረገድ የራሱ ሚና እንዳለው ተደርሶበታል።

5 ጳውሎስ የጠቀሰው ምሳሌ ሁሉም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ጠቃሚ እንደሆኑ ያጎላል። የሰዎችን ክብር ከማይጠብቀው ከሰይጣን በተቃራኒ ይሖዋ ደካማ የሚመስሉትን ጨምሮ ሁሉንም አገልጋዮቹን “አስፈላጊ” እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ኢዮብ 4:18, 19) ይህን ማወቃችን በጉባኤያችንም ሆነ በዓለም አቀፉ የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ እንዳለን እንድንገነዘብ ያደርገናል። ለምሳሌ በዕድሜ የገፋን አንድ ሰው ደግፈህ የያዝክበትን ጊዜ ለማስታወስ ሞክር። በዚህ ወቅት እርምጃህን ከእሱ እኩል ማድረግ ጠይቆብህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ ማበርከትህ ለግለሰቡ ጠቃሚ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። በእርግጥም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን መደገፋችን ደስታ ያስገኝልናል፤ እንዲሁም ይበልጥ ታጋሽ፣ አፍቃሪና የጎለመስን ክርስቲያኖች እንሆናለን። (ኤፌ. 4:15, 16) አፍቃሪው አባታችን፣ የአቅም ገደባቸው ምንም ይሁን ምን የጉባኤውን አባላት በሙሉ ከፍ አድርገን እንድንመለከታቸው ይፈልጋል፤ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ አፍቃሪ እንዲሁም ከሌሎች በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ እንደሆንን እናሳያለን።

6. ጳውሎስ “ደካማ” እና “ብርቱ” የሚሉትን ቃላት የተጠቀመው ምን ለማመልከት ነው?

6 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የማያምኑ ሰዎች በወቅቱ ለነበሩት ክርስቲያኖች ያላቸውን አመለካከት እንዲሁም ለራሱ ያለውን ስሜት ለመግለጽ ሲል “ደካማ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ ትኩረት የሚስብ ነው። (1 ቆሮ. 1:26, 27፤ 2:3) በሌላ በኩል ደግሞ ጳውሎስ “ብርቱ” ስለሆኑት ክርስቲያኖች ተናግሯል፤ ይሁንና ይህን የተናገረው አንዳንድ ክርስቲያኖች ከሌሎች እንደሚበልጡ እንዲሰማቸው ለማድረግ ፈልጎ አይደለም። (ሮም 15:1) ከዚህ ይልቅ የበለጠ ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያኖች በእውነት ውስጥ ሥር ያልሰደዱትን በትዕግሥት እንዲይዟቸው ማበረታታቱ ነበር።

አመለካከታችንን ማስተካከል ያስፈልገናል?

7. ‘ችግር’ ላይ ያሉትን ከመርዳት ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው?

7 ‘ችግር’ ላይ ያሉትን ስንረዳ ይሖዋን የምንመስል ከመሆኑም ሌላ ሞገሱን እናገኛለን። (መዝ. 41:1 የ1954 ትርጉም፤ ኤፌ. 5:1) እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው  ሰዎች አሉታዊ አመለካከት ማዳበር እነሱን ከመርዳት ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን እንደሚችል የታወቀ ነው። ወይም ደግሞ ምን ማለት እንዳለብን ካላወቅን በችግር ላይ ያሉ ሰዎችን ከመርዳት ይልቅ ተሸማቅቀን ልንርቃቸው እንችላለን። ባለቤቷ ትቷት የሄደ ሲንቲያ * የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞች ችላ ሲሏችሁ ወይም ደግሞ ከቅርብ ወዳጅ የሚጠበቀውን ነገር ሳያደርጉ ሲቀሩ ልትጎዱ ትችላላችሁ። ፈተናዎች ሲያጋጥሟችሁ ከጎናችሁ የሚሆን ሰው ትፈልጋላችሁ።” ዳዊትም ቢሆን ችላ መባል ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በሕይወቱ አይቷል።—መዝ. 31:12

8. በችግር ላይ ያሉ ሰዎችን ስሜት ለመረዳት ምን ሊረዳን ይችላል?

8 አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደካማ የሆኑት ከባድ ችግር ስለገጠማቸው ለምሳሌ በጤና እክል፣ በሃይማኖት የተከፋፈለ ቤት ውስጥ በመኖራቸው ወይም በመንፈስ ጭንቀት ምክንያት መሆኑን ካስታወስን ይበልጥ ስሜታቸውን ልንረዳላቸው እንችላለን። በተጨማሪም ‘ነግ በኔ’ ማለት ይኖርብናል። በግብፅ ምድር ሳሉ ድሆችና ደካሞች የነበሩት እስራኤላውያን ለተቸገሩ ወንድሞቻቸው ‘ልባቸውን እንዳያጨክኑባቸው’ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር። ይሖዋ ለድሆች እርዳታ እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸው ነበር።—ዘዳ. 15:7, 11፤ ዘሌ. 25:35-38

9. ችግር ውስጥ ያሉ ወንድሞችን ስንረዳ ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለምን ነገር ነው? በምሳሌ አስረዳ።

9 ተቺ ወይም ነቃፊ ከመሆን ይልቅ በችግር ውስጥ ላሉ ወንድሞቻችን መንፈሳዊ ማበረታቻ መስጠት ይኖርብናል። (ኢዮብ 33:6, 7፤ ማቴ. 7:1) ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ሰው የሞተር ብስክሌት ሲያሽከረክር አደጋ ቢደርስበትና ወደ ድንገተኛ ሕክምና ክፍል ቢገባ የሕክምና ባለሙያዎቹ አደጋውን ያደረሰው እሱ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት የሚሞክሩ ይመስልሃል? በፍጹም፣ ከዚህ ይልቅ ወዲያውኑ አስፈላጊውን የሕክምና እርዳታ ያደርጉለታል። በተመሳሳይም አንድ የእምነት ባልንጀራችን በገጠመው ችግር የተነሳ ቢደክም በቅድሚያ ጥረት ማድረግ ያለብን እሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት ነው።—1 ተሰሎንቄ 5:14ን አንብብ።

10. ደካማ የሚመስሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች “በእምነት ባለጸጋ” ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

10 ወንድሞቻችንን ከላይ ስንመለከታቸው ደካማ ይመስሉ ይሆናል፤ ሆኖም ሕይወታቸውን ቀረብ ብለን ለመመልከት ከሞከርን ሁኔታው እንዳሰብነው ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ለበርካታ ዓመታት የሚደርስባቸውን የቤተሰብ ተቃውሞ በጽናት ያሳለፉ እህቶችን ማሰብ ይቻላል። አንዳንዶች አንገታቸውን የደፉና ምስኪን ይመስሉ ይሆናል፤ ይሁንና ያላቸውን አስደናቂ እምነትና ውስጣዊ ጥንካሬ ለምን አትመለከትም? ልጆቿን አዘውትራ ወደ ስብሰባ ይዛ የምትመጣ ነጠላ ወላጅ የሆነች አንዲት እህት ያላትን እምነትና ቁርጠኝነት ስትመለከት አትደነቅም? በትምህርት ቤት መጥፎ ተጽዕኖዎች ቢደርሱባቸውም እውነትን አጥብቀው የያዙ ወጣቶች ስትመለከት አትደሰትም? በእርግጥም ወንድሞቻችን የሚያደርጉትን ጥረት ስንመለከት ደካማ የሚመስሉ ወንድሞችና እህቶች በአንጻራዊ ሁኔታ በተመቻቸ ሁኔታ ሥር ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሌሎች ክርስቲያኖች እኩል “በእምነት ባለጸጋ” እንደሆኑ እናስተውላለን።—ያዕ. 2:5

የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ይኑራችሁ

11, 12. (ሀ) ወንድሞቻችን በሰብዓዊ ድክመት የተነሳ ስህተት ሲፈጽሙ ለእነሱ ያለንን አመለካከት ለማስተካከል ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) ይሖዋ አሮንን ከያዘበት መንገድ ምን እንማራለን?

11 ይሖዋ አገልጋዮቹን የያዘበትን መንገድ መመልከታችን ወንድሞቻችን በሰብዓዊ ድክመት የተነሳ ስህተት ሲፈጽሙ ለእነሱ ያለንን አመለካከት ለማስተካከል ይረዳናል። (መዝሙር 130:3ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ አሮን የወርቅ ጥጃ ምስል በሠራበት ወቅት ከሙሴ ጋር ሆነህ ቢሆን ኖሮ አሮን ላደረገው ነገር ሰበብ አስባብ ሲደረድር ምን ይሰማህ ነበር? (ዘፀ. 32:21-24) አሊያም ደግሞ አሮን በእህቱ በማርያም ተጽዕኖ በመሸነፍ ሙሴን የሌላ አገር ሴት በማግባቱ ሲነቅፈው ምን ይሰማህ ነበር? (ዘኍ. 12:1, 2) ሙሴና አሮን በመሪባ ለሕዝቡ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ውኃ ባፈለቁ ጊዜ ለይሖዋ ክብር አለመስጠታቸውን ስትመለከት ምን ታደርግ ነበር?—ዘኍ. 20:10-13

 12 በእነዚህ ወቅቶች ይሖዋ፣ አሮን ላይ ወዲያውኑ እርምጃ ሊወስድ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ አሮን መጥፎ ሰው እንዳልሆነ ያውቃል። አሮን መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ሁኔታዎች ወይም ሌሎች ሰዎች ባሳደሩበት ተጽዕኖ በመሸነፉ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆኖ ጥፋተኛ እንደሆነ ሲነገረው ወዲያውኑ ስህተቱን ያመነ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን የፍርድ ውሳኔ ደግፏል። (ዘፀ. 32:26፤ ዘኍ. 12:11፤ 20:23-27) ይሖዋ ትኩረት ያደረገው በአሮን እምነትና ከልብ ንስሐ በመግባቱ ላይ ነው። እንዲያውም ዘመናት ካለፉ በኋላም አሮንና ዘሮቹ ይሖዋን እንደሚፈሩ ተገልጿል።—መዝ. 115:10-12፤ 135:19, 20

13. ደካማ መስለው ለሚታዩት ወንድሞቻችን ያለንን አመለካከት ማጤን የምንችለው እንዴት ነው?

13 የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ከፈለግን ደካማ ለሚመስሉ ወንድሞቻችን ያለንን አመለካከት ማጤን ይኖርብናል። (1 ሳሙ. 16:7) ለምሳሌ አንድ ወጣት የመዝናኛ ምርጫው ጥበብ የጎደለው ቢሆን ወይም የግድ የለሽነት ባሕርይ ቢታይበት ምን እናደርጋለን? ነቃፊ ከመሆን ይልቅ በመንፈሳዊ እንዲጎለምስ መርዳት ስለምንችልበት መንገድ ቆም ብለን ማሰብ አይኖርብንም? እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው በሚኖርበት ጊዜ ቅድሚያውን ወስደን መርዳት ይኖርብናል፤ እንዲህ ስናደርግ የሌሎችን ስሜት ይበልጥ የምንረዳ እንዲሁም አፍቃሪ እንሆናለን።

14, 15. (ሀ) ኤልያስ ለጊዜው ድፍረት ባጣበት ወቅት ይሖዋ እንዴት ተመለከተው? (ለ) ይሖዋ ኤልያስን ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ መንፈሳቸው የተደቆሰ አገልጋዮቹን የያዘበትን መንገድ መመልከታችን በዚህ ረገድ ራሳችንን እንድንፈትሽና የእሱን ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ይበልጥ ጥረት እንድናደርግ ያነሳሳናል። ኤልያስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኤልያስ 450 የበኣል ነቢያትን በድፍረት የተጋፈጠ ቢሆንም ንግሥት ኤልዛቤል ልትገድለው እንዳሴረች በሰማ ጊዜ ግን ሸሽቷል። መቶ ሃምሳ ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ወደምትገኘው የቤርሳቤህ ከተማ ከተጓዘ በኋላ ወደ ምድረ በዳ ሄደ። አናት በሚበሳው  ፀሐይ ያደረገው ረጅም ጉዞ ስላደከመው በአንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ ከዚያም “‘ነፍሴን ውሰዳት’ ብሎ ጸለየ።”—1 ነገ. 18:19፤ 19:1-4

ይሖዋ ኤልያስ ያለበትን ሁኔታ ስለተረዳ የሚያበረታታው መልአክ ልኮለታል (አንቀጽ 14, 15ን ተመልከት)

15 ይሖዋ በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠውን ይህን ታማኝ ነቢይ ከሰማይ ሆኖ ሲመለከተው ምን ተሰማው? ለጊዜው በጭንቀት የተዋጠውንና በፍርሃት የተሽመደመደውን አገልጋዩን ችላ ብሎት ይሆን? በፍጹም! ይሖዋ፣ ኤልያስ ያለበትን ሁኔታ በመረዳት አንድ መልአክ ላከለት። መልአኩ፣ እህል እንዲቀምስ ኤልያስን ሁለት ጊዜ አበረታታው። “ሩቅ መንገድ” ስለሚሄድ ኤልያስ ምግብ መብላቱ አስፈላጊ ነበር። (1 ነገሥት 19:5-8ን አንብብ።) ከዚህ መመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ ምንም ዓይነት መመሪያ ከመስጠቱ በፊት ነቢዩን ያዳመጠው ከመሆኑም ሌላ ብርታት እንዲያገኝ የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርጓል።

16, 17. ይሖዋ ለኤልያስ ያሳየው ዓይነት አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ታዲያ አሳቢ የሆነውን አምላካችንን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ምክር ለመስጠት መቸኮል አይኖርብንም። (ምሳሌ 18:13) ባሉበት ሁኔታ ምክንያት “ብዙም ክብር” እንደሌላቸው የሚሰማቸውን የእምነት ባልንጀሮቻችን ስናነጋግር በቅድሚያ ስሜታቸውን እንደተረዳንላቸው የሚያሳይ ነገር ማድረጋችን የተሻለ ነው። (1 ቆሮ. 12:23) ከዚያም የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠት እንችላለን።

17 ቀደም ሲል የተጠቀሰችውን ሲንቲያን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ባሏ እሷንና ሁለት ልጆቿን ጥሎ በሄደ ጊዜ ብቸኝነት ተሰምቷቸው ነበር። ታዲያ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ምን አደረጉ? ሲንቲያ እንዲህ ብላለች፦ “የተፈጠረውን ነገር በስልክ ስንነግራቸው በ45 ደቂቃ ውስጥ ቤታችን መጡ። በሁኔታው በጣም በማዘናቸው አለቀሱ። ከዚያም እስከ ሦስት ቀን ድረስ ትተውን አልሄዱም። በወቅቱ በደንብ አንበላም ነበር፤ እንዲሁም ስሜታዊ ነበርን፤ በመሆኑም ለተወሰነ ጊዜ ቤታቸው የወሰዱን ወንድሞች አሉ። ይህ ሁኔታ ያዕቆብ እንዲህ በማለት የጻፈውን ሐሳብ እንደሚያስታውሰን የታወቀ ነው፦ “አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ቢራቆቱና ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን በቂ ምግብ ባያገኙ ሆኖም ከመካከላችሁ አንዱ ‘በሰላም ሂዱ፣ ይሙቃችሁ፣ ጥገቡም’ ቢላቸው ለሰውነታቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ግን ባትሰጧቸው ምን ይጠቅማቸዋል? ስለዚህ በሥራ ያልተደገፈ እምነትም በራሱ የሞተ ነው።” (ያዕ. 2:15-17) ወንድሞችና እህቶች ለሲንቲያና ለሁለቱ ሴቶች ልጆቿ አስፈላጊውን እርዳታ ስላደረጉላቸው ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ካጋጠማቸው ከስድስት ወር በኋላ ተበረታትተው ረዳት አቅኚ መሆን ችለዋል።—2 ቆሮ. 12:10

ብዙዎችን ይጠቅማል

18, 19. (ሀ) ባጋጠማቸው ችግር የተነሳ ለጊዜው የደከሙ ክርስቲያኖችን እንዴት መርዳት እንችላለን? (ለ) የደከሙትን ስንረዳ ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ነው?

18 አቅም የሚያሳጣ በሽታ ይዞህ የሚያውቅ ከሆነ ለማገገም የተወሰነ ጊዜ እንደሚወስድ ከራስህ ተሞክሮ ተመልክተህ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም ባጋጠመው ችግር ወይም ተፈታታኝ ሁኔታ የተነሳ የደከመ አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ለመበርታት ጊዜ ሊወስድበት ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠመው ክርስቲያን በግል ጥናት፣ በጸሎት ወይም በሌሎች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት እምነቱን ማጠናከር እንዳለበት የታወቀ ነው። ይሁንና ወደ ቀድሞ ሁኔታው እስኪመለስ ድረስ በትዕግሥት እንይዘዋለን? በመንፈሳዊ በሚያገግምበት ወቅት ፍቅር ማሳየታችንን እንቀጥላለን? ባጋጠማቸው ችግር የተነሳ ለጊዜው የደከሙትን ክርስቲያኖች ትልቅ ቦታ እንዳላቸው እንዲሁም እንደምንወዳቸው እንዲያውቁ ለማድረግ እንጥራለን?—2 ቆሮ. 8:8

19 ወንድሞቻችንን ስንረዳቸው በመስጠት ብቻ የሚገኘውን ደስታ ማጣጣም እንደምንችል አትዘንጉ። በተጨማሪም የሌሎችን ስሜት በተሻለ መንገድ መረዳትና ይበልጥ ታጋሾች መሆን እንችላለን። ከዚህ ባለፈም ትልቅ ጥቅም ያስገኛል። መላው ጉባኤ ሞቅ ያለ መንፈስ የሚኖረው ከመሆኑም ሌላ በፍቅር ያድጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እያንዳንዱን ሰው ከፍ አድርጎ የሚመለከተውን ይሖዋን መምሰል እንችላለን። አዎ፣ ሁላችንም ‘ደካማ የሆኑትን እንድንረዳ’ ለቀረበልን ማበረታቻ ምላሽ የምንሰጥበት በቂ ምክንያት አለን።—ሥራ 20:35

^ አን.4 ቻርልስ ዳርዊን የሰው አመጣጥ (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፉ ላይ የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎች “ጥቅም የሌላቸው” እንደሆኑ ገልጾ ነበር። ሌሎች የዝግመተ ለውጥ አራማጆችም ትርፍ አንጀትንና እንጥልን ጨምሮ በሰውነታችን ውስጥ አስፈላጊ ያልሆኑ በርካታ የአካል ክፍሎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

^ አን.7 ስሟ ተቀይሯል።