በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ማይክሮኔዥያ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ማይክሮኔዥያ

ካትሪን ያደገችው በዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን በ16 ዓመቷ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። አገልግሎቷን በቁም ነገር ትመለከት የነበረ ቢሆንም በምትሰብክበት አካባቢ የነበሩ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ያን ያህል ፍላጎት አልነበራቸውም። እንዲህ ትላለች፦ “አምላክ፣ እሱን እንዲያውቁ የሚረዳቸው ሰው እንዲልክላቸው ጸልየው ስለነበሩ ሰዎች የሚገልጹ ተሞክሮዎችን አንብቤያለሁ። እኔም እንዲህ ያሉ ሰዎችን እንዳገኝ ብዙ ጊዜ ብመኝም ያሰብኩት አልሆነም።”

ካትሪን በዚሁ ክልል ለብዙ ዓመታት ስትሰብክ ከቆየች በኋላ የመንግሥቱ መልእክት ይበልጥ ተቀባይ ወደሚያገኝበት አካባቢ ተዛውራ ለማገልገል አሰበች። ይሁን እንጂ በሌላ አገር ማገልገል እንዳይከብዳት ሰግታ ነበር። በሕይወቷ ሁሉ ከቤተሰቧ ተለይታ የምታውቀው አንድ ጊዜ ያውም ለሁለት ሳምንት ብቻ ነው፤ ያን ጊዜም በየቀኑ ቤተሰቧን ትናፍቅ ነበር። ሆኖም ስለ ይሖዋ ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎችን በመርዳት የሚገኘውን ደስታ ለማጣጣም ያላት ልባዊ ፍላጎት ይህን ስጋት ለማሸነፍ አስቻላት። ልትሄድባቸው ስለምትችላቸው የተለያዩ ቦታዎች ካሰበች በኋላ በጉዋም ላለው ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ በመጻፍ የሚያስፈልጋትን መረጃ አገኘች። ከዚያም ሐምሌ 2007፣ የ26 ዓመቷ ካትሪን ከአገሯ 10,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ወደምትገኝ ሳይፓን የምትባል ደሴት ተዛወረች። ታዲያ በዚያ ምን አጋጥሟት ይሆን?

ሁለቱም ጸሎቶች መልስ አገኙ

ካትሪን አዲሱ ጉባኤ ከደረሰች ብዙም ሳትቆይ፣ ዶሪስ ከምትባል በ40ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ከምትገኝ ሴት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ምዕራፎች ካጠኑ በኋላ ካትሪን አንድ ነገር አሳሰባት። እንዲህ ብላለች፦ “ዶሪስ ጥሩ ጥናት ስለነበረች ‘በሚገባ አላስጠናት ይሆን?’ የሚል ስጋት አደረብኝ። ከዚያ በፊት ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መርቼ ስለማላውቅ ዶሪስን የተሻለ ተሞክሮ ያላት ከተቻለም በዕድሜ እኩያዋ የሆነች እህት ብታስጠናት እንደሚሻል ተሰማኝ።” ካትሪን፣ ዶሪስን ለማስጠናት ብቃት ያላት እህት ለማግኘት እንዲረዳት ይሖዋን በጸሎት ጠየቀች። ከዚያም አስጠኚ ልትለውጥላት መሆኑን ለዶሪስ ለመንገር ወሰነች።

ካትሪን እንዲህ ብላለች፦ “ጉዳዩን ከማንሳቴ በፊት ዶሪስ ስለገጠማት አንድ ችግር ልታማክረኝ እንደምትፈልግ ነገረችኝ። ካዳመጥኳት በኋላ በሕይወቴ ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታ ባጋጠመኝ ወቅት ችግሩን ለመወጣት ይሖዋ እንዴት እንደረዳኝ ገለጽኩላት። ዶሪስም አመሰገነችኝ።” ከዚያም ዶሪስ ለካትሪን እንዲህ አለቻት፦ “ይሖዋ እኔን ለመርዳት በአንቺ እየተጠቀመ ነው። መጀመሪያ ወደ ቤቴ የመጣሽ ቀን መጽሐፍ ቅዱሴን ለብዙ ሰዓታት ሳነብ ነበር። አምላክ፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንድረዳ የሚያግዘኝ ሰው እንዲልክልኝ እያለቀስኩ ለምኜው ነበር። ከዚያም አንቺ በሬን አንኳኳሽ። ይሖዋ ጸሎቴን መልሶልኛል!” ካትሪን ይህን  ልብ የሚነካ ታሪክ በምትናገርበት ጊዜ ዓይኖቿ እንባ ያቀርራሉ። እንዲህ ትላለች፦ “ዶሪስ የተናገረቻቸው ቃላት የጸሎቴ መልስ ነበሩ። ይሖዋ እሷን ማስጠናቴን መቀጠል እንደምችል እንድገነዘብ አድርጎኛል።”

ዶሪስ በ2010 የተጠመቀች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እሷም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ትመራለች። ካትሪን “ቅን ልብ ያለው ሰው የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆን ለመርዳት የነበረኝ የረጅም ጊዜ ምኞት በመፈጸሙ እጅግ አመስጋኝ ነኝ!” ብላለች። በዛሬው ጊዜ ካትሪን ኮስሬ በሚባል የፓስፊክ ደሴት ልዩ አቅኚ ሆና በደስታ ታገለግላለች።

ሦስት ተፈታታኝ ሁኔታዎች —መወጣት የሚቻለው እንዴት ነው?

ከተለያዩ አገራት የመጡ ከመቶ የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች (ከ19 እስከ 79 ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ) የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት በማይክሮኔዥያ እያገለገሉ ነው። የእነዚህን ቀናተኛ አገልጋዮች ስሜት በ2006 በ19 ዓመቷ ወደ ጉዋም የተዛወረችው ኤሪካ ጥሩ አድርጋ ገልጻዋለች። እንዲህ ብላለች፦ “እውነትን የተጠሙ ሰዎች ባሉበት ክልል ውስጥ አቅኚ ሆኖ ማገልገል በጣም ያስደስታል። ይሖዋ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ እንድሰማራ ስለረዳኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። በሕይወቴ ውስጥ ላከናውነው የምችለው ከሁሉ የተሻለ ነገር ይህ ነው!” በአሁኑ ጊዜ ኤሪካ በማርሻል ደሴቶች በምትገኘው በኢባይ ልዩ አቅኚ ሆና በማገልገል ደስታ እያገኘች ነው። እርግጥ ነው፣ በውጭ አገር ማገልገል ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አሉት። እስቲ ከእነዚህ ተፈታታኝ ችግሮች ውስጥ ሦስቱን እናንሳና ወደ ማይክሮኔዥያ ሄደው የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች እንዴት እንደተቋቋሟቸው እንመልከት።

ኤሪካ

የአኗኗር ለውጥ። በ2007 ወደ ፓላው ደሴት የሄደው የ22 ዓመቱ ሳይመን እዚያ ሠርቶ የሚያገኘው ገቢ በትውልድ አገሩ በእንግሊዝ ሳለ ከሚያገኘው ገቢ ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ መሆኑን ብዙም ሳይቆይ ተገነዘበ። እንዲህ ብሏል፦ “የፈለግሁትን ሁሉ መግዛት እንደማልችል መማር ነበረብኝ። አሁን ምን ዓይነት ምግቦችን መግዛት እንዳለብኝ በጥንቃቄ ከመረጥኩ በኋላ ዋጋው የሚቀንስበትን ቦታ ለማግኘት እሞክራለሁ። አንድ ነገር ሲበላሽብኝ ያገለገሉ መለዋወጫዎች እንዲሁም የሚጠግንልኝ ሰው ለማግኘት እጥራለሁ።” ታዲያ አኗኗሩን ቀላል በማድረጉ ምን ትምህርት አግኝቷል? ሳይመን እንዲህ ይላል፦ “በሕይወት ውስጥ የግድ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ እንዲሁም በአነስተኛ ገቢ እንዴት መኖር እንደምችል ተምሬያለሁ። በተለያዩ ጊዜያት የይሖዋን እጅ በግልጽ ተመልክቻለሁ። እዚህ ባገለገልኩባቸው ሰባት ዓመታት፣ የምበላው ነገርና የማድርበት ቦታ አጥቼ አላውቅም።” በእርግጥም ይሖዋ መንግሥቱን ለማስቀደም ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል የሚያደርጉ ክርስቲያኖችን ይደግፋል።—ማቴ. 6:32, 33

ናፍቆት። ኤሪካ እንዲህ ትላለች፦ “ከቤተሰቤ ጋር በጣም ስለምቀራረብ ናፍቆት በአገልግሎቴ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት ነበረኝ።” ታዲያ ራሷን ለማዘጋጀት ምን አደረገች? “ወደ ሌላ አገር ከመዛወሬ በፊት ስለ ናፍቆት የሚገልጹ መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡ ርዕሶችን አነበብኩ። ይህም ናፍቆት የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም እንድዘጋጅ በጣም ረድቶኛል። ካነበብኳቸው ርዕሶች በአንዱ ላይ አንዲት እናት ልጇን ‘ከእኔ ይልቅ ይሖዋ በተሻለ ሁኔታ ሊንከባከብሽ ይችላል’ እንዳለቻት ተገልጿል። ይህ ሐሳብ እኔንም በጣም አጠንክሮኛል።” ሐና እና ባሏ ፓትሪክ በማርሻል ደሴቶች በምትገኘው በማጁሮ ያገለግላሉ። ሐና ናፍቆትን ለመቋቋም የረዳት በጉባኤያቸው  ላሉ ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ ትኩረት ለመስጠት ጥረት ማድረጓ ነው። እንዲህ ትላለች፦ “ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር ስለሰጠን ይሖዋን ዘወትር አመሰግነዋለሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞችም ቤተሰቦቼ ናቸው። እነሱ በፍቅር ባይደግፉኝ ኖሮ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል አልችልም ነበር።”

ሳይመን

መላመድ። ሳይመን “ወደ ሌላ አገር ስትሄዱ ሁሉም ነገር አዲስ ይሆንባችኋል” በማለት ይናገራል። “አንዳንድ ጊዜ፣ የምናገረው ቀልድ በደንብ ከሚገባቸው ሰዎች ጋር ብሆን ብዬ እመኛለሁ።” ኤሪካ ደግሞ እንዲህ ትላለች፦ “መጀመሪያ ላይ ከሌሎች ጋር መቀላቀል እንዳልቻልኩ ይሰማኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አጋጣሚ ወደዚህ የተዛወርኩት ለምን እንደሆነ እንዳስብ አድርጎኛል። ወደዚህ የመጣሁት የራሴን ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን ለይሖዋ የበለጠ ለመሥራት ነው።” አክላም “ከጊዜ በኋላ ጥሩ ጓደኞች ያገኘሁ ሲሆን ወዳጅነታችንን ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ” ብላለች። ሳይመን የፓላውን ቋንቋ ለመማር ከፍተኛ ጥረት አደረገ፤ ይህም ለአካባቢው ወንድሞችና እህቶች ‘ልቡን ወለል አድርጎ እንዲከፍት’ አስችሎታል። (2 ቆሮ. 6:13) ቋንቋውን ለመማር ያደረገው ጥረት በአካባቢው ወንድሞች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎለታል። በእርግጥም ከሌላ አገሩ የመጡትም ሆኑ የአካባቢው ወንድሞች ተባብረው መሥራታቸው በጉባኤው ውስጥ የቅርብ ወዳጆች ለማፍራት ያስችላቸዋል። የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ወንድሞችና እህቶች የሚያገኟቸው ሌሎች ወሮታዎችስ ምንድን ናቸው?

‘በብዛት ማጨድ’

ሐዋርያው ጳውሎስ “በብዛት የሚዘራ . . . በብዛት እንደሚያጭድ” ተናግሯል። (2 ቆሮ. 9:6) በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት አገልግሎታቸውን ለማስፋት ጥረት በሚያደርጉ ወንድሞችና እህቶች ላይ እንደሚፈጸም የተረጋገጠ ነው። ታዲያ ወደ ማይክሮኔዥያ የሄዱት ክርስቲያኖች ‘በብዛት እያጨዱ’ ያሉት ምን ዓይነት ፍሬ ነው?

ፓትሪክና ሐና

አሁንም ቢሆን በማይክሮኔዥያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለማስጀመር እንዲሁም ከአምላክ ቃል የተማሩትን እውነት በሥራ ላይ የሚያውሉ ግለሰቦች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ አለ። ፓትሪክና ሐና አንጋኡር በምትባል 320 ነዋሪዎች ባሉባት አንዲት ትንሽ ደሴትም ሰብከዋል። ለሁለት ወራት ከሰበኩ በኋላ አንዲት ነጠላ እናት አገኙ። እሷም ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማማች ሲሆን እውነትን በጉጉት በመቀበል በሕይወቷ ውስጥ ትላልቅ ለውጦችን አደረገች። ሐና እንዲህ ብላለች፦ “ከእያንዳንዱ ጥናት በኋላ ከቤቷ ወጥተን በብስክሌታችን ወደ ቤታችን ስንመለስ እርስ በርስ እንተያይና ‘ይሖዋ እናመሰግንሃለን!’ እንል ነበር። ይሖዋ ይህችን ሴት በሆነ መንገድ ወደ ራሱ መሳቡ እንደማይቀር አውቃለሁ፤ ያም ቢሆን ይህችን በግ መሰል ሴት ማግኘትና ይሖዋን እንድታውቅ መርዳት የቻልነው የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ በማገልገላችን ነው። በሕይወታችን ሙሉ ካጋጠሙን እጅግ አስደሳች ተሞክሮዎች አንዱ ይህ ነው!” ኤሪካ እንደተናገረችው “አንድ ሰው ይሖዋን እንዲያውቅ ስትረዱ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ደስታ ታጭዳላችሁ!”

አንተስ የበኩልህን ድርሻ ማበርከት ትችላለህ?

በብዙ አገሮች ተጨማሪ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ያስፈልጋሉ። አንተም እርዳታ ማበርከት ወደሚያስፈልግባቸው አካባቢዎች ሄደህ ማገልገል ትችል ይሆን? አገልግሎትህን ለማስፋት ያለህን ፍላጎት እንዲያጠናክርልህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው። ጉዳዩን በጉባኤህ ካሉ ሽማግሌዎች፣ ከወረዳ የበላይ ተመልካቹ ወይም ተጨማሪ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደው የማገልገል መብት ካገኙ ወንድሞችና እህቶች ጋር ተወያይበት። ዕቅድ ማውጣት ስትጀምር፣ ልታገለግል የምትፈልግበትን ክልል ወደሚመለከተው ቅርንጫፍ ቢሮ ጽፈህ ተጨማሪ መረጃ ጠይቅ። * ራሳቸውን በፈቃደኝነት በማቅረብ ‘በብዛት የሚያጭዱ’ ወጣትም ሆኑ አረጋውያን እንዲሁም ያገቡም ሆኑ ያላገቡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች አሉ፤ አንተም ከእነሱ መካከል አንዱ መሆን ትችል ይሆናል።

^ አን.17 በነሐሴ 2011 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን “‘ወደ መቄዶንያ መሻገር’ ትችላለህ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።