በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሕይወት ታሪክ

አባቴን ባጣም አባት አግኝቻለሁ

አባቴን ባጣም አባት አግኝቻለሁ

አባቴ የተወለደው በግራትስ፣ ኦስትሪያ በ1899 ነው፤ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ገና ወጣት ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 ከፈነዳ ብዙም ሳይቆይ በጀርመን ሠራዊት ውስጥ እንዲያገለግል ተመለመለ። በ1943 ሩሲያ ውስጥ በውጊያ ላይ ሳለ ሞተ። የሚያሳዝነው፣ ገና የሁለት ዓመት ሕፃን ሳለሁ በዚህ ሁኔታ አባቴን በሞት አጣሁ። በመሆኑም አባቴን ለማወቅ አጋጣሚ አላገኘሁም፤ በተለይ ደግሞ አብረውኝ የሚማሩት አብዛኞቹ ልጆች አባት እንዳላቸው ሳውቅ እኔ አባት የሌለኝ መሆኑ በጣም ይሰማኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለሁ ፈጽሞ ስለማይሞተውና ከሁሉ ስለላቀው ስለ ሰማዩ አባታችን መማሬ አጽናናኝ።—ዕን. 1:12 NW

የቦይ ስካውት አባል ሆንኩ

ትንሽ ልጅ ሳለሁ

ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ቦይ ስካውት የተባለ የወጣቶች እንቅስቃሴ አባል ሆንኩ። ቦይ ስካውት የብሪታንያ ሠራዊት ሌተና ጄኔራል የነበረው ሮበርት ስቲቨንሰን ስሚዝ ቤደን-ፖል በታላቋ ብሪታንያ በ1908 ያቋቋመው ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው። ይህ ሰው፣ በእኔ ዕድሜ ለሚገኙ ትናንሽ ልጆች ዉልፍ ከብ (ወይም ከብ ስካውት) የተባለውን ቡድን በ1916 አቋቁሞ ነበር።

በሳምንቱ መጨረሻ ቀኖች ከከተማ ወጣ ብለን ከቡድኑ ጋር የምናሳልፈው ጊዜ ያስደስተኝ ነበር፤ በዚያ ወቅት የምናድረው ድንኳኖች ውስጥ ሲሆን የደንብ ልብስ ለብሰን ከበሮ እየተመታ በሰልፍ እንሄድ ነበር። በተለይ ምሽት ላይ እሳት ካቀጣጠልን በኋላ በዙሪያው ሆነን መዘመርና በጫካው ውስጥ መጫወትን ጨምሮ ከሌሎች ስካውቶች ጋር የማሳልፈው ጊዜ ያስደስተኝ ነበር። በተጨማሪም ስለ ተፈጥሮ ብዙ ነገር መማራችን የፈጣሪያችንን ሥራ እንዳደንቅ አድርጎኛል።

የቦይ ስካውት አባላት በየዕለቱ መልካም ተግባር እንዲፈጽሙ ይበረታቱ ነበር። ዋና መመሪያቸው ይህ ነበር። እርስ በርሳችን ሰላምታ ስንለዋወጥ “ምንጊዜም ዝግጁ” የምንባባል ሲሆን ይህን በጣም እወደው ነበር። ከመቶ በላይ ወንዶች ልጆችን ባቀፈው ቡድናችን ውስጥ ግማሽ የምንሆነው ካቶሊኮች፣ ከፊሎቹ ደግሞ ፕሮቴስታንቶች ሲሆኑ አንዱ የቡድሂዝም እምነት ተከታይ ነበር።

ከ1920 ጀምሮ በየተወሰኑ ዓመታት ዓለም አቀፍ የስካውት ስብሰባ (ጃምቦሪ) ይካሄዳል። በባት ኢሽል፣ ኦስትሪያ ነሐሴ 1951 በተደረገው ሰባተኛው የዓለም ስካውት ጃምቦሪ እና በበርሚንግሃም፣ እንግሊዝ አቅራቢያ በሚገኘው በሰተን ፓርክ ነሐሴ 1957 በተካሄደው ዘጠነኛው የዓለም ስካውት ጃምቦሪ ላይ ተገኝቼ ነበር። በሰተን ፓርክ ባደረግነው ስብሰባ ላይ ከ85 አገሮችና ክልሎች የመጡ 33,000 የሚያህሉ ስካውቶች ተገኝተው ነበር። በተጨማሪም በዚህ ጃምቦሪ ላይ እያለን የእንግሊዟን ንግሥት ኤልሳቤጥን ጨምሮ 750,000 ሰዎች ጎብኝተውናል። ያን ጊዜ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ እንዳለሁ ተሰምቶኝ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ከዚያ ይበልጥ አስደናቂ የሆነ መንፈሳዊ የወንድማማች ኅብረት አባል እንደምሆን በወቅቱ አላወቅሁም ነበር።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ መገናኘት

መጀመሪያ የመሠከረልኝ ኬክ ጋጋሪ የነበረው ሩዲ ችገርል ነው

በ1958 ጸደይ ላይ በግራትስ፣ ኦስትሪያ በሚገኘው ቪስለ ግራንድ ሆቴል የምወስደውን የአስተናጋጅነት ሥልጠና  ወደማጠናቀቁ ተቃርቤ ነበር። እዚያም በሆቴሉ ውስጥ ኬክ የሚጋግር ሩዶልፍ ችገርል የተባለ የሥራ ባልደረባዬ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሠከረልኝ። ከዚያ በፊት ስለ እውነት ምንም ነገር ሰምቼ አላውቅም ነበር። ሩዶልፍ መጀመሪያ ያነሳው የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ነገረኝ። እኔም ሥላሴን በመደገፍ ተከራከርኩት፤ መሳሳቱን ላሳየው ፈልጌ ነበር። የሥራ ባልደረባዬን ስለምወደው ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለስ ላሳምነው አስቤ ነበር።

ሩዲ ብለን የምንጠራው ሩዶልፍ መጽሐፍ ቅዱስ አመጣልኝ። የምፈልገው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያሳተመችውን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ነግሬው ነበር። መጽሐፍ ቅዱሱን ማንበብ ከጀመርኩ ብዙም ሳይቆይ፣ ሩዲ የሰጠኝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስቀመጠውን ዋች ታወር ሶሳይቲ ያሳተመው አንድ ትራክት አገኘሁ። እንዲህ ያለ ጽሑፍ ትክክል ያልሆነውን ነገር ትክክል እንደሆነ በሚያሳምን መልኩ ሊያስቀምጥ እንደሚችል ስላሰብኩ ትራክቱን ለማንበብ አልፈለግኩም። ይሁን እንጂ ከሩዲ ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ ነበርኩ። ሩዲ ስሜቴ ስለገባው ከዚያ በኋላ ምንም ዓይነት ጽሑፍ አልሰጠኝም። ለሦስት ወራት ያህል አልፎ አልፎ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እናደርግ ነበር፤ ውይይቱ እስከ ሌሊት የሚቆይበት ጊዜ ነበር።

በትውልድ ከተማዬ በግራትስ በሚገኘው ሆቴል የምወስደውን ሥልጠና ሳጠናቅቅ እናቴ የሆቴል አስተዳደር ትምህርት በሚሰጥበት ትምህርት ቤት ሥልጠናዬን እንድቀጥል የሚያስፈልገውን ወጪ ሸፈነችልኝ። በመሆኑም ትምህርት ቤቱ ወዳለበት በአልፕስ ተራሮች ሥር ወደሚገኝ ባት ሆፍጋስታይን የተባለ ከተማ ሄድኩ። ትምህርት ቤቱ በባት ሆፍጋስታይን ካለው ግራንድ ሆቴል ጋር ግንኙነት ስለነበረው በክፍል ውስጥ ከምማረው ያለፈ ልምድ ለማግኘት አንዳንድ ጊዜ በዚያ እሠራ ነበር።

ሁለት ሚስዮናውያን እህቶች ሊጠይቁኝ መጡ

በ1958 ከኢልዘ ኡንተርደርፈር እና ኤልፍሬደ ሉር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ

ሩዲ አዲሱን አድራሻዬን በቪየና ላለው ቅርንጫፍ ቢሮ ልኮት ነበር፤ ቢሮው ደግሞ አድራሻዬን ኢልዘ ኡንተርደርፈር እና ኤልፍሬደ ሉር ለሚባሉ ሁለት ሚስዮናውያን እህቶች ላከው። * አንድ ቀን የሆቴሉ እንግዳ ተቀባይ ጠራኝና ሁለት ሴቶች ሊያነጋግሩኝ ፈልገው ውጭ መኪና ውስጥ እየጠበቁ እንደሆነ ነገረኝ። ስለ እነሱ የማውቀው ነገር ስላልነበረ ግራ ገባኝ። ይሁን እንጂ እነማን እንደሆኑ ለማየት ወደ እነሱ ሄድኩ። ከጊዜ በኋላ መገንዘብ እንደቻልኩት እነዚህ እህቶች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በናዚ ጀርመን ውስጥ የስብከቱ ሥራ ታግዶ በነበረበት ጊዜ ጽሑፎች በማድረስ አገልግለዋል። ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊትም እንኳ በጀርመን የሚስጥር ፖሊሶች (ጌስታፖ) ተይዘው ወደ ሊሽተንበርግ ማጎሪያ ካምፕ ተልከው ነበር። ከዚያም በጦርነቱ ወቅት፣ በበርሊን አቅራቢያ ወደሚገኘው ራቨንስብሩክ ካምፕ ተዛውረው ነበር።

እነዚህ እህቶች በእናቴ ዕድሜ አካባቢ ስለነበሩ ላከብራቸው እንደሚገባ ተሰማኝ። በመሆኑም ከእነሱ ጋር ጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት ስወያይ ቆይቼ ውይይቱን መቀጠል እንደማልፈልግ ብነግራቸው ጊዜያቸውን ማባከን እንደሚሆን አሰብኩ። ስለዚህ ስለ ሐዋርያዊ ተተኪነት ከሚገልጸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር የተያያዙ ጥቅሶችን በዝርዝር ጽፈው ካመጡልኝ በቂ እንደሆነ ነገርኳቸው። ጥቅሶቹን በአካባቢው ከሚገኝ ቄስ ጋር እንደምወያይባቸውም ገለጽኩላቸው። በዚህ መንገድ እውነቱን ማወቅ እንደምችል አስቤ ነበር።

በሰማይ ስላለው እውነተኛው ቅዱስ አባት ማወቅ

ስለ ሐዋርያዊ ተተኪነት የሚገልጸው የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሥልጣን ከሐዋርያው  ጴጥሮስ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እንደሆነ ይገልጻል። (ቤተ ክርስቲያኗ በማቴዎስ 16:18, 19 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ የተሳሳተ ትርጉም ሰጥታዋለች።) በተጨማሪም የካቶሊክ ሃይማኖት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በመንበረ ሥልጣናቸው (ኤክስ ካቲድራ) ላይ እያሉ ከመሠረተ ትምህርት ጋር በተያያዘ በሚናገሩት ነገር ረገድ ፈጽሞ እንደማይሳሳቱ ይገልጻል። እኔም በዚህ አምን ነበር፤ በመሆኑም ካቶሊኮች ቅዱስ አባት ብለው የሚጠሯቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በመሠረተ ትምህርቶች ረገድ የማይሳሳቱ ከሆነና ሥላሴ እውነት እንደሆነ ከተናገሩ ይህ ትምህርት እውነት መሆን አለበት ብዬ አስብ ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ሊሳሳቱ የሚችሉ ከሆነ ግን ይህ ትምህርትም ሐሰት ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር፣ ብዙ ካቶሊኮች የሐዋርያዊ ተተኪነት ትምህርትን ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት መሆኑ አያስደንቅም፤ ምክንያቱም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸው ሌሎቹ መሠረተ ትምህርቶች ትክክል ወይም ስህተት መሆናቸው የተመካው በዚህ ላይ ነው!

ቄሱን ሄጄ ሳነጋግራቸው ጥያቄዎቼን ሊመልሱልኝ አልቻሉም፤ ከዚህ ይልቅ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሐዋርያዊ ተተኪነት የምታስተምረውን መሠረት ትምህርት የሚያብራራ አንድ መጽሐፍ ከመጽሐፍ መደርደሪያቸው ላይ አንስተው ሰጡኝ። እኔም እሳቸው ባቀረቡልኝ ሐሳብ መሠረት መጽሐፉን ቤቴ ወስጄ አነበብኩት፤ ተጨማሪ ጥያቄዎች ስለተፈጠሩብኝ ወደ ቄሱ ተመልሼ ሄድኩ። በመጨረሻም ቄሱ ጥያቄዎቼን መመለስ ባለመቻላቸው “እኔ ላሳምንህ አልችልም፤ አንተም ልታሳምነኝ አትችልም። . . . መልካሙን ሁሉ እመኝልሃለሁ!” አሉኝ። ከዚያ በኋላም ከእኔ ጋር ውይይት ማድረግ አልፈለጉም።

በዚህ ጊዜ ከኢልዘ እና ኤልፍሬደ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማሁ። እነሱም በሰማይ ስላለው እውነተኛው ቅዱስ አባት ይኸውም ስለ ይሖዋ አምላክ ብዙ ነገር አስተማሩኝ። (ዮሐ. 17:11) በዚያን ጊዜ በአካባቢው ጉባኤ ገና አልተቋቋመም፤ በመሆኑም ሁለቱ እህቶች ስብሰባ የሚያደርጉት ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ባሳየ አንድ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር። በስብሰባው ላይ የሚገኙት በጣም ጥቂት ሰዎች ነበሩ። ስብሰባውን መምራት የሚችል አንድም የተጠመቀ ወንድም ስላልነበረ እህቶች በስብሰባ ላይ ከሚወሰደው ትምህርት አብዛኛውን እርስ በርስ እየተወያዩ ያቀርቡት ነበር። አልፎ አልፎ ከሌላ ቦታ አንድ ወንድም ሲመጣ ሌላ መሰብሰቢያ ቦታ እንከራይና በዚያ የሕዝብ ንግግር ያቀርብልን ነበር።

አገልግሎት መጀመር

ከኢልዘ እና ኤልፍሬደ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመርኩት ጥቅምት 1958 ሲሆን ከሦስት ወራት በኋላ ይኸውም ጥር 1959 ተጠመቅሁ። ከመጠመቄ በፊት የስብከቱ ሥራ እንዴት እንደሚከናወን ለማየት አብሬያቸው ከቤት ወደ ቤት መሄድ እችል እንደሆነ ጠየቅኋቸው። (ሥራ 20:20) ለመጀመሪያ ጊዜ አብሬያቸው ካገለገልኩ በኋላ የራሴ የአገልግሎት ክልል እንዲሰጡኝ ጠየቅኋቸው። እነሱም አንድ መንደር ውስጥ እንዳገለግል መደቡኝ፤ ብቻዬን እዚያ እየሄድኩ ከቤት ወደ ቤት እሰብክ እንዲሁም ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ አደርግ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት አብሬው ያገለገልኩት ወንድም ከጊዜ በኋላ ሊጎበኘን የመጣው የወረዳ የበላይ ተመልካች ነው።

በ1960 የሆቴል ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ ዘመዶቼ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ ለመርዳት ወደ ትውልድ ከተማዬ ተመልሼ ሄድኩ። እስካሁን ድረስ አንዳቸውም ወደ እውነት አልመጡም፤ ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ መጠነኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኩት ሕይወት

በ20ዎቹ ዕድሜ ሳለሁ

በ1961 ቅርንጫፍ ቢሮው፣ አቅኚነትን የሚያበረታቱ ደብዳቤዎች ለጉባኤዎች ልኮ ነበር። እኔም ያላገባሁ ከመሆኔም ሌላ ሙሉ ጤንነት ስላለኝ አቅኚ መሆን የማልችልበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ተሰማኝ። ለአቅኚነት የምጠቀምበት መኪና መግዛት እንድችል ተጨማሪ ጥቂት ወራት መሥራት እንደምፈልግ የወረዳ የበላይ ተመልካች ለሆነው ለወንድም ኩርት ኩን  ነገርኩት። እሱም “ኢየሱስና ሐዋርያቱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሰማራት መኪና አስፈልጓቸው ነበር?” አለኝ። ይህ ውሳኔ እንዳደርግ ረዳኝ። በተቻለ መጠን ቶሎ አቅኚነት ለመጀመር ዕቅድ አወጣሁ። ይሁን እንጂ በአንድ ሆቴል ውስጥ በየሳምንቱ 72 ሰዓት እሠራ ስለነበረ በቅድሚያ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ነበረብኝ።

አለቃዬን በ72 ሰዓት ፈንታ 60 ሰዓት እንድሠራ ይፈቅድልኝ እንደሆነ ጠየቅሁት። እሱም ደሞዜ ሳይቀነስ ይህን እንዳደርግ ፈቀደልኝ። ትንሽ ቆይቼ ደግሞ በሳምንት 48 ሰዓት እንድሠራ ይፈቅድልኝ እንደሆነ ጠየቅሁት። አሁንም የጠየቅሁትን የፈቀደልኝ ሲሆን ደሞዜ ሳይቀነስ በዚያው ቀጠለ። ቀጥዬ ደግሞ በሳምንት 36 ሰዓት ወይም ለ6 ቀናት በቀን 6 ሰዓት ብቻ እንድሠራ እንዲፈቀድልኝ ጠየቅሁ፤ ይህም ተፈቀደልኝ። የሚገርመው ነገር አሁንም ደሞዜ አልተቀነሰም! አለቃዬ ሥራዬን እንድለቅ የፈለገ አይመስልም። በዚህ ፕሮግራም እየሠራሁ የዘወትር አቅኚነት ጀመርኩ። በዚያን ጊዜ አቅኚዎች በየወሩ እንዲያገለግሉ የሚጠበቅባቸው 100 ሰዓት ነበር።

ከአራት ወራት በኋላ በከሪንቲያ ግዛት ሽፒታል አን ዴር ድራው በተባለ ከተማ በሚገኝ አንድ አነስተኛ ጉባኤ ውስጥ ልዩ አቅኚ እንዲሁም የጉባኤ አገልጋይ (አሁን የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ይባላል) ሆኜ ተሾምኩ። በዚያን ጊዜ ልዩ አቅኚዎች በየወሩ 150 ሰዓት እንዲያገለግሉ ይጠበቅባቸው ነበር። አብሮኝ የሚያገለግል አቅኚ አልነበረም፤ ይሁን እንጂ በወቅቱ ረዳት የጉባኤ አገልጋይ (አሁን ጸሐፊ ይባላል) የነበረችው ገርትሩደ ሎብነር የምትባል እህት በአገልግሎት ብዙ ረድታኛለች።

ቶሎ ቶሎ የሚለዋወጡ ምድቦች

በ1963 በወረዳ ሥራ እንድካፈል ተጋበዝኩ። አንዳንድ ጊዜ ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው የምጓዘው በባቡር ሲሆን ከባድ ሻንጣዎችን እይዝ ነበር። በወቅቱ አብዛኞቹ ወንድሞች መኪና ስላልነበራቸው ወደ ባቡር ጣቢያው መጥቶ በመኪና የሚወስደኝ አልነበረም። እኔ ደግሞ “ይታይልኝ” ማለት እንዳይሆንብኝ ስለምፈራ ወደማርፍበት ቤት ለመሄድ ታክሲ ከመያዝ ይልቅ በእግሬ እጓዝ ነበር።

በ1965 በ41ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድካፈል ተጋበዝኩ። እኔም ሆንኩ በዚህ ክፍል ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ተማሪዎች አላገባንም ነበር። ከተመረቅሁ በኋላ በትውልድ አገሬ በኦስትሪያ በወረዳ ሥራ እንድቀጥል ስመደብ በጣም ተገረምሁ። ይሁን እንጂ ከዩናይትድ ስቴትስ ከመውጣቴ በፊት ለአራት ሳምንታት ያህል ከአንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጋር እንዳገለግል ተጠየቅሁ። አገልግሎት ከሚወደውና በዚህ ሥራ በጣም ውጤታማ ከነበረው አንቶኒ ኮንቲ የተባለ አፍቃሪ ወንድም ጋር የማገልገል መብት በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ። ከአንቶኒ ጋር በሰሜን ኒው ዮርክ በሚገኘው በኮርንዎል አካባቢ አብረን አገልግለናል።

በሠርጋችን ዕለት

ወደ ኦስትሪያ ስመለስ በተመደብኩበት ወረዳ ውስጥ ቶቬ ሜሬቴ ከምትባል ነጠላ የሆነች ውብ እህት ጋር ተዋወቅሁ። ሜሬቴ ከአምስት ዓመቷ ጀምሮ ያደገችው በእውነት ውስጥ ነው። ወንድሞች እንዴት እንደተገናኘን ሲጠይቁን “ቅርንጫፍ ቢሮው ነው ያመቻቸልን” እያልን እንቀልዳለን። ከአንድ ዓመት በኋላ ሚያዝያ 1967 ተጋባንና አብረን በተጓዥነት ሥራ እንድንቀጥል ተፈቀደልን።

በቀጣዩ ዓመት ይሖዋ በጸጋው አማካኝነት መንፈሳዊ ልጁ አድርጎ እንደተቀበለኝ ተገነዘብኩ። ከሰማዩ አባቴና በሮም 8:15 መሠረት ‘“አባ፣ አባት!” ብለው ከሚጠሩት’ ሁሉ ጋር ያለኝ ልዩ የሆነ ዝምድና የጀመረው በዚህ ጊዜ ነው።

እኔና ሜሬቴ እስከ 1976 ድረስ በወረዳና በአውራጃ ሥራ ላይ አብረን ማገልገላችንን ቀጠልን። አንዳንድ ጊዜ የምናድርባቸው መኝታ ቤቶች ማሞቂያ ስለሌላቸው ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች ይወርድ ነበር። በአንድ ወቅት ከእንቅልፋችን ስንነቃ፣ ወደ ውጭ የምንተነፍሰው አየር በጣም በመቀዝቀዙ አፍንጫችን አካባቢ በነበረው ብርድ ልብስ ላይ በረዶ እንደሠራ  ተመለከትን! በኋላ ግን የሌሊቱን ቅዝቃዜ ለመቋቋም እንዲረዳን አንድ ትንሽ የኤሌክትሪክ ማሞቂያ ይዘን ለመጓዝ ወሰንን። በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ሌሊት መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም ከፈለግን ከበረዶውና ከኃይለኛው ነፋስ ጋር እየታገልን ከቤት ውጭ ወደሚገኘው መጸዳጃ ቤት መሄድ ነበረብን። በተጨማሪም የምናርፍበት የራሳችን ቤት ስላልነበረን አብዛኛውን ጊዜ ሰኞ ሰኞን የምናሳልፈው ሳምንቱን ስናገለግል ባረፍንበት ቤት ነበር። ከዚያም ማክሰኞ ጠዋት ወደ ቀጣዩ ጉባኤ እንጓዛለን።

በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውዷ ባለቤቴ ምንጊዜም ላደረገችልኝ ከፍተኛ ድጋፍ በጣም አመስጋኝ ነኝ። አገልግሎት በጣም ስለምትወድ አገልግሎት እንድትወጣ አንድም ቀን ማበረታታት አስፈልጎኝ አያውቅም። በተጨማሪም ወንድሞችና እህቶችን የምትወድ ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ከልብ ታስባለች። እንዲህ ዓይነት ሰው መሆኗ በጣም ጠቅሞኛል።

በ1976 በቪየና ባለው የኦስትሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል የተጋበዝን ሲሆን እኔም የቅርንጫፍ ኮሚቴው አባል ሆኜ ተሾምኩ። በዚያን ጊዜ የኦስትሪያ ቅርንጫፍ በተለያዩ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ያለውን ሥራ በበላይነት ይከታተል እንዲሁም ወደ እነዚያ አገሮች ጽሑፎችን በድብቅ ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት ያስተባብር ነበር። ይህን ሥራ የሚከታተለው ወንድም ዩርገን ሩንደል ነበር፤ ለሥራው ከፍተኛ ቅንዓት ከነበረው ከዚህ ወንድም ጋር የመሥራት መብት አግኝቼ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በምሥራቅ አውሮፓ በሚነገሩ አሥር ቋንቋዎች የሚካሄደውን የትርጉም ሥራ በበላይነት እንድመራ ተጠየቅሁ። ዩርገንና ባለቤቱ ገርትሩደ በጀርመን ልዩ አቅኚዎች ሆነው አሁንም በታማኝነት እያገለገሉ ነው። ከ1978 ጀምሮ የኦስትሪያው ቅርንጫፍ ቢሮ ፎቶታይፕሴቲንግ በሚባለው ዘዴ በመጠቀም በአንድ አነስተኛ ማተሚያ መጽሔቶችን በስድስት ቋንቋዎች ያትም ነበር። በተጨማሪም የመጽሔት ኮንትራት ላላቸው የተለያዩ አገሮች መጽሔቶችን እንልክ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በጀርመን ቅርንጫፍ ቢሮ ከባለቤቱ ከኢንግሪት ጋር የሚያገለግለው ኦቶ ኩግሊች ከእነዚህ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ቁልፍ ሚና ይጫወት ነበር።

በኦስትሪያ እያለሁ መንገድ ላይ ማገልገልን ጨምሮ በብዙ ዓይነት የስብከት ዘዴዎች እካፈል ነበር

በምሥራቅ አውሮፓ የነበሩት ወንድሞችም የማባዣ ማሽኖችን በመጠቀም አለዚያም ከፊልም ላይ እየወሰዱ በማተም በየአገራቸው ጽሑፎችን ያዘጋጁ ነበር። ያም ሆኖ ከሌሎች አገሮች ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። ይሖዋ ይህ ሥራ እንዳይስተጓጎል ጥበቃ አድርጎለታል፤ በቅርንጫፍ ቢሮ ያለነው ወንድሞችም በአስቸጋሪ ሁኔታዎችና በእገዳ ሥር ለብዙ ዓመታት ያገለገሉትን እነዚህ ታማኝ ወንድሞች በጣም እናደንቃቸዋለን።

በሩማኒያ የተደረገ ለየት ያለ ጉብኝት

የበላይ አካል አባል ከነበረው ከወንድም ቴዎዶር ጃራዝ ጋር በ1989 ወደ ሩማንያ የመሄድ መብት አግኝቼ ነበር። የጉብኝቱ  ዓላማ በዚያ የነበረው በርካታ ወንድሞችን ያቀፈ አንድ ትልቅ ቡድን ከድርጅቱ ጋር እንደገና እንዲቀላቀል መርዳት ነበር። እነዚህ ወንድሞች ከ1949 ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከድርጅቱ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በማቋረጥ የራሳቸውን ጉባኤዎች አቋቁመው ነበር። ሆኖም መስበካቸውንና ማጥመቃቸውን ቀጥለው ነበር። በተጨማሪም በዋናው መሥሪያ ቤት አመራር ሥር እንዳሉት የድርጅቱ አባል የሆኑ ወንድሞች ሁሉ እነሱም በክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸው የተነሳ ታስረው ነበር። በወቅቱ በሩማንያ ሥራችን ታግዶ ስለነበር ቁልፍ ቦታ ካላቸው አራት ሽማግሌዎችና በይሖዋ ድርጅት ከተሾሙ የሩማንያ የአገር ኮሚቴ ተወካዮች ጋር የተገናኘነው በወንድም ፓምፊል አልቡ ቤት በሚስጥር ነበር። በተጨማሪም አስተርጓሚ እንዲሆንልን ከኦስትሪያ ሮልፍ ኬልነርን ይዘን ሄድን።

ውይይቱን በጀመርን በሁለተኛው ሌሊት ወንድም አልቡ አራቱን ሽማግሌዎች ከይሖዋ ድርጅት ጋር እንዲቀላቀሉ ለማሳመን ሲል “ይህን አሁን ካላደረግነው እንዲህ ዓይነት ሌላ ዕድል ላናገኝ እንችላለን” አላቸው። ከዚያ በኋላ 5,000 የሚያህሉ ወንድሞች ከድርጅቱ ጋር ተዋህደዋል። ይህ ለይሖዋ ታላቅ ድል ሲሆን ለሰይጣን ደግሞ ታላቅ ሽንፈት ነበር!

በምሥራቅ አውሮፓ ኮሚኒዝም ከመውደቁ በፊት ይኸውም በ1989 መጨረሻ አካባቢ፣ የበላይ አካሉ እኔና ባለቤቴን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት እንድንዛወር ጋበዘን። ይህ ያልጠበቅነው ነገር ስለነበር በጣም ተደሰትን። ሐምሌ 1990 በብሩክሊን ቤቴል ማገልገል ጀመርን። በ1992 የበላይ አካሉ የአገልግሎት ኮሚቴ ረዳት ሆኜ ተሾምኩ፤ ከሐምሌ 1994 ጀምሮ የበላይ አካል አባል ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።

ትዝታዎችና የወደፊቱ ጊዜ

ከባለቤቴ ጋር በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ

በሆቴል አስተናጋጅነት ከሠራሁ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። አሁን ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን መንፈሳዊ ምግብ በማዘጋጀትና በማሰራጨት ሥራ ላይ የመሳተፍ መብት አግኝቻለሁ። (ማቴ. 24:45-47) በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን ከ50 የሚበልጡ ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበራችንን እንደባረከው ይሰማኛል፤ ይህ የሚፈጥርብኝን ጥልቅ አድናቆትና ደስታ በቃላት መግለጽ ያስቸግረኛል። ስለ ሰማዩ አባታችን ስለ ይሖዋና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት በጥልቀት በምንማርባቸው ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ያስደስተኛል።

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ የሰው ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት እውነትን እንዲያውቁና ከዓለም አቀፉ ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበራችን ጋር በአንድነት ይሖዋን እንዲያገለግሉ እጸልያለሁ። (1 ጴጥ. 2:17) በተጨማሪም የሞቱ ሰዎች ምድር ላይ ሲነሱ ከሰማይ ሆኜ የምመለከትበትንና ከእነሱ መካከል ወላጅ አባቴን የማገኝበትን ጊዜ በናፍቆት እጠባበቃለሁ። አባቴ፣ እናቴና ሌሎች የምወዳቸው ዘመዶቼ በሙሉ በገነት ውስጥ ይሖዋን ለማምለክ እንደሚፈልጉ ተስፋ አደርጋለሁ።

የሞቱ ሰዎች ምድር ላይ ሲነሱ ከሰማይ ሆኜ የምመለከትበትንና ከእነሱ መካከል ወላጅ አባቴን የማገኝበትን ጊዜ በናፍቆት እጠባበቃለሁ

^ አን.15 የሕይወት ታሪካቸውን የኅዳር 1, 1979 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ ተመልከት።