‘በተገቢው ጊዜ ምግብ’ እያገኘህ ነው?
በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የዛሬን ያህል እጅግ ተፈታታኝ የሆነ ዘመን የለም። (2 ጢሞ. 3:1-5) ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ሳንወጣ ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚፈታተኑ ነገሮች በየዕለቱ ያጋጥሙናል። ኢየሱስ እንዲህ ያለ የመከራ ዘመን እንደሚመጣ አስቀድሞ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ተከታዮቹ እስከ መጨረሻው ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን ማበረታቻ እንደሚያገኙ ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ማቴ. 24:3, 13፤ 28:20) እነሱን ለማጠናከር ሲል “በተገቢው ጊዜ” መንፈሳዊ ‘ምግብ’ የሚያቀርብ ታማኝ ባሪያ ሾሟል።—ማቴ. 24:45, 46
ኢየሱስ በ1919 ታማኙን ባሪያ ከሾመበት ጊዜ አንስቶ ከሁሉም ቋንቋዎች የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአምላክ ‘አገልጋዮች’ ወደ አምላክ ድርጅት የጎረፉ ሲሆን መንፈሳዊ ምግብ እየቀረበላቸው ነው። (ማቴ. 24:14፤ ራእይ 22:17) ይሁን እንጂ ይህ ዝግጅት በሁሉም ቋንቋዎች በእኩል መጠን አይገኝም፤ በተጨማሪም በኤሌክትሮኒክ ፎርማት የተዘጋጀውን መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት የሚችለው ሁሉም ሰው አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በjw.org ላይ ብቻ የሚወጡትን ርዕሶችና ቪዲዮዎች ማግኘት የማይችሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ታዲያ አንዳንዶች በመንፈሳዊ ጤናማ ሆነው ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ሳያገኙ ይቀራሉ ማለት ነው? በዚህ ረገድ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አራት ቁልፍ ጥያቄዎችን እንመርምር።
1. ከይሖዋ የምናገኘው ዋነኛ መንፈሳዊ ምግብ ምንድን ነው?
ሰይጣን ኢየሱስን፣ ድንጋዩን ወደ ዳቦ እንዲለውጥ በፈተነው ጊዜ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም” በማለት መልስ ሰጥቷል። (ማቴ. 4:3, 4) የይሖዋ ቃል የሚገኘው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። (2 ጴጥ. 1:20, 21) በመሆኑም ዋነኛው መንፈሳዊ ምግባችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው።—2 ጢሞ. 3:16, 17
የይሖዋ ድርጅት የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን በሙሉ ወይም በከፊል ከ120 በሚበልጡ ቋንቋዎች ያዘጋጀ ሲሆን በየዓመቱ ሌሎች ቋንቋዎች እየተጨመሩ ነው። ከአዲስ ዓለም ትርጉም በተጨማሪም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በሺዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ከመሆኑም ሌላ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ቅጂዎች ተሰራጭተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት ረገድ የተገኘው ይህ አስገራሚ ውጤት ይሖዋ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ካለው ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ከዚህም ሌላ “[ከይሖዋ] እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት” ስለሌለ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ” ሰዎችን ወደ ድርጅቱ እንደሚስባቸውና መንፈሳዊ ምግብ እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዕብ. 4:13፤ ማቴ. 5:3, 6፤ ዮሐ. 6:44፤ 10:14
2. ጽሑፎቻችን መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ረገድ ያላቸው ድርሻ ምንድን ነው?
አንድ ሰው ጠንካራ እምነት ማዳበር ከፈለገ መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ያለፈ ነገር ማድረግ ያስፈልገዋል። የሚያነበውን ነገር መረዳትና የተማረውን ተግባራዊ ማድረግ አለበት። (ያዕ. 1:22-25) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ይህን ሐቅ ተገንዝቦ ነበር። ይህ ሰው የአምላክን ቃል እያነበበ ሳለ ወንጌላዊው ፊልጶስ “ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” ብሎ ጠየቀው። ጃንደረባው “የሚመራኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” በማለት መልስ ሰጠ። (ሥራ 8:26-31) ፊልጶስም ጃንደረባው ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኝ ረዳው። ጃንደረባው በተማረው ነገር ልቡ ስለተነካ ተጠመቀ። (ሥራ 8:32-38) በተመሳሳይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችን የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንድናገኝ ረድተውናል። ልባችን እንዲነካ እንዲሁም የተማርነውን ነገር በተግባር ለማዋል እንድንነሳሳ አድርገዋል።—ቆላ. 1:9, 10
የይሖዋ አገልጋዮች በእነዚህ ጽሑፎች አማካኝነት የተትረፈረፈ ምግብ ስለሚቀርብላቸው መንፈሳዊ ረሃባቸውንና ጥማቸውን ማርካት ችለዋል። (ኢሳ. 65:13) ለምሳሌ ያህል፣ ከ210 በሚበልጡ ቋንቋዎች የሚዘጋጀው መጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ያብራራል፤ ጥልቅ ስለሆኑ መንፈሳዊ እውነቶች ያለንን ግንዛቤ ያሳድግልናል እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንመራ ያነሳሳናል። ንቁ! መጽሔት ደግሞ 100 በሚያህሉ ቋንቋዎች የሚታተም ሲሆን ስለ ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ያለንን እውቀት ያሰፋልናል፤ በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጠቃሚ ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያሳየናል። (ምሳሌ 3:21-23፤ ሮም 1:20) ታማኙ ባሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከ680 በሚበልጡ ቋንቋዎች እያቀረበ ነው! አንተስ በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጊዜ ትመድባለህ? በየወሩ የሚወጡትን አዳዲስ መጽሔቶችና በየዓመቱ በቋንቋህ የሚዘጋጁትን አዳዲስ ጽሑፎች በሙሉ ታነብባለህ?
የይሖዋ ድርጅት፣ ከጽሑፎች በተጨማሪ በሳምንታዊ ስብሰባዎችና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለሚቀርቡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች አስተዋጽኦዎችን ያዘጋጃል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ንግግሮች፣ ድራማዎች፣ ሠርቶ ማሳያዎችና ቃለ ምልልሶች በትኩረት ትከታተላለህ? ይሖዋ በእርግጥም መንፈሳዊ ድግስ እያቀረበልን ነው!—ኢሳ. 25:6
3. ከሚዘጋጁት ጽሑፎች መካከል የተወሰኑትን በቋንቋህ ማግኘት የማትችል ከሆነ በቂ መንፈሳዊ ምግብ አላገኘህም ማለት ነው?
አይደለም። ደግሞም አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ከሌሎች የበለጠ መንፈሳዊ ምግብ የሚያገኙበት ጊዜ መኖሩ ሊያስደንቀን አይገባም። ለምን? ሐዋርያትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሐዋርያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከኖሩ በርካታ ደቀ መዛሙርት የበለጠ ትምህርት አግኝተዋል። (ማር. 4:10፤ 9:35-37) ያም ቢሆን ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በቂ መንፈሳዊ ምግብ አላገኙም ማለት አልነበረም፤ ምክንያቱም የሚያስፈልጋቸውን ያህል አግኝተዋል።—ኤፌ. 4:20-24፤ 1 ጴጥ. 1:8
በተጨማሪም ኢየሱስ ከተናገራቸውና ካደረጋቸው ነገሮች መካከል አብዛኞቹ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ እንዳልሰፈሩ ልብ ሊባል ይገባዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ፤ እነዚህ ሁሉ በዝርዝር ቢጻፉ ዓለም ራሱ የተጻፉትን ጥቅልሎች ለማስቀመጥ የሚበቃ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም” በማለት ጽፏል። (ዮሐ. 21:25) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት የኢየሱስ ተከታዮች ፍጹም ሰው ስለነበረው ስለ ኢየሱስ ከእኛ የበለጠ ቢያውቁም የቀረብን ነገር እንዳለ ሆኖ ሊሰማን አይገባም። ምክንያቱም ይሖዋ የኢየሱስን ፈለግ እንድንከተል የሚያስችል በቂ መረጃ እንዲሰፍርልን አድርጓል።—1 ጴጥ. 2:21
ከዚህም ሌላ ሐዋርያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ጉባኤዎች ስለላኳቸው ደብዳቤዎች አስብ። ጳውሎስ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ውስጥ ቢያንስ አንዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኝ እናውቃለን። (ቆላ. 4:16) ታዲያ ይህ ደብዳቤ ስለሌለን በቂ መንፈሳዊ ምግብ አላገኘንም ማለት ነው? በፍጹም። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ስለሚያውቅ በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነን እንድንቀጥል የሚረዳንን በቂ መረጃ ሰጥቶናል።—ማቴ. 6:8
ይሖዋ የሚያስፈልገንን ስለሚያውቅ በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነን እንድንቀጥል የሚረዳንን በቂ መረጃ ሰጥቶናል
በዛሬው ጊዜ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ከሌሎቹ የበለጠ መንፈሳዊ ምግብ የማግኘት አጋጣሚ አላቸው። አንተ በምትናገረው ቋንቋ የተዘጋጁት ጽሑፎች ጥቂት ናቸው? ከሆነ ይሖዋ ለአንተም እንደሚያስብልህ እርግጠኛ ሁን። ያለህን መንፈሳዊ ምግብ በሚገባ ተመገብ፤ የሚቻል ከሆነ ደግሞ አንተ በምትረዳው ቋንቋ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ጥረት አድርግ። እንዲሁም ይሖዋ በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድትሆን እንደሚረዳህ እምነት ይኑርህ።—መዝ. 1:2፤ ዕብ. 10:24, 25
4. በjw.org ላይ የሚወጡትን ትምህርቶች የማግኘት አጋጣሚ ከሌለህ በመንፈሳዊ ደካማ ትሆናለህ?
በድረ ገጻችን ላይ መጽሔቶቻችንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ሌሎች ጽሑፎች ይገኛሉ። በተጨማሪም ለባለትዳሮች፣ ለወጣቶችና ለወላጆች የሚጠቅሙ ትምህርቶች በድረ ገጹ ላይ ይወጣሉ። ቤተሰቦች እነዚህን ትምህርቶች በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ላይ በማካተት ይጠቀማሉ። ድረ ገጻችን እንደ ጊልያድ ምረቃና ዓመታዊ ስብሰባ ስላሉት ልዩ ፕሮግራሞችም የሚዘግብ ሲሆን የይሖዋ ሕዝቦችን ስለሚነኩ የተፈጥሮ አደጋዎችና ሕግ ነክ ጉዳዮች ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ያሳውቃል። (1 ጴጥ. 5:8, 9) ከዚህም ሌላ ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ለሚኖሩ ሰዎች ጭምር ምሥራቹን ለማዳረስ የሚያስችል ከፍተኛ ኃይል ያለው የስብከት መሣሪያ ነው።
ይሁን እንጂ በድረ ገጻችን የመጠቀም አጋጣሚ ባይኖርህም እንኳ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነህ መኖር ትችላለህ። ባሪያው እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ በመንፈሳዊ በደንብ መመገብ እንዲችል የሚታተሙ ጽሑፎችን ለማዘጋጀት ጠንክሮ ይሠራል። በመሆኑም jw.orgን ለመጠቀም በማሰብ ብቻ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ መግዛት እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። አንዳንድ ወንድሞች በድረ ገጻችን ላይ ከሚወጡት ትምህርቶች መካከል የተወሰኑትን ኢንተርኔት መጠቀም ለማይችሉ ወንድሞች አትመው ይሰጡ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ጉባኤዎች እንዲህ ማድረግ አይጠበቅባቸውም።
ኢየሱስ በመንፈሳዊ የሚያስፈልገንን በማቅረብ እንደሚንከባከበን የገባውን ቃል በመጠበቁ አመስጋኞች ነን። እነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀናት ወደ ፍጻሜያቸው እየቀረቡ ሲሄዱ ይሖዋ “በተገቢው ጊዜ” መንፈሳዊ ‘ምግብ’ ማቅረቡን እንደሚቀጥል ልንተማመን እንችላለን።