‘ተመልሰህ ወንድሞችህን አበርታ’
ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደማያውቀው ከካደ በኋላ ምርር ብሎ አልቅሷል። ሐዋርያው ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ አቋሙ ለመመለስ ጥረት ማድረግ ቢኖርበትም ኢየሱስ ሌሎችን ለመርዳት ሊጠቀምበት ፈልጎ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ “አንተም በተመለስክ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ” አለው። (ሉቃስ 22:32, 54-62) ከጊዜ በኋላ ጴጥሮስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ዓምድ ከነበሩት አንዱ ለመሆን በቅቷል። (ገላ. 2:9) በተመሳሳይም በአንድ ወቅት በሽምግልና ሲያገለግል የነበረ አንድ ወንድም እንደገና ያንን ኃላፊነት መሸከምና የእምነት አጋሮቹን በመንፈሳዊ በማጠናከር ደስታ ማግኘት ይችላል።
በአንድ ወቅት በበላይ ተመልካችነት ያገለገሉ አንዳንድ ወንድሞች ከኃላፊነታቸው ሲወርዱ ሽማግሌ ሆነው ይሖዋን ለማገልገል ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካ ሊሰማቸው ይችላል። በደቡብ አሜሪካ የሚኖረውና ከ20 ዓመት በላይ ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለው ሁልዮ * እንዲህ ብሏል፦ “የሕይወቴ አብዛኛው ክፍል ንግግሮችን በመዘጋጀት፣ ወንድሞችን በመጠየቅና ለጉባኤው አባላት እረኝነት በማድረግ የተሞላ ነበር! ይህ ሁሉ በድንገት ሲቀር በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ክፍተት ተፈጠረ። ያ ወቅት ለእኔ በጣም ከባድ ነበር።” በአሁኑ ጊዜ ሁልዮ እንደገና ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው።
“እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት”
ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 1:2) ያዕቆብ እዚህ ላይ የጠቀሰው ፈተና የሚያመለክተው ስደትንና የራሳችን አለፍጽምና የሚያስከትልብንን ተጽዕኖ ነው። የራስ ወዳድነት ምኞቶችን፣ አድልዎ ማድረግንና የመሳሰሉትን ነገሮች ጠቅሷል። (ያዕ. 1:14፤ 2:1፤ 4:1, 2, 11) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በሚገሥጸን ጊዜ ተግሣጹ ሊያሳዝነን ይችላል። (ዕብ. 12:11) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ተግሣጽ ደስታችንን እንድናጣ ሊያደርገን አይገባም።
በጉባኤ ውስጥ ካለን የኃላፊነት ቦታ ብንወርድም የእምነታችንን ጥንካሬ ለመመርመርና ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳየት አሁንም አጋጣሚው አለን። በተጨማሪም በኃላፊነት ቦታ ላይ ያገለገልንበትን ምክንያት ቆም ብለን ማሰብ እንችላለን። ኃላፊነቱን የተቀበልነው ለራሳችን ጥቅም ስንል ነበር? ወይስ እንዲህ ያለው የአገልግሎት መብት ላይ ለመድረስ የተጣጣርነው ለአምላክ ፍቅር ስላለንና ጉባኤው የእሱ ንብረት በመሆኑ በርኅራኄ ልንንከባከበው ይገባል የሚል እምነት ስለነበረን ነው? (ሥራ 20:28-30) ከዚህ በፊት ሽማግሌ የነበሩ ወንድሞች በደስታ ይሖዋን ማገልገላቸውን ሲቀጥሉ ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር እንዳላቸው በሰይጣንም ሆነ በሌሎች ሰዎች ፊት ያረጋግጣሉ።
ንጉሥ ዳዊት ከባድ ኃጢአት በመፈጸሙ ምክንያት በተገሠጸ ጊዜ ተግሣጹን ስለተቀበለ ይቅርታ ተደርጎለታል። ዳዊት “መተላለፉ ይቅር የተባለለት፣ ኀጢአቱም የተሸፈነለት፣ እንዴት ቡሩክ ነው! እግዚአብሔር ኀጢአቱን የማይቈጥርበት፣ በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው፣ እርሱ ቡሩክ ነው” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 32:1, 2) ተግሣጽ ዳዊትን እንዳጠራውና ለአምላክ ሕዝቦች የተሻለ እረኛ እንዲሆን እንደረዳው ጥርጥር የለውም።
ብዙውን ጊዜ ተመልሰው በሽምግልና የሚያገለግሉ ወንድሞች ከበፊቱ የተሻሉ እረኞች ይሆናሉ። ወደ ኃላፊነት ቦታው የተመለሰ አንድ ወንድም “ስህተት የሚሠሩ ሰዎችን እንዴት መያዝ እንዳለብኝ አሁን የተሻለ ግንዛቤ አግኝቻለሁ” በማለት ተናግሯል። አንድ ሌላ ሽማግሌ ደግሞ “ወንድሞችን የማገልገል መብቴን አሁን ይበልጥ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ” በማለት ተናግሯል።
መመለስ ትችላለህ?
መዝሙራዊው፣ “[ይሖዋ] ሁልጊዜ በደልን አይከታተልም” በማለት ጽፏል። (መዝ. 103:9) በመሆኑም አምላክ ከአሁን በፊት ከባድ ስህተት በሠራ ሰው ላይ እንደገና እምነት አይጥልም ብለን ማሰብ የለብንም። ለብዙ ዓመታት በሽምግልና ሲያገለግል ከቆየ በኋላ መብቱን ያጣው ሪካርዶ እንዲህ ብሏል፦ “ስህተት በመሥራቴ በራሴ በጣም አዝኜ ነበር። ብቃት የለኝም የሚለው ስሜት በድጋሚ የበላይ ተመልካች ሆኜ ወንድሞችን እንዳላገለግል ለረጅም ጊዜ እንቅፋት ሆኖብኝ ነበር። እምነት የሚጣልብኝ መሆኔን እንደገና ማሳየት እንደምችል እርግጠኛ መሆን አቅቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ሌሎችን መርዳት ስለሚያስደስተኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት፣ መንግሥት አዳራሽ ውስጥ ወንድሞችን ማበረታታትና ከእነሱ ጋር በመስክ አገልግሎት መካፈል ችዬ ነበር። ይህም የመተማመን ስሜቴን መልሼ ለማግኘት የረዳኝ ሲሆን አሁን እንደገና ሽማግሌ ሆኜ እያገለገልኩ ነው።”
ቂም መያዝ አንድ ወንድም ሽማግሌ ሆኖ እንዳያገለግል እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል። በዚህ ጊዜ የይሖዋ አገልጋይ የነበረውን የዳዊትን ምሳሌ መከተል የተሻለ ነው፤ ዳዊት በቅናት ከተሞላው ከንጉሥ ሳኦል መሸሽ አስፈልጎት ነበር። ዳዊት በተለያየ ጊዜ ሳኦልን የመበቀል አጋጣሚ ቢያገኝም እንኳ ይህን ከማድረግ ተቆጥቧል። (1 ሳሙ. 24:4-7፤ 26:8-12) ሳኦል ጦርነት ላይ እያለ ሲሞት ዳዊት ያለቀሰለት ሲሆን ሳኦልና ልጁ ዮናታን “የሚወደዱና የሚደነቁ” ሰዎች እንደነበሩ ተናግሯል። (2 ሳሙ. 1:21-23 NW) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ዳዊት በሳኦል ላይ ቂም አልያዘም።
ወንድሞች እንዳልተረዱህ ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደተደረገብህ ከተሰማህ ቂም ላለመያዝ ተጠንቀቅ፤ ካልሆነ ይህ ስሜት አስተሳሰብህን ሊቆጣጠረው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በብሪታንያ 30 ለሚያህሉ ዓመታት ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለው ዊሊያም ከኃላፊነቱ እንዲወርድ ሲደረግ በአንዳንድ ሽማግሌዎች ላይ ቂም ይዞ ነበር። ዊሊያም አስተሳሰቡን ለማስተካከል የረዳው ምን ነበር? እንዲህ ብሏል፦ “የኢዮብን መጽሐፍ ማንበቤ አበረታትቶኛል። ይሖዋ፣ ኢዮብን ከሦስቱ ወዳጆቹ ጋር ሰላም እንዲፈጥር ከረዳው እኔንም ከክርስቲያን ሽማግሌዎች ጋር እንድስማማ እንደሚረዳኝ እርግጠኛ ሆንኩ!”—ኢዮብ 42:7-9
አምላክ እንደገና እረኛ ሆነው የሚያገለግሉትን ይባርካቸዋል
የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ ሆኖ የመጠበቅ ኃላፊነትህን የተውከው በራስህ ፈቃድ ከሆነ ይህን ያደረግህበትን ምክንያት ቆም ብለህ ማሰብህ ተገቢ ነው። ያሉብህ ችግሮች ከአቅምህ በላይ ስለሆኑብህ ነው? ሌሎች ነገሮች በሕይወትህ ውስጥ ቀዳሚ ስፍራ ስለያዙ ነው? በሌሎች አለፍጽምና ተሰናክለህ ነው? ምክንያትህ ምንም ይሁን ምን፣ ሌሎችን ይበልጥ መርዳት የቻልከው ሽማግሌ ሆነህ ስታገለግል እንደነበር አስታውስ። የሰጠሃቸው ንግግሮች ወንድሞችን አጠናክረዋቸዋል፤ ምሳሌነትህ አበረታቷቸዋል፤ እንዲሁም የእረኝነት ጉብኝትህ በፈተናዎቻቸው እንዲጸኑ ረድቷቸዋል። ሽማግሌ ሆነህ በታማኝነት ያከናወንከው ሥራ የይሖዋንም ሆነ የአንተን ልብ አስደስቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 27:11
ይሖዋ ብዙ ወንድሞች ደስታቸውን መልሰው እንዲያገኙና በጉባኤ ውስጥ እንደገና ኃላፊነት ወስደው የማገልገል ምኞታቸውን እንዲያሳኩ ረድቷቸዋል። አንተም በሽምግልና ማገልገል ያቆምከው በራስህ ፈቃድም ይሁን ከኃላፊነትህ ወርደህ፣ እንደገና ‘የበላይ ተመልካች ለመሆን ልትጣጣር’ ትችላለህ። (1 ጢሞ. 3:1) ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖች በአምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀት ተሞልተው “ይሖዋን ሙሉ በሙሉ በማስደሰት ለእሱ በሚገባ ሁኔታ [እንዲመላለሱ]” ‘መጸለዩን አላቋረጠም ነበር።’ (ቆላ. 1:9, 10) እንደገና ሽማግሌ ሆነህ የማገልገል መብት አግኝተህ ከሆነ ይሖዋ ጥንካሬ፣ ትዕግሥትና ደስታ እንዲሰጥህ ጸልይ። በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የአምላክ ሕዝቦች፣ አፍቃሪ ሽማግሌዎች የሚሰጡት መንፈሳዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ወንድሞችህን የማበርታት ችሎታውና ፍላጎቱ አለህ?
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።