የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ፣ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች “አያገቡም እንዲሁም አይዳሩም” በማለት ለሰዱቃውያን ነግሯቸው ነበር። (ሉቃስ 20:34-36) ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ስለ ምድራዊ ትንሣኤ ነው?
ይህ ጥያቄ፣ በተለይም የሚወዱትን የትዳር ጓደኛ በሞት ላጡ ሰዎች ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። እንዲህ ያሉ ሰዎች በአዲሱ ዓለም ከሞት ከተነሳው የትዳር ጓደኛቸው ጋር እንደገና በጋብቻ ለመጣመር ይናፍቁ ይሆናል። ሚስቱ የሞተችበት አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ሚስቴ ትዳራችን ያከተመው በራሳችን ምርጫ አይደለም። ባልና ሚስት ሆነን ለዘላለም ይሖዋን እያገለገልን መኖር እንፈልግ ነበር። ይህ ፍላጎቴ አሁንም አልተለወጠም።” ታዲያ ከሞት የተነሱ ሰዎች ማግባት እንደሚችሉ ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ? በአጭሩ ለመናገር፣ ለዚህ ጥያቄ በእርግጠኝነት መልስ መስጠት አንችልም።
ኢየሱስ ስለ ትንሣኤና ስለ ጋብቻ የተናገረው ሐሳብ ከምድራዊው ትንሣኤ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ለብዙ ዓመታት በጽሑፎቻችን ላይ ስንገልጽ ቆይተናል፤ በተጨማሪም በአዲሱ ዓለም ከሞት የሚነሱ ሰዎች ላያገቡ እንደሚችሉ ይገለጽ ነበር። * (ማቴ. 22:29, 30፤ ማር. 12:24, 25፤ ሉቃስ 20:34-36) ስለዚህ ጉዳይ በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ‘እዚህ ላይ ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ስለ ሰማያዊ ትንሣኤ ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። እስቲ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር በደንብ እንመርምረው።
ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ለእነማን እንደሆነ እንመልከት። (ሉቃስ 20:27-33ን አንብብ።) በትንሣኤ የማያምኑት ሰዱቃውያን ስለ ትንሣኤና ስለ ዋርሳ * ጋብቻ ጥያቄ በማንሳት ኢየሱስን ሊያጠምዱት እየሞከሩ ነበር። ኢየሱስም እንደሚከተለው በማለት መልስ ሰጠ፦ “የዚህ ሥርዓት ልጆች ያገባሉ እንዲሁም ይዳራሉ፤ ሆኖም የሚመጣውን ሥርዓትና የሙታን ትንሣኤን ማግኘት የሚገባቸው አያገቡም እንዲሁም አይዳሩም። እንዲያውም እንደ መላእክት ስለሆኑ ከዚያ በኋላ ሊሞቱ አይችሉም፤ የትንሣኤ ልጆች ስለሆኑም የአምላክ ልጆች ናቸው።”—ሉቃስ 20:34-36
ታዲያ ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ስለ ምድራዊ ትንሣኤ ሊሆን እንደሚችል ቀደም ሲል በጽሑፎቻችን ላይ የተገለጸው ለምንድን ነው? እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስነው በዋነኝነት በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው። አንደኛ፣ ሰዱቃውያን ጥያቄውን ሲያነሱ በአእምሯቸው የያዙት ምድራዊ ትንሣኤን ሊሆን እንደሚችልና ኢየሱስም በዚያው መሠረት መልስ እንደሰጣቸው በማሰብ ነው። ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የሰጠውን መልስ የደመደመው በጥንት ዘመን የኖሩትን አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን በመጥቀስ ሲሆን እነዚህ ታማኝ ሰዎች ያላቸው ተስፋ ደግሞ ትንሣኤ አግኝቶ በምድር ላይ መኖር ነው።—ሉቃስ 20:37, 38
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከላይ ያለውን ሐሳብ የተናገረው ሰማያዊ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎችን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የሚያበቃ መሠረት አለ? እስቲ ኢየሱስ የተናገራቸውን ሁለት ቁልፍ ሐረጎች እንመልከት።
“የሙታን ትንሣኤን ማግኘት የሚገባቸው።” ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ለአምላክ መንግሥት ብቁ ሆነው ተቆጥረዋል።’ (2 ተሰ. 1:5, 11) ቅቡዓን በቤዛው አማካኝነት ሕይወት ማግኘት የሚገባቸው ጻድቃን ተብለው ተጠርተዋል፤ በመሆኑም ሲሞቱ አምላክ ከኃጢአት ነፃ እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ሮም 5:1, 18፤ 8:1) እነዚህ ሰዎች “ደስተኞችና ቅዱሳን” ተብለው የተጠሩ ሲሆን ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ መሄድ የሚገባቸው እንደሆኑ ተደርገው ተቆጥረዋል። (ራእይ 20:5, 6) ከዚህ በተቃራኒ ለምድራዊ ሕይወት ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል “ዓመፀኞች” ይገኙበታል። (ሥራ 24:15) ታዲያ እነዚህ ሰዎች ትንሣኤ “ማግኘት የሚገባቸው” ሊባሉ ይችላሉ?
“ከዚያ በኋላ ሊሞቱ አይችሉም።” ኢየሱስ “ከእንግዲህ አይሞቱም” አላለም። ከዚህ ይልቅ “ከዚያ በኋላ ሊሞቱ አይችሉም” ብሏል። ሌሎች ትርጉሞች ይህን ሐረግ “ከእንግዲህ ሞት አይደርስባቸውም” እና “ሞት ከዚያ በኋላ በእነሱ ላይ ሥልጣን አይኖረውም” በማለት አስቀምጠውታል። ምድራዊ ሕይወታቸውን በታማኝነት የሚያጠናቅቁ ቅቡዓን ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ ሲሄዱ ያለመሞት ባሕርይ ይላበሳሉ፤ ይኸውም ፍጻሜ የሌለውና ሊጠፋ የማይችል ሕይወት ይሰጣቸዋል። (1 ቆሮ. 15:53, 54) ሰማያዊ ትንሣኤ ባገኙት ላይ ሞት ከዚያ በኋላ ምንም ኃይል አይኖረውም። *
እስካሁን ካየናቸው ነጥቦች አንጻር ምን ብለን መደምደም እንችላለን? ኢየሱስ ስለ ማግባትና ስለ ትንሣኤ የተናገረው ሐሳብ የሚሠራው ከሰማያዊው ትንሣኤ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ደግሞ እሱ የተናገራቸው ቃላት ሰማያዊ ሕይወት ለማግኘት ስለሚነሱ ሰዎች ብዙ ነገር ይነግሩናል፤ ይኸውም እነዚህ ሰዎች አያገቡም፣ ሊሞቱ አይችሉም እንዲሁም በአንዳንድ መንገዶች ከመላእክት ማለትም በመንፈሳዊው ዓለም ከሚኖሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር ይመሳሰላሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው መደምደሚያ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያስነሳል።
አንደኛ ነገር፣ ሰዱቃውያን ጥያቄውን ያነሱት ምድራዊ ትንሣኤን በአእምሯቸው ይዘው ሊሆን ይችላል፤ ታዲያ ኢየሱስ ሰማያዊ ትንሣኤን የሚመለከት መልስ የሰጠው ለምንድን ነው? ኢየሱስ፣ ተቃዋሚዎቹ ከሚያስቡት ነገር አንጻር መልስ ያልሰጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ምልክት እንዲያሳያቸው ለጠየቁት አይሁዳውያን “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን ውስጥ አነሳዋለሁ” ብሏቸው ነበር። ኢየሱስ እነሱ የሚያስቡት ስለ ቤተ መቅደሱ ሕንፃ እንደሆነ ሳያውቅ አይቀርም፤ እሱ “ቤተ መቅደስ ሲል ግን ስለ ራሱ ሰውነት መናገሩ ነበር።” (ዮሐ. 2:18-21) ምናልባት ኢየሱስ በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ የተናገረው በትንሣኤም ሆነ በመላእክት ሕልውና ለማያምኑት ቅንነት የጎደላቸው ሰዱቃውያን መልስ መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ ተሰምቶት ይሆናል። (ምሳሌ 23:9፤ ማቴ. 7:6፤ ሥራ 23:8) ኢየሱስ፣ ወደፊት እንዲህ ዓይነቱን ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ ላላቸው ቅን የሆኑ ደቀ መዛሙርቱ ጥቅም ሲል ስለ ሰማያዊው ትንሣኤ የሚገልጸውን እውነት መናገር ፈልጎ ይሆናል።
ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ውይይቱን ሲቋጭ በምድር ላይ ለመኖር ስለሚነሱት ስለ አብርሃም፣ ስለ ይስሐቅና ስለ ያዕቆብ የጠቀሰው ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 22:31, 32ን አንብብ።) ኢየሱስ ስለ እነዚያ ታማኝ ሰዎች ከመጥቀሱ በፊት “የሙታንን ትንሣኤ በተመለከተ” ማለቱን ልብ በል። ይህ የመሸጋገሪያ ሐረግ የውይይቱ አቅጣጫ እንደተቀየረ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ሰዱቃውያኑ እንደሚቀበሏቸው ከሚገልጹት ሙሴ ከጻፋቸው መጻሕፍት ላይ የጠቀሰ ሲሆን ይሖዋ በእሳት በተያያዘው ቁጥቋጦ መካከል ለሙሴ የተናገራቸውን ቃላት በመጠቀም ምድራዊ ትንሣኤ አምላክ የሰጠው የተረጋገጠ ተስፋ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ሰጥቷል።—ዘፀ. 3:1-6
ሦስተኛ፣ ኢየሱስ ስለ ትንሣኤና ስለ መጋባት የተናገረው ሐሳብ የሚሠራው ሰማያዊ ትንሣኤ ለሚያገኙ ሰዎች ከሆነ ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የሚኖሩት ማግባት ይችላሉ ማለት ነው? የአምላክ ቃል ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አይሰጥም። እንዲያውም ኢየሱስ የተናገረው ስለ ሰማያዊ ትንሣኤ ከሆነ የተናገረው ሐሳብ፣ ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ማግባት ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ምንም ፍንጭ አይሰጥም።
ለጊዜው የምናውቀው ነገር ቢኖር፣ የአምላክ ቃል በግልጽ እንደሚናገረው ሞት የጋብቻ ትስስርን ያፈርሳል። በመሆኑም የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ሰው እንደገና ለማግባት ቢወስን የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማው አይገባም። ይህ የግል ውሳኔ ነው፤ እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ከትዳር ጓደኛ የሚገኘውን የቅርብ ወዳጅነት በመፈለጋቸው ሌሎች ሊወቅሷቸው አይገባም።—ሮም 7:2, 3፤ 1 ቆሮ. 7:39
በአዲሱ ዓለም ውስጥ ስለሚኖረው ሕይወት ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩን የሚገርም አይሆንም። ለእነዚህ ጥያቄዎች የግምት መልስ ለመስጠት መሞከሩ አስፈላጊ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እዚያ ደርሰን የሚሆነውን እስክናይ በትዕግሥት መጠበቁ የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ደስተኞች ይሆናሉ፤ ምክንያቱም ይሖዋ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮችና ምኞታቸውን በሙሉ በላቀ መንገድ ያሟላላቸዋል።—መዝ. 145:16
^ አን.4 የሰኔ 1, 1987 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 30-31ን ተመልከት።
^ አን.5 በጥንት ዘመን የነበረው የዋርሳ ጋብቻ፣ አንድ ሰው ዘር ሳይተካ ከሞተ ወንድሙ የሟቹን ሚስት በማግባት የሟቹ የዘር ሐረግ እንዲቀጥል የሚደረግበት ልማድ ነበር።—ዘፍ. 38:8፤ ዘዳ. 25:5, 6
^ አን.9 ምድራዊ ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት እንጂ ያለመሞት ባሕርይ አይሰጣቸውም። ባለመሞት ባሕርይና በዘላለማዊ ሕይወት መካከል ስላለው ልዩነት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚያዝያ 1, 1984 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 30-31ን [መግ 22-108 ገጽ 22ን] እና የየካቲት 15, 2009 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 25 አንቀጽ 6ን ተመልከት።