በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሴቶች በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ምን ሚና አላቸው?

ሴቶች በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ምን ሚና አላቸው?

“ምሥራቹን የሚያውጁ ሴቶች ታላቅ ሠራዊት ናቸው።”—መዝ. 68:11 NW

1, 2. (ሀ) አምላክ ለአዳም ምን ስጦታዎች ሰጥቶታል? (ለ) አምላክ ለአዳም ሚስት የሰጠው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ይሖዋ ምድርን የፈጠራት በዓላማ ይኸውም “የሰው መኖሪያ” እንድትሆን ነው። (ኢሳ. 45:18) የመጀመሪያው ሰው አዳም ፍጹም የነበረ ከመሆኑም ሌላ አምላክ ውብ መኖሪያ የሆነችውን ኤደን ገነት ሰጥቶት ነበር። ግርማ ሞገስ ያላቸው ዛፎችን፣ ኩልል እያሉ የሚወርዱ ጅረቶችንና የሚቦርቁ እንስሳትን መመልከት ለአዳም ምን ያህል አስደሳች ሊሆን እንደሚችል አስበው! ይሁንና አዳም በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ነገር ጎድሎት ነበር። ይሖዋ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” በማለት የተናገረው ሐሳብ አዳም የጎደለው ነገር ምን እንደሆነ ይጠቁማል። በመሆኑም አምላክ በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ከጣለበት በኋላ ከጎድኑ አንዲት አጥንት ወስዶ “የወሰዳትን ዐጥንት ሴት አድርጎ ሠራት።” አዳም ከእንቅልፉ ሲነቃ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! “ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት። ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ማለቱ ይህን ያሳያል።—ዘፍ. 2:18-23

2 ልዩ ስጦታ የሆነችው ይህች ሴት የተፈጠረችው ለአዳም ፍጹም ረዳት እንድትሆነው ነው። በተጨማሪም ልጆች የመውለድ ልዩ መብት ነበራት። እንዲያውም አዳም “ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት”፤ ይህም “የሕያዋን ሁሉ እናት” እንደምትሆን ያሳያል። (ዘፍ. 3:20) አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አስደናቂ ስጦታ ሰጥቷቸዋል! ፍጹም የሆኑ ልጆችን የመውለድ ችሎታ ነበራቸው። በዚህ መንገድ ቀስ በቀስ መላዋን ምድር ገነት በማድረግ ፍጹም በሆኑ የሰው ልጆች የመሙላት አጋጣሚ የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ሌሎች ሕያዋን  ፍጥረታትን እንዲገዙ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር።—ዘፍ. 1:27, 28

3. (ሀ) አዳምና ሔዋን የአምላክን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር? ይሁን እንጂ ምን ተፈጠረ? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 አዳምና ሔዋን ይሖዋ ያዘጋጀላቸውን በረከት ማግኘት ከፈለጉ እሱን መታዘዝና ሥልጣኑን መቀበል ነበረባቸው። (ዘፍ. 2:15-17) አምላክ ለእነሱ ያሰበው ነገር ሊፈጸምላቸው የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው። የሚያሳዝነው ግን “የመጀመሪያው እባብ” የተባለውን ሰይጣንን በመስማት በአምላክ ላይ ዓመፁ። (ራእይ 12:9፤ ዘፍ. 3:1-6) ለመሆኑ ይህ ዓመፅ በሴቶች ላይ ምን ውጤት አስከትሏል? በጥንት ዘመን የኖሩ አምላክን የሚፈሩ ሴቶች ምን አከናወነዋል? በዘመናችን ያሉ ክርስቲያን ሴቶች “ታላቅ ሠራዊት” ሊባሉ የሚችሉትስ እንዴት ነው?—መዝ. 68:11 NW

ዓመፁ ያስከተለው ውጤት

4. የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ለሠሩት ኃጢአት ተጠያቂው ማን ነበር?

4 አዳም ስለሠራው ኃጢአት ሲጠየቅ “ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” የሚል ተልካሻ ምክንያት አቀረበ። (ዘፍ. 3:12) አዳም ለሠራው ኃጢአት ኃላፊነቱን ከመውሰድ ይልቅ ጥፋቱን አምላክ በሰጠው ሴት እንዲሁም ለጋስ በሆነው ፈጣሪው ላይ ለማላከክ ሞከረ። ኃጢአት የፈጸሙት ሁለቱም ቢሆኑም ለሠሩት ጥፋት ተጠያቂው ግን አዳም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ” በማለት የተናገረው ለዚህ ነው።—ሮም 5:12

5. አምላክ፣ የሰው ልጆች ያለ እሱ ጣልቃ ገብነት ለተወሰነ ጊዜ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፍቀዱ ምን አሳይቷል?

5 የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በሰይጣን ስለተታለሉ የይሖዋ አገዛዝ እንደማያስፈልጋቸው አሰቡ። ይህም ‘የመግዛት መብት ያለው ማን ነው?’ የሚል ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጋር የተያያዘ ወሳኝ ጥያቄ አስነሳ። አምላክ ለዚህ ጥያቄ የማያዳግም መልስ ለመስጠት ሲል የሰው ልጆች ያለ እሱ ጣልቃ ገብነት ለተወሰነ ጊዜ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፈቀደላቸው። ይሖዋ፣ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ረገድ እንደማይሳካላቸው አስቀድሞ ያውቃል። ባለፉት ዘመናት እንደታየው እንዲህ ያለው አገዛዝ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚባለው በጥፋት ላይ ጥፋት አስከትሏል። ባለፈው መቶ ዓመት ብቻ 100,000,000 የሚያህሉ ሰዎች በጦርነት ያለቁ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሐን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ይገኙበታል። በመሆኑም የሰው ልጅ ‘አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል’ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። (ኤር. 10:23) ይህን እውነታ ስለምንገነዘብ ይሖዋን እንደ ገዢያችን አድርገን እንቀበለዋለን።—ምሳሌ 3:5, 6ን አንብብ።

6. በበርካታ አገሮች ውስጥ ሰዎች ለሴቶች ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?

6 በሰይጣን ኃይል ሥር በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ግፍ ሲደርስባቸው ኖሯል። (መክ. 8:9፤ 1 ዮሐ. 5:19) በጣም የከፉ ከሚባሉት ድርጊቶች መካከል አንዱ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ነው። በዓለም ዙሪያ 30 በመቶ ገደማ የሚሆኑ ሴቶች በወንድ ጓደኛቸው ወይም በትዳር ጓደኛቸው ጥቃት እንደሚደርስባቸው ሪፖርቶች ያሳያሉ። በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ ወንዶች ከፍ ያለ ቦታ ይሰጣቸዋል፤ ምክንያቱም የቤተሰቡን የዘር ሐረግ እንዲቀጥል የሚያደርጉት እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውንና አያቶቻቸውን የሚንከባከቡት እነሱ እንደሆኑ ተደርጎ ይታሰባል። በተወሰኑ አገሮች ደግሞ ሴት ልጆች ተፈላጊ ስላልሆኑ ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴት ሕፃናት ውርጃ ይፈጸምባቸዋል።

7. አምላክ ለወንዶችና ለሴቶች በመጀመሪያ ያዘጋጀላቸው ሕይወት ምን ዓይነት ነበር?

7 አምላክ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ግፍ ሲመለከት እንደሚያዝን ምንም ጥርጥር የለውም። ሴቶችን የሚይዘው ፍትሕ በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው፤ እንዲሁም ለእነሱ አክብሮት አለው። አምላክ፣ ሔዋንን ፍጹም አድርጎ የፈጠራት ከመሆኑም ሌላ እንደ ባሪያ እንድትታይ ሳይሆን ለአዳም ጥሩ ማሟያ እንድትሆን የሚያስችል ግሩም ተፈጥሮ ሰጥቷታል፤ ይህም ይሖዋ ለሴቶች ከፍ ያለ ቦታ እንደሚሰጥ ያሳያል። ስድስተኛው የፍጥረት ቀን ሲጠናቀቅ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” የተባለበት አንዱ  ምክንያት ይህ ነው። (ዘፍ. 1:31) አዎ፣ ይሖዋ የሠራው ነገር “ሁሉ . . . እጅግ መልካም ነበረ።” አምላክ ለወንዶችና ለሴቶች ያዘጋጀላቸው ነገር ጅምሩ በጣም ግሩም ነበር!

የይሖዋ ድጋፍ ያልተለያቸው ሴቶች

8. (ሀ) በአጠቃላይ ሲታይ የሰዎች ባሕርይ ምን እንደሚመስል ግለጽ። (ለ) በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ሞገሱን ያሳየው ለእነማን ነው?

8 የወንዶችም ሆነ የሴቶች ባሕርይ እየተበላሸ የሄደው በኤደን ዓመፅ ከተነሳ በኋላ ነው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ባለፈው መቶ ዓመት፣ ከዚህ በፊት ከነበረው ሁሉ የከፋ ሆኗል። “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ክፋት እንደሚበዛ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል። ሰዎች የሚፈጽሙት መጥፎ ተግባር በጣም እየተስፋፋ መምጣቱ በእርግጥም የምንኖረው “በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ እንደሆነ ይጠቁማል። (2 ጢሞ. 3:1-5) ይሁን እንጂ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ በእሱ ለሚታመኑ፣ ትእዛዙን ለሚከተሉና እሱን እንደ ገዢያቸው አድርገው ለሚቀበሉ ወንዶችና ሴቶች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሞገሱን አሳይቷል።መዝሙር 71:5ን አንብብ።

9. ከጥፋት ውኃው የተረፉት ሰዎች ስንት ናቸው? ከጥፋቱ መዳን የቻሉትስ እንዴት ነው?

9 አምላክ በኖኅ ዘመን የነበረውን ክፉ ዓለም በውኃ ባጠፋ ጊዜ የተረፉት በጣም ጥቂት ሰዎች ነበሩ። የኖኅ ወንድሞችና እህቶች በወቅቱ በሕይወት ከነበሩ እነሱም በጥፋት ውኃው ሞተዋል። (ዘፍ. 5:30) ይሁንና ከጥፋቱ የተረፉት ሴቶችና ወንዶች ቁጥር እኩል ነበር። በሕይወት የተረፉት ኖኅና ሚስቱ እንዲሁም ሦስት ልጆቹና ሚስቶቻቸው ነበሩ። ከጥፋቱ መዳን የቻሉት አምላክን በመፍራታቸውና ፈቃዱን በማድረጋቸው ነው። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተገኙት የአምላክ ድጋፍ ካልተለያቸው ከእነዚህ ስምንት ሰዎች ነው።—ዘፍ. 7:7፤ 1 ጴጥ. 3:20

10. በጥንት ዘመን የኖሩ አምላክን የሚፈሩ ሚስቶች የይሖዋን ድጋፍ ያገኙት ለምን ነበር?

10 ከብዙ ዓመታት በኋላ የኖሩት እንደ አብርሃም ያሉ ታማኝ ሰዎች ያገቧቸው ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶችም የይሖዋ ድጋፍ አልተለያቸውም። እነዚህ ሴቶች ስለ ኑሯቸው የሚያማርሩ ቢሆኑ ኖሮ እንዲህ ዓይነቱን ድጋፍ አያገኙም ነበር። (ይሁዳ 16) ለባሏ አክብሮት የነበራት የአብርሃም ሚስት ሣራ በዑር የነበራቸውን የተመቻቸ ኑሮ ትተው በመውጣት በባዕድ አገር በድንኳን መኖር ሲጀምሩ አጉረምርማ ነበር ብሎ ማሰብ ይከብዳል። እንዲያውም “ሣራ አብርሃምን ‘ጌታዬ’ እያለች በመጥራት ትታዘዘው” ነበር። (1 ጴጥ. 3:6) የይሖዋ ስጦታና ጥሩ ሚስት የነበረችው ርብቃም ብትሆን አምላክን የምትፈራ ሴት ነበረች። ‘ይስሐቅ ርብቃን ወደዳት፤ ከእናቱም ሞት ተጽናና’ መባሉ አያስገርምም። (ዘፍ. 24:67) በዛሬው ጊዜም ቢሆን እንደ ሣራና ርብቃ ያሉ አምላክን የሚፈሩ ሴቶች በመኖራቸው በጣም ደስተኞች ነን!

11. ሁለቱ ዕብራውያን አዋላጆች ድፍረት ያሳዩት እንዴት ነው?

11 እስራኤላውያን ግብፅ ውስጥ በባርነት ሥር በነበሩበት ወቅት ቁጥራቸው በጣም እየጨመረ በመሄዱ ፈርዖን ዕብራውያን ሴቶች ወንድ ልጅ ከወለዱ ልጁ እንዲገደል ትእዛዝ አስተላለፈ። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት ሲራና ፉሐ የተባሉት ዕብራውያን አዋላጆች (የአዋላጆች ኃላፊ ሳይሆኑ አይቀሩም) ያደረጉትን እስቲ እንመልከት። ለይሖዋ ጥልቅ ፍርሃት ስለነበራቸው ሕፃናቱን ለመግደል ፈቃደኞች ባለመሆን ድፍረት አሳይተዋል። ይሖዋም ቤተሰብ በመስጠት እነዚህን ሴቶች ባርኳቸዋል።—ዘፀ. 1:15-21

12. ዲቦራና ኢያዔል ምን የሚያስደንቅ ተግባር ፈጽመዋል?

12 እስራኤላውያን በመሳፍንት በሚተዳደሩበት ዘመን የይሖዋ ድጋፍ ያልተለያት ዲቦራ የተባለች አንዲት ነቢይት ነበረች። መስፍኑን ባርቅን ያበረታታችው ከመሆኑም ሌላ እስራኤላውያን ከጭቆና ነፃ እንዲወጡ የበኩሏን አስተዋጽኦ አበርክታለች፤ ይሁንና በከነዓናውያን ላይ ድል ሲቀዳጁ ክብሩን የሚወስደው ባርቅ አለመሆኑን ትንቢት ተናገረች። ከዚህ ይልቅ አምላክ የከነዓናውያን የሠራዊት አዛዥ የሆነውን ሲሣራን “ለሴት አሳልፎ” እንደሚሰጠው ገለጸች። እስራኤላዊ ያልሆነችው ኢያዔል ሲሣራን ስትገድለው ይህ ትንቢት ተፈጽሟል።—መሳ. 4:4-9, 17-22

13. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አቢግያ ምን ይነግረናል?

13 በ11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረችው የአቢግያ ሁኔታም ትኩረት የሚስብ ነው። አቢግያ አስተዋይ ሴት ነበረች፤ በአንጻሩ ግን ባሏ ናባል ባለጌ፣  ምግባረ ብልሹና ጅል ሰው ነበር። (1 ሳሙ. 25:2, 3, 25) ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በአንድ ወቅት የናባልን ንብረት ይጠብቁለት ነበር፤ ይሁንና የዳዊት ሰዎች ምግብ እንዲሰጣቸው ናባልን በጠየቁት ጊዜ ‘የስድብ ናዳ በማውረድ’ ባዷቸውን ሰደዳቸው። ዳዊት በዚህ በጣም በመናደዱ ናባልንና የእሱ የሆኑትን ወንዶች ለመግደል ተነሳ። አቢግያ ጉዳዩን ስትሰማ ምግብና መጠጥ ይዛ ወደ ዳዊት ሄደች፤ እንዲህ በማድረጓም ዳዊትን ደም ከማፍሰስ ጠብቃዋለች። (1 ሳሙ. 25:8-18) በኋላም ዳዊት አቢግያን “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን” አላት። (1 ሳሙ. 25:32) ናባል ሲሞት ዳዊት አቢግያን አገባት።—1 ሳሙ. 25:37-42

14. የሰሎም ሴቶች ልጆች በየትኛው ሥራ ተካፍለዋል? በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሴቶች ተመሳሳይ ነገር እያደረጉ ያሉት እንዴት ነው?

14 በ607 ዓ.ዓ. የባቢሎን ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ባጠፋበት ጊዜ በርካታ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በ455 ዓ.ዓ. በነህምያ መሪነት የከተማይቱ ቅጥር እንደገና ተገነባ። ቅጥሩን መልሶ በመገንባቱ ሥራ ከተካፈሉት ሰዎች መካከል የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሰሎም ሴት ልጆች ይገኙበታል። (ነህ. 3:12) እነዚህ ሴቶች ዝቅ ተደርጎ የሚታይ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ሆነዋል። በዛሬው ጊዜም በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ሥራዎች በተለያየ መንገድ በደስታ የሚካፈሉ በርካታ ክርስቲያን ሴቶችን እናደንቃቸዋለን!

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አምላክን የሚፈሩ ሴቶች

15. አምላክ ለማርያም ምን ልዩ መብት ሰጥቷታል?

15 ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመንና ከዚያ ጥቂት ቀደም ብሎ ለነበሩ በርካታ ሴቶች ግሩም የሆኑ መብቶችን በመስጠት ባርኳቸዋል። ከእነዚህ መካከል ድንግል የነበረችው ማርያም ትገኝበታለች። ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ፀነሰች። አምላክ፣ የኢየሱስ እናት እንድትሆን የመረጣት ለምንድን ነው? ፍጹም የሆነውን ልጇን ከልጅነት እስከ እውቀት ተንከባክባ ለማሳደግ የሚያስችሉ መንፈሳዊ ባሕርያት ስለነበሯት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠውን ታላቅ ሰው ወልዶ ማሳደግ እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው!—ማቴ. 1:18-25

16. ኢየሱስ ለሴቶች የነበረውን አመለካከት የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

16 ኢየሱስ ሴቶችን በደግነት ይይዝ ነበር። ለ12 ዓመት ደም ይፈስሳት የነበረችውን ሴት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህች ሴት ከሕዝቡ መሃል የኢየሱስን ልብስ ነካች። ኢየሱስ እሷን ከመገሠጽ ይልቅ ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፣ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም እረፊ።”—ማር. 5:25-34

17. በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ምን ተአምራዊ ክንውን ተፈጸመ?

17 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የነበሩ አንዳንድ ሴቶች እሱንና ሐዋርያቱን ያገለግሏቸው ነበር። (ሉቃስ 8:1-3) በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ደግሞ ልዩ በሆነ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ከተቀበሉት 120 ሰዎች መካከል ሴቶችም ይገኙበታል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4ን አንብብ።) ይሖዋ፣ መንፈስ ቅዱስ በዚህ መንገድ በሰዎች ላይ እንደሚፈስ በትንቢት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ . . . በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ እንኳ፣ መንፈሴን አፈሳለሁ።” (ኢዩ. 2:28, 29) አምላክ በጴንጤቆስጤ ዕለት ይህን ተአምር መፈጸሙ ከሃዲ የሆነውን የእስራኤል ብሔር በመተው ድጋፉን ‘ለአምላክ እስራኤል’ እንደሰጠ ያሳያል፤ ይህ አዲስ ብሔር ወንዶችንና ሴቶችን ያቀፈ ነው። (ገላ. 3:28፤ 6:15, 16) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአገልግሎት ይካፈሉ ከነበሩት ክርስቲያን ሴቶች መካከል የወንጌላዊው ፊልጶስ አራት ሴቶች ልጆች ይገኙበታል።—ሥራ 21:8, 9

‘ታላቅ የሴቶች ሠራዊት’

18, 19. (ሀ) ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ አምላክ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ምን መብት ሰጥቷል? (ለ) መዝሙራዊው፣ ምሥራቹን የሚሰብኩትን ሴቶች የገለጻቸው እንዴት አድርጎ ነው?

18 በ1800ዎቹ መገባደጃ ላይ ለእውነተኛው አምልኮ  ፍላጎት ያሳዩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ነበሩ። እነዚህ ክርስቲያኖች “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል፤ በዚህ መንገድ በአሁኑ ጊዜ ለሚገኙ ምሥራቹን የሚሰብኩ ክርስቲያኖች ፈር ቀዳጅ ሆነዋል።—ማቴ. 24:14

19 በዚያን ወቅት ጥቂት የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቁጥራቸው የጨመረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 8,000,000 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። ከ11,000,000 የሚበልጡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ በመገኘት ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ሥራችን የማወቅ ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። በአብዛኞቹ አገሮች በበዓሉ ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል አብላጫ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ናቸው። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ካሉት ከ1,000,000 የሚበልጡ የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ሴቶች ናቸው። በእርግጥም አምላክ ታማኝ የሆኑ ሴቶች ስለ እሱ እንዲመሠክሩ መብት ሰጥቷቸዋል፤ በመሆኑም “ምሥራቹን የሚያውጁ ሴቶች ታላቅ ሠራዊት ናቸው” በማለት መዝሙራዊው የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከት ችለዋል።—መዝ. 68:11 NW

ምሥራቹን እያወጁ ያሉ ሴቶች በእርግጥም “ታላቅ ሠራዊት” ናቸው (አንቀጽ 18, 19ን ተመልከት)

አምላክን የሚፈሩ ሴቶች የሚጠብቃቸው ታላቅ ሽልማት

20. ስለ የትኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ማጥናት እንችላለን?

20 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ታማኝ ሴቶችን በዚህ ርዕስ ውስጥ ዘርዝረን መጨረስ አንችልም። ይሁንና ከአምላክ ቃል እንዲሁም ከጽሑፎቻችን ላይ ስለ እነሱ ማንበብ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሩት ባሳየችው ታማኝነት ላይ ማሰላሰል ይቻላል። (ሩት 1:16, 17) በንግሥት አስቴር የተሰየመውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲሁም ስለ እሷ በጽሑፎቻችን ላይ የወጡትን ርዕሶች ስናነብ እምነታችን ይጠናከራል። እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችን ላይ ማካተታችን ጥቅም ያስገኝልናል። የምንኖረው ብቻችንን ከሆነም እንዲህ ዓይነት ርዕሶችን በግል ጥናታችን ላይ ማካተት እንችላለን።

21. አምላክን የሚፈሩ ሴቶች በአስቸጋሪ ወቅቶች ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ያሳዩት እንዴት ነው?

21 ይሖዋ፣ ክርስቲያን ሴቶች የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ እንደሚባርክ እንዲሁም በመከራ ወቅት እንደሚረዳቸው ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል በናዚና በኮሚኒስት አገዛዝ ሥር የነበሩ አምላክን የሚፈሩ ሴቶች እሱን ለመታዘዝ በመምረጣቸው የተነሳ ብዙዎቹ መከራ ቢደርስባቸውም አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹ ሕይወታቸውን ቢያጡም ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቅ የቻሉት ይሖዋ ስለረዳቸው ነው። (ሥራ 5:29) በጥንት ዘመን እንደነበሩት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ እህቶቻችንም ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር ሆነው የአምላክን ሉዓላዊነት ይደግፋሉ። በመሆኑም ይሖዋ ልክ ለጥንት እስራኤላውያን እንዳደረገው ቀኝ እጃቸውን በመያዝ ‘አትፍሩ፤ እረዳችኋለሁ’ ያላቸው ያህል ነው።—ኢሳ. 41:10-13

22. ወደፊት ምን መብት እናገኛለን?

22 አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ወንዶችና ሴቶች በቅርቡ ምድርን ወደ ገነትነት የሚለውጧት ሲሆን ከሙታን የሚነሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስለ ይሖዋ ዓላማዎች ያስተምራሉ። እስከዚያው ድረስ ግን ወንዶችም ሆንን ሴቶች ይሖዋን በአንድነት የማገልገል መብታችንን ከፍ አድርገን እንመልከት።—ሶፎ. 3:9