የአምላክ ቃል ሕያው ነው—ተጠቀሙበት!
“የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው።”—ዕብ. 4:12
1, 2. ይሖዋ ሙሴን ምን ኃላፊነት እንዲወጣ አዘዘው? ምን ማረጋገጫስ ሰጠው?
በምድር ላይ ካሉ ገዢዎች ሁሉ እጅግ ከፍተኛ ሥልጣን ባለው ሰው ፊት በመቅረብ የይሖዋን ሕዝቦች ወክለህ የመናገር ኃላፊነት ቢሰጥህ ምን ይሰማህ ነበር? ጭንቀት ሊሰማህ፣ ብቃት እንደሌለህ ልታስብና ሁኔታው ሊያስፈራህ እንደሚችል ጥያቄ የለውም። ምን ብለህ ትናገራለህ? ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ወክለህ በምትቀርብበት ጊዜ ንግግርህ ይበልጥ ኃይል እንዲኖረው ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
2 ይህ ሁኔታ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት” የሆነው ሙሴ ያጋጠመውን ነገር በትክክል የሚገልጽ ነው፤ ሙሴ በግብፅ የሚኖረውን የአምላክ ሕዝብ ከጭቆናና ከባርነት ነፃ እንዲያወጣ ወደ ፈርዖን እንደሚልከው ይሖዋ ነገረው። (ዘኍ. 12:3) በኋላ ላይ እንደታየው ፈርዖን አክብሮት የጎደለውና ማን አለብኝ ባይ ሰው ነበር። (ዘፀ. 5:1, 2) ያም ቢሆን ሙሴ ፈርዖን ፊት ቀርቦ ይህ አምባገነን መሪ በባርነት የያዛቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲለቅ ትእዛዝ እንዲያስተላልፍ ይሖዋ ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ሙሴ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” በማለት ይሖዋን መጠየቁ የሚገርም አይደለም። ሙሴ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ብቃቱም ሆነ ችሎታው እንደሌለው ተሰምቶት መሆን አለበት። ይሖዋ ግን “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት ከጎኑ እንደማይለይ አረጋገጠለት።—ዘፀ. 3:9-12
3, 4. (ሀ) ሙሴን ያስፈራው ምንድን ነው? (ለ) የሙሴን ስሜት እንድትጋራ የሚያደርግ ምን ሁኔታ ሊያጋጥምህ ይችላል?
3 ሙሴ ያስፈራው ነገር ምንድን ነው? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ፈርዖን፣ የይሖዋ አምላክን መልእክተኛ እንደማይቀበል ሙሴ ተሰምቶት ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ እነሱን ከግብፅ ነፃ ለማውጣት እሱን እንደሾመው ወገኖቹ የሆኑ እስራኤላውያን እንደማይቀበሉ በማሰብ ሰግቶ ነበር። በመሆኑም ሙሴ “ባያምኑኝስ፤ ቃሌን ባይቀበሉስ፤ ‘እግዚአብሔር አልተገለጠልህም’ ቢሉኝስ?” በማለት ይሖዋን ጠየቀው።—ዘፀ. 3:15-18፤ 4:1
4 ይሖዋ ለሙሴ የሰጠው ምላሽና ከዚያ በኋላ የተከናወኑት ነገሮች ለሁላችንም ትልቅ ትምህርት ይሰጡናል። እርግጥ ነው፣ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ፊት አትቀርብ ይሆናል። ይሁንና በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ለምታገኛቸው ሰዎችም እንኳ ስለ አምላክና ስለ መንግሥቱ መናገር ከባድ ይሆንብሃል? ከሆነ ሙሴ ካጋጠመው ሁኔታ ምን ትምህርት ማግኘት እንደሚቻል ተመልከት።
‘በእጅህ የያዝካት ምንድን ናት?’
5. ሙሴ በእጁ ያለውን ነገር እንዲጠቀም ይሖዋ ምን ችሎታ ሰጠው? ይህስ ፍርሃቱን እንዲያሸንፍ የረዳው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
5 ሙሴ፣ መልእክቱ ተቀባይነት እንደማያገኝ በመናገር ፍርሃቱን በገለጸ ጊዜ አምላክ የሚያጋጥመውን ፈታኝ ሁኔታ መወጣት እንዲችል አዘጋጀው። በዘፀአት መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔርም፣ ‘በእጅህ የያዝሀት እርሷ ምንድን ናት?’ ሲል [ሙሴን] ጠየቀው፤ እርሱም መልሶ፣ ‘በትር ናት’ አለው። እግዚአብሔርም፣ ‘መሬት ላይ ጣላት’ አለው። ሙሴ በትሩን መሬት ላይ ጣላት፤ እባብም ሆነች፤ ከአጠገቧም ሸሸ። እግዚአብሔር ሙሴን፣ ‘በል እጅህን ዘርጋና ጅራቷን ያዛት’ አለው። ሙሴም እጁን ዘር[ግ]ቶ ሲይዛት እባቧ ተለውጣ በእጁ ላይ እንደገና በትር ሆነች። እግዚአብሔርም ‘ይህ የሆነው . . . እግዚአብሔር የተገለጠልህ መሆኑን እንዲያምኑ ነው’ አለው።” (ዘፀ. 4:2-5) አዎ ይሖዋ፣ ሙሴ እጁ ላይ ባለው ነገር ተጠቅሞ መልእክቱ ከአምላክ የመጣ መሆኑን ማረጋገጥ የሚችልበትን መንገድ አሳየው። በሌሎች ዓይን ሲታይ ተራ እንጨት የነበረው በትር በአምላክ ኃይል ሕይወት ያለው ነገር ሆነ! በእርግጥም ይህ ተአምር ሙሴ የሚናገረው መልእክት ይበልጥ ኃይል እንዲኖረው የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ድጋፍ እንዳለው በማያሻማ ሁኔታ የሚያረጋግጥ ነው! በመሆኑም ይሖዋ “ታምራዊ ምልክት እንድታሳይባት ይህችን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ” አለው። (ዘፀ. 4:17) ሙሴ ከአምላክ እንደተላከ የሚያሳየው ይህ ማስረጃ በእጁ ስላለ እውነተኛውን አምላክ ወክሎ በልበ ሙሉነት በወገኖቹም ሆነ በፈርዖን ፊት መቆም ይችላል።—ዘፀ. 4:29-31፤ 7:8-13
6. (ሀ) በምንሰብክበት ወቅት ምን ነገር ከእጃችን መጥፋት የለበትም? ለምንስ? (ለ) “የአምላክ ቃል ሕያው” እንዲሁም “ኃይለኛ” የሆነው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
6 የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎች ለመናገር በምንወጣበት ጊዜ ‘በእጅህ የያዝካት ምንድን ናት?’ የሚለው ጥያቄ ለእኛም ሊነሳ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ከእጃችን አይጠፋም። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከአንድ ተራ መጽሐፍ ለይተው ባያዩትም እኛ ግን ይሖዋ የሚናገረው በመንፈስ መሪነት ባስጻፈው በዚህ ቃል አማካኝነት እንደሆነ እናውቃለን። (2 ጴጥ. 1:21) ይህ መጽሐፍ፣ አምላክ በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር እንደሚፈጸሙ ቃል የገባቸውን ነገሮች ይዟል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” በማለት የጻፈው በዚህ የተነሳ ነው። (ዕብራውያን 4:12ን አንብብ።) ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች ወደ ፍጻሜያቸው የሚገሰግሱ በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ መፈጸማቸው አይቀርም። (ኢሳ. 46:10፤ 55:11) አንድ ሰው ስለ አምላክ ቃል ይህን ግንዛቤ ማግኘቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያነበው ነገር በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ የማምጣት ኃይል እንዲኖረው ያደርጋል።
7. ‘የእውነትን ቃል በአግባቡ መጠቀም’ የምንችለው እንዴት ነው?
7 በእርግጥም ይሖዋ ሕያው የሆነውን ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በእጃችን ሰጥቶናል፤ በዚህ ቃል ተጠቅመን መልእክታችን እምነት የሚጣልበትና ከእሱ የመነጨ መሆኑን ለሌሎች ማረጋገጥ እንችላለን። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ከጻፈ በኋላ መንፈሳዊ ልጁ ለሆነው ለጢሞቴዎስ ‘የእውነትን ቃል በአግባቡ ለመጠቀም የተቻለውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርግ’ ማሳሰቢያ መስጠቱ አያስገርምም። (2 ጢሞ. 2:15) ታዲያ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በአገልግሎት ለምናገኛቸው ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች፣ ልባቸውን የሚነካ የታሰበበት ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጥተን በማንበብ ነው። በ2013 የወጡት አዳዲስ ትራክቶች ይህን ማድረግ እንድንችል ይረዱናል።
የታሰበበት ጥቅስ አንብቡ!
8. አንድ የአገልግሎት የበላይ ተመልካች ስለ አዳዲሶቹ ትራክቶች ምን ብሏል?
8 አዳዲሶቹ ትራክቶች የተዘጋጁበት መንገድ ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ አንዱን እንዴት እንደምንጠቀምበት ካወቅን ሌሎቹንም በዚያው መንገድ መጠቀም እንችላለን። ትራክቶቹ ለአጠቃቀም አስቸጋሪ ናቸው? በሃዋይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ የአገልግሎት የበላይ ተመልካች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከቤት ወደ ቤት ስናገለግልም ሆነ የአደባባይ ምሥክርነት ስንሰጥ እነዚህ አዳዲስ መሣሪያዎች ይህን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ ብለን አልጠበቅንም ነበር።” ትራክቶቹ ሰዎች በቀላሉ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሚያበረታቱ እንደሆነና ይህም አብዛኛውን ጊዜ ሞቅ ያለ ውይይት ለመጀመር እንደሚያስችል ይህ ወንድም ተገንዝቧል። ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገው የትራክቱ ርዕስ በጥያቄ መልክ መቅረቡና ለጥያቄው መልስ የሚሆኑ አማራጮች መሰጠታቸው እንደሆነም ገልጿል። ምክንያቱም የቤቱ ባለቤት ምን ብዬ ልመልስ ብሎ አይጨነቅም።
9, 10. (ሀ) ትራክቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ለመጠቀም የሚያበረታቱን እንዴት ነው? (ለ) አንተ ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ ያገኘኸው ትራክት የትኛው ነው? ለምንስ?
9 ሁሉም ትራክቶች ተስማሚ የሆነ አንድ ጥቅስ እንድናነብ ያበረታቱናል። መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል? የሚለውን ትራክት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የቤቱ ባለቤት ለቀረበው ጥያቄ “ይመጣል?” “አይመጣም?” ወይም “ምናልባት?” ከሚሉት ምርጫዎች መካከል የትኛውንም ቢመርጥ በሰጠው መልስ ላይ ሐሳብ መስጠት አያስፈልግህም፤ ከዚህ ይልቅ ትራክቱን ገልጠህ “እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት” ልትለው ትችላለህ። ከዚያም ራእይ 21:3, 4ን አንብብለት።
10 በተመሳሳይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን አመለካከት አለህ? የሚለውን ትራክት በምትጠቀምበት ጊዜ የቤቱ ባለቤት ከቀረቡት ሦስት አማራጮች መካከል የትኛውንም ቢመርጥ ለውጥ የለውም። በሰጠው መልስ ላይ ከማተኮር ይልቅ ትራክቱን ገልጠህ “‘ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው’ በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል” ልትለው ትችላለህ። አክለህም “የዚህን ጥቅስ ሙሉ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ አውጥተን ብናነበው ጥሩ ነው” ማለት ትችላለህ። ከዚያም 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብለት።
11, 12. (ሀ) ከአገልግሎታችን እርካታ ማግኘት የምንችለው ምን ስናደርግ ነው? (ለ) ትራክቶች ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የሚረዱን እንዴት ነው?
11 ከትራክቱ ላይ ምን ያህሉን አንብበን መወያየት እንችላለን የሚለው ጉዳይ የተመካው በቤቱ ባለቤት ሁኔታ ላይ ነው። ያም ሆነ ይህ ትራክቱን ከማበርከት በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበባችን እርካታ ያስገኝልናል፤ እርግጥ ነው፣ በመጀመሪያው ቀን የምናነበው አንድ ወይም ሁለት ጥቅስ ብቻ ሊሆን ይችላል። በሌላ ጊዜ ውይይቱን መቀጠል እንችላለን።
12 በትራክቶቹ የጀርባ ገጽ ላይ የሚገኘው “ምን ይመስልሃል?” የሚለው ክፍል በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት ልንወያይበት የምንችል አንድ ጥያቄና ጥቅሶች ይዟል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይሰማሃል? በሚለው ትራክት ላይ የቀረበው ጥያቄ “አምላክ ዓለማችን የተሻለች እንድትሆን የሚያደርገው እንዴት ነው?” ይላል። ከዚያም ማቴዎስ 6:9, 10ን እና ዳንኤል 2:44ን ይጠቅሳል። የሞቱ ሰዎች እንደገና በሕይወት መኖር ይችላሉ? በሚለው ትራክት ላይ የቀረበው ጥያቄ ደግሞ “የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?” የሚል ነው። ከዚያም ዘፍጥረት 3:17-19ን እና ሮም 5:12ን ይጠቅሳል።
13. ትራክቶቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
13 ትራክቶቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር መሸጋገሪያ አድርጋችሁ ልትጠቀሙባቸው ትችላላችሁ። አንድ ሰው በትራክቱ ጀርባ ላይ ያለውን ኪው አር (QR) ኮድ ሲያስነብብ ወደ ድረ ገጻችን ይወስደዋል፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የሚያበረታታ ግብዣ ያገኛል። በተጨማሪም ትራክቶቹ ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለውን ብሮሹር የሚያስተዋውቁ ሲሆን ግለሰቡ ከብሮሹሩ ላይ የትኛውን ትምህርት ማንበብ እንዳለበት ለይተው ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ዓለምን እየተቆጣጠረ ያለው ማን ነው? የሚለው ትራክት ወደ ትምህርት 5 ይመራል። የቤተሰብን ሕይወት አስደሳች ለማድረግ ቁልፉ ምንድን ነው? የሚለው ትራክት ደግሞ ወደ ትምህርት 9 ይመራል። ትራክቶቹን ስንጠቀም የተዘጋጁበትን ዓላማ ግምት ውስጥ የምናስገባ ከሆነ በመጀመሪያው ቀንም ሆነ በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን የመጠቀም ጥሩ ልማድ እናዳብራለን። ይህም በርካታ ጥናቶች ለማስጀመር ይረዳናል። የአምላክን ቃል በአገልግሎትህ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ሌላስ ልታደርገው የምትችለው ነገር አለ?
ሰዎችን የሚያሳስቡ ጉዳዮችን አንስታችሁ ተወያዩ
14, 15. ጳውሎስ ለአገልግሎት የነበረው ዓይነት አመለካከት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ በአገልግሎት ላይ “በተቻለ መጠን ብዙ” ሰዎችን ለማናገር ልባዊ ፍላጎት ነበረው። (1 ቆሮንቶስ 9:19-23ን አንብብ።) ጳውሎስ ‘አይሁዳውያንን፣ በሕግ ሥር ያሉትን ብሎም ሕግ የሌላቸውንና ደካሞችን’ ለመማረክ ጥረት ያደርግ እንደነበረ ልብ በል። አዎ፣ ‘በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን ለማዳን ሲል ሁሉንም ዓይነት ሰዎች’ ለመርዳት ይፈልግ ነበር። (ሥራ 20:21) ታዲያ በክልላችን ውስጥ ለምናገኛቸው “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” እውነትን ለማስተማር ዝግጅት በምናደርግበት ወቅት የጳውሎስን አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?—1 ጢሞ. 2:3, 4
15 በየወሩ በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የአቀራረብ ናሙናዎች ይወጣሉ። ለምን አትሞክራቸውም? በክልልህ ያሉ ሰዎች የሚያሳስባቸው ጉዳይ ሌላ ከሆነ ግን የእነሱን ትኩረት ሊስብ የሚችል መግቢያ አዘጋጅ። ስለምትኖርበት አካባቢ፣ ስለ ነዋሪዎቹ እንዲሁም ሰዎቹ ስለሚያሳስባቸው ነገር ቆም ብለህ አስብ። ከዚያም ለጉዳዩ የሚስማማ ጥቅስ ምረጥ። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ እሱና ባለቤቱ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ስለሚጠቀሙበት ዘዴ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አቀራረባችን አጭር ከሆነና ቶሎ ወደ ዋናው ነጥብ የምንሄድ ከሆነ የምናነጋግራቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ አንድ ጥቅስ ስናነብላቸው ለመስማት ፈቃደኛ ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱሳችንን ገልጠን በእጃችን እንደያዝን ለሰዎቹ ሰላምታ እንሰጣቸዋለን፤ ከዚያም ጥቅሱን እናነብላቸዋለን።” ከዚህ በመቀጠል በመስክ አገልግሎት ላይ ተሞክረው ጥሩ ውጤት ያስገኙ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች፣ ጥያቄዎችና ጥቅሶች ቀርበዋል፤ እነዚህን አቀራረቦች በክልልህ ውስጥ ልትሞክራቸው ትችላለህ።
16. ኢሳይያስ 14:7ን በአገልግሎታችን ላይ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
16 የምትኖረው ሰላም በሌለበት አካባቢ ከሆነ የምታነጋግረውን ሰው እንዲህ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ፦ “‘ምድር ሁሉ ሰላምና እረፍት አገኘች፤ የደስታም ዝማሬ እያስተጋባች ነው’ የሚል ዜና የምንሰማበት ቀን ይመጣል ብለው አስበው ያውቃሉ? መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳይያስ 14:7 ላይ የሚናገረው ይህንኑ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ ሰላም የሰፈነበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚናገሩ ሌሎች በርካታ ተስፋዎችን ይዟል።” ከዚያም ከእነዚህ ተስፋዎች መካከል አንዱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ብታነብለት ደስ እንደሚልህ ግለጽለት።
17. በአገልግሎት ላይ ማቴዎስ 5:3ን ለማንበብ ምን መግቢያ መጠቀም ትችላለህ?
17 የምትኖረው ወንዶች ቤተሰባቸውን ማስተዳደር አስቸጋሪ በሚሆንባቸው አካባቢ ነው? ከሆነ እንዲህ በማለት ውይይት መጀመር ትችላለህ፦ “አንድ ሰው ቤተሰቡን በደንብ ለማስተዳደር ምን ያህል ገቢ ሊኖረው ይገባል ይላሉ?” ግለሰቡ የሚሰጠውን ምላሽ ካዳመጥክ በኋላ እንዲህ ብለህ መመለስ ትችላለህ፦ “ብዙ ወንዶች ከዚህ የበለጠ ገቢ ቢኖራቸውም የቤተሰባቸውን ፍላጎት ማርካት አልቻሉም። ታዲያ ከሁሉ ይበልጥ መሟላት ያለበት ነገር ምንድን ነው?” ማቴዎስ 5:3ን ካነበብክ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ግብዣ አቅርብለት።
18. መዝሙር 37:11ን ተጠቅመን ሰዎችን ማጽናናት የምንችለው እንዴት ነው?
18 በአካባቢህ የሚኖሩ ሰዎች በቅርቡ በተከሰተ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ የተነሳ ሐዘን ላይ ወድቀዋል? ከሆነ ውይይቱን እንዲህ በማለት መጀመር ትችላለህ፦ “ዛሬ ወደ ቤትዎ የመጣሁት አንድ የሚያጽናና ሐሳብ ልነግርዎት ነው። (መዝሙር 37:11ን አንብብ።) አምላክ ለእኛ ምን እንደሚመኝልን ልብ አሉ? ጥቅሱ ላይ ‘ሰላም’ እና ‘ሐሴት’ የሚሉትን ቃላት ይመልከቱ። ታዲያ አምላክ እንዲህ ዓይነት አስደሳች ሕይወት እንድንመራ የሚፈልግ መሆኑን ማወቅ አያጽናናም? ለመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?” ከዚያም ለርዕሰ ጉዳዩ ተስማሚ የሆነውን ትምህርት ምሥራች ከተባለው ብሮሹር ላይ መርጠህ አሳየው።
19. ሃይማኖተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ስንወያይ ራእይ 14:6, 7ን መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
19 በምትኖርበት አካባቢ ብዙ ሃይማኖተኛ ሰዎች አሉ? ከሆነ ውይይት ለመጀመር እንዲህ ማለት ትችላለህ፦ “አንድ መልአክ ቢያናግርዎት ኖሮ የሚናገረውን ነገር ይሰሙ ነበር? (ራእይ 14:6, 7ን አንብብ።) መልአኩ የያዘውን ጠቃሚ መልእክት ልብ አሉ? መልአኩ ‘ሰማይንና ምድርን የሠራውን’ መፍራት እንዳለብን ተናግሯል። ታዲያ አምላክን እንደምንፈራ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?” ግለሰቡ የሚሰጠውን ምላሽ ካዳመጥክና ካመሰገንከው በኋላ ዘዳግም 6:2ን አንብብለት፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የምሰጣችሁን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ በመጠበቅ፣ ዕድሜያችሁ እንዲረዝም፣ አንተ፣ ልጆችህና ከእነርሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቻቸው በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈሩት ዘንድ ነው።” ከዚያም እንዲህ ማለት ትችላለህ፦ “ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው አምላክን እንደምንፈራ ማሳየት የምንችለው ትእዛዛቱን በመጠበቅ ነው። ብዙ ሰዎች ግን አምላክ ከሰጣቸው ትእዛዛት ሁሉ የላቀውን ይኸውም እሱን በሙሉ ልባችን እንድንወድ የሰጠንን ትእዛዝ አያውቁትም።” በመጨረሻም አምላክን እንደምንወደው ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
20. (ሀ) ምሳሌ 30:4ን ተጠቅመን የአምላክን ስም ለሰዎች ማስተማር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) አንተስ በአገልግሎት ላይ ጥሩ ውጤት ያገኘህበት ጥቅስ አለ?
20 ወጣቶችን ስታገኝ ደግሞ እንዲህ በማለት ውይይት መጀመር ትችላለህ፦ “በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ የያዘ አንድ ጥቅስ ባነብልህ ደስ ይለኛል። (ምሳሌ 30:4ን አንብብ።) መቼም በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጹትን ነገሮች ያደረገ ሰው የለም፤ ስለዚህ ጥቅሱ የሚናገረው ስለ ፈጣሪያችን መሆን አለበት። * ታዲያ ስሙን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? የፈጣሪን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ባሳይህ ደስ ይለኛል።”
የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል በአገልግሎታችሁ ተጠቀሙበት
21, 22. (ሀ) የታሰበበት ጥቅስ የሰዎችን ሕይወት የሚለውጠው እንዴት ነው? (ለ) አገልግሎትህን ስትፈጽም ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?
21 የታሰበበት ጥቅስ ከተጠቀምን ሰዎች የሚያስገርም ምላሽ ሊሰጡን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአውስትራሊያ የሚኖሩ ሁለት ወንድሞች አንድ በር ሲያንኳኩ አንዲት ወጣት አገኙ። ከዚያም አንደኛው ወንድም “የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ታውቂያለሽ?” በማለት ጠየቃት፤ ከዚያም መዝሙር 83:18ን (NW) አነበበላት። ይህች ወጣት “በጣም ደነገጥኩ!” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “እነሱ ከሄዱ በኋላ ስሙ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ይኖር እንደሆነ ለማረጋገጥ 56 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ አንድ የመጻሕፍት መደብር በመኪናዬ ሄድኩ፤ ከዚያም ስሙን መዝገበ ቃላት ላይ አገኘሁት። የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ሳረጋግጥ ‘ይሄኔ እኮ ሌላም ብዙ የማላውቀው ነገር አለ’ ብዬ አሰብኩ።” ብዙም ሳይቆይ እሷና ባለቤቷ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ፤ ከዚያም ተጠመቁ።
22 አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብና ይሖዋ ቃል በገባቸው ተስፋዎች ላይ እምነት የሚያሳድር ከሆነ የአምላክ ቃል ሕይወቱን ይለውጠዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:13ን አንብብ።) ስለተለያዩ ነገሮች በመናገር የሰዎችን ልብ ለመንካት ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ኃይል ሊኖረው አይችልም። ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ የአምላክን ቃል መጠቀም ያለብን ለዚህ ነው። ምክንያቱም ቃሉ ሕያው ነው!
^ አን.20 በሐምሌ 15, 1987 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 31 ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።