በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትም ብትሆን የይሖዋን ድምፅ ስማ

የትም ብትሆን የይሖዋን ድምፅ ስማ

“ጆሮህ ከኋላህ፣ ‘መንገዱ ይህ ነው፤ . . .’ የሚል ድምፅ ይሰማል።”—ኢሳ. 30:21

1, 2. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ መልእክት የሚያስተላልፈው እንዴት ነው?

ይሖዋ ከጥንት ጀምሮ ለግለሰቦች በተለያየ መንገድ አመራር ይሰጥ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ለአንዳንዶች በመላእክት፣ በራእይ ወይም በሕልም አማካኝነት ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ገልጦላቸዋል። ይሖዋ በእነዚህ መንገዶች ተጠቅሞ ልዩ ልዩ ተልዕኮዎችን የሰጠበት ጊዜም አለ። (ዘኍ. 7:89፤ ሕዝ. 1:1፤ ዳን. 2:19) በሌላ በኩል ደግሞ በድርጅቱ ምድራዊ ክፍል የሚያገለግሉ ሰብዓዊ ወኪሎቹን ተጠቅሞ መመሪያ ይሰጣል። ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያ የሚሰጥበት መንገድ ምንም ይሁን ምን መመሪያውን ተግባራዊ የሚያደርጉ ሁሉ ይባረካሉ።

2 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን የሚመራው በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በመንፈስ ቅዱስና በጉባኤው አማካኝነት ነው። (ሥራ 9:31፤ 15:28፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17) ከእሱ የምናገኘው መመሪያ በጣም ግልጽ ነው፤ ‘ጆሯችን ከኋላ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” የሚል ድምፅ የሚሰማ’ ያህል ነው። (ኢሳ. 30:21) በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ጉባኤዎችን እየመራ ሲሆን በዚህ መንገድ የይሖዋን ድምፅ እንድንሰማ እያደረገን ነው። (ማቴ. 24:45) የሚሰጠንን መመሪያ ትኩረት ሰጥተን ማዳመጥ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው ታዛዥ በመሆናችን ላይ ነው።—ዕብ. 5:9

3. የይሖዋን መመሪያ እንዳንሰማ እንቅፋት የሚሆንብን ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

3 ሰይጣን ዲያብሎስ ይሖዋ የሚሰጠንን ሕይወት አድን መመሪያ እንዳንሰማ  ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል። ከዚህም ሌላ “ተንኰለኛ” የሆነው ልባችን ይሖዋ ለሚሰጠን መመሪያ ጥሩ ምላሽ እንዳንሰጥ እንቅፋት ይሆንብናል። (ኤር. 17:9) እንግዲያው የአምላክን ድምፅ እንዳንሰማ የሚጋረጡብንን እንቅፋቶች እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል እንመልከት። በተጨማሪም ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ከይሖዋ ጋር አዘውትረን የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋችን ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

የሰይጣንን ዘዴዎች ማሸነፍ

4. ሰይጣን በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚሞክረው እንዴት ነው?

4 ሰይጣን የሐሰት መረጃ በመስጠትና አሳሳች ፕሮፓጋንዳዎችን በመንዛት በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክራል። (1 ዮሐንስ 5:19ን አንብብ።) በወረቀት ታትመው ከሚወጡት ነገሮች በተጨማሪ ምድራችንን ባዳረሱት በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በኢንተርኔት አማካኝነት እነዚህን መረጃዎች ያስተላልፋል። እነዚህ መገናኛ ብዙኃን አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ከይሖዋ መሥፈርት ጋር የሚጋጭ ምግባርንና ድርጊትን ያስፋፋሉ። (ኤር. 2:13) ለምሳሌ ያህል፣ የዜና ማሰራጫዎችና የመዝናኛው ኢንዱስትሪ በተመሳሳይ ፆታ መካከል የሚፈጸም ጋብቻ ተቀባይነት ያለው ነገር እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል፤ ከዚህም ሌላ ብዙ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም የሚናገረው ሐሳብ ጽንፈኝነት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ይሰማቸዋል።—1 ቆሮ. 6:9, 10

5. በሰይጣን ፕሮፓጋንዳ እንዳንወሰድ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

5 የአምላክን ጽድቅ የሚወዱ ሰዎች በዛሬው ጊዜ ዓለምን ባጥለቀለቀው የሰይጣን የፕሮፓጋንዳ ጎርፍ እንዳይወሰዱ ምን ማድረግ ይችላሉ? ጥሩውን ከመጥፎው መለየት የሚችሉትስ እንዴት ነው? ‘በአምላክ ቃል መሠረት በመኖር ነው’! (መዝ. 119:9) በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል እውነተኛ መረጃን ከአሳሳች ፕሮፓጋንዳ ለመለየት የሚያስችል አስፈላጊ መመሪያ ይዟል። (ምሳሌ 23:23) ኢየሱስ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሶ ሲናገር “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል” መኖር እንዳለበት ገልጿል። (ማቴ. 4:4) በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ መማር አለብን። ዮሴፍን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ዮሴፍ የኖረው ሙሴ ምንዝርን የሚከለክለውን የይሖዋን ሕግ በጽሑፍ ከማስፈሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ቢሆንም እንዲህ ያለው ምግባር በአምላክ ዘንድ ኃጢአት እንደሆነ ተገንዝቧል። የጲጥፋራ ሚስት መጥፎ ነገር እንዲፈጽም ብታባብለውም የይሖዋን መሥፈርት መጣስ ቀርቶ ሐሳቡ እንኳ ወደ አእምሮው አልመጣም። (ዘፍጥረት 39:7-9ን አንብብ።) የጲጥፋራ ሚስት በተደጋጋሚ እንዲህ ያለ ድምፅ ማሰማቷ የይሖዋን ድምፅ ከመስማት እንዲያደነቁረው አልፈቀደም። ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት ቁልፉ የሰይጣን ፕሮፓጋንዳ ያለማቋረጥ የሚያሰማውን የሚረብሽ ድምፅ ላለመስማት ጆሯችንን በመዝጋት የይሖዋን ድምፅ ብቻ መስማት ነው።

6, 7. የሰይጣንን ክፉ ምክር ላለመስማት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

6 ዓለማችን ግራ በሚያጋቡ የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች የተሞላ በመሆኑ ብዙ ሰዎች እውነተኛውን ሃይማኖት ፈልጎ ማግኘት ከንቱ ድካም እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና ይሖዋ እሱን መስማት ለሚፈልጉ ሁሉ ግልጽ በሆነ መንገድ አመራር ይሰጣል። በመሆኑም ማንን መስማት እንዳለብን መወሰን ይኖርብናል።  ሁለት ድምፆችን በአንድ ጊዜ ማዳመጥ እንደማይቻል የታወቀ ነው፤ ስለዚህ የኢየሱስን ‘ድምፅ ማወቅ’ እንዲሁም እሱን ማዳመጥ ያስፈልገናል። ምክንያቱም ይሖዋ በበጎቹ ላይ ሾሞታል።—ዮሐንስ 10:3-5ን አንብብ።

7 ኢየሱስ “የምትሰሙትን ነገር ልብ በሉ” ብሏል። (ማር. 4:24) ይሖዋ የሚሰጠው ምክር ግልጽና ትክክለኛ ነው፤ ይሁን እንጂ ምክሩን ትኩረት ሰጥተን ማዳመጥ እንድንችል ጥሩ የልብ ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል። ጠንቃቆች ካልሆንን የይሖዋን ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ትተን ለሰይጣን ክፉ ምክር ጆሮ ልንሰጥ እንችላለን። በመሆኑም ዓለማዊ ሙዚቃ፣ ቪዲዮዎች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ መጻሕፍት፣ ጓደኞች፣ አስተማሪዎች ወይም ባለሙያ ተብዬዎች ሕይወትህን እንዲቆጣጠሩት አትፍቀድ።—ቆላ. 2:8

8. (ሀ) ልባችን በሰይጣን ዘዴዎች እንድንሸነፍ ሊያደርገን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ችላ የምንል ከሆነ ምን ሊያጋጥመን ይችላል?

8 ሰይጣን በውስጣችን የኃጢአት ዝንባሌ እንዳለ ስለሚያውቅ ይህን ፍላጎታችንን እንድናረካ ሊገፋፋን ይሞክራል። በዚህ መንገድ እኛን ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት በሚሞክርበት ጊዜ ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ በጣም ፈታኝ ይሆንብናል። (ዮሐ. 8:44-47) ታዲያ ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? ጊዜያዊ ደስታ ለማግኘት ሲል በፍጹም አደርገዋለው ብሎ ያላሰበውን ነገር የፈጸመን አንድ ሰው እስቲ ለማሰብ ሞክር። (ሮም 7:15) እዚህ አሳዛኝ ደረጃ ላይ ያደረሰው ነገር ምን ሊሆን ይችላል? ግለሰቡ ለይሖዋ ድምፅ ጆሮ መስጠቱን ቀስ በቀስ አቁሞ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ልቡ ወደ አደገኛ ሁኔታ እያዘነበለ እንደሆነ የሚጠቁሙትን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች አላስተዋለ ወይም ምልክቶቹን ችላ ብሎ ይሆናል። ለምሳሌ መጸለይ አቁሞ፣ አገልግሎት ቀንሶ ወይም በስብሰባዎች ላይ መቅረት ጀምሮ ሊሆን ይችላል። ብዙም ሳይቆይ ለምኞቱ በመሸነፍ ስህተት እንደሆነ የሚያውቀውን ነገር ፈጸመ። እኛም የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን በንቃት የምንከታተል እንዲሁም ችግሩን ለማስተካከል ፈጣን እርምጃ የምንወስድ ከሆነ እንዲህ ዓይነት አዘቅት ውስጥ ከመግባት እንድናለን። በተጨማሪም የይሖዋን ድምፅ የምንሰማ ከሆነ የከሃዲዎችን ትምህርት አናስተናግድም።—ምሳሌ 11:9 የ1980 ትርጉም

9. ያሉብንን የኃጢአት ዝንባሌዎች ቶሎ ማወቃችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 አንድ ሰው በሽታው ቶሎ ከታወቀለት ሕይወቱ ሊተርፍ ይችላል። በተመሳሳይም ለፈተና የሚያጋልጡ ዝንባሌዎች በልባችን ውስጥ ማቆጥቆጥ እንደጀመሩ ቶሎ ማወቃችን ከአደጋ ይጠብቀናል። እንዲህ ያለውን አዝማሚያ ካስተዋልን ወዲያውኑ አፋጣኝ እርምጃ መውሰዳችን ጥበብ ነው፤ አለበለዚያ ሰይጣን ‘የእሱን ፈቃድ እንድናደርግ ከነሕይወታችን አጥምዶ ሊይዘን’ ይችላል። (2 ጢሞ. 2:26) አስተሳሰባችንና ምኞታችን ከይሖዋ መሥፈርቶች ወጣ ማለት እንደጀመረ ካስተዋልን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ሳንዘገይ በትሕትና ወደ ይሖዋ መመለስ፣ ለምክሩ ጆሯችንን መስጠት እንዲሁም የሚነግረንን ነገር በሙሉ ልባችን ማዳመጥ አለብን። (ኢሳ. 44:22) የተሳሳተ ውሳኔ ማድረጋችን የማይሽር  ጠባሳ ትቶብን ሊያልፍ እንደሚችል መዘንጋት የለብንም፤ ምናልባትም ይህ ሥርዓት እስካለ ድረስ መዘዙ ከሚያስከትለው ሥቃይ ጋር አብረን ለመኖር እንገደድ ይሆናል። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ከባድ ችግር ውስጥ ከመግባታችን በፊት ቶሎ እርምጃ መውሰዳችን ምንኛ የተሻለ ነው!

ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበር ከሰይጣን ዘዴዎች የሚጠብቅህ እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 4-9ን ተመልከት)

ኩራትንና ስግብግብነትን ማሸነፍ

10, 11. (ሀ) አንድ ሰው ኩራት እንዳለበት የሚታወቀው እንዴት ነው? (ለ) ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን ከተከተሉት መጥፎ አካሄድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

10 ልባችን ከትክክለኛው ጎዳና ሊያርቀን እንደሚችል መገንዘብ አለብን። በውስጣችን ያለው የኃጢአት ዝንባሌ በእኛ ላይ ያለውን ኃይል አቅልለን ልንመለከተው አይገባም! እስቲ ኩራትንና ስግብግብነትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ ባሕርያት የይሖዋን ድምፅ እንዳንሰማ እንቅፋት የሚሆኑት እንዲሁም ወደ ጥፋት ጎዳና ሊመሩን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ኩሩ ሰው ለራሱ የተጋነነ አመለካከት አለው። የፈለገውን ነገር የማድረግ መብት እንዳለው ብሎም ማንም ሰው ‘እንዲህ አድርግ፣ እንዲህ አታድርግ’ ሊለው እንደማይችል ይሰማዋል። በመሆኑም የእምነት ባልንጀሮቹ፣ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሌላው ቀርቶ የይሖዋ ድርጅት የሚሉትን ነገር የመስማት ግዴታ እንደሌለበት ያስብ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው የይሖዋ ድምፅ እየራቀው ይሄዳል።

11 እስራኤላውያን በምድረ በዳ በሚጓዙበት ወቅት ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን በሙሴና በአሮን ሥልጣን ላይ ዓምፀው ነበር። እነዚህ ዓመፀኞች፣ ኩራተኛ ስለነበሩ ይሖዋን ለማምለክ የራሳቸውን ዝግጅት አደረጉ። ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? ዓመፀኞቹን በሙሉ በሞት ቀጣቸው። (ዘኍ. 26:8-10) ይህ ዘገባ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ትምህርት ይዞልናል! በይሖዋ ላይ ማመፅ ውጤቱ ጥፋት ነው። ‘ትዕቢት ጥፋትን እንደሚቀድም’ ፈጽሞ አንዘንጋ።—ምሳሌ 16:18፤ ኢሳ. 13:11

12, 13. (ሀ) ስግብግብነት ጉዳት የሚያስከትለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር። (ለ) ስግብግብነት በአጭሩ ካልተቀጨ ግለሰቡን በፍጥነት ሊቆጣጠረው የሚችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

12 እስቲ አሁን ደግሞ ስግብግብነት ምን እንደሚያስከትል እንመልከት። ስግብግብ የሆነ ሰው ዓይን ያወጣና ተገቢ ያልሆነ ምግባር ሊፈጽም ይችላል። የሶርያ የጦር አዛዥ የሆነው ንዕማን ከለምጹ በተፈወሰ ጊዜ ለነቢዩ ኤልሳዕ ስጦታ አቀረበለት፤ ነቢዩ ኤልሳዕ ግን ስጦታውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። የኤልሳዕ አገልጋይ የሆነው ግያዝ ስጦታዎቹን ለማግኘት ጎመጀ። ግያዝ “ሕያው እግዚአብሔርን! ተከትዬ ሄጄ [ከንዕማን] አንድ ነገር ማግኘት አለብኝ” ብሎ አሰበ። ከኤልሳዕ ተደብቆ ወደ ንዕማን እየሮጠ ሄደ፤ ከዚያም “አንድ መክሊት ብርና ሁለት ሙሉ ልብስ” ለማግኘት ሲል ዓይን ያወጣ ውሸት ተናገረ። ግያዝ እንዲህ በማድረጉና የይሖዋን ነቢይ በመዋሸቱ ምን ተፈጠረ? የንዕማን ለምጽ በስግብግቡ ግያዝ ላይ ተጣበቀ!—2 ነገ. 5:20-27

13 ስግብግብነት የሚጀምረው በትንሹ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና በአጭሩ ካልተቀጨ ግለሰቡን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የአካን ታሪክ ስግብግብነት ምን ያህል ኃይል እንዳለው በግልጽ ያሳያል። ስግብግብነት አካንን በምን ያህል ፍጥነት እንደተቆጣጠረው እስቲ እንመልከት። አካን እንዲህ ብሏል፦ “ከምርኮው ዕቃ መካከል ከሰናዖር የመጣ አንድ የሚያምር ካባ፣ ሁለት መቶ ሰቅል ብርና ክብደቱ አምሳ ሰቅል የሚሆን የወርቅ ቡችላ አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም።” አካን መጥፎ ምኞቱን ለማሸነፍ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ዕቃዎቹን በስግብግብነት ከሰረቀ በኋላ ድንኳኑ ውስጥ ደበቃቸው። የኋላ ኋላ ግን አካን የሠራው ኃጢአት ተጋለጠ፤ በዚህ ጊዜ ኢያሱ፣ ይሖዋ በእሱ ላይ መከራ እንደሚያመጣበት ነገረው። አካንና ቤተሰቡም በዚያኑ ዕለት በድንጋይ ተወግረው ተገደሉ። (ኢያሱ 7:11, 21, 24, 25) ማናችንም ብንሆን በስግብግብነት ወጥመድ ልንያዝ እንችላለን። በመሆኑም ራሳችንን ‘ከስግብግብነት ሁሉ መጠበቅ’ አለብን። (ሉቃስ 12:15 አ.መ.ት) እርግጥ ነው፣ አልፎ አልፎ ጤናማ ያልሆነ ወይም የብልግና ሐሳብ ወደ አእምሯችን ሊመጣ ይችላል፤ ያም ቢሆን ምኞታችን አድጎ ኃጢአት ወደ መፈጸም ደረጃ ሳይደርስ በፊት አስተሳሰባችንን መቆጣጠራችን አስፈላጊ ነው።—ያዕቆብ 1:14, 15ን አንብብ።

14. ኩራት ወይም ስግብግብነት መጥፎ አካሄድ እንድንከተል እየገፋፉን እንደሆነ ካስተዋልን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

14 ኩራትም ሆነ ስግብግብነት ጥፋት ሊያስከትሉብን ይችላሉ። የተሳሳተ አካሄድ መከተል የሚያስከትለውን  ውጤት ማሰባችን ግን እነዚህ ዝንባሌዎች የይሖዋን ድምፅ ከመስማት እንዳያግዱን ይረዳናል። (ዘዳ. 32:29) እውነተኛው አምላክ፣ ትክክለኛው ጎዳና የትኛው እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ይህን ጎዳና መከተል የሚያስገኘውን ጥቅም በተጨማሪም የተሳሳተ አካሄድ መከተል የሚያስከትለውን መዘዝ በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል። ልባችን በኩራት ወይም በስግብግብነት መንፈስ ተነሳስተን አንድ ነገር እንድናደርግ በሚገፋፋን ጊዜ መዘዙን ማሰባችን ጥበብ ነው! የስህተት አካሄድ መከተል በእኛ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እንዲሁም ቤተሰባችንንና ወዳጆቻችንን በተለይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚነካው እንዴት እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል።

ምንጊዜም ከይሖዋ ጋር የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ

15. ከይሖዋ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ስለ ማድረግ ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

15 ይሖዋ ለእኛ የሚመኘው ከሁሉ የተሻለውን ነው። (መዝ. 1:1-3) በሚያስፈልገን ጊዜ ላይ የሚያስፈልገንን መመሪያ ይሰጠናል። (ዕብራውያን 4:16ን አንብብ።) ኢየሱስ ፍጹም ሰው ቢሆንም እንኳ በራሱ ከመመካት ይልቅ ከይሖዋ ጋር አዘወትሮ የሐሳብ ልውውጥ ያደርግ ነበር፤ እንዲሁም ያለማቋረጥ ይጸልይ ነበር። ይሖዋ ኢየሱስን አስደናቂ በሆነ መንገድ ደግፎታል እንዲሁም መርቶታል። መላእክት እንዲያገለግሉት ልኮለታል፤ ቅዱስ መንፈሱን እንዲረዳው ሰጥቶታል፤ ብሎም 12ቱን ሐዋርያት ሲመርጥ መርቶታል። ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ ድምፁን በማሰማት ኢየሱስን እንደሚደግፈውና እንደሚወደው አረጋግጦለታል። (ማቴ. 3:17፤ 17:5፤ ማር. 1:12, 13፤ ሉቃስ 6:12, 13፤ ዮሐ. 12:28) እኛም እንደ ኢየሱስ በጸሎት ለይሖዋ የልባችንን ማፍሰስ ያስፈልገናል። (መዝ. 62:7, 8፤ ዕብ. 5:7) ጸሎት ከይሖዋ ጋር አዘውትረን የሐሳብ ልውውጥ እንድናደርግና እሱን የሚያስከብር ሕይወት መምራት እንድንችል ይረዳናል።

16. ይሖዋ የእሱን ድምፅ መስማት እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?

16 ይሖዋ የእሱን ምክር በቀላሉ ማግኘት እንድንችል ዝግጅት ቢያደርግልንም ምክሩን እንድንከተል አያስገድደንም። አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቅ ያስፈልገናል፤ በዚህ ጊዜ እሱም በደግነት መንፈሱን ይሰጠናል። (ሉቃስ 11:10-13ን አንብብ።) ይሁንና ‘እንዴት እንደምናዳምጥ በጥሞና ማሰብ’ ይኖርብናል። (ሉቃስ 8:18) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ፖርኖግራፊ ወይም የብልግና ፊልሞችን መመልከቱን ለማቆም ምንም ጥረት ሳያደርግ መጥፎ ስሜት ማሸነፍ እንዲችል ይሖዋ እንዲረዳው መለመኑ ግብዝነት ነው። የይሖዋ መንፈስ በሚገኝበት ቦታ ወይም ሁኔታ ላይ መገኘት ይኖርብናል። መንፈሱ ደግሞ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን። በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች በስብሰባዎቻችን ላይ ይሖዋ ሲናገር በማዳመጣቸው ከብዙ ጣጣ ድነዋል። ምክንያቱም ስብሰባ ላይ መገኘታቸው በልባቸው ውስጥ መጥፎ ምኞቶች እያቆጠቆጡ እንደሆነ እንዲያስተውሉና አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ረድቷቸዋል።—መዝ. 73:12-17፤ 143:10

ምንጊዜም የይሖዋን ድምፅ በጥሞና አዳምጡ

17. በራሳችን መታመን አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

17 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረውን የዳዊትን ሁኔታ እስቲ እንመልከት። ዳዊት ልጅ ሳለ ፍልስጤማዊ የሆነውን ግዙፉን ጎልያድን ማሸነፍ ችሎ ነበር። በኋላም ወታደር፣ ንጉሥ፣ የብሔሩ ጠባቂና ፈራጅ ሆነ። ይሁንና ዳዊት በራሱ በታመነ ጊዜ ልቡ ያታለለው ሲሆን ከቤርሳቤህ ጋር ከባድ ኃጢአት ፈጸመ፤ አልፎ ተርፎም ባሏን ኦርዮንን አስገደለው። ዳዊት ተግሣጽ ሲሰጠው በትሕትና ስህተቱን አምኖ የተቀበለ ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝምድና ለማስተካከል ጥረት አድርጓል።—መዝ. 51:4, 6, 10, 11

18. ምንጊዜም የይሖዋን ድምፅ እንድንሰማ ምን ሊረዳን ይችላል?

18 ከልክ በላይ በራሳችን ባለመታመን በ1 ቆሮንቶስ 10:12 ላይ የሚገኘውን ምክር ሥራ ላይ እናውል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አካሄዳችንን የመምራት’ ችሎታ እንደሌለን በግልጽ ይናገራል፤ በመሆኑም ወይ የይሖዋን ድምፅ አሊያም የእሱን ጠላት ድምፅ መስማታችን አይቀርም። (ኤር. 10:23) እንግዲያው አዘውትረን እንጸልይ፤ የመንፈስ ቅዱስን አመራር እንከተል፤ እንዲሁም የይሖዋን ድምፅ ምንጊዜም እንስማ።