በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ከታሪክ ማኅደራችን

“ዩሬካ ድራማ” ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያገኙ ረድቷል

“ዩሬካ ድራማ” ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያገኙ ረድቷል

“ዩሬካ!” ይህ ቃል “አገኘሁት!” የሚል ትርጉም አለው። በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሰዎች ወርቅ ለማግኘት ይራወጡ በነበረበት በ19ኛው መቶ ዘመን አንድ ሰው ወርቅ ማግኘቱን ለመግለጽ በዚህ ቃል ይጠቀም ነበር። ይሁንና ቻርልስ ቴዝ ራስልና አብረውት የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከወርቅ እጅግ የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር ይኸውም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አገኙ። በመሆኑም ይህን እውነት ለሌሎች ለማካፈል ጓጉተው ነበር።

በ1914 ክረምት ላይ በትላልቅ ከተሞች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ታሪክ የያዘውንና በዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር የተዘጋጀውን ስምንት ሰዓት የሚፈጅ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ለማየት ይጎርፉ ነበር። አስደናቂ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን፣ ጥርት ያሉ ባለ ቀለም ስላይዶችን፣ ቀልብ የሚስብ ትረካ እንዲሁም ግሩም ጣዕም ያለው ሙዚቃ አቀናብሮ የያዘው ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፊልም ከፍጥረት አጀማመር አንስቶ የሰው ልጆችን ታሪክ በመዳሰስ የኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ድረስ የሚከናወኑትን ነገሮች ያስቃኛል።—ራእይ 20:4 *

ታዲያ በትናንሽ ከተሞችና በገጠራማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ምን ዝግጅት ተደርጎ ነበር? እውነትን የተራቡ ሰዎች ይህ ፊልም እንዳያመልጣቸው በማሰብ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር ነሐሴ 1914 “ከፍጥረት ፎቶ ድራማ” ላይ ተንቀሳቃሽ ምስሉን በማውጣት በቀላሉ ከቦታ ቦታ ሊጓጓዝ የሚችል “ዩሬካ” የተባለ ድራማ አዘጋጀ። ድራማው በበርካታ ቋንቋዎች በሦስት ዓይነት መልክ ተዘጋጅቶ ነበር፦ “ዩሬካ ኤክስ” የተባለው ሙዚቃውንና ሙሉውን ትረካ የያዘ ነበር። “ዩሬካ ዋይ” የተባለው የሚደመጡትን ነገሮች በሙሉና ውብ ባለ ቀለም ስላይዶችን የያዘ ነበር። “ዩሬካ የቤተሰብ ድራማ” የተባለው ደግሞ ቤት ውስጥ እንዲታይ ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን የተወሰኑ ትረካዎችና መዝሙሮች አሉት። በቅናሽ ዋጋ የሚሸጡ የሸክላ ማጫወቻዎችና የስላይድ ማሳያ መሣሪያም ማግኘት ይቻል ነበር።

ባለ ቀለም ስላይዶችን ለማሳየት ይውል የነበረ ፕሮጀክተር

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የፊልም ማሳያ መሣሪያ ወይም ትልቅ ስክሪን መጠቀም ሳያስፈልጋቸው ይህን በነፃ የሚተላለፍ ፕሮግራም ወደ ገጠራማ ክልሎች በመውሰድ የመንግሥቱን መልእክት ወደ አዳዲስ አካባቢዎች ማዳረስ ችለው ነበር። የሚደመጡ ነገሮችን ብቻ የያዘውን “ዩሬካ ኤክስ” የተባለውን ድራማ በቀንም ሆነ በማታ ማጫወት ይቻል ነበር። “ዩሬካ ዋይ” የተባለውን ድራማ ለማጫወት የሚያገለግለው ፕሮጀክተር ያለኤሌክትሪክ ኃይል በጋዝ መብራት ሊሠራ ይችል ነበር። በፊኒሽ ቋንቋ በተዘጋጀ አንድ መጠበቂያ ግንብ ላይ የቀረበ ሪፖርት “እነዚህን ምስሎች በየትኛውም ቦታ ማሳየት እንችላለን” ብሏል። በእርግጥም ይህ ትክክል ነበር!

መላ የማያጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትላልቅ ቲያትር ቤቶችን ከመከራየት ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ በነፃ የሚገኙ ቦታዎችን ይጠቀሙ ነበር፤ ለምሳሌ ትምህርት ቤቶችን፣ የመንግሥት  ሕንፃዎችን፣ የባቡር ጣቢያዎችን አልፎ ተርፎም በትላልቅ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ እንግዳ መቀበያ ክፍሎችን ተጠቅመዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች በእህል ማከማቻ ቤት ግድግዳ ላይ ነጭ ጨርቅ በመወጠር ደጅ ላይ ሆነው ድራማውን ይመለከቱ ነበር። አንቶኒ ሀምቡክ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ገበሬዎች በእርሻ ቦታቸው ውስጥ ሰዎች ተቀምጠው ፕሮግራሙን እያዩ መደሰት እንዲችሉ ግንድ በማጋደም ወንበሮችን ያዘጋጁ ነበር።” “ዩሬካ” የሚያሳየው ቡድን አባላት፣ ፊልሙን ለማሳየት የሚጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች፣ ሻንጣቸውን እንዲሁም ማደሪያ ድንኳናቸውንና የማብሰያ ዕቃቸውን ለማጓጓዝ “በድራማ መኪና” ይጠቀሙ ነበር።

“የዩሬካ” ተመልካቾች ብዛት ከእፍኝ አንስቶ እስከ እልፍ ይደርሳል። በዩናይትድ ስቴትስ በምትገኝ 150 ነዋሪዎች ባሏት አንዲት ከተማ ውስጥ 400 የሚያህሉ ሰዎች “የዩሬካ ድራማን” ለመመልከት በአንድ የትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ ተገኝተው ነበር። በሌላ አካባቢ ደግሞ አንዳንዶች “ድራማውን” ለማየት ደርሶ መልስ 16 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዘዋል። ስዊድን በምትኖረው ሻርሎት አልበርግ ትንሽ ቤት ውስጥ ተሰብስበው የነበሩት የአካባቢው ሰዎች የተቀዱትን ንግግሮች ሲሰሙ “ልባቸው በጥልቅ ተነክቶ ነበር።” በአውስትራሊያ ባለች ርቃ በምትገኝ አንዲት ማዕድን የሚወጣባት ከተማ ውስጥ ድራማውን ለማየት 1,500 ሰዎች መጥተው ነበር። መጠበቂያ ግንብ እንደገለጸው በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች የነበሩ “አስተማሪዎችም ሆኑ ተማሪዎች በምስሎቹና ሸክላ ላይ በተቀረጹት አስደናቂ የሆኑ ንግግሮች በጣም ተማርከው ነበር።” “ዩሬካ ድራማ” የፊልም ቲያትር ቤቶች በሚገኙባቸው ቦታዎችም ሳይቀር ተወዳጅ ሆኖ ነበር።

የእውነትን ዘሮች ተንከባክቦ ማሳደግ

“ዩሬካ ድራማ” አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍሎችን ወይም ጉባኤዎችን ለማቋቋም ትልቅ እገዛ አበርክቷል፤ ቀደም ሲል ከተቋቋሙት ክፍሎች ወይም ጉባኤዎች መካከል ወደተለያዩ ቦታዎች የሚላኩት ተናጋሪዎች፣ ንግግር በመስጠትና “ዩሬካ ድራማን” በማሳየት አዳዲስ ክፍሎችን ያቋቁሙ ነበር። “ዩሬካ ድራማን” ምን ያህል ሰዎች እንዳዩት በትክክል መናገር ያዳግታል። ብዙ “የድራማው” ቅጂዎች በተደጋጋሚ ታይተዋል። ሆኖም በ1915 ከ86 “የድራማ” ቡድኖች መካከል አዘውትረው ሪፖርት ያደረጉት 14ቱ ብቻ ነበሩ። የተሟላ ሪፖርት መጠናቀር አለመቻሉ የሚያሳዝን ቢሆንም ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች “ድራማውን” እንዳዩት በዓመቱ መጨረሻ የቀረበው ሪፖርት ያሳያል። በተጨማሪም 30,000 የሚያህሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ለማግኘት ጠይቀዋል።

“ዩሬካ ድራማ” በታሪክ ውስጥ የተወው አሻራ ያን ያህል የጎላ ባይሆንም ከአውስትራሊያ እስከ አርጀንቲና፣ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ብሪታንያ ደሴቶች፣ በሕንድ እና በካሪቢያን የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ልዩ “ድራማ” አይተውታል። ከእነሱ መካከል አብዛኞቹ ከወርቅ እጅግ የሚበልጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያገኙ ሲሆን በአድናቆት “ዩሬካ!” ብለዋል።

^ አን.4 በየካቲት 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 30-32 ላይ የሚገኘውን “ከታሪክ ማኅደራችን—አንድ መቶ ዓመት ያስቆጠረ የእምነት ገድል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።