በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነትን እንዳገኘህ እርግጠኛ ነህ? ለምን?

እውነትን እንዳገኘህ እርግጠኛ ነህ? ለምን?

“ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]።”—ሮም 12:2

የአምላክ ፈቃድ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ጦር ሜዳ ዘምተው ከእነሱ የተለየ ዘር ያላቸውን ሰዎች እንዲገድሉ ነው? ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች ባለፈው 100 ዓመት ውስጥ ይህን አድርገዋል። ካቶሊክ የሆኑ የጦር ሠራዊት ቄሶች በሌላ አገር ከሚኖሩ ካቶሊኮች ጋር በተካሄዱ ጦርነቶች ላይ የሚካፈሉ ወታደሮችንና የጦር መሣሪያቸውን ባርከዋል። የፕሮቴስታንት ቀሳውስትም ተመሳሳይ ነገር አድርገዋል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዲህ ያለው ድርጊት የሚያስከትለውን እልቂት የሚያሳይ ትልቅ ምሳሌ ነው።

2, 3. የይሖዋ ምሥክሮች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትና ከዚያም በኋላ ምን ዓይነት አቋም ይዘዋል? ለምንስ?

2 በዚያ ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ምን አድርገዋል? ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውን እንደጠበቁ ታሪክ በግልጽ ያሳያል። እንዲህ ዓይነት አቋም እንዲወስዱ ምክንያት የሆናቸው ምንድን ነው? በዋነኝነት የኢየሱስ ምሳሌነትና ትምህርቱ ነው። ኢየሱስ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐ. 13:35) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ አድርገዋል።2 ቆሮንቶስ 10:3, 4ን አንብብ።

3 በመሆኑም ሕሊናቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ያሠለጠኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች ጦርነትን አይማሩም እንዲሁም በውጊያ አይካፈሉም። እንዲህ ዓይነት  ክርስቲያናዊ አቋም በመያዛቸው ምክንያት ወጣት አዋቂ እንዲሁም ወንድ ሴት ሳይል በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ስደት ደርሶባቸዋል። ብዙዎች በእስር ቤቶች እና የጉልበት ሥራ በሚሠራባቸው ካምፖች ውስጥ ተንገላተዋል። በጀርመን በናዚ የግዛት ዘመን ሕይወታቸውን ያጡ የይሖዋ ምሥክሮችም አሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በአውሮፓ ዘግናኝ ስደት ቢደርስባቸውም የይሖዋን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ ፈጽሞ አልዘነጉም። በእስር ቤቶች፣ በማጎሪያ ካምፖች እንዲሁም በግዞት በተወሰዱባቸው ቦታዎች ምሥራቹን በታማኝነት ሰብከዋል። * የይሖዋ ምሥክሮች ሩዋንዳ ውስጥ በ1994 በተካሄደው ከጦርነት የማይተናነስ የዘር ማጥፋት ዘመቻም አልተካፈሉም። በተጨማሪም የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ስትከፋፈል በተነሳው ከፍተኛ ደም መፋሰስ ያስከተለ ግጭት ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የገለልተኝነት አቋማቸውን ጠብቀዋል።

4. የይሖዋ ምሥክሮች ገለልተኛ አቋም መያዛቸው ሌሎች ምን እንዲያስተውሉ አድርጓቸዋል?

4 የይሖዋ ምሥክሮች ጥብቅ የገለልተኝነት አቋም በመያዛቸው ለአምላክና ለሰዎች ልባዊ ፍቅር እንዳላቸው በዓለም ዙሪያ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ማስተዋል ችለዋል። በሌላ አባባል እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን አሳይተዋል። ብዙ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን እንዲያምኑ ያደረጓቸው ሌሎች የአምልኳችን ገጽታዎችም አሉ።

በታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው የማስተማር ሥራ

5. የጥንቶቹ የክርስቶስ ተከታዮች ምን ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር?

5 ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ አስፈላጊ መሆኑን አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አበክሮ ገልጿል። በዓለም ዙሪያ ለሚከናወነው አገልግሎት መሠረት በመጣሉ ሥራ እንዲካፈሉ 12 ደቀ መዛሙርት መረጠ፤ ከዚያም 70 ደቀ መዛሙርትን አሠለጠነ። (ሉቃስ 6:13፤ 10:1) እነዚህ ደቀ መዛሙርት ምሥራቹን ለሌሎች ለመስበክ የተዘጋጁ ሲሆን መጀመሪያ የሚያስተምሩት አይሁዳውያንን ነበር። ከዚያም የሚያስገርም ተልእኮ ተሰጣቸው! ላልተገረዙ አሕዛብ ምሥራቹን እንዲሰብኩ ታዘዙ። ይህ መመሪያ፣ ቀናተኛ ለሆኑት አይሁዳውያን ደቀ መዛሙርት ትልቅ ለውጥ ማድረግ ጠይቆባቸው መሆን አለበት!—ሥራ 1:8

6. ጴጥሮስ፣ ይሖዋ እንደማያዳላ እንዲገነዘብ የረዳው ምንድን ነው?

6 ሐዋርያው ጴጥሮስ ከአሕዛብ ወገን ወደሆነው ቆርኔሌዎስ የተባለ ያልተገረዘ ሰው ቤት ተላከ። በዚያም ጴጥሮስ፣ አምላክ እንደማያዳላ ተገነዘበ። በዚያ ወቅት ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ተጠመቁ። ከዚያ በኋላ ክርስትና የሚሰበክበት ሰፊ መስክ ተከፈተ፤ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች እውነትን መስማትና መቀበል ቻሉ። (ሥራ 10:9-48) ምሥራቹም በዓለም ዙሪያ መሰበክ ጀመረ።

7, 8. ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ ለመርዳት ሲባል የይሖዋ ድርጅት ምን አድርጓል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

7 የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ ታሪክ እንደሚያሳየው በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች፣ በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን ምሥራቹን የመስበክና የማስተማር ሥራ በቅንዓት እየደገፉና እያደራጁ ነው። በዛሬው ጊዜ ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቶስን መልእክት ከ600 በሚበልጡ ቋንቋዎች ለማሠራጨት አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ እያደረጉ ነው፤ ምሥራቹ የሚሰበክባቸው ቋንቋዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ቀጥሏል! የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እና በመንገድ ላይ በሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ተለይተው የሚታወቁ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም በጠረጴዛዎችና በጋሪዎች ላይ ጽሑፎቻቸውን ደርድረው በማሳየት ምሥራቹን ይሰብካሉ።

8 ከ2,900 የሚበልጡ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲተረጉሙ ልዩ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። እነዚህ ተርጓሚዎች የትርጉም ሥራቸውን የሚያካሂዱት ዋና ዋና በሚባሉት ቋንቋዎች ብቻ አይደለም። በሰፊው በማይታወቁ ሆኖም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች ባሏቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎችም ጽሑፎችን ይተረጉማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በስፔን  በሚሊዮን የሚቆጠሩ የካታላን ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚጠቀሙት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሆነው በካታላን ቋንቋ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባሊያሪክ ደሴቶች፣ በአሌካንቴ፣ በአንዶራ እንዲሁም በቫሌንሲያ የሚገኙ ብዙዎች በካታላንና በዚህ ቋንቋ ቀበልኛዎች መጠቀም ጀምረዋል። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በካታላን ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እያዘጋጁ ሲሆን የካታላንን ሰዎች ልብ በሚነካው በዚህ ቋንቋ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ይካሄዳሉ።

9, 10. የአምላክ ድርጅት የሁሉም ዓይነት ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት እንደሚያሳስበው የሚያሳየው ምንድን ነው?

9 ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ ለማድረግ የሚያስችለው እንዲህ ያለው የትርጉም ሥራ በዓለም ዙሪያ እየተካሄደ ነው። በሜክሲኮ በዋነኝነት የሚነገረው ስፓንኛ ነው፤ ይሁንና ሌሎች ቋንቋዎችን የሚናገሩ በርካታ የአገሬው ተወላጆች አሉ። ከእነዚህ መካከል የማያ ሕዝቦች ይገኙበታል። በሜክሲኮ ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የማያን ቋንቋ ወደሚጠቀሙበት አካባቢ የትርጉም ቡድኑ እንዲዛወር አድርጓል። ሌላው ምሳሌ ደግሞ ኔፓልኛ ሲሆን ይህ ቋንቋ 29 ሚሊዮን ነዋሪዎች ባሉት በኔፓል ከሚነገሩት ቋንቋዎች አንዱ ነው። በአገሪቱ ውስጥ 120 ያህል ቋንቋዎች ይነገራሉ፤ ከአሥር ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በኔፓልኛ ይጠቀማሉ፤ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ ኔፓልኛ ሁለተኛ ቋንቋቸው ነው። በዚህ ቋንቋም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ይዘጋጃሉ።

10 በዓለም ዙሪያ ላሉት የትርጉም ቡድኖች የሚደረገው ድጋፍ የይሖዋ ድርጅት የመንግሥቱን ምሥራች በመላው ምድር ለማወጅ የተሰጠውን ተልእኮ ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው የሚያሳይ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ባካሄዷቸው ዘመቻዎች በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ትራክቶችን፣ ብሮሹሮችንና መጽሔቶችን ያለ ክፍያ አሠራጭተዋል። ይህን ለማድረግ ያወጡት ወጪ የሚሸፈነው “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” የሚለውን የኢየሱስን መመሪያ በተግባር የሚያውሉ የይሖዋ ምሥክሮች በፈቃደኝነት በሚያደርጉት መዋጮ ነው።—ማቴ. 10:8

በሎ ጀርመን ቋንቋ ጽሑፎችን የሚያዘጋጅ የትርጉም ቡድን (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

በሎ ጀርመን የተዘጋጁ ጽሑፎች በፓራጓይ ጥቅም ላይ ይውላሉ (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍም ተመልከት)

11, 12. የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ እያሳደረ ያለው እንዴት ነው?

11 ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንዳገኙ በጣም እርግጠኞች በመሆናቸው ከፍተኛ መሥዋዕትነት በመክፈል የተለያየ ብሔርና ዘር ላላቸው ሰዎች ምሥራቹን ይሰብካሉ። ብዙዎች በጣም አስፈላጊ በሆነው በዚህ ሥራ ላይ ለመካፈል ሲሉ ኑሯቸውን ቀላል ማድረግ፣ ሌላ ቋንቋ መማር እንዲሁም አዲስ ባሕል መልመድ አስፈልጓቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቶስ ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናቸውን  እርግጠኛ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምክንያት እነዚህ ክርስቲያኖች በዓለም ዙሪያ የሚያከናውኑት የስብከትና የማስተማር ሥራ ነው።

12 የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሁሉ የሚያደርጉት እውነትን እንዳገኙ እርግጠኛ ስለሆኑ ነው። ይሁንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን መያዛቸውን እንዲያምኑ ያደረጓቸው ሌሎች ምክንያቶችስ ምንድን ናቸው?ሮም 14:17, 18ን አንብብ።

እውነትን እንዳገኙ እርግጠኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

13. የይሖዋ ምሥክሮች የድርጅቱን ንጽሕና የሚጠብቁት እንዴት ነው?

13 በዘመናችን ያሉ ቀናተኛ ክርስቲያኖች እውነትን እንዳገኙ እርግጠኛ የሆኑበትን ምክንያት መመልከታችን ይጠቅመናል። ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ያገለገለ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ድርጅት በሥነ ምግባር ንጹሕ እንዲሆንና እንዳይበከል ለማድረግ ሲባል ማንኛውም ሰው ምክር ወይም ተግሣጽ ሊሰጠው ይችላል።” ታዲያ እንዲህ ያለ የላቀ የሥነ ምግባር አቋም ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን መሥፈርቶች በመጠበቅ እንዲሁም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የተዉትን ምሳሌ በመከተል ነው። ከዘመናዊው የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ መመልከት እንደሚቻለው የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርት ባለመጠበቃቸው ምክንያት ከክርስቲያን ጉባኤ የሚወገዱት ክርስቲያኖች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ነው። ቀደም ሲል አምላክን የሚያሳዝን አኗኗር ሲመሩ የነበሩና በኋላ ላይ የተለወጡትን ጨምሮ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ንጹሕና ምሳሌ የሚሆን ምግባር አላቸው።1 ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብብ።

14. በርካታ የተወገዱ ሰዎች ምን አድርገዋል? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

14 ቅዱስ ጹሑፋዊ መመሪያዎችን ለመከተል ሲባል ከጉባኤ ስለተወገዱ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ከእነዚህ መካከል በሺዎች የሚቆጠሩት ይከተሉ የነበረውን ክርስቲያናዊ ያልሆነ አካሄድ ትተው ንስሐ በመግባታቸው ወደ ጉባኤው ተመልሰዋል። (2 ቆሮንቶስ 2:6-8ን አንብብ።) የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደንቦች የሚከተሉ በመሆናቸው ንጹሕ የሆነ የክርስቲያን ጉባኤ ሊገኝ ችሏል፤ ይህም አምልኳቸውን ይሖዋ እንደሚቀበለው እርግጠኛ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በብዙ ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ከሚታየው ልል አቋም በተቃራኒ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጥብቅ መከተላቸው በርካታ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን መያዛቸውን እንዲያምኑ አድርጓቸዋል።

15. አንድ ወንድም እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?

15 የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ብዙ ዓመታት ያስቆጠሩ ሌሎች ክርስቲያኖችስ እውነትን እንዳገኙ እርግጠኞች የሆኑት ለምንድን ነው? በ50ዎቹ ዕድሜ የሚገኝ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ከልጅነቴ ጀምሮ ለእምነቴ መሠረት የሆኑት ሦስት ነገሮች ናቸው፤ (1) አምላክ መኖሩን፣ (2) መጽሐፍ ቅዱስን ማስጻፉንና (3) በዛሬው ጊዜ እየተጠቀመበትና እየባረከው ያለው የይሖዋ ምሥክሮችን የክርስቲያን ጉባኤ መሆኑን አምናለሁ። ለዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ስማር ለእምነቴ መሠረት የሆኑት ነገሮች በጠንካራ ማስረጃ ላይ መመሥረታቸውን ለማረጋገጥ ጥረት አድርጌያለሁ። ከዓመት ዓመት ለእያንዳንዱ መሠረት ጠንካራ ማስረጃ ስለማገኝ  እምነቴ ተጠናክሯል፤ እንዲሁም እውነትን እንዳገኘሁ ይበልጥ እርግጠኛ መሆን ችያለሁ።”

16. አንዲት እህት እውነትን እንዳገኘች እርግጠኛ የሆነችው ለምንድን ነው?

16 ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት የምታገለግል አንዲት ባለትዳር እህት ስለ ይሖዋ ድርጅት እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋን ስም ምንጊዜም የሚያውጀው ብቸኛው ድርጅት ይህ ነው። መለኮታዊው ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 7,000 ጊዜ ገደማ የሚገኝ በመሆኑ ይህ ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማኛል! ‘በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ’ የሚለውን በ2 ዜና መዋዕል 16:9 (NW) ላይ የሚገኝ የሚያበረታታ ሐሳብ እወደዋለሁ።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “እውነትን ማወቄ፣ ይሖዋ እንዲያበረታኝ የሚያስችል ሙሉ ልብ ሊኖረኝ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንድገነዘብ ረድቶኛል። ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ። እንዲሁም ኢየሱስ ስለ አምላክ ለገለጠልን ጥልቅ እውቀት አመስጋኝ ነኝ፤ ይህ እውቀት ብርታት ሰጥቶኛል።”

17. ቀደም ሲል በአምላክ መኖር የማያምን አንድ ወንድም ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ሆኗል? ለምንስ?

17 ቀደም ሲል በአምላክ መኖር የማያምን አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ፍጥረትን በመመልከት አምላክ፣ ሰዎች በሕይወት እንዲደሰቱ ፍላጎት እንዳለው ማስተዋል ችያለሁ፤ በመሆኑም መከራ ለዘላለም እንዲቀጥል እንደማይፈቅድ እርግጠኛ ነኝ። በተጨማሪም ከቀን ወደ ቀን ሰዎች ፈሪሃ አምላክ እያጡ ባሉበት በዚህ ዘመን የይሖዋ ሕዝቦች የሚያሳዩት እምነት፣ ቅንዓትና ፍቅር እየጨመረ ነው። በዘመናችን እንዲህ ያለውን ተአምር ሊያስገኝ የሚችለው የይሖዋ መንፈስ ብቻ ነው።”1 ጴጥሮስ 4:1-4ን አንብብ።

18. ሁለት ወንድሞች የተናገሩትን ስታነብ ምን ተሰማህ?

18 ለረጅም ጊዜ እውነት ቤት የቆየ ሌላ የይሖዋ ምሥክር ደግሞ የምንሰብከው ነገር እውነት እንደሆነ እንዲያምን ያደረጉትን ምክንያቶች እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “ለዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ የይሖዋ ምሥክሮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ክርስትና ለመከተል ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ አሳምኖኛል። ወደተለያዩ አገሮች ስለሄድኩ የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፋዊ አንድነት እንዳላቸው መመሥከር እችላለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት እርካታና ደስታ እንዳገኝ አድርጎኛል።” ዕድሜው ከ60 ዓመት በላይ የሆነ አንድ ወንድም ደግሞ እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ የሆነው ለምን እንደሆነ ሲጠየቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲህ ብሏል፦ “የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት በጥንቃቄ ያጠናን ሲሆን ይህም የእሱን ምሳሌነት ከፍ አድርገን እንድንመለከት አድርጎናል። በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ወደ አምላክ ለመቅረብ በሕይወታችን ላይ ማስተካከያዎች አድርገናል። መዳን የሚገኘው በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት እንደሆነ እንገነዘባለን። እንዲሁም እሱ ከሞት እንደተነሳ እናውቃለን። ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን የተመለከቱ ተአማኒ የሆኑ የዓይን ምሥክሮች ቃል ሰፍሮልናል።”1 ቆሮንቶስ 15:3-8ን አንብብ።

ያገኘነውን እውነት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19, 20. (ሀ) ጳውሎስ በሮም ለነበረው ጉባኤ ሲጽፍ የትኛውን ኃላፊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል? (ለ) ራሳችንን የወሰንን ክርስቲያኖች በመሆናችን ምን መብት አለን?

19 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሰዎችን ስለምንወድ ያገኘነውን ውድ እውነት ለራሳችን ይዘን መቀመጥ አንፈልግም። ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች ይህንን ሲያስረዳቸው እንዲህ ብሏል፦ “‘በአፍህ ውስጥ ያለውን ይህን ቃል’ ይኸውም ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በይፋ ብትናገር እንዲሁም አምላክ ከሞት እንዳስነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህ። ምክንያቱም አንድ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፤ በአፉ ደግሞ እምነቱን በይፋ ተናግሮ ይድናል።”—ሮም 10:9, 10

20 ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን ምሥክሮች በመሆናችን እውነትን እንደያዝን እርግጠኞች ነን፤ እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች ለሌሎች የማስተማር መብት እንዳለን እንገነዘባለን። የተሰጠንን የስብከት ተልእኮ ስንወጣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ ብቻ ሳይሆን የያዝነው ጎዳና እውነት መሆኑን ከልባችን እንደምናምን እንዲያዩ ለማድረግ እንጣር።

^ አን.3 የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 191-198, 448-454 ተመልከት።