ከይሖዋ ጋር የመሥራት መብታችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ!
“ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።”—1 ቆሮ. 3:9
1. ይሖዋ ስለ ሥራ ምን አመለካከት አለው? ይህስ ምን እንዲያደርግ አነሳስቶታል?
ይሖዋ በሥራው የሚደሰት አምላክ ነው። (መዝ. 135:6፤ ዮሐ. 5:17) የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱም በሚያከናውኑት ሥራ እንደ እሱ እንዲደሰቱ ስለሚፈልግ አስደሳችና እርካታ የሚያስገኝ ሥራ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ሲያከናውን የበኩር ልጁም በሥራው እንዲካፈል አድርጓል። (ቆላስይስ 1:15, 16ን አንብብ።) ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ “ዋና ባለሙያ” ሆኖ ከአምላክ ጎን እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።—ምሳሌ 8:30
2. መንፈሳዊ ፍጥረታት ምንጊዜም አስፈላጊና አርኪ ሥራ እንዳላቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?
2 መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ብንመለከት ይሖዋ ለመንፈሳዊ ልጆቹ ምንጊዜም ሥራ እንደሚሰጣቸው የሚሳዩ ብዙ ምሳሌዎችን ማግኘት እንችላለን። አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመሥራታቸው መኖሪያቸው ከሆነችው ገነት ከተባረሩ በኋላ አምላክ “ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሠይፍ ከዔድን በስተ ምሥራቅ አኖረ።” (ዘፍ. 3:24) ራእይ 22:6 እንደሚገልጸው ደግሞ ይሖዋ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ መፈጸም ያለባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ ለማሳየት መልአኩን ልኳል።”
ለሰው ልጆች የተሰጣቸው ሥራ
3. ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የአባቱን ምሳሌ የተከተለው እንዴት ነው?
3 ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ምድር ላይ ሲመላለስ ይሖዋ የሰጠውን ሥራ በደስታ ያከናውን ነበር። ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ በመከተል ለደቀ መዛሙርቱም አስፈላጊ የሆነ ሥራ ሰጥቷቸዋል። ለሚያከናውኑት ሥራ ጉጉት እንዲያድርባቸው ለማድረግ ሲል እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ እኔ የምሠራቸውን ሥራዎች ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ እሱ ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል።” (ዮሐ. 14:12) ኢየሱስ የዚህን ሥራ አጣዳፊነት ሲያጎላ ደግሞ “የላከኝን የእሱን ሥራ ቀን ሳለ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል” ብሏቸዋል።—ዮሐ. 9:4
4-6. (ሀ) ኖኅና ሙሴ፣ ይሖዋ የሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣታቸው አመስጋኞች የሆንነው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ ለሰዎች የሰጣቸውን ሥራዎች ሁሉ የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?
4 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትም የሰው ልጆች እርካታ የሚያስገኝ ሥራ ተሰጥቷቸው ነበር። አዳምና ሔዋን የተሰጣቸውን ሥራ ማከናወን ባይችሉም ሌሎች አምላክ የሰጣቸውን ሥራ አከናውነዋል። (ዘፍ. 1:28) ኖኅ ከሚመጣው የጥፋት ውኃ ለመትረፍ የሚያስችል መርከብ እንዴት እንደሚሠራ ዝርዝር መመሪያ ተሰጥቶት ነበር። እሱም ይሖዋ ያዘዘውን ምንም ሳያጓድል ፈጽሟል። እኛ ዛሬ እዚህ የተገኘነው ኖኅ የተሰጠውን ሥራ በጥንቃቄ በማከናወኑ ነው!—ዘፍ. 6:14-16, 22፤ 2 ጴጥ. 2:5
5 ሙሴ የማደሪያውን ድንኳን ስለሚገነባበትም ሆነ የክህነት ሥራውን ስለሚያደራጅበት መንገድ ዝርዝር መመሪያ ተሰጥቶት ነበር፤ እሱም መመሪያውን በጥብቅ ተከትሏል። (ዘፀ. 39:32፤ 40:12-16) ሙሴ የተሰጠውን ተልእኮ በታማኝነት በመወጣቱ እኛም ተጠቅመናል። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ የሕጉ ገጽታዎች “ለሚመጡት መልካም ነገሮች” ጥላ እንደነበሩ ተናግሯል።—ዕብ. 9:1-5, 9፤ 10:1
6 የአምላክ ዓላማ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ ሲሄድ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚሰጣቸው ኃላፊነትም የተለያየ ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚሰጣቸው ሥራ ምንጊዜም እሱን የሚያስከብርና በአምላክ ለሚያምኑ ሰዎች ጥቅም የሚያስገኝ ነው። ኢየሱስ፣ ሰው ከመሆኑ በፊትም ሆነ በምድር ላይ እያለ ካከናወነው ሥራ የዚህን እውነተኝነት መመልከት ይቻላል። (ዮሐ. 4:34፤ 17:4) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ለእኛ የተሰጠን ሥራ ይሖዋን የሚያስከብር ነው። (ማቴ. 5:16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58ን አንብብ።) ይህን የምንለው ለምንድን ነው?
ለተሰጡን ሥራዎች አዎንታዊ አመለካከት ማዳበር
7, 8. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ሥራ የማከናወን መብት አግኝተዋል? (ለ) ይሖዋ መመሪያ ሲሰጠን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
7 ይሖዋ፣ ፍጽምና የጎደላቸውን የሰው ልጆች ከእሱ ጋር አብረው እንዲሠሩ መጋበዙ በጣም አስደናቂ እንደሆነ የታወቀ ነው። (1 ቆሮ. 3:9) የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን፣ የመንግሥት አዳራሾችን ወይም ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመገንባቱ ሥራ የሚካፈሉ ሁሉ ኖኅና ሙሴ እንዳደረጉት ቃል በቃል በግንባታ ሥራ እየተካፈሉ ነው። በአካባቢህ ያለ የመንግሥት አዳራሽን በማደሱም ሆነ በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ የሚገኘውን ዋና መሥሪያ ቤታችንን በመገንባቱ ሥራ እየተካፈልክ ከሆነ በዚህ መንገድ አምላክን የማገልገል መብትህን ከፍ አድርገህ ልትመለከተው ይገባል። (በመግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።) ምክንያቱም ይህ ቅዱስ አገልግሎት ነው። በሌላ በኩል ግን ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ የሚካፈሉት በመንፈሳዊ የግንባታ ሥራ ነው። ይሄም ሥራ ቢሆን ለይሖዋ ክብር የሚያመጣና ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን የሚጠቅም ነው። (ሥራ 13:47-49) ይህን ሥራ በተሻለ መንገድ ለመሥራት የሚረዳ ጠቃሚ መመሪያ በአምላክ ድርጅት በኩል እናገኛለን። ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ አዳዲስ የሥራ ምድቦችን ይጨምራል።
8 ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ምንጊዜም ለቲኦክራሲያዊ መመሪያዎች ሲገዙ ቆይተዋል። (ዕብራውያን 13:7, 17ን አንብብ።) አንዳንድ ጊዜ፣ የተሰጠንን ሥራ በታዘዝነው መሠረት ማከናወን ያለብን ለምን እንደሆነ መጀመሪያ ላይ ላይገባን ይችላል። ያም ቢሆን ይሖዋ አስፈላጊ ነው ብሎ ያደረገውን ማንኛውንም ማስተካከያ መቀበል ጠቃሚ እንደሆነ እንገነዘባለን።
9. ሽማግሌዎች ለጉባኤው ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?
9 ሽማግሌዎች ጉባኤውን የሚመሩበት መንገድ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል። (2 ቆሮ. 1:24፤ 1 ተሰ. 5:12, 13) ተግተው ለመሥራትና ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን ለማስማማት ይጥራሉ። በመግዛት ላይ ስላለው የአምላክ መንግሥት ለመስበክ የምንጠቀምባቸውን አዳዲስ መንገዶች ለመልመድ ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። አንዳንዶች የስልክ ምሥክርነት፣ የወደብ ምሥክርነት ወይም የአደባባይ ምሥክርነት ለመስጠት መጀመሪያ ላይ አመንትተው የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ጥሩ ውጤት ማግኘት ችለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በጀርመን የሚገኙ አራት አቅኚዎች ለረጅም ጊዜ ሳይሠራበት በቆየ የንግድ አካባቢ ለማገልገል ወሰኑ። ሚካኤል እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ከተካፈልን ብዙ ዓመታት ስላለፉ ጭንቅ ብሎን ነበር። ይሖዋም ይህን ተመልክቶ መሆን አለበት፣ በጠዋቱ ክፍል ጊዜ በአገልግሎት የማይረሳ አስደሳች ጊዜ እንድናሳልፍ ረዳን። በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረጋችንና ይሖዋ እንደሚደግፈን በመታመናችን በጣም ተደሰትን!” አንተስ በአካባቢያችሁ በተጀመሩ አዳዲስ የአገልግሎት መስኮች ለመካፈል ትጓጓለህ?
10. በቅርብ ዓመታት በድርጅቱ ውስጥ ምን ማስተካከያዎች ተደርገዋል?
10 አንዳንድ ጊዜ በድርጅቱ ውስጥ ማስተካከያዎች ማድረግ ያስፈልጋል። በቅርብ ዓመታት በርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጋር ተቀላቅለዋል። እንዲህ ዓይነት ለውጦች መደረጋቸው በእነዚህ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለሚያገለግሉት ወንድሞችና እህቶች ማስተካከያ ማድረግ የሚጠይቅባቸው ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ግን ማስተካከያው ጥቅሞች እንዳሉት ለሁሉም ግልጽ ሆኗል። (መክ. 7:8) እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች በይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ የራሳቸውን ሚና መጫወት በመቻላቸው ምንኛ ደስተኞች ናቸው!
11-13. በድርጅቱ ውስጥ ማስተካከያዎች በመደረጋቸው አንዳንዶች ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል?
11 በተቀላቀሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ከሚያገለግሉት ክርስቲያኖች ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። አንዳንዶች በነበሩበት ቤቴል ውስጥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በመካከለኛው አሜሪካ በሚገኝ አነስተኛ ቤቴል ውስጥ ያገለግሉ የነበሩ አንድ ባልና ሚስት፣ እነሱ ከነበሩበት ቤቴል ወደ 30 እጥፍ ገደማ የሚበልጡ አባላት ባሉት በሜክሲኮ በሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንዲያገለግሉ ተጠየቁ። ሮሄልዮ “ወዳጅ ዘመዶቻችንን ትተን መሄድ በጣም ከብዶን ነበር” ብሏል። ወደ ሜክሲኮ እንዲዛወር የተጠየቀ ኹዋን የተባለ ሌላ ወንድም ሕይወቱን እንደገና ሀ ብሎ የጀመረ ያህል ሆኖ ተሰምቶታል፤ እንዲህ ብሏል፦ “አዳዲስ ጓደኞች ማፍራት ያስፈልጋል። እንዲሁም ከአዲስ ባሕልና አመለካከት ጋር መላመድ ይጠይቃል።”
12 ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች ወደ ጀርመን ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲዛወሩ የተጠየቁ ቤቴላውያንም ቢሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። ተራሮችን የሚወድ ማንኛውም ሰው፣ ውብ የሆኑትን የአልፕስ ተራሮች ትቶ ከስዊዘርላንድ ወደ ጀርመን መሄድ ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መረዳት አያዳግተውም። ከኦስትሪያ የመጡ ቤቴላውያን ደግሞ መጀመሪያ ላይ በአገራቸው የለመዱት ዘና ያለ ሕይወት ናፍቋቸው ነበር።
13 ወደ ሌላ አገር ተዛውረው የሚያገለግሉ ቤቴላውያን አዲስ የመኖሪያ አካባቢን መልመድ፣ ከዚያ በፊት ከማያውቋቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር መሥራት ምናልባትም ለሌላ ሥራ መሠልጠን ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም ሌላ ወደማያውቁት ጉባኤ መሄድ፣ በአዲስ ክልል ውስጥ መስበክ አንዳንድ ጊዜም ሌላ ቋንቋ መማር ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ያሉ ለውጦችን ማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ብዙ ቤቴላውያን ከእነዚህ ለውጦች ጋር ተስማምተው እየኖሩ ነው። ይህን ለማድረግ የረዳቸው ምንድን ነው?
14, 15. (ሀ) ብዙዎች የሚያከናውኑት ሥራ ምንም ይሁን ምን ከይሖዋ ጋር የመሥራት መብታቸውን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) እነዚህ ወንድሞች ለሁላችንም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?
14 ግሪቴል እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ግብዣ የተቀበልኩት ይሖዋን የምወደው፣ በአንድ አገር ወይም ሕንፃ ውስጥ እስካገለገልኩ አሊያም አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት እስካገኘሁ ድረስ ብቻ እንዳልሆነ ለማሳየት አጋጣሚ እንደሚሰጠኝ ስለተሰማኝ ነው።” ዳኢስካ ደግሞ “ግብዣውን ያቀረበልኝ ይሖዋ እንደሆነ ስለተገነዘብኩ በደስታ ተቀበልኩት” ብላለች። ኦንድሬ እና ጋብሬዬላም በዚህ ይስማማሉ፤ እንዲህ ብለዋል፦ “የራሳችንን ፍላጎት ወደኋላ ትተን ይሖዋን ለማገልገል የሚያስችለን ተጨማሪ አጋጣሚ እንደተከፈተልን ተሰማን። ‘ይሖዋ የሚያመጣውን የለውጥ ነፋስ ከመከላከል ይልቅ ሸራችንን ወጥረን ከዚያ ጋር መሄዱ የተሻለ ነው’ ብለን አሰብን።”
15 የተወሰኑ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በመዋሃዳቸው የተነሳ አንዳንድ ቤቴላውያን አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። በስዊድን፣ በኖርዌይና በዴንማርክ የነበሩ አንዳንድ ቤቴላውያን ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ ተዋህደው የስካንዲኔቪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሲቋቋም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። ከእነዚህ መካከል ፍሎሪያን እና አንያ ይገኙበታል፤ እንዲህ ብለዋል፦ “አዲሱ ምድባችን ፈታኝ ቢሆንም አስደሳች ነው። የምናገለግለው የትም ይሁን የት ይሖዋ እየተጠቀመብን መሆኑን ማወቃችን ያስደስተናል። የተትረፈረፈ በረከት አግኝተናል ብለን ብንናገር ማጋነን አይሆንብንም!” አብዛኞቻችን እንዲህ ያሉ ማስተካከያዎችን ማድረግ ባይጠበቅብንም እንኳ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች መንግሥቱን በማስቀደም ረገድ የተዉትን ምሳሌ መከተል እንችላለን። (ኢሳ. 6:8) ይሖዋ ከእሱ ጋር የሚሠሩ አገልጋዮቹ፣ የሚያከናውኑት ሥራ ምንም ይሁን ምን ከአምላክ ጋር የመሥራት መብታቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ከሆነ ምንጊዜም ይባርካቸዋል።
ከይሖዋ ጋር የመሥራት መብትህን ምንጊዜም ከፍ አድርገህ ተመልከተው!
16. (ሀ) ገላትያ 6:4 ምን እንድናደርግ ይመክረናል? (ለ) ማንኛውም ሰው ሊያገኝ የሚችለው ከሁሉ የላቀ መብት የትኛው ነው?
16 ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ይቀናቸዋል፤ ይሁንና የአምላክ ቃል እኛ ማድረግ በምንችለው ነገር ላይ እንድናተኩር ይመክረናል። (ገላትያ 6:4ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ብዙዎቻችን በድርጅቱ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ የለንም። አቅኚ፣ ሚስዮናዊ ወይም ቤቴላዊ መሆን የምንችለውም ሁላችንም አይደለንም። እነዚህ ግሩም የአገልግሎት መብቶች እንደሆኑ ጥርጥር የለውም! ያም ቢሆን ማንኛውም ሰው ሊያገኝ የሚችለው ከሁሉ የላቀ መብት ለሁላችንም እንደተዘረጋ መዘንጋት አይኖርብንም። ይህም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ከይሖዋ ጋር አብሮ መሥራት ነው። ይህ ከፍ አድርገን ልንመለከተው የሚገባ መብት ነው!
17. የሰይጣን ዓለም እስካለ ድረስ ከየትኛው እውነታ መሸሽ አይቻልም? ይህ ሁኔታ ተስፋ ሊያስቆርጠን የማይገባውስ ለምንድን ነው?
17 የሰይጣን ዓለም እስካለ ድረስ በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የምንችለው ነገር ውስን ሊሆን ይችላል። ከቤተሰብ ኃላፊነታችን፣ ከጤንነታችንና ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙን ሁኔታዎች ከቁጥጥራችን ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ግን ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ የአምላክን ስም እያወጅንና መንግሥቱን እያሳወቅን ከሆነ ከይሖዋ ጋር ለመሥራት ብቁ እንዳልሆንን ፈጽሞ ሊሰማን አይገባም። ዋናው ነገር፣ አቅምህ በፈቀደልህ መጠን ከአምላክ ጋር መሥራትህና ከአንተ የበለጠ ለመሥራት ሁኔታቸው የፈቀደላቸውን ወንድሞችህን ይሖዋ እንዲባርካቸው መጸለይህ ነው። የይሖዋን ስም የሚያወድስ ሁሉ በእሱ ፊት ውድ እንደሆነ አትዘንጋ!
18. የትኞቹን ነገሮች አሁን ለማግኘት መጣር የለብንም? ለምንስ?
18 ድክመትና አለፍጽምና ያለብን ቢሆንም ይሖዋ ከእሱ ጋር አብረን እንድንሠራ ይፈልጋል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ከአምላካችን ጋር አብረን የመሥራት መብታችንን በጣም ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን! እንግዲያው የምንፈልጋቸውን ብዙዎቹን ነገሮች አሁን ለማግኘት ከመጣር ይልቅ በአዲሱ ዓለም ይሖዋ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ይኸውም አስደሳችና ሰላማዊ የሆነ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጠን ማስታወስ ይኖርብናል፤ በዚያን ጊዜ የምንፈልጋቸውን ነገሮች እናገኛለን።—1 ጢሞ. 6:18, 19
19. ይሖዋ ለወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ዘርግቶልናል?
19 በአዲሱ ዓለም ደፍ ላይ ባለንበት በዚህ ጊዜ፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ትንሽ ሲቀራቸው ሙሴ የተናገረውን ሐሳብ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው፤ “አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ . . . እጅግ ያበለጽግሃል” ብሏቸው ነበር። (ዘዳ. 30:9) ከአርማጌዶን በኋላ በአምላክ ሥራ ተጠምደው የቆዩ ሁሉ ይሖዋ ቃል የገባላቸውን ምድር ይወርሳሉ። ከዚያም በሌላ የሥራ ምድብ ይኸውም ምድርን ውብ ገነት በማድረጉ ሥራ ላይ ያተኩራሉ!