የአንባቢያን ጥያቄዎች
በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎችና አገልጋዮች የሚሾሙት እንዴት ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ጉባኤ ያገለግሉ የነበሩትን ሽማግሌዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ለራሳችሁም ሆነ አምላክ በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤውን እንድትጠብቁ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ።” (ሥራ 20:28) በዛሬው ጊዜ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በሚሾሙበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ምን ሚና ይጫወታል?
አንደኛ፣ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ሊያሟሉት የሚገባውን ብቃት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እንዲዘግቡ የመራቸው መንፈስ ቅዱስ ነው። በ1 ጢሞቴዎስ 3:1-7 ላይ ሽማግሌዎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ 16 የተለያዩ ብቃቶች ተዘርዝረዋል። ተጨማሪ ብቃቶች ደግሞ እንደ ቲቶ 1:5-9 እና ያዕቆብ 3:17, 18 ባሉት ጥቅሶች ላይ ይገኛሉ። የጉባኤ አገልጋዮች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶች በ1 ጢሞቴዎስ 3:8-10, 12, 13 ላይ ተገልጸዋል። ሁለተኛ፣ አንድ ሰው እነዚህን ኃላፊነቶች እንዲቀበል የድጋፍ ሐሳብ የሚያቀርቡትም ሆነ ሹመቱን የሚያጸድቁት ወንድሞች አንድ ወንድም ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን በበቂ ደረጃ ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ ሲገመግሙ የይሖዋ መንፈስ እንዲመራቸው ይጸልያሉ። ሦስተኛ፣ ይህን መብት ለማግኘት የታጨው ወንድም በግል ሕይወቱ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ፍሬ ማፍራት ያስፈልገዋል። (ገላ. 5:22, 23) በመሆኑም አንድ ሰው በሚሾምበት ወቅት በእያንዳንዱ ሂደት ላይ የአምላክ መንፈስ ሚና አለው።
ይሁን እንጂ እንደዚህ ያሉትን ወንድሞች የሚሾመው ማን ነው? ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር መሠረት፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችንና አገልጋዮችን ሹመት በሚመለከት የሚቀርቡት የድጋፍ ሐሳቦች በሙሉ በአካባቢው ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ይላኩ ነበር። በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ ደግሞ በበላይ አካሉ የተሾሙ ወንድሞች እነዚህን የድጋፍ ሐሳቦች ከገመገሙ በኋላ የታጩትን ወንድሞች ሹመት ያጸድቃሉ። ቀጥሎ ቅርንጫፍ ቢሮው ውሳኔውን ለሽማግሌዎች አካል ያሳውቃል። ሽማግሌዎቹ ደግሞ በበኩላቸው አዲስ ለተሾሙት ወንድሞች ስለ ሹመቱ ይነግሯቸውና ይህን ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸውን እንዲሁም መብቱን ለመቀበል ብቁ ስለመሆናቸው ይጠይቋቸዋል። በመጨረሻም ማስታወቂያው ለጉባኤ ይነገራል።
ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ ዓይነቶቹ ሹመቶች የሚጸድቁት እንዴት ነበር? ሐዋርያት በቀጥታ ወንድሞችን የሾሙባቸው ጊዜያት አሉ፤ ለምሳሌ ለመበለቶች ምግብ እንዲያከፋፍሉ ሰባት ሰዎችን ሾመው ነበር። (ሥራ 6:1-6) እርግጥ ነው፣ እነዚህ ወንድሞች ይህን ተጨማሪ ሹመት ከመቀበላቸውም በፊት ሽማግሌዎች ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ።
በዚያ ዘመን ወንድሞች እንዴት ይሾሙ እንደነበር ቅዱሳን መጻሕፍት በዝርዝር ባይገልጹም ይህ እንዴት ይከናወን እንደነበረ አንዳንድ ፍንጮች ማግኘት እንችላለን። ጳውሎስና በርናባስ ከመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞአቸው ሲመለሱ “በየጉባኤው ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው፤ ከጾሙና ከጸለዩም በኋላ ላመኑበት ለይሖዋ አደራ ሰጧቸው” የሚል ሐሳብ እናነባለን። (ሥራ 14:23) ከዓመታት በኋላ ደግሞ ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛው ለነበረው ለቲቶ “አንተን በቀርጤስ የተውኩበት ምክንያት ያልተስተካከሉትን ነገሮች እንድታስተካክልና በሰጠሁህ መመሪያ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው” በማለት ጽፎለታል። (ቲቶ 1:5) ከጳውሎስ ጋር ወደ ብዙ ቦታዎች የተጓዘው ጢሞቴዎስም ተመሳሳይ ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ይመስላል። (1 ጢሞ. 5:22) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ወንድሞችን የሾሙት በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ሳይሆኑ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ነበሩ።
ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አሠራር በመነሳት የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል ከሽማግሌዎችና ከጉባኤ አገልጋዮች ሹመት ጋር በተያያዘ ማስተካከያ አድርጓል። ከመስከረም 1, 2014 ጀምሮ ወንድሞች የሚሾሙት በሚከተለው መንገድ ይሆናል፦ እያንዳንዱ የወረዳ የበላይ ተመልካች በወረዳው ውስጥ የድጋፍ ሐሳብ የሚቀርብላቸውን ግለሰቦች ብቃት በጥንቃቄ ይገመግማል። ከዚያም ጉባኤዎችን በሚጎበኝበት ጊዜ የድጋፍ ሐሳብ ከቀረበላቸው ወንድሞች ጋር በተቻለው መጠን በአገልግሎት አብሮ በመሥራት እነሱን በደንብ ለማወቅ ጥረት ያደርጋል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ እየጎበኘ ካለው ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል ጋር በድጋፍ ሐሳቡ ላይ ከተወያየ በኋላ በወረዳው ውስጥ ሽማግሌዎችንና አገልጋዮችን የመሾሙ ኃላፊነት የእሱ ይሆናል። ይህ ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው አሠራር ጋር የሚመሳሰል ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ የተለያዩ የሥራ ድርሻዎችን የሚያከናውኑት እነማን ናቸው? አሁንም ቢሆን የአምላክን አገልጋዮች የመመገብ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ነው። (ማቴ. 24:45-47) ይህም ከዓለም አቀፉ ጉባኤ አደረጃጀት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግን በተመለከተ አመራር መስጠት እንዲቻል በመንፈስ ቅዱስ እየታገዘ ቅዱሳን መጻሕፍትን መመርመርን ያካትታል። በተጨማሪም ሁሉንም የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት የሚሾመው ታማኙ ባሪያ ነው። እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ቢሮ ደግሞ ታማኙ ባሪያ ካስተላለፈው መመሪያ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ተግባራዊ መሆን የሚችል እርዳታ ይሰጣል። እያንዳንዱ የሽማግሌዎች አካል በአምላክ ጉባኤ ውስጥ ሹመት እንዲቀበሉ የድጋፍ ሐሳብ የሚያቀርብላቸው ወንድሞች ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን የሚያሟሉ መሆን አለመሆናቸውን በጥንቃቄ የመገምገም ከባድ ኃላፊነት አለበት። እያንዳንዱ የወረዳ የበላይ ተመልካች ደግሞ በሽማግሌዎች የቀረበለትን የድጋፍ ሐሳብ በጥንቃቄና በጸሎት ከመረመረ በኋላ ብቃቱን የሚያሟሉትን ወንድሞች የመሾም ከባድ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
ሹመቶች የሚጸድቁት እንዴት እንደሆነ ማወቃችን በጉዳዩ ላይ መንፈስ ቅዱስ ያለውን ድርሻ በደንብ ለማስተዋል ይረዳናል። ይህ ደግሞ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በተሾሙት ላይ ይበልጥ እንድንተማመንና እንድናከብራቸው ያነሳሳናል።—ዕብ. 13:7, 17
በራእይ ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሱት ሁለት ምሥክሮች እነማን ናቸው?
ራእይ 11:3 ለ1,260 ቀናት ትንቢት ስለሚናገሩ ሁለት ምሥክሮች ይገልጻል። ከዚያም ዘገባው፣ አውሬው ‘ድል እንደሚነሳቸውና እንደሚገድላቸው’ ይናገራል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ምሥክሮች “ከሦስት ቀን ተኩል” በኋላ ወደ ሕልውና የሚመለሱ ሲሆን በዚህ ጊዜ እያዩዋቸው የነበሩት ሰዎች ሁሉ ይገረማሉ።—ራእይ 11:7, 11
ሁለቱ ምሥክሮች እነማን ናቸው? በዘገባው ውስጥ ያለው ዝርዝር መግለጫ ማንነታቸውን ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። አንደኛ እነዚህ ሁለት ምሥክሮች “በሁለቱ የወይራ ዛፎችና በሁለቱ መቅረዞች የተመሰሉ” እንደሆኑ እናነብባለን። (ራእይ 11:4) ይህም በዘካርያስ ትንቢት ውስጥ የተገለጸውን መቅረዝና ሁለት የወይራ ዛፎች ያስታውሰናል። እነዚህ የወይራ ዛፎች “በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙ” እንደሆኑ የተገለጹትን ‘ሁለት ቅቡዓን’ ማለትም ገዢው ዘሩባቤልንና ሊቀ ካህናቱ ኢያሱን እንደሚያመለክቱ ተገልጿል። (ዘካ. 4:1-3, 14 የ1954 ትርጉም) ሁለተኛ፣ ሁለቱ ምሥክሮች ሙሴና ኤልያስ ከፈጸሟቸው ጋር የሚመሳሰሉ ምልክቶችን እንደሚፈጽሙ ተገልጿል።—ራእይ 11:5, 6ን ከዘኍልቍ 16:1-7, 28-35 እና ከ1 ነገሥት 17:1፤ 1 ነገሥት 18:41-45 ጋር አወዳድር።
በራእይና በዘካርያስ መጻሕፍት ላይ የሚገኙትን ዘገባዎች የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው? በሁሉም ዘገባዎች ላይ፣ በከባድ የፈተና ወቅት አመራር የሚሰጡ የአምላክ ቅቡዕ አገልጋዮች ተጠቅሰዋል። በመሆኑም በራእይ ምዕራፍ 11 ፍጻሜ መሠረት የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ በተቋቋመበት ጊዜ አመራር የሚሰጡ ቅቡዓን ወንድሞች ለሦስት ዓመት ተኩል “ማቅ ለብሰው” ሰብከዋል።
እነዚህ ቅቡዓን ማቅ ለብሰው የሚሰብኩበት ጊዜ ሲያበቃ በአንጻራዊ ሁኔታ ለአጭር ጊዜ፣ ማለትም ለሦስት ቀን ተኩል እስር ቤት መግባታቸው በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደተገደሉ ያሳያል። በአምላክ ሕዝብ ጠላቶች ዓይን ሲታይ የቅቡዓኑ ሥራ የሞተ ያህል ስለሆነ ለተቃዋሚዎች ታላቅ ደስታ አምጥቶላቸዋል።—ራእይ 11:8-10
ይሁን እንጂ ልክ በትንቢት በተነገረው መሠረት ሦስት ቀን ተኩሉ ሲያበቃ ሁለቱ ምሥክሮች ወደ ሕልውና ተመልሰዋል። እነዚህ ቅቡዓን ከእስር የተፈቱ ከመሆኑም በላይ ታማኝነታቸውን ለጠበቁት ቅቡዓን፣ አምላክ በጌታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ልዩ ሹመት ሰጥቷቸዋል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የአምላክን ሕዝቦች መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ ሲባል ከእነዚህ ቅቡዓን መካከል የተወሰኑት በ1919 “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው ተሹመዋል።—ማቴ. 24:45-47፤ ራእይ 11:11, 12
የሚገርመው ነገር ራእይ 11:1, 2 እነዚህን ክስተቶች መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ከሚለካበት ወይም ከሚመረመርበት ጊዜ ጋር አያይዞ ይጠቅሳቸዋል። ሚልክያስ ምዕራፍ 3 መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ተመሳሳይ ምርመራ እንደሚካሄድበትና ከዚያም ቤተ መቅደሱ እንደሚነጻ ይገልጻል። (ሚል. 3:1-4) ይህ የምርመራና የማንጻት ሥራ ምን ያህል ጊዜ ወስዷል? ከ1914 ጀምሮ እስከ 1919 መጀመሪያ ድረስ የዘለቀ ነበር። ይህ ወቅት 1,260 ቀናትን (42 ወራት) እና በራእይ ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሰውን ምሳሌያዊ ሦስት ቀን ተኩል ያጠቃልላል።
ይሖዋ ሕዝቡን አጥርቶ ለመልካም ሥራ የሚቀና ልዩ ሕዝብ ለማድረግ ይህን መንፈሳዊ የማንጻት ሥራ በማዘጋጀቱ ምንኛ ደስተኞች ነን! (ቲቶ 2:14) በተጨማሪም በዚያ የፈተና ወቅት አመራር በመስጠት ምሳሌያዊ ሁለት ምሥክሮች በመሆን ያገለገሉ ታማኝ ቅቡዓን የተዉትን ምሳሌ እናደንቃለን። *
^ አን.18 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 22 አንቀጽ 12ን ተመልከት።