በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዚህ አሮጌ ዓለም መጨረሻ አንድነታችንን ማጠናከር

በዚህ አሮጌ ዓለም መጨረሻ አንድነታችንን ማጠናከር

“ሁላችንም የአንድ አካል ክፍሎች ነን።”—ኤፌ. 4:25

1, 2. አምላክ፣ ወጣትም ሆነ አዋቂ ከሆኑ አገልጋዮቹ ምን ይጠብቃል?

ወጣት ነህ? ከሆነ ዓለም አቀፍ በሆነው የይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለህ ሊሰማህ ይገባል። በብዙ አገሮች ውስጥ ራሳቸውን ወስነው ከሚጠመቁት መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። በርካታ ወጣቶች ይሖዋን ለማገልገል እንደወሰኑ መመልከት ምንኛ የሚያበረታታ ነው!

2 ወጣት እንደመሆንህ መጠን ከሌሎች ወጣቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስትህ ይሆናል። ሁላችንም ብንሆን ከእኩዮቻችን ጋር መጫወት እንደሚያስደስተን የታወቀ ነው። ወጣቶችም ሆንን አዋቂዎች እንዲሁም አስተዳደጋችን ምንም ሆነ ምን አምላክ በአንድነት እንድናመልከው ይፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” መሆኑን ጽፏል። (1 ጢሞ. 2:3, 4) በራእይ 7:9 ላይ “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች” ስለተውጣጡ የአምላክ አገልጋዮች የሚገልጽ ሐሳብ እናገኛለን።

3, 4. (ሀ) በዛሬው ጊዜ በሚገኙ በርካታ ወጣቶች ዘንድ ምን ዓይነት መንፈስ በስፋት ይታያል? (ለ) በኤፌሶን 4:25 ላይ ከተገለጸው ሐሳብ ጋር የሚስማማው የትኛው አመለካከት ነው?

3 ወጣት በሆኑ የይሖዋ አገልጋዮችና በዓለም ላይ ባሉ ወጣቶች መካከል ያለው ልዩነት ምንኛ ሰፊ ነው! ይሖዋን የማያገለግሉ ብዙ ወጣቶች እነሱ በሚፈልጉት ነገር ላይ ብቻ ያተኮረና ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ሕይወት ይመራሉ። አንዳንድ ተመራማሪዎች እንዲህ ያሉትን ወጣቶች “እኔ ብቻ የሚል ትውልድ” በማለት ይጠሯቸዋል። እነዚህ ወጣቶች በአነጋገራቸውም ሆነ በአለባበሳቸው ለቀደመው ትውልድ ንቀት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሲሆን በዕድሜ ከእነሱ የሚበልጡ ሰዎችን ኋላ ቀር እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል።

4 ይህ ዓይነቱ መንፈስ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ ይገኛል። በመሆኑም ወጣት የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲህ ካለው መንፈስ ለመራቅና የአምላክ ዓይነት አመለካከት ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም እንኳ ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ” ካለው መንፈስና በአንድ ወቅት ‘ይመላለሱበት ከነበረው’ መንገድ እንዲርቁ ማሳሰብ አስፈልጎታል። (ኤፌሶን 2:1-3ን አንብብ።) እንደዚህ ካለው መንፈስ የመራቅን አስፈላጊነት የሚገነዘቡና ከሁሉም ወንድሞቻቸው ጋር በአንድነት ለመሥራት ጥረት የሚያደርጉ ወጣቶች ሊመሰገኑ ይገባል። እንዲህ ያለው አመለካከት ጳውሎስ “ሁላችንም የአንድ አካል ክፍሎች ነን” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ኤፌ. 4:25) ይህ አሮጌ ዓለም ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ሲሄድ በአንድነት አብረን መሥራታችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናል። አንድነታችንን ጠብቀን የመኖርን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ የሚረዱ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

አንድነት ነበራቸው

5, 6. የሎጥና የሴቶች ልጆቹ ታሪክ የአንድነትን አስፈላጊነት በተመለከተ ምን ያስተምረናል?

5 ባለፉት ዘመናት የአምላክ ሕዝቦች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመወጣት በአንድነት ሆነው እርስ በርስ ሲረዳዱ ይሖዋ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። በዘመናችንም ወጣትም ሆኑ አዋቂ የአምላክ አገልጋዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ ምሳሌዎች ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። እስቲ የሎጥን ታሪክ እንመልከት።

6 ሎጥና ቤተሰቡ የሚኖሩባት የሰዶም ከተማ ልትጠፋ በመሆኑ አደገኛ ሁኔታ ተጋርጦባቸው ነበር። በመሆኑም የአምላክ መላእክት “ሕይወታችሁን ለማትረፍ . . . ሽሹ” በማለት ከጥፋቱ ለማምለጥ ከሰዶም ወጥተው ወደ ተራራማው አካባቢ እንዲሄዱ አሳሰቧቸው። (ዘፍ. 19:12-22) ሎጥም መላእክቱን የታዘዘ ሲሆን ሁለቱ ልጆቹም ከእሱ ጋር በመተባበር ከከተማዋ ወጡ። የሚያሳዝነው ግን ለእነሱ ቅርብ የነበሩት ሰዎች ይህን አላደረጉም። የሎጥ ልጆች እጮኛ የነበሩት ወንዶች፣ በዕድሜ የሚበልጣቸው ሎጥ ‘የሚቀልድ መስሏቸው’ ነበር። እርምጃ አለመውሰዳቸው ሕይወታቸውን አሳጣቸው። (ዘፍ. 19:14) ከጥፋቱ የተረፉት ሎጥና ከእሱ ጋር አንድነት የነበራቸው ሴቶች ልጆቹ ብቻ ነበሩ።

7. እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡበት ወቅት ይሖዋ አንድነት የነበረውን ሕዝብ የረዳው እንዴት ነው?

7 ሌላ ምሳሌ እንመልከት። እስራኤላውያን ከግብፅ ሲወጡ በተለያዩ ቡድኖች እንደተከፋፈሉ ወይም እያንዳንዱ ቡድን የራሱን መንገድ ተከትሎ እንደሄደ የሚገልጽ ዘገባ አናገኝም። ‘ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ በዘረጋበት’ እና ይሖዋ ቀይ ባሕርን በከፈለበት ወቅት ሙሴ ብቻውን ወይም ጥቂት እስራኤላውያንን አስከትሎ አልተሻገረም። ከዚህ ይልቅ መላው ጉባኤ ይሖዋ ጥበቃ እያደረገለት ባሕሩን ተሻግሯል። (ዘፀ. 14:21, 22, 29, 30) ሕዝቡ አንድነት የነበረው ሲሆን ከእስራኤላውያን ወገን ያልሆነ “ቍጥሩ የበዛ ሌላ ድብልቅ ሕዝብ” ከእነሱ ጋር ነበር። (ዘፀ. 12:38) በዚያ ወቅት አንዳንድ ግለሰቦች ምናልባትም የተወሰኑ ወጣቶች የተሻለ ብለው ያሰቡትን መንገድ ተከትለው በራሳቸው መንገድ ሄደዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። እንዲህ በማድረግ የይሖዋን ጥበቃ አጥተው ቢሆን ኖሮ ይህ ሞኝነት አይሆንም ነበር?—1 ቆሮ. 10:1

8. በኢዮሣፍጥ ዘመን የአምላክ ሕዝቦች አንድነት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

8 በንጉሥ ኢዮሣፍጥ ዘመን፣ በአምላክ ሕዝቦች ዙሪያ የነበሩ ጠላቶች እነሱን ለመውጋት ብርቱ የሆነ “ግዙፍ ሰራዊት” አሰልፈው መጡ። (2 ዜና 20:1, 2) የአምላክ አገልጋዮች ግን ጠላቶቻቸውን በራሳቸው ኃይል ለመመከት አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን እርዳታ ጠየቁ። (2 ዜና መዋዕል 20:3, 4ን አንብብ።) ይህንን ያደረጉት ደግሞ እያንዳንዳቸው መልካም መስሎ እንደታያቸው ወይም እንዳሰኛቸው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃኖቻቸው ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር” ይላል። (2 ዜና 20:13) ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች በይሖዋ በመታመን የእሱን መመሪያ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል፤ ይሖዋም ከጠላቶቻቸው ታድጓቸዋል። (2 ዜና 20:20-27) ታዲያ ይህ የአምላክ ሕዝቦች በአንድነት ሆነው ፈታኝ ሁኔታዎችን እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ አይደለም?

9. ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች ድርጊትና አመለካከት ስለ አንድነት ምን እንማራለን?

9 የጥንቶቹ ክርስቲያኖችም በአንድነት በመሥራት ይታወቁ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በርካታ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተቀየሩ ሰዎች ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ ምን እንዳደረጉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “የሐዋርያቱንም ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ፤ ያላቸውን ነገር ሁሉ አብረው ይካፈሉ፣ ምግባቸውንም አብረው ይበሉ እንዲሁም በጸሎት ይተጉ ነበር” ይላል። (ሥራ 2:42) በተለይ ስደት ባጋጠማቸውና እርስ በርስ መረዳዳት ባስፈለጋቸው ጊዜ ይህ አንድነታቸው በግልጽ ታይቷል። (ሥራ 4:23, 24) አንተስ በአስቸጋሪ ወቅቶች በአንድነት መሥራት አስፈላጊ ነው ቢባል አትስማማም?

የይሖዋ ቀን እየቀረበ ሲመጣ አንድ መሆን

10. አንድነት ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆነው መቼ ነው?

10 በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስጨናቂ የሆነው ጊዜ እየቀረበ ነው። ነቢዩ ኢዩኤል ይህን ወቅት “የጨለማና የጭጋግ ቀን” በማለት ገልጾታል። (ኢዩ. 2:1, 2፤ ሶፎ. 1:14) የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ወቅት አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። ኢየሱስ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል” በማለት እንደተናገረ መዘንጋት አይኖርብንም።—ማቴ. 12:25

11. በዘመናችን ባሉ የአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሠራው በመዝሙር 122:3, 4 ላይ የሚገኘው የትኛው ሐሳብ ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

11 ወደፊት በሚመጣው አስጨናቂ ወቅት አንድነታችንን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል። በዚህ ጊዜ ሊኖረን የሚገባው አንድነት በጥንቷ ኢየሩሳሌም የነበሩት ቤቶች እርስ በርስ ተጠጋግተው የተሠሩ ከመሆናቸው ጋር ሊነጻጸር ይችላል። እነዚያ ቤቶች በጣም ተቀራርበው የተገነቡ ስለነበሩ መዝሙራዊው “ኢየሩሳሌም እጅግ እንደ ተጠጋጋች፣ ከተማ ሆና ተሠርታለች” ብሏል። ይህም ነዋሪዎቹ አንዳቸው ለሌላው እርዳታ ማበርከትና ጥበቃ ማድረግ እንዲችሉ አጋጣሚ ከፍቷል። ከዚህም ሌላ ቤቶቹ የተጠጋጉ መሆናቸው “የእግዚአብሔር ነገዶች” ለአምልኮ ሲሰባሰቡ መላው ብሔር የሚኖረውን አንድነት ሊያመለክት ይችላል። (መዝሙር 122:3, 4ን አንብብ።) እኛም በዛሬው ጊዜም ሆነ ወደፊት በሚመጣው አስጨናቂ ወቅት “እጅግ እንደ ተጠጋጋች” ከተማ መሆን ያስፈልገናል።

12. ወደፊት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከሚሰነዘረው ጥቃት ጥበቃ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

12 በዚያ ወቅት እርስ በርስ ‘መጠጋጋታችን’ በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር የሚገልጽ ትንቢት ይዟል። በዚህ ጊዜ ምንም ነገር እንዲከፋፍለን መፍቀድ አይኖርብንም። እርዳታ ለማግኘት ወደ ዓለም ዘወር እንደማንል የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ከወንድሞቻችን ጋር መቀራረብ ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ መዳን የምናገኘው የአንድ ቡድን አባል በመሆናችን ብቻ አይደለም። ይሖዋ እና ኢየሱስ የአምላክን ስም የሚጠሩትን ሁሉ ከዚህ ጥፋት ያድኗቸዋል። (ኢዩ. 2:32፤ ማቴ. 28:20) ያም ቢሆን ከአምላክ መንጋ ጋር አንድነት የሌላቸው በሌላ አባባል ከዚህ መንጋ ተለይተው የራሳቸውን አካሄድ የሚከተሉ ሰዎች እንደሚድኑ ማሰብ ምክንያታዊ ነው?—ሚክ. 2:12

13. ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወጣቶች እስከ አሁን ከተመለከትናቸው ነገሮች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

13 ከአምላክ ሕዝብ ተለይተው በራሳቸው ዓለም የሚኖሩ ወጣቶችን አካሄድ መከተል ሞኝነት መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አንዳችን ለሌላው በጣም የምናስፈልግበት ጊዜ እየቀረበ ነው። ይህም ወጣት አዋቂ ሳይል ሁላችንንም የሚነካ ነው! ከሌሎች ጋር አብረን መሥራትን ለመማርና ወደፊት በጣም የሚያስፈልገንን አንድነት ለማዳበር ጊዜው አሁን ነው።

“አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን”

14, 15. (ሀ) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ወጣቶችንም ሆነ አዋቂዎችን እያሠለጠነ ያለው የትኛውን ዓላማ ለማሳካት ሲል ነው? (ለ) ይሖዋ አንድነት እንዲኖረን ለማበረታታት ምን ምክር ሰጥቶናል?

14 ይሖዋ፣ እርስ በርስ “ተስማምተው እንዲያገለግሉት” አገልጋዮቹን እየረዳቸው ነው። (ሶፎ. 3:8, 9) ከዘላለማዊ ዓላማው ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ እንድንችል እያሠለጠነን ነው። ይህ ዓላማ ምንን ይጨምራል? ዓላማው “ሁሉንም ነገሮች . . . በክርስቶስ አንድ ላይ ለመጠቅለል ነው።” (ኤፌሶን 1:9, 10ን አንብብ።) አምላክ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ፈቃደኛ የሆኑ ፍጥረታት በሙሉ አንድነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይፈልጋል፤ ደግሞም ይህንን ዓላማውን ማሳካቱ አይቀርም። ወጣት ከሆንክ ይህን ማወቅህ ከይሖዋ ድርጅት ጋር በአንድነት የመሥራትን አስፈላጊነት እንድትገነዘብ አያደርግህም?

15 ይሖዋ ለዘላለም አንድነት እንዲኖረን ስለሚፈልግ ከአሁኑ ኅብረት እንዲኖረን እያሠለጠነን ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት ‘እርስ በርሳችሁ እኩል ተሳሰቡ፣’ “እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፣” “ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ” እንዲሁም “እርስ በርስ መተናነጻችሁን ቀጥሉ” በማለት በተደጋጋሚ ይመክሩናል። (1 ቆሮ. 12:25፤ ሮም 12:10፤ 1 ተሰ. 4:18፤ 5:11) ይሖዋ፣ ክርስቲያኖች ፍጹማን እንዳልሆኑ ያውቃል፤ ይህ ደግሞ አንድነታችንን መጠበቅ ተፈታታኝ እንዲሆንብን ሊያደርግ ስለሚችል “እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልገናል።—ኤፌ. 4:32

16, 17. (ሀ) የክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አንዱ ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) ወጣቶች ኢየሱስ በወጣትነቱ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

16 ይሖዋ፣ አንድነት እንዲኖረን ለማሠልጠን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ይጠቀማል። በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ የሚገኘውን ማበረታቻ ብዙ ጊዜ አንብበነዋል። የእነዚህ ስብሰባዎች አንዱ ዓላማ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት [እንድንሰጥ]” ማነሳሳት ነው። ስብሰባዎች የሚዘጋጁት “ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ እርስ በርስ [እንድንበረታታ]” መሆኑም ትኩረት የሚስብ ነው።

17 ኢየሱስ ወጣት እያለ ለዚህ ዝግጅት አድናቆት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። የ12 ዓመት ልጅ እያለ በአንድ ትልቅ መንፈሳዊ ስብሰባ ላይ ከወላጆቹ ጋር ተገኝቶ ነበር። በሆነ ወቅት ላይ ወላጆቹ ሊያገኙት አልቻሉም፤ ይህ የሆነው ግን ከሌሎች ወጣቶች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ስለሄደ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዮሴፍና ማርያም ሲያገኙት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካሉት መምህራን ጋር መንፈሳዊ ውይይት እያደረገ ነበር።—ሉቃስ 2:45-47

18. ጸሎት ለአንድነታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?

18 ለወንድሞቻችን ፍቅር ከማዳበርና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አንድነታችንን ከማጠናከር በተጨማሪ አንዳችን ለሌላው መጸለይ ይኖርብናል። ወንድሞቻችንን ጠቅሰን ወደ ይሖዋ መጸለያችን አንዳችን ለሌላው ማሰብ እንዳለብን እንድናስታውስ ይረዳናል። ይህን ማድረግ የሚችሉትና የሚጠበቅባቸው አዋቂ የሆኑ ክርስቲያኖች ብቻ አይደሉም። ወጣት ከሆንክ ይህን ዝግጅት ከመንፈሳዊ ቤተሰብህ ጋር የቀረበ ዝምድና ለመመሥረት ትጠቀምበታለህ? እንዲህ ማድረግህ ከዚህ አሮጌ ዓለም ጋር አብረህ እንዳትጠፋ ይጠብቅሃል።

ሁላችንም ስለ ወንድሞቻችን መጸለይ እንችላለን (አንቀጽ 18ን ተመልከት)

“አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል” መሆናችንን ማሳየት

19-21. (ሀ) “አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል” መሆናችንን ማሳየት የምንችለው በየትኛው መንገድ ነው? ምሳሌ ስጥ። (ለ) አንዳንድ ወንድሞች አደጋ ሲደርስ ከወሰዱት እርምጃ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

19 የይሖዋ ሕዝቦች በሮም 12:5 ላይ ከሚገኘው “አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን” ከሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ እየኖሩ ነው። የዚህን እውነተኝነት የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ከወሰድነው እርምጃ ማየት ይቻላል። ታኅሣሥ 2011 በተከሰተ ኃይለኛ ማዕበል የተነሳ ሚንዳናው የተባለች የፊሊፒንስ ደሴት በጎርፍ ተጥለቀለቀች። በአንድ ሌሊት ከ40,000 በላይ ቤቶች በውኃ ተጥለቀለቁ፤ ከእነዚህ መካከል የበርካታ ወንድሞቻችን ቤቶች ይገኙበታል። የሚገርመው ግን ቅርንጫፍ ቢሮው እንደገለጸው “የእርዳታ ኮሚቴዎቹ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት እንኳ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች የእርዳታ ቁሳቁሶች መላክ ጀምረው ነበር።”

20 በተመሳሳይም ምሥራቃዊ ጃፓን በከባድ ርዕደ መሬትና ይህን ተከትሎ በተከሰተ ሱናሚ በተመታችበት ወቅት በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብዙ ነገር አጥተዋል። አንዳንዶች ንብረታቸው በሙሉ ወድሟል። ከመንግሥት አዳራሹ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትኖረው ዮሺኮ ቤቷን አጥታለች። እንዲህ ብላለች፦ “የወረዳ የበላይ ተመልካቹና አንድ ሌላ ወንድም የመሬት መናወጡ በተከሰተ ማግሥት እኛን ለመፈለግ መጥተው እንደነበረ በኋላ ላይ ስናውቅ ተገረምን።” ከዚያም ፊቷ በፈገግታ ተሞልቶ እንደሚከተለው በማለት ተናግራለች፦ “በጉባኤ በኩል መንፈሳዊ ፍላጎታችን ሙሉ በሙሉ ስለተሟላልን በጣም አመስጋኞች ነን። ከዚህም ሌላ ኮት፣ ጫማ፣ ቦርሳ እንዲሁም የሌሊት ልብስ ተሰጥቶናል።” የእርዳታ ኮሚቴው አባል የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በመላው ጃፓን የሚገኙ ወንድሞች እንደ አንድ በመሆን እርስ በርስ ተረዳድተዋል። ሌላው ቀርቶ እርዳታ ለመስጠት ሲሉ ከዩናይትድ ስቴትስ እንኳ የመጡ ወንድሞች ነበሩ። ይህን ሁሉ ርቀት ተጉዘው የመጡት ለምን እንደሆነ ሲጠየቁ ‘በጃፓን ካሉ ወንድሞቻችን ጋር አንድ ነን፤ እነሱ ደግሞ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል’ ብለዋል።” አንተስ ለአባላቱ ይህን ያህል በሚያስብ ድርጅት ውስጥ በመታቀፍህ አትኮራም? ይሖዋ እንዲህ ያለ የአንድነት መንፈስ ሲመለከት በጣም እንደሚደሰት ምንም ጥርጥር የለውም።

21 በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ዓይነት መንፈስ ማዳበራችን፣ ወደፊት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ካሉ ወንድሞቻችን ጋር መገናኘት ባንችል እንኳ ችግሩን በአንድነት ለመወጣት ይረዳናል። እንዲያውም እንዲህ ያለው መንፈስ ይህ አሮጌ ዓለም ሊጠፋ ሲል ለሚያጋጥሙን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያሠለጥነናል። በጃፓን ዝናብ የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ካስከተለው አደጋ የተረፈችው ፉሚኮ እንዲህ ብላለች፦ “መጨረሻው በጣም ቀርቧል። የተፈጥሮ አደጋዎች የማይኖሩበትን ጊዜ እየተጠባበቅን ባለንበት ወቅት የእምነት ባልንጀሮቻችንን ምንጊዜም ለመርዳት ዝግጁ መሆን ያስፈልገናል።”

22. ክርስቲያናዊ አንድነት ምን ዘላቂ ጥቅም ያስገኛል?

22 በአሁኑ ጊዜ አንድነታቸውን ለማጠናከር የሚጥሩ ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች፣ መከፋፈል በነገሠበት በዚህ ክፉ ዓለም ላይ ከሚደርሰው ጥፋት ለመትረፍ ራሳቸውን እያዘጋጁ ነው። አምላካችን ቀደም ባሉት ዘመናት እንዳደረገው ሁሉ ወደፊትም ሕዝቡን ይታደጋል። (ኢሳ. 52:9, 10) ከሚተርፉት መካከል መሆን የምትችለው አንድነት ካለው የአምላክ ሕዝብ ጋር ከተባበርክ እንደሆነ ምንጊዜም አስታውስ። ከጥፋቱ ለመትረፍ የሚረዳህ ሌላው ነገር ደግሞ ለተቀበልከው ነገር አድናቆት ማሳየት ነው። ይህ ሐሳብ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።