በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

አስከሬን ማቃጠል ለክርስቲያኖች ተገቢ ነው?

አስከሬን ማቃጠልም ሆነ አለማቃጠል የግል ውሳኔ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ልማድ አስመልክቶ በቀጥታ ሐሳብ ባይሰጥም የንጉሥ ሳኦልና የልጁ የዮናታን አስከሬን እንደተቃጠለና ከዚያ በኋላ እንደተቀበረ ልብ ማለት ያስፈልጋል። (1 ሳሙ. 31:2, 8-13)—6/15 ገጽ 7

መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ የሚያደርገው አምላክ እንዳልሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

አምላክ በመንገዶቹ ሁሉ ጻድቅ ነው። እሱ ፍትሐዊ፣ ታማኝና ትክክለኛ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ከአንጀት የሚራራና መሐሪ ነው። (ዘዳ. 32:4፤ መዝ. 145:17፤ ያዕ. 5:11)—7/1 ገጽ 4

ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ወደ ሌላ አገር የሚሄዱ አስፋፊዎች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ?

ሦስቱ ተፈታታኝ ሁኔታዎች (1) የተለየ አኗኗርን መልመድ፣ (2) ናፍቆትን መቋቋም እና (3) ከአካባቢው ወንድሞች ጋር መላመድ ናቸው። እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች የተወጡ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በእጅጉ ተባርከዋል።—7/15 ከገጽ 4-5

የዮሴፍ ወንድሞች በጠላትነት የተነሱበት ለምን ነበር?

አንደኛው ምክንያት ያዕቆብ ለዮሴፍ ልዩ ልብስ በመስጠት ከሁሉም አብልጦ እንደሚወደው ማሳየቱ ነው። የዮሴፍ ወንድሞች ስለቀኑበት በባርነት ሸጡት።—8/1 ከገጽ 11-13

አዳዲሶቹ ትራክቶች ውጤታማና ለአጠቃቀም ቀላል እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

ሁሉም የተዘጋጁበት መንገድ ተመሳሳይ ነው። ትራክቶቹ፣ ተስማሚ የሆነ አንድ ጥቅስ እንድናነብና ለቤቱ ባለቤት ጥያቄ እንድናቀርብ ያበረታቱናል። ግለሰቡ የሚሰጠን መልስ ምንም ሆነ ምን፣ ትራክቱን ገልጠን መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ልናሳየው እንችላለን። በተጨማሪም ተመላልሶ መጠይቅ ለማድረግ ተመልሰን ስንመጣ የምንወያይበትን አንድ ጥያቄ ከትራክቱ ላይ ልናሳየው እንችላለን።—8/15 ከገጽ 13-14

ሲሪያክ ፐሺታ ምንድን ነው?

ከአረማይክ ቋንቋ ቀበሌኛዎች አንዱ የሆነው ሲሪያክ በሰፊው ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ነው። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በከፊል ለመጀመሪያ ጊዜ የተተረጎሙት በሲሪያክ ቋንቋ ሳይሆን አይቀርም። በሲሪያክ የተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ ፐሺታ በመባል ይታወቃል።—9/1 ከገጽ 13-14

ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ እረኛ መንከባከብ የሚችሉት እንዴት ነው?

ልጆቻችሁን በደንብ ማወቅ እንድትችሉ ሲናገሩ ማዳመጥ ወሳኝ ነው። እነሱን በመንፈሳዊ ለመመገብ ጥረት አድርጉ። ልጆቻችሁ ለምሳሌ ከእምነታችሁ ጋር የተያያዘ ጥርጣሬ ቢፈጠርባቸው ይህን ለማስወገድ በፍቅር አመራር ስጧቸው።—9/15 ከገጽ 18-21

በአምላክ መንግሥት ሥር የማይኖሩት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

የጤና ችግሮች፣ ሞት፣ ሥራ አጥነት፣ ጦርነት፣ የምግብ እጥረትና ድህነት አይኖሩም።—10/1 ከገጽ 6-7

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ቃል ኪዳኖች ውስጥ ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙ እንዲኖሩ የሚያስችለው የትኛው ነው?

ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የመጨረሻውን የማለፍ በዓል ካከበረ በኋላ ከታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል፤ ይህም የመንግሥት ቃል ኪዳን ይባላል። (ሉቃስ 22:28-30) ይህ ቃል ኪዳን፣ ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ እንደሚገዙ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል።—10/15 ከገጽ 16-17

ሰይጣን በእውን ያለ አካል መሆኑን የሚያረጋግጡ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ሰይጣን ኢየሱስን ለመፈተን ሲል እንዳነጋገረው ይገልጻሉ። በተጨማሪም በኢዮብ ዘመን ሰይጣን ከአምላክ ጋር ተነጋግሯል። እነዚህ ዘገባዎች ሰይጣን በእውን ያለ አካል እንደሆነ ያረጋግጣሉ።—11/1 ከገጽ 4-5

በሐዋርያት ሥራ 15:14 ላይ ያዕቆብ “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች” በማለት የጠቀሳቸው እነማን ነበሩ?

አምላክ የተመረጠ ዘር እንዲሆኑና “የእሱን ድንቅ ባሕርያት በስፋት [እንዲያስታውቁ]” የመረጣቸው አይሁዳውያንና አይሁዳውያን ያልሆኑ አማኞች ነበሩ። (1 ጴጥ. 2:9, 10)—11/15 ከገጽ 24-25

ቲምጋድ የት ነበረች? በዚያ የነበሩ አንዳንዶች ምን አመለካከት ነበራቸው?

ቲምጋድ፣ በሰሜን አፍሪካ (በዘመናዊቷ አልጀሪያ) የምትገኝ አንዲት ትልቅ የሮማውያን ከተማ ነበረች። በቁፋሮ የወጣ በድንጋይ ላይ የተቀረጸ አንድ ጽሑፍ በዚያ የነበሩ አንዳንዶች የነበራቸውን አመለካከት ያሳያል፤ ጽሑፉ “ማደን፣ መታጠብ፣ መጫወት፣ መሣቅ—ሕይወት ማለት እንደዚህ ነው!” ይላል። ይህ አስተሳሰብ በ1 ቆሮንቶስ 15:32 ላይ ከተጠቀሰው አመለካከት ጋር ተመሳሳይ ነው።—12/1 ከገጽ 8-10