በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ስሙ፤ የሚነገረውን አስተውሉ’

‘ስሙ፤ የሚነገረውን አስተውሉ’

“ሁላችሁም ስሙኝ፤ የምናገረውንም አስተውሉ።”—ማር. 7:14

1, 2. ኢየሱስን ያዳምጡ የነበሩ ብዙ ሰዎች የተናገረውን ማስተዋል ያቃታቸው ለምን ነበር?

አንድ ሰው ሲያነጋግረን እንሰማው እንዲሁም የድምፁን ቃና እናስተውል ይሆናል። ሆኖም የሚናገረውን ነገር ትርጉም ማስተዋል ካልቻልን ምን ጥቅም አለው? (1 ቆሮ. 14:9) በተመሳሳይም፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ የተናገረውን ሰምተዋል። እንዲያውም ያነጋገራቸው በሚያውቁት ቋንቋ ነበር። ይሁንና የተናገረውን ነገር ትርጉም ያስተዋሉት ሁሉም አይደሉም። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ አድማጮቹን “ሁላችሁም ስሙኝ፤ የምናገረውንም አስተውሉ” ብሏቸው ነበር።—ማር. 7:14

2 ብዙዎች ኢየሱስ የተናገረውን ማስተዋል ያቃታቸው ለምን ነበር? አስቀድመው የራሳቸውን አመለካከት ይዘው ነበር፤ እንዲሁም የሚያዳምጡት በቅን ልቦና ተነሳስተው አልነበረም። ኢየሱስ እንዲህ ያሉትን ሰዎች “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ የአምላክን ትእዛዝ በዘዴ ገሸሽ ታደርጋላችሁ” ብሏቸዋል። (ማር. 7:9) እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የሚናገረውን ለማስተዋል ልባዊ ጥረት አላደረጉም። አካሄዳቸውንና አመለካከታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልነበሩም። ጆሯቸው ቢሰማም ልባቸው ግን ተዘግቶ ነበር! (ማቴዎስ 13:13-15ን አንብብ።) ታዲያ እኛስ ከኢየሱስ ትምህርት ጥቅም ለማግኘት ልባችንን ክፍት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ከኢየሱስ ትምህርት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

3. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ማስተዋል የቻሉት ለምንድን ነው?

3 እኛም ትሑት የሆኑትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምሳሌ መከተላችን ይጠቅመናል። ኢየሱስ “እናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ደስተኞች ናችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 13:16) ኢየሱስ የተናገረውን ሌሎች ማስተዋል ሳይችሉ ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህን ማድረግ የቻሉት ለምንድን ነው? አንደኛ፣ ጥያቄ የመጠየቅና ኢየሱስ ከተናገረው ነገር በስተጀርባ ያለውን ትርጉም የመመርመር ፍላጎት ነበራቸው። (ማቴ. 13:36፤ ማር. 7:17) ሁለተኛ፣ ቀደም ሲል ባመኑበት ነገር ላይ አዲስ ነገር ለመጨመር ፈቃደኞች ነበሩ። (ማቴዎስ 13:11, 12ን አንብብ።) ሦስተኛ፣ የሰሙትንና ያስተዋሉትን ነገር በራሳቸው ሕይወት ተግባራዊ ያደርጉ ነበር፤ ከዚያም አልፈው ሌሎችን ለመርዳት ተጠቅመውበታል።—ማቴ. 13:51, 52

4. የኢየሱስን ምሳሌዎች ትርጉም ለማስተዋል ከፈለግን የትኞቹን ሦስት እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብናል?

4 እኛም የኢየሱስን ምሳሌዎች ትርጉም ለማስተዋል ከፈለግን የታማኝ ደቀ መዛሙርቱን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። እንዲህ ለማድረግ ሦስት እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልገናል። በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ጊዜ ወስደን ማጥናትና በዚያ ላይ ማሰላሰል፣ አስፈላጊውን ምርምር ማድረግ እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን እውቀት ለማግኘት ያስችለናል። (ምሳሌ 2:4, 5) ቀጥሎ ደግሞ ያገኘነው እውቀት በፊት ከምናውቀው ነገር ጋር እንዴት እንደሚዛመድ መረዳትና በግለሰብ ደረጃ እንዴት እንደሚጠቅመን መገንዘብ ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ ማስተዋል እንዲኖረን ያደርጋል። (ምሳሌ 2:2, 3) በመጨረሻም የተማርነውን ነገር ሥራ ላይ ማዋል ይኸውም በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ይህም ጥበበኛ እንደሆንን ያሳያል።—ምሳሌ 2:6, 7

5. በእውቀት፣ በማስተዋልና በጥበብ መካከል ያለውን ልዩነት በምሳሌ አስረዳ።

5 በእውቀት፣ በማስተዋልና በጥበብ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ መኪና መንገድ መሃል ላይ ቆመህ እያለ አንድ አውቶቡስ ወደ አንተ ሲመጣ ተመለከትክ እንበል። በመጀመሪያ፣ ወደ አንተ እየመጣ ያለው አውቶቡስ መሆኑን ተገነዘብክ፤ እውቀት ማለት ይህ ነው። ከዚያም፣ ባለህበት ብትቆም አውቶቡሱ እንደሚገጭህ አሰብክ፤ ይህ ማስተዋል ይባላል። በመሆኑም በፍጥነት ወደ ዳር ትወጣለህ። ይህ ደግሞ ጥበብ ነው! በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጥበብን’ እንድንፈልግ የሚመክረን መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ምክንያቱም ሕይወታችን የተመካው ይህን በማድረጋችን ላይ ነው!—ምሳሌ 2:2፤ 1 ጢሞ. 4:16

6. ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች መካከል ሰባቱን ስንመረምር የትኞቹን አራት ጥያቄዎች እናነሳለን? ( ገጽ 8 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

6 በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ኢየሱስ የተናገራቸውን ሰባት ምሳሌዎች እንመረምራለን። ይህን ስናደርግ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናነሳለን፦ የምሳሌው ትርጉም ምንድን ነው? (ይህን ማወቃችን እውቀት ለማካበት ይረዳናል።) ኢየሱስ ምሳሌውን የተጠቀመው ለምንድን ነው? (ይህን መገንዘባችን ማስተዋል ለማግኘት ይረዳናል።) ከዚህ ምሳሌ ትምህርት የምናገኘው እንዲሁም ሌሎችን ለመርዳት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? (ይህ ደግሞ ጥበበኞች እንድንሆን ያስችለናል።) በመጨረሻም ‘ምሳሌው ስለ ኢየሱስና ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?’ የሚለውን ጥያቄ እናነሳለን።

የሰናፍጩ ዘር

7. ስለ ሰናፍጩ ዘር የሚገልጸው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው?

7 ማቴዎስ 13:31, 32ን አንብብ። ኢየሱስ ስለ ሰናፍጩ ዘር የተናገረው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው? ዘሩ የመንግሥቱን መልእክትና ይህ መልእክት መሰበኩ የሚያስገኘውን ውጤት ይኸውም የክርስቲያን ጉባኤን ያመለክታል። “ከሌሎች ዘሮች ሁሉ ያነሰች” ከተባለችው የሰናፍጭ ዘር ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ፣ የክርስቲያን ጉባኤም በ33 ዓ.ም. ሲቋቋም ጅምሩ አነስተኛ ነበር። ይሁንና በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ጉባኤው ፈጣን እድገት አድርጓል። የመንግሥቱ መልእክት ከሚታሰበው በላይ በስፋት ተሰራጭቷል። (ቆላ. 1:23) እንዲህ ያለ እድገት ማድረጉ ጠቃሚ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ እንደገለጸው “የሰማይ ወፎች” በዚህ ዛፍ “[ቅርንጫፎች] ላይ መስፈሪያ” አግኝተዋል። በምሳሌው ላይ የተገለጹት ወፎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ መጥተው በመንፈሳዊ ሁኔታ ምግብ፣ እረፍትና መጠለያ ያገኙትን ልበ ቅን ሰዎች ያመለክታሉ።—ከሕዝቅኤል 17:23 ጋር አወዳድር።

8. ኢየሱስ ስለ ሰናፍጭ ዘር የሚገልጸውን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው?

8 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው? ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እድገት የሚያደርገው፣ ጥበቃ የሚያስገኘውና የሚያጋጥሙትን መሰናክሎች ሁሉ የሚቋቋመው እንዴት እንደሆነ ለመግለጽ የሰናፍጭ ዘር የሚያደርገውን አስደናቂ እድገት እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። ከ1914 ወዲህ የክርስቲያን ጉባኤ አስገራሚ እድገት አድርጓል! (ኢሳ. 60:22) ከዚህ ጉባኤ ጋር የሚተባበሩ ሁሉ በመንፈሳዊ ሁኔታ ልዩ የሆነ ጥበቃ እያገኙ ነው። (ምሳሌ 2:7፤ ኢሳ. 32:1, 2) ከዚህም በተጨማሪ ጉባኤው የሚያጋጥመውን ተቃውሞ ሁሉ በመቋቋም ማንም ሊገታው በማይችል መንገድ እድገት እያደረገ ነው።—ኢሳ. 54:17

9. (ሀ) ከሰናፍጩ ዘር ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ይህ ምሳሌ ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል?

9 ከሰናፍጩ ዘር ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? የምንኖረው ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ባሉበት ወይም የስብከቱ ሥራችን ብዙም ውጤት የሚያስገኝ በማይመስልበት ቦታ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን መንግሥቱ ማንኛውንም መሰናከል እንደሚወጣ ማስታወሳችን እንድንጸና ብርታት ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ ወንድም ኤድዊን ስኪነር በ1926 ወደ ሕንድ ሲሄድ በዚያ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። በዚህች አገር፣ መጀመሪያ ላይ እድገቱ እጅግ አዝጋሚ ነበር፤ እንዲሁም ሥራው “በጣም አስቸጋሪ” እንደሆነ ተገልጾ ነበር። ያም ሆኖ ወንድም ስኪነር መስበኩን የቀጠለ ሲሆን የመንግሥቱ መልእክት ከባድ የሆኑ መሰናክሎችን ማለፍ እንደቻለ ተመልክቷል። በአሁኑ ጊዜ በሕንድ ከ37,000 በላይ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ፤ ባለፈው ዓመት በመታሰቢያው በዓል ላይ ከ108,000 በላይ ሰዎች ተገኝተዋል። የመንግሥቱ ሥራ ምን ያህል እየተስፋፋ እንዳለ የሚያሳይ ሌላም ምሳሌ እንመልከት። በዛምቢያ ምሥራቹ መሰበክ የጀመረው ወንድም ስኪነር ወደ ሕንድ በሄደበት ዓመት ነበር። በአሁኑ ጊዜ በዚህ አገር ከ170,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ምሥራቹን የሚሰብኩ ሲሆን በ2013 በተከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ 763,915 ሰዎች ተገኝተዋል። ይህም ከ18 ሰዎች አንዱ በበዓሉ ላይ ተገኝቶ ነበር ማለት ነው። እንዴት ያለ አስገራሚ እድገት ነው!

እርሾው

10. የእርሾው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው?

10 ማቴዎስ 13:33ን አንብብ። የእርሾው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው? ይህ ምሳሌም የመንግሥቱን መልእክትና መልእክቱ የሚያስገኘውን ውጤት የሚያመለክት ነው። “በሙሉ” የሚለው አገላለጽ በሁሉም ብሔራት ውስጥ ያሉትን ሰዎች ያመለክታል፤ የሊጡ መቡካት ደግሞ በስብከቱ ሥራ አማካኝነት የመንግሥቱ መልእክት መሰራጨቱን ይጠቁማል። የሰናፍጩ ዘር እድገት በግልጽ ይታያል፤ እርሾው በሊጡ ውስጥ የሚሰራጭበት ሂደት ግን መጀመሪያ ላይ አይታይም። ውጤቱን ማስተዋል የሚቻለው ከጊዜ በኋላ ነው።

11. ኢየሱስ ስለ እርሾው የሚገልጸውን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው? የመንግሥቱ መልእክት በስፋት ለመሰራጨትና ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ኃይል እንዳለው መግለጽ ፈልጎ ነው። የመንግሥቱ መልእክት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተሰራጭቷል። (ሥራ 1:8) ሆኖም መልእክቱ የሚያመጣው ለውጥ አንዳንድ ጊዜ በግልጽ አይታይም፤ እንዲያውም የሚያስገኘው ውጤት መጀመሪያ ላይስተዋል ይችላል። ያም ሆኖ መልእክቱ ለውጥ ያመጣል፤ ለውጡ የቁጥር ጭማሪ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በስፋት እየተሰራጨ ያለውን ይህን መልእክት በተቀበሉት ሰዎች ባሕርይ ላይም ይታያል።—ሮም 12:2፤ ኤፌ. 4:22, 23

12, 13. በእርሾው ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው የመንግሥቱ የስብከት ሥራ እየተስፋፋ የሄደው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ተናገር።

12 ብዙውን ጊዜ የስብከቱ ሥራ የሚያመጣው ለውጥ የሚታየው ሥራው ከተጀመረ ከዓመታት በኋላ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አሁን በሌላ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግሉ ፍራንዝ እና ማርጊት የተባሉ ባልና ሚስት በ1982 በብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ ነበሩ። በዚያ ወቅት በብራዚል በአንዲት ትንሽ የገጠር መንደር ሰብከው ነበር። ከእነሱ ጋር ማጥናት ከጀመሩት ሰዎች መካከል አንዲት ሴት እና አራት ልጆቿ ይገኙበታል። በወቅቱ 12 ዓመት የሚሆነው ትልቁ ልጅ በጣም ዓይናፋር ከመሆኑ የተነሳ ብዙውን ጊዜ ሊያስጠኗቸው ሲመጡ ለመደበቅ ይሞክር ነበር። ወንድም ፍራንዝ እና እህት ማርጊት በሌላ ቦታ እንዲያገለግሉ በመመደባቸው ከዚህ ቤተሰብ ጋር ጥናታቸውን አልቀጠሉም። ሆኖም ከ25 ዓመታት በኋላ ወደዚህ መንደር የመሄድ አጋጣሚ አገኙ። እዚያስ ምን ተመለከቱ? በመንደሯ ውስጥ 69 አስፋፊዎች (13ቱ የዘወትር አቅኚዎች ናቸው) ያሉት ጉባኤ አዲስ በተገነባ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ይሰበሰባል። ዓይናፋር የነበረው ልጅስ ምን ሆነ? አሁን የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ሆኖ ያገለግላል! በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው እርሾ ሁሉ የመንግሥቱ መልእክትም እድገት አድርጎ በብዙዎች ሕይወት ላይ ለውጥ አምጥቷል፤ ባልና ሚስቱ ይህን በማየታቸው በጣም ተደስተዋል!

13 የመንግሥቱ መልእክት በግልጽ በማይታይ ሁኔታ ሰዎችን የመለወጥ ኃይል እንዳለው በተለይ ሥራው በታገደባቸው አገሮች ውስጥ ታይቷል። እንደ እነዚህ ባሉት አገሮች መልእክቱ ምን ያህል እንደተስፋፋ ማወቅ አስቸጋሪ ነው፤ ብዙውን ጊዜም ውጤቱ በጣም ያስገርመናል። ኩባን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የመንግሥቱ መልእክት ኩባ የደረሰው በ1910 ነው፤ ከዚያም በ1913 ወንድም ራስል ወደዚህ አገር ሄደ። ይሁንና መጀመሪያ ላይ እድገቱ አዝጋሚ ነበር። ታዲያ አሁን በኩባ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? ምሥራቹን የሚሰብኩ ከ96,000 በላይ አስፋፊዎች ያሉ ሲሆን በ2013 በመታሰቢያው በዓል ላይ 229,726 ሰዎች ተገኝተዋል፤ ይህም በዚህች ደሴት ላይ ከሚኖሩ 48 ሰዎች አንዱ በበዓሉ ላይ ተገኝቷል ማለት ነው። ሥራችን ባልታገደባቸው ሆኖም ወንድሞች የመንግሥቱ መልእክት በስፋት እየተሰበከ እንዳልሆነ በሚያስቧቸው ቦታዎችም ጭምር ምሥራቹ ሊደርስ ይችላል። *መክ. 8:7፤ 11:5

14, 15. (ሀ) ከእርሾው ምሳሌ የሚገኘው ትምህርት በግለሰብ ደረጃ የሚጠቅመን እንዴት ነው? (ለ) ይህ ምሳሌ ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል?

14 ኢየሱስ ስለ እርሾው ከተናገረው ምሳሌ ምን ጥቅም እናገኛለን? ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ትርጉም ላይ ስናሰላስል ‘የመንግሥቱን መልእክት ያልሰሙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹ እንዴት ይደርሳቸዋል?’ የሚለው ጉዳይ ከልክ በላይ ሊያሳስበን እንደማይገባ እንገነዘባለን። ይሖዋ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው። ታዲያ የእኛ ድርሻ ምንድን ነው? የአምላክ ቃል እንዲህ የሚል መልስ ይሰጠናል፦ “ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ፣ ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ፣ የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና።” (መክ. 11:6) እርግጥ ነው፣ በተለይ ሥራችን በታገደባቸው አገሮች የስብከቱ ሥራ እንዲስፋፋ መጸለያችንንም ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም።—ኤፌ. 6:18-20

15 ከዚህም ሌላ ሥራችን መጀመሪያ ላይ ፍሬ ባያስገኝ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። “የጥቂቱን ነገር ቀን” መናቅ የለብንም። (ዘካ. 4:10) ምክንያቱም ውሎ አድሮ የሚገኘው ውጤት ካሰብነውና ከጠበቅነው በጣም የላቀ ሊሆን ይችላል!—መዝ. 40:5፤ ዘካ. 4:7

ተጓዡ ነጋዴ እና የተደበቀው ውድ ሀብት

16. ስለ ተጓዡ ነጋዴና ስለተደበቀው ውድ ሀብት የሚናገሩት ምሳሌዎች ትርጉም ምንድን ነው?

16 ማቴዎስ 13:44-46ን አንብብ። ስለ ተጓዡ ነጋዴ እና ስለተደበቀው ውድ ሀብት የሚናገሩት ምሳሌዎች ትርጉም ምንድን ነው? በኢየሱስ ዘመን አንዳንድ ነጋዴዎች በጣም ምርጥ የሆነ ዕንቁ ለማግኘት እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ ይጓዙ ነበር። በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ነጋዴ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት ሲሉ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችን ያመለክታል። “ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ ዕንቁ” የተባለው ደግሞ ውድ የሆነው የመንግሥቱ እውነት ነው። ነጋዴው፣ ዕንቁው ውድ ዋጋ እንዳለው ስለተገነዘበ ዕንቁውን ለመግዛት ሲል ያለውን ሁሉ “ወዲያውኑ” ሸጧል። ኢየሱስ፣ በእርሻ ውስጥ እየሠራ ሳለ የተደበቀ “ውድ ሀብት” ስላገኘ ሰውም ተናግሯል። ከነጋዴው በተለየ መልኩ ይህ ሰው ሀብት ለማግኘት ጥረት እያደረገ አልነበረም። ያም ቢሆን ያገኘውን ውድ ሀብት የራሱ ለማድረግ ሲል ልክ እንደ ነጋዴው “ያለውን ሁሉ” ለመሸጥ ፈቃደኛ ነበር።

17. ኢየሱስ ስለ ተጓዡ ነጋዴና ስለተደበቀው ውድ ሀብት የሚናገሩትን ምሳሌዎች የተጠቀመው ለምንድን ነው?

17 ኢየሱስ እነዚህን ሁለት ምሳሌዎች የተጠቀመው ለምንድን ነው? ሰዎች እውነትን የሚያገኙት በተለያዩ መንገዶች እንደሆነ ለማሳየት ነው። አንዳንዶች እውነትን ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉ ሲሆን ለዚህም ሲሉ ብዙ ደክመዋል። ሌሎች ግን እውነትን ለመፈለግ ጥረት ባያደርጉም እውነትን አግኝተዋል፤ ምናልባትም ይህ የሆነው ምሥራቹ ተሰብኮላቸው ሊሆን ይችላል። ይህን ውድ ሀብት ያገኙበት መንገድ ምንም ይሁን ምን ሁሉም ያገኙት ነገር የላቀ ዋጋ እንዳለው ስለተገነዘቡ ይህን ሀብት የራሳቸው ለማድረግ ከፍተኛ መሥዋዕት ከፍለዋል።

18. (ሀ) ከእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ምን ጥቅም እናገኛለን? (ለ) ምሳሌዎቹ ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምሩናል?

18 ከእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ምን ጥቅም እናገኛለን? (ማቴ. 6:19-21) ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘እነዚህ ሰዎች የነበራቸው ዓይነት አመለካከት አለኝ? ልክ እንደ እነሱ እውነትን እንደ ውድ ሀብት አድርጌ እመለከተዋለሁ? እውነትን የራሴ ለማድረግ ስል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ ወይስ የኑሮ ጭንቀቶችን የመሳሰሉ ሌሎች ነገሮች ትኩረቴን እንዲከፋፍሉት እፈቅዳለሁ?’ (ማቴ. 6:22-24, 33፤ ሉቃስ 5:27, 28፤ ፊልጵ. 3:8) እውነትን በማግኘታችን በጣም የምንደሰት ከሆነ በሕይወታችን ውስጥ ለእውነት ቅድሚያ ለመስጠት ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔም የዚያኑ ያህል ጠንካራ ይሆናል።

19. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

19 እንግዲያው ስለ መንግሥቱ የሚገልጹትን እነዚህን ምሳሌዎች እንደሰማንና ትርጉማቸውን በሚገባ እንዳስተዋልን እናሳይ። ይህን የምናደርገው የምሳሌዎቹን ትርጉም በማወቅ ብቻ ሳይሆን ያገኘነውን ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ ጭምር እንደሆነ እናስታውስ። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ ሌሎች ሦስት ምሳሌዎችን የምንመረምር ሲሆን ከእነሱ ምን ትምህርት እንደምናገኝም እንመለከታለን።

^ አን.13 በምሥራቅ ጀርመን (የ1999 የዓመት መጽሐፍ [እንግሊዝኛ] ገጽ 83)፣ በሮቢንሰን ክሩሶ ደሴት (መጠበቂያ ግንብ ሰኔ 15, 2000 ገጽ 9)፣ በአርጀንቲና (የ2001 የዓመት መጽሐፍ [እንግሊዝኛ] ገጽ 186 ሣጥኑ) እንዲሁም በፓፑዋ ኒው ጊኒ (የ2005 የዓመት መጽሐፍ [እንግሊዝኛ] ገጽ 63) ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ ተሞክሮዎች ተገኝተዋል።