በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ በፈቃደኝነት የሚሰጡትን አብዝቶ ይባርካል

ይሖዋ በፈቃደኝነት የሚሰጡትን አብዝቶ ይባርካል

ፈጣሪያችን ለሰዎች የመምረጥ ነፃነት በመስጠት አክብሯቸዋል፤ ይህ በዋጋ ሊተመን የማይችል ስጦታ ነው። የመምረጥ ነፃነታቸውን እውነተኛውን አምልኮ ለማራመድ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ የሚጠቀሙና የአምላክን ቅዱስ ስም ለመቀደስና ታላቅ ዓላማውን ለመደገፍ የበኩላቸውን የሚያደርጉ ሰዎችን ይሖዋ አብዝቶ ይባርካቸዋል። ይሖዋ፣ ሰዎች ፈርተውና ተገድደው እንዲታዘዙት አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ ለእሱ ባላቸው እውነተኛ ፍቅርና ጥልቅ አድናቆት ተነሳስተው በፈቃደኝነት ራሳቸውን ለእሱ የሚሰጡ ሰዎችን ከፍ አድርጎ ይመለከታል።

ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ይሖዋ ለአምልኮ የሚውል ድንኳን እንዲሠሩ አዟቸው ነበር። እንዲህ አላቸው፦ “ካላችሁ ነገር ለይሖዋ መዋጮ አምጡ። ልቡ ያነሳሳው ማንኛውም ሰው . . . ለይሖዋ መዋጮ . . . ያምጣ።” (ዘፀ. 35:5 NW) እያንዳንዱ እስራኤላዊ የአቅሙን መስጠት ይችል ነበር፤ የስጦታው ዓይነትና መጠን ምንም ሆነ ምን በፈቃደኝነት የቀረበው እያንዳንዱ ስጦታ የይሖዋን ዓላማ ለመፈጸም ተገቢ በሆነ መንገድ አገልግሎት ላይ ይውል ነበር። ታዲያ ሕዝቡ ምን ምላሽ ሰጠ?

“ፈቃደኛ የነበረና [ልቡ] ያነሣሣው ሁሉ” ለይሖዋ ስጦታ አመጣ። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ለይሖዋ ሥራ የሚከተሉትን ነገሮች በፈቃዳቸው አምጥተዋል፦ የደረት ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ ቀለበት እንዲሁም ወርቅ፣ ብር፣ መዳብ፣ ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣ ደማቅ ቀይ ማግ፣ ጥሩ በፍታ፣ የፍየል ፀጉር፣ ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፣ የአቆስጣ ቆዳ፣ የግራር እንጨት፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ ዘይትና የበለሳን ዘይት። የመጣው ስጦታ “ሥራውን ሁሉ ለማከናወን” ከሚያስፈልገው “በላይ ነበረ።”—ዘፀ. 35:21-24, 27-29፤ 36:7

ይሖዋን ይበልጥ ያስደሰተው ግን ሕዝቡ ያመጡት ቁሳዊ ነገር ሳይሆን በዚህ መንገድ እውነተኛውን አምልኮ የደገፉት ሰዎች ያሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ነበር። ሕዝቡ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እንዲሰጡም ልባቸው አነሳስቷቸው ነበር። ዘገባው “ጥበበኞች የሆኑ ሴቶች ሁሉ በእጃቸው ፈተሉ” ይላል። “ፈቃደኛ የነበሩና ጥበቡ ያላቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ጠጕር ፈተሉ።” ከዚህም ሌላ ይሖዋ፣ ባስልኤል “በጥበብ፣ በችሎታና በዕውቀት፣ በማናቸውም ዐይነት ሙያ” የተካነ እንዲሆን አድርጎ ነበር። እንዲያውም ባስልኤልና ኤልያብ የታዘዙትን ነገር ሁሉ ለመሥራት የሚያስፈልጋቸውን ችሎታ የሰጣቸው አምላክ ነው።—ዘፀ. 35:25, 26, 30-35

ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን ስጦታ እንዲያመጡ ሲጋብዛቸው “ልቡ ያነሳሳው ማንኛውም ሰው” እውነተኛውን አምልኮ እንደሚደግፍ ሙሉ እምነት ነበረው። እሱም በምላሹ ፈቃደኛ ልብ ላላቸው ሰዎች አመራርና የላቀ ደስታ በመስጠት አትረፍርፎ ባርኳቸዋል። ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያሳዩትን የፈቃደኝነት መንፈስ በመባረክ ፈቃዱን ለማከናወን የሚያስፈልገው የሀብት አቅርቦትም ሆነ ችሎታ እንዲኖር ማድረግ የሚችል መሆኑን አሳይቷል። (መዝ. 34:9) አንተም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ይሖዋን በማገልገል የምታሳየውን የፈቃደኝነት መንፈስ እንደሚባርክልህ የተረጋገጠ ነው።