‘መንገዱን አውቆታል’
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የነበረው ጋይ ኸሊስ ፒርስ ማክሰኞ፣ መጋቢት 18, 2014 ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቅቋል። ወንድም ፒርስ ትንሣኤ አግኝተው የክርስቶስ ወንድሞች ከሚሆኑት መካከል አንዱ የመሆን ተስፋው ተፈጽሟል፤ በዚህ ጊዜ 79 ዓመቱ ነበር።—ዕብ. 2:10-12፤ 1 ጴጥ. 3:18
ጋይ ፒርስ የተወለደው ኅዳር 6, 1934 በኦበርን፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሲሆን የተጠመቀው በ1955 ነበር። በ1977 ውድ ባለቤቱን ፔኒን አግብቶ ልጆቻቸውን አብረው አሳድገዋል። ቤተሰብ ያለው መሆኑ ለሌሎችም እንደ አባት እንዲሆን አድርጎታል። በ1982 እሱና ፔኒ በአቅኚነት በትጋት ይካፈሉ የነበረ ሲሆን በ1986 በዩናይትድ ስቴትስ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ማገልገል ጀመረ፤ በዚህ ምድብ ለ11 ዓመታት ሠርቷል።
ጋይ ፒርስ እና ባለቤቱ ፔኒ በ1997 የዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል ቤተሰብ አባላት ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ወንድም ፒርስ በአገልግሎት ዘርፍ የሠራ ሲሆን በ1998 የበላይ አካሉ ፐርሶኔል ኮሚቴ ረዳት ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ። ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ ጥቅምት 2, 1999 ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ወንድም ፒርስ የበላይ አካሉ አባል ሆኖ መሾሙን የሚገልጽ ማስታወቂያ ተነገረ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፐርሶኔል፣ በጽሑፍ ዝግጅት፣ በሕትመትና በአስተባባሪዎች ኮሚቴዎች ውስጥ አገልግሏል።
ወንድም ፒርስ፣ ሞቅ ያለ ፈገግታ ስላለውና ተጫዋች ስለሆነ የተለያየ አስተዳደግና ባሕል ያላቸው ሰዎች ይቀርቡት ነበር። ይበልጥ ተወዳጅ ያደረጉት ባሕርያት ግን ፍቅሩ፣ ትሕትናው እንዲሁም ጽድቅ ለሚንጸባረቅባቸው ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለው አክብሮትና በይሖዋ ላይ ያለው ጠንካራ እምነት ነበሩ። ወንድም ጋይ ፒርስ የይሖዋ ተስፋዎች ሳይፈጸሙ ከሚቀሩ ፀሐይ ሳትወጣ ትቀራለች ብሎ ማሰብ ይቀልለው ነበር፤ ይህን እውነትም ለመላው ዓለም የማወጅ ፍላጎት ነበረው።
ወንድም ፒርስ በይሖዋ አገልግሎት ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል ሰው ነበር፤ ማለዳ የሚነሳ ሲሆን ብዙውን ጊዜ እስከ ሌሊት አምሽቶ ይሠራል። በመላው ዓለም እየተጓዘ ክርስቲያን ወንድሞቹንና እህቶቹን አበረታትቷል፤ ከዚህም ሌላ ከእሱ ጋር መጫወት እንዲሁም ምክርና እገዛ ለሚፈልጉ የቤቴል ቤተሰብ አባላትና ሌሎች ሰዎች ጊዜ አጥቶ አያውቅም። ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ የእምነት አጋሮቹ እንግዳ ተቀባይነቱን፣ የነበረውን ወዳጅነት መንፈስና የሰጣቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ ያስታውሳሉ።
ወንድማችንና ውድ ወዳጃችን ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ነበር፤ እንዲሁም የልጅ ልጆች እና የልጅ ልጅ ልጆች አሉት። ከዚህም ሌላ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መንፈሳዊ ልጆች አሉት። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን ቅዳሜ፣ መጋቢት 22, 2014 ለወንድም ፒርስ በብሩክሊን ቤቴል የመታሰቢያ ንግግር አቅርቧል። ወንድም ሳንደርሰን በንግግሩ ላይ ወንድም ፒርስ ሰማያዊ ተስፋ እንዳለው የጠቀሰ ሲሆን ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብም አንብቧል፦ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ። . . . ሄጄ ቦታ የማዘጋጅላችሁ ከሆነ ደግሞ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ። እኔ ወደምሄድበትም ቦታ የሚወስደውን መንገድ ታውቃላችሁ።”—ዮሐ. 14:2-4
ወንድም ፒርስን በጣም እንደምንናፍቀው የታወቀ ነው። ሆኖም ዘላቂ ወደሆነው ‘መኖሪያው’ የሚወስደውን ‘መንገድ ስላወቀ’ ደስተኞች ነን።