ለይሖዋ ምስጋና አቅርቡለት፤ ትባረካላችሁ
“ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት።”
1. ይሖዋ ምስጋና ይገባዋል እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?
‘የመልካም ስጦታና የፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ’ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ልናመሰግነው እንደሚገባ ጥያቄ የለውም። (ያዕ. 1:17) አፍቃሪ እረኛ በመሆኑ ሰብዓዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንን በሙሉ በደግነት ያሟላልናል። (መዝ. 23:1-3) በተለይ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋ “መጠጊያችንና ኀይላችን” እንደሚሆንልን አሳይቷል! (መዝ. 46:1) በእርግጥም፣ “ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት ከጻፈው መዝሙራዊ ጋር ሙሉ በሙሉ እንድንስማማ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉን።
የ2015 የዓመት ጥቅሳችን፦“ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት።”
2, 3. (ሀ) ላገኘናቸው በረከቶች አድናቆት ማጣት ምን አደጋ አለው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 አመስጋኝ መሆን ይህን ያህል ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው? በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ሰዎች የማያመሰግኑ እየሆኑ እንደሚሄዱ አስቀድሞ ተነግሯል። (2 ጢሞ. 3:2) ብዙዎች ያሏቸውን ነገሮች አያደንቁም። የንግዱ ዓለምና ማስታወቂያዎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ባላቸው ከመርካት ይልቅ ተጨማሪ ነገር ለማግኘት እንዲጣጣሩ አድርጓቸዋል። እንዲህ ያለው አድናቆት የማጣት መንፈስ ወደ እኛም ሊጋባ ይችላል። እንደ ጥንቶቹ እስራኤላውያን ሁሉ እኛም የአመስጋኝነት መንፈስ ልናጣ ብሎም ከይሖዋ ጋር ላለን ውድ ዝምድና እንዲሁም ከእሱ ላገኘናቸው በረከቶች አድናቆት ሳናሳይ ልንቀር እንችላለን።
3 በሌላ በኩል ደግሞ ከባድ ፈተናዎች ምን ዓይነት ስሜት ሊፈጠሩብን እንደሚችሉ እንመልከት። እንዲህ ባሉ ወቅቶች ስለደረሰብን ፈተና ብቻ ማሰባችን ያሉንን በረከቶች ማስተዋል እንዲያቅተን ሊያደርገን ይችላል። (መዝ. 116:3) ታዲያ የአመስጋኝነትን መንፈስ ለማዳበርና ምንጊዜም አመስጋኝ ለመሆን ምን ማድረግ እንችላለን? ከባድ ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ አዎንታዊ አመለካከት ይዘን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል? እስቲ መልሶቹን እንመልከት።
“አምላኬ ሆይ፤ አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው”
4. ምንጊዜም አመስጋኝ የሆነ ልብ እንዲኖረን ምን ማድረግ አለብን?
4 የአመስጋኝነት መንፈስ እንድናዳብርና ምንጊዜም አመስጋኝ ልብ እንዲኖረን ከፈለግን ከይሖዋ ያገኘናቸውን በረከቶች ማስተዋልና በእነዚህ ላይ በአድናቆት ማሰላሰል እንዲሁም ይሖዋ በታማኝ ፍቅሩ ስላከናወናቸው ነገሮች በጥሞና ማሰብ አለብን። መዝሙራዊው ይህን በማድረጉ፣ ይሖዋ ባከናወናቸው በርካታ ድንቅ ነገሮች ተደምሟል።—መዝሙር 40:5፤ 107:43ን አንብብ።
5. የአመስጋኝነት መንፈስ በማዳበር ረገድ ከሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንማራለን?
5 የአመስጋኝነት መንፈስ በማዳበር ረገድ ከሐዋርያው ጳውሎስ ልንማር የምንችለው ብዙ ነገር አለ። ጳውሎስ በበረከቶቹ ላይ ያሰላስል የነበረ ይመስላል፤ ምክንያቱም በተደጋጋሚ ጊዜያት ከልብ የመነጨ ምስጋና አቅርቧል። ጳውሎስ “ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ” እንደነበር ተናግሯል። ቀደም ሲል የኃጢአት አካሄድ ይከተል የነበረ ቢሆንም አምላክና ክርስቶስ ምሕረት ስላሳዩትና አገልግሎቱን በአደራ ስለሰጡት ምስጋናውን ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 1:12-14ን አንብብ።) ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹም ጥልቅ አድናቆት ነበረው፤ እንዲሁም ስለ ግሩም ባሕርያቸውና በታማኝነት ስላከናወኑት አገልግሎት ይሖዋን በተደጋጋሚ ጊዜያት አመስግኗል። (ፊልጵ. 1:3-5, 7፤ 1 ተሰ. 1:2, 3) ከዚህም ሌላ ጳውሎስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባጋጠሙት ወቅት መንፈሳዊ ወንድሞቹ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ስላደረጉለት ይሖዋን አመስግኗል። (ሥራ 28:15፤ 2 ቆሮ. 7:5-7) ከዚህ አንጻር ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ክርስቲያኖችን ማበረታታቱ የሚያስገርም አይደለም፦ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ። . . . በመዝሙራት፣ ለአምላክ በሚቀርብ ውዳሴና ለዛ ባላቸው መንፈሳዊ ዝማሬዎች . . . መምከራችሁን ቀጥሉ።”—
ማሰላሰልና ጸሎት ምንጊዜም የአመስጋኝነት መንፈስ እንዲኖረን ይረዱናል
6. አንተ በግልህ ይሖዋን እንድታመሰግን የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?
6 የአመስጋኝነት መንፈስ በማዳበርና ምስጋናችንን በመግለጽ ረገድ የጳውሎስን ግሩም ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ባደረገልን ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። (መዝ. 116:12) ‘አመስጋኝ እንድትሆን የሚያነሳሳህ ከይሖዋ ያገኘኸው ምን በረከት አለ?’ ተብለህ ብትጠየቅ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ከይሖዋ ጋር ያለህ ውድ ዝምድና ነው? ወይስ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን የኃጢአት ይቅርታ ማግኘትህ? የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባጋጠሙህ ጊዜ ከጎንህ የቆሙ ወንድሞችህንና እህቶችህን ትጠቅሳለህ? የምትወዳትን የትዳር ጓደኛህንና ልጆችህን ሳትጠቅስ እንደማታልፍ የታወቀ ነው። አፍቃሪ ከሆነው አባታችን ከይሖዋ ባገኘሃቸው እንደ እነዚህ ያሉ ግሩም በረከቶች ላይ ጊዜ ወስደህ ማሰላሰልህ ልብህ በአድናቆት እንዲሞላ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ በየዕለቱ እንድታመሰግነው ያነሳሳሃል።—መዝሙር 92:1, 2ን አንብብ።
7. (ሀ) የምስጋና ጸሎት ማቅረብ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በጸሎትህ ውስጥ ምስጋናን ማካተትህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?
7 በሕይወታችን ያገኘናቸው በረከቶች በአእምሯችንም ሆነ በልባችን ውስጥ ቁልጭ ብለው የሚታዩን ከሆነ ለይሖዋ በጸሎት ምስጋናችንን ለመግለጽ እንነሳሳለን። (መዝ. 95:2፤ 100:4, 5) ብዙዎች ወደ አምላክ የሚጸልዩት የሚፈልጉት ነገር ሲኖር ብቻ ነው። እኛ ግን ላለን ነገር ምስጋናችንን ስንገልጽ ይሖዋ እንደሚደሰት እናውቃለን። መጽሐፍ ቅዱስ ልብ የሚነኩ በርካታ የምስጋና ጸሎቶችን ይዟል፤ ከእነዚህም መካከል ሐና እና ሕዝቅያስ ያቀረቧቸው ጸሎቶች ይገኙበታል። (1 ሳሙ. 2:1-10፤ ኢሳ. 38:9-20) እንግዲያው እኛም የአመስጋኝነት መንፈስ ያሳዩትን እነዚህን ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች እንምሰል። በእርግጥም ላገኘሃቸው በረከቶች ይሖዋን በጸሎት ልታመሰግነው ይገባል። (1 ተሰ. 5:17, 18) እንዲህ ማድረግ ብዙ ጥቅሞች ያስገኛል። አመስጋኝ ከሆንክ መንፈስህ ይታደሳል፤ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል እንዲሁም ወደ እሱ ይበልጥ ትቀርባለህ።
8. ይሖዋ ላደረገልን ነገሮች አድናቆት እንድናጣ ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው?
8 ለይሖዋ ጥሩነት አድናቆት እንዳናጣ መጠንቀቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ምክንያቱም አመስጋኝ ያለመሆን ዝንባሌ ስለወረስን ነው። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን የሚኖሩት በገነት ውስጥ ነበር። የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ሁሉ የተሟሉላቸው ከመሆኑም ሌላ ሰላም በሰፈነበት ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ተዘርግቶላቸው ነበር። (ዘፍ. 1:28) ይሁንና ላገኟቸው በረከቶች አድናቆት አላሳዩም። እንዲያውም ስግብግብ በመሆን ሌላም ነገር ፈለጉ። ይህ ደግሞ የነበራቸውን በሙሉ አሳጣቸው። (ዘፍ. 3:6, 7, 17-19) እኛም የምንኖረው አመስጋኝነት በጠፋበት ዓለም ውስጥ በመሆኑ ይሖዋ ያደረገልንን ነገሮች አቅልለን መመልከት ልንጀምር እንችላለን። ከይሖዋ ጋር ለመሠረትነው ወዳጅነት አድናቆት እናጣ ይሆናል። አሊያም የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር አባል የመሆን መብታችንን ከፍ አድርገን መመልከት ልናቆም እንችላለን። እንዲሁም በቅርቡ በሚጠፋው በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉ ነገሮች ይማርኩን ይሆናል። (1 ዮሐ. 2:15-17) እንዲህ ካለው ወጥመድ ለመራቅ፣ ባሉን በረከቶች ላይ ማሰላሰልና የይሖዋ ሕዝብ የመሆን መብት በማግኘታችን አዘውትረን እሱን ማመስገን ይኖርብናል።
ፈተናዎች ሲያጋጥሙን
9. በጣም ከባድ የሆኑ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን፣ ባሉን በረከቶች ላይ ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው?
9 አመስጋኝ መሆን በጣም ከባድ የሆኑ ፈተናዎችን ለመቋቋም ይረዳናል። የትዳር ጓደኛችን ቢከዳን፣ ለሕይወት የሚያሰጋ ሕመም ቢይዘን፣ የምንወደውን ሰው በሞት ብናጣ፣ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ቢደርስብን ወይም እነዚህን የመሳሰሉ በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን መከራው ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። እንደነዚህ ባሉ ወቅቶች፣ ባሉን በረከቶች ላይ ማሰላሰላችን እንድንጽናና ብሎም እንድንበረታ ይረዳናል። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን እውነተኛ ታሪኮች እስቲ እንመልከት።
10. አይሪና ባሏት በረከቶች ላይ ማሰላሰሏ ምን ጥቅም አስገኝቶላታል?
10 በሰሜን አሜሪካ የምትኖረው አይሪና * የዘወትር አቅኚ ናት፤ የጉባኤ ሽማግሌ የነበረው ባለቤቷ ታማኝነቱን ከማጉደሉም ሌላ እሷንም ሆነ ልጆቻቸውን ጥሏቸው ሄደ። አይሪና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሏን እንድትቀጥል የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለእኔ ስለሚያደርግልኝ እንክብካቤ አመስጋኝ ነኝ። ባሉኝ በረከቶች ላይ በየዕለቱ ማሰላሰሌ፣ ጥበቃ በሚያደርግልን አባታችን ዘንድ መታወቅና በእሱ መወደድ ትልቅ መብት መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል። ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይተወኝ እርግጠኛ ነኝ።” አይሪና በሕይወቷ ውስጥ በርካታ አሳዛኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟትም ደስተኛ መንፈስ ያላት መሆኑ ታማኝነቷን ጠብቃ እንድትመላለስና ለሌሎችም የብርታት ምንጭ እንድትሆን ረድቷታል።
11. ክዮንግ ሱክ ለሕይወት የሚያሰጋ ሕመም እንዳለባት ስታውቅ ሁኔታውን ለመቋቋም የረዳት ምንድን ነው?
11 በእስያ የምትኖረው ክዮንግ ሱክ ከባለቤቷ ጋር ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት አገልግላለች። ክዮንግ ሱክ የመጨረሻው ደረጃ ላይ የደረሰ የሳንባ ካንሰር እንዳለባት በድንገት ታወቀ፤ በሕይወት የምትቆየው ቢበዛ ከሦስት እስከ ስድስት ወር እንደሆነ ተነገራት። እሷና ባለቤቷ ትላልቅ መከራዎችም ሆነ ትናንሽ ችግሮች ብዙ ጊዜ አጋጥመዋቸዋል፤ ያም ቢሆን ምንጊዜም ጤነኞች እንደሆኑ ይሰማቸው ነበር። “የጤንነቴን ሁኔታ መቀበል በጣም ከብዶኝ ነበር፤ ሁሉን ነገር እንዳጣሁ የተሰማኝ ሲሆን በፍርሃት ተዋጥኩ” በማለት ተናግራለች። ታዲያ ክዮንግ ሱክ ይህንን ፈተና ለመቋቋም የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “በየዕለቱ ከመተኛቴ በፊት የቤታችን ጣሪያ ላይ እወጣና በዚያ ቀን ያገኘኋቸውን አምስት ነገሮች በመጥቀስ ይሖዋን ጮክ ብዬ አመሰግነዋለሁ። ይህን ማድረግ ያረጋጋኛል፤ እንዲሁም ለይሖዋ ያለኝን ፍቅር ለመግለጽ እነሳሳለሁ።” ክዮንግ ሱክ በየምሽቱ የምታቀርበው ጸሎት የጠቀማት እንዴት ነው? “ይሖዋ ከባድ ፈተናዎችን መቋቋም እንድንችል እንደሚረዳንና በሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን ችግሮች ጋር ሲወዳደሩ የምናገኛቸው በረከቶች በጣም ብዙ እንደሆኑ ተገንዝቤያለሁ” ብላለች።
12. ጄሰን ባለቤቱን በሞት ካጣ በኋላ እንዲጽናና የረዳው ምንድን ነው?
12 በአፍሪካ በሚገኝ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግለው ጄሰን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ30 ዓመት በላይ ቆይቷል። ጄሰን እንዲህ ብሏል፦ “ከሰባት ዓመት በፊት ባለቤቴን በሞት አጣሁ፤ ሐዘኑን መቋቋም በጣም ከባድ ነው። የነበረባት ካንሰር ምን ያህል እንዳሠቃያት ሳስብ በጣም እረበሻለሁ።” ታዲያ ጄሰን ይህን ፈተና እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት፣ እኔና ባለቤቴ ያሳለፍነውን አስደሳች ጊዜ አስታወስኩ፤ ከዚያም ያንን ጊዜ እንዳስታውስ ስለረዳኝ ይሖዋን አመሰገንኩት። በዚህ ወቅት ውስጤ የተረጋጋ ሲሆን ከዚያ በኋላ እንዲህ ስላሉት አስደሳች ትዝታዎች ይሖዋን አዘውትሬ ማመስገን ጀመርኩ። አመስጋኝ መሆኔ በአመለካከቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ባለቤቴን ማጣቴ ያስከተለብኝ ሥቃይ አሁንም አለ፤ ይሁንና ጥሩ ትዳር ስለነበረኝና ይሖዋን በጣም ከምትወድ የትዳር ጓደኛ ጋር እሱን የማገልገል መብት ስላገኘሁ ይሖዋን ማመስገኔ የተሻለ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድቶኛል።”
“አምላኬ፣ ይሖዋ በመሆኑ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”
13. ሼረል አብዛኞቹን የቤተሰቧን አባላት በማጣቷ ያጋጠማትን ሐዘን ለመቋቋም የረዳት ምንድን ነው?
13 ሃያን የተባለው ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ በ2013 መገባደጃ አካባቢ መካከለኛውን ፊሊፒንስ በመታበት ወቅት ሼረል ሁሉን ነገር አጥታለች ማለት ይቻላል። በወቅቱ የ13 ዓመት ልጅ የነበረችው ሼረል “መኖሪያዬንም ሆነ አብዛኞቹን የቤተሰቤን አባላት አጣሁ” ብላለች። አባቷ፣ እናቷ እንዲሁም ወንድሟና ሁለት እህቶቿ በደረሰው ከባድ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸው አለፈ። ሼረል ምሬት ሳያድርባት ይህን አሳዛኝ ሁኔታ እንድትቋቋም የረዳት ምንድን ነው? የአመስጋኝነት መንፈስ ያላት ከመሆኑም ሌላ አሁን ባሏት በረከቶች ላይ ታተኩራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞችና እህቶች እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ምን ያህል እርዳታና ማበረታቻ እንደሰጡ ተመለከትኩ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞች ስለ እኔ እንደሚጸልዩ አውቃለሁ።” አክላም “አምላኬ፣ ይሖዋ በመሆኑ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ምንጊዜም ቢሆን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ይሰጠናል” በማለት ተናግራለች። በእርግጥም ያሉንን በረከቶች ማስተዋል በሐዘን እንዳንዋጥ የሚረዳ ፍቱን መድኃኒት ነው። ልባችን በአድናቆት ከተሞላ ማንኛውንም ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ መቋቋም እንችላለን።
‘እኔ ግን በይሖዋ ደስ ይለኛል’
14. ወደፊት ምን አስደሳች ነገር ይጠብቀናል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
14 በታሪክ ዘመናት ሁሉ የይሖዋ ሕዝቦች ላገኟቸው በረከቶች አድናቆታቸውን ሲገልጹ ኖረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ሲሻገሩ ይሖዋ ከፈርዖንና ከሠራዊቱ እጅ ስላዳናቸው ደስታቸውን ለመግለጽ የውዳሴና የምስጋና መዝሙር ዘምረዋል። (ዘፀ. 15:1-21) በአሁኑ ጊዜ ካሉን ውድ በረከቶች አንዱ ሥቃይና ጭንቀት የሚያስከትሉብን ነገሮች በሙሉ እንደሚወገዱ የሚገልጸው እርግጠኛ ተስፋ ነው። (መዝ. 37:9-11፤ ኢሳ. 25:8፤ 33:24) ይሖዋ፣ ጠላቶቹን በሙሉ አጥፍቶ ሰላምና ጽድቅ ወደሰፈነበት አዲስ ዓለም ሲያስገባን ምን ሊሰማን እንደሚችል እስቲ አስበው። በዚያ ጊዜ ለይሖዋ ልባዊ ምስጋና እንደምናቀርብ ጥርጥር የለውም!—ራእይ 20:1-3፤ 21:3, 4
15. በ2015 ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?
15 በ2015 ይሖዋ የሚሰጠንን ስፍር ቁጥር የሌላቸው መንፈሳዊ በረከቶች እንጠባበቃለን። እርግጥ ነው፣ ፈተናዎችም ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ሆኖም፣ ምንም ይምጣ ምን ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወን እርግጠኞች ነን። (ዘዳ. 31:8፤ መዝ. 9:9, 10) እሱን በታማኝነት ለማገልገል የሚያስፈልገንን ሁሉ ምንጊዜም ይሰጠናል። በመሆኑም እንደ ነቢዩ ዕንባቆም ያለ አመለካከት ለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ ዕንባቆም እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣ ከወይን ተክልም ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራም ዛፍ ፍሬ ባይሰጥ፣ ዕርሻዎችም ሰብል ባይሰጡ፣ የበጎች ጕረኖ እንኳ ባዶውን ቢቀር፣ ላሞችም በበረት ውስጥ ባይገኙ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በድነቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።” (ዕን. 3:17, 18) እንግዲያው በዚህ ዓመት፣ ባሉን በረከቶች ላይ በአድናቆት እያሰላሰልን “ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት” የሚለውን የ2015 የዓመት ጥቅስ ተግባራዊ እናድርግ።
^ አን.10 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።