በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል?

የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል?

“የፍቅር ወላፈን የእሳት ወላፈን ነው፤ የያህም ነበልባል ነው።”—ማሕ. 8:6 NW

1, 2. የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍን በትኩረት በመመርመር እነማን ጥቅም ማግኘት ይችላሉ? እንዴት? (በመግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።)

‘እጅ ለእጅ ተያይዘው በፍቅር ዓይን ሲተያዩ እንዴት ያምራሉ! መቼም በጣም እንደሚዋደዱ መገመት አያዳግትም!’ እንዲህ ብሎ ያሰበው እነዚህን ሙሽሮች ያጋባቸው ሽማግሌ ነው። አዲሶቹ ተጋቢዎች በሠርጉ ግብዣ ላይ ተያይዘው ሲደንሱ የሚከተሉት ጥያቄዎች በሽማግሌው አእምሮ ይመላለሱ ጀመር፦ ‘ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ትዳራቸው ይዘልቅ ይሆን? ዓመታት ሲያልፉ ፍቅራቸው እየጠነከረ ይሄዳል ወይስ በንኖ ይጠፋል?’ በወንድና ሴት መካከል ያለው ፍቅር ጊዜ የማይለውጠውና ዘላቂ ሲሆን በጣም ደስ ይላል። ይሁንና በርካታ ትዳሮች እየፈረሱ ከመሆናቸው አንጻር ‘በእርግጥ የማይቀዘቅዝ ፍቅር ሊኖር ይችላል?’ ብሎ መጠየቁ ምክንያታዊ ነው።

2 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ በነበረው በሰለሞን ዘመንም እንኳ እውነተኛ ፍቅር ብርቅ ነበር። ሰለሞን በዘመኑ ስለነበረው የሥነ ምግባር ሁኔታ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ከሺህ ወንዶች መካከል አንድ ቅን ሰው አገኘሁ፣ በእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ቅን ሴት አላገኘሁም። ይህን አንድ ነገር ብቻ አገኘሁ፤ እግዚአብሔር ሰውን ቅን አድርጎ መሥራቱን፣ ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ ቀየሱ።” (መክ. 7:26-29) በዓል አምላኪ የሆኑ የባዕድ አገር ሴቶች ባሳደሩት ተጽዕኖ ምክንያት በዘመኑ የሕዝቡ ሥነ ምግባር በጣም አሽቆልቁሎ ነበር፤ በዚህም የተነሳ ሰለሞን ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ሴትም ሆነ ወንድ ማግኘት አስቸግሮት ነበር። * ያም ቢሆን ከላይ ያለውን ሐሳብ ከማስፈሩ  ከ20 ዓመት በፊት የጻፈው ግጥም ይኸውም የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ዘላቂ ፍቅር ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማል። ይህ መጽሐፍ፣ እንዲህ ያለው ፍቅር ምን ዓይነት እንደሆነና እንዴት ሊገለጽ እንደሚችል ሕያው በሆነ መልኩ ያሳያል። ባለትዳሮችም ሆኑ ያላገቡ የይሖዋ አምላኪዎች ይህን መጽሐፍ በትኩረት በመመርመር ዘላቂ ስለሆነ ፍቅር ብዙ መማር ይችላሉ።

እውነተኛ ፍቅር አለ!

3. በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል እውነተኛ ፍቅር ሊኖር ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

3 ማሕልየ መሓልይ 8:6ን አንብብ። ፍቅርን ለመግለጽ የተሠራበት ‘የያህ ነበልባል’ የሚለው ሐረግ ትልቅ ትርጉም አለው። እውነተኛ ፍቅር ‘የያህ ነበልባል’ የተባለው እንዲህ ያለው ፍቅር ምንጭ ይሖዋ ስለሆነ ነው። ሰው የተፈጠረው በአምላክ አምሳል በመሆኑ ፍቅር የማንጸባረቅ ችሎታ አለው። (ዘፍ. 1:26, 27) አምላክ የመጀመሪያዋን ሴት ማለትም ሔዋንን ወደ አዳም ሲያመጣት አዳም ደስታውን የገለጸው በግጥም ነው ሊባል ይችላል። ሔዋን ‘የተገኘችው’ ከአዳም በመሆኑ በጣም ትቀርበው እንደነበር ጥርጥር የለውም። (ዘፍ. 2:21-23) ይሖዋ፣ ሰዎችን ሲፈጥር ፍቅር ማሳየት እንዲችሉ አድርጎ በመሆኑ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ጊዜ የማይለውጠውና የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል።

4, 5. በማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ላይ ያለውን ታሪክ በአጭሩ ተናገር።

4 ተቃራኒ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል ያለው ፍቅር የማይለዋወጥና ዘላቂ ሊሆን ይችላል፤ እንዲህ ያለው ፍቅር ሌሎች መለያዎችም አሉት። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ውስጥ ግሩም በሆነ ሁኔታ ተገልጸዋል። በሙዚቃ ተውኔት መልክ የተጻፈው ይህ መዝሙር፣ በሹነም ወይም በሱለም መንደር በምትኖር አንዲት ወጣት እና በምትወደው እረኛ መካከል ስላለው ፍቅር የሚተርክ ነው። ሰለሞን ሱላማዊቷ ልጃገረድ በምትጠብቀው የወይን ተክል እርሻ አቅራቢያ ለተወሰነ ጊዜ በተቀመጠበት ወቅት በውበቷ ስለተማረከ እሱ ወዳለበት ሰፈር አስመጣት። ይሁንና ሱላማዊቷ ከእረኛው ጋር ፍቅር እንደያዛት ከመጽሐፉ መጀመሪያ አንስቶ በግልጽ መመልከት ይቻላል። ሰለሞን ልቧን ለመማረክ ሲሞክር፣ ልጅቷ ከምትወደው ወጣት ጋር ለመሆን ያላትን ጉጉት በተደጋጋሚ ትገልጻለች። (ማሕ. 1:4-14) ከዚያም እረኛው ወደ ሰለሞን ሰፈር ሲመጣ ሁለቱ ወጣቶች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ውብ በሆኑ ቃላት ይገልጻሉ።—ማሕ. 1:15-17

5 በኋላም ሰለሞን፣ ወጣቷን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ እረኛውም ተከትሏት መጣ። (ማሕ. 4:1-5, 8, 9) ሰለሞን የሱላማዊቷን ፍቅር ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሁሉ አልተሳካም። (ማሕ. 6:4-7፤ 7:1-10) በመጨረሻም ወደ ቤቷ እንድትመለስ ፈቀደላት። መዝሙሩ የሚደመደመው ሱላማዊቷ፣ እንደ ሚዳቋ ‘ፈጥኖ’ እንዲመጣ ለውዷ በምታቀርበው ጥያቄ ነው።—ማሕ. 8:14

6. በታሪኩ ላይ የተናጋሪዎቹን ማንነት ማወቅ አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?

6 ‘ከመዝሙሮች ሁሉ የሚበልጠው የሰለሞን መዝሙር’ ትልቅ ትርጉም ያለውና ማራኪ በሆነ መንገድ የተጻፈ ቢሆንም በመዝሙሩ ውስጥ በተካተቱት ውይይቶች የተካፈሉት እንዲሁም መነባንቦቹንና ሕልሞቹን የተናገሯቸው እነማን እንደሆኑ ማወቁ ቀላል አይደለም። (ማሕ. 1:1) ዘ ኒው ኢንተርፕሪተርስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንደሚገልጸው በዚህ መጽሐፍ ላይ “ለታሪኩ መዋቅር፣ ለታሪኩ፣ ለትረካው፣ ለባለታሪኮቹና ለመሳሰሉት ነገሮች ትኩረት አልተሰጠም።” የተናጋሪዎቹ ስም ሳይጠቀስ የቀረው የግጥሙና የመዝሙሩ ውበት እንዳይሸፈን ሲባል ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ባለታሪኮቹ አንዳቸው ለሌላው ከሚናገሩት ወይም ስለ እነሱ ከሚነገረው ሐሳብ በመነሳት የተናጋሪዎቹን ማንነት ማወቅ ይቻላል። *

 “የፍቅር መግለጫዎችህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ደስ ያሰኛሉ”

7, 8. በማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኙት “የፍቅር መግለጫዎች” ምን ማለት ይቻላል? ምሳሌ ስጥ።

7 የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ወጣቷ ሴትና እረኛው የተጠቀሙባቸውን በርካታ “የፍቅር መግለጫዎች” [NW] ይዟል። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት አገላለጾች ከዛሬ 3,000 ዓመታት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ የነበረውን ባሕል የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው በዘመናችን ላሉ አንባቢዎች እንግዳ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ያም ቢሆን ጥልቅ ትርጉም ያላቸው ሲሆን በመዝሙሩ ላይ የተገለጹትን ስሜቶችም መረዳት አይከብደንም። ለምሳሌ እረኛው፣ ደግነት የሚንጸባረቅባቸው የወጣቷ ዓይኖች “እንደ ርግብ ዐይኖች” መሆናቸውን በመግለጽ አሞካሽቷታል። (ማሕ. 1:15) እሷ ደግሞ የእረኛውን ዓይኖች ከርግብ ዓይኖች ሳይሆን ከርግቦች ጋር አመሳስላቸዋለች። (ማሕልየ መሓልይ 5:12ን አንብብ።) በነጭ የተከበበው የዓይኑ ብሌን በወተት እንደሚታጠብ ርግብ ውብ ሆኖ ታይቷት ነበር።

8 በመዝሙሩ ውስጥ ካሉት የፍቅር መግለጫዎች መካከል በውጫዊ ውበት ላይ ያተኮሩት ሁሉም አይደሉም። እረኛው ስለ ወጣቷ አንደበት ምን እንዳለ እንመልከት። (ማሕልየ መሓልይ 4:7, 11ን አንብብ።) “ከንፈሮችሽ የማር እንጀራ ወለላ ያንጠባጥባሉ” [NW] ብሏታል። ይህን ያለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የማር እንጀራ ወለላ፣ ተቆርጦ ከቆየ ማር ይልቅ ጣፋጭ ከመሆኑም ሌላ ግሩም ጣዕም አለው። ከአንደበቷ “ወተትና ማር ይፈልቃል”፤ በሌላ አባባል ንግግሯ መልካምና ለዛ ያለው ነው። በእርግጥም እረኛው፣ “ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ እንከንም አይወጣልሽም” ሲላት ከአካላዊ ውበቷ ባሻገር እንደተመለከተ ግልጽ ነው።

9. (ሀ) በትዳር ጓደኛሞች መካከል ያለው ፍቅር የትኞቹን ነገሮች ይጨምራል? (ለ) የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር መግለጻቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 ጋብቻ፣ ፍቅር የሌለበት ውል ወይም ስምምነት አይደለም። እንዲያውም ፍቅር የክርስቲያኖች ጋብቻ መለያ ነው። ይሁንና ይህ ምን ዓይነት ፍቅር ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ ፍቅር ነው? (1 ዮሐ. 4:8) በቤተሰብ አባላት መካከል የሚኖረው ዓይነት ተፈጥሯዊ ፍቅር ነው? በእውነተኛ ጓደኛሞች መካከል የሚኖረውን ዓይነት መቀራረብና የጠበቀ ወዳጅነት ያመለክታል? (ዮሐ. 11:3) ወይስ በተቃራኒ ፆታዎች መካከል የሚኖረው ዓይነት ፍቅር ነው? (ምሳሌ 5:15-20) በትዳር ጓደኛሞች መካከል የሚኖረው እውነተኛና ጊዜ የማይለውጠው ፍቅር ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ ያካትታል። ፍቅር ይበልጥ የሚታየው በቃላትም ሆነ በተግባር ሲገለጽ ነው። ባለትዳሮች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ቢጠመዱም አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር መግለጻቸው በጣም አስፈላጊ ነው! እንዲህ ያሉት የፍቅር መግለጫዎች በጋብቻ ውስጥ መተማመን እንዲኖርና ደስታ እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ሙሽሮች የሚያገቡት ሌሎች የመረጡላቸውን ሰው ሲሆን ተጋቢዎቹ ከሠርጉ ቀን በፊት ብዙም ላይተዋወቁ ይችላሉ፤ እንዲህ ያለ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር በቃላት መግለጻቸው ፍቅራቸው እንዲያድግና ጋብቻቸው እየጠነከረ እንዲሄድ ያደርጋል።

10. የፍቅር መግለጫዎች የሚፈጥሩት ትዝታ ምን ጥቅም አለው?

10 ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን መግለጻቸው ሌላም ጥቅም አለው። ንጉሥ ሰለሞን ለሱላማዊቷ ልጃገረድ “ባለ ብር ፈርጥ፣ የወርቅ ጕትቻ” እንደሚሰጣት ነግሯት ነበር። እንዲሁም “እንደ ጨረቃ የደመቀች፣ እንደ ፀሓይ ያበራች” መሆኗን በመግለጽ የውዳሴ ቃላት አዥጎድጉዶላታል። (ማሕ. 1:9-11፤ 6:10) ወጣቷ ግን ለምትወደው እረኛ ታማኝ ነበረች። ከፍቅረኛዋ ርቃ በቆየችበት ወቅት በአቋሟ እንድትጸና የረዳትና ያጽናናት ምን ነበር? በመዝሙሩ ላይ መልሱን ነግራናለች። (ማሕልየ መሓልይ 1:2, 3ን አንብብ።) የእረኛውን “የፍቅር መግለጫዎች” ማስታወሷ ነው። ፍቅረኛዋ የተናገረው ነገር ልብን ደስ ከሚያሰኘው  “ከወይን ጠጅ” የላቀ እንደሆነ ተሰምቷታል፤ ስሙም በራስ ላይ ‘እንደሚፈስ ሽቱ’ ሆኖላታል። (መዝ. 23:5፤ 104:15) በእርግጥም የትዳር ጓደኛሞች የሚጠቀሙባቸው የፍቅር መግለጫዎች የሚፈጥሩት አስደሳች ትዝታ ፍቅራቸው ዘላቂ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንግዲያው ባልና ሚስት፣ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር አዘውትረው መግለጻቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!

“ራሱ እስኪፈልግ ድረስ” ፍቅርን አትቀስቅሱት

11. ሱላማዊቷ ወጣት፣ ፍቅርን በውስጧ እንዳይቀሰቅሱ ሌሎችን ማስማሏ ላላገቡ ክርስቲያኖች ምን ትምህርት ይሰጣል?

11 የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ላላገቡ በተለይ ደግሞ ማግባት ለሚፈልጉ ክርስቲያኖችም ጠቃሚ ምክር ይዟል። ሱላማዊቷ ወጣት ለሰለሞን ፍቅር አልነበራትም። በመሆኑም የኢየሩሳሌምን ሴቶች “ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት” በማለት አምላቸዋለች። (ማሕ. 2:7፤ 3:5) ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ፍቅር ሊኖረን የሚገባው ለሁሉም ሰው አይደለም። እንግዲያው የማግባት ፍላጎት ያለው አንድ ክርስቲያን ከልቡ የሚወዳት ሴት እስኪያገኝ ድረስ በትዕግሥት መጠበቁ ጥበብ ነው።

12. ሱላማዊቷ ልጃገረድ እረኛውን የወደደችው ለምንድን ነው?

12 ሱላማዊቷ ልጃገረድ እረኛውን የወደደችው ለምንድን ነው? እረኛው “ሚዳቋ” እንደሚመስል ስለተገለጸ መልከ መልካም እንደነበረ ግልጽ ነው፤ ክንዶቹ እንደ “ወርቅ ዘንግ” ብርቱ ሲሆኑ እግሮቹም እንደ “ዕብነ በረድ ምሰሶዎች” ውብና ጠንካራ ናቸው። ወጣቷን የማረካት ግን መልኩና ጥንካሬው ብቻ አይደለም። “በዱር ዛፎች መካከል እንዳለ እንኰይ [“የፖም ዛፍ፣” NW]፣ ውዴም በጐልማሶች መካከል እንዲሁ ነው” ብላለች። ለይሖዋ ታማኝ የሆነች አንዲት ወጣት እንዲህ ሊሰማት የቻለው እረኛው መንፈሳዊ ዝንባሌ ስላለው መሆን አለበት።—ማሕ. 2:3, 9፤ 5:14, 15

13. እረኛው ወጣቷን የወደዳት ለምንድን ነው?

13 ስለ ሱላማዊቷ ልጃገረድስ ምን ማለት ይቻላል? በወቅቱ “ሥልሳ ንግሥቶች፣ ሰማንያ ቁባቶች፣ ቍጥራቸውም የበዛ ደናግል” የነበሩትን ንጉሥ የማረከ ውበት ቢኖራትም “እኔ የሳሮን ጽጌረዳ፣ የሸለቆም አበባ ነኝ” በማለት ራሷን በየቦታው ከሚገኝ አበባ ጋር አመሳስላለች። ይህች ወጣት ቦታዋን የምታውቅና በጣም ትሑት ነበረች። በእርግጥም እረኛው፣ የትም እንደሚገኝ አበባ ሳይሆን “በእሾኽ መካከል እንዳለ ውብ አበባ” አድርጎ የተመለከታት መሆኑ የሚገርም አይደለም! ይህች ወጣት ለይሖዋ ታማኝ ነበረች።—ማሕ. 2:1, 2፤ 6:8

14. በማሕልየ መሓልይ ላይ ስለ ፍቅር የተገለጸው ሐሳብ ማግባት ለሚያስቡ ክርስቲያኖች ምን ትምህርት ይዟል?

 14 ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ክርስቲያኖች “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ይሰጣሉ። (1 ቆሮ. 7:39) ትዳር የመመሥረት ፍላጎት ያለው አንድ ክርስቲያን ከማያምኑ ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት ከመጀመር ይርቃል፤ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት የሚሞክረው ከይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች መካከል ብቻ ነው። የትዳር ጓደኛሞች የሕይወትን ውጣ ውረድ እየተቋቋሙ ትዳራቸው ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ለማድረግና በመንፈሳዊ ነገሮች አንድነታቸውን ለመጠበቅ እምነትና ለአምላክ ያደሩ መሆን ያስፈልጋቸዋል፤ በመሆኑም አንድ ክርስቲያን፣ የትዳር ጓደኛ ሲመርጥ እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቅ ሰው መፈለጉ የተገባ ነው። እረኛውም ሆነ ወጣቷ እነዚህ ባሕርያት ነበሯቸው።

ክርስቲያኖች ለማያምኑ ሰዎች የፍቅር ስሜት እንዳያድርባቸው ይጠነቀቃሉ (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

ሙሽራዬ “የታጠረ የአትክልት ቦታ” ናት

15. ሱላማዊቷ ልጃገረድ፣ አምላካዊ ፍርሃት ላላቸው ያላገቡ ወንዶችና ሴቶች ምሳሌ የምትሆነው እንዴት ነው?

15 ማሕልየ መሓልይ 4:12ን አንብብ። እረኛው፣ ውዱን “የታጠረ የአትክልት ቦታ” እንደሆነች አድርጎ የገለጻት ለምንድን ነው? ወደታጠረ የአትክልት ቦታ መግባት የሚችለው ሁሉም ሰው አይደለም። መግባት የሚችለው የበሩ ቁልፍ ያለው ሰው ብቻ ነው። ሱላማዊቷ እንዲህ ባለ የአትክልት ስፍራ የተመሰለችው ፍቅሯን የምትሰጠው ልታገባው ላሰበችው ሰው ይኸውም ለእረኛው ብቻ በመሆኑ ነው። ወጣቷ ለንጉሡ ማባበያዎች አልተሸነፈችም፤ በመሆኑም ወለል ብሎ እንደሚከፈት “በር” ሳይሆን እንደ “ቅጥር” መሆኗን አሳይታለች። (ማሕ. 8:8-10) በተመሳሳይም አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ያላገቡ ወንዶችና ሴቶች ለሚያገቡት ሰው ካልሆነ በቀር ለሌላ ሰው ፍቅር ከማሳየት ይቆጠባሉ።

16. ከማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ስለ መጠናናት ምን ትምህርት እናገኛለን?

16 እረኛው በአንድ የጸደይ ዕለት አብረው በእግራቸው እንዲንሸራሸሩ ሱላማዊቷን ወጣት ጠይቋት ነበር፤ ወንድሞቿ ግን አልፈቀዱላትም። ከዚህ ይልቅ የወይን እርሻዎች ጠባቂ አደረጓት። ይህን ያደረጉት ለምንድን ነው? ሳያምኗት ቀርተው ነው? ወይስ ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር ትፈጽማለች ብለው ስለፈሩ? ይህን ያደረጉት እህታቸው ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳትገባ ጥንቃቄ ለማድረግ ብለው ነው። (ማሕ. 1:6፤ 2:10-15) ያላገባችሁ ክርስቲያኖች ከዚህ ግሩም ትምህርት ታገኛላችሁ፦ በምትጠናኑበት ወቅት ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችሁን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጉ። ማንም ሰው በሌለበት ቦታ ጊዜ ከማሳለፍ ተቆጠቡ። ንጹሕ የሆኑ የፍቅር መግለጫዎችን ማሳየት ተገቢ ሊሆን ቢችልም ወደ ፈተና ሊመሯችሁ ከሚችሉ ሁኔታዎች ራቁ።

17, 18. የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍን በመመርመራችን ምን ጥቅም አግኝተሃል?

17 ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ትዳር ሲመሠርቱ አንዳቸው ለሌላው ጥልቅ ፍቅር ይኖራቸዋል። ይሖዋ የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው ዘላቂ እንዲሆን አስቦ በመሆኑ ባልና ሚስት የፍቅራቸው ነበልባል ሁልጊዜ እንዲነድድ እንዲሁም ፍቅራቸው እያደገ እንዲሄድ ጥረት ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው።—ማር. 10:6-9

18 የትዳር ጓደኛ የምትፈልጉ ከሆነ ደግሞ በማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው፣ ከልባችሁ የምትወዱት ሰው ለማግኘት ብሎም ለዚህ ሰው ጥልቅና ፈጽሞ የማይከስም ፍቅር ለማዳበር እንደምትጥሩ የታወቀ ነው። የትዳር ጓደኛ እየፈለጋችሁ ያላችሁም ሆነ ትዳር የመሠረታችሁ ክርስቲያኖች ‘በያህ ነበልባል’ የተመሰለው ዓይነት እውነተኛ ፍቅር እንዲኖራችሁ ምኞታችን ነው።ማሕ. 8:6

^ አን.2 የጥር 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31ን ተመልከት።

^ አን.6 በአዲስ ዓለም ትርጉም ማሕልየ መሓልይ ላይ “የመጽሐፉ ይዘት” የሚለውን ክፍል ተመልከት።