በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስን በድፍረቱና በአስተዋይነቱ ምሰሉት

ኢየሱስን በድፍረቱና በአስተዋይነቱ ምሰሉት

“እሱን አይታችሁት ባታውቁም እንኳ ትወዱታላችሁ። አሁን እያያችሁት ባይሆንም እንኳ በእሱ ላይ ያላችሁን እምነት በተግባር እያሳያችሁ . . . ነው።”—1 ጴጥ. 1:8

1, 2. (ሀ) መዳን ለማግኘት ምን ማድረግ አለብን? (ለ) መዳን ለማግኘት በምናደርገው ጉዞ ከመንገዳችን ሳንወጣ እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?

የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስንሆን አንድ ዓይነት ጉዞ ጀምረናል። ይህ ጉዞ በሰማይ አሊያም በምድር ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻው [እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ወይም እስከዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ] የጸና . . . እሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴ. 24:13) በእርግጥም በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በታማኝነት ጎዳና ጸንተን የምንመላለስ ከሆነ መዳን እናገኛለን። ይሁንና በጉዟችን ላይ መንገዳችንን እንዳንስት ወይም መንገዱ እንዳይጠፋብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 2:15-17) ለመሆኑ ከመንገድ ሳንወጣ ለመጓዝ ምን ይረዳናል?

2 ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ መንገዱን አሳይቶናል። እሱ ያደረገው ጉዞ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ዘገባ በማጥናት ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው እንደነበር ማወቅ እንችላለን። ይህን ማድረጋችን እሱን እንድንወድደውና እምነት እንድንጥልበት ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 1:8 9ን አንብብ።) ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድንከተል አርዓያ እንደተወልን መግለጹን አስታውስ። (1 ጴጥ. 2:21) የእሱን ፈለግ በጥብቅ ከተከተልን የእምነታችን ግብ ወይም “የመጨረሻ ውጤት”  ላይ እንደርሳለን፤ አዎ ለመዳን እንበቃለን። * ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ኢየሱስ ትሕትና እና ርኅራኄ በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ እንዴት መከተል እንደምንችል መርምረናል። አሁን ደግሞ ድፍረት እና ማስተዋል በማሳየት ረገድ የእሱን ፈለግ እንዴት መከተል እንደምንችል እንመልከት።

ኢየሱስ ደፋር ነው

3. ድፍረት ምንድን ነው? ማዳበር የምንችለውስ እንዴት ነው?

3 ድፍረት የልበ ሙሉነት መገለጫ ከመሆኑም ሌላ ብርታትና ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል። ደፋር መሆን “አስቸጋሪ ሁኔታን በጽናት መቋቋም፣” “ትክክል ለሆነው ነገር አቋም መውሰድ” እና “ክብርን ጠብቆ ወይም በእምነት መከራን መጋፈጥ” ተብሎ ተገልጿል። ድፍረት ከፍርሃት፣ ከተስፋና ከፍቅር ጋር ተያያዥነት አለው። እንዴት? አምላካዊ ፍርሃት፣ የሰው ፍርሃትን እንድናሸንፍ የሚያስችል ድፍረት ይሰጠናል። (1 ሳሙ. 11:7፤ ምሳሌ 29:25) እውነተኛ ተስፋ አሁን እየደረሰብን ካለው መከራ ባሻገር መመልከት እንድንችልና የወደፊቱን ጊዜ በእርግጠኝነት እንድንጠባበቅ ይረዳናል። (መዝ. 27:14) የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት እንድናደርግ የሚያነሳሳ ፍቅር ደግሞ ለአደጋ በሚያጋልጠን ሁኔታ ውስጥም እንኳ ድፍረት እንድናሳይ ይገፋፋናል። (ዮሐ. 15:13) በአምላክ በመታመንና የልጁን ፈለግ በመከተል ድፍረት ማዳበር እንችላለን።—መዝ. 28:7

4. ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ “በመምህራን መካከል ተቀምጦ” ሳለ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

4 ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ እንኳ ለትክክለኛው ነገር በድፍረት አቋም ወስዷል። ኢየሱስ በልጅነቱ “ቤተ መቅደሱ ውስጥ በመምህራን መካከል ተቀምጦ” ሳለ የተከሰተውን ነገር ልብ በል። (ሉቃስ 2:41-47ን አንብብ።) እነዚያ መምህራን የሙሴን ሕግ ብቻ ሳይሆን ይህን ሕግ የሚያወሳስቡትን የሰዎች ወጎችም አሳምረው ያውቁ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ፈርቶ ዝም አላለም፤ እንዲያውም ጥያቄ “ሲጠይቃቸው” ነበር። ኢየሱስ እንዲሁ የልጅ ጥያቄ እንዳልጠየቃቸው ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። እነዚያ ከፍተኛ እውቀት ያላቸው አስተማሪዎች ጆሮ ሰጥተው በትኩረት እንዲያዳምጡት የሚያደርጉ አመራማሪ ጥያቄዎችን እንደጠየቃቸው መገመት እንችላለን። መምህራኑ ኢየሱስን ለማሳሳት ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች አቅርበውለት ከነበረም እንዳልተሳካላቸው ግልጽ ነው። እነሱን ጨምሮ ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ሁሉ “በማስተዋል ችሎታውና በመልሱ ተደንቀው” ነበር፤ የሰጣቸው መልሶችም የአምላክን ቃል እውነት ይደግፉ እንደነበር ጥርጥር የለውም!

5. ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ድፍረት ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

5 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት በተለያዩ መንገዶች ድፍረት አሳይቷል። በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የሐሰት ትምህርት እያስተማሩ ሕዝቡን እንደሚያሳስቱ በመግለጽ በድፍረት አጋልጧቸዋል። (ማቴ. 23:13-36) የዓለምን በካይ ተጽዕኖዎች በጽናት ተቋቁሟል። (ዮሐ. 16:33) ተቃዋሚዎች ስደት ቢያደርሱበትም ከመስበክ ወደኋላ አላለም። (ዮሐ. 5:15-18፤ 7:14) በቤተ መቅደሱ የሚከናወነውን አምልኮ የሚያረክሱትን ሰዎች ከአንዴም ሁለቴ በድፍረት በማባረር ቤተ መቅደሱን አጽድቷል።—ማቴ. 21:12, 13፤ ዮሐ. 2:14-17

6. ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ዕለት ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ መከራ ቢደርስበትም በድፍረት ስለወሰዳቸው እርምጃዎች መመርመራችን እምነታችንን ያጠናክርልናል። በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ዕለት ድፍረት ያሳየው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ኢየሱስ አሳልፎ የሚሰጠው ሰው በሚፈጽመው ድርጊት የተነሳ በተከታታይ የሚደርሱበትን ነገሮች ያውቃል። ያም ሆኖ የፋሲካን ራት እየበሉ ሳለ ይሁዳን “እያደረግከው ያለኸውን ነገር ቶሎ አድርገው” ብሎታል። (ዮሐ. 13:21-27) በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራም ኢየሱስ ሊይዙት ለመጡት ወታደሮች ያለ ምንም ፍርሃት ማንነቱን አሳውቋቸዋል። የገዛ ሕይወቱ ለአደጋ ተጋልጦ የነበረ ቢሆንም ደቀ መዛሙርቱን እንዲተዉአቸው በድፍረት  ተናግሯል። (ዮሐ. 18:1-8) በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ጥያቄ ሲቀርብለት ሊቀ ካህናቱ ሊያስገድለው ሰበብ እየፈላለገ እንደሆነ ቢያውቅም እሱ ክርስቶስና የአምላክ ልጅ መሆኑን አስረግጦ ተናግሯል። (ማር. 14:60-65) ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ከንጹሕ አቋሙ ፍንክች አላለም። በእስትንፋሱ ማቆሚያ ላይ እያቃሰተ ባለበት ሰዓት “ተፈጸመ” ሲል በድል አድራጊነት ስሜት ተናግሯል።—ዮሐ. 19:28-30

ኢየሱስን በድፍረቱ ምሰሉት

7. ወጣቶች በይሖዋ ስም በመጠራታችሁ ምን ይሰማችኋል? ደፋር መሆናችሁን ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው?

7 ድፍረት በማሳየት ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? በትምህርት ቤት፦ ወጣቶች፣ የይሖዋ ምሥክር መሆናችሁን ማሳወቃችሁ ከእናንተ ጋር የሚማሩ ልጆች ወይም ሌሎች ሰዎች እንዲያሾፉባችሁ ሊያደርግ ቢችልም ማንነታችሁን መናገራችሁ ድፍረት እንዳላችሁ ያሳያል። ይህን ስታደርጉ በይሖዋ ስም በመጠራታችሁ ኩራት እንደሚሰማችሁ ታረጋግጣላችሁ። (መዝሙር 86:12ን አንብብ።) የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ እውነት እንደሆነ አድርጋችሁ እንድትቀበሉ ጫና ይደረግባችሁ ይሆናል። ሆኖም ፍጥረትን በተመለከተ ያላችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት ትክክል መሆኑን በእርግጠኝነት እንድትቀበሉ የሚያደርጉ በቂ ማስረጃዎች አሉ። “ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው” አሳማኝ መልስ ለመስጠት የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች በሚለው ብሮሹር መጠቀም ትችላላችሁ። (1 ጴጥ. 3:15) በዚህ መንገድ፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ደግፋችሁ መቆማችሁ እርካታ ያስገኝላችኋል።

8. በድፍረት እንድንሰብክ የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉ?

8 በአገልግሎታችን፦ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን “በይሖዋ ሥልጣን በድፍረት” ከመናገር ወደኋላ ማለት የለብንም። (ሥራ 14:3) በድፍረት ወይም ያለ ፍርሃት እንድንሰብክ የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉ? የምንሰብከው መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ እውነት መሆኑን እናውቃለን። (ዮሐ. 17:17) “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ” እንደሆንን እና የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ እንደማይለየን እንገነዘባለን። (1 ቆሮ. 3:9፤ ሥራ 4:31) በቅንዓት መስበካችን ለይሖዋ ያደርን እንደሆን ብሎም ለሰዎች ፍቅር እንዳለን የሚያሳይ መሆኑን እንረዳለን። (ማቴ. 22:37-39) ድፍረት ከመስበክ ወደኋላ እንዳንል ያደርገናል። እንዲያውም ሰዎች እውነትን እንዳያዩ የሚያሳውሯቸውን ሃይማኖታዊ ውሸቶች ለማጋለጥ ቆርጠን እንነሳለን። (2 ቆሮ. 4:4) በተጨማሪም ሰዎች ግድ የለሽ ቢሆኑም፣ ቢያፌዙብንም ወይም ቢቃወሙንም ምሥራቹን በመስበክ እንጸናለን።—1 ተሰ. 2:1, 2

9. መከራ ሲያጋጥመን ድፍረት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

9 መከራ ሲያጋጥመን፦ በአምላክ መታመናችን፣ የሚያጋጥሙንን መከራዎች በእምነትና በድፍረት እንድንጋፈጥ ያስችለናል። የምንወደው ሰው ቢሞት ማዘናችን አይቀርም፤ ሆኖም ተስፋ እንደሌላቸው አንሆንም። “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ብርታት እንደሚሰጠን በመተማመን ወደ እሱ ዞር እንላለን። (2 ቆሮ. 1:3, 4፤ 1 ተሰ. 4:13) ከባድ በሽታ ቢይዘን ወይም ጉዳት ቢደርስብን እንደምንሠቃይ የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን አቋማችንን አናላላም። ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጭ ምንም ዓይነት ሕክምና አንቀበልም። (ሥራ 15:28, 29) በመንፈስ ጭንቀት ብንዋጥ ‘ልባችን ይኮንነን’ ይሆናል፤ ሆኖም “ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ” በሆነው አምላክ ስለምንተማመን ተስፋ አንቆርጥም። *1 ዮሐ. 3:19, 20፤ መዝ. 34:18

ኢየሱስ አስተዋይ ነው

10. ማስተዋል ምንድን ነው? አስተዋይ የሆነ የይሖዋ አገልጋይ ንግግሩም ሆነ ድርጊቱ ምን ይመስላል?

10 ማስተዋል፣ ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታ ሲሆን ይህ ባሕርይ ክፉና ደጉን ለይተን እንድናውቅና የጥበብ ጎዳና እንድንመርጥ ያስችለናል። (ዕብ. 5:14) ማስተዋል “ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ  ትክክለኛ ውሳኔ የማድረግ ችሎታ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። አስተዋይ የሆነ የይሖዋ አገልጋይ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ አምላክን ለማስደሰት ይጥራል። እንዲህ ያለው ሰው ሌሎችን የሚጎዳ ሳይሆን የሚጠቅም ነገር ለመናገር ይጠነቀቃል። (ምሳሌ 11:12, 13) ደግሞም “ታጋሽ” ነው፤ በሌላ አባባል ቶሎ አይቆጣም። (ምሳሌ 14:29) በሕይወት ጎዳና ላይ ሲመላለስ “ቀጥተኛውን መንገድ” ሳይለቅ ማለትም ከትክክለኛው ጎዳና ሳይወጣ ይጓዛል። (ምሳሌ 15:21) ታዲያ ማስተዋል ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክን ቃል ማጥናትና የተማርነውን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:1-5, 10, 11) በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ ይበልጥ አስተዋይ ሰው የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ መመርመራችን በዚህ ረገድ በጣም ይረዳናል።

11. ኢየሱስ በንግግሩ አስተዋይ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ የሚናገረውም ሆነ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ማስተዋል ይንጸባረቅበት ነበር። በንግግሩ፦ ምሥራቹን ሲሰብክ አድማጮቹን ያስደነቁ “የሚማርኩ ቃላት” በመጠቀም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዳለው አሳይቷል። (ሉቃስ 4:22፤ ማቴ. 7:28) የሚፈልገውን ነጥብ ለማስተላለፍ ከቅዱሳን መጻሕፍት ተስማሚ የሆነ ጥቅስ በማንበብ ወይም በቃሉ በመናገር አሊያም የጥቅሱን ሐሳብ በመግለጽ በአምላክ ቃል የመጠቀም ልማድ ነበረው። (ማቴ. 4:4, 7, 10፤ 12:1-5፤ ሉቃስ 4:16-21) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ የአድማጮቹን ልብ በሚነካ መንገድ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያብራራ ነበር። ከሞት ከተነሳ በኋላ ደግሞ ወደ ኤማሁስ እየሄዱ ለነበሩ ሁለት ደቀ መዛሙርት “ስለ እሱ በቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን በሚገባ [አብራርቶላቸዋል]።” በኋላ ላይ እነዚህ ደቀ መዛሙርት “ቅዱሳን መጻሕፍትን ግልጽልጽ አድርጎ ሲያስረዳን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረም?” ብለዋል።—ሉቃስ 24:27, 32

12, 13. ኢየሱስ ቶሎ እንደማይቆጣና ምክንያታዊ እንደሆነ የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?

12 በሚያሳየው መንፈስና በአስተሳሰቡ፦ ኢየሱስ አስተዋይ መሆኑ ስሜቱን እንዲቆጣጠርና “ታጋሽ” በሌላ አባባል ቶሎ የማይቆጣ ሰው እንዲሆን ረድቶታል። (ምሳሌ 16:32) ኢየሱስ “ገር” ነበር። (ማቴ. 11:29) ደቀ መዛሙርቱ የተለያዩ ድክመቶች ቢኖሩባቸውም ምንጊዜም በትዕግሥት ይይዛቸው ነበር። (ማር. 14:34-38፤ ሉቃስ 22:24-27) ኢየሱስ በደል በተፈጸመበት ጊዜ እንኳ ሁኔታውን በሰከነ መንፈስ አሳልፏል።—1 ጴጥ. 2:23

13 ኢየሱስ አስተዋይ መሆኑ ምክንያታዊ እንዲሆንም ረድቶታል። በሙሴ ሕግ ላይ የሰፈሩትን ቃላት እንዳለ ከመውሰድ ይልቅ ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን መንፈስ በመረዳት ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስዷል። በማርቆስ 5:25-34 ላይ የሚገኘውን ዘገባ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (ጥቅሱን አንብብ።) ደም ይፈሳት የነበረ አንዲት ሴት በሰዎች መካከል አልፋ በመምጣት የኢየሱስን ልብስ ስትነካ ተፈወሰች። በሕጉ መሠረት ርኩስ ስለነበረች ማንንም መንካት አልነበረባትም። (ዘሌ. 15:25-27) ኢየሱስ ግን ‘በሕጉ ውስጥ ከሚገኙት ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች’ መካከል “ምሕረትና ታማኝነት” እንደሚካተቱ ስላስተዋለ ልብሱን በመንካቷ አልተቆጣትም። (ማቴ. 23:23) ከዚህ ይልቅ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፣ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም እረፊ” በማለት በደግነት አናግሯታል። አስተዋይነት ኢየሱስ እንዲህ የመሰለ ደግነት እንዲያሳይ ያነሳሳው መሆኑ ምንኛ ልብ የሚነካ ነው!

14. ኢየሱስ ምን ለማድረግ መርጧል? ከመንገዱ ሳይወጣ ለመጓዝስ ምን አድርጓል?

14 በተከተለው የሕይወት ጎዳና፦ ኢየሱስ ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና በመምረጥና ያንን በጥብቅ በመከተል አስተዋይ መሆኑን አሳይቷል። ራሱን ሳይቆጥብ በምሥራቹ ስብከት ሥራ በመካፈል ሕይወቱ በዚያ ላይ ያተኮረ እንዲሆን አድርጓል። (ሉቃስ 4:43) በተጨማሪም በሥራው ላይ እንዲያተኩርና ሥራው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የሚረዱ ውሳኔዎች በማድረግ ከመንገዱ ሳይወጣ በጽናት ተጉዟል። ጊዜውንና ጉልበቱን ለአገልግሎቱ ለማዋል ሲል ቀላል ሕይወት በመምራት የጥበብ አካሄድ ተከትሏል። (ሉቃስ 9:58) እሱ ከሞተ በኋላ ሥራውን የሚቀጥሉ ሌሎች ሰዎችን ማሠልጠን አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ሉቃስ 10:1-12፤  ዮሐ. 14:12) ደግሞም “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ” በሥራው እንደሚረዳቸው ለተከታዮቹ ቃል ገብቶላቸዋል።—ማቴ. 28:19, 20

ኢየሱስን በአስተዋይነቱ ምሰሉት

የሰዎችን ዝንባሌ አስተውለህ በዚያ መሠረት አነጋግራቸው (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

15. ንግግራችን ማስተዋል የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ምን ማድረግ እንችላለን?

15 ኢየሱስን መምሰል የምንችልበትን ሌላ መንገድ ደግሞ እንመልከት። በንግግራችን፦ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ስንነጋገር የሚያፈርስ ሳይሆን የሚያንጽ ቃል እንጠቀማለን። (ኤፌ. 4:29) ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ስንሰብክ ንግግራችን “በጨው” የተቀመመ እንዲሆን ለማድረግ እንጥራለን። (ቆላ. 4:6) የምናነጋግራቸው ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገርና ዝንባሌያቸውን አስተውለን በዚያ መሠረት እናወያያቸዋለን። ንግግራችን ለዛ ያለው መሆኑ መስበክ የምንችልበት አጋጣሚም ሆነ የሰዎችን ልብ ሊከፍት እንደሚችል አንዘነጋም። በተጨማሪም ስለ እምነታችን ስንገልጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን። በመሆኑም እንደ ባለሥልጣን የምንጠቅሰው መጽሐፍ ቅዱስን ነው፤ እንዲሁም አመቺ በሆነ ጊዜ ሁሉ ለሰዎች ጥቅስ አውጥተን እናነብላቸዋለን። ከራሳችን አመንጭተን ከምንናገረው ከየትኛውም ሐሳብ በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ከፍተኛ ኃይል እንዳለው እንገነዘባለን።—ዕብ. 4:12

16, 17. (ሀ) ለቁጣ የዘገየንና ምክንያታዊ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ትኩረታችን በአገልግሎታችን ላይ ያረፈ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

16 በምናሳየው መንፈስና በአስተሳሰባችን፦ ማስተዋል መንፈሳችንን እንድንቆጣጠር ስለሚረዳን ‘ለቁጣ የዘገየን’ እንድንሆን ያስችለናል። (ያዕ. 1:19) ሌሎች ቅር የሚያሰኘን ነገር ሲናገሩ ወይም ሲያደርጉ ይህን ያደረጉበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለመረዳት እንጥራለን። እንዲህ ዓይነት ማስተዋል ያለን መሆኑ ቁጣችን እንዲበርድና ‘በደልን ንቀን እንድንተው’ ይረዳናል። (ምሳሌ 19:11) አስተዋይነት ምክንያታዊ ለመሆንም ያስችለናል። ምክንያታዊ ከሆንን የእምነት ባልንጀሮቻችን፣ እኛ ሙሉ በሙሉ የማንረዳላቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች እየተጋፈጡ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ከእነሱ ብዙ ላለመጠበቅ ጥረት እናደርጋለን። አመለካከታቸውን ለማዳመጥና ተገቢ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የእነሱን አስተሳሰብ ለማስቀደም ፈቃደኞች እንሆናለን።—ፊልጵ. 4:5

17 በምንከተለው የሕይወት ጎዳና፦ የኢየሱስ ተከታዮች በመሆናችን፣ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ከመካፈል መብታችን የበለጠ ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን። ምንጊዜም በአገልግሎታችን ላይ ለማተኮር የሚያስችሉንን ውሳኔዎች በማድረግ ከመንገዳችን ሳንወጣ እንጓዛለን። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት፣ ከሁሉ በላይ አስፈላጊ በሆነው የስብከት ሥራ የምንችለውን ያህል ለመካፈል ስንል መንፈሳዊ ነገሮችን እናስቀድማለን፤ እንዲሁም ቀላል ሕይወት እንመራለን።—ማቴ. 6:33፤ 24:14

18. ለመዳን በምናደርገው ጉዞ ከመንገድ ሳንወጣ ለመሄድ ምን ይረዳናል? ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

18 ማራኪ ከሆኑት የኢየሱስ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹን በመመርመርህ አልተደሰትክም? ሌሎች ባሕርያቱን መመርመር እንዲሁም እሱን ይበልጥ መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ደግሞ ምን ያህል እንደሚክስ አስብ። እንግዲያው ቁርጥ ውሳኔያችን የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል ይሁን። ይህን ስናደርግ ለመዳን በምናደርገው ጉዞ ከመንገድ ሳንወጣ የምንሄድ ከመሆኑም ሌላ ኢየሱስ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ወደመሰለው አካል ይኸውም ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን።

^ አን.2 አንደኛ ጴጥሮስ 1:8, 9 የተጻፈው ሰማያዊ ተስፋ ላላቸው ክርስቲያኖች ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ግን ምድራዊ ተስፋ ላላቸውም ይሠራል።

^ አን.9 መከራ ቢደርስባቸውም ድፍረት ያሳዩ ሰዎችን ምሳሌ በታኅሣሥ 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 24-28፣ በግንቦት 2003 ንቁ! ከገጽ 16-19 እንዲሁም በጥር 22, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 11-15 ላይ ማግኘት ይቻላል።