በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሽማግሌዎች፣ ሌሎችን ስለማሠልጠን ምን አመለካከት አላችሁ?

ሽማግሌዎች፣ ሌሎችን ስለማሠልጠን ምን አመለካከት አላችሁ?

“ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።”—መክ. 3:1

1, 2. የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ምን ነገር አስተውለዋል?

የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ከሽማግሌዎች አካል ጋር የሚያደርገውን ስብሰባ ሊያጠናቅቅ ተቃርቧል። እነዚህን ትጉ እረኞች ሲመለከታቸው በውስጡ ልዩ ስሜት ተሰማው፤ አንዳንዶቹ በዕድሜ ትልቅ በመሆናቸው አባቱ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። በሌላ በኩል ግን አንድ ያሳሰበው ነገር ስለነበር እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ወንድሞች፣ ሌሎች በጉባኤ ውስጥ ለተጨማሪ ኃላፊነት እንዲበቁ በማሠልጠን ረገድ ምን አድርጋችኋል?” ሽማግሌዎቹ፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ባለፈው ጉብኝቱ ወቅት ሌሎችን ለማሠልጠኑ ሥራ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስቧቸው እንደነበር ትዝ አላቸው። አንደኛው ሽማግሌ “እውነቱን ለመናገር፣ ያን ያህል ጥረት አላደረግንም” በማለት መለሰ። ሌሎቹም ሽማግሌዎች በመልሱ መስማማታቸውን ለማሳየት ራሳቸውን ነቀነቁ።

2 አንተም ሽማግሌ ከሆንክ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ወጣቶችንም ሆነ በዕድሜ ከፍ ያሉትን ወንድሞች አሠልጥኖ ለኃላፊነት በማብቃት ረገድ ብዙ የሚቀር ነገር እንዳለ አስተውለዋል። ይሁንና ይህን ኃላፊነት መወጣት የራሱ ተፈታታኝ ነገሮች አሉት። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

3. (ሀ) ሌሎችን ማሠልጠን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው እንዴት ነው? ለዚህ ጉዳይ ሁላችንም ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) አንዳንድ ሽማግሌዎች ሌሎችን ማሠልጠን ከባድ የሆነባቸው ለምንድን ነው?

3 እረኛ እንደመሆንህ መጠን ሌሎችን በግለሰብ ደረጃ ማሠልጠን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ሳትገነዘብ አትቀርም። * አሁን ያሉት ጉባኤዎች በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው እንዲቀጥሉ ብሎም አዳዲስ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ከተፈለገ ተጨማሪ ወንድሞች እንደሚያስፈልጉ የታወቀ ነው። (ኢሳይያስ 60:22ን አንብብ።) በተጨማሪም የአምላክ ቃል ‘ሌሎችን እንድታስተምር’ ማሳሰቢያ እንደሰጠህ ታውቃለህ። (2 ጢሞቴዎስ 2:2ን አንብብ።) ያም ሆኖ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሱት ሽማግሌዎች አንተም ሌሎችን ማሠልጠን ከብዶህ ሊሆን ይችላል። የቤተሰብህን ፍላጎት ማሟላትን፣ ሰብዓዊ ሥራ መሥራትንና የጉባኤ ኃላፊነት መወጣትን ጨምሮ ሌሎች አጣዳፊ ሥራዎች እንዳሉብህ ስታስብ ሌሎችን ለማሠልጠን ጊዜ እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። ይህ ሁሉ ኃላፊነት እያለብህም ሌሎችን ለማሠልጠኑ ሥራ ትልቅ ቦታ መስጠት ያለብህ ለምንድን ነው? እስቲ ምክንያቶቹን እንመልከት።

ሌሎችን ማሠልጠን ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል

4. አንዳንድ ሽማግሌዎች የማሠልጠኑን ሥራ ለሌላ ጊዜ የሚያስተላልፉበት አንዱ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል?

4 አንዳንድ ሽማግሌዎች ጊዜ መድበው ሌሎችን ማሠልጠን ከባድ እንዲሆንባቸው የሚያደርገው አንዱ ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? አንዳንዶች እንዲህ ብለው ያስቡ ይሆናል፦ ‘ሌሎችን ማሠልጠን አስፈላጊ ቢሆንም ጊዜ ከማይሰጡ ሌሎች የጉባኤ ሥራዎች አንጻር ሲታይ ያን ያህል አጣዳፊ አይደለም። ሥልጠናውን በሌላ ጊዜ ባደርገው ጉባኤው ላይ የሚያመጣው ጉዳት የለም።’ ጊዜ የማይሰጡ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው እውነት ቢሆንም ሥልጠናውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ የጉባኤውን መንፈሳዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል።

5, 6. በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሾፌር መኪናውን የያዘበትን መንገድ እንዴት ትገልጹታላችሁ? ይህ ምሳሌ በጉባኤ ውስጥ ለሌሎች ሥልጠና ከመስጠት ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

5 እስቲ ይህን ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ ሾፌር የመኪናው ሞተር ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን ከፈለገ በየጊዜው ዘይት መቀየር እንዳለበት ያውቃል። ያም ቢሆን ዘይት መቀየር ነዳጅ የመሙላትን ያህል አጣዳፊ እንዳልሆነ ይሰማዋል። ደግሞም ነዳጅ ካልሞላ መኪናው መቆሙ አይቀርም። ሾፌሩ ‘ዘይት መቀየሩን ለሌላ ጊዜ ባስተላልፈው ሞተሩ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን መሥራቱ አይቀርም’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። ይሁንና እንዲህ ማድረጉ ምን አደጋ አለው? ሾፌሩ ዘይት መቀየሩን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉን ከቀጠለ አንድ ቀን ሞተሩ ነክሶ መኪናው መቆሙ አይቀርም። በዚህ ጊዜ መኪናውን ለመጠገን ብዙ ጊዜ ማጥፋትና በርካታ ገንዘብ ማውጣት ግድ ይሆንበታል። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?

6 ሽማግሌዎች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ በርካታ አጣዳፊ ጉዳዮች አሉ፤ እነዚህ ጉዳዮች በአስቸኳይ ካልተከናወኑ ጉባኤው በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሾፌር ነዳጅ መሙላቱ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ሽማግሌዎችም ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተው ማወቅ’ አለባቸው። (ፊልጵ. 1:10) ይሁንና አንዳንድ ሽማግሌዎች ጊዜ በማይሰጡ ሌሎች ጉዳዮች ስለሚጠመዱ ሌሎችን ማሠልጠን በምሳሌያዊ አባባል ዘይት መቀየራቸውን ችላ ይላሉ። ሆኖም ሽማግሌዎች ሥልጠናውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፋቸውን ከቀጠሉ ይዋል ይደር እንጂ ጉባኤው አስፈላጊ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ብቃት ያላቸው ወንድሞችን በማጣት መቸገሩ አይቀርም።

7. ሌሎችን ለማሠልጠን ጊዜያቸውን መሥዋዕት የሚያደርጉ ሽማግሌዎችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?

7 ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሥልጠና መስጠት ‘ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም’ የሚለውን አስተሳሰብ ማስወገድ ይኖርብናል። ልምድ የሌላቸውን ወንድሞች ለማሠልጠን ጊዜያቸውን መሥዋዕት የሚያደርጉና አርቆ አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች ጥበበኛ መጋቢዎች ከመሆናቸውም በላይ ለጉባኤው በረከት ናቸው። (1 ጴጥሮስ 4:10ን አንብብ።) ለመሆኑ ጉባኤው ጥቅም ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?

ጊዜን በአግባቡ መጠቀም

8. (ሀ) ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? (ለ) እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደው የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ምን አጣዳፊ ሥራ ማከናወን ይኖርባቸዋል? (“ አጣዳፊ ሥራ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

8 ተሞክሮ ያካበቱ ሽማግሌዎችም እንኳ በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ በጉባኤ ውስጥ የሚያከናውኑት ሥራ ውስን እየሆነ እንደሚመጣ አምነው በመቀበል ልካቸውን እንደሚያውቁ ማሳየት አለባቸው። (ሚክ. 6:8) በተጨማሪም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” በሕይወታቸው ውስጥ ድንገተኛ ለውጥ ሊያመጡና የጉባኤ ኃላፊነታቸውን መወጣት ሊያቅታቸው እንደሚችል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (መክ. 9:11, 12ያዕ. 4:13, 14) ስለሆነም የይሖዋ በጎች ደህንነት የሚያሳስባቸው አርቀው የሚመለከቱ ሽማግሌዎች ያካበቱትን ተሞክሮ ከእነሱ በዕድሜ ለሚያንሱ ወንድሞች በማካፈል ጊዜያቸውን በአግባቡ ይጠቀማሉ።መዝሙር 71:17, 18ን አንብብ።

9. ሥልጠና መስጠት በጣም አስፈላጊ የሆነው ከፊታችን ምን ስለሚጠብቀን ነው?

9 ሽማግሌዎች ሌሎችን ማሠልጠናቸው ሌላስ ምን ጥቅም ያስገኛል? የጉባኤው መንፈሳዊነት ይጠናከራል። እንዴት? ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን ጥረት ማድረጋቸው ጉባኤውን የሚረዱ ብዙ ወንድሞች እንዲገኙ ያደርጋል፤ እነዚህ ወንድሞች ደግሞ ጉባኤው በአሁኑ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተለይ በታላቁ መከራ ወቅት ጸንቶ እንዲቆምና አንድነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። (ሕዝ. 38:10-12ሚክ. 5:5, 6) በመሆኑም ውድ ሽማግሌዎች፣ የሥራችሁ አንዱ ክፍል እንደሆነ አድርጋችሁ በመቁጠር ከዛሬ ጀምሮ ሌሎችን እንድታሠለጥኑ እንለምናችኋለን።

10. አንድ ሽማግሌ ሌሎችን ለማሠልጠን የሚያስችል ጊዜ ማግኘት ከፈለገ ምን ማድረግ ይኖርበታል?

10 በጉባኤ ውስጥ ያሉ አስፈላጊ የሆኑ ኃላፊነቶችን መወጣት በራሱ ጊዜያችሁን ሊወስድባችሁ እንደሚችል እንረዳለን። ያም ቢሆን ከዚህ ጊዜ ላይ የተወሰነውን በመውሰድ ሌሎችን ለማሠልጠን መጠቀም ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። (መክ. 3:1) እንዲህ ማድረጋችሁ ጊዜያችሁን በአግባቡ እንደምትጠቀሙ የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ጉባኤውን ይጠቅማል።

ለሥልጠና አመቺ ሁኔታ መፍጠር

11. (ሀ) በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሽማግሌዎች ሌሎችን ስለማሠልጠን የሰጡት ሐሳብ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በምሳሌ 15:22 መሠረት ሌሎች ሽማግሌዎች የሰጧቸውን ሐሳቦች መመርመር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

11 ወንድሞችን በመንፈሳዊ እንዲያድጉ በመርዳት ረገድ የተዋጣላቸው አንዳንድ ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን ምን ዓይነት ዘዴዎችን እንደተጠቀሙ በቅርቡ ተጠይቀው ነበር። * እነዚህ ሽማግሌዎች ያሉበት ሁኔታ በእጅጉ የተለያየ ቢሆንም የሰጡት ምክር በሚያስገርም ሁኔታ ይመሳሰላል። ይህ ምን ይጠቁማል? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ለተማሪዎች የሚሰጠው ይህ ሥልጠና በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ብቻ ሳይሆን ዛሬም በሁሉም ‘ስፍራ በሚገኙ ጉባኤዎች’ ውስጥ ይሠራል። (1 ቆሮ. 4:17) በመሆኑም እነዚህ ሽማግሌዎች የሰጧቸውን አንዳንድ ሐሳቦች በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን። (ምሳሌ 15:22) ለአጻጻፍ እንዲመች ስንል በእነዚህ ርዕሶች ውስጥ ሥልጠና የሚሰጡትን ሽማግሌዎች “አስተማሪዎች” ሥልጠና የሚቀበሉትን ደግሞ “ተማሪዎች” እንላቸዋለን።

12. አስተማሪዎች ሥልጠና ከመጀመራቸው በፊት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ለምንስ?

12 አስተማሪዎች ለሥልጠና አመቺ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባቸዋል። አንድ ገበሬ ዘር ከመዝራቱ በፊት መሬቱን ማለስለስ እንዳለበት ሁሉ አንድ አስተማሪም ተማሪውን ማሠልጠን ከመጀመሩ በፊት የተማሪውን ልብ ማዘጋጀት ይኖርበታል። ታዲያ አስተማሪዎች ሌሎችን ለማሠልጠን አመቺ ሁኔታ መፍጠር የሚችሉት እንዴት ነው? በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ነቢይ የተጠቀመውን ዘዴ በመከተል ነው። ይህ ዘዴ ምንድን ነው?

13-15. (ሀ) ነቢዩ ሳሙኤል ምን ኃላፊነት ተሰጠው? (ለ) ሳሙኤል ኃላፊነቱን የተወጣው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ሐ) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ሽማግሌዎች ስለ ሳሙኤል ለሚናገረው ለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ልዩ ትኩረት መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ ከዛሬ 3,000 ዓመታት በፊት፣ በዕድሜ ለገፋው ለነቢዩ ሳሙኤል እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ነገ በዚህ ጊዜ ገደማ ከቢንያም ምድር የመጣ አንድ ሰው ወደ አንተ እልካለሁ። አንተም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ አድርገህ ቀባው።” (1 ሳሙ. 9:15, 16) ሳሙኤል እሱን የሚተካ ሰው እንዲቀባ ይሖዋ ተልእኮ ሲሰጠው እስራኤልን የመምራት ኃላፊነቱ እንዳበቃ ተገነዘበ። ሳሙኤል ‘ይህን ሰው ለዚህ ኃላፊነት ማዘጋጀት የምችለው እንዴት ነው?’ ብሎ አስቦ መሆን አለበት። ሳሙኤል አንድ ሐሳብ መጣለት፤ ከዚያም ሐሳቡን ተግባራዊ ማድረግ የሚችልበትን እቅድ አወጣ።

14 በማግስቱ ሳሙኤል ከሳኦል ጋር ተገናኘ፤ በዚህ ጊዜ ይሖዋ ለሳሙኤል “የነገርኩህ ሰው ይህ ነው” አለው። ከዚያም ሳሙኤል አስቀድሞ ባወጣው እቅድ መሠረት፣ አብሮት ምግብ እንዲበላ ሳኦልን ወደ መመገቢያ አዳራሹ ወሰደው። እዚያ ሲደርሱ ሳኦልና አገልጋዩ በክብር ቦታ እንዲቀመጡ አደረገ፤ ከዚያም ሳሙኤል ምርጥ የሆነውን ሥጋ ሳኦል ፊት በማቅረብ “ይህ ለዚህ ጊዜ ብለው ለይተው ያስቀመጡልህ ስለሆነ ብላ” አለው። ከምግብ በኋላ ሳሙኤል ሳኦልን ወደ ቤቱ ወሰደው፤ ወደ ነቢዩ ቤት የሄዱት እየተጨዋወቱ ነበር። ሳሙኤል ጥሩ ምግብ መመገባቸውና እንዲህ ያለ ዘና ያለ ጉዞ የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞበታል። ወደ ቤት ሲደርሱም ሳኦልን ወደ ሰገነቱ ይዞት ወጣ። የምሽቱን ነፋሻማ አየር እያጣጣሙ እንቅልፋቸው እስኪመጣ ድረስ ‘በቤቱ ሰገነት ላይ ሆነው ሲነጋገሩ ቆዩ።’ በማግስቱ ሳሙኤል ሳኦልን ቀባው፤ ከዚያም ከሳመው በኋላ ተጨማሪ መመሪያዎችን ሰጠው። ሳሙኤል በዚህ መንገድ ሳኦልን ከፊቱ ለሚጠብቀው ነገር ካዘጋጀው በኋላ አሰናበተው።—1 ሳሙ. 9:17-27፤ 10:1

15 እርግጥ ነው፣ አንድን ሰው የአንድ ብሔር መሪ እንዲሆን መሾምና አንድን ወንድም ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ እንዲሆን ማሠልጠን የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ያም ቢሆን ሽማግሌዎች ሳሙኤል ከተጠቀመበት ዘዴ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት ይችላሉ። እስቲ ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እንመልከት።

በደስታ አስተምሩ፤ እውነተኛ ጓደኛ ሁኑ

16. (ሀ) ሳሙኤል እስራኤላውያን ንጉሥ እንዲሾምላቸው ሲጠይቁት ምን ተሰማው? (ለ) ሳሙኤል ሳኦልን እንዲሾም የተሰጠውን ኃላፊነት የተወጣው በምን ዓይነት መንፈስ ነው?

16 ግዴታ እንደሆነ ተሰምቷችሁ ሳይሆን በደስታ አስተምሩ። ሳሙኤል እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ እንደሚፈልጉ ሲነግሩት መጀመሪያ ላይ ተከፍቶና እሱን እንዳልተቀበሉት ተሰምቶት ነበር። (1 ሳሙ. 8:4-8) እንዲያውም የሕዝቡን ጥያቄ ለመፈጸም አመንትቶ ስለነበር ይሖዋ ሕዝቡን እንዲሰማ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ነግሮታል። (1 ሳሙ. 8:7, 9, 22) ያም ቢሆን ሳሙኤል እሱን በሚተካው ሰው ላይ ጥላቻ ወይም ቅሬታ እንዲያድርበት አልፈቀደም። ይሖዋ ሳኦልን እንዲቀባ ሲነግረው ታዟል፤ ይህን ያደረገው ግዴታ ስለሆነበት ሳይሆን በፍቅር ተነሳስቶና ደስ እያለው ነበር።

17. በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች የሳሙኤል ዓይነት ባሕርይ ማንጸባረቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህስ ምን እርካታ ያስገኝላቸዋል?

17 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ለሚያሠለጥኗቸው ወንድሞች ልክ እንደ ሳሙኤል ጥሩ መንፈስ ማሳየት አለባቸው። (1 ጴጥ. 5:2) እንዲህ ያሉ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያሏቸውን አንዳንድ መብቶች ተማሪዎቹ ሊወስዱባቸው እንደሚችሉ በመፍራት እነሱን ከማሠልጠን ወደኋላ አይሉም። ደጎችና ሌሎችን በደስታ የሚረዱ አስተማሪዎች፣ ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ተማሪዎችን የሚመለከቷቸው እንደ ተቀናቃኝ ሳይሆን ‘ከእነሱ ጋር አብረው እንደሚሠሩና’ ለጉባኤው ውድ ስጦታ እንደሆኑ አድርገው ነው። (2 ቆሮ. 1:24፤ ዕብ. 13:16) ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ሌሎችን የሚያሠለጥኑ እንዲህ ያሉ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎቹ ችሎታቸውን ተጠቅመው ጉባኤውን ሲያገለግሉ ማየታቸው ልዩ የእርካታ ስሜት እንደሚፈጥርላቸው ግልጽ ነው!—ሥራ 20:35

18, 19. አንድ ሽማግሌ የተማሪውን ልብ ለሥልጠና ማዘጋጀት የሚችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለው አቀራረብ ውጤታማ የሆነውስ ለምንድን ነው?

18 አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ጓደኛም ሁኑ። ሳሙኤል ሳኦልን ሲያገኘው ወዲያውኑ የዘይቱን ዕቃ አውጥቶ በሳኦል ራስ ላይ በማፍሰስ ሊሸኘው ይችል ነበር። እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ሳኦል ንጉሥ መሆኑ አይቀርም ነበር፤ ኃላፊነቱን ለመወጣት ግን ሙሉ በሙሉ ዝግጁ አይሆንም ነበር። ሳሙኤል እንዲህ ከማድረግ ይልቅ የሳኦልን ልብ ለማዘጋጀት ጊዜ ወስዶ አንዳንድ ነገሮችን አድርጓል። ሳኦልን የቀባው ጥሩ ምግብ ከተመገቡ፣ ደስ የሚል የእግር ጉዞ ካደረጉ፣ ለረጅም ጊዜ ሲያወሩ ከቆዩና ጥሩ እረፍት ካደረጉ በኋላ ነው።

አንድ አስተማሪ ሥልጠና መስጠት ከመጀመሩ በፊት ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ያስፈልገዋል (አንቀጽ 18, 19ን ተመልከት)

19 በዛሬው ጊዜም አንድ አስተማሪ ሥልጠና ከመጀመሩ በፊት ዘና ያለ ሁኔታ እንዲኖርና ከተማሪው ጋር ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ሽማግሌዎች እንዲህ ያለ ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚወስዷቸው እርምጃዎች እንደ አካባቢው ሁኔታና ባሕል ሊለያዩ ይችላሉ። ይሁንና የምትኖረው የትም ይሁን የት እንዲሁም ምንም ያህል ሥራ የሚበዛብህ ሽማግሌ ብትሆን ከተማሪው ጋር ጊዜ ማሳለፍህ ‘በእኔ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለህ’ የሚል መልእክት ያስተላልፋል። (ሮም 12:10ን አንብብ።) በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ለመማር ፈቃደኛ የሆነ ተማሪ ይህን መልእክት በሚገባ እንደሚያስተውልና በጥልቅ እንደሚነካው ጥርጥር የለውም።

20, 21. (ሀ) አንድ አስተማሪ ውጤታማ ነው የሚባለው ምን ካለው ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኛውን ጉዳይ እንመረምራለን?

20 አንድ አስተማሪ ውጤታማ የሚባለው ሌሎችን የማሠልጠን ፍቅር ስላለው ብቻ ሳይሆን ለሚያሠለጥነው ሰው ጭምር ፍቅር ሲኖረው እንደሆነ ሽማግሌዎች ማስታወስ አለባቸው። (ከዮሐንስ 5:20 ጋር አወዳድር።) አንድ አስተማሪ ለተማሪው ፍቅር ካለው ተማሪው ይህን በቀላሉ ሊያስተውል ይችላል፤ እንዲሁም ለሥልጠናው ጥሩ ምላሽ እንዲሰጥ ያነሳሳዋል። በመሆኑም ውድ ሽማግሌዎች፣ ሌሎችን ስታሠለጥኑ አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ጓደኛም ሁኗቸው።—ምሳሌ 17:17፤ ዮሐ. 15:15

21 አንድ ሽማግሌ የተማሪውን ልብ ካዘጋጀ በኋላ ሥልጠናውን መስጠት መጀመር ይችላል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ዓይነት ዘዴዎችን መጠቀም ይችላል? ይህን ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።

^ አን.3 በዚህና በሚቀጥለው ሳምንት የሚጠኑት ርዕሶች በዋነኝነት የተዘጋጁት ለሽማግሌዎች ቢሆንም ሌሎቹ የጉባኤው አባላትም ለትምህርቱ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። ለምን? እነዚህ የጥናት ርዕሶች የተጠመቁ ወንዶች በሙሉ በጉባኤ ውስጥ ለበለጠ ኃላፊነት እንዲበቁ ሥልጠና ማግኘታቸው አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ይረዷቸዋል። እንዲህ ከሆነ ሁሉም ጥቅም ማግኘት ይችላሉ።

^ አን.11 እነዚህ ሽማግሌዎች የተውጣጡት ከሜክሲኮ፣ ከሩሲያ፣ ከሪዩኒየን፣ ከባንግላዲሽ፣ ከቤልጅየም፣ ከብራዚል፣ ከናሚቢያ፣ ከናይጄሪያ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከኮሪያ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከጃፓን፣ ከፈረንሳይ እና ከፍሬንች ጊያና ነው።