ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን
“እጆቻችሁን አንጹ፤ . . . ልባችሁን አጥሩ።”—ያዕ. 4:8
1. ዓለም ስለ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መጠበቅ በተለይ በዘመናችን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር አይደለም። በብዙ አገሮች ውስጥ ግብረ ሰዶማዊነትና ከጋብቻ ውጪ የፆታ ግንኙነት መፈጸም ተቀባይነት ያላቸው ነገሮች ሆነዋል። ማስታወቂያዎችም ሆነ የመዝናኛው ዓለም እንዲህ ያለውን አኗኗር ያበረታታሉ። (መዝ. 12:8) የብልግና አኗኗር በጣም ከመስፋፋቱ የተነሳ ‘ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ጠብቆ መኖር ይቻላል?’ የሚለው ነገር ያሳስብህ ይሆናል። በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው አንድ ነገር አለ፦ እውነተኛ ክርስቲያኖች በይሖዋ እርዳታ ንጽሕናቸውን ጠብቀው መኖር ይችላሉ።—1 ተሰሎንቄ 4:3-5ን አንብብ።
2, 3. (ሀ) ርኩስ የሆኑ ምኞቶችን ለማስወገድ መጣር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 ንጹሕ ሆነን ለመኖር ግን በመጀመሪያ የብልግና ምኞቶችን ማስወገድ እንዳለብን መገንዘብ ያስፈልገናል። መንጠቆ ላይ የሚንጠለጠለው ምግብ ዓሣዎችን እንደሚማርክ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም የብልግና ሐሳቦችንና አስነዋሪ ምኞቶችን ወዲያውኑ ከአእምሮው ካላስወገደ በምኞቱ ሊማረክና ሊታለል ይችላል። እንዲህ ያሉት ምኞቶች ኃጢአተኛ የሆነውን ሥጋችንን በመማረክ ወደ ሥነ ምግባራዊ ብልግና ሊመሩን ይችላሉ። ውሎ አድሮም የኃጢአት መስህብ እየበረታ ስለሚሄድ ርኩስ የሆኑ ምኞቶች በውስጣችን ይፀነሳሉ። አንድ የይሖዋ አገልጋይም እንኳ እዚህ ደረጃ ከደረሰ፣ አጋጣሚውን ሲያገኝ ምኞቱን ሊፈጽም ይችላል። አዎን፣ “ምኞት . . . ኃጢአትን ትወልዳለች።”—ያዕቆብ 1:14, 15ን አንብብ።
ገላ. 5:16) ርኩስ የሆኑ ምኞቶችን ለማስወገድ የሚረዱንን ሦስት ነገሮች እስቲ እንመልከት፤ እነሱም ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና፣ ከቃሉ የምናገኘው ምክርና የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚሰጡን እርዳታ ናቸው።
3 መጥፎ ምኞት ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም ሊያመራ የሚችል መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። ይሁንና ርኩስ የሆኑ ምኞቶች ሥር እንዳይሰዱ ከተከላከልን ከሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ብልግና ከሚያስከትላቸው አስከፊ መዘዞች መራቅ እንደምንችል ማወቁ ምንኛ የሚያበረታታ ነው። (“ወደ አምላክ ቅረቡ”
4. ወደ ይሖዋ መቅረብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ ‘ወደ አምላክ መቅረብ’ ለሚፈልጉ ሁሉ “እጆቻችሁን አንጹ” እንዲሁም “ልባችሁን አጥሩ” የሚል መመሪያ ይሰጣል። (ያዕ. 4:8) ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ የምናስባቸውን ነገሮች ጨምሮ በመላ ሕይወታችን አምላክን ለማስደሰት ጥረት እናደርጋለን። አእምሯችን ንጹሕና በጎ በሆኑ እንዲሁም ምስጋና በሚገባቸው ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ “ንጹሕ ልብ” እንዲኖረን እንደምንፈልግ እናሳያለን። (መዝ. 24:3, 4፤ 51:6፤ ፊልጵ. 4:8) ይሖዋ ፍጽምና የሚጎድለን መሆኑን ከግምት እንደሚያስገባ ጥያቄ የለውም። ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶች በቀላሉ ሊያድሩብን እንደሚችሉ ያውቃል። ያም ቢሆን መጥፎ ሐሳቦችን ለማስወገድ የምንችለውን ያህል ጥረት ከማድረግ ይልቅ የምናሰላስልባቸው ከሆነ ይሖዋ እንደሚያዝን እንገነዘባለን። (ዘፍ. 6:5, 6) በዚህ እውነታ ላይ ማተኮራችን ሐሳባችን ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን ይበልጥ ጥረት ለማድረግ ያነሳሳናል።
5, 6. ጸሎት የብልግና ምኞቶችን ለማስወገድ የሚረዳን እንዴት ነው?
5 በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደምንታመን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ርኩስ ሐሳቦችን ለማስወገድ በምናደርገው ትግል እሱ እንዲረዳን መጸለይ ነው። በጸሎት አማካኝነት ወደ ይሖዋ ስንቀርብ እሱም ወደ እኛ ይቀርባል። ቅዱስ መንፈሱን በልግስና ስለሚሰጠን የብልግና ሐሳቦችን ለማስወገድና ንጹሕ ሆነን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። እንግዲያው በልባችን በምናሰላስለው ነገር አምላክን የማስደሰት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን ለእሱ በጸሎት እንንገረው። (መዝ. 19:14) ታዲያ ወደ ኃጢአት ሊመራን የሚችል ማንኛውም “ጎጂ የሆነ ዝንባሌ” ይኸውም ተገቢ ያልሆነ ምኞት ወይም ሐሳብ በውስጣችን መኖሩን ማወቅ እንድንችል አምላክ እንዲመረምረን በትሕትና እንጠይቀዋለን? (መዝ. 139:23, 24) እንዲሁም ፈተና ሲያጋጥመን ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ እንዲረዳን አዘውትረን እንለምነዋለን?—ማቴ. 6:13
6 አስተዳደጋችን ወይም የቀድሞ አኗኗራችን ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች እንድንወድ ተጽዕኖ ያደርግብን ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚያስፈልጉትን ለውጦች ለማድረግ ይረዳናል። ንጉሥ ዳዊት ይህን ተገንዝቦ ነበር። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ይሖዋን “ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር” በማለት ተማጽኖታል። (መዝ. 51:10, 12) ደካማው ሥጋችን በኃጢአት ድርጊቶች በቀላሉ ሊማረክ ይችላል፤ ይሁንና ይሖዋ የፈቃደኝነት መንፈስ ይኸውም እሱን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጣችን እንዲቀሰቀስ ሊረዳን ይችላል። መጥፎ ምኞቶች በውስጣችን ሥር ሰደው ንጹሕ ሐሳቦችን ገፍተው ለማውጣት ቢሞክሩም እንኳ ይሖዋ የእሱን መመሪያዎች በመታዘዝ በዚያ መሠረት መኖር እንድንችል አካሄዳችንን ይመራልናል። ይሖዋ ማንኛውም ጎጂ ነገር በእኛ ላይ እንዳይሠለጥን ሊከላከልልን ይችላል።—መዝ. 119:133
“ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ”
7. የአምላክ ቃል ርኩስ የሆኑ ሐሳቦች ወደ አእምሯችን እንዳይገቡ ለመከላከል የሚረዳን እንዴት ነው?
7 ይሖዋ የእሱን እርዳታ ለማግኘት የምናቀርበውን ጸሎት በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይመልስልናል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ጥበብ “በመጀመሪያ ንጹሕ ነው።” (ያዕ. 3:17) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል የብልግና ሐሳቦች ወደ አእምሯችን እንዳይገቡ ለመከላከል ይረዳናል። (መዝ. 19:7, 11፤ 119:9, 11) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ርኩስ በሆኑ ምኞቶች እንዳንሸነፍ የሚረዱ ምሳሌዎችና ግልጽ ምክሮች ይዟል።
8, 9. (ሀ) አንድ ወጣት ሥነ ምግባር ከጎደላት ሴት ጋር የፆታ ብልግና ወደ መፈጸም የመራው ምንድን ነው? (ለ) በምሳሌ 7 ላይ የሚገኘውን ማስጠንቀቂያ በዘመናችን ካሉ ከየትኞቹ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ልናደርገው እንችላለን?
8 በምሳሌ 5:8 ላይ “ከእሷ [ሥነ ምግባር ከጎደላት ሴት] ራቅ፤ ወደ ቤቷም ደጃፍ አትቅረብ” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። እንዲህ ያለውን ምክር ችላ ማለት የሚያስከትለው አደጋ በምሳሌ ምዕራፍ 7 ላይ ተገልጿል፤ ምዕራፉ ሥነ ምግባር የጎደላት ሴት በምትኖርበት አካባቢ ቀኑ መሸትሸት ሲል በእግሩ መንሸራሸር ስለጀመረ አንድ ወጣት ይናገራል። በመንገዱ መታጠፊያ ላይ ሴትየዋ አገኘችው፤ ይህች ሴት ሰውነቷን የሚያጋልጥ ልብስ ለብሳ ይሆናል። ወጣቱን አፈፍ አድርጋ ይዛ ሳመችው። የሚያማልለው ንግግሯ በውስጡ የቀሰቀሰበትን ምኞት መቋቋም አልቻለም። በመሆኑም የፆታ ብልግና ፈጸሙ። ይህ ወጣት ከቤቱ የወጣው የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም አስቦ እንደማይሆን ግልጽ ነው። ወጣቱ ተሞክሮና ማስተዋል ይጎድለዋል። የሆኖ ሆኖ ድርጊቱ የሚያስከትልበትን አስከፊ መዘዝ ማምለጥ አይችልም። ይህች ሴት ወዳለችበት ባይቀርብ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር!—ምሳሌ 7:6-27
9 እኛም አንዳንድ ጊዜ ማመዛዘን እንደጎደለን የሚያሳይ ነገር እንፈጽም ምናልባትም መጥፎ ምኞቶች እንዲቀሰቀሱብን በሚያደርግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ
እንገባ ይሆን? ለምሳሌ ሌሊት ላይ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በፕሮግራሞቻቸው ላይ ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ እምብዛም ቁጥጥር አያደርጉ ይሆናል። እንግዲያው ምን እየተላለፈ እንዳለ ለማየት ብለን ብቻ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የምንቀያይር ከሆነ አደጋ ውስጥ ልንገባ እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ ኢንተርኔት ላይ የሚያጋጥሙንን ሊንኮች ወዴት እንደሚመሩን ሳናውቅ የመክፈት ልማድ ይኖረን ይሆናል፤ አሊያም የፖርኖግራፊ ማስታወቂያዎች ወይም ሌላ ዓይነት ከፆታ ብልግና ጋር የተያያዙ ግብዣዎች የሚመጡባቸው ድረ ገጾችን ወይም ቻት ሩሞችን አዘውትረን እንጠቀም ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ውስጥ መጥፎ ምኞቶችን የሚቀሰቅሱ ወይም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ የምናደርገውን ትግል የሚያዳክሙ ፈተናዎች ሊያጋጥሙን አይችሉም?10. ማሽኮርመም አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
10 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ምክር በመስጠትም እርዳታ ያበረክትልናል። (1 ጢሞቴዎስ 5:2ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ከማሽኮርመም መራቅ እንዳለብን በግልጽ ያሳያል። አንዳንዶች ከአንድ ሰው ጋር እስካልተነካኩ ድረስ፣ የፍቅር ስሜት እንዳላቸው የሚጠቁም አካላዊ መግለጫ ማሳየት ወይም በፍቅር ስሜት መተያየት ምንም ጉዳት እንደሌለው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ማሽኮርመምም ሆነ መሽኮርመም ርኩስ የሆኑ ሐሳቦች እንዲቀሰቀሱ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ይህም የብልግና ድርጊቶችን ወደመፈጸም ሊመራ ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ከአሁን በፊት አጋጥሟል፤ ወደፊትም ሊያጋጥም ይችላል።
11. ዮሴፍ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
11 በዚህ ረገድ ዮሴፍ ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ ወስዷል። የጌታው የጶጢፋር ሚስት አብሯት እንዲተኛ ለማድረግ በሞከረች ጊዜ ዮሴፍ አልተሸነፈም። እሷ ግን ተስፋ አልቆረጠችም። አብሯት እንዲሆን ነጋ ጠባ ትወተውተው ነበር። (ዘፍ. 39:7, 8, 10) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደተናገሩት የጶጢፋር ሚስት “ዮሴፍ የመጀመሪያውን እርምጃ እንዲወስድ ለማነሳሳት ስትል ‘ብቻችንን ትንሽ ጊዜ ብናሳልፍ ምናለበት?’” ትለው የነበረ ያህል ነው። ዮሴፍ ግን እሱን ለማማለል የምታደርገውን ጥረት እንድትቀጥልበት ላለማበረታታት ሌላው ቀርቶ በዝምታ ላለማለፍ ቆርጦ ነበር። ዮሴፍ አልተሽኮረመመም፤ እሷንም አላሽኮረመማትም፤ ይህ ደግሞ ምንም ዓይነት መጥፎ ምኞት በልቡ ውስጥ ሥር እንዳይሰድ ረድቶታል። ከእሷ ጋር የፆታ ብልግና እንዲፈጽም ልታስገድደው ስትሞክር ዮሴፍ ቆራጥ እርምጃ ወሰደ። “ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ወደ ውጭ ሸሽቶ ወጣ።”—ዘፍ. 39:12
12. የምናየው ነገር በልባችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እንዴት እናውቃለን?
12 ዓይናችን በልባችን ውስጥ መጥፎ ምኞት እንዲጫር ሊያደርግ እንደሚችልም መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቀናል። ቅብዝብዝ የሆነ ዓይን መጥፎ የፆታ ምኞት በውስጣችን እንዲቀሰቀስ ወይም እያደገ እንዲሄድ ሊያደርግ ይችላል። ኢየሱስ “አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ማቴ. 5:28) ንጉሥ ዳዊት ምን እንዳጋጠመው አትዘንጋ። ዳዊት “በሰገነቱ ላይ ሳለ . . . አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ።” (2 ሳሙ. 11:2) ዳዊት ወዲያውኑ ዘወር በማለት ትኩረቱን በሌላ ነገር ላይ ከማድረግ ይልቅ ሴትየዋን መመልከቱን ቀጠለ። ይህም የሌላን ሰው ሚስት እንዲመኝ ያደረገው ሲሆን ይህ ደግሞ ከእሷ ጋር ምንዝር ወደ መፈጸም መራው።
13. ‘ከዓይናችን ጋር ቃል ኪዳን መግባት’ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይህስ ምን ማድረግን ይጨምራል?
13 የብልግና ምኞቶችን ለማስወገድ ታማኙ ኢዮብ እንዳደረገው ‘ከዓይናችን ጋር ቃል ኪዳን መግባት’ ይኖርብናል። (ኢዮብ 31:1, 7, 9) ዓይናችንን ለመቆጣጠርና አንድን ሰው በፍትወት ስሜት ከመመልከት ለመቆጠብ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልገናል። ይህም በኮምፒውተር፣ በመጽሔት፣ በተሰቀለ ማስታወቂያ ወይም በማንኛውም ቦታ ላይ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ምስል ካጋጠመን ዞር በማለት ትኩረታችንን በሌላ ነገር ላይ ማድረግን ይጨምራል።
14. ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን እንድንኖር ከተሰጠን ምክር ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
ያዕቆብ 1:21-25ን አንብብ።
14 መጥፎ ምኞቶችን ለማስወገድ በመታገል ረገድ እስካሁን ከተመለከትናቸው ነጥቦች መካከል ይበልጥ ልትሠራባቸው የሚገቡ አቅጣጫዎች እንዳሉ ከተሰማህ ወዲያውኑ እርምጃ ውሰድ። ታዛዥ በመሆን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ አድርግ፤ ይህም መጥፎ ድርጊቶችን ለማስወገድና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናህን ጠብቀህ ለመኖር ይረዳሃል።—‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን ጥሩ’
15. ከመጥፎ ምኞቶች ጋር እየታገልን ከሆነ እርዳታ መጠየቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 መጥፎ የፆታ ምኞቶችን ለማስወገድ እየታገልን ከሆነ የእምነት ባልንጀሮቻችንም በዚህ ረገድ ሊረዱን ይችላሉ። በእርግጥ እንደዚህ ስላሉ የግል ጉዳዮች ከሌሎች ጋር ማውራት ቀላል አይደለም። ሆኖም ጉዳዩን በድፍረት ለአንድ የጎለመሰ ክርስቲያን መናገራችን በደግነት ከሚሰጠን ምክር ለመጠቀም ስለሚያስችለን መጥፎ ምኞቶችን ከማስተናገድ እንድንርቅ ይረዳናል። (ምሳሌ 18:1፤ ዕብ. 3:12, 13) ጎልማሳ ከሆነና መንፈሳዊ ብቃት ካለው ክርስቲያን ጋር ስለ ድክመቶቻችን ማውራታችን ያላስተዋልናቸውን ክፍተቶች ለመመልከት ያስችለናል። ይህም ከይሖዋ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ማስተካከያዎች ለማድረግ ይረዳናል።
16, 17. (ሀ) ሽማግሌዎች ከርኩስ ምኞቶች ጋር ለሚታገሉ ክርስቲያኖች እርዳታ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (ለ) ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ክርስቲያኖች በአፋጣኝ እርዳታ መጠየቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?
16 በተለይ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እኛን ለመርዳት ብቃት አላቸው። (ያዕቆብ 5:13-15ን አንብብ።) በብራዚል የሚኖር አንድ ወጣት መጥፎ ከሆኑ ምኞቶች ጋር ለብዙ ዓመታት ሲታገል ቆይቷል። እንዲህ ብሏል፦ “የማስበው ነገር ይሖዋን እንደሚያሳዝነው አውቅ ነበር፤ ሆኖም በልቤ ውስጥ ያለውን ነገር አውጥቼ ለሌሎች መናገር በጣም አሳፈረኝ።” ደስ የሚለው ነገር በጉባኤው ውስጥ ያለ አንድ አሳቢ ሽማግሌ ይህ ወጣት እርዳታ እንደሚያስፈልገው ስለተገነዘበ ሽማግሌዎችን እንዲያነጋግር አበረታታው። ወጣቱ እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ሽማግሌዎቹ ለእኔ ምን ያህል ደግ እንደሆኑ ሳይ ተገረምኩ፤ ይህን ያህል ደግነትና አሳቢነት ሊያሳዩኝ እንደሚገባ አልተሰማኝም። ችግሮቼን ስናገር በትኩረት አዳመጡኝ። ይሖዋ እንደሚወደኝ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ያረጋገጡልኝ ከመሆኑም ሌላ አብረውኝ ጸለዩ። ይህ ደግሞ የሰጡኝን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር መቀበል ቀላል እንዲሆንልኝ አድርጓል።” ይህ ከሆነ ዓመታት ያለፉ ሲሆን ወጣቱም ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አድርጓል፤ “ሸክማችንን ብቻችንን ከመሸከም ይልቅ የሌሎችን እርዳታ መጠየቅ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ አሁን ተገንዝቤያለሁ” ብሏል።
17 የብልግና ምኞቶች በውስጣችን የተፈጠሩት ፖርኖግራፊ የመመልከት ርኩስ ልማድ ስለተጠናወተን ከሆነ እርዳታ መጠየቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። እርዳታ ሳንጠይቅ በቆየን መጠን ርኩስ ምኞቶች በውስጣችን ‘ፀንሰው ኃጢአትን የመውለዳቸው’ አጋጣሚ ይበልጥ ሰፊ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ሌሎችን የሚጎዳ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ያመጣል። ብዙ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን ለማስደሰትና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለመኖር ያላቸው ፍላጎት የሽማግሌዎችን እርዳታ እንዲጠይቁ ብሎም የሚሰጣቸውን ፍቅራዊ እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።—ያዕ. 1:15፤ መዝ. 141:5፤ ዕብ. 12:5, 6
ንጽሕናችሁን ጠብቃችሁ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ!
18. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
18 የሰይጣን ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሥነ ምግባር እያዘቀጠ ባለበት በዚህ ወቅት ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ ሐሳባቸውን ምንጊዜም ንጹሕ ለማድረግና የእሱን ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጠብቀው ለመኖር ከልባቸው ሲጥሩ ሲመለከት እንዴት ይደሰት ይሆን! እንግዲያው ምንጊዜም ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር እንዲሁም እሱ በቃሉና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያዎች ለመቀበል ሁላችንም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖር በአሁኑ ጊዜ እርካታና የአእምሮ ሰላም ይሰጠናል። (መዝ. 119:5, 6) ወደፊት ደግሞ ሰይጣን ሲጠፋ፣ እሱ ከሚያሳድረው በካይ ተጽዕኖ በጸዳ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር መብት እናገኛለን።