በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

‘ብዙ ደሴቶች ሐሴት ያድርጉ’

‘ብዙ ደሴቶች ሐሴት ያድርጉ’

መቼም ቢሆን ያን ቀን አልረሳውም! እኔና ከተለያየ የዓለም ክፍል የመጡ የተወሰኑ ወንድሞች፣ የበላይ አካሉ ስብሰባ በሚያደርግበት ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለን እየተጠባበቅን ነው። ለጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ አባላት የምናቀርበው ሪፖርት ስላለ ጭንቅ ብሎናል። ተርጓሚዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ስናጠና ቆይተናል፤ አሁን የመፍትሔ ሐሳቦች እንድናቀርብ ይጠበቅብናል። ዕለቱ ግንቦት 22, 2000 ነው። ይህ ስብሰባ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ከመግለጼ በፊት ስላሳለፍኩት ሕይወት እስቲ ላውጋችሁ።

በኩዊንስላንድ ተጠመቅኩ፤ በታዝሜንያ አቅኚ ነበርኩ፤ በቱቫሉ፣ በሳሞኣ እና በፊጂ ደግሞ በሚስዮናዊነት አገልግያለሁ

የተወለድኩት በኩዊንስላንድ፣ አውስትራሊያ በ1955 ነው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እናቴ ኤስቴል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። እናቴ በቀጣዩ ዓመት የተጠመቀች ሲሆን ከ13 ዓመት በኋላ አባቴ ሮን ወደ እውነት መጣ። እኔ ደግሞ በ1968 በኩዊንስላንድ ግዛት፣ ሴይንት ጆርጅ በተባለ ራቅ ብሎ በሚገኝ ከተማ ተጠመቅኩ።

ከልጅነቴ ጀምሮ ማንበብ እወዳለሁ፤ ለቋንቋም ልዩ ትኩረት እሰጣለሁ። በቤተሰብ ሆነን ረዘም ያለ ጉዞ ስናደርግ መልክዓ ምድሩን ከማየት ይልቅ ከኋላ ተቀምጬ መጽሐፍ አነብ ነበር፤ ይህ ወላጆቼን ግራ አጋብቷቸው መሆን አለበት። ሆኖም የንባብ ፍቅር ያለኝ መሆኑ በትምህርት ቤት ጠቅሞኛል። በታዝሜንያ ደሴት ላይ በምትገኘው በግሌኖርኪ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስከታተል ጥሩ ውጤት በማምጣቴ ሽልማቶች አግኝቻለሁ።

ከዚያ በኋላ ግን ከባድ ውሳኔ ተደቀነብኝ፦ ‘ያገኘሁትን ነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቅሜ ዩኒቨርሲቲ ብገባ ይሻል ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። ምንም እንኳ መጻሕፍት የማንበብና የመማር ፍቅር ቢኖረኝም እናቴ ለይሖዋ የበለጠ ፍቅር እንዲኖረኝ አድርጋ ስላሳደገችኝ አመስጋኝ ነኝ። (1 ቆሮ. 3:18, 19) በመሆኑም መሠረታዊ የሆነውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዳጠናቀቅኩ ወላጆቼን አማክሬ ጥር 1971 በ15 ዓመቴ ትምህርቴን በማቆም አቅኚ ሆንኩ።

በቀጣዮቹ ስምንት ዓመታት በታዝሜንያ አቅኚ ሆኖ የማገልገል መብት አገኘሁ። በዚያ ጊዜ ውስጥ ጄኒ አልኮክ የተባለችና የታዝሜንያ ተወላጅ የሆነች ቆንጆ እህት አገባሁ፤ ከጄኒ ጋር ሆነን ርቀው በሚገኙት በስሚዝተን እና በኩዊንስታውን ለአራት ዓመታት በልዩ አቅኚነት አገልግለናል።

ወደ ፓስፊክ ደሴቶች አመራን

በ1978 ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ፖርት ሞርዝቢ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ሄድን። አንድ ሚስዮናዊ በሂሪ ሞቱ ቋንቋ የሰጠው ንግግር እስካሁን ትዝ ይለኛል። የተናገረው ነገር ፈጽሞ ባይገባኝም ንግግሩ ሚስዮናዊ ለመሆን፣ ሌላ ቋንቋ ለመማርና እንደ እሱ የመናገር ችሎታ ለማዳበር አነሳሳኝ። በመጨረሻ፣ ለይሖዋ ያለኝን ፍቅር ለቋንቋ ካለኝ ፍቅር ጋር አንድ ላይ አጣምሬ ማስኬድ የምችልበት መንገድ አገኘሁ።

ወደ አውስትራሊያ ስንመለስ በቱቫሉ (ቀደም ሲል የኤሊስ ደሴቶች ይባሉ ነበር) በሚገኘው በፉናፉቲ ደሴት ሚስዮናዊ ሆነን እንድናገለግል እንደተጋበዝን ማወቃችን አስገረመን። ጥር 1979 አዲሱ ምድብ ቦታችን ደረስን። በዚያ ጊዜ ከእኛ ሌላ በመላው ቱቫሉ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ሦስት ብቻ ነበሩ።

በቱቫሉ ከጄኒ ጋር

ቱቫሉኛ መማር ቀላል አልነበረም። በዚያ ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ “አዲስ ኪዳን” ብቻ ነበር። የቱቫሉኛ መዝገበ ቃላትም ሆነ ቋንቋውን ለመማር የሚያስችል ዝግጅት ስላልነበረ በየቀኑ ከ10 እስከ 20 አዳዲስ ቃላት ለማጥናት ወሰንን። ብዙም ሳይቆይ ግን የአብዛኞቹን ቃላት ትርጉም በትክክል እንዳልተረዳን ተገነዘብን። ለምሳሌ ያህል፣ ለሰዎች ሟርት ስህተት መሆኑን ለማስተማር ብናስብም የምንነግራቸው ግን ሚዛንና ምርኩዝ መጠቀም ትክክል እንዳልሆነ ነበር! ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያስጀመርናቸውን በርካታ ሰዎች ለመርዳት ቋንቋውን መማር ያስፈልገን ነበር። በመሆኑም ጥረት ማድረጋችንን ገፋንበት። መጀመሪያ አካባቢ መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናናቸው ሰዎች አንዷ ከዓመታት በኋላ እንዲህ አለችን፦ “አሁን ቋንቋችንን መናገር በመቻላችሁ በጣም ደስ ብሎናል። መጀመሪያ ላይ ግን ምን ለማለት እንደምትፈልጉ ጨርሶ አይገባንም ነበር!”

በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ ቋንቋ ለመማር ምቹ አጋጣሚ አግኝተናል። የሚከራይ ቤት ስላላገኘን በዋናው መንደር ውስጥ ከሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ጋር መኖር ጀመርን። እንዲህ ያለው የገጠር ሕይወት ውስጥ በመግባታችን በቤትም ሆነ በማንኛውም ቦታ ቱቫሉኛ መናገር ነበረብን። በዚህ ሁኔታ እንግሊዝኛ ሳንናገር የተወሰኑ ዓመታት በማለፋቸው ቱቫሉኛ ዋነኛ መግባቢያችን ሆነ።

ብዙም ሳይቆይ በርከት ያሉ ሰዎች ለእውነት ፍላጎት ማሳየት ጀመሩ። ይሁንና እነዚህን ሰዎች ለማስጠናት በምን መጠቀም እንችላለን? በቋንቋቸው የተዘጋጀ ምንም ጽሑፍ አልነበረንም። ደግሞስ እነዚህ ሰዎች እንዴት የግል ጥናት ማድረግ ይችላሉ? ወደ ስብሰባዎች መምጣት ሲጀምሩ ምን ይዘምራሉ? ምን ጽሑፍ ይጠቀማሉ? ለስብሰባዎች እንዴት መዘጋጀት ይችላሉ? እድገት አድርገው መጠመቅ የሚችሉትስ እንዴት ነው? በእርግጥም እነዚህ ትሑት ሰዎች በቋንቋቸው የተዘጋጀ መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልጋቸዋል! (1 ቆሮ. 14:9) ‘ከ15,000 የሚያንሱ ተናጋሪዎች ባሉት በቱቫሉኛ ጽሑፎች ይዘጋጁ ይሆን?’ ብለን እናስብ ነበር። ይሖዋ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሰጠው መልስ ሁለት ነገሮችን አረጋግጦልናል፦ (1) “ርቀው በሚገኙ ደሴቶች” እንኳ ቃሉ እንዲታወጅ ይፈልጋል፤ እንዲሁም (2) ዓለም ‘ትሑትና ዝቅ ያሉ’ እንደሆኑ አድርጎ የሚመለከታቸው ሰዎች የእሱን ስም መጠጊያቸው እንዲያደርጉ ይሻል።—ኤር. 31:10፤ ሶፎ. 3:12

መንፈሳዊ ምግብ መተርጎም

በ1980 ቅርንጫፍ ቢሮው በትርጉም ሥራ እንድንካፈል መደበን፤ እኛ ግን ይህን ሥራ ለማከናወን ፈጽሞ ብቁ እንዳልሆንን ተሰማን። (1 ቆሮ. 1:28, 29) መጀመሪያ ላይ አንድ ያረጀ የማባዣ ማሽን ከመንግሥት ገዝተን ለስብሰባዎች የሚያስፈልጉንን ጽሑፎች እናትም ነበር። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ እንኳ በቱቫሉኛ ተርጉመን በዚህ ማሽን ማተም ችለናል። ያንን ሁሉ ጽሑፍ ስናትም የነበረው ኃይለኛ የቀለም ሽታ እንዲሁም በዚያ ሞቃታማ አካባቢ የሕትመት ሥራን በእጅ ማከናወን ምን ያህል አድካሚ እንደነበር እስካሁን አይረሳኝም። በወቅቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አልነበረም!

በቱቫሉኛ የነበሩት የማመሳከሪያ ጽሑፎች በጣም ጥቂት በመሆናቸው ወደዚህ ቋንቋ መተርጎም ቀላል አልነበረም። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ካልጠበቅነው አቅጣጫ እርዳታ እናገኝ ነበር። አንድ ቀን ጠዋት፣ እውነትን የሚቃወሙ አንድ ሰው ቤት በስህተት አንኳኳሁ። በዕድሜ የገፉትና መምህር የነበሩት የቤቱ ባለቤት ቤታቸው እንድንመጣ እንደማይፈልጉ ነገሩኝ። ከዚያም እንዲህ አሉኝ፦ “ልነግራችሁ የምፈልገው አንድ ነገር አለ። በትርጉም ሥራችሁ ላይ ብዙውን ጊዜ ሐሳቡን የምትገልጹት ከተደራጊው አንጻር ነው። በአብዛኛው በቱቫሉኛ በዚህ መንገድ ሐሳባችንን አንገልጽም።” ይህን ለማረጋገጥ ሌሎችን ጠየቅኩ፤ በእርግጥም ሰውየው ትክክል ነበሩ። በመሆኑም አስፈላጊውን ማስተካከያ አደረግን። ይሖዋ፣ ተቃዋሚ በሆኑት በእኚህ ሰው አማካኝነት እርዳታ እንድናገኝ ማድረጉ አስገረመኝ፤ ሰውየው ጽሑፎቻችንን እንዳነበቡ ግልጽ ነው!

የመንግሥት ዜና ቁ. 30 በቱቫሉኛ

ለሕዝብ እንዲሰራጭ በቱቫሉኛ የተዘጋጀው የመጀመሪያው ጽሑፍ የመታሰቢያው በዓል መጋበዣ ነው። ቀጥሎም የመንግሥት ዜና ቁ. 30 ከእንግሊዝኛው እኩል ወጣ። ለሕዝቡ በቋንቋቸው የተዘጋጀ ጽሑፍ ማበርከት ምንኛ አስደሳች ነው! እያደር አንዳንድ ብሮሹሮች እንዲያውም ጥቂት መጻሕፍት በቱቫሉኛ ተዘጋጁ። በ1983 የአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ባለ 24 ገጽ መጠበቂያ ግንብ በየሦስት ወሩ ማተም ጀመረ፤ በዚህም የተነሳ በየሳምንቱ በአማካይ ሰባት አንቀጽ ማጥናት ቻልን። ሕዝቡ ምን ምላሽ ሰጠ? የቱቫሉ ሕዝብ ማንበብ ስለሚወድ ጽሑፎቻችን ተወዳጅ ሆኑ። አዲስ ጽሑፍ በወጣ ቁጥር በመንግሥት የሬዲዮ ጣቢያ ማስታወቂያ የሚነገር ሲሆን አንዳንድ ጊዜም አርዕስተ ዜና ሆኖ ይቀርባል! *

መጀመሪያ ላይ የምንተረጉመው እስክሪብቶ እና ወረቀት ተጠቅመን ነበር። ቀጥሎም በእጅ የተጻፈውን ትርጉም፣ ምንም ስህተት ሳይኖረው ለሕትመት ወደ አውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ ለመላክ የሚያስችል ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ደግመን ደጋግመን በጽሕፈት መሣሪያ እንተይበዋለን። በአንድ ወቅት ቅርንጫፍ ቢሮው ሁለት እህቶች፣ እያንዳንዱን በእጅ የተዘጋጀ ጽሑፍ ኮምፒውተር ላይ እንዲያስገቡት ያደርግ ነበር። እነዚህ እህቶች ቋንቋውን ባያውቁትም እንኳ ጽሑፉ ሁለት ጊዜ ስለገባ ይህን በማነጻጸር ልዩነቱን ማየት ይቻላል፤ እንዲህ መደረጉ ስህተቶችን በእጅጉ ለመቀነስ አስችሏል። በመጽሔት መልክ የተዘጋጀውን ጽሑፍ እንደገና እንድናየው በአየር ወደ እኛ ይላካል፤ ከዚያም ለሕትመት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው መልሰን እንልከዋለን።

አሁን አሠራሩ በጣም ተለውጧል! የትርጉም ቡድኖቹ የሚተረጉሙትን ነገር ቀጥታ ኮምፒውተር ላይ ይጽፋሉ። የተጣራው ትርጉም በአብዛኛው እዚያው ትርጉሙ በሚሠራበት ቦታ በመጽሔት መልክ ይዘጋጃል፤ ከዚያም ፋይሉ፣ ለሚያትመው ቅርንጫፍ ቢሮ በኢንተርኔት አማካኝነት ይላካል። ጽሑፉን በፖስታ ቤት በኩል ለመላክ መጣደፍ አያስፈልግም።

ሌሎች ምድቦች

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ እኔና ጄኒ በፓስፊክ አካባቢ የተለያዩ ምድቦች ተሰጡን። በ1985 ከቱቫሉ ወደ ሳሞኣ ቅርንጫፍ ቢሮ ተዛወርን። በዚያም በቱቫሉኛ ከምናከናውነው ሥራ በተጨማሪ በሳሞኣና በቶንጋ ቋንቋዎች እንዲሁም በቶኮላዋኛ በሚካሄደው የትርጉም ሥራ እገዛ እናበረክት ነበር። * ከዚያም በ1996 በፊጂ ቅርንጫፍ ቢሮ ተመሳሳይ ሥራ እንድናከናውን ተመደብን፤ በዚያም በሮቱማኛ፣ በቱቫሉኛ፣ በናውሩኛ፣ በኪሪባቲና በፊጂኛ ለሚካሄደው የትርጉም ሥራ ድጋፍ እንሰጥ ነበር።

በቱቫሉኛ ጽሑፍ ተጠቅሜ ሳስተምር

ጽሑፎቻችንን የሚተረጉሙት ክርስቲያኖች የሚያሳዩት ቅንዓት ምንጊዜም ያስገርመኛል። ሥራው አታካችና አድካሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ይሁንና እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ ምሥራቹ “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” እንዲሰበክ ያለውን ፍላጎት ይጋራሉ። (ራእይ 14:6) ለምሳሌ ያህል፣ በቶንጋ ቋንቋ መጠበቂያ ግንብ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲተረጎም ዝግጅት በተደረገ ጊዜ በቶንጋ ካሉት ከሁሉም የጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበን ነበር፤ ለትርጉም ሥራው ማን መሠልጠን እንደሚችል ጠየቅኳቸው። በሜካኒክነት ጥሩ ሥራ ያለው አንዱ ሽማግሌ ሥራውን በማግሥቱ ለቅቆ ወዲያውኑ ተርጓሚ ለመሆን ፈቃደኛ መሆኑን ገለጸ። ወንድም ራሱን በዚህ መንገድ ማቅረቡ ልብ የሚነካ ነው፤ ምክንያቱም ቤተሰብ ያለው ሲሆን ይህን እርምጃ ሲወስድ ቤተሰቡን በምን እንደሚያስተዳድር የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ያም ሆኖ ይሖዋ እሱንም ሆነ ቤተሰቡን ተንከባክቧቸዋል፤ ይህ ወንድም በትርጉም ሥራ ለበርካታ ዓመታት አገልግሏል።

እንዲህ ያለ ቅንዓት ያላቸው ተርጓሚዎች፣ ብዙ ተናጋሪ የሌላቸው ቋንቋዎች በሚነገሩበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት በጥልቅ የሚያሳስባቸውን የበላይ አካል አባላት ስሜት ያንጸባርቃሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በቱቫሉኛ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ይህን ሁሉ ጥረት ማድረጉ ዋጋ ያለው ስለ መሆኑ በአንድ ወቅት ጥያቄ ተነስቶ ነበር። የበላይ አካሉ የሰጠውን የሚከተለውን መልስ ማንበቤ በጣም አበረታትቶኛል፦ “በቱቫሉኛ የሚካሄደውን የትርጉም ሥራ ማቆም አስፈላጊ የሚሆንበት ምንም ምክንያት አይታየንም። ከሌሎች ቋንቋዎች አንጻር ቱቫሉኛ የሚናገሩት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም እነዚህ ሰዎችም ምሥራቹ በቋንቋቸው ሊደርሳቸው ይገባል።”

በሐይቅ ውስጥ የተካሄደ ጥምቀት

በ2003 እኔና ጄኒ በፊጂ ቅርንጫፍ ቢሮ ከሚገኘው የትርጉም ክፍል በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የትርጉም አገልግሎት ክፍል ተዛወርን። ምኞታችን እውን የሆነ ያህል ነበር! ጽሑፎቻችን ወደ ሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎች እንዲተረጎሙ የሚያግዘው ቡድን አባላት ሆንን። ከዚያ በኋላ ለሁለት ዓመት ገደማ ወደተለያዩ አገሮች በመሄድ የትርጉም ቡድኖችን የማሠልጠን መብት አግኝተናል።

ታሪካዊ የሆኑ ውሳኔዎች

አሁን በመግቢያዬ ላይ ወደጠቀስኩት ታሪክ ልመልሳችሁ። በ2000 የበላይ አካሉ በዓለም ዙሪያ ያሉ የትርጉም ቡድኖችን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘበ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ አብዛኞቹ ተርጓሚዎች ያን ያህል ሥልጠና አላገኙም። በዚያን ቀን ሪፖርታችንን ለጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴው ካቀረብን በኋላ የበላይ አካሉ፣ በዓለም ዙሪያ ለሁሉም ተርጓሚዎች ሥልጠና እንዲሰጥ ወሰነ። ይህም ስለ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣ ስለ አተረጓጎም ዘዴዎችና በቡድን ስለ መተርጎም ሥልጠና መስጠትን ያካትታል።

ለትርጉም ሥራ ይህን ያህል ትኩረት መሰጠቱ ምን ውጤት አስገኝቷል? አንደኛ ነገር፣ የትርጉሙ ጥራት ተሻሽሏል። ከዚህም ሌላ በአሁኑ ጊዜ ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁባቸው ቋንቋዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። በ1979 ወደ መጀመሪያው የሚስዮናዊ ምድባችን ስንሄድ መጠበቂያ ግንብ የሚዘጋጀው በ82 ቋንቋዎች ብቻ ነበር። በአብዛኞቹ ቋንቋዎችም መጽሔቱ የሚወጣው የእንግሊዝኛው መጽሔት ከወጣ ከወራት በኋላ ነበር። አሁን ግን መጠበቂያ ግንብ ከ240 በሚበልጡ ቋንቋዎች የሚሰራጭ ሲሆን አብዛኞቹ እትሞች የሚወጡት ከእንግሊዝኛው እኩል ነው። መንፈሳዊ ምግብ በአሁኑ ጊዜ በተለያየ መልኩ ከ700 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይቀርባል። ከዓመታት በፊት ይህ ሕልም መስሎ ይታየን ነበር።

በ2004 ደግሞ የበላይ አካሉ ሌላ ታሪካዊ ውሳኔ አስተላለፈ፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ከማፋጠን ጋር የተያያዘ ነው። ውሳኔው ከተላለፈ ከጥቂት ወራት በኋላ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ሌሎች ጽሑፎች በሚተረጎሙበት መንገድ እንዲከናወን ተደረገ፤ ይህም አዲስ ዓለም ትርጉም በብዙ ቋንቋዎች እንዲዘጋጅ መንገድ ከፍቷል። እስከ 2014 ባለው ጊዜ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል በ128 ቋንቋዎች ታትሟል፤ ከእነዚህ መካከል በደቡብ ፓስፊክ የሚነገሩ ቋንቋዎች ይገኙበታል።

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቱቫሉኛ መውጣቱን ስገልጽ

በሕይወቴ ውስጥ የጎላ ቦታ ከምሰጣቸው መብቶች አንዱ፣ በ2011 በቱቫሉኛ በተዘጋጀው ትልቅ ስብሰባ ላይ እንድገኝ መመደቤ ነው። በመላ አገሪቱ ለወራት የዘለቀ ከባድ ድርቅ በመከሰቱ ስብሰባው የሚሰረዝ ይመስል ነበር። ይሁንና እዚያ በደረስኩበት ምሽት ላይ ኃይለኛ ዝናብ በመጣሉ ስብሰባው መካሄድ ቻለ! በዚህ ስብሰባ ላይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቱቫሉኛ መውጣቱን የመግለጽ ተወዳዳሪ የሌለው መብት አገኘሁ፤ ከዚህ በፊት የቱቫሉ ሕዝብን ያህል ጥቂት ተናጋሪዎች ኖረውት ይህን ውብ ስጦታ ያገኘ ሌላ ሕዝብ የለም። ስብሰባው ሲያበቃ እንደገና ኃይለኛ ዝናብ ጣለ። በመሆኑም ሁሉም ሰው በመንፈሳዊ ሁኔታም ሆነ ቃል በቃል የተትረፈረፈ ውኃ ማግኘት ችሏል!

በታወንስቪል፣ አውስትራሊያ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለወላጆቼ ለሮንና ለኤስቴል ቃለ መጠይቅ ሳደርግላቸው፣ 2014

የሚያሳዝነው ግን ከ35 ለሚበልጡ ዓመታት ታማኝ የትዳር አጋሬ የነበረችው ጄኒ ይህን ታሪካዊ ክንውን መመልከት አልቻለችም። ለአሥር ዓመት ያህል በጡት ካንሰር ስትሠቃይ ቆይታ በ2009 በሞት አንቀላፋች። ጄኒ ከሞት ስትነሳ፣ በቱቫሉኛ መጽሐፍ ቅዱስ እንደወጣ መስማቷ በጣም እንደሚያስደስታት ጥርጥር የለውም።

ከዚያ ወዲህ ይሖዋ፣ ሎሬኒ ሲኪቮ የተባለች ሌላ ቆንጆ የትዳር አጋር በመስጠት ባርኮኛል። ሎሬኒ እና ጄኒ በፊጂ ቤቴል አብረው አገልግለዋል፤ ሎሬኒ የፊጂ ቋንቋ ተርጓሚ ነበረች። በመሆኑም ይሖዋን አብራኝ የምታገለግልና እንደ እኔ ለቋንቋ ፍቅር ያላት ታማኝ ሚስት እንደገና አግኝቻለሁ!

ከሎሬኒ ጋር በፊጂ ስንሰብክ

ያሳለፍኳቸውን ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ፣ በሰማይ ያለው አፍቃሪ አባታችን ይሖዋ ብዙም ሆነ ጥቂት ተናጋሪ ባሏቸው ቋንቋዎች የሚግባቡ ሰዎችን ፍላጎት ምንጊዜም የሚያሟላ መሆኑ በጣም ያበረታታኛል። (መዝ. 49:1-3) ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በቋንቋቸው አንዳንድ ጽሑፎችን ሲያገኙ ወይም ልባቸውን በሚነካው ቋንቋ ለይሖዋ ሲዘምሩ በፊታቸው ላይ የሚነበበው ደስታ የይሖዋን ፍቅር እንዳስታውስ ያደርገኛል። (ሥራ 2:8, 11) የቱቫሉ ተወላጅ የሆኑ ሳውሎ ቲአሲ የተባሉ አንድ አረጋዊ ወንድም የተናገሩት ነገር እስካሁን በጆሮዬ ያቃጭላል። የመንግሥቱን መዝሙር ለመጀመሪያ ጊዜ በቋንቋቸው ከዘመሩ በኋላ “እነዚህ መዝሙሮች ከእንግሊዝኛ ይልቅ በቱቫሉኛ ይበልጥ እንደሚጥሙ ለበላይ አካሉ አባላት ብትነግራቸው ጥሩ ነው” ብለዋል።

ከመስከረም 2005 ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ፤ ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅኩት መብት ነው። አሁን ተርጓሚ ሆኜ ማገልገል ባልችልም ይሖዋ በዓለም ዙሪያ ለሚካሄደው የትርጉም ሥራ እገዛ ማድረጌን እንድቀጥል ስለፈቀደልኝ አመስጋኝ ነኝ። ይሖዋ በፓስፊክ ውቅያኖስ መሃል ባሉት ርቀው የሚገኙ ደሴቶች የሚኖሩትን ጨምሮ ለሁሉም ሕዝቦቹ መንፈሳዊ ፍላጎት እንደሚያስብ ማወቁ ምንኛ ያስደስታል! መዝሙራዊው እንዳለው “ይሖዋ ነገሠ! ምድር ደስ ይበላት። ብዙ ደሴቶችም ሐሴት ያድርጉ” የሚለው ጥቅስ በእርግጥም እየተፈጸመ ነው።—መዝ. 97:1

^ አን.18 ለጽሑፎቻችን የተሰጠውን ምላሽ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ለማግኘት የታኅሣሥ 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 32ን፣ የነሐሴ 1, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 22ን እንዲሁም የታኅሣሥ 22, 2000 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 9ን ተመልከት።

^ አን.22 በሳሞኣ የሚካሄደውን የትርጉም ሥራ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የ2009 የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 120-121, 123-124 ተመልከት።