በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

በወጣትነቱ ባደረገው ውሳኔ ፈጽሞ አይቆጭም

በወጣትነቱ ባደረገው ውሳኔ ፈጽሞ አይቆጭም

በሕይወት ዘመኑ መገባደጃ ላይ አጎቴ (የአባቴ እናት ታላቅ ወንድም) ኒከላይ ዱበቪንስኪ የሕይወት ታሪኩን ጽፎ አዘጋጅቶ ነበር። ታሪኩ ያሳለፈውን ደስታና ጭንቀት የሚያወሳ ሲሆን በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት፣ በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ እገዳ ተጥሎ በነበረበት ወቅት ባከናወነው አገልግሎት ላይ ያተኩራል። ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ችግሮች ቢገጥሙትም ምንጊዜም ታማኝነቱን ጠብቆ ከመኖሩም ሌላ በሕይወት በመኖሩ በጣም ደስተኛ ነበር። አጎቴ ኒከላይ፣ ወጣቶች ያሳለፈውን ታሪክ እንዲሰሙ እንደሚፈልግ ብዙ ጊዜ ይናገር ስለነበረ ከሕይወት ታሪኩ ውስጥ መጠቀስ ያለባቸውን አንዳንድ ነጥቦች ብነግራችሁ ደስ ይለኛል። ኒከላይ በዩክሬን፣ በቸርኒቭትሲ ኦብላስት በምትገኝ ፐድቪሪፍከ የምትባል መንደር ውስጥ በ1926 ተወለደ፤ ቤተሰቦቹ ገበሬዎች ነበሩ።

ኒከላይ እውነትን የሰማው እንዴት ነበር?

አጎቴ ኒከላይ ታሪኩን እንዲህ በማለት ያወሳል፦ “በ1941 አንድ ቀን ታላቅ ወንድሜ ኢቫን ዘ ሃርፕ ኦቭ ጎድ እና ዘ ዲቫይን ፕላን ኦቭ ዚ ኤጅስ የተባሉትን መጻሕፍትና የተወሰኑ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን እንዲሁም በርከት ያሉ ቡክሌቶችን ወደ ቤት ይዞ መጣ። እኔም ሁሉንም አነበብኳቸው። በዓለም ላይ ላለው መከራ በሙሉ መንስኤው አምላክ ሳይሆን ዲያብሎስ መሆኑን ሳውቅ ተገረምኩ። ከጽሑፎቹ ጋር የወንጌል ዘገባዎችንም አብሬ አነበብኩ፤ በዚህ ጊዜ እውነትን እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ። ከዚያም ያወቅኩትን የመንግሥቱን ተስፋ ለሌሎች በቅንዓት መናገር ጀመርኩ። እነዚህን ጽሑፎች ሳጠና እውነት ይበልጥ እየገባኝ ስለሄደ የይሖዋ አገልጋይ ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት አደረብኝ።

“በእምነቴ የተነሳ መከራ ሊደርስብኝ እንደሚችል ተረዳሁ። በወቅቱ ጦርነት እየተካሄደ ነበር፤ እኔም በምንም ዓይነት ሰው አልገድልም ብዬ ወሰንኩ። ወደፊት ሊገጥሙኝ ለሚችሉ ፈተናዎች ራሴን ለማዘጋጀት ስል እንደ ማቴዎስ 10:28 እና 26:52 ያሉትን ጥቅሶች በቃሌ አጠናሁ። ሞት የሚያስከትልብኝ ቢሆንም እንኳ ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ!

“በ1944 አሥራ ስምንት ዓመት ስለሞላኝ ለውትድርና አገልግሎት ተጠራሁ። ከእምነት ባልንጀሮቼ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘሁት ዕድሜያቸው ለምልመላ ደርሶ የነበረ ሌሎች ወጣት ወንድሞችም ወደምዝገባ ጣቢያው መጥተው ስለነበር ነው። ለባለሥልጣናቱ በጦርነቱ እንደማንሳተፍ በግልጽ ነገርናቸው። የጦር መኮንኖቹ በጣም ከመናደዳቸው የተነሳ በረሃብ እንደሚቀጡን፣ ጉድጓድ እንደሚያስቆፍሩን ካስፈለገም እንደሚገድሉን ዛቱብን። ሁላችንም ያላንዳች ፍርሃት እንዲህ አልናቸው፦ ‘በእጃችሁ ነን። የፈለጋችሁትን ብታደርጉም “አትግደል” የሚለውን የአምላክን ሕግ አንጥስም።’—ዘፀ. 20:13

“እኔና ሌሎች ሁለት ወንድሞች ወደ ቤላሩስ ሄደን በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች እንድንጠግን ተመደብን። በሚኒስክ ከተማ ዙሪያ ያየሁት የጦርነቱ አስከፊ ገጽታ እስካሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። በመንገዱ ዳር በእሳት የተለበለቡ ዛፎች ነበሩ። በየመንገዱ የወዳደቁ አስከሬኖችና ሞተው ሰውነታቸው ያበጠ ፈረሶች በየቦዩና በጫካው ውስጥ ይታዩ ነበር። በየቦታው የተተዉ የጭነት መኪኖችና መድፎች አልፎ ተርፎም የተከሰከሰ አውሮፕላን አይቻለሁ። የአምላክን ሕግ መጣስ የሚያስከትለውን መዘዝ በገዛ ዓይኔ መመልከት ችያለሁ።

“ጦርነቱ በ1945 አበቃ፤ እኛ ግን ለመዋጋት ፈቃደኛ ባለመሆናችን የአሥር ዓመት እስራት ተፈረደብን። በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ስብሰባ አድርገንም ሆነ መንፈሳዊ ጽሑፍ አግኝተን አናውቅም። ከአንዳንድ እህቶች ጋር ደብዳቤ እንጻጻፍ የነበረ ቢሆንም እነሱም ተይዘው የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ ውስጥ የ25 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው።

“ከዚያ በኋላ ግን በ1950 እስራታችንን ከመጨረሳችን በፊት ተፈትተን ወደ ቤታችን ተመለስን። እስር ቤት እያለሁ እናቴና ታናሽ እህቴ ማሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ጠበቁኝ! ታላላቅ ወንድሞቼ ገና ያልተጠመቁ ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረው ነበር። በቅንዓት እሰብክ ስለነበረ የሶቪየት የደህንነት ቢሮ በድጋሚ ይዞ ሊያሳስረኝ ፈለገ። ከዚያም ለሥራው አመራር ይሰጡ የነበሩ ወንድሞች በድብቅ ጽሑፎች በማዘጋጀቱ ሥራ እንድረዳ ጠየቁኝ። በዚያን ጊዜ 24 ዓመቴ ነበር።”

ጽሑፎች ማዘጋጀት

“በአገሪቱ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ‘የመንግሥቱ ሥራ ከመሬት በላይ ከታገደ፣ ከመሬት በታች ይቀጥላል’ የሚል አባባል ነበራቸው። (ምሳሌ 28:28) በዚህ ጊዜ የሕትመት ሥራውን በአብዛኛው የምናከናውነው በድብቅ፣ ከመሬት በታች ነበር። የመጀመሪያው ‘ቢሮዬ’ ታላቅ ወንድሜ ዲሚትሪ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ የሚገኝ እንደ ምሽግ ያለ ክፍል ነበር። አንዳንድ ጊዜ በተከታታይ ለሁለት ሳምንታት ከዚያ ሳልወጣ እቆያለሁ። በኦክሲጅን እጥረት ምክንያት ኩራዙ ከጠፋብኝ ክፍሉ እንደገና በንጹሕ አየር እስኪሞላ ድረስ ጋደም ብዬ እጠብቃለሁ።

ኒከላይ ጽሑፎችን ያባዛበት የነበረውን ከቤት ሥር የሚገኝ እንደ ምሽግ ያለ ሰዋራ ክፍል የሚያሳይ ንድፍ

“አብሮኝ የሚሠራ አንድ ወንድም የሆነ ቀን ላይ ‘ኒከላይ ተጠምቀሃል?’ ብሎ ጠየቀኝ። ይሖዋን ለ11 ዓመታት ያገለገልኩ ብሆንም እንኳ ገና አልተጠመቅኩም ነበር። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ከተነጋገርን በኋላ ያን ዕለት ሌሊት በ26 ዓመቴ በአንድ ሐይቅ ውስጥ ተጠመቅኩ። ከሦስት ዓመት በኋላ የአገር ኮሚቴ አባል በመሆን ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጠኝ። በዚህ ጊዜ እስር ቤት ያልገቡ ወንድሞች የታሰሩትን ወንድሞች እንዲተኩ በማድረግ የመንግሥቱን ሥራ ማስቀጠል ተችሎ ነበር።”

ከመሬት በታች ሆኖ መሥራት ያለው ችግር

“ከመሬት በታች ሆኖ የሕትመት ሥራ ማከናወን ከእስር ቤት የከፋ ነበር! ኬጂቢ ተከታትሎ እንዳይዘኝ ሲባል ለሰባት ዓመታት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አልቻልኩም፤ ስለዚህ ራሴን በመንፈሳዊ መመገብ ነበረብኝ። ከቤተሰቤ ጋር የምገናኘው አልፎ አልፎ ልጠይቃቸው በምሄድበት ጊዜ ብቻ ነበር። ያም ሆኖ ሁኔታዬን የሚረዱልኝ መሆኑ አበረታቶኛል። ውጥረት የሞላበት ሕይወት መምራትና ሁልጊዜ በስጋት መኖር ኃይሌን አሟጠጠው። የመጣውን ነገር ሁሉ ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆን ነበረብን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቀን ምሽት ላይ ሁለት ፖሊሶች ወደምኖርበት ቤት መጡ። በሌላ አቅጣጫ በመስኮት በኩል ዘልዬ ወጣሁና እየሮጥኩ ጫካው ውስጥ ገባሁ። አንድ ሜዳ ላይ ስደርስ ለየት ያለ የፉጨት ድምፅ ሰማሁ። ተኩስ ስሰማ ፉጨቱ የጥይት ድምፅ እንደሆነ ገባኝ! ከሚያሳድዱኝ ሰዎች አንዱ ፈረስ ላይ ዘሎ ወጣና ጥይቱ እስኪያልቅበት ድረስ የተኩስ እሩምታ አወረደብኝ። ክንዴ ላይ በጥይት ተመታሁ። በመጨረሻም 5 ኪሎ ሜትር ያህል እየተከታተለ ካሳደደኝ በኋላ ጫካ ውስጥ ተደብቄ አመለጥኩ። ከጊዜ በኋላ ለፍርድ ስቀርብ ያን ዕለት የተኮሱብኝ 32 ጥይት እንደሆነ ሰማሁ!

“ለረጅም ጊዜ ከመሬት በታች ስለቆየሁ በጣም ገርጥቼ ነበር። ይህም ምን እንደምሠራ ሰዎች በቀላሉ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። ስለዚህ የቻልኩትን ያህል ፀሐይ ላይ እቆይ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ መኖር በጤንነቴም ላይ ያስከተለው ቀውስ አለ። በአንድ ወቅት ደም በአፍንጫዬና በአፌ ይፈስ ስለነበረ ወንድሞች በሚያደርጉት አንድ አስፈላጊ ስብሰባ ላይ መገኘት ሳልችል ቀረሁ።”

ኒከላይ ተያዘ

በሞርድቪኒያ የጉልበት ሥራ የሚሠራበት ካምፕ ውስጥ በ1963

“ጥር 26, 1957 ላይ ተያዝኩ። ከስድስት ወራት በኋላ የዩክሬን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእኔ ላይ የተላለፈውን ብይን አሳወቀ። እንድረሸን ተፈረደብኝ፤ ይሁንና በአገሪቱ ውስጥ የሞት ቅጣት ስለቀረ ፍርዱ በ25 ዓመት እስራት ተቀየረ። ስምንት የምንሆን ወንድሞች የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ ውስጥ በድምሩ 130 ዓመታት ተፈረደብን። ከዚያም በሞርድቪኒያ ወደሚገኝ ካምፕ ተላክን፤ ካምፑ ውስጥ 500 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ጥቂት ወንድሞች በቡድን በቡድን ሆነን መጠበቂያ ግንብ ለማጥናት በድብቅ እንሰበሰብ ነበር። ከጠባቂዎቹ አንዱ ከተወረሱብን መጽሔቶች አንዳንዶቹን ከመረመረ በኋላ በአድናቆት ስሜት ‘እነዚህን መጽሔቶች ማንበባችሁን ከቀጠላችሁ ምንም ነገር አይበግራችሁም!’ በማለት ተናገረ። የዕለቱን ሥራችንን በሐቀኝነት እናከናውን፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ከሚጠበቅብን በላይ እንሠራ ነበር። ያም ሆኖ የካምፑ አዛዥ ‘እዚህ የምትሠሩት ሥራ ለእኛ አይጠቅመንም። እኛ የምንፈልገው የእናንተን ታማኝነትና ድጋፍ ነው’ ሲል ምሬቱን ገለጸ።”

“የዕለቱን ሥራችንን በሐቀኝነት እናከናውን፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ከሚጠበቅብን በላይ እንሠራ ነበር”

ንጹሕ አቋሙን እስከ መጨረሻው ጠብቋል

በቪሊኪየ ሉኪ የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ

አጎቴ ኒከላይ የጉልበት ሥራ ከሚሠራበት ካምፕ በ1967 ከተፈታ በኋላ በኢስቶኒያና በሩሲያ፣ ሴንት ፒተርስበርግ ጉባኤዎችን በማደራጀቱ ሥራ እገዛ አበርክቷል። በ1991 መጀመሪያ ላይ፣ በ1957 የተላለፈው የፍርድ ቤት ብይን ተሻረ፤ ይህም የሆነው ወንጀል ለመፈጸሙ ማስረጃ ስላልተገኘ ነው። በዚያ ወቅት በባለሥልጣናቱ እጅ ከፍተኛ በደል የተፈጸመባቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ክሱ ተነሳላቸው። በ1996 ኒከላይ ከሴንት ፒተርስበርግ 500 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በስኮፍ ኦብላስት ወደምትገኘው ቪሊኪየ ሉኪ የምትባል ከተማ ተዛወረ። በዚያም አነስተኛ ቤት ገዛ፤ በኋላም በ2003 በቦታው ላይ የመንግሥት አዳራሽ ተገነባ። በዛሬው ጊዜ በአዳራሹ ውስጥ ሁለት ጠንካራ ጉባኤዎች ይሰበሰባሉ።

እኔና ባለቤቴ በሩሲያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እናገለግላለን። አጎቴ ኒከላይ ከመሞቱ ከጥቂት ወራት በፊት መጋቢት 2011 ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ሊያየን መጥቶ ነበር። በዚያን ጊዜ ኒከላይ “በአጠቃላይ አዝማሚያው ሲታይ ኢያሪኮን የምንዞርበት ሰባተኛው ቀን ጀምሯል ብዬ ለመናገር እደፍራለሁ” ብሎ ሲነግረን ዓይኑ ላይ ደስታ ይነበብ ነበር፤ ይህ አባባሉ በጥልቅ ነክቶናል። (ኢያሱ 6:15) በዚያን ጊዜ 85 ዓመቱ ነበር። አጎቴ ኒከላይ ብዙ ውጣ ውረድ ያየ ቢሆንም ያሳለፈውን ሕይወት በተመለከተ “ገና ወጣት ሳለሁ ይሖዋን ለማገልገል በመወሰኔ እጅግ ደስተኛ ነኝ! በውሳኔዬ ፈጽሞ አልቆጭም!” ብሏል።