በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትኩረታችሁ ሳይከፋፈል ይሖዋን አገልግሉ

ትኩረታችሁ ሳይከፋፈል ይሖዋን አገልግሉ

“ማርያም . . . [ኢየሱስ] የሚናገረውን ታዳምጥ ነበር። ማርታ ግን በብዙ ሥራ ተጠምዳ ትባክን ነበር።”—ሉቃስ 10:39, 40

መዝሙሮች፦ 94, 134

1, 2. ኢየሱስ ማርታን ይወዳት የነበረው ለምንድን ነው? ሆኖም ፍጹም ሰው እንዳልሆነች የሚያሳየው ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሰችው ስለ ማርታ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ኢየሱስ እንደሚወዳት በስም የተጠቀሰችው ብቸኛዋ ሴት እሷ ናት፤ እርግጥ ኢየሱስ አምላክን ለሚታዘዙ ለሌሎች ሴቶችም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ነበረው፤ ለምሳሌ ሥጋዊ እናቱን ማርያምን እንዲሁም የማርታን እህት ማርያምን ይወድዳቸው ነበር። (ዮሐ. 11:5፤ 19:25-27) ታዲያ ማርታ በወንጌል ዘገባው ውስጥ በዚህ መንገድ የተገለጸችው ለምንድን ነው?

2 ኢየሱስ ማርታን ይወዳት የነበረው እንግዳ ተቀባይና ታታሪ በመሆኗ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊነቷም ጭምር እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በኢየሱስ ትምህርቶች ከልብ የምታምን ሴት ነበረች። ማርታ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ እንደሆነ አምና በመቀበል አስደናቂ እምነት እንዳላት አሳይታለች። (ዮሐ. 11:21-27) ይሁንና እሷም እንደ ሌሎቻችን ሁሉ ፍጽምና ይጎድላታል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ በቤቷ እየተስተናገደ ሳለ ማርታ ትክክል አይደለም ብላ ያሰበችውን አንድ ሁኔታ ለማስተካከል ኢየሱስ ምን ማድረግ እንዳለበት ለመናገር ደፍራ ነበር። ማርታ “ጌታ ሆይ፣ እህቴ ሥራውን ሁሉ ለእኔ ጥላ ስትቀመጥ ምንም ግድ አይሰጥህም? መጥታ እንድታግዘኝ ንገራት እንጂ” አለችው። (ሉቃስ 10:38-42ን አንብብ።) ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ማርታ ትባክን ነበር

3, 4. ማርያም “ጥሩ የሆነውን ድርሻ” የመረጠችው በምን መንገድ ነው? ማርታ የትኛውን እርማት እንደተቀበለች ጥርጥር የለውም? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

3 ኢየሱስ፣ ማርታና ማርያም ቤታቸው በእንግድነት ስለተቀበሉት አመስጋኝነቱን ለመግለጽ መንፈሳዊ ስጦታ ሊያካፍላቸው ፈለገ። ማርያም ከታላቁ አስተማሪ እውቀት መቅሰም የምትችልበት ይህ አጋጣሚ እንዲያመልጣት ስላልፈለገች “በጌታ እግር ሥር ተቀምጣ የሚናገረውን ታዳምጥ ነበር።” ማርታም እንዲህ ማድረግ ትችል ነበር። ማርታ በትኩረት ብታዳምጠው ኖሮ ኢየሱስ ያመሰግናት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።

4 ይሁን እንጂ ማርታ፣ አቅሟ በሚፈቅደው መጠን ኢየሱስን ለማስደሰት ለየት ያለ ምግብ በማዘጋጀትና ሌሎች ሥራዎችን በማከናወን ተጠምዳ ነበር። ይህ ሁሉ ሥራ ግን አላስፈላጊ ጭንቀት ስለፈጠረባት የማርያም ሁኔታ አበሳጫት። ኢየሱስ፣ ማርታ ብዙ ነገር ለማከናወን እየጣረች እንደሆነ ስላስተዋለ በደግነት “ማርታ፣ ማርታ፣ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፤ ደግሞም ትጠበቢያለሽ” አላት። አንድ ዓይነት ምግብ ብቻ በቂ እንደሆነ ሐሳብ ሰጣት። ከዚያም ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ ማርያም ዞር በማድረግ “ማርያም በበኩሏ ጥሩ የሆነውን ድርሻ መርጣለች፤ ይህም ከእሷ አይወሰድም” በማለት ድርጊቷ እንደ ቸልተኝነት ሊታይ እንደማይገባ ተናገረ። ማርያም በዚህ ልዩ ወቅት የተመገበችውን ምግብ ብዙም ሳይቆይ ትረሳው ይሆናል፤ ይሁንና ትኩረቷ ሳይከፋፈል ኢየሱስን በማዳመጧ የተቸራትን ምስጋናም ሆነ ያገኘችውን ግሩም መንፈሳዊ ምግብ መቼም አትረሳውም። ሐዋርያው ዮሐንስ ከ60 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ “ኢየሱስ ማርታንና እህቷን . . . ይወዳቸው” እንደነበር ጽፏል። (ዮሐ. 11:5) በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ ማርታ፣ ኢየሱስ የሰጣትን ፍቅራዊ እርማት እንደተቀበለችና በቀሪው ሕይወቷ ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ጥረት እንዳደረገች በግልጽ ያሳያል።

5. የምንኖርበት ዓለም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበረው ዓለም ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

5 ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን በተመለከተ እኛ የምንኖርበት ዓለም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበረው ዓለም ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል? “በታሪክ ዘመን ውስጥ የሰው ልጅ በመገናኛ አውታሮች፣ በፈጣን የማተምያ ማሽኖች፣ ቀልብ በሚስቡ መጽሔቶች፣ በሬዲዮ፣ በፊልሞችና በቴሌቪዥን ረገድ እንደ አሁኑ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ የለም። . . . በእነዚህ አማካኝነት በየዕለቱ ትኩረታችንን የሚስቡ የተለያዩ አዳዲስ ነገሮች በገፍ ይቀርቡልናል . . . ከቅርብ ዓመታት በፊት ዘመናችን ‘የእውቀት ዘመን’ ተብሎ ሲሞገስ ነበር። ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ ‘ትኩረት የሚከፋፍል ዘመን’ እየሆነ መጥቷል።” ይህ ከ60 ዓመታት በፊት በዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙ የተወሰኑ ተማሪዎች የተነገረ ሐሳብ ነበር። የመስከረም 15, 1958 መጠበቂያ ግንብ “ይህ ዓለም ወደ ጥፋት እየቀረበ ሲመጣ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች እየጨመሩ መሄዳቸው አይቀርም” ብሏል። በእርግጥም ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል! ይህ ደግሞ የሚከተለውን ወሳኝ የሆነ ጥያቄ ያስነሳል፦ አላስፈላጊ ከሆኑ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች መራቅና እንደ ማርያም ትኩረታችንን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

በዓለም ሙሉ በሙሉ አለመጠቀም

6. የይሖዋ ሕዝቦች፣ ዓለም ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀሙ ያለው እንዴት ነው?

6 የአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል፣ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት ዓለም በሚያቀርባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች በጥሩ ሁኔታ ሲጠቀም ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ባለ ቀለም ሥዕሎች ያሉትና በድምፅ የተቀነባበረ ተንቀሳቃሽ ፊልም እንመልከት። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊትና በጦርነቱ ወቅት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ፊልም ተመልክተው ማጽናኛ አግኝተዋል፤ ፊልሙ ወደፊት ሰላም የሰፈነበት የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት እንደሚመጣ በመግለጽ ይደመደማል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በመላው ምድር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት በሬዲዮ ስርጭት አማካኝነት የመስማት አጋጣሚ ተከፍቶላቸው ነበር። በዛሬው ጊዜ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂና ኢንተርኔት ርቀው በሚገኙ ደሴቶችና በሁሉም የምድር ክፍሎች ምሥራቹን ለማዳረስ በሰፊው እየተሠራባቸው ነው።

አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮች መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችሁን እንዲያስተጓጉሉባችሁ አትፍቀዱ (አንቀጽ 7ን ተመልከት)

7. (ሀ) በዓለም ከመጠን በላይ መጠቀም አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) እኛን ይበልጥ ሊያሳስበን የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

7 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስጠነቅቀው ዓለም በሚያቀርባቸው ነገሮች ከልክ በላይ መጠቀም አደጋ አለው። (1 ቆሮንቶስ 7:29-31ን አንብብ።) አንድ ክርስቲያን በራሳቸው ስህተት ባይኖራቸውም እንደ ትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ፣ መጻሕፍትን እንደ ማንበብ፣ ቴሌቪዥን እንደ መመልከት፣ የተለያዩ ቦታዎችን እንደ መጎብኘት፣ በየሱቁ እየዞሩ ዕቃዎችን እንደ ማየትና አዳዲስ የኤሌክትሮኒክስ ወይም የቅንጦት ዕቃዎችን እንደ ማፈላለግ ባሉ እንቅስቃሴዎች ከመጠን በላይ ጊዜ ሊያጠፋ ይችላል። ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ማሰስ፣ የስልክ መልእክቶችን መለዋወጥ፣ ኢሜይሎችን መላላክና አዳዲስ ዘገባዎችን ወይም ከስፖርት ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን በየሰዓቱ መከታተል ጊዜያችንን ሊያባክንብን እንዲያውም ሱስ ሊሆንብን ይችላል። * (መክ. 3:1, 6) እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ ጉዳዮች በምናጠፋው ጊዜ ላይ፣ ገደብ ካላደረግን ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነውን ማለትም ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ ችላ ልንል እንችላለን።—ኤፌሶን 5:15-17ን አንብብ።

8. በዓለም ያሉ ነገሮችን እንዳንወድ የተሰጠን ምክር እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 ሰይጣን እሱ የሚገዛውን ዓለም ያዋቀረው የሰዎችን ትኩረት እንዲስብና እንዲከፋፍል አድርጎ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ ያለ ሁኔታ ከነበረ ዛሬማ ምን ያህል የከፋ ይሆን! (2 ጢሞ. 4:10) በመሆኑም “በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ” የሚለውን ምክር መከተል ይኖርብናል። ከዚህ ምክር ጋር ተስማምተን ለመኖር ሁልጊዜ ማስተካከያ የምናደርግ ከሆነ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን ማስወገድ የምንችል ከመሆኑም ሌላ ‘ለአብ ያለን ፍቅር’ እያደገ ይሄዳል። ይህ ደግሞ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ቀላል እንዲሆንልን ብሎም ምንጊዜም የእሱን ሞገስ እንዳናጣ ያስችለናል።—1 ዮሐ. 2:15-17

ዓይናችሁ በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ ይሁን

9. ኢየሱስ ምሳሌያዊ ዓይናችንን በተመለከተ ምን ብሏል? ምሳሌ የተወልንስ እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ ለማርታ በደግነት የሰጣት ምክር፣ ካስተማረው ትምህርትና ከተወው ምሳሌ ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል። ደቀ መዛሙርቱ ትኩረታቸው ሳይከፋፈል ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማስቀደም እንዲችሉ ምሳሌያዊ ዓይናቸው “በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ” እንዲሆን አበረታቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:22, 33ን አንብብ።) ኢየሱስ ቁሳዊ ንብረት ሸክም እንዲሆንበት አልፈቀደም፤ ቤት ወይም መሬት አልነበረውም።—ሉቃስ 9:58፤ 19:33-35

10. ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

10 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ትኩረቱን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አጋጥመውት ነበር፤ እሱ ግን ለእነዚህ ነገሮች አልተሸነፈም። በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ በቅፍርናሆም ብዙ ሕዝብ ካስተማረና ተአምር ከፈጸመ በኋላ የከተማዋ ነዋሪዎች እዚያው እንዲቆይ ለመኑት። ታዲያ ኢየሱስ ሰዎቹ ባቀረቡለት በዚህ ጥያቄ ተሸንግሎ ይሆን? በፍጹም፤ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 4:42-44) ኢየሱስ ልክ እንደተናገረው እየሰበከና እያስተማረ በመላው የፓለስቲና ምድር ተዘዋውሯል። ፍጹም ቢሆንም እንኳ እንደ ማንኛውም ሰው መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጉት ነበር፤ እንዲሁም በአምላክ አገልግሎት በትጋት በመካፈሉ በጣም የደከመው ጊዜ ነበር።—ሉቃስ 8:23፤ ዮሐ. 4:6

11. ኢየሱስ በንብረት ክፍፍል የተነሳ ከወንድሙ ጋር የተጋጨውን ሰው ምን አለው? ምን ማስጠንቀቂያስ ሰጠ?

11 በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ተከታዮቹ የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ እያስተማራቸው ሳለ አንድ ሰው በንግግሩ መሃል ጣልቃ ገብቶ “መምህር፣ ወንድሜ ውርሳችንን እንዲያካፍለኝ ንገረው” አለው። ኢየሱስ ግን እዚህ ጭቅጭቅ ውስጥ መግባት ስላልፈለገ “አንተ ሰው፣ በእናንተ መካከል ፈራጅና ዳኛ እንድሆን ማን ሾመኝ?” አለው። ከዚያም አንድ ሰው ለቁሳዊ ነገሮች ባለው ጉጉት ትኩረቱ ተሰርቆ አምላክን ከማገልገል ዞር ቢል የሚያጋጥመውን አደጋ በመግለጽ አድማጮቹን አስጠነቀቀ።—ሉቃስ 12:13-15

12, 13. (ሀ) ወደ ይሁዲነት የተለወጡ የተወሰኑ ግሪካውያን ኢየሱስን ለማግኘት የፈለጉት ለምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ትኩረቱን ሊከፋፍል ከሚችል ሁኔታ የራቀው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ ሰው ሆኖ ያሳለፈው ሕይወት የመጨረሻ ሳምንት በጣም አስጨናቂ ነበር። (ማቴ. 26:38፤ ዮሐ. 12:27) ብዙ የሚያከናውነው ሥራ ነበር፤ ደግሞም ችሎት ፊት የሚደርስበትን ውርደትና የሚጠብቀውን አሰቃቂ ሞት መጋፈጥ ነበረበት። ለምሳሌ ያህል፣ እሁድ ኒሳን 9, 33 ዓ.ም. የተፈጸመውን ነገር እንመልከት። በትንቢት በተነገረው መሠረት ኢየሱስ በውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕዝቡ “በይሖዋ ስም ንጉሥ ሆኖ የሚመጣ የተባረከ ነው!” እያለ ያወድሰው ጀመር። (ሉቃስ 19:38) በሚቀጥለው ቀን ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ወገኖቻቸው ከሆኑት አይሁዳውያን ላይ ያላግባብ ገንዘብ ለማግኘት በአምላክ ቤት ውስጥ ይነግዱ የነበሩትን ስግብግብ ሰዎች በድፍረት አባረረ።—ሉቃስ 19:45, 46

13 በኢየሩሳሌም ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ወደ ይሁዲነት የተለወጡ አንዳንድ ግሪካውያን ኢየሱስ ባደረገው ነገር በጣም ተደንቀው እንደነበር መገመት እንችላለን፤ ምክንያቱም ከኢየሱስ ጋር እንዲያገናኛቸው ሐዋርያው ፊልጶስን ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስ ግን ከፊቱ ከሚጠብቀው ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ትኩረቱ እንዲሰረቅ አልፈለገም። በአምላክ ጠላቶች እጅ መሥዋዕታዊ ሞት ላለመሞት ሲል በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነት ለማትረፍ አልሞከረም። በመሆኑም በቅርቡ እንደሚገደል ከገለጸ በኋላ እንድርያስንና ፊልጶስን እንዲህ አላቸው፦ “ሕይወቱን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ሁሉ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።” ኢየሱስ የእነዚህን ግሪካውያን ስሜት ከማስተናገድ ይልቅ እሱ ያሳየውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማንጸባረቅ የተሻለ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ “የሚያገለግለኝንም ሁሉ አብ ያከብረዋል” በማለት ቃል ገብቷል። ፊልጶስ ይህን አበረታች መልእክት ሄዶ ለግሪካውያኑ እንደነገራቸው ምንም ጥርጥር የለውም።—ዮሐ. 12:20-26

14. ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ለስብከቱ ሥራ ቢሆንም ሚዛናዊ ሰው እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?

14 ምንም እንኳ ኢየሱስ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በስብከቱ ሥራ ላይ ያደረገ ቢሆንም ሁልጊዜ ስለ ሥራ ብቻ ያስብ ነበር ማለት አይደለም። ቢያንስ በአንድ የሠርግ ግብዣ ላይ የተገኘ ሲሆን በዚያም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥ ለግብዣው መሳካት አስተዋጽኦ አድርጓል። (ዮሐ. 2:2, 6-10) በተጨማሪም የቅርብ ወዳጆቹም ሆኑ ለምሥራቹ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ያቀረቡለትን የራት ግብዣ ተቀብሏል። (ሉቃስ 5:29፤ ዮሐ. 12:2) ከሁሉም በላይ ግን ኢየሱስ ለመጸለይ፣ ብቻውን ሆኖ ለማሰላሰልና ለእረፍት ጊዜ ይዋጅ ነበር።—ማቴ. 14:23፤ ማር. 1:35፤ 6:31, 32

‘ማንኛውንም ሸክም ከላያችን አንስተን እንጣል’

15. ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ምክር ሰጥቷል? ግሩም ምሳሌ የተወውስ እንዴት ነው?

15 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች የሚከተሉትን የሕይወት መንገድ ጽናት ከሚጠይቅ የሩጫ ውድድር ጋር በማመሳሰል ‘ማንኛውንም ሸክም ከላያችን አንስተን እንጣል’ ሲል ጽፏል። (ዕብራውያን 12:1ን አንብብ።) ጳውሎስ በአይሁድ እምነት ውስጥ ሀብትና ዝና የሚያስገኝለትን ትልቅ ቦታ በመተው ከሚሰብከው መልእክት ጋር የሚስማማ ነገር አድርጓል። ‘ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች’ ላይ ትኩረት ያደረገ ከመሆኑም በላይ ወደ ሶርያ፣ ትንሿ እስያ፣ መቄዶንያና ይሁዳ ብዙ ጊዜ በመሄድ አምላክን በትጋት አገልግሏል። ጳውሎስ የሚያገኘውን ዘላለማዊ ሕይወት አስመልክቶ “ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ፤ . . . የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት አገኝ ዘንድ ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው” በማለት ጽፏል። (ፊልጵ. 1:10፤ 3:8, 13, 14) ነጠላ መሆኑ ባስገኘለት አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ‘ሐሳቡ ሳይከፋፈል ዘወትር ለጌታ ያደረ’ መሆን ችሏል።—1 ቆሮ. 7:32-35

16, 17. ያገባንም ሆንን ያላገባን ክርስቲያኖች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነው ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ተሞክሮ ተናገር።

16 እንደ ጳውሎስ ሁሉ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮችም ነጠላ ሆነው ለመኖር ወስነዋል፤ ይህ ደግሞ የቤተሰብ ኃላፊነት እንዳይበዛባቸው ስለሚያደርግ የመንግሥቱን አገልግሎት በቅንዓት ለማከናወን አስችሏቸዋል። (ማቴ. 19:11, 12) አብዛኛውን ጊዜ ያገቡ ክርስቲያኖች ብዙ የቤተሰብ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። ይሁንና ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ክርስቲያኖች ‘ማንኛውንም ሸክም አንስተው በመጣል’ ብዙ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ሳይኖሩባቸው አምላክን ማገልገል ይችላሉ። ይህ ደግሞ ጊዜ የሚያባክኑ ልማዶችን ማስወገድና በአምላክ አገልግሎት የሚያሳልፉትን ጊዜ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ግብ ማውጣት ይጠይቅባቸው ይሆናል።

17 የዌልስ ተወላጅ የሆኑት ማርክና ክሌር የተባሉ ባልና ሚስት ያደረጉትን እንመልከት፤ ሁለቱም ትምህርት እንደጨረሱ አቅኚ የሆኑ ሲሆን ከተጋቡ በኋላም በአቅኚነት ቀጥለዋል። ማርክ እንዲህ ብሏል፦ “በዓለም አቀፍ የግንባታ ሥራ መካፈል እንድንችል ሦስት የመኝታ ክፍሎች ያለውን ቤታችንን በመሸጥና የግማሽ ቀን ሥራችንን በማቆም ኑሯችንን ቀላል አደረግን።” ባለፉት 20 ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ወደተለያዩ አገሮች በመጓዝ ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራ ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል። በአንድ ወቅት የነበራቸው ገንዘብ ተሟጦ 15 ዶላር ብቻ ቀርቷቸው ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ተንከባክቧቸዋል። ክሌር እንዲህ ብላለች፦ “በየዕለቱ ይሖዋን በማገልገል የምናሳልፈው ጊዜ ከፍተኛ ደስታ ይሰጠናል። በሄድንበት ቦታ ሁሉ ብዙ ወዳጆችን አፍርተናል፤ ያጣነው ምንም ነገር የለም። ይሖዋን በሙሉ ጊዜ በማገልገል ከምናገኘው ደስታ ጋር ሲወዳደር እኛ የከፈልነው መሥዋዕት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።” በርካታ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ተመሳሳይ ተሞክሮ አላቸው። *

18. አንዳንዶች የትኞቹን ጥያቄዎች ሊያስቡባቸው ይገባል?

18 የአንተ ሁኔታስ እንዴት ነው? በሕይወትህ ውስጥ ባጋጠሙህ ትኩረት የሚከፋፍሉ አላስፈላጊ ነገሮች የተነሳ የመንግሥቱን ጉዳዮች እንደቀድሞው በቅንዓት እያከናወንክ እንዳልሆነ ካስተዋልክ ምን ማድረግ ትችላለህ? የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህንና ጥናትህን ይበልጥ ትርጉም ያለው በማድረግ ለዚህ ችግር መፍትሔ ልታገኝ ትችላለህ። ታዲያ እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።

^ አን.7ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.17ትክክል የሆነውን ማወቅና መፈጸም” በሚል ርዕስ የወጣውን የሃደን እና የሜሎዲ ሳንደርሰንን የሕይወት ታሪክ ተመልከት። (መጋቢት 1, 2006 መጠበቂያ ግንብ) እነዚህ ባልና ሚስት ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ለመግባት ሲሉ በአውስትራሊያ የነበራቸውን አትራፊ ንግድ ሸጠዋል። በሕንድ ሚስዮናዊ ሆነው ሲያገለግሉ የገንዘብ ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ ይህን ችግር እንዴት እንደተወጡት ማንበብ ትችላለህ።