በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘወትር በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ አሰላስሉ

ዘወትር በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ አሰላስሉ

“እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።”—1 ጢሞ. 4:15

መዝሙሮች፦ 57, 52

1, 2. የሰው አእምሮ በዓይነቱ ልዩ የሆነባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ቋንቋ የሰው ልጆች የማንበብ፣ የመጻፍ፣ የመናገር፣ ሌሎች የሚናገሩትን የመረዳት፣ የመጸለይና ይሖዋን በመዝሙር የማወደስ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጓል። እነዚህ አስገራሚ ነገሮች የሚከናወኑት በተወሰኑ የአንጎላችን ክፍሎችና የነርቭ ሥርዓቶች ውስጥ ነው፤ የሳይንስ ሊቃውንት እነዚህ ነገሮች እንዴት እንደሚሠሩ እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ አልደረሱበትም። አንጎላችን ለሰው ልጆች የተሰጠ ልዩ ስጦታ በመሆኑ ቋንቋ መማር እንችላለን። አንድ የቋንቋ ፕሮፌሰር “ልጆች ያላቸው ቋንቋ የመማር ችሎታ፣ ሰዎችን ልዩ ከሚያደርጓቸው ነገሮች አንዱ ነው” ብለዋል።

2 የሰዎች ቋንቋ የመማር ችሎታ ከአምላክ የተገኘ ተአምራዊ ስጦታ ነው። (መዝ. 139:14፤ ራእይ 4:11) አምላክ የሰጠን አእምሮ ከሌላም አቅጣጫ ሲታይ በጣም ጠቃሚ የሆነ ስጦታ ነው። ከእንስሳት በተለየ ሰዎች የተፈጠሩት “በአምላክ መልክ” ነው። ሰዎች ነፃ ምርጫ ስላላቸው የቋንቋ ችሎታቸውን ተጠቅመው አምላክን ማወደስ ይችላሉ።—ዘፍ. 1:27

3. ይሖዋ ጥበበኛ እንድንሆን የሚያስችለን ምን ግሩም ስጦታ ሰጥቶናል?

3 ቋንቋን የፈጠረው አምላክ እሱን ማክበር ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ግሩም የሆነ ስጦታ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በከፊልም ሆነ በሙሉ ከ2,800 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ ስታነብ የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖርሃል። (መዝ. 40:5፤ 92:5፤ 139:17) በዚህ መንገድ “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ” በሚያስችሉህ ነገሮች ላይ ማሰላሰል ትችላለህ።—2 ጢሞቴዎስ 3:14-17ን አንብብ።

4. ማሰላሰል ሲባል ምን ማለት ነው? ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?

4 ማሰላሰል ሲባል አእምሮ በአንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይኸውም በአንድ ጉዳይ ላይ (ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን ይችላል) ማውጠንጠን ወይም በተመስጦ ማሰብ ማለት ነው። (መዝ. 77:12፤ ምሳሌ 24:1, 2) ከምንም ነገር በላይ የሚጠቅመን ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማሰላሰል ነው። (ዮሐ. 17:3) ይሁንና ‘በማንበብና በማሰላሰል መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል። ማሰላሰል የምንችልባቸው ምን ሌሎች ነገሮች አሉ? እንዲሁም ማሰላሰል አስደሳች ሊሆንልን የሚችለው እንዴት ነው?

ከጥናታችሁ ጥሩ ጥቅም ለማግኘት ጥረት አድርጉ

5, 6. አንድ ጽሑፍ ስታነብ ያነበብከውን ነገር በተሻለ ሁኔታ መረዳትና ማስታወስ እንድትችል የሚረዳህ ምንድን ነው?

5 አእምሯችን አስገራሚ የሆኑ ነገሮችን ማከናወን ይችላል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ነገሮች የሚከናወኑት እኛ ምንም ጥረት ሳናደርግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ መተንፈስ፣ መራመድ፣ ብስክሌት መንዳት ወይም ታይፕ ማድረግ በደመነፍስ ልናከናውናቸው የምንችላቸው ነገሮች ናቸው። በተወሰነ መጠንም ቢሆን ይህ ከማንበብ ጋር በተያያዘ ይሠራል። በመሆኑም የምታነበው ነገር ምን ትርጉም እንዳለው ትኩረት መስጠትህ አስፈላጊ ነው። አንድ ጽሑፍ እያነበብክ ሳለ አንድ አንቀጽ መጨረሻ ወይም ንዑስ ርዕስ ላይ ስትደርስ ያነበብከው ነገር በትክክል ገብቶህ እንደሆነ ለማረጋገጥ ቆም ብለህ አሰላስል። እርግጥ ነው፣ የሚረብሹ ነገሮች ካጋጠሙህና ትኩረትህን መሰብሰብ ካቃተህ አእምሮህ ስለሚባዝን ከምታነበው ነገር ጥቅም ሳታገኝ ትቀራለህ። ታዲያ ይህን ማስወገድ የምትችለው እንዴት ነው?

6 ጮክ ብሎ ማንበብ ያነበቡትን ነገር በቀላሉ ለማስታወስ እንደሚረዳ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች አረጋግጠዋል። አእምሯችንን የፈጠረው አምላክ ደግሞ ይህን ያውቃል። በመሆኑም ኢያሱን የሕጉን መጽሐፍ “በለሆሳስ አንብበው” በማለት አዞታል። (ኢያሱ 1:8ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስን ዝቅ ባለ ድምፅ ወይም በለሆሳስ ማንበብ የምታነበው ነገር አእምሮህ ላይ በሚገባ እንዲቀረጽ ያደርጋል። ይህም በተሻለ ሁኔታ አእምሮህን መሰብሰብ እንድትችል ይረዳሃል።

7. በአምላክ ቃል ላይ ለማሰላሰል ይበልጥ አመቺ የሆነው ጊዜ መቼ ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

7 ማንበብ ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ባይሆንም ማሰላሰል ግን ትኩረትን ማሰባሰብ ይጠይቃል። ፍጽምና የሚጎድለው የሰው አእምሮ ብዙ ማሰብ በማይጠይቁና እምብዛም አድካሚ ባልሆኑ ሥራዎች በቀላሉ የመወሰድ አዝማሚያ ያለው ከዚህ የተነሳ ነው። በመሆኑም ለማሰላሰል ይበልጥ አመቺ የሆነው ጊዜ ዘና የምትልበት እንዲሁም ትኩረትህን የሚሰርቁና የሚያስጨንቁ ነገሮች የሌሉበት ወቅት ነው። መዝሙራዊው ሌሊት ከእንቅልፉ የሚነቃበት ጊዜ ለማሰላሰል ጥሩ ሰዓት እንደሆነ ተረድቷል። (መዝ. 63:6) ፍጹም አእምሮ የነበረው ኢየሱስ ጸጥ ባለ ቦታ ማሰላሰልና መጸለይ ምን ያህል ጥቅም እንዳለው ተገንዝቦ ነበር።—ሉቃስ 6:12

ልናሰላስልባቸው የሚገቡ መልካም ነገሮች

8. (ሀ) ከአምላክ ቃል ሌላ በምን ላይ ማሰላሰል እንችላለን? (ለ) ይሖዋ እርስ በርሳችን ስለ እሱ ስንነጋገር ምን ይሰማዋል?

8 ከመጽሐፍ ቅዱስ ባነበብከው ነገር ላይ ቆም ብለህ ማሰብህ ማሰላሰል የምትችልበት አንድ መንገድ ነው፤ ይሁንና ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ አስደናቂ የሆኑ የፍጥረት ሥራዎችን ስትመለከት ቆም ብለህ አስብ። እንዲህ ማድረግህ ይሖዋን ስለ ጥሩነቱ ለማወደስና ሌላ ሰው አብሮህ ካለ ደግሞ አድናቆትህን ለመግለጽ እንደሚያነሳሳህ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 104:24፤ ሥራ 14:17) ይሖዋ ስለ እሱ ስናሰላስልና እርስ በርስ ስንነጋገር ብሎም ወደ እሱ ስንጸልይ በትኩረት ይከታተላል፤ እንዲሁም ደስ ይለዋል። ቃሉ የሚከተለውን ማረጋገጫ ይሰጠናል፦ “በዚያ ጊዜ ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው፣ ከየባልንጀሮቻቸው ጋር ተነጋገሩ፤ ይሖዋም በትኩረት አዳመጠ፤ ደግሞም ሰማ። ይሖዋንም ለሚፈሩና በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።”—ሚል. 3:16

መጽሐፍ ቅዱስ የምታስተምራቸው ሰዎች ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮችና ስላሉበት ሁኔታ ቆም ብለህ ታሰላስላለህ? (አንቀጽ 9ን ተመልከት)

9. (ሀ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በየትኞቹ ነገሮች ላይ እንዲያሰላስል ነግሮታል? (ለ) ለአገልግሎት ስንዘጋጅ የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ንግግሩ፣ አኗኗሩና የሚያስተምረው ትምህርት በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ‘እንዲያሰላስል’ ነግሮት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 4:12-16ን አንብብ።) እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እኛም ልናሰላስልባቸው የሚገቡ በርካታ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አሉ። ለምሳሌ አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ስንዘጋጅ የምናሰላስልበት ጊዜ ያስፈልገናል። እያንዳንዱን ተማሪ በአእምሯችን በመያዝ የምንዘጋጅ ከሆነ ተማሪው እድገት እንዲያደርግ ለመርዳት ምን ዓይነት የአመለካከት ጥያቄ ብንጠይቀው ወይም የትኛውን ምሳሌ ብንጠቀም የተሻለ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። እንዲህ በማድረግ የምናሳልፈው ጊዜ አስደሳች ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም በእነዚህ ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን የእኛን እምነት ያጠናክራል፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችንን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድና በቅንዓት ለማስጠናት ያስችለናል። ወደ መስክ አገልግሎት ለመውጣት ልባችንን በምናዘጋጅበት ጊዜም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። (ዕዝራ 7:10ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ አንድ ምዕራፍ ማንበባችን ለአገልግሎት ያለን ‘ቅንዓት’ እንዲቀጣጠል ያደርጋል። በዚያን ዕለት ልንጠቀምበት ባሰብነው ጥቅስና ጽሑፍ ላይ ማሰላሰላችን አገልግሎታችንን በቅንዓት እንድናከናውን ይረዳናል። (2 ጢሞ. 1:6) በክልልህ ስላሉ ሰዎችና ፍላጎታቸውን ለመቀስቀስ ማድረግ ስለምትችለው ነገር አስብ። እንዲህ ያለ ዝግጅት ማድረጋችን ከአምላክ ቃል በሚገኘው “መንፈስና ኃይል” ተጠቅመን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንሰብክ ያነሳሳናል።—1 ቆሮ. 2:4

10. በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ምን ተጨማሪ አጋጣሚዎች አሉን?

10 በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ንግግር ሲሰጥ ማስታወሻ ትይዛለህ? የያዝከውን ማስታወሻ መከለስህ ከአምላክ ቃልም ሆነ ከድርጅቱ በተማርካቸው ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልሃል። በተጨማሪም በየወሩ የሚወጡት የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትሞች እንዲሁም በክልል ስብሰባ ላይ የሚወጡ አዳዲስ ጽሑፎች የምናነባቸውና የምናሰላስልባቸው መረጃዎች ይዘዋል። የዓመት መጽሐፍ በምታነብበት ጊዜ አንድ ተሞክሮ ጨርሰህ ወደ ሌላ ከመሸጋገርህ በፊት ቆም ብለህ ማሰብህ ጠቃሚ ነው። ይህ ደግሞ ባነበብከው ተሞክሮ ላይ እንድታሰላስልና ልብህ እንዲነካ አጋጣሚ ይሰጥሃል። ተመላልሶ መጠየቅ ወይም የእረኝነት ጉብኝት ለማድረግ አሊያም ንግግር ለመስጠት በምትዘጋጅበት ጊዜ ቁልፍ በሆኑ ሐሳቦች ላይ ማስመርህ ወይም በኅዳጉ ላይ ማስታወሻ መያዝህ ይጠቅምሃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ስታነብ አልፎ አልፎ ቆም እያልክ ማሰላሰልህ ትምህርቱ ወደ ልብህ ዘልቆ እንዲገባና ለተማርከው መልካም ነገር ይሖዋን በጸሎት እንድታመሰግን አጋጣሚ ይሰጥሃል።

በየዕለቱ በአምላክ ቃል ላይ አሰላስሉ

11. በዋነኝነት ልናሰላስልበት የሚገባው ጽሑፍ ምን መሆን አለበት? ለምንስ? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

11 እርግጥ ነው፣ ልናሰላስልባቸው ከሚገቡ ጽሑፎች ዋነኛው በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ነው። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት የማትችልበት ሁኔታ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። * በዚህ ጊዜም ቢሆን ቀደም ሲል በአእምሮህ ባከማቸኸው እውቀት ላይ ማለትም በምትወዳቸው ጥቅሶች ወይም የመዝሙር ስንኞች ላይ እንዳታሰላስል ሊያግድህ የሚችል ሰው የለም። (ሥራ 16:25) ደግሞም የአምላክ መንፈስ ከዚህ በፊት የተማርካቸውን መልካም ነገሮች እንድታስታውስ ሊረዳህ ይችላል።—ዮሐ. 14:26

12. የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን በየትኞቹ መንገዶች ማከናወን እንችላለን?

12 ከሳምንቱ ቀናት መካከል የተወሰኑትን በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ የሚወጣውን የሳምንቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለማንበብና ለማሰላሰል ማዋል ይቻላል። በሌሎች ቀናት ደግሞ ኢየሱስ በተናገረውና ባደረገው ነገር ላይ ማሰላሰል እንችላለን። ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጹት የወንጌል ዘገባዎች በሰፊው ከሚታወቁት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል እንደሚገኙ ግልጽ ነው። (ሮም 10:17፤ ዕብ. 12:2፤ 1 ጴጥ. 2:21) እንዲያውም የአምላክ ሕዝቦች፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን ሕይወት በጊዜ ቅደም ተከተል የሚያቀርብ ጽሑፍ አግኝተዋል። በእያንዳንዱ የመጽሐፉ ምዕራፍ ላይ የቀረቡትን ተዛማጅ የወንጌል ዘገባዎች በጥሞና ማንበባችንና በዚያ ላይ ማሰላሰላችን በጣም ይጠቅመናል።—ዮሐ. 14:6

ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13, 14. ዘወትር በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

13 በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማሰላሰል አንድ ሰው ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና እንዲደርስ ይረዳዋል። (ዕብ. 5:14፤ 6:1) ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ለማሰላሰል በቂ ጊዜ የማይሰጥ ሰው ጠንካራ እምነት ሊኖረው አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ቀስ በቀስ የመወሰድ ወይም ከእውነት የመራቅ አደጋ ተደቅኖበታል። (ዕብ. 2:1፤ 3:12) ኢየሱስ የአምላክን ቃል “በመልካምና በጥሩ ልብ” የማንሰማ ወይም የማንቀበል ከሆነ ቃሉን ‘በውስጣችን ማኖር’ እንደማንችል ተናግሯል። ከዚህ ይልቅ ‘የዚህ ዓለም የኑሮ ጭንቀት፣ ሀብትና ሥጋዊ ደስታ ትኩረታችንን ሊከፋፍልብንና ለፍሬ እንዳንበቃ’ ሊያደርገን ይችላል።—ሉቃስ 8:14, 15

14 በመሆኑም በአምላክ ቃል ላይ ዘወትር እናሰላስል። ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸውን የይሖዋን ክብርና ባሕርይ ለማንጸባረቅ ያነሳሳናል። (2 ቆሮ. 3:18) ደግሞስ ከዚህ የበለጠ ምን እንፈልጋለን? በአምላክ እውቀት ማደግና የእሱን ክብር ማንጸባረቅ መቻል ግሩም መብት ከመሆኑም ሌላ በሰማይ የሚኖረውን አፍቃሪ አባታችንን እንዴት መምሰል እንደምንችል በተማርን መጠን ክብሩን ማንጸባረቃችንን እንቀጥላለን።—መክ. 3:11

15, 16. (ሀ) በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማሰላሰል በግለሰብ ደረጃ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? (ለ) አንዳንድ ጊዜ ማሰላሰል አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሆኖም ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

15 ሁልጊዜ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ ለእውነት ያለንን ቅንዓት ይዘን መቀጠል እንችላለን። በዚህ መንገድ ለወንድሞቻችንም ሆነ በመስክ አገልግሎት ለምናገኛቸው ሰዎች የእረፍት ምንጭ እንሆናለን። አምላክ በሰጠን ታላቅ ስጦታ ላይ ማለትም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ማሰላሰላችን ቅዱስ ከሆነው አባታችን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን የጠበቀ ዝምድና ከፍ አድርገን እንድንመለከት ይረዳናል። (ሮም 3:24፤ ያዕ. 4:8) ማርክ የተባለ በደቡብ አፍሪካ የሚኖርና በክርስቲያናዊ ገለልተኛ አቋሙ የተነሳ ለሦስት ዓመት ታስሮ የነበረ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ማሰላሰል በጣም ከሚያስደስት ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ይበልጥ ባሰላሰልን መጠን ስለ አምላካችን ስለ ይሖዋ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን እያወቅን እንሄዳለን። አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ስቆርጥ ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስጨነቅ መጽሐፍ ቅዱሴን አውጥቼ አነባለሁ፤ ከዚያም በጥቅሶቹ ላይ አሰላስላለሁ። በዚህ ጊዜ ውስጤ ይረጋጋል።”

16 እውነት ነው፣ ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ትኩረት የሚከፋፍሉ ብዙ ነገሮች ስላሉ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ማሰላሰል አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። ፓትሪክ የተባለ በአፍሪካ የሚኖር ሌላ ታማኝ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አእምሮዬ፣ የሚፈለጉም ሆነ የማይፈለጉ ብዙ ደብዳቤዎች እንደሞሉበት የፖስታ ሣጥን ነው፤ ይህ ደግሞ የሚፈለገውንና የማይፈለገውን በየዕለቱ መለየት ይጠይቃል። በአእምሮዬ ውስጥ ያለውን ነገር ስመረምር ብዙ ጊዜ ‘እረፍት የሚነሱ ሐሳቦች በውስጤ’ አገኛለሁ፤ በንጹሕ አእምሮ ማሰላሰል እንድችል በቅድሚያ ስለ እነዚህ ነገሮች ወደ ይሖዋ መጸለይ ያስፈልገኛል። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማሰላሰል ከመጀመሬ በፊት እንዲህ ማድረጌ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ የሚችል ቢሆንም ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንደቀረብኩ እንዲሰማኝ ያደርጋል። ይህ ደግሞ እውነትን በተሻለ መንገድ እንድረዳ አእምሮዬን ይከፍትልኛል።” (መዝ. 94:19 የግርጌ ማስታወሻ) በእርግጥም ‘በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን የሚመረምሩ’ እና በተማሩት ነገር ላይ የሚያሰላስሉ ሁሉ በርካታ ጥቅሞችን ያገኛሉ።—ሥራ 17:11

ለማሰላሰል ጊዜ ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው?

17. ለማሰላሰል ጊዜ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

17 አንዳንዶች ለማንበብ፣ ለማሰላሰልና ለመጸለይ በማለዳ ይነሳሉ። ሌሎች በምሳ እረፍታቸው ወቅት እንዲህ ያደርጋሉ። አንተ ደግሞ አመሻሹ ላይ ወይም ከመተኛትህ በፊት ታሰላስል ይሆናል። አንዳንዶች ጠዋት እንዲሁም ማታ ከመተኛታቸው በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ያነብባሉ። በመሆኑም “ቀንም ሆነ ሌሊት” በሌላ አባባል አዘውትረው የአምላክን ቃል ‘ያነብባሉ’ ሊባል ይችላል። (ኢያሱ 1:8) ዋናው ቁም ነገር፣ በአምላክ ቃል ላይ ለማሰላሰል እምብዛም አስፈላጊ ካልሆኑ ነገሮች ላይ ጊዜ መግዛት መቻላችን ነው።—ኤፌ. 5:15, 16

18. መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ ቃል ላይ በየዕለቱ የሚያሰላስሉና የተማሩትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች ስለሚያገኙት በረከት ምን ይላል?

18 መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ ቃል ላይ የሚያሰላስሉና የተማሩትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች በረከት እንደሚያገኙ ደጋግሞ ይናገራል። (መዝሙር 1:1-3ን አንብብ።) ኢየሱስ “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 11:28) ከሁሉም በላይ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ በየዕለቱ ማሰላሰላችን አእምሯችንን ድንቅ አድርጎ ለፈጠረው አምላክ ክብር ያመጣል፤ እሱም በአሁኑ ጊዜ ደስተኛ እንድንሆን ያደርገናል፤ ወደፊት ደግሞ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርከናል።—ያዕ. 1:25፤ ራእይ 1:3

^ አን.11 በታኅሣሥ 1, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን ለመቀጠል ያደረግነው ትግል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።