ለይሖዋ ለጋስነት አድናቆት አሳዩ
ይሖዋ ለጋስ አምላክ ነው። (ያዕ. 1:17) በምሽት ጨለማ በከዋክብት ተሞልተው የሚታዩት ሰማያትም ሆኑ ምድርን የሸፈናት ልምላሜ እንዲሁም ሌሎቹ የይሖዋ ፍጥረታት በአጠቃላይ የእሱን ልግስና ያንጸባርቃሉ።—መዝ. 65:12, 13፤ 147:7, 8፤ 148:3, 4
መዝሙራዊው ለፈጣሪው የነበረው አድናቆት እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ የይሖዋን ሥራዎች የሚያወድስ መዝሙር ለማቀናበር ተገፋፍቷል። አንተም 104ኛውን መዝሙር ስታነብ የመዝሙራዊውን ስሜት እንደምትጋራ ምንም ጥርጥር የለውም። መዝሙራዊው “በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ለይሖዋ እዘምራለሁ፤ በሕይወት እስካለሁ ድረስ ለአምላኬ የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ” ብሏል። (መዝ. 104:33) የአንተስ ምኞት ይህ ነው?
ከሁሉ የላቀ የልግስና ምሳሌ
ይሖዋ በልግስና ረገድ የእሱን ምሳሌ እንድንከተል ይፈልጋል። እንዲሁም ለጋስ ለመሆን የሚያነሳሱን አጥጋቢ ምክንያቶች ሰጥቶናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ መሪነት ያሰፈረውን ሐሳብ ልብ በል፦ “አሁን ባለው ሥርዓት ሀብታም የሆኑትን ሰዎች እንዳይታበዩ እንዲሁም ተስፋቸውን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን የሚያስደስቱንን ነገሮች ሁሉ አትረፍርፎ በሚሰጠን አምላክ ላይ እንዲጥሉ እዘዛቸው። በተጨማሪም መልካም ነገር እንዲያደርጉ፣ በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ እንዲሆኑ እንዲሁም ለጋሶችና ለሌሎች ለማካፈል ፈቃደኞች እንዲሆኑ ምከራቸው፤ እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀው መያዝ ይችሉ ዘንድ ለራሳቸው ውድ ሀብት ማከማቸታቸውን ይኸውም ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን መልካም መሠረት መጣላቸውን ይቀጥሉ።”—1 ጢሞ. 6:17-19
ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኘው ጉባኤ በመንፈስ መሪነት ሁለተኛውን ደብዳቤ በጻፈ ጊዜ ልግስናን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባውን ትክክለኛ አመለካከት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ጳውሎስ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ” ብሏል። (2 ቆሮ. 9:7) ጳውሎስ ቀጥሎም ልግስና እነማንን እንደሚጠቅም ገልጿል፤ ስጦታውን የሚቀበሉት ሰዎች የጎደላቸው ነገር ይሟላላቸዋል፤ ሰጪዎቹ ደግሞ መንፈሳዊ በረከት ያገኛሉ።—2 ቆሮ. 9:11-14
ጳውሎስ ሐሳቡን ሲደመድም፣ አምላክ ለጋስ መሆኑን የሚያሳየውን ከሁሉ የላቀ ማስረጃ ጠቅሷል። ጳውሎስ “በቃላት ሊገለጽ ለማይችለው ነፃ ስጦታው አምላክ የተመሰገነ ይሁን” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮ. 9:15) የይሖዋ ስጦታ፣ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሕዝቦቹ የዘረጋውን የጥሩነቱን መግለጫዎች ሁሉ እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው። ስጦታው እጅግ የላቀ ዋጋ ያለው በመሆኑ በቃላት ሊገለጽ አይችልም።
ታዲያ ይሖዋና ልጁ ላደረጉልን እንዲሁም ወደፊት ለሚያደርጉልን ነገር ሁሉ አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ መጠኑ አነሰ በዛ ሳንል ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ጥሪታችንን የይሖዋን ንጹሕ አምልኮ ለማራመድ በልግስና በመስጠት ነው።—1 ዜና 22:14፤ 29:3-5፤ ሉቃስ 21:1-4