በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ያሳለፍነው መቶ ዓመት!
“የሰላም አምላክ ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ።”—ዕብ. 13:20, 21
መዝሙሮች፦ 136, 14
1. ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ ምን ያህል ከፍ አድርጎ ይመለከተው ነበር? አስረዳ።
ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት መናገር ያስደስተው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ከማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ይበልጥ ስለ አምላክ መንግሥት ብዙ ጊዜ ተናግሯል፤ አገልግሎቱን ሲያከናውን ስለዚህ መንግሥት ከ100 ጊዜ በላይ ጠቅሷል። በእርግጥም ለመንግሥቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል።—ማቴዎስ 12:34ን አንብብ።
2. ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ የሚገኘውን ተልእኮ ሲሰጥ ምን ያህል ደቀ መዛሙርት ተገኝተው ሊሆን ይችላል? እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረስነው ለምንድን ነው?
2 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ለሚሆኑ ከ500 የሚበልጡ ደቀ መዛሙርት ታይቶ ነበር። (1 ቆሮ. 15:6) የመንግሥቱን መልእክት “ከሁሉም ብሔራት” ለተውጣጡ ሰዎች እንዲያደርሱ ያዘዛቸው በዚያ ወቅት ሳይሆን አይቀርም፤ በወቅቱ ይህን ሥራ ማከናወን ተፈታታኝ ነበር! * ኢየሱስ ይህ ታላቅ ሥራ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ” እንደሚከናወን የተነበየ ሲሆን ይህም እየተፈጸመ ነው። አንተም ይህ ተልእኮና ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ የበኩልህን አስተዋጽኦ እያደረግክ ሊሆን ይችላል።—ማቴ. 28:19, 20
3. ምሥራቹን የመስበኩን ተልእኮ ለመወጣት በየትኞቹ ሦስት አቅጣጫዎች በሚገባ ታጥቀናል?
3 ኢየሱስ ለተከታዮቹ የስብከት ተልእኮ ከሰጣቸው በኋላ “ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (ማቴ. 28:20) በመሆኑም ይህ ሰፊ የስብከት ሥራ የሚከናወነው በእሱ አመራር ሥር ነው። አምላካችንም ይህን ተልእኮ ለመወጣት በሚረዳን “መልካም ነገር ሁሉ” አስታጥቆናል። (ዕብ. 13:20, 21) በዚህ ርዕስ ላይ ከእነዚህ መልካም ነገሮች መካከል ሦስቱን ይኸውም (1) የተሰጡንን መሣሪያዎች፣ (2) የተጠቀምንባቸውን ዘዴዎች እንዲሁም (3) ያገኘነውን ሥልጠና እንመረምራለን። በመጀመሪያ፣ ባለፈው 100 ዓመት ውስጥ ከተጠቀምንባቸው መሣሪያዎች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
ንጉሡ አገልጋዮቹን ለስብከት አስታጥቋቸዋል
4. በስብከቱ ሥራችን የተለያዩ መሣሪያዎችን ስንጠቀም የቆየነው ለምንድን ነው?
4 ኢየሱስ “የመንግሥቱን ቃል” በተለያየ ዓይነት አፈር ላይ ከተዘራ ዘር ጋር አመሳስሎታል። (ማቴ. 13:18, 19) አንድ አትክልተኛ መሬቱን ለዘር ለማዘጋጀት የተለያዩ መሣሪያዎችን ሊጠቀም ይችላል። በተመሳሳይም ንጉሣችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ ልባቸውን ለማዘጋጀት የሚረዱ የተለያዩ መሣሪያዎችን ባለፉት ዓመታት ሰጥቶናል። ከእነዚህ መሣሪያዎች አንዳንዶቹ ያገለገሉት ለተወሰኑ አሥርተ ዓመታት ሲሆን አንዳንዶቹ ግን አሁንም ጠቃሚ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። ይሁንና ሁሉም መሣሪያዎች ከወንጌላዊነቱ ሥራችን ጋር በተያያዘ በተለያየ መንገድ ችሎታችንን እንድናዳብር ረድተውናል።
5. የምሥክርነት መስጫ ካርድ ምንድን ነው? ጥቅም ላይ የሚውለውስ እንዴት ነበር?
5 ብዙዎች አገልግሎት እንዲጀምሩ የረዳቸው አንዱ መሣሪያ የምሥክርነት መስጫ ካርድ ሲሆን የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይህን መሣሪያ መጠቀም የጀመሩት በ1933 ነው። አጠር ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የያዘው ይህ ካርድ መጠኑ 7.6 ሴንቲ ሜትር በ12.7 ሴንቲ ሜትር ነው። አዲስ መልእክት የያዘ አዲስ ካርድ በየጊዜው ይዘጋጃል። አስፋፊዎቹ ካርዱን የሚጠቀሙበት መንገድ ቀላል ነበር! ወንድም ቻርልስ ኤርለንማየር በዚህ ዓይነቱ አገልግሎት መካፈል ሲጀምር ዕድሜው አሥር ዓመት ገደማ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የምንጠቀምበት መግቢያ ‘እባክዎ፣ ይህን ካርድ ያንብቡት!’ የሚል ነበር። የምናነጋግረው ግለሰብ ካርዱን ካነበበ በኋላ ጽሑፍ እንዲወስድ እንጋብዘውና እንሄዳለን።”
6. የምሥክርነት መስጫ ካርድ ምን ጥቅም ነበረው?
6 የምሥክርነት መስጫ ካርድ ብዙ ጥቅሞች ነበሩት። አንዳንድ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ የመካፈል ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም ዓይናፋር ነበሩ፤ ምን ብለው መናገር እንዳለባቸው አያውቁም። ሌሎች ደግሞ በጣም ደፋሮች ነበሩ። የሚያውቁትን ሁሉ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ለቤቱ ባለቤት መናገር ይችላሉ፤ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ዘዴኛነት ይጎድላቸው ነበር! የምሥክርነት መስጫ ካርዶች ግን በሚገባ የተመረጡ ጥቂት ቃላትን ስለሚጠቀሙ ለአስፋፊዎቹ እንደ “አንደበት ሆነውላቸዋል።”
7. አንዳንዶች በምሥክርነት መስጫ ካርድ ሲጠቀሙ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል?
7 እርግጥ ነው፣ ከዚህ መሣሪያ ጋር በተያያዘ አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ። ግሬስ ኢስቴፕ የተባሉ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ እህት እንዲህ በማለት ያስታውሳሉ፦ “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ‘ካርዱ ምንድን ነው የሚለው? መልእክቱን ለምን እናንተ አትነግሩኝም?’ የሚል ጥያቄ ያቀርቡልናል።” አስፋፊዎቹ፣ በካርዱ ላይ የተጻፈውን ማንበብ የማይችሉ ሰዎችም ያጋጥሟቸዋል። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ካርዱን እንዲወስዱት የተሰጣቸው ስለሚመስላቸው ከአስፋፊዎቹ ከተቀበሉ በኋላ በራቸውን ይዘጋሉ። የቤቱ ባለቤት ተቃዋሚ ከሆነም ካርዱን ይቀዳድደው ይሆናል። ያም ሆኖ ወንድሞቻችን ለሰዎች መመሥከርና የመንግሥቱ ወኪሎች መሆናቸውን በይፋ መግለጽ እየለመዱ ነበር።
8. የሸክላ ማጫወቻዎች ጥቅም ላይ የሚውሉት እንዴት እንደነበር አብራራ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
8 በ1930ዎቹ እንዲሁም በ1940ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ጥቅም ላይ የዋለው ሌላው መሣሪያ በቀላሉ ዘፀአት 4:14-16ን አንብብ።) አስፋፊው የቤቱን ባለቤት ፈቃድ ከጠየቀ በኋላ አራት ደቂቃ ተኩል የሚፈጅ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ይከፍትለታል፤ ከዚያም ጽሑፍ እንዲወስድ ይጋብዘዋል። በሸክላ የተቀዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለማዳመጥ አንዳንድ ጊዜ የአንድ ቤተሰብ አባላት በሙሉ ይሰበሰባሉ! በ1934 ዎች ታወር ሶሳይቲ በአገልግሎት ላይ ለመጠቀም ተብለው የተዘጋጁ የሸክላ ማጫወቻዎችን ማምረት ጀመረ። ከጊዜ በኋላም 92 ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ንግግሮች ተቀዱ።
ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችል የሸክላ ማጫወቻ ነበር፤ አንዳንድ ወንድሞች፣ በእነሱ ፋንታ የሚናገረው የሸክላ ማጫወቻው በመሆኑ አሮን የሚል ቅጽል ስም አውጥተውለት ነበር። (9. የሸክላ ማጫወቻ ምን ያህል ውጤታማ ነበር?
9 ሂለሪ ጎስለን የተባለ ሰው፣ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ካዳመጠ በኋላ ለጎረቤቶቹም የመንግሥቱን መልእክት ማሰማት እንዲችል የሸክላ ማጫወቻውን ለአንድ ሳምንት እንዲያውሰው አስፋፊውን ጠየቀው። አስፋፊው ተመልሶ ሲመጣ ፍላጎት ያላቸው የተወሰኑ ሰዎች አገኘ። ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሲሆን ውሎ አድሮም የሂለሪ ሁለት ሴቶች ልጆች ከጊልያድ ትምህርት ቤት ተመርቀው ወደ ሌሎች አገሮች ተልከዋል። እንደ ምሥክርነት መስጫ ካርዱ ሁሉ የሸክላ ማጫወቻም ብዙዎች የስብከቱን ሥራ እንዲጀምሩ ረድቷል። ብዙም ሳይቆይ ንጉሡ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በመጠቀም የሚናገሩትን ነገር በአፋቸው ላይ አስቀመጠ።
ምሥራቹን ለማዳረስ በማንኛውም ዘዴ መጠቀም
10, 11. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማሰራጨት ጋዜጣና ሬዲዮ ጥቅም ላይ የዋሉት እንዴት ነው? እነዚህ ዘዴዎች ውጤታማ የነበሩት ለምንድን ነው?
10 የአምላክ ሕዝቦች በንጉሡ እየተመሩ በተቻለ መጠን ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል። በተለይ ‘ሠራተኞቹ ጥቂት’ በነበሩበት ወቅት ይህ በጣም አስፈላጊ ነበር። (ማቴዎስ 9:37ን አንብብ።) በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አካባቢ የይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር ጥቂት በሆነባቸው ቦታዎች ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ለማድረስ ጋዜጦች ጥቅም ላይ ውለዋል። ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል፣ ስብከቶቹን ለአንድ የጋዜጣ ድርጅት በየሳምንቱ ይልክ ነበር። ድርጅቱም ስብከቶቹን በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳና በአውሮፓ ባሉ ጋዜጦች ላይ እንዲወጡ በቴሌግራፍ ይልካል። በ1913 የወንድም ራስል ስብከቶች በ2,000 ጋዜጦች ላይ ይታተሙ የነበረ ሲሆን 15,000,000 የሚያህሉ አንባቢዎች ዘንድ ይደርሱ እንደነበር ይገመታል።
11 ወንድም ራስል ከሞተ በኋላ ምሥራቹን ለማዳረስ የሚያስችል ሌላ ውጤታማ ዘዴ ጥቅም ላይ ዋለ። ሚያዝያ 16, 1922 ወንድም ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ በሬዲዮ የሚተላለፍ ንግግር አቀረበ፤ ወንድም ራዘርፎርድ በሬዲዮ ካስተላለፋቸው የመጀመሪያ ንግግሮች አንዱ የሆነውን ይህን ንግግር 50,000 ያህል ሰዎች እንዳዳመጡት ይገመታል። ከዚያም የካቲት 24, 1924 የድርጅቱ የመጀመሪያ የሬዲዮ ጣቢያ ይኸውም ደብልዩ ቢ ቢ አር ስርጭት ጀመረ። የታኅሣሥ 1, 1924 መጠበቂያ ግንብ ለሰዎች ለመስበክ የሚያስችለውን ይህን አዲስ ዘዴ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “የእውነትን መልእክት ለማሰራጨት እስከ ዛሬ ከተጠቀምንባቸው ዘዴዎች ሁሉ፣ ብዙ ወጪ የማይጠይቀውና ውጤታማ የሆነው ዘዴ ሬዲዮ እንደሆነ እናምናለን።” እንደ ጋዜጣው ሁሉ ሬዲዮም ጥቂት የመንግሥቱ አስፋፊዎች በሚኖሩበት አካባቢ ምሥራቹን ለብዙዎች ለማድረስ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
12. (ሀ) የአደባባይ ምሥክርነት ከሚሰጥባቸው መንገዶች መካከል ይበልጥ የምትወደው የትኛውን ነው? (ለ) በአደባባይ ምሥክርነት መካፈል የሚያስፈራን ከሆነ ፍርሃታችንን ለማሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል?
12 በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በአውቶቡስ ማቆሚያዎች፣ በባቡር ጣቢያዎች፣ በመኪና ማቆሚያዎች እንዲሁም ሕዝብ በሚበዛባቸውና በገበያ ቦታዎች ለሚከናወነው የአደባባይ ምሥክርነት ትልቅ ትኩረት እየተሰጠ ነው። ከእነዚህ የአገልግሎት መስኮች መካከል በአንዳንዶቹ መካፈል የሚያስፈራህ ከሆነ ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ፤ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያገለገለው አንጄሎ መኔራ (ጁኒየር) የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ በቁም ነገር አስብበት፤ እንዲህ ብሏል፦ “አዳዲስ የአገልግሎት ዘርፎችን 2 ቆሮንቶስ 12:9, 10ን አንብብ።
የምንመለከታቸው ይሖዋን ለማገልገልና ለእሱ ታማኝ መሆናችንን ለማሳየት እንደሚያስችል አዲስ አጋጣሚ አድርገን ነበር፤ በተጨማሪም ንጹሕ አቋማችን የሚፈተንበት ሌላ አጋጣሚ እንደሆነ እናስብ ነበር፤ ይሖዋ በጠየቀን በማንኛውም መንገድ እሱን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናችንን ለማሳየት ጓጉተን ነበር።” በአዲስ ምናልባትም ከለመድነው በተለየ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል በይሖዋ ይበልጥ ለመተማመን ይረዳናል፤ ይህ ደግሞ መንፈሳዊነታችንን ያሳድጋል።—13. በአገልግሎት ረገድ jw.org የተባለው ድረ ገጻችን ምን እያከናወነ ነው? ሰዎች ይህን ድረ ገጽ እንዲጎበኙ ስትጋብዝ ምን ተሞክሮ አግኝተሃል?
13 በርካታ አስፋፊዎች፣ ሰዎች jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን እንዲቃኙ ይጋብዛሉ፤ ከዚህ ድረ ገጽ ላይ ከ700 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብና ማውረድ ይቻላል። በየዕለቱ ከ1.6 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ድረ ገጻችንን ይጎበኛሉ። ባለፉት ዓመታት በሬዲዮ እንደተሰጠው ምሥክርነት ሁሉ ድረ ገጻችንም ርቀው በሚገኙ ቦታዎች ለሚኖሩ ሰዎች ጭምር ምሥራቹ እንዲደርስ እያደረገ ነው።
የምሥራቹን አገልጋዮች ማሠልጠን
14. የመንግሥቱ አስፋፊዎች ምን ዓይነት ሥልጠና ያስፈልጋቸው ነበር? ውጤታማ አስተማሪዎች እንዲሆኑ የረዳቸው የትኛው ትምህርት ቤት ነው?
14 ምሥራቹን ለማሰራጨት ከተጠቀምንባቸው መሣሪያዎችና ዘዴዎች መካከል እስካሁን ጥቂቶቹን ተመልክተናል። ይሁንና ስላገኘነው ሥልጠናስ ምን ማለት ይቻላል? የምናነጋግረው ሰው የተቀዳውን ንግግር በሸክላ ማጫወቻ ካዳመጠ በኋላ የሰማውን ነገር እንዳልተቀበለው ቢገልጽ አሊያም ደግሞ የምሥክርነት መስጫ ካርዱ ላይ ያለውን መልእክት አንብቦ ፍላጎት ቢያሳይ ምን እናደርጋለን? አስፋፊዎች ለተቃወማቸው ሰው በዘዴ መልስ መስጠት እንዲሁም ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በጥበብ ማስተማር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ወንድም ናታን ሆመር ኖር፣ አስፋፊዎች የመናገር ስጦታቸውን በአገልግሎት ላይ እንዲጠቀሙበት ሥልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘበ፤ ወንድም ኖር እንዲህ ዓይነት ሐሳብ እንዲያመነጭ የረዳው የአምላክ መንፈስ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ታዲያ ምን ተደረገ? ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተቋቋመ፤ ከዚያም በ1943 ትምህርት ቤቱ በጉባኤዎች ውስጥ መካሄድ ጀመረ። ይህ ትምህርት ቤት ውጤታማ አስተማሪዎች እንድንሆን ረድቶናል።
15. (ሀ) አንዳንዶች በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ሲሰጣቸው ምን አጋጥሟቸዋል? (ለ) ይሖዋ በመዝሙር 32:8 ላይ የገባው ቃል በሕይወትህ ሲፈጸም የተመለከትከው እንዴት ነው?
15 ብዙዎች በሕዝብ ፊት ንግግር ማቅረብን ለመልመድ ጊዜ ወስዶባቸዋል። ሁልዮ ራሙ በ1944 በትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ንግግሩን ያቀረበበትን ጊዜ ያስታውሳል። የንግግሩ ርዕሰ ጉዳይ ምን ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምስት ጥቅሶች ላይ ብቻ የሚገኘው ዶይቅ ነበር! ሁልዮ “ጉልበቶቼ ይብረከረኩ፣ እጆቼ ይንቀጠቀጡና ጥርሴ ይንገጫገጭ መዝሙር 32:8ን አንብብ።
ነበር” ብሏል፤ አክሎም ንግግሩን በአምስቱ ጥቅሶች ላይ ብቻ ተመሥርቶ ማቅረብ እንደነበረበት ገልጿል። ሁልዮ “ንግግሬን በሦስት ደቂቃ ውስጥ ጨረስኩ፤ መድረክ ላይ ወጥቼ ያቀረብኩት የመጀመሪያ ንግግር ይህ ነበር፤ ያም ሆኖ ንግግር ማቅረቤን አላቆምኩም” በማለት ተናግሯል። ልጆችም በትምህርት ቤቱ ይካፈላሉ፤ እርግጥ ነው፣ በጉባኤ ንግግር ማቅረብ ቀላል የሆነው ለሁሉም አልነበረም። ቀደም ሲል የተጠቀሰው አንጄሎ መኔራ፣ ትምህርት ቤት ከገባ ብዙም ያልቆየ አንድ ትንሽ ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረበውን ንግግር ያስታውሳል። ወንድም መኔራ እንደገለጸው ልጁ “በጣም ከመፍራቱ የተነሳ ንግግሩን ሲያቀርብ ማልቀስ ጀመረ። ሆኖም ንግግሩን ማቋረጥ ስላልፈለገ እያለቀሰ ጨረሰው።” አንተስ ዓይናፋር በመሆንህ ወይም በሌላ ምክንያት፣ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ከመስጠት ወይም በሌሎች መንገዶች ተሳትፎ ከማድረግ ወደኋላ ትላለህ? ከሆነ ይሖዋ ፍርሃትህን ለማስወገድ እንዲረዳህ ጠይቀው። ቀደም ባሉት ዓመታት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተካፈሉትን ተማሪዎች እንደረዳ ሁሉ አንተንም ይረዳሃል።—16. (ሀ) ቀደም ባሉት ዓመታት (ለ) ከ2011 ወዲህ በጊልያድ ትምህርት ቤት የሚሠለጥኑት እነማን ናቸው?
16 የይሖዋ ሕዝቦች ሥልጠና የሚያገኙት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ብቻ አይደለም። ሚስዮናውያንና ሌሎች ክርስቲያኖች በጊልያድ ትምህርት ቤት በመካፈላቸው በእጅጉ ተጠቅመዋል። አንድ የጊልያድ አስተማሪ እንደገለጸው ከትምህርት ቤቱ ዓላማዎች አንዱ “ተማሪዎቹ በወንጌላዊነቱ ሥራ ለመካፈል ይበልጥ ጉጉት እንዲያድርባቸው መርዳት ነው።” የጊልያድ ትምህርት ቤት የተቋቋመው በ1943 ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከ8,500 የሚበልጡ ተማሪዎች ሠልጥነዋል። በጊልያድ የሠለጠኑ ሚስዮናውያን 170 በሚያህሉ አገሮች ያገለግላሉ። ከ2011 ወዲህ በትምህርት ቤቱ መሠልጠን የሚችሉት በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩ ክርስቲያኖች ይኸውም ልዩ አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ቤቴላውያን እንዲሁም በትምህርት ቤቱ ያልተካፈሉ ሚስዮናውያን ብቻ ናቸው።
17. በጊልያድ የሚሰጠው ሥልጠና ምን ያህል ውጤታማ ነው?
17 ይህ ተጨማሪ ሥልጠና ምን ያህል ውጤታማ ነው? ጃፓንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ነሐሴ 1949 በአገሪቱ የነበሩት ጃፓናውያን አስፋፊዎች አሥር አይሞሉም። በዚያ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ግን በጊልያድ የሠለጠኑ 13 ሚስዮናውያን በዚህች አገር በስብከቱ ሥራ ተጠምደው ነበር። በአሁኑ ጊዜ በጃፓን ከ216,000 በላይ አስፋፊዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት አቅኚዎች ናቸው!
18. ብቃት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የረዱ ሌሎች ትምህርት ቤቶችን ጥቀስ።
18 ሌሎች ትምህርት ቤቶችም የይሖዋ ሕዝቦች መንፈሳዊነትና ውጤታማነት በእጅጉ እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ ለምሳሌ የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤትን፣ የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤትን፣ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤትን፣ ለወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤትን እንዲሁም ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤትን መጥቀስ ይቻላል። በእርግጥም ንጉሡ ተገዢዎቹን ማሠልጠኑን ቀጥሏል!
19. ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን ማስተዋል የተንጸባረቀበት ሐሳብ ተናግሯል? የተናገረው የተፈጸመውስ እንዴት ነው?
19 የአምላክ መንግሥት ከተወለደ 100 ዓመት አልፎታል። ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስም እኛን ማሠልጠኑን ቀጥሏል። ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1916 ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የተናገረው ሐሳብ፣ የስብከቱ ሥራ ምን ያህል በስፋት እንደሚከናወን ማስተዋሉን ያሳያል። ለቅርብ የሥራ ባልደረባው እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ሥራው በፍጥነት እያደገ ሲሆን እድገት ማድረጉንም ይቀጥላል፤ ምክንያቱም ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ከመስበኩ ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ የሚከናወን ሥራ አለ።” (ፌዝ ኦን ዘ ማርች በአሌክሳንደር ሂዩ ማክሚላን፣ ገጽ 69) ወንድም ራስል ምንኛ ትክክል ነበር! እኛም የሰላም አምላክ እጅግ አስደሳች ለሆነው ሥራ ምንጊዜም ስለሚያስታጥቀን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በእርግጥም ይሖዋ ፈቃዱን ለማድረግ የሚያስፈልገንን “መልካም ነገር ሁሉ” ይሰጠናል!
^ አን.2 በዚህ ጊዜ ከተገኙት መካከል አብዛኞቹ፣ በኋላ ላይ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለን። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እነሱን አስመልክቶ ሲናገር ‘ከ500 የሚበልጡ ወንድሞች’ ብሏቸዋል። አክሎም “አንዳንዶቹ በሞት ቢያንቀላፉም አብዛኞቹ ግን አሁንም ከእኛ ጋር አሉ” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው። በመሆኑም ጳውሎስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሌሎች ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ በቦታው ተገኝተው ከሰሙት ወንድሞች አብዛኞቹን የሚያውቋቸው ይመስላል።