በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ የፍቅር አምላክ ነው

ይሖዋ የፍቅር አምላክ ነው

“አምላክ ፍቅር ነው።”—1 ዮሐ. 4:8, 16

መዝሙሮች፦ 18, 91

1. የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ምንድን ነው? ይህን ማወቅህስ ስለ እሱ ምን ስሜት ያሳድርብሃል?

በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የይሖዋ ቃል ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። ጥቅሱ፣ ፍቅር አምላክ ካሉት አስደናቂ ባሕርያት መካከል አንዱ እንደሆነ በመግለጽ ብቻ ሳይወሰን “አምላክ ፍቅር ነው” እንዳለ ልብ ማለት ያስፈልጋል። (1 ዮሐ. 4:8) ፍቅር ዋነኛውና ከሁሉ የላቀው የይሖዋ ባሕርይ ነው። ይሖዋ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን የፍቅር ተምሳሌት ነው። የጽንፈ ዓለምና የሁሉም ሕይወት ያላቸው ነገሮች ፈጣሪ የፍቅር አምላክ መሆኑን ማወቅ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው።

2. አምላክ ፍቅር መሆኑ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

2 አምላክ ለፍጡራኑ ደግነት የሚንጸባረቅበትና ጥልቅ የሆነ ፍቅር ያለው መሆኑ፣ ለሰው ዘር ቤተሰብ ያለው ዓላማ በሙሉ ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንደሚፈጸምና ይህም በእሱ አገዛዝ ሥር ላሉ ሁሉ ወደር የሌለው ጥቅም እንደሚያስገኝ ለመተማመን ያስችለናል። ለምሳሌ፣ ይሖዋ “በሾመው ሰው [በኢየሱስ ክርስቶስ] አማካኝነት በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህን ለማድረግም ቀን ወስኗል”፤ እንዲህ ያደረገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። (ሥራ 17:31) ይህ ዓላማው መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውና ታዛዥ የሆኑ ሰዎች መልካም ፍርድ የሚበየንላቸው ሲሆን ይህም በበረከት የተሞላና ማብቂያ የሌለው ዘላለማዊ ሕይወት ያስገኝላቸዋል።

ታሪክ ምን አሳይቷል?

3. አምላክ ለሰው ልጆች ፍቅር ባይኖረው የወደፊት ሕይወታችን ምን ዓይነት የሚሆን ይመስልሃል?

3 አምላክ ለሰው ልጆች ፍቅር ባይኖረው የወደፊት ሕይወታችን ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስበው። ሰይጣን ዲያብሎስ አምላክ የሆነለት ብሎም በሰብዓዊ አገዛዝ የሚመራው ይህ ዓለም ያስመዘገበውን አሰቃቂ ታሪክ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፤ ሰይጣን ፍቅር የሌለው ከመሆኑም ሌላ በቁጣ ተሞልቷል። (2 ቆሮ. 4:4፤ 1 ዮሐ. 5:19፤ ራእይ 12:9, 12ን አንብብ።) አፍቃሪ የሆነው አምላክ አመራር ባይኖር ኖሮ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ፍጥረታት የወደፊት ሕይወት ምን ያህል አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ከዚህ መረዳት ይቻላል።

4. ይሖዋ በጽድቅ አገዛዙ ላይ የተነሳው ዓመፅ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው?

4 ዲያብሎስ በይሖዋ አገዛዝ ላይ ባመፀበት ጊዜ የመጀመሪያዎቹ ሰዎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል። የአምላክ ጽንፈ ዓለማዊ አገዛዝ ትክክለኛና ጽድቅ የሰፈነበት ስለመሆኑ ጥያቄ አንስቷል። በሌላ አባባል ሰይጣን የእሱ አገዛዝ ከፈጣሪ አገዛዝ የተሻለ እንደሚሆን መናገሩ ነበር። (ዘፍ. 3:1-5) ሰይጣን ያነሳው ጥያቄ ትክክል መሆኑን ለማሳየት እንዲሞክር ይሖዋ ጊዜ የሰጠው ቢሆንም ይህ ጊዜ ገደብ አለው። ይሖዋ ከእሱ በቀር ሌሎች አገዛዞች በሙሉ ብቃት እንደሌላቸው በማያሻማ መንገድ መረጋገጥ እንዲችል በቂ ጊዜ በመስጠት ታላቅ ጥበቡን አሳይቷል። አሳዛኝ የሆነው የሰው ዘር ታሪክ እንደሚያሳየው የሰው ልጆችም ሆኑ ሰይጣን መልካም አገዛዝ እንዲሰፍን ማድረግ አይችሉም።

5. የሰው ዘር ታሪክ ምን ነገር በግልጽ አሳይቷል?

5 ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ብቻ እንኳ ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ብሔራት ባደረጓቸው ጦርነቶች አልቀዋል። ዛሬ የዓለም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው። ይህም የአምላክ ቃል በዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ’ ብሎ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው። (2 ጢሞ. 3:1, 13) “ይሖዋ ሆይ፣ የሰው መንገድ በራሱ እጅ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ትክክል መሆኑን ታሪክ በበቂ ሁኔታ አረጋግጧል። (ኤር. 10:23) በእርግጥም ይሖዋ የሰው ልጆችን ሲፈጥር ከእሱ አገዛዝ ርቀው ራሳቸውን ለመምራት የሚያበቃ ችሎታም ሆነ መብት አልሰጣቸውም።

6. አምላክ ለተወሰነ ጊዜ ክፋት እንዲኖር መፍቀዱ ምን ጥቅም ያስገኛል?

6 አምላክ ክፋት ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል መፍቀዱ የሰዎች አገዛዝ ከንቱ እንደሆነ ከማሳየቱም ባሻገር ዘላቂ ጥቅም አለው። ውጤታማ የሚሆነው የአምላክ አገዛዝ ብቻ እንደሆነ በማያዳግም ሁኔታ ያረጋግጣል። ይሖዋ ክፋትንና ክፉ አድራጊዎችን ካጠፋ በኋላ፣ የእሱ አገዛዝ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ጥያቄ የሚያነሳ አካል ቢኖር አምላክ ይህ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ጊዜ መስጠት አያስፈልገውም። እንዲህ ያሉት ዓመፀኞች ወዲያውኑ ሊጠፉ እንጂ ክፋትን እንደገና እንዲያስፋፉ ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ የሰው ልጆች ታሪክ በቂ ማስረጃ ይሆናል።

ይሖዋ ፍቅሩን አሳይቷል

7, 8. ይሖዋ ታላቅ ፍቅሩን ካሳየባቸው በርካታ መንገዶች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

7 የይሖዋ ታላቅ ፍቅር በብዙ መንገዶች ታይቷል። አስደናቂ የሆነውን ጽንፈ ዓለም እንደ ምሳሌ እንመልከት። በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብትንና ፕላኔቶችን የያዙ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ጋላክሲዎች አሉ። ፍኖተ ሐሊብ በተባለው በእኛ ጋላክሲ ውስጥ ከታቀፉት ከዋክብት መካከል ፀሐይ ትገኝበታለች፤ ፀሐይ ባትኖር ኖሮ በምድር ላይ ያሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ሕልውና ያከትም ነበር። እነዚህ ሁሉ ፍጥረታት ይሖዋ፣ አምላክ ለመሆኑ እንዲሁም እንደ ኃይል፣ ጥበብና ፍቅር ላሉት ባሕርያቱ ማስረጃ ናቸው። በእርግጥም “የማይታዩት [የአምላክ ባሕርያት] ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።”—ሮም 1:20

8 ይሖዋ ምድርን ሲፈጥር በእሷ ላይ እንዲኖሩ ላሰባቸው ሕያዋን ፍጥረታት አስፈላጊ ነገሮችን በሙሉ አብሮ ፈጥሯል። ለሰው ልጆች ውብ የአትክልት ቦታ ያዘጋጀ ሲሆን ለዘላለም መኖር የሚያስችላቸው ፍጹም አእምሮና አካል ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 4:11ን አንብብ።) በተጨማሪም “ሕይወት ላለው ሁሉ ምግብ ይሰጣል፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና።”—መዝ. 136:25

9. ይሖዋ አፍቃሪ አምላክ ቢሆንም ምንን ይጠላል?

9 ይሖዋ የፍቅር አምላክ እንደሆነ ከማሳየቱም ባሻገር ክፋትን እንደሚጠላ ገልጿል። ለምሳሌ መዝሙር 5:4-6 ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “አንተ በክፋት የምትደሰት አምላክ አይደለህም፤ . . . መጥፎ ምግባር ያላቸውን ሁሉ ትጠላለህ።” ጥቅሱ አክሎም “ይሖዋ ዓመፀኞችንና አታላዮችን ይጸየፋል” ይላል።

ክፋት በቅርቡ ይወገዳል

10, 11. (ሀ) ይሖዋ ክፉዎችን ምን ያደርጋቸዋል? (ለ) ይሖዋ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች የሚባርከው እንዴት ነው?

10 ይሖዋ ከእሱ አገዛዝ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ አጥጋቢ በሆነ መንገድ መልስ ሲያገኝ ክፋትን ከምድርና ከመላው ጽንፈ ዓለም ያስወግዳል፤ ይህን የሚያደርገው የፍቅር አምላክ ስለሆነና ክፋትን ስለሚጠላ ነው። የአምላክ ቃል የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል፦ “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ። ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ . . . የይሖዋ ጠላቶች እንደ መስክ ውበት ይከስማሉ፤ እንደ ጭስ ይበናሉ።”—መዝ. 37:9, 10, 20

11 በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክ ቃል “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል ተስፋ ይዟል። (መዝ. 37:29) እንዲህ ያሉት ቅን ሰዎች “በብዙ [ሰላም] እጅግ ደስ ይላቸዋል።” (መዝ. 37:11) ይህ እንደሚፈጸም እርግጠኞች ነን፤ ምክንያቱም አፍቃሪው አምላካችን ምንጊዜም ለታማኝ አገልጋዮቹ ከሁሉ የተሻለውን ነገር ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” (ራእይ 21:4) የይሖዋን ፍቅር ከልባቸው የሚያደንቁና እንደ ገዢያቸው አድርገው የሚታዘዙት ሁሉ ከፊታቸው እጅግ ግሩም ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል!

12. “ነቀፋ የሌለበት” የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው?

12 የይሖዋ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ነቀፋ የሌለበትን ሰው ልብ በል፤ ቀና የሆነውንም ሰው በትኩረት ተመልከት፤ የዚህ ሰው የወደፊት ሕይወት ሰላማዊ ይሆናልና። ኃጢአተኞች ሁሉ ግን ይጠፋሉ፤ ክፉዎች ምንም ተስፋ አይኖራቸውም።” (መዝ. 37:37, 38) “ነቀፋ የሌለበት” ሰው ይሖዋንና ልጁን ያውቃል፤ እንዲሁም ታዛዥ በመሆን የአምላክን ፈቃድ ይፈጽማል። (ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።) እንዲህ ያለው ሰው በ1 ዮሐንስ 2:17 ላይ የሚገኘውን “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለውን ሐሳብ በቁም ነገር ይመለከተዋል። ይህ ዓለም የሚጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ በመሆኑ “ይሖዋን ተስፋ አድርግ፤ መንገዱንም ተከተል” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን አጣዳፊ ነው።—መዝ. 37:34

የአምላክ ፍቅር የተገለጸበት የላቀ መንገድ

13. ይሖዋ ለኃጢአተኞች ፍቅሩን የገለጸበት የላቀ መንገድ ምንድን ነው?

13 ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ብንሆንም የይሖዋን ‘መንገድ መከተል’ እንችላለን። በተጨማሪም ይሖዋ ፍቅሩን የገለጸበት የላቀ መንገድ ከእሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ የቀረበ ዝምድና ለመመሥረት አስችሎናል። ይሖዋ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት በማዘጋጀት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ከአዳም ከወረሱት ኃጢአትና ሞት ነፃ መውጣት የሚችሉበት መንገድ ከፍቷል። (ሮም 5:12 እና 6:23ን አንብብ።) ይሖዋ፣ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ከእሱ ጋር በሰማይ ሲኖር ታማኝነቱን ባሳየው አንድያ ልጁ ሙሉ በሙሉ ይተማመናል። አምላክ አፍቃሪ እንደመሆኑ መጠን ኢየሱስ በምድር ላይ በደረሰበት ግፍ በጥልቅ እንዳዘነ ምንም ጥያቄ የለውም። ያም ሆኖ ኢየሱስ ታማኝ በመሆን የአምላክን ሉዓላዊነት ደግፏል፤ እንዲሁም ፍጹም የሆነ ሰው በጣም ከባድ የሆነ ፈተና ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙን መጠበቅ እንደሚችል አሳይቷል።

አምላክ ፈቃደኛ የሆነውን ልጁን ወደ ምድር እንዲልክ ያነሳሳው ፍቅር ነው (አንቀጽ 13ን ተመልከት)

14, 15. የኢየሱስ ሞት ምን አከናውኗል?

14 ኢየሱስ እጅግ ከባድ የሆነ ፈተና ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ ለአባቱ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሆኗል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ በሞቱ አማካኝነት የቤዛውን ዋጋ በመክፈሉ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህን ማድረጉ የሰው ልጆች የሚቤዡበትና አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ከፍቷል። ይሖዋና ኢየሱስ ይህን በማድረግ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳዩን ሐዋርያው ጳውሎስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለኃጢአተኞች ሞቷልና። ለጻድቅ ሰው የሚሞት ማግኘት በጣም አዳጋች ነው፤ ለጥሩ ሰው ለመሞት የሚደፍር ግን ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ሆኖም አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።” (ሮም 5:6-8) ሐዋርያው ዮሐንስም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል። ይህ ፍቅር የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው፦ እኛ አምላክን ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን ስለላከ ነው።”—1 ዮሐ. 4:9, 10

15 ኢየሱስ፣ አምላክ ለሰው ዘር ስላለው ፍቅር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን [ከቤዛው ተጠቃሚ የሚሆኑ የሰው ልጆችን] እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐ. 3:16) አምላክ ለሰዎች ያለው ፍቅር እጅግ የላቀ በመሆኑ ለእነሱ መልካም ነገር ማድረግ ምንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍለው እንኳ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አይልም። ፍቅሩ ዘላለማዊ ነው። ምንጊዜም በፍቅሩ ልንተማመን እንችላለን። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሞትም ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ማንኛውም ኃይል ቢሆን፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።”—ሮም 8:38, 39

መንግሥቱ በመግዛት ላይ ነው

16. መሲሐዊው መንግሥት ምንድን ነው? ይሖዋ ይህን መንግሥት ለማን ሰጥቶታል?

16 አምላክ መሲሐዊውን መንግሥት ማቋቋሙ የሰው ልጆችን እንደሚወድ ያረጋግጣል። ይሖዋ ይህን መንግሥት ለልጁ ሰጥቶታል፤ ኢየሱስ የሰው ልጆችን የሚወድ ከመሆኑም ሌላ እነሱን ለመግዛት የላቀ ብቃት አለው። (ምሳሌ 8:31) ከኢየሱስ ጋር ሰማያዊ ውርሻ የሚያገኙት 144,000ዎች ከሞት ከተነሱ በኋላ፣ ሰው ሆነው ሲኖሩ ያካበቱትን ልምድ ይጠቀሙበታል። (ራእይ 14:1) የኢየሱስ ስብከት ዋና ጭብጥ የአምላክ መንግሥት ሲሆን ደቀ መዛሙርቱንም እንደሚከተለው ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም።” (ማቴ. 6:9, 10) የኢየሱስ ተከታዮች የሚያቀርቡት ጸሎት ሲፈጸም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የሚያገኙት በረከት ምንኛ አስደናቂ ነው!

17. የኢየሱስ አገዛዝ ኃጢአተኛ ከሆኑት የሰው ልጆች አገዛዝ የሚለየው እንዴት ነው?

17 ፍቅር የሚንጸባረቅበት የኢየሱስ አገዛዝ፣ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነት ሕይወታቸውን እንዲያጡ ካደረገው ሰብዓዊ አገዛዝ ምንኛ የተለየ ነው! ኢየሱስ ለተገዢዎቹ ከልቡ ያስባል፤ እንዲሁም የአምላክን ግሩም ባሕርያት በተለይም ፍቅርን ያንጸባርቃል። (ራእይ 7:10, 16, 17) ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።” (ማቴ. 11:28-30) ይህ ፍቅር የተንጸባረቀበት እንዴት ያለ አስደሳች ግብዣ ነው!

18. (ሀ) የአምላክ መንግሥት ከተቋቋመበት ጊዜ ወዲህ ምን ሲያከናውን ቆይቷል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

18 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚያሳየው በ1914 ክርስቶስ በሥልጣኑ ሲገኝ የአምላክ መንግሥት በሰማይ መግዛት ጀምሯል። ከዚያ ጊዜ ወዲህ፣ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙት ቅቡዓን ቀሪዎችና ከዚህ ሥርዓት ጥፋት ተርፈው ወደ አዲሱ ዓለም የሚገቡት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እየተሰበሰቡ ነው። (ራእይ 7:9, 13, 14) በዛሬው ጊዜ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ምን ያህል ታላቅ ሆነዋል? የዚህ ቡድን አባላት ምን ይጠበቅባቸዋል? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።