በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጃችሁ ይሖዋን እንዲያገለግል አሠልጥኑት—ክፍል 2

ልጃችሁ ይሖዋን እንዲያገለግል አሠልጥኑት—ክፍል 2

“ኢየሱስም በአካልና በጥበብ እያደገ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ይበልጥ ሞገስ እያገኘ ሄደ።”—ሉቃስ 2:52

መዝሙሮች፦ 41, 89

1, 2. (ሀ) አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ምን ዓይነት ስጋት ያድርባቸዋል? (ለ) ክርስቲያን ልጆች በጉርምስና ዕድሜ ላይ እያሉ በየትኞቹ አቅጣጫዎች እድገት ማድረግ ይችላሉ?

ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸው ሲጠመቁ ማየት በጣም እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ነው። * አራቱም ልጆቿ 14 ዓመት ሳይሞላቸው የተጠመቁላት ቤረኒሲ እንዲህ ብላለች፦ “የተደበላለቀ ስሜት ተሰምቶን ነበር። ልጆቻችን ይሖዋን ለማገልገል መፈለጋቸው እንዳስደሰተን ጥያቄ የለውም። ይሁንና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በመሆናቸው ብዙ ተፈታታኝ ነገሮች እንደሚያጋጥሟቸው ተገንዝበን ነበር።” እናንተም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወይም ወደ ጉርምስና ዕድሜ እየተጠጋ ያለ ልጅ ካላችሁ የቤረኒሲን ስሜት መረዳት አይከብዳችሁም።

2 ስለ ልጆች ሥነ ልቦና የሚያጠኑ አንድ ባለሙያ፣ የጉርምስና ዕድሜ ለወላጆችም ሆነ ለልጆች ተፈታታኝ እንደሆነ ከገለጹ በኋላ ወላጆች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸው እንዳበዱ ወይም ብስለት እንደጎደላቸው አድርገው ሊያስቡ እንደማይገባ ተናግረዋል። ከዚህ ይልቅ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸው፣ በዚህ ጊዜ የፈጠራ ችሎታቸው እንደሚዳብር፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ጊዜ ለማሳለፍ እንደሚፈልጉ እንዲሁም ለነገሮች ጠንካራ ስሜት እንደሚኖራቸውና ስሜታቸውን መግለጽ እንደሚፈልጉ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ልጆቻችሁ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ ከይሖዋ ጋር ይበልጥ ትርጉም ያለው ወዳጅነት መመሥረት፣ ለአገልግሎታቸው ግብ ማውጣትና እዚያ ላይ ለመድረስ መሥራት እንዲሁም ራሳቸውን መወሰን ብሎም ከውሳኔያቸው ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት ማድረግ ይችላሉ። ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉ ለእነሱም ይህ ዕድሜ በመንፈሳዊ እድገት የሚያደርጉበት አስደሳች ጊዜ ሊሆንላቸው ይችላል። (ሉቃስ 2:52ን አንብብ።) ወላጆች በእነዚህ ወሳኝ ዓመታት ምን አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላላችሁ? ኢየሱስ አድጎ ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ ፍቅርን፣ ትሕትናን እና ማስተዋልን ያሳየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። እነዚህን ባሕርያት ማሳየታችሁ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲያገለግሉ ለማሠልጠን የሚረዳችሁ እንዴት ነው?

ለልጃችሁ ፍቅር አሳዩ

3. ኢየሱስ ሐዋርያቱን ወዳጆቼ ብሎ ሊጠራቸው የቻለው ለምንድን ነው?

3 ኢየሱስ አፍቃሪና ታማኝ ጓደኛ ነበር። (ዮሐንስ 15:15ን አንብብ።) በጥንት ዘመን አንድ ጌታ ሐሳቡንና ስሜቱን አውጥቶ ለባሪያዎቹ ማውራቱ የተለመደ አልነበረም። ኢየሱስ ግን ለታማኝ ሐዋርያቱ ጌታቸው ብቻ ሳይሆን ወዳጃቸውም ነበር። አብሯቸው ጊዜ ያሳልፍ፣ ስሜቱን ያካፍላቸው እንዲሁም የልባቸውን አውጥተው ሲነግሩት በጥሞና ያዳምጣቸው ነበር። (ማር. 6:30-32) እንዲህ ያለ ፍቅር የተንጸባረቀበት የሐሳብ ልውውጥ በኢየሱስና በሐዋርያቱ መካከል ጠንካራ ወዳጅነት እንዲመሠረት ያደረገ ሲሆን ይህም በአምላክ አገልግሎት ለሚኖራቸው ኃላፊነት አዘጋጅቷቸዋል።

4. የወላጅነት ሥልጣናችሁን እንደያዛችሁ የልጆቻችሁ ጓደኞች መሆን የምትችሉት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

4 የሁለት ልጆች አባት የሆነው ማይክል “ወላጆች እንደመሆናችን መጠን የልጆቻችን እኩዮች መሆን ባንችልም ጓደኞቻቸው መሆን እንችላለን” ብሏል። ጓደኛሞች አብረው ጊዜ ያሳልፋሉ። ከልጆቻችሁ ጋር የምታሳልፉት ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት በሥራችሁ ወይም በሌሎች ጉዳዮቻችሁ ረገድ ማስተካከያ ማድረግ ትችሉ እንደሆነ በጸሎት አስቡበት። በተጨማሪም ጓደኛሞች ተመሳሳይ ፍላጎት አላቸው። እናንተም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ የሚያስደስቱትን ነገሮች ለምሳሌ የሚወደውን ሙዚቃ፣ ፊልም ወይም ስፖርት ለመውደድ ጥረት አድርጉ። በጣሊያን የምትኖረው ኢላሪያ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ እኔ ስለማዳምጠው ሙዚቃ ማወቅ ያስደስታቸዋል። እንዲያውም በጣም የምቀርበው ጓደኛዬ አባቴ ነው፤ ለማውራት የሚከብዱ ጉዳዮችን እንኳ ሳይቀር ከእሱ ጋር መጫወት አያሳፍረኝም።” በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ “ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት” እንዲመሠርቱ ለመርዳት ስትሉ የእነሱ ጓደኛ በመሆናችሁ የወላጅነት ሥልጣናችሁን እንደምታጡ አይሰማችሁ። (መዝ. 25:14) እንዲያውም እንደምትወዷቸውና እንደምታከብሯቸው ታሳዩአቸዋላችሁ፤ እነሱም እናንተን መቅረብ ይቀላቸዋል። እንዲህ ካደረጋችሁ የሚያሳስባቸውን ነገር ለእናንተ መንገር አይከብዳቸውም።

5. ኢየሱስ በይሖዋ አገልግሎት ራስን ማስጠመድ የሚያስገኘውን ደስታ ደቀ መዛሙርቱ እንዲያጣጥሙ የረዳቸው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ የሚወዳቸው ደቀ መዛሙርቱና ጓደኞቹ በይሖዋ አገልግሎት ራስን ማስጠመድ የሚያስገኘውን ደስታ እንዲያጣጥሙ ይመኝ ነበር። በመሆኑም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በቅንዓት እንዲካፈሉ አበረታቷቸዋል። በእርግጥም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በትጋት እንዲያከናውኑ ይፈልግ ነበር! ደግሞም በሥራቸው እንዲሳካላቸው እንደሚረዳቸው የሚገልጽ ፍቅር የተንጸባረቀበት ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል።—ማቴ. 28:19, 20

6, 7. ወላጆች ቋሚ መንፈሳዊ ፕሮግራም እንዲኖር ማድረጋቸው ለልጆቻቸው ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳየው እንዴት ነው?

6 በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ በመንፈሳዊ ጤናማ ሆነው እንዲቀጥሉ ትፈልጋላችሁ። አምላክም ልጆቻችሁን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” እንድታሳድጓቸው ይፈልጋል። (ኤፌ. 6:4) በመሆኑም አምላክ የሰጣችሁን ኃላፊነት ለመወጣት ቋሚ የሆነ መንፈሳዊ ፕሮግራም እንዲኖራችሁ አድርጉ። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ልጆቻችሁ ትምህርት መቅሰማቸው አስፈላጊ እንደሆነ ስለምታውቁና የመማር ፍቅር እንዲያዳብሩ ስለምትፈልጉ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ታደርጋላችሁ። በተመሳሳይም አፍቃሪ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በጉባኤ ስብሰባዎችና በሌሎች መንፈሳዊ ፕሮግራሞች አማካኝነት ከሚቀርበው ‘የይሖዋ ተግሣጽ’ እንዲጠቀሙ ጥረት ያደርጋሉ። መለኮታዊ ትምህርት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ልጆቻችሁ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር እንዲያድርባቸውና ጥበብን እንዲወዱ ለመርዳት ትጥራላችሁ። (ምሳሌ 24:14) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዳደረገው ሁሉ እናንተም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ የአምላክን ቃል የማስተማር ፍቅር እንዲያድርባቸውና በመስክ አገልግሎት ዘወትር እንዲካፈሉ በማገዝ በአገልግሎታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳት ትችላላችሁ።

7 ቤተሰባችሁ ቋሚ መንፈሳዊ ልማድ እንዲኖረው ማድረጋችሁ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁን የሚረዳቸው እንዴት ነው? በደቡብ አፍሪካ የምትኖረው ኤሪን እንዲህ ብላለች፦ “እኛ ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የስብሰባና የመስክ አገልግሎት ነገር ሲነሳ ብዙ ጊዜ እንነጫነጭና እናጉረመርም ነበር። አንዳንድ ጊዜ የቤተሰብ ጥናቱን የሚያስተጓጉል ነገር ሆን ብለን እናደርግ ነበር። ወላጆቻችን ግን ጥናቱ እንዲቋረጥ አይፈቅዱም። ይህን ሥልጠና ማግኘቴ በፕሮግራሜ እንድጸና ረድቶኛል። አሁን መንፈሳዊ ልማዴ ሲስተጓጎልብኝ፣ ሳልውል ሳላድር የድሮው ዓይነት መንፈሳዊ ፕሮግራም እንዲኖረኝ ለማድረግ እጓጓለሁ። ወላጆቼ መንፈሳዊ ፕሮግራማችንን በማክበር ረገድ ጥብቅ ባይሆኑ ኖሮ እንዲህ ዓይነት ጉጉት የሚኖረኝ አይመስለኝም። አቋማቸውን ቢያላሉ ኖሮ አሁን ከስብሰባዎች መቅረት ወይም ሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ችላ ማለት ቀላል ይሆንልኝ ነበር።”

ምሳሌ በመሆን ትሕትናን አስተምሯቸው

8. (ሀ) ኢየሱስ አቅሙ ውስን መሆኑን እንደሚገነዘብ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ትሑት መሆኑ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል?

8 ኢየሱስ ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም አቅሙ ውስን መሆኑን በመገንዘብና በይሖዋ እንደሚታመን በመግለጽ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ዮሐንስ 5:19ን አንብብ።) ኢየሱስ ትሑት መሆኑ ደቀ መዛሙርቱ ለእሱ ያላቸው አክብሮት እንዲቀንስ አድርጓል? በፍጹም። እንዲያውም በይሖዋ ይበልጥ በታመነ መጠን ደቀ መዛሙርቱም በእሱ ይበልጥ ታምነዋል። ከጊዜ በኋላም በትሕትና ረገድ የኢየሱስን አርዓያ ተከትለዋል።—ሥራ 3:12, 13, 16

9. በትሕትና ይቅርታ መጠየቃችሁና አቅማችሁ ውስን መሆኑን አምናችሁ መቀበላችሁ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በሚገኙ ልጆቻችሁ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

9 እኛም የተለያዩ የአቅም ገደቦች አሉብን፤ ከዚህም ሌላ ከኢየሱስ በተለየ ፍጹም ባለመሆናችን ስህተት እንሠራለን። በመሆኑም አቅማችሁ ውስን መሆኑን እንደምትገነዘቡ ግለጹ፤ እንዲሁም ስህተት ስትሠሩ ጥፋታችሁን እመኑ። (1 ዮሐ. 1:8) ደግሞም ይበልጥ የምታከብሩት ምን ዓይነት አለቃን ነው? ስህተት መሥራቱን አምኖ የሚቀበልን ወይስ ይቅርታ መጠየቅ የሚተናነቀውን? በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ለሠራችሁት ስህተት ይቅርታ ስትጠይቁ ሲመለከት ለእናንተ ያለው አክብሮት መጨመሩ አይቀርም። እሱም የሚሠራውን ስህተት አምኖ መቀበልን ሊማር ይችላል። ሦስት ልጆቿን ያሳደገች ሮዝሜሪ የተባለች እናት እንዲህ ብላለች፦ “ስህተት ስንሠራ ጥፋታችንን አምነን እንቀበላለን፤ ይህም ልጆቻችን ችግር ሲያጋጥማቸው በግልጽ እንዲነግሩን በር ከፍቶላቸዋል። አቅማችን ውስን መሆኑን በመገንዘብ፣ ልጆቻችን ለችግሮቻቸው ጥሩ መፍትሔ ማግኘት የሚችሉት ከየት እንደሆነ አስተምረናቸዋል። እርዳታ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን እንዲያነቡ እንጠቁማቸዋለን፤ እንዲሁም አብረናቸው እንጸልያለን።”

10. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ትእዛዝ ሲሰጥ ትሑት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ ተከታዮቹን የማዘዝ ሥልጣን ነበረው። ያም ቢሆን ብዙውን ጊዜ፣ ትእዛዝ የሰጠበትን ምክንያት በመግለጽ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ እንዲፈልጉ በመናገር ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ “እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል” ብሏቸዋል። “በሌሎች ላይ አትፍረዱ” ካለ በኋላም ምክንያቱን ሲገልጽ “በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል” ብሏል።—ማቴ. 6:31 እስከ 7:2

11. ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ወላጆች አንድ ዓይነት መመሪያ ወይም ውሳኔ ያስተላለፉበትን ምክንያት መግለጻቸው ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው?

11 እናንተም ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ፣ አንድ ዓይነት መመሪያ ወይም ውሳኔ ያስተላለፋችሁበትን ምክንያት ንገሯቸው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ ስለ ጉዳዩ ያላችሁ አመለካከት ግልጽ ከሆነለት ከልቡ ለመታዘዝ ሊነሳሳ ይችላል። የአራት ልጆች አባት የሆነው ባሪ እንዲህ ብሏል፦ “ምክንያታችሁን መግለጻችሁ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ እንዲተማመኑባችሁ ያደርጋል፤ ምክንያቱም ውሳኔ የምታደርጉት እንዳሰኛችሁ እንዳልሆነ ወይም ሐሳባችሁን ዝም ብላችሁ እንደማትለዋውጡ ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊ እንደሆናችሁ መመልከት ይችላሉ።” በተጨማሪም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ‘የማሰብ ችሎታቸውን’ ተጠቅመው ወደ ጉልምስና እያደጉ መሆኑን አስታውሱ። (ሮም 12:1) ባሪ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች በስሜት ሳይሆን በምክንያት ላይ የተመሠረተ ጥሩ ውሳኔ ማድረግን መማር አለባቸው” ብሏል። (መዝ. 119:34) በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ አንድን ውሳኔ ያደረጋችሁበትን ምክንያት በትሕትና ስትገልጹለት፣ ወደ ጉልምስና እያደገ መሆኑን እንደተገነዘባችሁ ማስተዋል ይችላል፤ እንዲሁም ‘የማሰብ ችሎታውን’ ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ ማድረግን ይማራል።

አስተዋይ በመሆን ልጆቻችሁን ለመረዳት ጥረት አድርጉ

12. ኢየሱስ ጴጥሮስን በማስተዋል የረዳው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ አስተዋይ በመሆን ደቀ መዛሙርቱ በየትኛው አቅጣጫ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቦ ነበር። ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን በራሱ ላይ እንዳይጨክን ይኸውም ራሱን ለሞት አሳልፎ እንዳይሰጥ የመከረው ለእሱ አስቦ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ የተናገረው ነገር የተሳሳተ አመለካከት እንዳለው የሚጠቁም መሆኑን አስተውሏል። ኢየሱስ ጴጥሮስንና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱን ለመጥቀም ሲል ግልጽ ምክር ሰጥቷል፤ ለራስ መሳሳት ምን እንደሚያስከትል የተናገረ ከመሆኑም ሌላ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚያስገኘውን በረከት ጠቁሟል። (ማቴ. 16:21-27) ጴጥሮስ ከዚህ ምክር ጥቅም እንዳገኘ ግልጽ ነው።—1 ጴጥ. 2:20, 21

13, 14. (ሀ) በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ እምነቱ እየተዳከመ እንዳለ የሚጠቁሙት የትኞቹ ነገሮች ናቸው? (ለ) ልጃችሁን ለመረዳትና የሚያስፈልገውን እርዳታ ለመስጠት አስተዋይ መሆናችሁ የሚረዳችሁ እንዴት ነው?

13 በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ በየትኛው አቅጣጫ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ለመረዳት የሚያስችል ማስተዋል እንዲሰጣችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። (መዝ. 32:8) ለምሳሌ የልጃችሁ እምነት እየተዳከመ እንደመጣ የሚጠቁሙ ነገሮች ምንድን ናቸው? ደስታው እየጠፋ እንደሆነ፣ የእምነት ባልንጀሮቹን መተቸት እንደጀመረ ወይም ድብቅ እየሆነ እንደመጣ አስተውላችሁ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ነገሮች ‘ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ሁለት ዓይነት ሕይወት እየመራ መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው’ ብላችሁ ለመደምደም አትቸኩሉ። * በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ምልክቶች በቸልታ አትለፏቸው፤ ወይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ራሱን ማግለሉ በዚህ ዕድሜ የሚያጋጥም የተለመደ ነገር እንደሆነ በማሰብ ሁኔታውን አቅልላችሁ አትመልከቱት።

ልጆቻችሁ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጓደኞች ማፍራት እንዲችሉ አጋጣሚውን አመቻቹላቸው (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

14 ልክ እንደ ኢየሱስ እናንተም ልጆቻችሁን ጥያቄ የምትጠይቋቸው በደግነትና በአክብሮት ይሁን። ከጉድጓድ ውኃ ስትቀዱ ባልዲውን በፍጥነት ካወጣችሁት የተወሰነው ውኃ እንደሚፈስ ሁሉ ልጃችሁ ስሜቱን እንዲነግራችሁ ማስገደድም ሐሳቡንና ፍላጎቱን ለማወቅ የሚያስችላችሁን ግሩም አጋጣሚ እንድታጡ ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 20:5ን አንብብ።) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኢላሪያ እንዲህ ብላለች፦ “በጉርምስና ዕድሜ ላይ እያለሁ በእውነት ጎዳና በመመላለስና አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች ጋር የበለጠ ጊዜ በማሳለፍ መሃል ልቤ ይዋልል ነበር። ከራሴ ጋር የማደርገው ይህ ትግል ፀባዬ እንዲቀየር አደረገ። ወላጆቼ ይህን ስለተመለከቱ አንድ ምሽት አነጋገሩኝ፤ ብዙም ደስተኛ አለመሆኔን እንዳስተዋሉ ከነገሩኝ በኋላ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ጠየቁኝ። እኔም ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፤ ከዚያም ሁኔታውን ከነገርኳቸው በኋላ እንዲረዱኝ ጠየቅኳቸው። እቅፍ አድርገው በማባበል ስሜቴን እንደተረዱልኝ ገለጹልኝ፤ እንዲሁም እንደሚረዱኝ ቃል ገቡልኝ።” የኢላሪያ ወላጆች አዲስና የተሻሉ ጓደኞች ከጉባኤ አባላት መካከል እንድታገኝ ወዲያውኑ ረዷት።

15. ኢየሱስ ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት አስተዋይ መሆኑን ያሳየው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

15 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ በየትኞቹ መስኮች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው፣ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ደግሞ ግሩም ባሕርይ እንዳላቸው በመገንዘብም አስተዋይ መሆኑን አሳይቷል። ለምሳሌ ናትናኤል የተባለ ሰው ኢየሱስ የመጣው ከናዝሬት እንደሆነ ሲሰማ “ደግሞ ከናዝሬት ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 1:46) ናትናኤል ከተናገረው ሐሳብ አንጻር ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ይሰማሃል? ነቃፊ? ጭፍን ጥላቻ ያለው? ወይስ እምነተ ቢስ? ኢየሱስ አስተዋይ በመሆን በናትናኤል ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ተመልክቷል። ናትናኤልን “ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ” በማለት ጠርቶታል። (ዮሐ. 1:47) ኢየሱስ ልብ የማንበብ ችሎታ ያለው ሲሆን ይህን ችሎታውን የሌሎችን መልካም ጎን ለመመልከት ተጠቅሞበታል።

16. በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ ጥሩ ባሕርያት እንዲያዳብር መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

16 እናንተ ልብ ማንበብ የማትችሉ ቢሆንም በአምላክ እርዳታ፣ በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ማስተዋል ትችላላችሁ። አስተዋይ በመሆን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ ያላቸውን መልካም ጎን ለመመልከት ትጥራላችሁ? ማንም ቢሆን “ችግር ፈጣሪ” የሚል ስም እንዲሰጠው አይፈልግም። እናንተም ስለ ልጃችሁ ያላችሁ አመለካከትና የምትናገሩት ነገር ልጁን እንደ “ዓመፀኛ” ወይም “አስቸጋሪ” አድርጋችሁ እንደምትመለከቱት የሚያሳይ እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ልጃችሁ ጥፋት ቢሠራም እንኳ ያሉትን መልካም ባሕርያት እንደምታውቁና ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ከልቡ የሚፈልግ መሆኑን እንደምትገነዘቡ ንገሩት። ለውጥና መሻሻል እያደረገ እንዳለ የሚጠቁም ነገር ስትመለከቱ አመስግኑት። የሚቻል ከሆነ ተጨማሪ ኃላፊነት በመስጠት ያሉትን መልካም ባሕርያት እንዲያዳብር እርዱት። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተያያዘ እንዲህ አድርጓል። ኢየሱስ ከናትናኤል (በርቶሎሜዎስ ተብሎም ይጠራል) ጋር ከተገናኘ ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ ናትናኤልን ሐዋርያ አድርጎ የመረጠው ሲሆን እሱም ቀናተኛ ክርስቲያን መሆኑን አስመሥክሯል። (ሉቃስ 6:13, 14፤ ሥራ 1:13, 14) ልጃችሁን ማመስገናችሁና ማበረታታታችሁ ልጁ የሚጠበቅበትን የማያሟላ ሰው እንዳልሆነ እንዲገነዘብ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ሊጠቀምበት የሚችል ብቁ ክርስቲያን እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል።

ወደር የሌለው ደስታ የሚያስገኝ ሥልጠና

17, 18. በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆኑ ያለመታከት ጥረት ማድረጋችሁ ምን ውጤት ያስገኛል?

17 ልጆቻችሁን በምታሳድጉበት ጊዜ የብዙ ሰዎች መንፈሳዊ አባት እንደሆነው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ይሰማችሁ ይሆናል። ጳውሎስ ልቡ “በብዙ መከራና ጭንቀት” እንደተዋጠ የገለጸበት ወቅት ነበር፤ ይህ የሆነው በቆሮንቶስ ላሉት መንፈሳዊ ልጆቹ “ጥልቅ ፍቅር” ስለነበረው ነው። (2 ቆሮ. 2:4፤ 1 ቆሮ. 4:15) የሁለት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጅ አባት የሆነው ቪክተር እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያሉ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ነበሩ። ሆኖም ካጋጠሙን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይልቅ የሚያመዝነው ያሳለፍነው መልካም ጊዜ ነው። በይሖዋ እርዳታ፣ ከልጆቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ችለናል።”

18 ልጆቻችሁ የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆኑ ለመርዳት ያለመታከት ጥረት ማድረጋችሁን ቀጥሉ። ለልጆቻችሁ ጥልቅ ፍቅር እንዳላችሁ የምታሳዩአቸው ከሆነ እውነትን የራሳቸው ሲያደርጉና ‘በእውነት ውስጥ የሚመላለሱ’ መንፈሳዊ ልጆች ሲሆኑ መመልከት የሚያስገኘውን ወደር የሌለው ደስታ ታጣጥማላችሁ።—3 ዮሐ. 4

^ አን.1 ይህ የጥናት ርዕስ ወላጆች፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲያገለግሉ መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ያብራራል።