በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለመጠበቂያ ግንብ አንባቢያን

ለመጠበቂያ ግንብ አንባቢያን

ለመጠበቂያ ግንብ አንባቢያን

ከዚህ እትም ጀምሮ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ አንዳንድ ለውጦች መደረጋቸውን ስንነግራችሁ ደስ ይለናል። የተደረጉትን ለውጦች ከመግለጻችን በፊት ማስተካከያ ያልተደረገባቸውን ነገሮች እስቲ እንመልከት።

የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የሚለው የዚህ መጽሔት ስም አይለወጥም። በመሆኑም መጠበቂያ ግንብ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማክበሩን እንዲሁም አንባቢዎቹ በአምላክ መንግሥት ምሥራች እንዲጽናኑ መርዳቱን ይቀጥላል። በዚህ መጽሔት ከገጽ 5 እስከ 9 ላይ የወጡት ርዕሶች የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነና መቼ እንደሚመጣ ያብራራሉ። ከዚህም በተጨማሪ መጠበቂያ ግንብ ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት ሲያደርግ እንደነበረው፣ አንባቢዎቹ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ከመርዳቱም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መደገፉን ይቀጥላል፤ እንዲሁም ይህ መጽሔት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተጠቀሱት ትንቢቶች በመጠቀም ሰዎች በዓለም ላይ የሚከናወኑት ሁኔታዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው እንዲገነዘቡ ይረዳል።

የተደረጉት ለውጦችስ ምንድን ናቸው? በወሩ መጀመሪያ በሚወጣው እትም ላይ የሚገኙትን አንዳንድ አስደሳች ዓምዶች እንመልከት። *

ይህ መጽሔት ሰዎች ስለተለያዩ ጉዳዮች በቁም ነገር እንዲያስቡ የሚያበረታቱ በርካታ ርዕሶችን በየወሩ ይዞ ይወጣል። “ይህን ያውቁ ኖራል?” የሚለው ዓምድ ስለ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳል። “ወደ አምላክ ቅረብ” የሚለው ዓምድ ደግሞ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምሩን ያብራራል። “አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ” የሚለው ዓምድ ሰዎች ብዙ ጊዜ ለሚያቀርቧቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ለአብነት ያህል፣ ብዙ ሰዎች “የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በልብህ ውስጥ ነው?” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። የዚህን ጥያቄ መልስ በገጽ 13 ላይ ታገኛለህ።

ቤተሰቦችን የሚጠቅሙ በርካታ ቋሚ ዓምዶችም አሉ። “ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?” የሚለው ዓምድ በዓመት አራት ጊዜ የሚወጣ ሲሆን በገሃዱ ዓለም በቤተሰብ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን ያነሳል፤ ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እንዴት እንደሚረዱ ያብራራል። “ልጆቻችሁን አስተምሩ” የሚለው ዓምድ በሁለት ወር አንዴ የሚወጣ ሲሆን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሆነው እንዲያነቡት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ይህ ዓምድ በማይወጣባቸው ወራት ደግሞ ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምርምር እንዲያደርጉ የሚያበረታታ “ለወጣት አንባቢያን” የሚል ዓምድ ይወጣል።

በዓመት አራት ጊዜ የሚወጡ ሌሎች ተጨማሪ ዓምዶችም ይኖራሉ። “በእምነታቸው ምሰሏቸው” የሚለው ዓምድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ የአንድ ግለሰብ ምሳሌ እንድንከተል ያበረታታናል። ለአብነት ያህል፣ በዚህ መጽሔት ከገጽ 18 እስከ 21 ላይ ስለ ነቢዩ ኤልያስ የሚገልጽ ልብ የሚነካ ዘገባ የሚገኝ ሲሆን እምነቱን መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነም እንማራለን። “ከ . . . የተላከ ደብዳቤ” የሚለው ዓምድ በተለያየ የዓለም ክፍል ከሚኖሩ ሚስዮናውያንና ሌሎች ሰዎች የተገኙ ዘገባዎችን ያቀርባል። “ከኢየሱስ ምን እንማራለን?” የሚለው ዓምድ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ቀለል ባለ መልኩ ያብራራል።

መጠበቂያ ግንብ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ያላቸውና ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚሹ ሰዎችን ፍላጎት ማሟላቱን እንደሚቀጥል እንተማመናለን። ይህ መጽሔት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማወቅ ያለህን ፍላጎት እንደሚያረካልህ ተስፋ እናደርጋለን።

አዘጋጆቹ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ከዚህ ወር ጀምሮ መጠበቂያ ግንብ በሁለት እትሞች ይዘጋጃል። የወሩ የመጀመሪያው እትም ለሁሉም ሰው የሚዘጋጅ ነው። የወሩ ሁለተኛው እትም ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤ ስብሰባዎቻቸው ላይ የሚጠቀሙበት የጥናት እትም ነው፤ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ማንኛውም ሰው መገኘት ይችላል።