በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በወጣትነቴ ካጋጠመኝ ተስፋ መቁረጥ እፎይታ አገኘሁ

በወጣትነቴ ካጋጠመኝ ተስፋ መቁረጥ እፎይታ አገኘሁ

በወጣትነቴ ካጋጠመኝ ተስፋ መቁረጥ እፎይታ አገኘሁ

ኤውሴቢዮ ሞርሲዮ እንደተናገረው

በመስከረም ወር 1993 ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት ወኅኒ ቤት ሄጄ ነበር። ወደዚያ የሄድኩት ታናሽ እህቴ ማሪቪ ትጠመቅ ስለነበር ነው። አንዳንድ የሕግ ታራሚዎችና የወኅኒ ቤቱ ባለ ሥልጣናት የጥምቀት ሥነ ሥርዓቱን ሳከናውን በአክብሮት ይከታተሉ ነበር። እኔም ሆንኩ ማሪቪ እዚያ ልንገኝ የቻልነው ለምን እንደሆነ ከመግለጼ በፊት እስቲ ስለ ልጅነት ሕይወታችን ላውጋችሁ።

የተወለድኩት ግንቦት 5, 1954 ስፔን ውስጥ ሲሆን በቤተሰባችን ውስጥ ካሉት ስምንት ልጆች የመጀመሪያው ነኝ። ማሪቪ ደግሞ ሦስተኛ ልጅ ናት። አያታችን ቀናተኛ ካቶሊኮች እንድንሆን አድርጋ አሳድጋናለች፤ ከእሷ ጋር በነበርኩበት ወቅት ለአምላክ ፍቅር እንዳለኝ ይሰማኝ ስለነበር አስደሳች የልጅነት ትዝታዎች አሉኝ። በወላጆቼ ቤት ውስጥ ግን አምላካዊ ፍርሃት አልነበረም። አባቴ እናቴንም ሆነ እኛን ልጆቹን ሁልጊዜ ይደበድበን ነበር። ፍርሃት የሕይወታችን ክፍል ሆኖ ነበር፤ የእናቴን ሥቃይ መመልከት በጣም ያሠቃየኝ ነበር።

በትምህርት ቤት ደግሞ ሌሎች ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ያጋጥሙኝ ነበር። ቄስ የሆነው አንዱ አስተማሪያችን የተሳሳተ መልስ ከመለስን ጭንቅላታችንን ከግድግዳ ጋር ያጋጨዋል። ሌላው ቄስ ደግሞ የተማሪዎችን የቤት ሥራ በሚያርምበት ጊዜ ተማሪዎቹን በጾታ ያስነውራቸዋል። ከዚህም በላይ እንደ ሲኦል እሳት ያሉት የካቶሊክ ትምህርቶች ግራ ያጋቡኝና ያስፈሩኝ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ለአምላክ የነበረኝ ፍቅር እየቀዘቀዘ ሄደ።

ትርጉም የሌለው ሕይወት

መንፈሳዊ መመሪያ ባለማግኘቴ በጭፈራ ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ ምግባረ ብልሹና ዓመጸኛ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ጀመርኩ። በእነዚህ ቦታዎች ብዙውን ጊዜ ጠብ የሚነሳ ሲሆን በጩቤ፣ በሰንሰለት፣ በጠርሙስ እንዲሁም በወንበር ይደባደቡ ነበር። እንደነዚህ ባሉት ድብድቦች ባልካፈልም በአንድ ወቅት በጠቡ መሃል በመመታቴ ራሴን ስቼ ነበር።

ከጊዜ በኋላ ግን በእነዚህ ቦታዎች የማየው ሁኔታ እየሰለቸኝ ስለመጣ ግርግር ያልበዛባቸው ጭፈራ ቤቶች መፈለግ ጀመርኩ። እዚያም ቢሆን አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድ የተለመደ ነበር። ሆኖም እነዚህ ዕፆች ደስታና የአእምሮ ሰላም ከመስጠት ይልቅ በቅዠት ዓለም ውስጥ እንድገባና እንድጨነቅ ያደርጉኝ ነበር።

በሕይወቴ ደስተኛ ባልሆንም እንኳ ታናሽ ወንድሜ ሆሴ ሉዊስና የቅርብ ጓደኛዬ ሚጌል እንዲህ ዓይነት ሕይወት ውስጥ እንዲገቡ አደረግኳቸው። በዚያን ወቅት በስፔን እንደነበሩት በርካታ ወጣቶች ሁሉ እኛም በሥነ ምግባር ባዘቀጠ አኗኗር ውስጥ ተዘፈቅን። ዕፅ ለመግዛት የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ስል ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አልልም ነበር። ክብሬን አጥቼ ነበር።

ይሖዋ ገላገለኝ

በዚህ ወቅት ስለ አምላክ መኖርና ስለ ሕይወት ትርጉም ከጓደኞቼ ጋር ብዙ ጊዜ አወራ ነበር። ስለ አምላክ ለማወቅ ስል ሐሳቤን የማካፍለው ሰው መፈለግ ጀመርኩ። ከሥራ ባልደረቦቼ መካከል ፍራንዚስኮ የተባለው ሰው ከሌሎቹ የተለየ እንደሆነ አስተዋልኩ። ይህ ሰው ደስተኛ፣ ታማኝና ደግ ስለመሰለኝ ለእሱ የልቤን ላጫውተው ወሰንኩ። ፍራንዚስኮ የይሖዋ ምሥክር ሲሆን ስለ አደንዛዥ ዕፆች የሚያወሳ ርዕስ የያዘ መጠበቂያ ግንብ ሰጠኝ።

መጽሔቱን ካነበብኩ በኋላ አምላክ እንዲረዳኝ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ:- “ጌታ ሆይ፣ አንተ እንዳለህ አውቃለሁ። አንተን ለማወቅና ፈቃድህን ለማድረግ እፈልጋለሁ። እባክህ እርዳኝ!” ፍራንዚስኮና ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመው ያበረታቱኝ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ይሰጡኝ ነበር። አምላክ እንዲረዳኝ ያቀረብኩት ጸሎት በእነዚህ ሰዎች አማካኝነት መልስ እያገኘ እንዳለ ተገነዘብኩ። ብዙም ሳይቆይ የምማራቸውን ነገሮች ለጓደኞቼና ለሆሴ ሉዊስ መናገር ጀመርኩ።

አንድ ቀን ከጓደኞቼ ጋር የሮክ የሙዚቃ ዝግጅት ከሚታይበት ቦታ እየወጣን እያለ ከቡድኑ ነጠል ብዬ ጓደኞቼን ተመለከትኳቸው። በዚህ ጊዜ ዕፅ መውሰዳችን ምግባራችንን ምን ያህል አሳፋሪ እንዳደረገው ተገነዘብኩ። በዚያች ቅጽበት ይህን ዓይነቱን አካሄድ ለመተውና የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወሰንኩ።

ፍራንዚስኮ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት፤ እሱም መጽሐፍ ቅዱስና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት * የተባለውን መጽሐፍ ሰጠኝ። አምላክ እንባን ሁሉ እንደሚያብስና ሞትን እንኳ እንደሚያስቀር የገባውን ቃል ሳነብ የሰው ልጆችን ነፃ የሚያወጣውን እውነት እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ። (ዮሐንስ 8:32፤ ራእይ 21:4) ከጊዜ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። በዚያ የተመለከትኩት ሞቅ ያለ ወዳጃዊ አቀባበልና ፍቅር በጥልቅ ነካኝ።

በመንግሥት አዳራሽ የተመለከትኩትን ነገር ለሌሎች ለመናገር በጣም ስለጓጓሁ ሆሴ ሉዊስንና ጓደኞቼን ወዲያው ሰብስቤ ሁሉንም ነገር ነገርኳቸው። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሁላችንም በስብሰባ ላይ ተገኘን። በስብሰባው ላይ ከፊታችን የተቀመጠች አንዲት ወጣት ዞር ብላ ተመለከተችን። ረጃጅም ፀጉር ያላቸው ሂፒዎች ስትመለከት እንደፈራች ያስታውቅባት ነበር፤ ከዚያ በኋላ ወደ እኛ አልዞረችም። ይህች ወጣት በሳምንቱ፣ ሙሉ ልብስ ለብሰንና ክራቫት አስረን ወደ መንግሥት አዳራሹ ስንመጣ ሳትገረም አልቀረችም።

ብዙም ሳይቆይ እኔና ሚጌል በይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ ተገኘን። ከዚያ በፊት በሁሉም የዕድሜ ክልል በሚገኙ ሰዎች መካከል እንደዚህ ያለ እውነተኛ ወንድማማችነት አይተን አናውቅም ነበር። የሚገርመው ደግሞ ስብሰባው የተደረገው የሮክ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ በተገኘንበት ቲያትር ቤት ነበር። በዚህ ጊዜ ግን የነበረው ሁኔታም ሆነ ሙዚቃ መንፈስን የሚያድስ ነበር።

ሁሉም የቡድናችን አባላት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ከስምንት ወራት ገደማ በኋላ ሐምሌ 26, 1974 እኔና ሚጌል ተጠመቅን። በዚህ ጊዜ ሁለታችንም 20 ዓመታችን ነበር። ከቡድናችን ውስጥ አራቱ ደግሞ ከጥቂት ወራት በኋላ ተጠመቁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት ሥልጠና ታጋሽ የሆነችውን እናቴን በቤት ሥራዎች እንዳግዛትና ስለ አዲሱ እምነቴ እንድነግራት አነሳሳኝ። ይህም ከእናቴ ጋር እንድንቀራረብ አደረገን። ከዚህም በላይ ታናናሽ ወንድሞቼንና እህቶቼን ለመርዳት ከእነሱ ጋር የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ ጀመርኩ።

ከጊዜ በኋላ፣ ከአንድ ወንድሜ በስተቀር ሁሉም ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አውቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። መጀመሪያ ወደ መንግሥት አዳራሽ የሄድን ቀን በግርምት ካየችን ሶሌዳድ ከተባለችው ወጣት ጋር በ1977 ተጋባን። በጥቂት ወራት ውስጥ ሁለታችንም አቅኚዎች (ሙሉ ጊዜያቸውን የምሥራቹን በመስበክ የሚያሳልፉ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆንን።

የምወዳት እህቴም ነፃ ወጣች

ታናሽ እህቴ ማሪቪ በልጅነቷ በጾታ በመነወሯ ይህ ዘግናኝ ሁኔታ በሕይወቷ ላይ ትልቅ ጠባሳ ትቶ ነበር። ማሪቪ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለች ዕፅ በመውሰድና በመስረቅ እንዲሁም ሴተኛ አዳሪ በመሆን በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ሕይወት መምራት ጀመረች። በ23 ዓመቷ እስር ቤት የገባች ሲሆን እዚያም በመጥፎ አኗኗሯ ቀጠለች።

በዚያ ወቅት የወረዳ የበላይ ተመልካች (ከቦታ ወደ ቦታ እየተጓዘ የሚያገለግል የይሖዋ ምሥክር) ነበርኩ። በ1989 እኔና ሶሌዳድ፣ ማሪቪ በታሰረችበት አካባቢ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያን ጊዜ ባለ ሥልጣናቱ ልጇን ስለወሰዱባት በጣም ተስፋ ቆርጣና መኖር አስጠልቷት ነበር። አንድ ቀን ወደ እስር ቤቱ ሄድኩና መጽሐፍ ቅዱስን አብረን እንድናጠና ጠየቅኳት፤ እሷም በሐሳቡ ተስማማች። ማሪቪ ለአንድ ወር ካጠናች በኋላ ዕፅ መውሰድም ሆነ ሲጋራ ማጨስ አቆመች። በሕይወቷ ውስጥ እነዚህን ለውጦች እንድታደርግ ይሖዋ እንደረዳት መመልከቴ በጣም አስደስቶኛል።—ዕብራውያን 4:12

ማሪቪ፣ ማጥናት ከጀመረች ከጥቂት ጊዜ በኋላ አብረዋት ለታሰሩት ሰዎችና ለወኅኒ ቤቱ ባለ ሥልጣናት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መስበክ ጀመረች። በየጊዜው ወደተለያዩ እስር ቤቶች ትዘዋወር የነበረ ቢሆንም መስበኳን ቀጠለች። እንዲያውም በአንድ ወኅኒ ቤት ውስጥ ከክፍል ወደ ክፍል እየሄደች ሰብካለች። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ማሪቪ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ እስረኞችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀምራቸዋለች።

አንድ ቀን፣ ማሪቪ ሕይወቷን ለይሖዋ ወስና መጠመቅ እንደምትፈልግ ነገረችኝ። ሆኖም ከእስር ቤቱ መውጣት የማትችል ከመሆኑም በላይ ማንም ወደ ውስጥ ገብቶ እንዲያጠምቃት አልተፈቀደም። በመሆኑም ምግባረ ብልሹ ሰዎች ባሉበት በዚያ ወኅኒ ቤት ውስጥ ለአራት ተጨማሪ ዓመታት መቆየት ነበረባት። በዚያ ወቅት በእምነቷ እንድትጸና የረዳት ምን ነበር? በወኅኒ ቤቱ አካባቢ የሚገኘው ጉባኤ ስብሰባ በሚያደርግበት ሰዓት እሷም እስር ቤት ሆና በስብሰባው ላይ የሚሰጠውን ትምህርት ታነባለች። ከዚህም በላይ ቋሚ የሆነ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የጸሎት ፕሮግራም ነበራት።

ከጊዜ በኋላ ማሪቪ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት እስር ቤት ተዛወረች። ወኅኒ ቤቱ የመዋኛ ገንዳ ስለነበረው ማሪቪ በዚህ ቦታ መጠመቅ እንደምትችል ተሰማት። እንዳሰበችውም ለመጠመቅ ፈቃድ አገኘች። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የጥምቀት ንግግር ልሰጣት የቻልኩት በዚህ ምክንያት ነበር። በሕይወቷ ውስጥ ትልቅ ቦታ በምትሰጠው በዚህ ወቅት አብሬያት ነበርኩ።

ማሪቪ በቀድሞ አኗኗሯ ምክንያት ኤድስ ይዟት ነበር። በእስር ቤቱ ውስጥ በነበራት መልካም ምግባር የተነሳ የተፈረደባትን ጊዜ ሳትጨርስ መጋቢት 1994 ተለቀቀች። ከሁለት ዓመታት በኋላ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ከእናታችን ጋር የኖረች ሲሆን ቀናተኛ ክርስቲያን ነበረች።

አፍራሽ አመለካከትን መቋቋም

የቀድሞው ሕይወቴ በእኔም ላይ ያስከተለው ጠባሳ ነበር። አባቴ ያደረሰብኝ በደል እንዲሁም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት እከተለው የነበረው አኗኗር በባሕርዬ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ትልቅ ሰው ከሆንኩ በኋላ ብዙ ጊዜ የጥፋተኝነትና የከንቱነት ስሜት ያሠቃየኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በጣም ተስፋ እቆርጣለሁ። ሆኖም የአምላክ ቃል እነዚህን አፍራሽ ስሜቶች እንድቋቋም ከፍተኛ እርዳታ አድርጎልኛል። ባለፉት በርካታ ዓመታት እንደ ኢሳይያስ 1:18 እና መዝሙር 103:8-13 ባሉት ጥቅሶች ላይ አዘውትሬ ማሰላሰሌ በተደጋጋሚ የሚረብሸኝ የጥፋተኝነት ስሜት ቀስ በቀስ እንዲቀንስልኝ ረድቶኛል።

ከከንቱነት ስሜት ጋር በማደርገው ትግል የረዳኝ ሌላው መንፈሳዊ መሣሪያ ደግሞ ጸሎት ነው። ብዙ ጊዜ እያነባሁ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። በ1 ዮሐንስ 3:19, 20 ላይ የሚገኘው የሚከተለው ሐሳብ አበረታቶኛል:- “እኛ የእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፣ ይህም ልባችን በእኛ ላይ በሚፈርድብን ነገር ሁሉ ነው። እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉን ነገር ያውቃል።”

ወደ አምላክ የምጸልየው ‘በተሰበረና በተዋረደ’ ልብ በመሆኑ ቀደም ሲል አስብ የነበረውን ያህል መጥፎ ሰው እንዳልሆንኩ ተገንዝቤያለሁ። ይሖዋን የሚፈልጉት ሁሉ፣ በቀድሞ አኗኗራቸው ከልብ ተጸጽተው የእሱን ፈቃድ ለማድረግ ከተመለሱ ይሖዋ እንደማይንቃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል።—መዝሙር 51:17

በራስ ያለመተማመን ስሜት ሲያድርብኝ በፊልጵስዩስ 4:8 ላይ እንደተገለጹት ያሉትን መንፈሳዊ ሐሳቦችን ወደ አእምሮዬ በማምጣት አዎንታዊ ነገሮችን አስባለሁ። መዝሙር 23⁠ንና የተራራውን ስብከት በቃሌ አጥንቻቸዋለሁ። አፍራሽ ሐሳቦች ወደ አእምሮዬ ሲመጡ እነዚህን ጥቅሶች በቃሌ እደግማቸዋለሁ። በተለይ እንቅልፍ በማጣባቸው ሌሊቶች በዚህ መንገድ አእምሮዬን አፍራሽ ከሆኑ ሐሳቦች ማጽዳቴ ረድቶኛል።

ሌላው የእርዳታ ምንጭ ደግሞ ባለቤቴና ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚሰጡኝ ማበረታቻ ነው። መጀመሪያ ላይ፣ የሚሰጡኝን ማበረታቻ መቀበል ይከብደኝ የነበረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍቅር ሁሉን እንደሚያምን’ እንድገነዘብ ረድቶኛል። (1 ቆሮንቶስ 13:7 የ1954 ትርጉም) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ደግሞ ድክመቶቼንና የአቅም ገደቦቼን በትሕትና መቀበልን ተምሬያለሁ።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ አፍራሽ ከሆኑ ስሜቶች ጋር የምታገል መሆኔ የሌሎች ስሜት የሚገባኝ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ለመሆን አስችሎኛል። እኔና ባለቤቴ እያንዳንዳችን ምሥራቹን ሙሉ ጊዜ በመስበክ ወደ 30 የሚጠጉ ዓመታት አሳልፈናል። ሌሎችን በማገልገል የማገኘው ደስታ፣ አፍራሽ በሆኑ ሐሳቦችና በቀድሞ መጥፎ አኗኗሬ ትውስታዎች እንዳልረበሽ ይረዳኛል።

ይሖዋ አትረፍርፎ የሰጠኝን በረከት ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ እንደሚከተለው ብሎ እንደተናገረው መዝሙራዊ ለማለት እገፋፋለሁ:- “ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ . . . ኀጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፣ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፣ ሕይወትሽን ከጥፋት ጕድጓድ የሚያድን፣ ምሕረትንና ርኅራኄን የሚያቀዳጅሽ።”—መዝሙር 103:1-4

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ብዙ ጊዜ የጥፋተኝነትና የከንቱነት ስሜት ያሠቃየኝ ነበር። ሆኖም የአምላክ ቃል እነዚህን አፍራሽ ስሜቶች እንድቋቋም ከፍተኛ እርዳታ አድርጎልኛል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድሜ ሆሴ ሉዊስና ጓደኛዬ ሚጌል መጥፎም ሆነ መልካም ምሳሌዬን ተከትለዋል

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሞርሲዮ ቤተሰብ በ1973

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሪቪ እስረኛ እያለች

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከሶሌዳድ ጋር