በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች የሚያቀርቡት ጥያቄ
በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች የሚያቀርቡት ጥያቄ
ስለ አንድ ጉዳይ የሚጠይቁ በመቶ ሚሊዮኖች እንዲያውም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። እነዚህ ሰዎች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ለአንድ ጥያቄ መልስ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ነው። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ስለሚጠይቁት ነገር የሚያውቁት በጣም ጥቂቶች ናቸው። እንዲህ ያለ ነገር በእርግጥ ሊያጋጥም ይችላል? አዎን፣ ይህ ሁኔታ በየዕለቱ ይፈጸማል። እነዚህ ሁሉ ሰዎች እንዲከናወን የሚጠይቁት ነገር ምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ እየጠየቁ ነው!
በዓለም ዙሪያ ክርስቲያን እንደሆኑና ኢየሱስ ክርስቶስ መሪያቸው መሆኑን የሚናገሩ 37,000 የሚያህሉ ሃይማኖቶች እንዳሉ ይገመታል። እነዚህ ሃይማኖቶች ከሁለት ቢሊዮን በላይ ተከታዮች አሏቸው። አብዛኞቹ፣ አባታችን ሆይ ወይም አቡነ ዘበሰማያት ተብሎ የሚጠራውን ጸሎት ይጸልያሉ። አንተስ ይህን ጸሎት ታውቀዋለህ? ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንዳስተማረው ጸሎቱ እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን።”—ማቴዎስ 6:9, 10
በርካታ አማኞች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይህን ጸሎት በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ሲደግሙ ኖረዋል። ከዚህም በላይ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ጊዜ በቤተሰብ አንድ ላይ ሲሰባሰቡ እንዲሁም ለብቻቸው ሆነው ይህን ጸሎት በቃላቸው ይደግሙታል። ጸሎቱን የሚያቀርቡት ከልብ በመነጨ ስሜት ነው። ሌሎች ብዙዎች ደግሞ ጸሎቱን በቃላቸው ስላጠኑት ለትርጉሙ እምብዛም ትኩረት ሳይሰጡ ያነበንቡታል። ይሁን እንጂ የአምላክ መንግሥት እንደሚመጣ ተስፋ የሚያደርጉትና እንዲመጣ የሚጸልዩት እነዚህ የሕዝበ ክርስትና አባላት ብቻ አይደሉም።
ክርስቲያን ያልሆኑ ሃይማኖቶችም የሚያቀርቡት ጸሎት
በአይሁድ እምነት ውስጥ የሐዘንተኛ ካዲሽ የተባለ የታወቀ ጸሎት አለ። ይህ ጸሎት ስለ ሞት ወይም ስለ ሐዘን በቀጥታ ባይጠቅስም ብዙውን ጊዜ በሐዘን ወቅት ይደገማል። ጸሎቱ እንዲህ ይላል:- “[አምላክ] መንግሥቱን በአንተ የሕይወት ዘመን ያቋቁም . . . እንዲያውም ይህን በፍጥነት ያድርገው።” * ሌላ ጥንታዊ የምኩራብ ጸሎት ደግሞ ከዳዊት ቤት የሚመጣው መሲሕ የሚገዛበትን መንግሥት በተመለከተ ስለተሰጠው ተስፋ ይገልጻል።
ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ሐሳብ ክርስቲያን ያልሆኑ ሃይማኖቶችንም ትኩረት ስቧል። ዘ ታይምስ ኦቭ ኢንዲያ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው በ19ኛው መቶ ዘመን የነበሩ እንዲሁም በሂንዱ፣ በእስልምና ብሎም በክርስትና እምነቶች መካከል የጋራ ነጥቦች ለማግኘት የሚጥሩ አንድ የታወቁ ህንዳዊ የሃይማኖት መሪ እንዲህ ብለዋል:- “ምሥራቅና ምዕራብ አንድ እስካልሆኑ ድረስ እውነተኛው የአምላክ መንግሥት እውን ሊሆን አይችልም።” በስትራትፊልድ፣ አውስትራሊያ የሚገኝ የእስልምና ኮሌጅ ዋና ኃላፊ የሆኑ አንዲት ሴት በቅርቡ ለአንድ ጋዜጣ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “እንደ ማንኛውም ሙስሊም ሁሉ እኔም፣ ኢየሱስ እንደሚመለስና እውነተኛውን የአምላክ መንግሥት እንደሚያቋቁም አምናለሁ።”
የአምላክን መንግሥት ተስፋ የሚያደርጉና ስለዚህ መንግሥት የሚጸልዩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ የሚከተለውን አስገራሚ እውነታ ልብ በል።
ይህን መጽሔት የምናዘጋጀው እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንደምናወያይ ታውቅ ይሆናል። ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ በዓለም ዙሪያ በ236 አገሮችና ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይህን እያደረግን ሲሆን የስብከታችን ዋና ጭብጥም የአምላክ መንግሥት ነው። የዚህ መጽሔት ሙሉ ስም የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ እንደሚል ልብ በል። ስለዚህ መንግሥት ይጸልዩ እንደሆነ ብዙውን ጊዜ ሰዎችን እንጠይቃቸዋለን። በርካታ ሰዎችም እንዲህ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። ሆኖም የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነ ስንጠይቃቸው ብዙዎች የሚሰጡት መልስ ስለዚህ መንግሥት እንደማያውቁ የሚያሳይ ነው፤ ወይም ደግሞ መልሳቸው የተድበሰበሰና ስለ ጉዳዩ እርግጠኞች እንዳልሆኑ የሚጠቁም ነው።
ታዲያ በርካታ ሰዎች መግለጽ ስለማይችሉት ነገር የሚጸልዩት ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ውስብስብና ግልጽ ያልሆነ ሐሳብ በመሆኑ ነው? አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ መንግሥት ግልጽ የሆነና የተሟላ ማብራሪያ ይሰጣል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው መልእክት ጨለማ በዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ እውነተኛ ተስፋ ይፈነጥቃል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ተስፋ እንዴት እንደሚያብራራው እንመለከታለን። ከዚያም ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ያቀረበው ጸሎት ምላሽ የሚያገኘው መቼ እንደሆነ እናያለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.6 ኢየሱስ እንደሰጠው የናሙና ጸሎት ሁሉ የሐዘንተኛ ካዲሽ የተባለው ጸሎትም የአምላክ ስም እንዲቀደስ ይጠይቃል። ይህ ጸሎት በክርስቶስ ዘመን እንዲያውም ከዚያ ቀደም ብሎ የነበረ ስለመሆኑ ውዝግብ ቢኖርም ኢየሱስ ከሰጠው የናሙና ጸሎት ጋር መመሳሰሉ ሊያስገርመን አይገባም። ኢየሱስ የሰጠው ጸሎት አዲስና የተለየ ሐሳብ የያዘ አልነበረም። በጸሎቱ ውስጥ የተካተተው እያንዳንዱ ልመና ሁሉም አይሁዳውያን በወቅቱ በነበሯቸው ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተ ነበር። ኢየሱስ፣ አይሁዳውያኑ እሱ ከመምጣቱ በፊት ሊጸልዩለት ይገባ የነበረውን ነገር እንዲለምኑ ማበረታታቱ ነበር።