በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤተሰባችሁን ‘ባማሩ ቃላት’ የምታንጹ ሁኑ

ቤተሰባችሁን ‘ባማሩ ቃላት’ የምታንጹ ሁኑ

ቤተሰባችሁን ‘ባማሩ ቃላት’ የምታንጹ ሁኑ

ደቂቃዎች ባለፉ ቁጥር ዴቪድ ይበልጥ እየተበሳጨ ነው። መኪናው ውስጥ ቁጭ ብሎ ባለቤቱን እየጠበቀ በተደጋጋሚ ሰዓቱን ይመለከታል። በመጨረሻም ባለቤቱ ዳያን ከቤት ስትወጣ ንዴቱን መቆጣጠር አልቻለም።

“እንዴት ይህን ያህል ታስጠብቂኛለሽ?” በማለት ጮኸባት። “ሁልጊዜ እንዳረፈድሽ ነው! አንድ ቀን እንኳ በሰዓቱ ብትወጪ ምናለበት?” አላት።

ዳያን በዴቪድ ንግግር በጣም ስለተሰማት እንባዋን መቆጣጠር አቅቷት እየሮጠች ተመልሳ ወደ ቤት ገባች። በዚያች ቅጽበት ዴቪድ እንደተሳሳተ ተገነዘበ። በቁጣ ገንፍሎ መናገሩ ሁኔታውን ከማባባስ ውጪ ምንም የፈየደው ነገር አልነበረም። ታዲያ አሁን ምን ማድረግ ይችላል? የመኪናውን ሞተር አጥፍቶ በረጅሙ ከተነፈሰ በኋላ በዝግታ ሚስቱን ተከትሎ ወደ ቤት ገባ።

ይህ ምሳሌ በገሃዱ ዓለም ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ ነው ቢባል አትስማማም? አንድ ነገር ከተናገርክ በኋላ ‘ምነው ምላሴን በቆረጠው’ ብለህ ታውቃለህ? ብዙውን ጊዜ ሳናስበው አንድ ነገር ስንናገር በኋላ ላይ እንጸጸታለን። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል” ማለቱ ተገቢ ነው።—ምሳሌ 15:28

ይሁን እንጂ በተለይ ተበሳጭተንና ፈርተን ወይም ስሜታችን ተጎድቶ ከሆነ ከመናገራችን በፊት ቆም ብለን በትክክል ማሰብ አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። በተለይም ለቅርብ የቤተሰባችን አባላት ስሜታችንን ለመግለጽ ስንሞክር ሌላውን ወገን መውቀስ ወይም መተቸት ይቀናን ይሆናል። ይህ ደግሞ የሌላውን ሰው ስሜት ሊጎዳ ወይም ጭቅጭቅ ሊፈጥር ይችላል።

ታዲያ የተሻለ ውጤት ለማግኘት ምን ልናደርግ እንችላለን? በስሜት ገንፍለን፣ መናገር የሌለብንን እንዳንናገር ምን ሊረዳን ይችላል? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ከሆነው ከሰሎሞን ጠቃሚ የሆኑ ምክሮችን ማግኘት እንችላለን።

ምን እንደምትናገርና እንዴት እንደምትናገር አስብ

የመክብብ መጽሐፍ ጸሐፊ የሆነው ሰሎሞን፣ ሕይወት ከንቱ መሆኑን ሲናገር ስለ ጉዳዩ ጠንከር ያለ ስሜት እንደነበረው ግልጽ ነው። ሰሎሞን “ሕይወትን ጠላሁ” በማለት የተናገረ ሲሆን እንዲያውም በአንድ ወቅት ሕይወትን በተመለከተ “ከንቱ! ከንቱ! . . . ነው” ብሏል። (መክብብ 2:17፤ 12:8) ያም ሆኖ የመክብብ መጽሐፍ፣ በሰሎሞን ምሬት የተሞላ አይደለም። ሰሎሞን የሕይወትን መጥፎ ገጽታዎች ብቻ ማውሳት ተገቢ እንደሆነ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፉ መደምደሚያ ላይ እንደተገለጸው ሰሎሞን “ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት [ፈልጓል]።” (መክብብ 12:10 የ1954 ትርጉም) ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:- “ተስማሚ የሆኑ ቃላትንም መረመረ፤ ስለዚህ እርሱ የጻፈው ሁሉ እውነትና ትክክል ነው።”—የ1980 ትርጉም

በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ሰሎሞን ስሜቱን መቆጣጠር እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። በሌላ አባባል ራሱን እንዲህ እያለ ይጠይቅ ነበር:- ‘ልናገር ያሰብኩት ነገር በእርግጥ እውነት ወይም ትክክል ነው? በእነዚህ ቃላት ብጠቀም ንግግሬ ተቀባይነት ያለውና ያማረ ይሆናል?’ ሰሎሞን “ያማረውን” እውነተኛ ቃል ፈልጓል፤ ይህም ስሜቱ አስተሳሰቡን እንዳያዛባበት ረድቶታል።

እንዲህ በማድረጉም ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ብቻ ሳይሆን የሕይወትን ትርጉም በተመለከተ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ጥበብ ያዘለ መጽሐፍ ሊያዘጋጅ ችሏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ሰሎሞን ስሜቱን የገለጸበት መንገድ ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር በተሻለ ሁኔታ ለመነጋገር ይረዳን ይሆን? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

ስሜትህን መቆጣጠር ተማር

የትምህርት ቤት ውጤቱን ተቀብሎ ወደ ቤቱ የሚመጣን አንድ ልጅ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ልጁ ፊቱ ላይ ሐዘን ይነበባል፤ አባቱ ውጤቱን ሲመለከት ልጁ በአንድ የትምህርት ዓይነት እንደወደቀ አስተዋለ። በዚህ ጊዜ አባትየው፣ ልጁ የቤት ሥራውን ለሌላ ጊዜ እያስተላለፈ ሳይሠራ የቀረባቸውን በርካታ ጊዜያት በማስታወስ በጣም ተበሳጭቶ “ሰነፍ ነህ! በዚሁ ከቀጠልክ ዋጋ የለህም!” ብሎ ሊቆጣው ይፈልግ ይሆናል።

ሆኖም አባትየው በቁጣ ከመናገሩ በፊት ‘ያሰብኩት ነገር በእርግጥ እውነት ወይም ትክክል ነው?’ ብሎ ራሱን መጠየቁ ተገቢ ነው። ይህም ስሜቱ፣ እውነታውን ከመመልከት እንዳያግደው ይረዳዋል። (ምሳሌ 17:27) ልጁ በአንድ የትምህርት ዓይነት ስለወደቀ ብቻ በቀሪው ሕይወቱም ስኬታማ አይሆንም ማለት ነው? ልጁ በሁሉም የሕይወቱ ዘርፎች ሰነፍ ነው ወይስ የቤት ሥራውን የማይሠራው ይህ ትምህርት ስለከበደው ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ነገሮችን በምክንያታዊነት መመልከት አስፈላጊ መሆኑን በተደጋጋሚ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ቲቶ 3:2 NW፤ ያዕቆብ 3:17 NW) አንድ ወላጅ ልጁን ለማበረታታት “እውነትና ትክክል” የሆነውን ነገር መናገር አለበት።

ትክክለኛ ቃላትን ምረጥ

አባትየው ምን ብሎ እንደሚናገር ከወሰነ በኋላ ‘ልናገረው ያሰብኩትን ነገር ልጄ ሊቀበለው በሚችል መንገድ እንዲሁም ባማሩ ቃላት መግለጽ የምችለው እንዴት ነው?’ ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይችላል። ትክክለኛ ቃላትን መምረጥ ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች በሁሉም ነገር ትክክል ካልሆኑ ዋጋ እንደሌላቸው ሊሰማቸው እንደሚችል ወላጆች ማስታወስ ይኖርባቸዋል። በአንድ ወቅት የሠሩትን ስህተት ወይም ድክመታቸውን በማሰብ ያንን አጋንነው ይመለከቱት ይሆናል፤ ይህም ስለ ራሳቸው ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። አንድ ወላጅ ከመጠን በላይ የሚቆጣ ከሆነ ልጁ ስለ ራሱ ያለውን አሉታዊ አመለካከት ያባብሰዋል። ቈላስይስ 3:21 “ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው” ይላል።

“ሁልጊዜ” እንዲሁም “ፈጽሞ” እንደሚሉት ያሉ ቃላት ብዙውን ጊዜ እውነታውን ያዛባሉ ወይም ያጋንናሉ። አንድ ወላጅ “ፈጽሞ አትረባም” ብሎ ሲናገር ልጁ ለራሱ ያለውን ክብር እንዲያጣ ያደርገዋል። ልጁ የማይረባ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚነገረው ከሆነ በሕይወቱ ስኬታማ እንደማይሆን ማሰብ ሊጀምር ይችላል። ይህ ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጥ ብቻ ሳይሆን ከእውነታውም የራቀ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን የሁኔታውን መልካም ጎን ለመመልከት መጣሩ በጣም የተሻለ ነው። እዚህ ላይ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰው አባት ልጁን እንዲህ ሊለው ይችላል:- “ልጄ፣ በዚህ ትምህርት በመውደቅህ እንደተበሳጨህ ይገባኛል። አብዛኛውን ጊዜ የትምህርት ቤት ሥራህን ተግተህ እንደምትሠራ አውቃለሁ። እስቲ ስለወደቅህበት የትምህርት ዓይነትና አስቸጋሪ የሆኑብህን ነገሮች እንዴት መወጣት እንደምትችል እንነጋገር።” አባትየው ልጁን በምን መንገድ ቢረዳው የተሻለ እንደሆነ ለማወቅ አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠየቅ መሠረታዊ የሆነውን ችግር መረዳት ይችላል።

እንዲህ ባለ ደግነት የተሞላበትና በደንብ የታሰበበት መንገድ ሐሳብን መግለጽ በቁጣ ገንፍሎ ከመናገር ይልቅ ውጤታማ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ደስ የሚያሰኝ ቃል . . . ለነፍስ ጣፋጭ፣ ለዐጥንትም ፈውስ ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:24) ልጆችን ጨምሮ ሁሉም የቤተሰብ አባላት ቤታቸው ሰላም የሰፈነበትና ፍቅር የሚንጸባረቅበት ከሆነ ደስተኞች ይሆናሉ።

“በልብ ውስጥ የሞላው”

እስቲ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ዴቪድን መለስ ብለን እንመልከት። ይህ ሰው በቁጣ ገንፍሎ ባለቤቱ ላይ ከመጮህ ይልቅ ጊዜ ወስዶ “ያማረውን” እውነተኛ ቃል ቢፈልግ የተሻለ አይሆንም ነበር? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠመው አንድ ባል እንደሚከተለው እያለ ራሱን መጠየቁ ተገቢ ነው:- ‘ባለቤቴ ሰዓት አክባሪ በመሆን ረገድ ማሻሻል ቢያስፈልጋትም ሁልጊዜ እንደምትዘገይ መናገሬ እውነት ነው? ይህን ድክመቷን በዚህ ወቅት ማንሳቱ ተገቢ ነው? በንዴት የሚሰነዘር ትችት ማሻሻያ እንድታደርግ ያነሳሳታል?’ ቆም ብለን እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን መጠየቃችን የምንወዳቸውን ሰዎች ሳናስበው ከመጉዳት እንድንቆጠብ ይረዳናል።—ምሳሌ 29:11

ይሁን እንጂ ከቤተሰባችን አባላት ጋር የምናደርገው ውይይት ብዙውን ጊዜ ወደ ጭቅጭቅ የሚያመራ ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን? በውስጣችን ስለ ቤተሰባችን አባላት ያለንን ስሜት መመርመር ያስፈልገን ይሆናል። በተለይ ስንጨነቅ ወይም ውጥረት ሲያጋጥመን የምንናገረው ነገር ውስጣዊ ማንነታችንን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ “በልብ ውስጥ የሞላውን አንደበት ይናገረዋል” ብሏል። (ማቴዎስ 12:34) በሌላ አባባል ብዙውን ጊዜ የምንናገረው ነገር ውስጣዊ ሐሳባችንን፣ ፍላጎታችንንና አመለካከታችንን ያንጸባርቃል።

ስለ ሕይወት ሚዛናዊና አዎንታዊ ብሎም ብሩሕ አመለካከት አለን? ከሆነ የድምፃችን ቃና እንዲሁም የንግግራችን ይዘት ይህን ያንጸባርቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ግትሮችና ነቃፊዎች ወይም አሉታዊ አመለካከት ያለን ነን? ይህ ከሆነ በምንናገረው ነገር ወይም በምንናገርበት መንገድ ሌሎችን ተስፋ ልናስቆርጥ እንችላለን። አስተሳሰባችን ወይም የምንናገረው ነገር ሌሎችን ምን ያህል ተስፋ እንደሚያስቆርጥ አንገነዘብ ይሆናል። እንዲያውም ነገሮችን በትክክለኛው መንገድ እንደምንመለከት ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ራሳችንን እንዳናታልል መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ምሳሌ 14:12

በዚህ ረገድ የአምላክ ቃል በጣም ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አስተሳሰባችንን እንድንመረምርና በአመለካከታችን ረገድ ትክክል የሆነውን እንዲሁም መስተካከል የሚያስፈልገውን እንድንገመግም ይረዳናል። (ዕብራውያን 4:12፤ ያዕቆብ 1:25) በተፈጥሯችን ምንም ዓይነት ሰዎች እንሁን ወይም ደግሞ አስተዳደጋችን ምንም ዓይነት ይሁን ለመለወጥ ከፈለግን በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንችላለን።—ኤፌሶን 4:23, 24

ከሌሎች ጋር የምንነጋገርበትን መንገድ ለመገምገም ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ ሊረዳን የሚችል ሌላም ነገር አለ። ሌሎች ምን እንደሚሰማቸው ጠይቅ። ለምሳሌ፣ የትዳር ጓደኛህ ወይም ልጅህ በዚህ ረገድ ስለ አንተ ምን እንደሚሰማቸው በግልጽ እንዲነግሩህ ጠይቃቸው። በደንብ የሚያውቅህን የጎለመሰ ጓደኛህንም አነጋግር። የሚሰጡህን ሐሳብ መቀበልና አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ትሕትና ይጠይቃል።

ከመናገርህ በፊት አስብ!

ለማጠቃለል ያህል፣ በንግግራችን ሌሎችን ላለመጉዳት የምንፈልግ ከሆነ በምሳሌ 16:23 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል:- “አስተዋይ ሰዎች ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ፤ ስለዚህ የሚናገሩት ሁሉ ተደማጭነት አለው።” (የ1980 ትርጉም) እርግጥ ነው፣ ስሜታችንን መቆጣጠር ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም ሌሎችን ከመውቀስ ወይም ከመንቀፍ ይልቅ ሁኔታቸውን ለመረዳት ከሞከርን ሐሳባችንን ለመግለጽ የሚያስችሉ ትክክለኛ ቃላትን መምረጥ ቀላል ይሆንልናል።

እርግጥ ነው፣ ማናችንም ብንሆን ፍጹማን አይደለንም። (ያዕቆብ 3:2) አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም ግድ የለሽ ቃል እንናገራለን። (ምሳሌ 12:18) ሆኖም የአምላክ ቃል፣ ከመናገራችን በፊት ማሰብን እንዲሁም የሌሎችን ስሜትና ፍላጎት ከራሳችን ማስቀደምን እንድንማር ይረዳናል። (ፊልጵስዩስ 2:4) እንግዲያው፣ በተለይ ከቤተሰባችን አባላት ጋር ስንነጋገር “ያማረውን” እውነተኛ ቃል ለመፈለግ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ካደረግን ንግግራችን የምንወዳቸውን ሰዎች የሚጎዳና ልብ የሚሰብር ሳይሆን የሚፈውስና የሚያንጽ ይሆናል።—ሮሜ 14:19

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምትጸጸትበትን ነገር ላለመናገር ምን ሊረዳህ ይችላል?